>

ኢትዮጵያ እና ምርጫ! ክፍል - ፪ (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

ኢትዮጵያ እና ምርጫ!

ክፍል -፪

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


 

 • እንደ መንደርደሪያ

 

በማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የሕዝብ አስተዳዳር መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ሳባቲ ማካራ (ዶ/ር.)፤ The Relationship between the Election and the Democracy በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው፤ ‘‘በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ዜጎች የወሳኝነት ሚና እንዳላቸውና ባለቤት መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት አንዱ መንገድ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲሳተፉ ነው፤ እናም ዴሞክራሲ ያለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውን ሊሆን አይችልም፡፡’’ ይላሉ፡፡ 

በርግጥም በአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለ ማለት ከሚያስችሉት አንዱ ወቅቱን የጠበቀ ነፃ ምርጫ ሲካሄድ ነው፡፡ ምርጫ የመንግሥት፣ የሕዝብ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልግ ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ምርጫ ማካሄድ ብቻውን ዴሞክራሲያዊ ህልውናን የሚወስን አይደለም፡፡ ይልቅ ምርጫ ለዴሞክራሲ ዕድገት አስተዋፅኦ የሚኖረው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ያለምንም ወገን ተፅዕኖ የተካሄደ እንደሆነ ነው፡፡

በተለይ ዜጎች ለምርጫ የሚቀርቡ አማራጭ አስተሳሰቦችን በሰከነ መንፈስ አውጥተውና አውርደው በተነጻጻሪ የተሻለ ነው የሚሉትን ለመምረጥ የሚያስችላቸው ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ ሐሳባቸውን ለውድድር የሚያቀርቡ የፖለቲካ ኃይሎችም እንዲሁ አለን የሚሉትን አማራጭ ሐሳብ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ማቅረብና ሕዝቡ የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ውሳኔ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡

ምርጫውን የሚያስፈጽሙ ተቋማት እንዲሁ ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው ማስፈጸም የሚችል አቅም መፍጠር ይገባቸዋል፡፡ ምርጫውን ለመታዘብ የሚንቀሳቀሱ አካላት ደግሞ ከየትኛውም አድሎአዊ አሠራር ነጻ ሆነው ለመታዘብ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ መንግሥት በበኩሉ እነዚህን ቅድመ-ሁኔታዎች ለማሟላት የሚያስችለው አቅም ላይ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ሰላም እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ የሚኖረው ውጤት የተዛባና ተዓማኒነት ያጣ ሊያደርገው ይችላል፡፡

 

 

 • የምርጫ ትርጉም 

 

ምርጫ ሰዎች አንድን ግለሰብ ወይም የሰዎች ቡድን በይፋ ለአስተዳዳራዊ ኃላፊነት የሚመርጡበት ሂደት ነው፡፡ በርናን ሎውስኪይ፤ Democracy and Decision: the Pure Theory of Electoral Preference በተባለው መጽሐፋቸው፤ ‘‘ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሁ ለይስሙላ የሚደረግ ሳይሆን ተወዳዳሪነት፣ ወቅታዊነትና አካታችነት ባለው መልኩ በሕዝብ ድምፅ መንግሥት መመስረቻ እንደሆነና፤ ዜጎች የመረጡትን አካል በነፃነት የሚተቹበት፤ ብሎም አማራጭ ሐሳብ የሚያቀርቡበት እንደሆነ፡፡’’ ይገልፃሉ፡፡ 

ተወዳዳሪነት፡- ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ዕጩዎች በነፃነት የመናገር፣ የመደራጀትና የመንቀሳቀስ መብት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህም አልፎ በመንግሥት ላይ ያላቸውን ትችት በነፃነት በማቅረብና አማራጭ ሐሳባቸውን ማቅረብ የሚያስችል መሆን አለበት፤

