>

ጠቢቡ ሰለሞን ደሬሳ...!!! (ሄኖክ በላይነህ)

ጠቢቡ ሰለሞን ደሬሳ…!!!

ሄኖክ በላይነህ

•  “–የፈረንሳይን ስነ ጽሑፍ አነብም አጠናም ነበር፡፡ የደረሱበትን አላውቅም እንጂ በፈረንሳይኛ የጻፍኳቸው፤ታትመው የወጡም ግጥሞች ነበሩኝ፡፡ በኔ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረብኝ የፈረንሳይ ስነ ጽሑፍ ሳይሆን ፓሪስ መኖሬ ነው፡፡ ፓሪስ ውስጥ ትልልቅ ፀሐፊዎች፣ የሙዚቃ ሰዎችና ሠዓሊዎች ነበሩ፡፡ ፓሪስ ስደርስ 20 ዓመቴ ነበር፡፡ ነጻና ክፍት ከተማ ስለሆነና ልጅም ስለነበርኩ ቁልፉን የከተማው ከንቲባ እንደሰጠኝ ነው ያየሁት፡፡ እንዲያውም ላንድ ኢቫንጋርድ የፈረንሳይ ጋለሪ ማንም ሳይሾመኝ ስዕል አውቃለሁ ብዬ ገብቼ እንደ አማካሪ ሆኜ ያኔ የመረጥኳቸው ሰዓሊዎች አሁን በዓለም የታወቁ አሉ፡፡ ከጥቁር አሜሪካውያን ጋር በጣም በጣም ቅርብ ነበርኩኝ፡፡ በተለይ ከጃዝ ሙዚቀኞች ጋር። ከፈረንሳይ ፀሐፊዎች ጋርም ያለ እድሜዬና ያለ እውቀቴ እኩል ገብቼ ዋልኩኝ፡፡ በማንበብ ሳይሆን አብሮ በመዋል እንዳባቶች ሆነው አሳድገውኛል። ወደ ሙዚየም፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቴአትር ቤት፣ ኮንሰርት እሄድ ነበር፡፡ ገንዘብ ብዙ አልነበረኝም፤ በተለይ መጨረሻው ላይ ምንም አልነበረኝም፡፡ ከትሬንታ ላይ ሌሊት ሌሊት አትክልት እያወረድኩ ነበረ የምኖረው፡፡ ግን አንድ ሳንቲም ኪሴ ሳይኖር እንደ ሚሊየነር ልጅ ነው ፓሪስን የኖርኩባት። ከአዲስ አበባ ቀጥላ የትውልድ ከተማዬ የምትመስለኝ ፓሪስ ነች፡፡ በኋላ ለእስክንድር ሚዜ ሆኜ ወደ አሜሪካ ሄድኩኝ፡፡ ሁለተኛ ወደ አውሮፓ አልተመለስኩም፡፡
…………………….
•“–ፍቅር ለያዛት የአዲስ አበባ ወጣት ለገጠምኩት የፍቅር ግጥም አሥር ሣንቲም ተከፍሎኛል – የመጀመሪያ ግጥሜ እሱ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ጀነራል ዊንጌት ተማሪ የነበርኩኝ ጊዜ ከነ አሰፋ ገብረ ወልድ ጋር የተማሪ ቤቱን መጽሄት አብረን አዘጋጀን፡፡ ከዚያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስገባ ለጥቂት ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መጽሔት አዘጋጅ ነበርኩ። እና መጀመሪያ ጊዜ የጻፍኳቸው ግጥሞች እንዲሁ አለ አይደለም የቀልድ ግጥሞች በእንግሊዝኛ ነበሩ። የቀሩትን እዚሁ ትቻቸው ሄድኩኝ፡፡ አንድ ሶስት ጅምር ተውኔቶች፣ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስቦችና ግጥሞች እዚሁ ቀሩ፡፡ ደርግ መጣ እኔም አሜሪካ ቀረሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጽሑፍ አስተምር ስለነበር ለብዙ ጊዜ አልጽፍም ነበር፡፡ ለኔ ሁለቱ አንድ ላይ አልሄደም፤ አስቸገረ፡፡
………………………
