>
5:33 pm - Tuesday December 6, 4557

የገዥው ፓርቲ የምርጫ ክንፍ (ጌጥዬ ያለው)

የገዥው ፓርቲ የምርጫ ክንፍ

(ጌጥዬ ያለው)

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊደረግ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ይቀረዋል። ትግራይ የጦርነት አውድማ በመሆኗ አትመርጥም፤ አትመረጥም። ምርጫ ይደረግ  ቢባል እንኳን ተወዳዳሪ ፓርቲ የለም። በአረጋዊ በርሄ የሚመራው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የጦርነቱን ክፍተት ተጠቅሞ በአብይ አሕመድ ሥልጣን ተሸልሟል። የፓርቲው ፕሬዚደንት አረጋዊ በርሄ  የታላቁ የአባይ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሓላፊ ተደርገው ሲሾሙ፤ ሌሎች አመራሮቹ ደግሞ ከዞን እስከ ክልል በትግራይ ተሹመዋል። በርግጥ ብዙዎቹ ውሎ አዳራቸው አዲስ አበባ ነው። በውጭ ሀገር ሆነው ያደርጉት ከነበረው የርቀት ትግል ወደ ርቀት መሪነት ተሸጋግረዋል።
በአብርሃ ደስታ የሚመራው አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነትም (አረና) በተመሳሳይ ከሥልጣን ቅርምቱ ተካፍሏል። የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲም (ዓዴፓ) ድርሻውን የተነፈገ አይመስለኝም። ወያኔ ከመቀሌ ወደ በረሃ ከተሸኘ በኋላ በትግራይ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ተቃዋሚዎች ሁሉ በአቋራጭ ሥልጣን ይዘዋል። ስለዚህ ምርጫ ይደረግ  ቢባልም  ገዥ እንጂ ተቃዋሚ የለም።
በነገራችን ላይ በበየነ ጴጦሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እና በብርሃኑ ነጋ የሚመራው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕም (ኢዜማ) በተመሳሳይ ሹመኛ ይበዛቸዋል። ምርጫ ቦርድ በተቃዋሚዎች ረድፍ ቢመዘግባቸውም ግብራቸው ግን የገዥነት ነው። ብርሃኑ ነጋ የወሰንና ማንነት ጉዳይ ኮሚሽን ሹመኛ ናቸው። በቀጥታ በጠቅላይ ሚንስትሩ ነው የተሾሙት። ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን እንደሚያስጠብቁ እጃቸውን አንስተው ምለዋል። የፖለቲካ አላማ በምርጫ የመንግሥት ሥልጣንን መያዝ ነው። እሳቸው በችሮታ ይዘዋል። ለምን ይታገላሉ፤  የተቃዋሚ ካርድ ይዘው ለምርጫ መቅረባቸው በሕዝብ ላይ እንደማሾፍ ይቆጠራል።
በየነ ጴጥሮስ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተደርገው በጠቅላይ ሚንስትሩ ተሹመዋል። እሳቸውም ሕገ መንግሥቱን እና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ተቀብለዋል።  የፓርቲያቸው የበታች አመራሮቻቸውም እንዲሁ ገዥው ፓርቲ በሚዘውረው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ እያገለገሉ ናቸው። እንዳውም አባሎቻቸው የመንግሥት አገልጋዮች በመሆናቸው እጩ ተወዳዳሪ ለማስመዝገብ መቸገራቸውን ለምርጫ ቦርድ አቤት ብለዋል። አቤቱታው ‘የመንግሥት አገልጋዮች ደሞዛችን ሳይቋረጥ የመንግሥትን ሥራ ለሦስት ወራት ያህል አቋርጠን የምርጫ ቅስቀሳ እናድርግ’ የሚል ነበር። ምርጫ ቦርድ ይህንን አቤቱታ ከሰማ በኋላ ይመስላል የመንግሥት ሠራተኞች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ደሞዛቸው እንደተከበረ ረፍት እንዲያደርጉ አዋጁን አሻሽሎ ፈቅዷል።
የሆነው ሆኖ እነኝህ ሹመኛ ፓርቲዎች ከተቃዋሚዎች መዝገብ የማይሰረዙበት ምክንያት ምን ይሆን? የገዥው ፓርቲ የምርጫ ክንፍ መሆናቸውንስ ሰፊ ሕዝብ ያውቃልን?
