>

ከጎሳ ፖለቲካ ለመገላገል ግዜው መቼ ይሆን ? ስንት አመት እንጠብቅ ? ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ከጎሳ ፖለቲካ ለመገላገል ግዜው መቼ ይሆን ? ስንት አመት እንጠብቅ ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


እንደ መንደርደሪያ

‹‹ ለወደፊቱ ወይም በመጪዎቹ አመታት የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሰማየ ሰማያት ላይ እውን መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ከአሁን በኋላ የጎሳ ፖለቲካ ሰማየ ሰማያት ላይ ለመቆየት ሞራል የለውም፡፡ ዛሬ ለደረስንበት ዘርፈ ብዙ ችግርና መከራ፣ ለተፈጸሙት አብዛኞቹ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ለተዘፈቅንበት የፖለቲካ ቅርቃር በአንዱም ሆነ በሌላ መልኩ ከጎሳ ፖለቲካ ችግር ጋር የተያያዘ ነው ብሎ መደምደሙ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የፋሺስት ጣሊያን የመንፈስ ልጅ የሆነው የወያኔ አገዛዝ አርሶ፣ዘርቶ፣አጭዶ፣ከምሮ፣ሰብስቦ፣አስፈጭቶ፣አቡክቶ ጋግሮ ያበሰለው የጎሳ ፖለቲካ ዛሬ ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከባድ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል ተብሎ ቢጻፍ ቡራከረዩ የሚል ይኖር ይሆን ካለም የጎሳ አምበሎችና ቃፊሮቻቸው ወይም ነገሩ ያልገባው የከንቱ ከንቱ ሰው ብቻ ይመስለኛል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያን እንደ ገና ዳቦ እያቃጠላት ወይም እያነደዳት ይገኛል፡፡ ይህ ያልገባው ካለ እና የሚኖር እሳት ብቻ ነው፡፡ ምክንቱም ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ብቻ ነው፡፡

“Ethnic politics has no moral to fly Ethiopians to the future. All the messes we are having today are in one way or the other associated to ethnic politics.”

የጎሳ/ ብሔር ብዝሃነት እና ፖለቲካ ምንና ምን

ብዝሃነት የተፈጥሮ ውበት ነው፡፡ ጎሳ ወይም ብሔርም የተፈጥሮ ውበት ነው፡፡ እኛ በብዙ አይነት መልኩ ከምነገነዘባቸው ቁም ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም በርካታ ጎሳዎች ወይም ብሔሮች በአንድ ሀገር መገኘታቸው ራሳችንን የምናይበት፣ የተፈጥሮ ውበት ናቸው፡፡ ስለሆነም የጎሳ ብዝሃነት እውቅና ሊቸረው ይገባል ተብሎ ሃሳብ ቢሰነዘር ጭቅጭቅ የሚፈጥር አይሆንም  ባይ ነኝ፡፡ከዚህ ባሻግር ጎሳን ወይም ብሔርን ከፖለቲካ ጋር ሳይቀላቅሉ ተቋማዊ ማድረጉ ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ የጎሳ ብዝሃነት ምንነት መሰረታዊ ምንጩ በህዝብ መሃከል ያለው የቋንቋና ባህል መመሳሰል እና መለያየት ነው፡፡ ስለ ጎሳ ወይም ብሔር በምናስብበት ግዜ በአይምሮአችን መጀመሪያ የሚመጣው ቋንቋና ባህል ነው፡፡ ይህ ችግር የለውም ፡፡ ችግር የሚሆነው ቋንቋና ባህልን ከፖለቲካ ጋር ስናያይዘው ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአንድ ሀገር የትምህርት ፖሊሲ በአንድ ገዢ ስርዓት ፖለቲከኞች ውሳኔ ብቻ የሚዘጋጅ ከሆነ የዛች ሀገር የትምህርት ጉዳይ አበቃለት ማለት ይቻላል፡፡ የወታደራዊው አገዛዝ የኢትዮጵያን የትምህርት ፖሊሲ ከሶሻሊስቱ አለም ብቻ በመቅዳት በማዘጋጀቱ፣ እንዲሁም የወያኔ አገዛዝ ደግሞ የትምህርት ፖሊሲውን ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በመቀላቀል በመቅረጹ ምክንያት ኢትዮጵያ አልተጠቀመችም፡፡ ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ ‹‹The crises of Ethiopian Education>> በተሰኘው ዝነኛ መጽሃፋቸው፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( አፈሩን ገለባ ያድርግላቸው)፣ በብዙ ጽሁፎቻቸው ሁለቱም ስርዓቶች የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት እንዴት እንዳበላሹት በደንብ አስረድተውናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አቶ ብርሃኑ ደቦጭ የተባሉ ሀገር ወዳድ ምሁር ‹‹ የድንቁርና ጌቶች ›› በተሰኘው ግሩም መጽሐፍ ላይ እንደጠቀሱት የትምህርት አምባዎች በፖለቲከኞች ሲጥለቀለቁ የአንድን ሀገር የትምህርት ደረጃ እንዴት አሽመድምደው እንደሚያስቀሩት በሰፊው ነግረውናል፡፡ ከታዋቂው የማካራሬ ዩንቨርስቲ ( በኡጋንዳ ካምፓላ ይገኛል) ጋር ይወዳደር የነበረውን የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አሁን ያለበትን ደረጃ ስናስብ ልባችን ይደማል፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ሙያን የሚጠይቁ የእውቀት ዘርፎች በፖለቲከኞች ሲዘወሩ ውድቀትን እንጂ እድገትን አይሰጡንም፡፡ በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያዩ ጎሳዎች ባህላቸውን፣ታሪካቸውን፣ቋንቋቸውን፣ ሙዚቃቸውን ወዘተ ወዘተ በባለሙያ በመታገዝ ቢያበለጽጉ፣ቢያሳድጉ ክፋት የለውም፡፡ ሆኖም ግን ችሎታን ሳይሆን ጎሳን መሰረት በማድረግ የስልጣን ማማ ላይ ቢንጠለጠሉ፣ የስራ ሃላፊ ቢሆኑ፣ ወዘተ ወዘተ ለሀገር ሰላምና አንድነት አይበጅም፡፡ በሀገራችን በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የጎሳዎች ግጭት መሰረታዊ ምክንያት የጎሳ ፖለቲካ የፈጠረው ሳንካ ነው፡፡(ሌሎች አስተዳደራዊ እና ተፈጥሮአዊ ችግሮችን ለአብነት ያህል በግጦሽ እና ውሃ እጥረት ወዘተ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡) ብዙዎች የሚጋጩት ይሕ የእኔ ወረዳ ነው፡፡ በዚህ ዞን ወይም ቀበሌ የስልጣን ባለቤት እኔ ብቻ ነኝ፣ ሌላው የሚሄድበት ይሂድ በሚሉ ከአፍንጫቸው አርቀው ባማያስቡ የህዝብ ወኪል ነን ባዮች፣ የከንቱ ከንቱ ሰዎች ምክንያት፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚኖረው ምልአተ ህዝቡ እጅግ ጨዋ፣ሀይማኖተኛ፣ ደግ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግጭት የሚቆሰቁሱት የጎሳ ታፔላ የለጠፉ ጥቂት የጎሳ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡  ለምን ይሆን ጎሳን፣ የቋንቋ እና ባህልን እኩልነት ከፖለቲካ ጋር የምናደባልቀው ? እውን የጎሳ መብት ከሌሎች የመብት አይነቶች የተለየ ነው ? ወይም የጎሳ መብት ከሰብዓዊ መብቶች የበለጠ ነውን ለአብነት ያህል ትምህርት ከማግኘት መብት የበለጠ ነውን ? በእኔ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ የጎሳ መብት ፖለቲካዊ ሆኗል፡፡ በብዙዎቻችን ላይም ተጽእኖው  የሰፋ ነው፡፡ ስለሆነም በጎሳ ላያ ያለንን አስተሳሰብና ፖሊሲ መፈተሸ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህል የጎሳ መብት እና ትምህርት የማግኘት መብት፣ንጹህ ውሃ የማግኘት መብት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ በእኩል ሚዛን ላይ መቀመጥ አለባቸው፡፡ ወይም እኩል ክብደት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

