>

ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባትም ሆነ  ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትም መመሥረት አልቻልንም... ምክንያቱም...?!? (ብላታ ታከለ)

ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባትም ሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትም መመሥረት አልቻልንም… ምክንያቱም…?!?
(ብላታ ታከለ)

የታወቁ የፖለቲካል ሳይንስ፣ የማኅበራዊ ሳይንስና የሕግ ምሁራን እንደሚስማሙበት፣ አንዲት አገር ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት ገንብታለች የሚባለው፣ ሦስት ምሰሶ የፖለቲካ ተቋማት ሲኖሯት እና እነዚህ ተቋማት ሚዛናቸውን ጠብቀው የሚንቀሳቀሱበት ሥርዓት ሲዘረጋ ብቻ ነው፡፡ እነሱም ዘመናዊ አገረ መንግሥት፣ ዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት ናቸው፡፡
ሀ) ዘመናዊ አገረ መንግሥት
ከሦስቱ ማዕከላዊ ተቋማት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አገረ መንግሥት (State) ነው፡፡ አገረ መንግሥት በአንድ ድንበሩ በታወቀ መልክዓምድራዊ ክልል ውስጥ ዓላማውን ለማስፈጸም ኀይል የሚጠቀምና ብቸኛው የቅቡለ ኀይል (legitimate use of force) ባለቤት የሆነ አካል ማለት ነው፡፡ የአገረ መንግሥት መኖር፣ በዚያ ድንበሩ በታወቀ መልክዓምድራዊ ክልል ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት እንዳይሰፍን፣ ደካሞች በኀይለኞች እንዲይደፈጠጡ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ እና ንብረታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡
እዚህ ላይ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ዘመናዊ ወይም ጠንካራ አገረ መንግሥት ግዙፍ ከሆነና የዜጎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ልቆጣጠር ከሚለው ወይም ለመቆጣጠር ከሚሞክረው አገረ መንግሥት (despotic state) በእጅጉ እንደሚለይ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ከሚጠቀመውና በብቸኝነት ከሚቆጣጠረው ኀይል በላይ አንድን አገረ መንግሥት ጠንካራ የሚያሰኘው በባለሥልጣናቱና በዜጎች መካከል ያለው ግንኙነት በአምቻና ጋብቻ፣ በጎሳ፣ በብሔረሰብ፣ በሃይማኖት ወይም በሌላ ማንኛውም ዓይነት ዝምድናና ግንኙነት (ኔትዎርክ) ያልተዋቀረ፣ ይልቁንም የባለሥልጣናትና የዜጎች ግንኙነት ሕግንና ሕግን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆኑ፣ እንዲሁም የግንኙነቱ ሁኔታ በሕግ በግልጽ የተደነገገና በሥራ ላይ የሚውል መሆኑ ነው፡፡
የአገረ መንግሥቱ ዘመናዊነትና ጠንካራነት ከሚለካባቸው ነጥቦች መካከል፣ የአገር መከላከያ ሠራዊቱና የጸጥታ ኀይል ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆኑ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ቁምነገር ነው፡፡ የእነዚህ መሠረታዊ ተቋማት ወገንተኛነት ከየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ጋር ሳይሆን ከአገርና ከሕዝብ ጋር ብቻ እንዲሆን ማረጋገጥ ትልቁና ተቀዳሚው የቤት ሥራ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ትልቁ የዘመናዊ አገረ መንግሥት መገለጫ፣ በዕውቀትና በክህልት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ቢሮክራሲ መኖሩ ነው፡፡ የአንዲት አገር የቢሮክራሲ አወቃቀር የዚያችን አገር ጥንካሬና የፖለቲካ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል ይባላል፡፡ ጠንካራ አገረ መንግሥታት ሁልጊዜም ቢሮክራሲያቸውን የሚያዋቅሩትና የሚገነቡት ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችልታን መሠረት አድርገው ነው፡፡ ቢሮክራሲው የየትኛውም የፖለቲካ ኀይል ወገንተኛ ያልሆነ እና ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችልታን ብቻ መሠረት አድርጎ የተገነባ እንደሆነ ሁሌጊዜም የፖለቲካ ኀይሎች በተቀያየሩ ቁጥር የሚበረግግ አይሆንም፡፡ በዚህ ሁኔታ የተገነባ ቢሮክራሲ ጠንካራ የአገርና የሕዝብ አገልጋይ ከመሆኑም በላይ ትልቅ የልማት ኀይል ይሆናል፡፡
