>
5:29 pm - Wednesday October 10, 2136

የምርጫ ክርክሮች ለቀጣይ ምን ያመላክቱናል.. ??? (ጌታቸው ሽፈራው)

ምርጫ ክርክሮች ለቀጣይ ምን ያመላክቱናል.. ???

ጌታቸው ሽፈራው

 

1)  ተከራካሪዎቹን ያስማማው ጉዳይ ክልሎች ልዩ ኃይል አያስፈልጋቸውም የሚል ነው። አብዛኛዎቹ እንደ መጀመርያ በጥቅሉ ልዩ ኃይል ወደ ፌደራል ፀጥታ ኃይል ይካተት ብለዋል። በቀጣይ ክርክሮች አሁን በቁንፅል ያለ በቂ እውቀትም መረጃም ያቀረቡት ጭምር  ዝርዝር ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል። ይህ ተቃዋሚዎችም ከብልፅግና ጋር የተስማሙበት የልዩ ኃይል ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ በገደምዳሜው ከነገሩን፣ የፓርላማ አባላትም ሆን ተብሎ አጀንዳ አድርገው እንዲናገሩት ከተደረገው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው። በቀጣይ ፓርቲዎቹ በዚህ ጉዳይ የሚያደርጉት ክርክር ከምርጫ በኋላ ለሚደረገውም የፖሊሲ ለውጥ ግብአት ነው። ከምርጫው በኋላ ከሚታሰቡት አንደኛው ክልሎች ልዩ ኃይል ወደ ፌደራል ፀጥታ ኃይል ማጠቃለል ነው የሚሆነው። ክልሎች ልዩ ኃይል እንዳይኖራቸው መደረጉ ሳይሆን ወደ ፌደራል ፀጥታ ኃይሉ ሲጠቃለል በርካታ መዛነፎችን ያመጣል። አንዳንድ ክልሎች በርካታ ቁጥር ያለው ኃይል አሰልጥነው፣ ሌሎች በጫና እንዲሁም በራሳቸው ድክመት ወደኋላ ባሉበትና ማስተካከያ ሳይደረግ ወደ ፌደራል ፀጥታ ኃይል ማጠቃለሉ አጋጣሚን ተጠቅመው ብዙ ላደራጁ ክልሎች ሚዛን የሚደፋ፣ ሌላውን የሚጎዳ ይሆናል። የልዩ ኃይሉ ሁኔታ እስኪወሰን ድረስ ይሄ መስተካከል ካልቻለ ለቀጣይ ዘመናት ሌላ የፖለቲካ ችግር ሆኖ ይቀጥላል።
 
2) ክርክሮቹ ከፖሊሲ ይልቅ መፈራረጅና እውቅና ለማግኘት ጥረት የተደረገባቸው ናቸው። ብልፅግና “ከኢህአዴግ ጋር ለውጥ የለውም” ተብሎ በተቃዋሚዎቹ ሲፈረጅ፣ ይህን ለማስተባበል ሲጥር ታይቷል። ተቃዋሚዎችም ሆነ ብልፅግና “ነፃ አውጭነት”ን ለየራሳቸው ወስደዋል።  ተቃዋሚዎቹ “የለውጡ ባለቤት እኛ እንጅ ብልፅግና አይደለም” ብለው እውቅና ለመውሰድ ሲከራከሩ፣ ብልፅግና ደግሞ ከ”ለውጡ” በተጨማሪ ትህነግን በመታገል ግንባር ቀደሙ እኔ ነኝ ብሎ እውቅና ስጡኝ ብሏል። በተቃራኒው ተቃዋሚዎቹ “ስንታገል የኖርነው እኛ ነን። እናንተ ከቀደሙት አትለዩም” ብለው እውቅና አይገባችሁም ብለዋል። ይህ ክርክር እስከምርጫው ድረስ የፌስቡክ አሉባልታና ዘመቻ ተጨምሮበት ሊቀጥል እንደሚችል የማታው ጠንከር ያለ መፈራረጅ፣ የድል ባለቤትነትና እውቅና ለማግኘት የተደረገው ጥረት አመላካች ነው።
 
