>
5:13 pm - Wednesday April 20, 1870

ምርጫ ብሄር፣ ዜግነትና ግብር - ንቁና ምክንያታዊ ዜጎች እንፍጠር.. !!! (አካለወልድ አንዳርጌ)

ምርጫ ብሄር፣ ዜግነትና ግብር – ንቁና ምክንያታዊ ዜጎች እንፍጠር.. !!!

አካለወልድ አንዳርጌ

 

1. ምርጫ
ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት የሚያስችል አንዱና ዋነኛ መሳሪያ ነው። በዴሞክራሲ ስርዓት የስልጣን ምንጭ የዜጎች ፍቃድና ፍላጎት ነው። ዜጎች የፈለጉትን ይበጁኛል የሚሉትን ይመርጣሉ ፣ የማይበጀውንና ጥፋተኛ የሆነውን ደግሞ የስልጣን ዘመኑን ሳይጨርስ የሚያወርዱበት ሁኔታ  የሚፈጥሩበት ስርዓት ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ የሚሳተፋት ዜጎች በከፍተኛ የንቃተ ሂሊና ደረጃ ላይ መገኘት ይጠበቅባቸዋል። አመዛዘኝና ምክንያታዊ ዜጎች መሆን ይጠበቅባቸዋል።
የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዋና ዋና  ባህሪያት ዜጎች በዴሞክራሲያዊ ስርዓት አልፋና ኦሜጋ መሆናቸው ፣ ዜጎች መራጭም ተመራጭም መሆናቸው፣ ግልፀኝነት የዴሞክራሲ ስርዓት ዋነኛ መገለጫ ሲሆን ዜጎች መንግስት የሚሠራውን የሚያደርገውን ስለሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ የማወቅ መብት ያላቸው መሆኑ፣ የመደራጀት፣ የመሰበሰብ፣ ሃሳብን በነፃነት የማንሸራሸር መብት እና ከሁሉ በላይ እምነት፣ ሂሊናና ነፃነት የዴሞክራሲ ዋና መሠረት ነው።
2. ብሔር
ብሔር የአንድ የጋራ ባህል ወይም ቋንቋ ያላቸው ማህበረሰብ ስብስብ ነው። ብሔር ሕጋዊ ሰውነት(legal personality) የለውም። አይከስም አይከሰስም። ግብር አይሠበስብም ግብር አይከፍልም። በሌላ አገላለፅ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው በብሄር ስም የተደረጁ ፓርቲዎች ወይም ድርጅቶች እንጂ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ብሕሮች የሉም።  ኦሮሚያ ክልል እንጂ ኦሮሞ ብሔር አይከሰስም፣ አብን እንጂ የአማራ ብሔር አይከስም፣ ህወሃት እንጂ የትግራይ ብሄር አይከስም አይከሰስም። ምክንያቱም ብሔር የተበለው ጉዳይ ሕጋዊ ሠውነት የለውም። በመሆኑም ብሔር አይመርጥም አይመረጥ ማለት ነው።
3. ዜግነት
አንድን ሀገር ሀገር ከሚያስብሉት ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች(መንግስት፣ ሉዓላዊ ድንበርና ዜጎች)  ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚወስዱት ዜጎች ናቸው። ምክንያቱም የሀገሩን መንግስት የሚፈጥሩትም ሆነ ሉዓላዊ ድንበር የሚወስኑት ዜጎች ናቸው። ዜጎች ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ በመሠረቱት መንግስት ይተዳደራሉ፣ ስያሰኛቸውም ያወርዳሉ። ዜጎች ሕጋዊ ሰውነት አለቸው። ይከሳሉ ይከሠሳሉ። ዜጎች ይመርጣሉ ይመረጣሉ። ዋነኛ የመንግስት የገቢ ምንጭ ዜጎች ናቸው። መንግስት ግብር የሚያስከፍለው ዜጎችን እንጂ ብሔርን አይደለም። በመሆኑም በዚህ አረዳድ የዜጎች መንግስት እንጂ የብሔር መንግስት የለም።
3. ግብር
መንግስት እንደ ማንኛውም ተቋም ህጋዊ ሰውነት አለው። የመንግስት ሕጋዊ ሰውነት የሚረጋገጠው በሕገ መንግስት ነው። መንግስት ይከሳል ይከሰሳል። መንግስት ተቋም ነው ገቢና ወጭ አለው። ገቢውን በአብዛኛው ከዜጎች በግብር መልክ ይሰበስባል። ዜጎች ግብር የመክፈል ግዴታ አለባቸው። መንግስትም በሠበሰበው ግብር ፍትሃዊ  እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አገልግሎቶች የማቅረብ ግዴታ አለበት። ይህንን ማድረግ ያልቻለ መንግስት በዜጎች ይሁንታ ስልጣን ላይ እንደ ወጣ ሁሉ በዜጎች ይሁንታ እንዲወርድ ይደረጋል።
4. ማጠቃለያ
በሀገራችን እስከ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በዜጎች ይሁንታ እና  በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን የያዘ ዴሞክራሲያዊ መንግስት መፍጠር አልቻልንም። ከዜጎች በሚሰበስበው ግብር መንፈስ የሆነውን ብሔርን ወይም ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውን ብሔሮች ላይ ተጣብቀው የዜጎችን ሃብት በብሔር ስም የሚያባክኑ መንግስታት የተፈጠረበት ዘመን ማብቃት አለበት። ይህንን ችግር  ለመቀየር ዜጎች በንቃታ ሂሊና መጎልበት እና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመፍጠር ግዴታቸውን መወጣትና መብታቸውን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።
Filed in: Amharic