የልማታዊ መንግሥት የዕድገት ፈለግ አብነት ተደርጋ የምትጠቀሰው ጃፓን፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከደረሰባት አሰቃቂ ሽንፈት አገግማ ዓለምን ያስደመመ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስመዝገብ የቻለችው በዕውቀትና በችልታ ሊይ የተመሠረተ ጠንካራ ቢሮክራሲ በመገንባቷ ነው፡፡ ይህ ጃፓን ከምዕራብ አውሮፓ አገሮች የቀሰመችውና ከአገሯ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አጣጥማ ተግባራዊ ያደረገችው የጠንካራ ቢሮክራሲ ግንባታ ተመክሮ ለብዙ የሩቅ ምሥራቅ ኢሲያ አገሮች አገልግሏል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል ዓለምን ያስደመመ ዕድገት ያስመዘገቡት የሲንጋፖር፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ማሌዥያና ሌሎች የኢሲያ አገሮች፣ ከጃፓን ባገኙት ተመክሮ ተነስተው ጠንካራ ቢሮክራሲ መገንባት ችለዋል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከነጃፓን ተመክሮ በእጅጉ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ያለው ቢሮክራሲ ዕውቀትንና ቴክኒካዊ ችሎታን መሠረት አድርጎ የተገነባ ሳይሆን በጎሳ፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ ወገንተኝነት የተዋቀረ፣ በሥልጣን ላይ ካለ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በእጅጉ የተሳሰረ፣ ታማኝነቱ ለባለጊዜ የፖለቲካ ኀይሎች የሆነና ለሙስና የተጋለጠ ደካማ ቢሮክራሲ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ ደካማ ቢሮክራሲ ተይዞ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ዘላቂ ልማት ማረጋገጥም ፈጽሞ የሚታሰብ አይሆንም፡፡
ለ) የሕግ የበላይነት
የሕግ የበላይነት በአጭሩ፣ በአንድ አገር ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ፣ ሁሉም ዜጎች ከሕግ በታች መሆናቸውንና ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን የሚያመለክት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ከሕግ በታች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሥርዓት መገንባት ዜጎች በኀይለኞች፣ በተለይ በመንግሥት እንዳይጠቁ ዋስትና ይሰጣል፡፡ ያለ ሕግ የበላይነት ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡ የቅቡለ ኀይል ብቸኛ ባለቤት የሆነው አገረ መንግሥት፣ ኀይሉ በሕግ የተገደበ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ የአገረ መንግሥቱ ኀይል በሕግ ካልተገደበ ትልቅ አደጋ ነው፤ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ምንጩም ይኸው ነው፡፡
የሕግ የበላይነት ከሌለ ጠንካሮች ደካሞችን የሚበዘብዙበት፣ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር የነገሠበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በዘህ ጥቂት ኀይለኞች፣ ወይም የፖለቲካ ሥልጣን ያላቸው ኀይሎች ከሕግ በላይ ሆነው እንደፈለጋቸው በሚፈነጩበት ሥርዓት ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ቢቻልም፣ ፍትሐዊነትዊና ዘላቂነት ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ግን ፈጽሞ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡
የሕግ የበላይነትና በሕግ መግዛት ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ጥቂት ሰዎች፣ ምናልባት ንጉሡና የንጉሡ ቤተሰቦች፣ ወይም ፕሬዚዲንቱና የፕሬዚዳንቱ ታማኞች ወይም ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች ሕዝቡን ሕግ እያወጡ የሚገዘበት፣ እነሱ ግን በሕግ የማይጠየቁበት ሥርዓት “በሕግ መግዛት” (rule by law) ይባላል፡፡ በአንባገነናዊ መንግሥታት ውስጥ የሕጉ ዓላማ ዜጎችን ከኀይለኞች፣ በተለይ ከመንግሥት መጠበቅ ሳይሆን፣ በሥልጣን ላይ ያለትን ኀይሎች ማገልገል ነው፡፡
በሕግ መግዛትና ፍትሕ ፈጽሞ ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ጥቂት ኀይለኛ ግለሰቦች ወይም ጥቂት ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮችና በእነሱ ዘሪያ የተኮለኮሉ ዜጎች ከሕግ በላይ ሆነው፣ ብዘሃኑን ዜጋ እንደፈለጉ በሚያሾሩበት ሁኔታ ፍትሕ ብሎ ነገር የለም፡፡