ለልጆቻችን ምርጥ እና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት የሚሠጡ፣ እንዲሁም የተሟላ ቤተሞከራና ቤተመጽፍት ቤቶች ያሏቸውን የትምህርት ተቋማትን ለመመስረት የምንፈልግ ከሆነ፣ የህዝቡን ልማት ማሻሻል፣የህዝቡን ቋንቋና ባህል ማበልጸግ፣ እንዲሁም ህዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ነጻነቱ መገደብ የለበትም፡፡ የሰው ልጅ ነጻነት ተፈጥሮአዊ መሆኑን መረዳት ብልህነት ነው፡፡ እንዳንዱ ግለሰብ፣ ሁሉም ማህበረሰብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ በጥቂት ፖለቲካ ዘዋሪዎችና ቃፊሮቻቸው ግልብ ውሳኔ መደፍጠጥ የለበትም፡፡ በአለም ላይ ካሉት ሀገራት መሃከል አብዛኞቹ ያደጉትና የሠለጠኑት 

ሀገራት ሚስጥር የሰው ልጅን ነጻነት በማክበራቸው ነው፡፡ ሌላውን ለግዜው ትተን በሰለጠነው አለም የማሰብ፣ የመናገርና የመስራት መብቶች ምሉሄበኩልሄ ወደመሆን ደረጃ እየደረሱ ይገኛሉ፡፡

ከታሪክ እንደምንማረው፣ወይም ታሪክ እንዳረጋገጠው ጎሳን ፖለቲካዊ ማድረግ፣ ወይም የጎሳ ፖለቲካ ለአንድ ሀገር የሚጠቅማት አይደለም፡፡ የታላቁ ብሮዝ ቲቶ ሀገር የነበረችው ዩጎዝላቪያ፣ሶሪያ፣የመን፣ሊቢያና ሶማሊያ ትምህርት ሊሆኑን ይገባል፡፡አንድን ጉዳይ ፖለቲካዊ ማድረግ፣ ለአብነት ያህል ከአንድ ጎሳ ወይም ከብዙ ጎሳዎች ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን ከፖለቲካ ጋር ማደባለቁ ለአንድ ሀገር ብሔራዊ አንድነት አደጋን ሊጋብዝ ይቻለዋል፡፡ የተረጋጋ የፖለቲካ ጨዋታ እንዳይኖርም ደንቃራ ይሆናል፡፡

ጎሳን ፖለቲካዊ ማድረግ ወይም የጎሳ ፖለቲካ ህዝብ ማናቸውንም ነገር ከጎሳ ጋር የሚያገናኝባቸውን አካባቢዎች እንዲፈጥር ያደርጋል፡፡ ጎሳ ማለት ማናቸውም ነገር ነው በማለት ሰዎች እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡ ለአብነት ያህል በአንድ የጎሳ ክልል የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ ሰው ሰራሽ ሀብት የጎሳው ተወላጆች ብቻ ነው በማለት ሰዎች ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ከዚህ ባሻግር የጎሳ ፖለቲካ የሚከተሉትን ችግሮች ይቀፈቅፋል፡፡