ወቅታዊነት፡- ዲሞክራሲ አንድን መሪ ለዘላለም መምረጫ አይደለም፡፡ ይልቅ በየተወሰነ ጊዜ ተመራጩ መልሶ የመራጩን ሕዝብ ፈቃድ የሚጠይቅበት ነው፡፡ በዚህ ሂደት መራጩ ሕዝብ ተመራጩን ከሥልጣን የማውረድና በሌላ ተፎካካሪ መቀየር የሚችልበት ነው፡፡

አካታችነት፡- በሀገሪቷ ለመራጭነት ዕድሜያቸው የደረሱ ዜጎች በስፋት ሊሳተፉበት ይገባል፡፡ በዓለማችን በምርጫ ተሳትፎ ላይ መገለል በብሄር፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በፆታና በመሳሰሉት ታይቷል፡፡ የተወሰኑ አካላትን የሚያገል፤ አጠቃላይ ሂደቱ የተዋጣለት እንኳን ቢሆን ዲሞክራሲያዊ አይባልም፡፡ 

በሀገራችን ምርጫ በፌደራልና በክልል ሕገ-መንግሥት እንዲሁም በሌሎች አግባብ ባላቸው ሕጎች መሠረት የሚካሄድ የጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የማሟያ ወይም የድጋሜ ምርጫ ነው፡፡ ምርጫ የአንድ ሀገር ሕዝብ የሉዓላዊነት መገለጫም ነው፡፡ ሕዝቦች በነፃነትና በቀጥታ በመሳተፍ ያስተዳድሩኛል የሚሉትን ወኪል በፈቃዳቸው የሚመርጡት በምርጫ ነው፡፡ በሀገራችን ምርጫን የማስፈፀም ሥልጣንና ኃላፊነት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰጥቷል፡፡ 

ምርጫ ማለት በየጊዜው ወቅቱን ጠብቆ እንደየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች የሚመረጡበት፣ በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት፣ የሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ መብት ማለትም የመምረጥ እና የመመረጥ መብት የሚተገበርበት ሂደት ነው፤በኢትዮጵያ ምርጫ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንኛዉም መልኩ ልዩነት ሳይደረግባቸዉ በቀጥታ፣ በነጻነትና በሚስጥር በመረጡዋቸዉ ተወካዮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ዕድል የሚያገኙበት ነዉ፡፡

 

 • የምርጫ ዓይነቶች በኢትዮጵያ

 

በተሻሻለው የምርጫ ሕግ 532/1999 ዓ.ም መሠረት አምስት የምርጫ ዓይነቶች መኖራቸው ይገልፃል፡፡ እነርሱም፡- የጠቅላላ ምርጫ፣ የአካባቢ ምርጫ፣ የማሟያ ምርጫ፣ የድጋሚ ምርጫና የሕዝብ ውሳኔ ምርጫዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ምን ማለት እንደሆኑ ቀጥሎ በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ 

 1. ጠቅላላ ምርጫ( General Elections) ማለት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡ 
 2. የአካባቢ ምርጫ (Local Elections) ማለት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የሚካሄድ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡
 3. የማሟያ ምርጫ (By-Elections) ማለት በይውረድልን ወይም በማንኛውም ምክንያት በየደረጃው የሚገኙ የተጓደሉ የምክር ቤት አባላት መቀመጫዎችን ለማሟላት የሚካሄድ ምርጫ ነው፡፡ 
 4. የድጋሚ ምርጫ (Re-election) ማለት ቦርዱ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ሲወስን ወይም ዕጩ ተወዳዳሪዎች እኩል ድምፅ በማግኘታቸው ምክንያት አሸናፊውን መለየት በማይቻልበት ጊዜ የሚካሄድ ምርጫ ነው፡፡ 
 5. የሕዝበ-ውሳኔ ምርጫ (Referendum) ማለት በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት መሰረት ሲፈቀድ፤ የሕዝብ ፍላጎትን ለመለካት እና የሕዝብን ውሳኔ ለማወቅ ድምፅ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው፡፡
 6. የዴሞክራሲያዊ ምርጫ መርሆዎች

የምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥ የዘርፉ ምሁራን የሚስማሙባቸው አምስት መርሆዎች አሉ፡፡ የAfrican Union Declaration on the Principles Governing Democratic Elections in Africa, AHG/Decl. 1 (XXXVIII) እና Article 21 of the Universal Declaration of Human Rights ሰነዶች የምርጫ ዴሞክራሲያዊነት ለማረጋገጥ የሚስማሙባቸውን አምስት መርሆዎች እንደሚከተሉት ይዘረዝሯቸዋል፡፡ እነርሱም፡-

 

ፍትሐዊነት፣ ነጻነት፣ አሳታፊነት፣ ወቅታዊነትና በሚስጥር የሚካሄድ የሚሉት ናቸው፡፡ መርሆዎቹ እስከ ስምንት ይደርሳሉ ብለው የሚከራከሩ ልሂቃንም አሉ፡፡ የመንግሥት ሚዲያን በፍትሐዊነት መጠቀም፣ የመቻቻል ፖለቲካ መኖርና የምርጫውን ውጤት አክብሮ መቀበል የሚሉትን በማከልም ይገልፃሉ፡፡ 

 1. ነጻነት፡- ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመደራጀት ጀምሮ የመሰብሰብ፣ የመንቀሳቀስ፣ የመናገርና በምርጫው የሚሳተፉበት ነጻነት መስጠት፤ 
 2. ፍትሐዊነት፡-  አገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ለምርጫ ቅስቀሳ የሚያስፈልገውን በጀት፣ የአየር ሰዓትና ሌሎች በፍትሃዊነት ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከፋፈልበት ነው፤
 3. አሳታፊነት፡- ሁሉም እድሜው ለመምረጥና ለመመረጥ የደረሰ ማኅበረሰብ/በሕግ ያልተገደበ ካልሆነ በስተቀር የሚሳተፍበት ሲሆን በዚህም ዜጎች በመምረጥ፣ በመመረጥ፣ በታዛቢነት፣ በአስመራጭነት እኩል ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፤ 
 4. በሚስጥር የሚካሄድ መሆኑ፡- ማንኛውም ካርድ የወሰደ ዜጋ ሁሉ ድምጹን በሚሰጥበት ወቅት ከራሱ ውጭ ማንም በማያውቀው መልኩ የሚፈልገው ላይ ምልክት አድርጎ የምርጫ ሳጥን ውስጥ የሚከትበት ነው፤ 
 5. ጊዜውን የጠበቀ ምርጫ ማካሄድ፡- አገራት በሚያወጡት ሕግ መሰረት በአምስት፣ በአራት ዓመት ተብሎ በመደንገግና ወቅቱን ጠብቆ የሚካሄድ መሆኑን ማረጋገጥ የሚሉት ናቸው፡፡ 

የእነዚህ መርሆዎች መነሻ በአንድ አገር የሚካሄድ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ መሆናቸው ነው፡፡

ዋቢ መጻሕፍትና ሰነዶች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (2003) የመራጮችና የሥነ-ዜጋ ትምህርት ማሰልጠኛ ማኑዋል፣ አዲስ አበባ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (2006) የመራጮችና የሥነ-ዜጋ ትምህርት አሰጣጥን በሚመለከት የትምህርቱ ተደራሽነትና ውጤታማነት ግምገማ፣ የሕዝብ አስተያየት ጥናት፣ ሰኔ 2006፡፡

የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/199 ዓ.ም. የተሻሻለው፣ ሐምሌ 1999፣ አዲስ አበባ፡፡

African Union Declaration on the Principles Governing Democratic Elections in Africa, AHG/Decl. 1 (XXXVIII), 2002.

Brennan, Geoffrey and Loren Lowasky. Democracy and Decision: the Pure Theory of Electoral Preference, New York: Cambridge University press, 1993.

National Electoral Board, Election Officers Manual, Addis Ababa, 2000.

Pastor, Robert A. (1999) ‘the Role of Electoral Administration in Democratic Transitions: Implications for Policy and Research’, Democratization, 6: 4, 1—27.

Filed in: Amharic