ሐ) ዲሞክራሲ
ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ የሆነበትና ዜጎች በነጻና ፍትሐዊ ምርጫ በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት የሚተዳደሩበት ሥርዓት ነው፡፡ አንድ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚባለው፡- (1) መንግሥታዊ ውሳኔዎችን የሚወስንኑና ፖሊሲዎችን የሚወጡ ባለሥልጣናት ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ የተመረጡ ሲሆኑ፤ (2) ባለሥልጣናት በነጻ፣ ፍትሐዊና ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ የተመረጡ ሲሆኑ፤ (3) ሁሉም ዕድሜው ለመምረጥ የሚያበቃው (እና በሕግ ያልተከለከለ) ዜጋ የመምረጥ መብቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤ (4) ሁለም ዕድሜው ለመመረጥ የሚያበቃው (እና በሕግ ያልተከለከለ) ዜጋ የመመረጥ መብቱ የተረጋገጠ ሲሆን፤ (5) ዜጎች ሐሳባቸውን ያለ ፍርሃትና ጣልቃ ገብነት የመግለጽ መብታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ (6) ዜጎች አማራጭ የመረጃ ምንጮችን የማግኘት መብታቸው ሲረጋገጥ፤ (7) ዜጎች ነጻ ማኅበራትን (የፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ) የማቋቋምና አባል የመሆን መብታቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡
እዚህ ላይ፣ በአንድ በኩል የምርጫው ነጻና ፍትሐዊነት ወሳኝ የመሆኑን ያህል፣ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ተከናውኖ የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች የሕዝቡን ጥቅም መወከላቸው እና የሕዝብን ጥቅም ወክለው ሳይገኙ ሲቀሩ ተጠያቂ መሆናቸውም ወሳኝ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሁሉ በላይ ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት በመሆኑ፣ የሕዝብን ጥቅም በአግባቡ የማያስተጋቡና የሕዝብ ጥቅም የማይታገሉ አመራሮች በመረጣቸው ሕዝብ ተጠያቂ የሚሆኑበት ወይም ሥልጣናቸውን የሚለቁበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሥርዓት ውስጥ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሕዝብ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ ከሠሩ በሥልጣን ላይ ይቆያሉ፣ ሕዝብ የማያገለግሉ ከሆነ ሥልጣናቸውን ያጣሉ፡፡ ግንኙነቱ ከሞላ ጎደል የአገልጋይና የተገልጋይ ግንኙነት ነው፡፡
እነዚህ ከላይ የቀረቡት ሦስት የፖለቲካ ተቋማት፣ ማለትም ዘመናዊ አገረ መንግሥት፣ የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ ናቸው በበለጸጉትና ባልበለጸጉት አገሮች መካከል የሚታዩት ልዩነቶች፡፡ የበለጸጉት አገሮች ከሞላ ጎደል እነዚህን ተቋማት የገነቡ ሲሆን፣ ያልበለጸጉት አገሮች በአንጻሩ በእነዚህ መመዘኛዎች ሲመዘኑ በብዙ መልኩ ወደኋላ የቀሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ዘመናዊ አገረ መንግሥት ቢኖራቸውም፣ የአገረ መንግሥቱ ኀይል በሕግ ስለማይገደብ ጥቂቶች  እንደፈለጋቸው የሚፈነጩበትና ተጠያቂነት የሌለበት የፖለቲካ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ዘመናዊና ጠንካራ አገረ መንግሥት ሳይገነቡ፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥት ስለሚንቀሳቀሱ ትንሽ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሲፈጠር በቀላሉ ሲፍረከረኩ ይታያል፡፡ ቁምነገሩ፣ ሦስቱን መሠረታዊ የፖለቲካ ተቋማት አመጣጥኖና ሚዛናቸውን ጠብቆ ከመገንባቱ ላይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በብዙ ምሁራን ዘንዴ እንደ አብነት የሚጠቀሰው የጃፓን፣ ቻይናና ሕንድ የፖለቲካ ሁኔታ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ጃፓን፣ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከደረሰባት አሰቃቂ ሽንፈት አገግማ ዓለምን ያስደመመ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ልማት ያስመዘገበች አገር ናት፡፡ በልማታዊ መንግሥትነቱ የሚታወቀው የጃፓን ዘመናዊ አገረ መንግሥት እጅግ የተዋጣለት ነጻና ዘመናዊ ቢሮክራሲ ገንብቷል፡፡ የጃፓን ቢሮክራሲ በፖለቲካ ወገንተኛነት፣ በዘመድ አዝማድ፣ በወንዜ ልጅ፣ በጎሳና ብሔረሰባዊ ማንነት መስፈርት ሳይሆን ዕውቀትንና ክህልትን መሠረት አድርጎ የተዋቀረ ዘመናዊ ቢሮክራሲ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቀያየሩ ቁጥር የሚቀያየር አይደለም፡፡ ጃፓን ከዘመናዊ አገረ መንግሥት በተጨማሪ፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የተገነባባት አገር በመሆኗ፣ የዜጎች ሁለንተናዊ ልማት በአስተማማኝ መሠረት ላይ የቆመ ነው፡፡