  • የጎሳ ፖለቲካ ሰዎች ምክንያታዊ እንዳይሆኑ ያደርጋል
  • ቁጭ ብሎ በመነጋገር ችግር ከመፍታት ይልቅ ለጠብ ይጋብዛል፡፡ ( ለአብነት ያህል በአንድ ገበያ ስፍራ ሁለት ከተለያዩ ጎሳዎች የመጡ ጀብራሬ ግለሰቦች በማይረባ  በፈጠሩት ጠብ ምክንያት( በግል ጉዳይ ሊሆን ይችላል) አንደኛው ግለሰብ ክፉኛ ቢጎዳ፣ የግለሰቡ የጎሳ አባላት ከእርቅ ይልቅ ወደ ጠብ ተንደርድረው ይገባሉ፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት በዝዋይ (ባቱ) ከተማ ሁለት የባንኮኒ አርበኞች በፈጠሩት ጠብ ምክንያት የአንደኛው ግለሰብ ህይወት በማለፉ ምክንያት የተነሳ በበነጋታው በከተማዋ የሚኖሩ የገዳይ ግለሰብ ብሔር ተወላጆች ላይ የተፈጸመው አስከፊ 
  • የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ( በነገራችን ገዳይ በህግ ቁጥጥር ስር ሆኖ ፍርዱን እየተከታተለ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በአጭሩ የጎሳ ፖለቲካ አቅልን የሚያሳጣ፣ የህሊና ሚዛንን የሚሰብር ነው ማለት ይቻላል፡፡
  • የጎሳ ፖለቲካ ሰዎች በጭፍን ጥላቻ ተነሳስተው የጋራ እሴታቸውን እንዲያጠፉ ይጋብዛል፡፡
  • ጎሳን የበለጠ ፖለቲካዊ ስናደርገው፣ የበለጠ ውጥረት እንፈጥራለን
  • አለመተማመን እና የጥላቻ መንፈስ እንደ ሰደድ እሳት ይቀጣጠላሉ
  • የጎሳ ፖለቲካ የሰዎችን አይምሮ ይሰርቃል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ሰዎች የአይምሮ ሀይላቸውን እንዳይጠቀሙ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡ ሰዎች የተስፋ ዳቦ እንዲገምጡ ከማዘናጋቱ ባሻግር፣ ውድ ግዜያቸውንና የተፈጥሮ ሀብታቸውን ያባክናል፡፡ ባለፉት ሰላሳ አመታት በኢትዮጵያ የነገሰው የጎሳ ፖለቲካ የኢትዮጵያን ህዝብ በየጎሳው ሸንሽኖ የስብሰባ መዓት አወረደለት እንጂ፣ የኢትዮጵያን አብዛኛውን ህዝብ አጠቃላይ የኑሮ እድገት አላመጣለትም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ቢያንስ የኢትዮጵያን ህዝብ የዳቦ ፍላጎት ለሟሟላት የሚያስችል የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ማውጣት አልሆነለትም፡፡ ከሶስት አመት ወዲህ በትረ ስልጣኑን የጨበጠው የብልጽግና ፓርቲ የሸገር ዳቦ ፕሮጄክት ቢያንስ የአዲስ አበባን ህዝብ የዳቦ ፍላጎት እንደሚያሟላ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
  • የጎሳ ፖለቲካ የአንድን ሀገር የረዥም ግዜ ህልምና ኢንስፓይሬሽን ያጠፋል
  • የጎሳ ፖለቲካ የአንድን ሀገር ብሔራዊ ፍላጎት ስእል ያጠፋል፤ በተቃራኒው ዜጎች ስለጣበቡ ጎጆአቸው( ክልላቸው) ብቻ እንዲያስቡ ከማድረጉ ባሻግር፣ ህብረተሰቡ ለጥቂት የስልጣን ጥመኞችና አድርባዮች መሳሪያ ወይም ተገዢ ሆኖ እንዲቀር ያደርገዋል፡፡ ዜጎች ስለ ክልላቸው ብቻ እንዲያስቡ በማድረግ በአለም ላይ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ፣ የአለም መዘባበቻ እንዲሆኑ ይጋብዛል፡፡

በአጠቃላይ ሀገሪቱ ወደኋላ የቀረረችው፣ በምግብ ራሷን መቻል ያቃታት፣ተረጂ የሆነችው ወዘተ ወዘተ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ተጨምረውበት በዋነኝነት በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት ነው፡፡

Politicization of ethnicity is the root causes of our poverty and backwardness

እኛ ኢትዮጵያውያን ለጎሳ ፖለቲካ ህይወታችንን ከፍለናል፣ ጉልበታችንን አፍሰናል፣ የወደፊት ህይወታችንም በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ እውን አብዝሃው ኢትዮጵያዊ በጎሳ ፖለቲካ ተጠቃሚ ነውን ህሊና ያላችሁ ጠይቁ መልሱንም በተመለከተ በየሰፈራችሁ ተወያዩበት፡፡ በነገራችን ላይ በሀገራችን ቤጊዜው ችጋር የሚከሰተው በሀብት እጦት ብቻ አይደለም፡፡ የሰለጠነ ሰው ሀይል እጥረትም አልነበረም፡፡ ወይም በሌላም ምክንያት አልነበረም፡፡ ሆኖም ግን የጎሳ ፖለቲካ፡-

  • ራእያችንን ስላጠፋብን
  • ጉልበታችንን
  • ጊዜያችንና
  • ሀብታችንን ለብዙ አመት ስላጠፋብን ነበር፡፡

ለአብነት ያህል እድሜ ልካቸውን አፈር ገፍተው በማምረት ኑሮአቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያዊ አርሶ አደሮች፣ በጎሳ ፖለቲካ በሰከሩ አክራሪ ብሔርተኞች በሚከፈትባቸው ድንገተኛ ጥቃት ውድ ሕይወታቸው ይቀጠፋል፤አካላቸው ይጎድላል፡፡በለስ የቀናቸው ቀዬአቸውን ለቀው ተንከራታች ይሆናሉ፡፡ በችጋር ይገረፋሉ፡፡ ከአሰቦት ገዳም እና አርባ ጉጉ ጀምሮ አሁን ድረስ፣ በምእራብ ወለጋ እና ቤኒሻንጉል ክልል ለዘመናት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በተለይም የአማራ ብሔር ገበሬዎች ከሚደርስባቸው ጥቃት ማግስት ጀምሮ እጣ ፈንታቸው በሀገራቸው ምድር መፈናቀል ነው፡፡ በአጭሩ ያቀረብኩት ምሳሌ የጎሳ ፖለቲካ መጨረሻው የሐገርን አንድነት ከማናጋቱ ባሻግር ችጋርን መቀፍቀፍ እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳላ የጎሳ ፖለቲካ ትሩፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ካለውም ትሩፋቱን ጠንቁን ማለት ሳይሻል አይቀርም፡፡ እንደሚከተለው እግልጸዋለሁ፡፡ የጎሳ ፖለቲካ፡-

  • የግጭትና የጦርነት ምንጭ ነው
  • ላለፉት ሰላሳ (30) አመታት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ለዘመናት ይኖሩበት ከነበረው ገጠሮችና ከተሞች ተፈናቅለው በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር ሆነው ቀርተዋል፡፡
  • ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያዊ ዜጎች ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡
  • በነገራችን ላይ በጎሳዎች መሃከል በግጦሽ እና ውሃ ምክንያት  ባለፉት 100 አመታት ውስጥ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የተነሳ ማሰብ የሚችሉ፣ ሀገርን ወደ አድገት ጎዳና መውሰድ የሚችሉ ትውልዶች ተቀጥፈው እንደቀሩ ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም በጎሳ ላይ ፖለቲካን መደባለቅ፣ በእሳት ላይ ቤንዚን እንደመጨመር ይቆጠራል፡፡ 