•“–በአጭሩ ለኔ እንደሚሰማኝ በስድ ንባብ የተጻፈው እንዲገባህ፣ በግጥም የተጻፈው እንዲሰማህ ነው፡፡ ገባህ አልገባህ ሁለተኛ ነገር ይመስለኛል፡፡ ግጥምን የማነበው እንዲገባኝ ሳይሆን እንድመሰጥበት ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ‹‹ጉማላሎ›› [የተባለውን] ግጥም የጻፍኩት በዚያን ጊዜ ስለ አማርኛ እድገት ብዙ የሚያወሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ ቋንቋን ላሳድግ ብሎ መነሳት ዛፍ ቶሎ አላደገምና እስቲ ጠዋት ጠዋት እየተነሳሁ ቶሎ ቶሎ ልሳበው እንደማለት ነው፡፡ እንደሱ ስትስበው ስሩ ከአፈር ይላቀቅና ይደርቃል እንጂ አያድግም፡፡ ውሃ አጠጥተኸው ፀሐይ ካገኘ ያድጋል፤ ያንተ ግዴታ የለበትም፡፡ እና ይህንን ግጥም እንደ ቀልድና እንደ አመጽ ነበር የጻፍኩት፡፡ ግብ መጀመሪያ ላይ ወስኜ እንዲህ ይሁን ብዬ አልነበረም የምጽፈው፡፡ ውስጤ ያለውን እንደመጣ ነበር የምጽፈው፡፡
………………………………
•“–እውነቱን ለመናገር እኔ ገጣሚ ነኝ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ እንዲሁ በየቦታው እየተጻፈ የጠፋው ጠፍቶ የተገኘውን ባለቤቴ ሰብስባ ካስቀመጠቻቸው ውስጥ ‹‹ልጅነት›› ወጣች። ‹‹ልጅነት››  ታትማ ስትወጣ በመጠኑ ቁጣ ወረደባት። የኢትዮጵያን የግጥም አወራረድ አበላሸ፤ ከፈረንጅ ያመጣው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሱሪያሊስቶቹን ገልብጦ ነው ምናምን ይባል ነበር፡፡ እኔ በተለይ በወጣትነቴ የጻፍኳቸው ለምሳሌ የዚህን ኮት እጅጌ አውልቄ ብስበው ውስጡ ወደ ውጭ ይገለበጣል፡፡ ልክ እንዲዚያ ውስጤን ወደ ውጪ ለመገልበጥ ነው የሞከርኩት፡፡ ሽፍትነቱ መጀመሪያ ከልጅነት ነው፡፡ ልጅ ነበርኩኝ ወጣት ነበርኩኝ፡፡ ልብ ማበጥ አለ አይደለም እንደዚያ ነው፡፡ አንዳንድ ወጣት ፊት ለፊት ይበጠብጣል፤ አንዳንዱ ደግሞ ልዝብ ጥጋብ አለበት፡፡ እኔ ድሮ ልዝብ ጥጋብ ነበረብኝ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ‹‹በቃ እስኪ! አዲስ ነገር ደግሞ እንጨዋወት፤ ያንኑ አትደጋግምብኝ›› ከሚል ነገር የመጣ ይመስለኛል ግጥሞች የምጽፈው፡፡
……………………….
•“–ከስብሃት ገብረ እግዚአብሔርና ከተስፋዬ ገሠሠ ጋር አብሮ አደጎች ነበርን፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፡፡ ሲመሽ ሁላችንም ወደ አንድ ሰፈር ነበር የምንሄደው – ውቤ በረሃ፡፡ ስብሃት ያን ጊዜ የሚጽፈው አጫጭር ልቦለዶች ሲሆን መጀመሪያ አስደንቆኝ ያየሁት ኤክስ አን ፕሮቫንስ ሆኖ የጻፈውን ነው፡፡ እኔ ፓሪስ ነበርኩ፡፡ ላየው ስለፈለግኩ መንገድ ላይ መኪና እየለመንኩ ደረስኩ። ይቺ ‹‹ትኩሳት›› ተብላ የወጣችው ያኔ እየተጻፈች ነበር፤ አጀማመሯን አየሁት፡፡ ከዚያ ደግሞ እዚህ ኢትዮጵያ መጥቼ በእጅ የተጻፈውን አስነበበኝ፡፡ የኔንም አብረን እናነብ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ እህቴን አገባ – ሃና ይልማን፡፡ ከመንገድ ወዲህና ከመንገድ ወዲያ ስለምንኖር ሁልጊዜ ማታ ማታ እንገናኝ ነበር። ስብሃትና ተስፋዬ በወንድምነትም በጓደኝነትም እንደ ወንድሞቼ የሚቀርቡኝ ናቸው፡፡
………………………….