3) በዚህ ወቅት በንፁሃን ላይ የሚፈፀሙት ጭፍጨፋዎች በትንሹም ቢሆን መከራከሪያዎች ሆነዋል። ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች ብልፅግና ከኢህአዴግ በተረከበው ፌደራሊዝም የመጣ ነው ብለው ወቅሰውታል። አብንና መኢአድ ጭፍጨፋዎቹ በብልፅግና  እንዝላልነት ብሎም የአሰራር ችግር የሚፈፀም ነው ብለዋል። የኢዜማው አንዱዓለም በየቀኑ ለሚገደሉት ንፁሃን እውቅና የማይሰጥ፣  ዜጎችን ይወክላል የሚባለውን ሰንደቅ አላማ እንኳን ዝቅ ለማድረግ ያልሞከረ ለንፁሃን መገደል ደንታ ቢስ ነው ብሎታል። ብልፅግና በአንፃሩ የንፁሃንን መገደል ተቃዋሚዎች ከሚሰሩት አሉታዊ ፖለቲካ የመጣ ነው ብሏል። በንፁሃን ጭፍጨፋ ላይ ብልፅግናን ጠበቅ አድርጎ ለኮነነው አብን እናንተ በምትሰሩት የብሔር ፖለቲካ ሰበብ የመጣ ነው በማለት የተወረውበትን አጀንዳ ወደ አብን ለመመለስ ተከራክሯል። ይህ እስከምርጫው ድረስ በስፋት የሚቀጥል ክርክር መሆኑ አይቀርም። ብልፅግና በንፁሃን ጭፍጨፋ ሲወቀስ ይቀጥላል። በተቃራኒው ብልፅግና አብንን ጨምሮ ለንፁሃን ጭፍጨፋ የእናንተ ፖለቲካ አስተዋፅኦ አለው እያለ ተቃዋሚዎችን ይወነጅላል። በሚቀጥሉት ክርክሮች እነዚህን አቋሞች ለማስረዳት በየፊናቸው ዝርዝር መረጃ ብለው ያመጣሉ። በማህበራዊ ሚዲያ በየፊናቸው ዘመቻና ቅስቀሳ ይጨምሩበታል።  እስከምርጫውም ሆነ ከምርጫው በኋላ ለፖለቲካው አሉታዊ ጎን የሚኖረው  ከዚህ ክርክር ጀርባ የተያዙ የተራራቁ አቋሞችና ይህ የሚያመጣው መካረር ይሆናል።
 
4) ከትናንትናው ክርክር ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ነፃነትና እኩልነት ይዞት የመጣው አቋም ነው። በብልፅግ፣ አብን፣ ኢዜማ እንዲሁም ኢሕአፓ ተከራካሪ መጉላትና  ግብረመልሶች ምክንያት ትኩረት ያልተሰጠው የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ኢህአዴግ ድሮ ሲከራከርበት የኖረውን “የድሮ ስሮ ስርዓት ናፋቂነት፣ አግላይነት፣……” ፖለቲካ አሽቶ፣ ትንሽ አለዝቦ ይዞ ቀርቧል። ፓርቲው “ከ30 አመት በፊት የነበረውን ስርዓት ለመመለስ የሚጥሩ፣  ሀገረ መንግስቱ አግላይ ነበር” እያለ የኢህአዴግን እንዲሁም የኦሮሞ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎችን አቋም አዋህዶ እጅግ ስልታዊ በሆነ መንገድ የመጣ መሆኑን አሳይቷል። አብዛኛዎቹ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምሳሌዎቹም ኦሮሚያ ክልል ላይ ሲሆን ንፁሃን ላይ ከተፈፀሙት ይልቅ ድርጅታዊ አፈናን የተመለከተ ነው። ይህ ክርክር ኦነግ ወይ ኦፌኮ ቢከራከሩ ከሚያቀርቡት በትንሹ ቀንጨብ ተደርጎ የቀረበ አይነት ነው። ተቃዋሚዎቹ በአንድ ሆነው ብልፅግናን ሲከራከሩ፣ ይህ ድርጅት ተቃዋሚዎችን “በድሮ ስርዓት ናፋቂነት”/ቃል በቃል አይደለም/ እንደሚቃወማቸው ፍንጭ ሰጥቷል። የብልፅግናው ተወካይም አድናቆት ሰጥቶት ያለፈው ይህን ድርጅት ሲሆን አንድም የቆየውን ስርዓት የሚመልሱ ከሚለው፣ ቀጥሎም እንደ ሌሎች ተቃዋሚዎች ብልፅግና ላይ ስላልተረባረበ ነው። ይህ ድርጅት የተቃዋሚ ድምፅ ለሳሳበት የኦሮሞ ብሔርተኛ ቀዳሚ ድምፅ ሊሆን እንደሚችል የታዩ ምልክቶች አሉ። በቀጣይ በሚቀርቡ ተከራካሪዎችም “የድሮ ስርዓት ናፋቂነት፣ አግላይነት፣ ጨቋኝ ተጨቋኝነትን” በዋነኛነት ይዞ የሚቀጥለው ይህ ድርጅት እንደሚሆን ፍንጭ ሰጥቶናል። የሀገረ መንግስቱን ስሪት በይፋ በመቃወም፣ አማራጭ ፖሊሲም ይዧለሁ ብሎ የመጣ ድርጅት ነው።
 