እንደ ጃፓን ሁለ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ዓለምን ያስደመመችው ቻይናም ብትሆን የዘመናዊ አገረ መንግሥት ባለቤት ናት፡፡ እንዲያውም ፕሮፌሰር ፉኩያማ በሰፊው እንደተነተነው፣ ቻይና ከየትኛውም አገር ቀድማ ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት የቻለች አገር ናት፡፡ የቻይና ቢሮክራሲ ከሺሕ ዘመናት በፊት ጀምሮ በአምቻና ገብቻ፣ በወንዜ ልጅነትና በጎሳ ትስስር ሳይሆን ዕውቀትንና ክህልትን መሠረት አድርጎ የተዋቀረ ዘመናዊ ቢሮክራሲ በመሆኑ የዚያች አገር ጥንካሬ መሠረት ከመሆኑም በላይ ትልቅ የልማት ኀይል የሆነ ቢሮክራሲም ነው፡፡ ሆኖም ቻይና የሕግ የበላይነት ያልሰፈነባትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያልገነባች አገር በመሆኗ፣ የቻይና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዘላቂነት ሁልጊዜም ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ወደ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ልማት እስካልተቀየረ ድረስ የቻይና ሁኔታ ሁልጊዜም ፈተና የተጋረጠበት ነው፡፡
የዓለማችን ትልቁ ዲሞክራሲ እየተባለች የምትጠራው ሕንድ በበኩሏ፣ ምንም እንኳን የሕግ የበላይነት የሰፈነባትና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥርዓትን የገነባች አገር ብትሆንም ዘመናዊና ጠንካራ አገረ መንግሥት (ቢሮክራሲ) መገንባት ባለመቻሏ እንደሌሎች የኢሲያ አገሮች ፈጣን የኢኮኖሚ ግስጋሴ ማድረግ አልቻለችም፡፡ የሕንድ ሕዝብ በበርካታ ቋንቋ ተናጋሪና የሃይማኖት ማኅበረሰቦች የተከፋፈለ ሕዝብ በመሆኑ የሕንድ አገረ መንግሥት እነዚህ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች በሚያደርጉት ፉክክርና ሽኩቻ የተወጠረና የሳሳ (fragile) አገረ መንግሥት ነው፡፡ ቢሮክራሲው በቋንቋና ሃይማኖት ወገንተኝነት (ቡድንተኝነት) የተበከለ እና ከፍተኛ የሆነ ንቅዘት ያለበት ቢሮክራሲ በመሆኑ የሕንድ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሌሎች የኢሲያ አገሮች ጋር ሲነጻጸር ወደኋላ የቀረ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ብዙሃኑ አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በበኩላቸው፣ ዘመናዊ አገረ መንግሥትም፣ የሕግ የበላይነትም፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትም መገንባት አልቻለም፡፡ በአገራችንና ከላይ በጠቀስኳቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚስተዋለው ትልቅ ችግር እነዚህን ሦስት መሠረታዊ የፖለቲካ ተቋማት አመጣጥኖና ሚዛናቸውን ጠብቆ ያለመገንባት ችግር ነው፡፡ የእነዚህ አገሮች መሠረታዊ ችግሮች የሚመነጩት ከዚህ ነባራዊ ዕውነታ መሆኑን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ይሆናል፡፡
በአገራችን መሠረታዊ በሆኑ ችግሮች ሊይ ሳናተኩር ነው ከ50 ዓመታት በላይ ጊዜያችን፣ ጉልበታችን፣ ሀብታችንና ሕይወታችን በከንቱ ስናባክን የኖርነው፡፡ ትናንትናም ሆነ ዛሬ የአገራችን መሠረታዊ ችግር የእነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ተቋማት አለመኖር ነው፡፡ ዘመናዊ አገረ መንግሥት መገንባት አልቻልንም፡፡ የሕግ የበላይነት የተከበረበት ሥርዓት መገንባት አልቻልንም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትም መመሥረት አልቻልንም፡፡ መሠረታዊ ችግሮቻችን እነዙህ ናቸው፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ኀይሎች ሁሉ ሊታገሉላቸው (ሊቆሙላቸው) የሚገባቸው አጀንዳዎችም እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
Filed in: Amharic