እኛ በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ የምንኖር ዜጎች የጎሳ ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ስለሚመክንበት ሁኔታ በስሜት ሳይሆን ቁጭ ብለን በሰከነ መንፈስ፣በሰለጠነ መንገድ መነጋገር በሚገባን የታሪክ መታጠፊያ ላይ እንገኛለን፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጎሳዎች ወይም ብሄሮች ቋንቋቸውና ባህላቸው ለዘመናት ከእኛ ጋር የኖረ ነው፡፡ሁሉም ከቋንቋቸውና ባህላቸው ጋር ለዝንተ አለም ኖረዋል፡፡ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም አንቺ ትብሽ፣ አንተ ትብስ በመባባል ለዘመናት በሰላምና በፍቅር እንደኖሩ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ ስለሆነም ድንገት ተነስተን የጎሳ ፖለቲካ መከተል አልነበረብንም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ አሰፈላጊ ነው የምትሉ ደግሞ ውጤቱን በህይወት እያላችሁ ለማየት ስለበቃችሁ ወደ ህሊናችሁ እንድትመለሱ ስማጸን በአክብሮት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በተቃራኒው አሳሳቢ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ከቁጥጥር ውጭ እየመጣ ይገኛል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ እየገነገነ ይገኛል፡፡ ቤእለቱ ህይወታችን እንደምናየው፣ እንደምነገነዘበው የጎሳ ፖለቲካ ስረ ሰዷል፡፡ ባለፉት 30 አመታት የጎሳን ፖለቲካ ስር እንዲሰድ ከማድረግ አኳያ በኢትዮጵያ ታሪክ አቻ አይገኝለትም፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 30 አመታት ለጎሳ ፖለቲካ ለም መሬት ሆናለች፡፡ ዛሬም አሁን ባለንበት ጊዜ ማለቴ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ  በማይታወቅበት ሁኔታ የጎሳ ፖለቲካ እግርና እጅ አውጥቷል፡፡ከኢትዮጵያዊ ማንነት፣ የጎሳ ማንነት እየቀደመ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የጎሳ ፖለቲካ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ሰማየሰማያት ላይ ለመስፈን ሞራል የለውም፡፡ ምክንያቱም በየአካባቢው የሚከሰቱ ጥፋቶች፣ችግሮች፣ግጭቶች፣ሰላምና አለመረጋጋት አለመኖር ምክንያታቸው በአንድም ሆነ በብዙ መልኩ በአብዛኛው የጎሳ ፖለቲካ ባመጣብን ጣጣ ነው፡፡ ( ሌሎች በርካታ ምክንያቶችን ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡)

በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ የጎሳ ፖለቲካ አልነበረም ማለት አይቻልም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ተጀመረው በ1966ቱ የዩነቨርስቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እና ከዛ ትንሽ ቀደም ብሎ በነበሩት አመታት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማየ ሰማያት ላይ ቦግ እልም ይል ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር በአንድ ወቅት ይታያል፣ተመልሶ ደግሞ ይከስም ነበር፡፡ ባለፉት 30 አመታት ግን የጎሳ ፖለቲካ ሁሉንም ነገር የሆነ ይመስላል፡፡

At some point in our history, ethnic politics was implicit and at some other time it was explicit. Today ethnic politics seems everything.

ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በአገዛዞች ስር እንደነበረች የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ በአገዛዞች የአምባገነንት ባህሪ የተነሳ በደሎች ነበሩ፣ ጭቆና ነበር፡፡ ጭቆናም ሆነ በደሉ ግን በአንድ ጎሳ ወይም ብሔር ላይ ያነጣጠረ አልነበረም፡፡ የበደሉ ተቋዳሽ ሁሉም የኢትዮጵያ አፈር ገፊ ወይም የከተማ ነዋሪ ላይ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጭቆና ለብዙ ዘመናት ስለመኖሩ የሚደበቅ አይደለም፡፡ በአጼ ሐይለስላሴ ዘመነ መንግስት፣ በደርግ አገዛዝ እና በወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ጭቆና ነበር፡፡  ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ህዘብ የመሬቱ ባለቤት አልነበረም፡፡ ዛሬም ቢሆን መሬት የመንግስት ነው፡፡ ዋነኛው የምጣኔ ሀብት እድገት ቁልፍ መሬት እውነተኛ ባለቤት ህዝቡ መሆን ካልቻለ ደግሞ ኑሮአችን አድሮ ቃሪያ ስለመሆኑ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኑሮ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) ቋሚ ምስክር ነው፡፡ በደርግ የአገዛዝ ዘመን የፕሬስ ነጻነት አልነበረም፡፡ በአጭሩ ከአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ጀምሮ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆን አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጣንን መግራት አልሆነለትም፡፡ ለምን መልሱን የህሊና ሚዛኑ ላልተሰበረበት ኢትዮጵያዊ ዜጋ ትቼዋለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ አንዳለ ዛሬ ደግሞ የጎሳ ፖለቲካው ጫፍ ላይ በመድረሱ የሀገሪቱን ብሔራዊ ፍላጎትና አንድነት አደጋ ላይ ጥሎት ይገኛል፡፡ ነገሩ አንዱን ችግራችንን ሳንፈታ በሌላ የችግር አዙሪት ውስጥ መዳከር እጣፈንታችን የሆነ ይመስላል፡፡ ሌሎች ትላንት ከቅኝ አገዛዝ መዳፍ ስር የተነሱ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ሀገራት ከጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥተው የነጻነት መንገድን ሲመርጡ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ተብላ የምትጠራ ሀገር እኛን ኢትዮጵያዊ ለምን አቃተን ?

ስለሆነም ካለፈው የታሪክ ስህተታችን እንማር፣ ለራሳችንም የሚከተለውን ጥያቀ እናቅርብ፡፡ ለምንድን ነው አሁን ድረስ በጎሳ ፖለቲካ አመድ ላይ የምንከባለለው ?

በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአለም ላይ እንደ ጨው ዘር ተበትነው  እንደሚገኙ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎቹ እንደው ዝም ብለው ሀገር ጥለው የሚሄዱ አይመስለኝም፡፡ ቀላል ቁጥር የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ከብዙ ሀገራት ልምድ ቀስመዋል፡፡ ለአብነት ያህል ውጭ ሀገር ሄደው የተመለሱ በሀብት ማማ ላይ ለመቀመጥ የቻሉ፣አዱኛ ቤታቸው የገባችላቸው ኢትዮጵያውያን ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ሆኖም ግን ከፖለቲካ ስህተታችን መማር አልቻልንም፡፡ በአጭሩ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ በመነሳት ለኢትዮጵያ የሰለጠነ ፖለቲካ ለማንበር አልሆነልንም፡፡ ሌሎች ሀገሮች የሰለጠነ መንግስት ለምን ማቆም ቻሉ እኛ ለምን አልሆነልንም በማለት ቁጭት ውስጥ በመግባት መነሳሳት አልሆነልንም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በህይወት በነበሩበት ግዜ እንደነገሩን፣ ከገባን ማለቴ ነው፡፡ ‹‹ እኛ መንቀል እንጂ፣ መትክል ›› አልቻልንም፡፡ ጭቆናን ሳይሆን ጨቋኝን እንቃወማለን፡፡ ጨቋኝን የምንቃወመው ደግሞ እኛ ራሳችን ጨቋኝ ለመሆን እንጂ ጭቋናን ለማጥፋት አይደለም፡፡ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አለም በሰለጠነበት ዘመን ከዚህ ድንዛዜ አለመውጣታችን ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡  ማሳዘን ብቻ አይደለም ይህች የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ ባለቤት የሆነች ሀገር፣ በርካታ ስመጥር ነገስታት የነበራት ሀገር፣ በአለም ደረጃ ሳይቀር ጥቂት የማይባሉ ምሁራን የነበሯት ኢትዮጵያ እንዴት ከጎሳ ፖለቲካ መውጣት ሊያቅጣት ቻለ የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡በአጭሩ ባለፉት 100 አመታት ርስበርሳችን ስንባለ ነው ውድ ግዜያችንን ያጠፋነው፡፡ እኛ ተመሳሳይ ስህተት  የምንፈጽም አሳዛኝ ዜጎች ነን፡፡ ለምንድን ነው በጎሳ ፖለቲካ አመድ ላይ ደግመን ደጋግመን የምንከባለለው የሰው ልጅ ከሌሎች እንሰሳት የሚለይበት ዋነኛው ምክንያት የአይምሮ ሐይሉን መጠቀም በመቻሉ ነው፡፡ ሌሎች ህይወት ያላቸው እንሰሳት ተፈጥሮአቸው ስለሆነ አንድን ስህተት በየጊዜው ሊፈጽሙ ይቻላቸዋል፡፡ የሰው ልጅ ግን አንድን ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጽም የአይምሮ ሀይሉ ይረደዋል፡፡ የሰው ልጅ ከግዜ ብዛት፣ ከትምህርት ባገኘው እውቀት በመረዳት ለኑሮው የሚያስፈልገውን ብልሃት ፈጥሯል፡፡ ተመሳሳይ ስህተት ላለመስራት ይጠነቀቃል፡፡ እኛም ካለፈው ስህተታችን መማር  ነበርብን፡፡ ሆነም ግን እንደው ተያይዞ እንዘጭ እምቦጭ ሆኗል ህይወታችን፡፡ በነገራችን ላይ ለብዙ ዘመናት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጭቆና ስለመኖሩ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስትም ሆነ በወታደራዊው ደርግ አገዛዝ ዘመን ፣ በወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ጭቆና ነበር፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ ይሕ በእንዲህ እንዳለ ከብዙ ዘመን ጀምሮ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እና ስልጣንን መግራት አልሆነለትም፡፡ ለምን መልሱን የህሊናው ሚዛን ላልተሰበረበት ኢትዮጵያዊ ዜጋ ትቼዋለሁ፡፡ ለአብነት ለኑሮ እድገት መሰረታዊ ቁልፍ የሆነው የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ አሁን ድረስ መልስ አልተገኘለትም፡፡ በዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተጨምረው የኢትዮጵያ ህዝብ አጠቃላይ የኑሮ እድገት አድሮ ቃሪያ ሆኗል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም እኛ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ስህተት ደግመን ደጋግመን እንሰራለን፡፡ ከታሪክ ስህተታችን መማር የቻልን አልመስልህ አለኝ፡፡ በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን የነበሩት ጄኔራል አብይ አበበ ‹‹ አውቀን እንታረም ›› በማለት ምክረ ሃሳብ ቢያቀርቡም ዛሬም አውቀን መታረም አልቻልንም፡፡ በእውነቱ አንገትን ያስደፋል፡፡ ያሳፍራልም፡፡

ከድህነት፣ ችጋር ነጻ ሳንወጣ፣ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ምሉሄ በኩልሄ በሆነ ሁኔታ ማንበር ሳይሆንልን፣ ባለፉት ሰላሳ አመታት ደግሞ የጎሳ ፖለቲካ ተከታይ በመሆናችን የሀገሪቱን ህልውና እና አንድነት አደጋ ላይ ጥለነዋል፡፡ የጎሳ ፖለቲካን መርዝ በሀገራችን በመርጨት የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ  ግንባር ቀደም ተጠያቂ ቢሆንም፣ አሁን ያለው ትውልድ ከተጠያቂነት አያመልጥም ምክንያቱም የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ይበጃታል ወይንም አይበጃትም በሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ላይ ቁጭ ብሎ በሰለጠነ መንገድ ለመነጋገር ባለመቻሉ ነው፡፡ ይሄ ሲባል ግን ጥቂት  እንደነ  ጋዜጠኛ ተመስገንን የመሰሉ ቆራጥ ኢትዮጵያውያን አልነበሩም ማለቴ አይደለም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የጎሳ ፖለቲካን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን በሰከነ መንፈስ እንዲነጋገሩ በድጋሚ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ይረዳን ዘንድ አዲስ ዘዴ፣ አዲስ አስተሳሰብ  ፣ አዲስ ስትራቴጂ በባለሙያዎችና ምሁራን  መነደፍ ያለበት ይመስለኛል፡፡

         We have to  move away to new approaches, thinking and strategies.

     ጸሃፊው የማናቸውም ፖለቲካ ድርጅት አሸርጋጅ ወይም ነቃፊ አይደለም፡፡ በማናቸውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ቆመው የፖለቲካ ድርጅት መስርተው የሚታገሉ ኢትዮጵያውያንን የሚቃወም ወይም ደግፎ የሚቆም አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ የሰለጠነ መንግስት እንዲኖር፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ሲል ነው የግል አስተያየቱን ማቅረቡን አንባቢውን ያስታውሳል፡፡ ከዚህ ባሻግር ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቱን በመጠቀም ነው ሃሳቡን ያንሸራሸረው፡፡ ለማናቸውም ምርጫውን የሚጥመውን ለሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ትቼዋለሁ፡፡

ከገባንበት የፖለቲካ ችግር አዙሪት እንዴት መውጣት ይቻለናል ?