በኦሮሚያ ሕዝብ የሚያውቃቸው ተቃዋሚዎች ሁሉ ራሳቸውን ከምርጫ አግለዋል። ድምፅ ተከፋፍሎ የመንግሥት ስልጣን ከኦሮሞ እጅ እንዳይወጣ ውስጥ ለውስጥ የኦሮሞ ፓርቲዎች የጋራ ራእያቸውን ለማሳካት ተስማምተው  ያደረጉት ይመስላል። እንደዛም ኾኖየእርስ በርስ   ኩርፊያቸው  አገርሽቶ  አካባቢውን ወደ ጦርነት ቀጣና  ሊቀይረው እንደሚችልም  ተገማች ነው።
ደቡብ ኢትዮጵያ የየራሱን ሽርፍራፊ ‘ክልል’ ለመመስረት በሚያደርገው መላፋት ትንፋሽ አጥሮታል። ተቃዋሚዎች ደግሞ ይህንን እያራገቡለት ነው። በመሆኑም የደቡቤ በየመንደሩ ካሉት ተቃዋሚዎች እንጂ ከገዥው ፓርቲ ዝምድና የለውም። እነ ሞፈሪያት አዋሳ መሰብሰብ የቻሉት እንኳን ሲዳማን ‘ክልል’ ካደረጉ በኋላ ነው። ድርጅታዊ ጉባዔያቸውን የሚያደርጉት አዲስ አበባ እና ናዝሬት ነበር።
ገዥው ፓርቲ በአማራው በኩል ሲሶ ድምፅ እንደማያገኝ የሰሞኑ ሕዝባዊ እምቢተኝነት አረጋግጦለታል። ሰፊ ሕዝብ ቀርቶ ከዞን ጀምሮ ወደ ታች ያሉት የራሱ ካድሬዎች እንኳን ይመርጡታል ብሎ መገመት ያስቸግራል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በሰፊ የድምፅ ልዩነት እንደሚዘርረው ርግጠኛ ሆኗል። ለዚህም ነው ንቅናቄውን ለመግረፍ ጅራፍ እየፈተለ የሚገኘው።
የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ (ኢነፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራት ሕብረት (ኢዴሕ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ ብልፅግና ፓርቲ (ወራሪው)፣ ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሕብር)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ እናት ፓርቲ እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴሃን) የአማራ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት የሚባል የገዥው ፓርቲ ሰባራ ክንፍ አቋቁመዋል።
 ይህ ክንፍ የኦሮሙማን ወራሪ መንግሥት ብሎም የሽብር ቡድኑን ለማጠናከር ያለመ ይመስላል። መንግሥት ተብየው በተለይም ሰፊው የአማራ ሕዝብ ምርጫው ብቻ ሳይሆን ብቸኛ መዳኛው አድርጎ የተቀበለውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለማዳከም ሲል ነው ሰባራ ክንፍ ለማቋቋም ሚውተፈተፈው።
ከዚህም በተጨማሪ ገዥው ፓርቲ አብን ላይ ለምርጫ ቦርድ ይፋዊ ክስ አቅርቧል። በርግጥ ክሱ ለጊዜው ‘ዕጩ ልሰርዝ እችላለሁ’ በሚል ለገዥው ፓርቲ ያጋደለ ፍርድ በማስፈራሪያ ታልፏል።
ገዥው ፓርቲ አዲስ አበባ ላይ ስለሚኖረው አሸናፊነት የዳሰሳ ጥናት አድርጓል። ይፋ ባልተደረገው በዚህ ምስጢራዊ ጥናት አሸናፊነቱ 7 ከመቶ ብቻ መሆኑን አረጋግጧል። ይህ ማለት ብልፅግናን የሚመርጡት የፓርቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ብቻ ናቸው ማለት ነው። የራሱ የበታች መዋቅር እንኳን አይመርጠውም። በዚህ የደነበሩት የብልፅግና አለቃ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ሲሉ ‘ጠቅላይ ሚንስትሩ ታመመ። ሞተ’ የሚል የሀሰት ወሬ አስወሩ። የአዲስ አበባ ሕዝብ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ ‘ኢትዮጵያ አብይ ሳይመጣም ነበረች። አሁንም አብይ ባይኖር ትቀጥላለች’ አለ።