5) ክርክሮቹ ከአሁኑ አጀንዳ የሚያስይዙ ሆነዋል። ፌደራሊዝሙ ወደ ክፍለ ሀገር መቀየር አለበት እና የቋንቋ  ጉዳይ በኦሮሞ ብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር ረዘም ያለ መልስ ተፅፎበታል። መኢአድና ሕብር ያነሱትን አጀንዳ የኦሮሚያ ብልፅግና አመራሮችና የኦነግ ብሔርተኞች ተችተውታል። ልክ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ በክርክሩ እንዳቀረበው፣ የክፍለ ሀገር ጉዳይ በኦሮሚያ ብልፅግና እና በኦነግ ብሔርተኞች ዘንድ “የድሮ ስርዓትን መናፈቅ ነው፣ ከ1983 ዓ/ም በፊት የነበረውን ስርዓት ለመመለስ ነው።” ተብሎ አጀንዳ ተይዞበታል። አቅም ይኑራቸውም አይኑራቸውም ተከራካሪዎች በቋንቋ፣ በፌደራሊዝም ጉዳይ የሚያነሱት መሰል አቋም የድሮ ስርዓትን መመለስ ተደርጎ ሕዝብን ማስፈራሪያ አጀንዳ ሆኖ እስከምርጫው ድረስ ይቀጥላል።
 
6) ምርጫው ከፓርቲዎችም በላይ ግለሰቦችን ሊያሳየን እንደሚችል ጠቋሚ ሆነዋል ክርክሮቹ። ከኢሕአፓ  በእድሜ ጠና ያሉ የቀድሞ ማርክሲስቶችን ስንጠብቅ ወጣት፣ ያውም መጋቢ ብሉይ ፖለቲከኛ ይዞ ብቅ ብሏል። ኢዜማ በአንዱዓለም አራጌ በኩል ለብልፅግና ይሉኝታ አልባ ሆኖ አምሽቷል። ከዚህ ግባ የሚባል አቅም የሌለው ሕብር በኢ/ር ይልቃል በኩል ስሙ ተዋውቋል። መኢአድና አብን እንደፓርቲ በሚታወቁበት ከረር ያለ አቋሙ መጥተዋል። /በስም የማላውቃቸው ሁለተኛው የአብን ተወካይ በክርክሩ ደካማውን አቋም ይዘው መቅረባቸው ሳይዘነጋ/ 
 
በሌላ በኩል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ኢዜማ እስካሁን ሲሄድበት ከቆየው ስልታዊና የጥንቃቄ መንገድ ሳይወጣ ክርክሩን አስኪደዋል። ኢዜማ በዚህ ክርክር እንደ አንዱዓለም ባሉ የግንባር ስጋዎች፣ እና እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከቆየው ስልታዊና ተጠግቶ የማለፍ ታክቲክ ያልወጡት በኩል ክርክር ሊያስኬድ የሚችል የተባደግ/ ከፍና ዝቅ/ አካሄድ እንዳለበት ጠቁሟል።
 
7/ የዘንድሮው ክርክር ብልፅግና ከኢህአዴግ ከወረሳቸው ፖሊሲዎች ይልቅ የኢህአዴግ ወራሽ የሚለው ቅድሚያ ተሰጥቶት ከተቃዋሚዎቹ በኩል የሚነሳ ሲሆን ብልፅግናም ለዚህ መልስ ሌሎቹን ፈርጆ ከሚደረጉ ክርክሮች ባሻገር የንፁሃን ጭፍጨፋ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ የሕግ የበላይነት፣  የኑሮ ውድነት፣ ሙስና፣ ተረኝነት፣ ፅንፈኝነትና ብሔርተኝነት……አጀንዳ ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተገማች ነው።
 
8/ ክርክሮቹ እስከምርጫው ያልተጠበቁና ብልፅግናን ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚከቱ አጀንዳዎችም ጭምር እንደሚነሱባቸውም የጠቆሙ ናቸው። በቀደመውም ሆነ በአሁኗ የአዲስ አበባ ከንቲባ ላይ የኢዜማው አንዱዓለም ያነሳቸው ከረር ያሉ ተቃውሞዎች ብልፅግና ከኢዜማ በዚህ መጠን ይመጡብኛል ብሎ የጠበቃቸው አይመስሉም። በቀጣይ ባልደራስ፣ አብን፣ መኢአድ፣ ሕብር፣ እንደ አንዱዓለም ያሉ የኢዜማ ተከራካሪዎች በአዲስ አበባ፣ በለውጥ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያመጧቸው መከራከሪያዎች ለብልፅግና ከፍተኛ ጫና የሚያመጡ ናቸው። በ1997 ዓ/ም ተቃዋሚዎች ፖሊሲ የላቸውም ብሎ ወደ ክርክር እንደገባው ኢህአዴግ፣ በፖሊሲ ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም ይዞ የመጣው ብልፅግና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከየአቅጣጫው ለሚነሱበት የምርጫ ክርክር አጀንዳዎች ግብረመልሱ ምን ይሆን የሚለውን ማጤን ጠቃሚ ነው።
Filed in: Amharic