በእኔ የግል አስተያየት የሚከተሉት  ምክረ ሀሳቦች ጠቃሚ ናቸው ብዬ አስባለሁ

  1. ባለፉት አመታት ለተፈጸሙ ፖለቲካዊ ስህተቶች ሁሉ ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊ ነው
  2. ለወደፊቱ ህይወታችን የሚበጅ በእውነት እና መግባባት ላይ የተመሰረተ አዲስ ራእይ ይበጀናል
  3. መሰረታቸው የማይናጋ የዲሞክራሲ ተቋማትን አጠናክሮ መገንባት
  4. ባለፉት አመታት የተከሰቱ ፖለቲካዊ ችግሮች በአብዛኛው ምክንያቱ የጎሳ ፖለቲካ ፍለስፍና በሀገሪቱ ስለሰፈነ መሆኑን ፣ በእውነት መሰረት ላይ ሆነን እንተማመን ( በነገራችን ላይ ለተፈጠሩት ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽ ሁሉ የገሳ ፖለቲካ ብቻ ነው ብሎ መደምደሙ ከባድ ስህተት ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ እነኚህን መጠነ ሰፊ ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ግን ከጎሳ አጥር ወጥተን መነጋገር አለብን፡፡ በርታ አፍሪካውያን ፖለቲካዊ ችግሮቻቸውን የፈቱት ከጎሳ ፖለቲካ ከተገላገሉ በኋላ ነው፡፡ ጎረቤታችን ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ፣ጋና፣ሞሪሸስ፣ቦትስዋና፣ናሚቢያ ፣ሴኒጋል ወዘተ ወዘተ የዲሞክራሲ ጎዳና ላይ የሚገኙት በህገመንግስታቸው ሳይቀር የጎሳን ፖለቲካ በማገዳቸው ይመስለኛል፡፡ አለምን ባስደነገጠ መልኩ አስከፊ የዘር ፍጅት የተፈጸመባት ሩዋንዳ ሳትቀር የጎሳን ፖለቲካ በህግ አግዳ በእድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰች ትገኛለች፡፡ መሪዋ ፖልካጋሚ ሳይቀሩ ኢትዮጵያ አፋጀሽኝ ከሆነው፣ መሰረቱን ቋንቋና ጎሳ ላይ ካደረገው ፖለቲካ መውጣት እንዳለባት የሚያሳይ ምክር መስጠታቸውን ከአለም መገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል
  5. አስተሳሰባችንን፣አመለካከታችንን ፣ መስመራችንን ከጎሳ ፖለቲካ ወደ የሕዝብ ፍላጎት ተቋም ወደ የሚወስደን ጎዳና መዘወር አለብን፡፡ ይህ የህዝብ ተቋም ደግሞ በህግ የበላይነት ፣ የዲሞክራና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ዙሪያ ላይ ተመስርቶ የህዝብን ፍላጎት ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

We have to change our paradigms from ethnic politics to institutionalization of people’s demands and enforcing those demands based on the rule of law. 

  1. በቅርብ ግዜ የመጣው ፋሽን በዲሞክራሲ ስም የህግ የበላይነትን በእጃቸው መዳፍ ላይ ማስቀመጣቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ሸፍጥ የጎሳ ፖለቲካ ሌላው መገለጫው ነው፡፡ ነገሩን ላብራራው፡፡ በዲሞክራሲ ስም የሕግ የነላይነትን መደፍጠጥ ተገቢ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ደሞክራሲ መሆን የሚቻለው በህግ ሲመራ ነው፡፡

ዴሞክራሲ ማለት፡-

  • የመናገር ነጻነት
  • የማወቅ ወይም መገንዘብ እና
  • የመስማት ወይም ማደመጥ ነጻነትን ያጠቃልላል፡፡

በሌላ አነጋገር ዴሞክራሲ አንዱ የህይወታችን ክፍል ነው፡፡ ህይወታችን ደግሞ በእቅድ የሚመራው ወይም ቀጣይነት ሊኖረው የሚቻለው የህግ የበላይነት እውን ሲሆን ነው፡፡ ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ የሚሆነው ፣ የህግ የበላይነት ሲከበር ነው፡፡ የህግ የበላይነት በማይከበርበት ዴሞክራሲ ሊሰፍን አይቻለውም፡፡ እንዲህ አይነት ክስተት ባለበት ሀገር የሚሰፍነው ዴሞክራሲ ሳይሆን፣ ዴሞን-ክራሲ( demon-cracy ) ነው፡፡ ይህም ማለት በዲሞክራሲ ስም ህዝብን መግዛት ማለት ነው፡፡

Democracy without the rule of law is not democracy but something else or we can call it demon-cracy, the democracy of the demon

በነገራችን ላይ ዴሞክራሲ ሁልግዜ አንድን ነገር ለማግኘት የሚረዳ መንገድ ላይሆን ይችላል፡፡ ራሱ ዴሞክራሲ ግብ ነው፡፡ ዴሞክራሲን ለማስፈን ሰዎች በብዙ መንገድ ይታገላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ብዙ ሰዎች ሌሎች ነገሮችን ለማግኘት ዴሞክራሲን እንደ አንድ ዘዴ (ወይም መንገድ (democracy is used as a means) ይጠቀማሉ፡፡ በውጤቱም አንዳንድ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ዴሞክራሲን አለአግባብ ይጠቀሙበታል፡፡ መሆን የነበረበትና መደረግ ያለበት ግን ዴሞክራሲን ራሱን በእውነት መሰረት ላይ ሆኖ ማስፈንና መተግበር ነው፡፡ በስመ ዴሞክራሲ ስንት ግፍ ተሰርቷል፡፡