ቀጥሎ ሕዝቡን በሽብር ዜናዎች ማስፈራራት ጀመሩ። ‘ምንነቱ ያልታወቀ ቦምብ ፈንድቶ ሰዎችን ገደለ፣ ቢፈነዳ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት አቅም ያለው የተበላሸ መድሃኒት አለ፤ ማስወገጃ መሳሪያ የለንም’ የሚሉ ዜናዎች በረከቱ። ሕዝቡ በዚህ አልሸበር ሲላቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ‘እንደ ምርጫ 1997 በዘንድሮው ምርጫ ድንጋይ ውርወራ አይኖርም፤ ካለም የወታደር ኃይላችን አስተማማኝ ነው’ በማለት ሕዝቡ በፍርሃት ራሱን ከፖለቲካ እንዲያርቅ ጥረት እያደረጉ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የሌለ ችግር እያወሩ ቀጥሎ ከችግር አዳንኩህ በማለት ተወዳጅነትን ለማትረፍ ላይ ታች ይዳክራሉ።
 እነዚህ ሙከራዎች ስኬታማ ባለመሆናቸው ተመሳሳይ ሰባራ ክንፍ በቅርቡ በአዲስ አበባም ሊፈጠር ይችላል። ይህ ክንፍ ዋና ዓላማው በከተማዋ ሰፊ ተቀባይነት ያለውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ማዳከም ነው። የክንፉ ዋነኛ መስራቾች ገዥው ፓርቲና አጋር ድርጅቱ ኢዜማ ሲሆኑ ራሱን ባልደራስን አባል ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። የስለላ መዋቅራቸው ይህንን ለማሳካት ታላቅ ተልዕኮ ይወስዳል። በመሆኑም ባልደራስም ሆነ ሰፊው የአዲስ አበባ ሕዝብ ጉዳዩን ከወዲሁ በንስር ዓይን ሊመለከቱት ይገባል።
ከላይ ከተጠቀሱት 8ቱ ፓርቲዎች መካከል የአንዳዶቹ መሪዎች ባለፉት ስርዓቶች ሲታገሉ ቆይተው ዳግም ይሄኛውን ስርዓት ለመታገል ሀሞታቸው የፈሰሰባቸው ናቸው። እጅ ሰጥተዋል።
 ለምሳሌ ኢሕአፓዎች ጓዶቻቸውን ከድተው ሀገር ቤት የገቡ ናቸው። ተስፋ ያልቆረጡት ኢሕአፓዎች አሁንም በውጭ ሀገር ሆነው እየታገሉ ነው። ሀገር ቤት በገቡት መከዳታቸውንም የነገሩን ‘ፍኖተ ዴሞክራሲ’ በተሰኘው የሳተላይት ራዲዮ ጣቢያቸው ነው።
የእነዚህኞቹ ትልቁ ርዕያቸው የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ለመሆን ይመስላል። ይህ ባይሳካ እንኳን ኑሯቸውና መቃብራቸው በሀገራቸው እንዲሆን ነው ህልማቸው።
 ኢዜማዎች አንድም ትግል የሰለቻቸው ናቸው ሁለትም ከወራሪው ገዥ ፓርቲ ጋር የዓላማ ተመሳስሎት አላቸው። ሁለቱም የሰሜን ፖለቲካን ይጠላሉ። ሰሜንን ለመበቀል በጋራ ይሰራሉ። ማሕበራዊ ፍትሕ የሚሉትም የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ውቅር ከሰሜን ወደ ኦሮሞና ደቡብ ማለትም ከሴማዊ ወደ ኩሻዊ መቀየርን ነው። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ስለሚያጠፋ አብዛኞቹን ኩሻውያንንም ጨምሮ ያጠፋል። ለእነርሱም የሚበጅ አይደለም። የኢዜማው ግርማ ሰይፉ “ሰይጣን ቤት (እምዬ ምኒልክ ያሠሩት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት) ሰይጣን ቤት ከመባሉ በፊት ሜዳ ነበርና ወደ ሜዳነት ይመለሳል” እንዳለው ኢትዮጵያን ወደ ሜዳነት የመመለስ ውጥን ነው።
አንዳንዶቹ በፓርቲዎች መዝገብ ውስጥ ስማቸው ስለመኖሩም ሕዝብ የማያውቃቸው ናቸው። ድምፃቸው ከሚጠፋ ገደል ውስጥ ገብቶ መጮህን መርጠዋል።
የሕብር ኢትዮጵያና የእናት ፓርቲ እዚህ ውስጥ መግባት ግን ራስን ከማጥፋት ተለይቶ አይታይም። በአስቸኳይ ቢወጡ የሚጠቅማቸው ይመስለኛል።
Filed in: Amharic