  1. ራሳችንን ከጎሳ ፖለቲካ ጋር ካጣበቅን፣ በተለያዩ ጎሳዎች ወይም ብሔር መሃከል የነበረው ወይም ያለው መተማመን እየተሟጠጠ ይሄዳል፡፡ በማናቸውም የሰው ልጆች ታሪከ ላይ እንደታየው የጎሳ ፍልስፍና የተመሰረተው በግንኙነት ላይ ነው፡፡ ይህም ማለት የአንድ ጎሳ ተወላጆች ከሌሎች ጎሳ አባላት ይለቅ ከራሳቸው ጎሳዎች ጋር መቀራረባቸው ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ስለሆነም የአንዲትን ሀገር የትላንት፣ዛሬና ነገን እጣ ፈንታን ለመወሰን የሚደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች መሰረታቸው አንድ ጎሳ ወይም ብሔር ላይ ከተንጠለጠለ የዛች ሀገር አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ ስለመውደቁ እነ ዩጎዝላቪያ፣ሶማሊያ፣የመን፣ኢራቅ፣ ሊቢያ ወዘተ ወዘተ ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ሲፋጅ በማንኪያ፣ ሲቀዘቅዝ …..እንዲሉ አንዳድ ፖለቲከኞች በመጥፎ እና በጥሩ ግዜያት ውስጥ ራሳቸውን በጎሳቸው ( ብሔር) ውስጥ እንደሚደብቁ መታወቅ አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር አቋማቸው እንደ አየሩ ጸባይ የሚለዋወጥ ነው፡፡ ዛሬ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አብዝሃው ፖለቲከኞች የብሔር ካባቸውን ለብሰው ብቅ ብለዋል፡፡ እነኚሁ ፖለቲከኞች ወደ ቀደመው፣ ወደ ጥንቱ የብሔር ዋሻቸው ውስጥ ተደብቀው ይታያሉ፡፡ወሳኙ የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ብረዳም ( የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ይበጃታል ወይም አይበጃትም በሚለው ውሳ ህዝብ ማለቴ ነው) የጎሳ ፖለቲካ ለአንዲት ትልቅ እና በርካታ ጎሳዎች ለሚኖሩባት ሀገር አደገኛ ነው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት ሃያ ሰባት ( 27) አመታት በጎሳ ፖለቲካ የተጓዝንበትን መራር ወጣ ገባ መንገድ በግልጽ አይተነዋል፣ተግተነዋል፡፡ ዛሬም እየቀመስነው እንገኛለን፡፡ በአስደንጋጭ ሁኔታ የጎሳ ፖለቲካ ወድቋል፡፡ በተፈጥሮው የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ አግላይ ነው፡፡ የእኔና የእነርሱ በሚል ትምክህት የታበየ ነው፡፡ በአደገኛ ሁኔታ ከአንድ ሀገር ብሐየራዊ ፍላጎት ጋር የሚጋጭም ነው፡፡ ከዚህም ባሻግር አንዱ ጎሳ ያለው ፍላጎት ከሌላው ጎሳ ጋር እንዲጣረስ ያደርጋል፡፡ የግለሰብ መብትንም ይጥሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ ሊወዳደሩ የማይችሉ የምጣኔ ሀብትና ማህበራዊ አካባቢዎችን እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ ሊፈቱ የማይችሉ ቅራኔዎች በህዘብ መሃከል ያሰፍናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ዘርፈ ብዙ አደጋዎችን በብሄራዊ ፍላጎት ላይ ሊጋርጥ ይቻለዋል፡፡

ስለሆነም እንደ አንድ የሠለጠነ ሀገር ዜጋ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞችን ፍላጎት ለመመለስ አንድ ዲሞክራቲክ ተቋም ማቆም ያለብን ይመስለኛል፡፡ ማለትም የጎሳ ፖለቲካ ፍላጎት የሕዝብ ጥያቄ ነው ወይንስ የጥቂት የስልጣን ህልመኞች ጥያቄ ነው የሚለውን ለማወቅ ይረዳናል፡፡

በነገራችን ላይ  በእኩልነት መርህ on the principles of equality ፣ ፍትህ, justice ፣ዴሞክራሲ democracy ፣ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት basic human rights,  ፣ አድሎአዊነትን ከማስወገድ አኳያ non-discrimination ፣ ከጋራ ፍላጎታችን አኳያ, common interest ላይ  ወዘተ ወዘተ ብሔራዊ መግባባት ላይ ከደረስን የጎሳን ፖለቲካ ለማራመድ ለምን እንፈልጋለን ? በነገራችን ላይ እንደ ብዙ የህግ አዋቂዎች ጥናት ከሆነ አሁን በስራ ላያ የሚገኘው ህገመንግስት ከእነብዙ ችግሮቹ የጎሳን ፖለቲካ ለማምከን የመጀመሪያው ነጥብ ሊሆን ይቻለዋል፡፡ የሕዝብንም ፍላጎት ከዲሞክራሲ መርሆ አንጻር ለመመለስ የሚያስችል ተቋማትን ለማጠናከር ይረዳል፡፡ በእኔ በኩል ወደፊት ሰፊ ውይይትና ክርክር ከተደረገ በኋላ ከጎሳ ፖለቲካ ባሻግር ወደ ዜግነት ፖለቲካ ሊወስድ የሚችል ጎዳና መገንባት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀላፊነት መሆኑን  እያስታወስኩ  ወደፊት በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ቢካተቱት ጠቃሚ መሆናቸውን እያስታውሰኩ  አንዳንድ ነጥቦች ዝቅ ብዬ ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡ እነኚህ ነጥቦች በህገመንግስቱ ውስጥ ቁልጭ ብለው ይታያሉ

1.ሁሉም ቋንቋዎችና ባህል እኩል መሆናቸውን በነቢብም በገቢርም መቀበል፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 5(1) ላይ እንደተጠቀሰው ማናቸውም ቋንቋና ባህል እኩል ናቸው ይላል

  1. ማናቸውንም ቋንቋና ባህል አለምንም አድልዎ ማሳደግ፣ ማበልጸግ የሚለውን ሙሉበሙሉ መቀበል ለውይይቱ በር ይከፍታል፡፡  በኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀጽ 39(2) እና አንቀጽ 91 (1) የተጠቀሱትን ልብ ይሏል፡፡
  2. ባለቤትነትና ተጠያቂነትን በትክክል ገቢራዊ ማድረግ፡፡ ማናቸውም ጎሳዎች ወይም ብሔሮች የራሳቸውን ባህልና ቋንቋ ማሳደግ ይችላሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ያለፌዴራሉ መንግስት ጣልቃ ገብነት እያንዳንዱ ጎሳ( ብሔር) የራሱን ቋንቋና ባህል እንዲያሳድግ ስልጣኑ አለው
    4. የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ዲሞክራቲክ ተቋማት መገንባት አሌ የሚባል ነገር አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀጽ 91(1) እና 51 እንደተጠቀሰው የፌዴራል መንግስቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩ ቋንቋዎችን እና ባህልን ለማሳደግ የህግ ማእቀፍ ማዘጋጀት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ልክ ጤና ፣ትምህርትና የመሳሰሉትን ለማስፋፋት እንደሚደረገው ማለቴ ነው፡፡
  3. ራስን በራስ የማስተዳደር አለም አቀፍ መብት ያለምንም ጣልቃ ገብነት ገቢራዊ መሆን አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ የህዝብን ፍላጎት ባማከለ መልኩ፣የሕዝብን አሰፋፈር በመስኩ ባለሙያዎች በማስጠናት፣ የመልክአምድር አቀማመጥ ባገናዘብ መልኩ፣የምጣኔ ሀብት እድገትን ሳይገታ፣ ለህዝብ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል፣ እንዲሁም ለአስተዳደር አመቺ በሆነ መልኩ ወዘተ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ወይም ያልተማከለ አስተዳደደር ገቢራዊ ከሆነ  እጅጉን ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

እንደ መደምደሚያ

ለሁልም ኢትዮጵያውያኖች በሙሉ፣ለህዝቡ፣ለምሁሩ፣ በሃይማኖት በኩል ያላችሁትን ሁሉ፣ወንዶችም ሴቶችም፣ወጣቶችም፣ህጻናትም ፣ሁላችሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ያላችሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን መስማማት አለብን፡፡ መነቋቆር፣መጎዳዳት  መገዳደል የለብንም፡፡አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም ያሳዝናል፡፡ ያሳፍራል፡፡ የሰላማዊ ዜጎች ግድያ አሳዛኝ ዜና ሰርክ አዲስ ይሰማል፡፡ እድሜ ለቴክኖሎጂ ይህ ደግሞ ለአለም  ሚስጥር አይደለም፡፡ 

እኛ በፍቅር በአንድነት መኖር አለብን እንጂ ጎራ ለይተን ወይም ብሔር ለይተን መጠፋፋት የለብንም፡፡ በየቦታው በህይወት የመኖር መብት እንዲከበር ሁላችንም አንድ አምሳል፣አንድ አካል መሆን ቢያቅተን መተባበር የሰውነት ግዴታችን መሆኑን ማወቅ ተፈጥሮአዊ ግዴታችን ነው፡፡ በትግራይ ጦርነት መከፈት አልነበረበትም ነበረ፡፡ ግን ሆነ፡፡ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ያደረጉት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ስለመሆናቸው ከመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ተሰምቷል፡፡ ለማናቸውም በጦርነቱ በይበልጥ የተጎዱት የጦርነቱ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆኑት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ እንደተከሰተ ይሰማል፡፡ ከ60000 በላይ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ከትግራይ ክልል ወደ ጎረቤት ሀገር ሱዳን ተሰደው እንደሄዱ ከአለም መገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰብዓዊ እርዳታ መስጠት አለባቸው፡፡ መንግስት የሚያደርገውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅም በፈቀደ መጠን ማገዝ አለብን፡፡ በሌላ በኩል፣ በወለጋ፣ ቤኒሻንጉል በሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በማንነታቸው በተለይም የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት  በማንም ይፈጸም፣ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቆም ኢትዮጵያውያን በህብረት መቆም አለብን፡፡ የሰብዓዊ መብት ከጎሳ ወይም ብሔር የሚቀድም ነው፡፡

በመንግስትም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር ቦታ ያላችሁ፣ከስህተታችሁ ተምራችሁ አንድነታችሁን ጠብቁ፣ ህብረታችሁን አጽኑ፡፡ እናተን (የመንግስት ባለስልጣናትና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ማለቴ ነው፡፡) በጣም አጥብቄ መማጸን እፈልጋለሁ፡፡

በውጭ ሀገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን  በኢትዮጵያ ምድር በህይወት የመኖር መብት እንዲከበር ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ አሰሙ፡፡ የጎሳን አጥር በማፍረስ ከሰብዓዊ መብት አከባበር አኳያ የህብረት ችቦ ለኩሱ፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለተፈጸመባቸው፣ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ የመጀመሪያው ሀላፊነት የእናንተ ነው፡፡ የውጭ ሀገር ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች በሁለተኛ ደረጃ ነው የሚመጡት፡፡ እስቲ እኛ ኢትዮጵያውን ተባብረን የተጎዱ ወገኖቻችንን አንታደግ፡፡ እራሳችንን መርዳት አለብን፡፡ አንድነታችንን ማጠንከር ይገባናል፡፡ አንድነታችን ከላላ በውጭ ሀገር ሳይቀር መብታችንን ማስከበር ሰማይ ይሆንብናል፡፡ የአለም መዘባበቻ ሆነንም እንቀራለን፡፡ ከአለም ሀገራት የተሰባሰቡ ዜጎች በተባበረችው አሜሪካ በነጻነት ሲኖሩ፣ እኛ በሀገራችን ውስጥ እንዴት በአንድነት መኖር ያቅተናል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግብጽና ሱዳን የተዘባበቱብን እንደው ዝም ብለው ተነስተው አይደለም፡፡ግብጾችና ሱዳኖች ያበጡብን ፣ በተለይ ሱዳኖች ጦራቸውን ከድንበራችን ያሰፈሩት ፣ በማሕበራዊው ሚዲያ ሲዝቱብን አድረው የዋሉት እኛን ለማስፈራራት የሚቃጣቸው ሁሉ የራሳችን ጠላቶች ራሳችን ሆነን ስላገኙን ነው። በመሃከላችን የባቢሎን ግንብ በመገንባታችን ነው፡፡ይህም ማለት በገዛ ራሳችን አርቆ አለማሰብ የተነሳ ሕብረታችን መላላቱን አይተው ተገንዝበው ነው፡፡

እኛ እርስ በራሳችን ባለመስማማታችን፣ ቁጭ ብለን አስበን አመዛዝን የሚበጀንን መሪ መምረጥ ባለመቻላችን በብልጣብልጥና አድርባይ ፖለቲከኞች ነን ባዮች እየተመራን ስንባላ፣ ስንጨቃጨቅ፣ ስንጋደል፣ ከመከባበር ይልቅ ስንደፋፈር፣ ከመፋቀር ይልቅ እርስበርሳችን  ስንሳደድ ሲያዩን የማያውቁት ድፍረት አናታቸው ላይ ስለወጣ በራችን ድረስ እየፎከሩ መጡ። 

ግብጽና ሱዳን ጀግና ጀግና የሚያጫውታቸው ራሳችን እየፈጠርነው ባለው የውስጥ ቅራኔ፣ ራሳችን በምንከተለው የዘር ፖለቲካ፣ ራሳችን በምንመትረው ከሐገር በፊት ብሄር በሚለው ድንቁርና እና በሃይማኖት ሽፋን ወገኖቻችን ላይ በምንፈጥረው አደጋና ክፋት እየተደፈርን መሆኑን ልናውቅ ይገባል። በነገራችን ላይ በዚህ ጉዳይ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ከህሊና ተጠያቂነት አናመልጥም፡፡ ችግራችን የጋራ ነው፡፡ የመንግስት ወይም የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ብቻ አይደለም፡፡ የአብዝሃው ኢትዮጵያዊ ችግር ነው፡፡ ቆም ብለን በሰከነ መንፈስ፣በሰለጠነ መንገድ፣ የህግ የበላይነት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተከበሩበት ሁኔታ ይህን መሰረታዊ ችግራችንን ልናስብበትና መፍትሔ ልናበጅለት ይገባል። ካልሆነ በራሳችን ጥፋት ራሳችን ላይ ጠላት መግዛታችንን እንቀጥላለን። ለማንኛውም የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም፡፡ ሰላም ለኢትዮጵያ፡፡ አቤቱ አምላኬ ሆይ የኢትዮጵያን ክፉዋን አታሳየን!

ሚያዚያ 4 ቀን 2013

Filed in: Amharic