•“–ከነገብረክርስቶስ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ዮሐንስ አድማሱ ጋር ያገናኘን ስነ ጽሑፍ ነው፡፡ ከዚያ ተነስቶ ነው ጓደኞች የሆንነው። ከዮሐንስ አድማሱ ጋር ትንሽ እንዳንቀራረብ ያደረገን የስነ ጽሑፍ አሳብ መለያየት ሳይሆን ሐረር ሊያስተምር መሄዱ ነው፡፡ የምንገናኘው [አዲስ አበባ] ሲመጣ ነበር፡፡ የሚገርመኝ ነገር እኔ የሱን ግጥም ሳነብ በሃሳብ ተለያየን ብዬ አልነበረም የማስበው፡፡ ‹‹ይሄ የዮሐንስ አድማሱ ነው›› ነው የምለው፡፡ እሱም አንስቶት በዚህ ስንከራከር አላውቅም ሲያነብ ግን ‹‹ይሄ የሰሎሞን ነው›› ይላል። ሳናስብበት መለያየታችንን ተቀብለን የምንናበብ ይመስለኛል። ገብረክርስቶስ ደስታ ዊንጌት አብረን ስንማር እሱ ስዕል ነበር የሚሰራው፡፡ ጀርመን አገር ሲማርም ሄጄ ጎብኝቼዋለሁ፤ ከእስክንድር ጋር። መጀመሪያ ግጥም ያነበበልኝ እዚያ ነው፤ ኮሎኝ አጠገብ ይኖር ነበር፡፡ ምንም እንኳን ስዕሎቹ ቆንጆ ቢሆኑም የሚያስደንቁኝ የአማርኛ ግጥሞቹ ነበሩ፡፡
…………………………
• “–ዳኛቸው ወርቁ ከሠው አይቀርብም ነበር። ከኔ ጋር ግን ወዳጆች ነበርን፡፡ እንደ አጋጣሚ ‹‹አደፍርስ››ን አግኝቼ ሳነብ ‹‹ማነው የጻፈው?››፣ ብዬ ስፈልግ እሱ ደግሞ ‹‹ማነው ‹ልጅነት›ን የጻፈው?›› ብሎ ሲፈልግ ነው የተገናኘነው፡፡ [ስለ ልጅነት] የማስታውሰው የምስጋና ጽሑፍ ያገኘሁት ከዳኛቸው ወርቁ ብቻ ነው፡፡ በጣም በጣም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ ከማደንቃቸው ፀሐፊዎች ዳኛቸው አንዱ ነው፡፡ በሁሉም ሳይሆን በ‹‹አደፍርስ›› እና በ ‹‹Thirteenth Sun›› መጽሐፉ፡፡
ከአቶ መንግሥቱ ለማ ጋር ጓደኞች ነን፡፡ አንዳንዶቹን ግጥሞቹን በጣም አደንቃቸው ነበር። እሱ እኔ ላይ ተጽዕኖ ሳይኖረው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም መጻፍ ሳልጀምር ነው የሱን ግጥም መስማት የጀመርኩት፡፡ እንዲያውም ‹‹ልጅነት›› ውስጥ ‹‹ቱሉዝ ገምቤላ›› የምትል አንድ ግጥም አለች፡፡ እሷ ያለ ጥርጥር የመንግሥቱ ተጽዕኖ አለባት፡፡ መንግሥቱ ለማ ፌዘኛ ተሰጥኦ ነበረው። ሌላ እንደሱ ተሰጥኦ የነበረው አቶ ነጋሽ ገብረ ማርያም ነበር – በጣም ለማሳቅ ስጦታ ያለው።
እስክንድር ቦጎስያን በኢትዮጵያ ስነ ሥዕል ውስጥ የተለየ ቦታ ያለው ይመስለኛል፡፡ ‹የተለየ ቦታ ያለው› ስል ከሌሎቹ ሁሉ ይልቃል ለማለት ሳይሆን ጨክኖ መንገድ ከፍቷል ብዬ ነው የምገምተው። መንገድ ሲከፍት ደግሞ ፓሪስና ሎንዶን አስር ዓመት ከተማረ በኋላ ከፈረንጆቹ ተፈናቅሎ ወደ አፍሪካ ትራዲሽን – በተለይ ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ ቅርጾች ተፅዕኖ አሳደሩበት፡፡ ከዚያ ተላቆ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ . . . በቅርብ ካሉት ውስጥ በጣም የማደንቀው ሰዓሊ እሱ ነው፡፡
…………………
•“–በአንድ በኩል ስታስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ “እኔ የትግራይ ሰው ነኝ፤ እኔ አማራ ነኝ” ብሎ አፍ ሞልቶ መናገሩም አለማወቅ ይመስለኛል። በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? የኔን ጥሩ ኦሮሞነት እግዚአብሔርና የሴት አያቶቼ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ የሁሉንም እንዲሁ፡፡ ጦር ባለፈ ቁጥር በመዋለድ፣ በንግድ በመገናኘት፣ ተቸግሮ ከአገር ወጥቶ ሌላ ቦታ በመኖር ይቀላቀላል፡፡ እኔ እናቴ ወለጋ ነበር የሚኖሩት፡፡ ያደግሁት ጋሼ መሃሪ፣ አባባ ደስታ እያልኩኝ ከትግራይ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ፣ ከጉራጌ የመጡና እዚያ የሰፈሩትን እየጠራሁ ነው፡፡ ዘር በመቁጠር ደረጃ እኔ ምንም ችግር አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም በራስህ ለመኩራት መጀመሪያ በእናትህና በአባትህ መኩራት አለብህ። እሱን እንደ ምግብ በልተኸው ነው፣ ያንተ በራስ መተማመን የሚመጣው፡፡ ለምሳሌ እኔ ከትግራይ ሰው ጋር ተገናኝቼ፣ “የማጫውትህ የትግራይን ትልቅነት ነው” ቢለኝ “በል ቁጭ በልና እንጨዋወት” ነው የምለው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ያጫውተኝ!? ጎንደር የሄድኩት የዘመዶቼን ትልቅነት ለመስማት አይደለም፡፡ የነሱን ትልቅነት ለማየትና ለመስማት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ስንት ኦሮሞ ከብት በነዳበት አገር፣ “እኔ የጠራሁ አማራ ነኝ” ወይ “ንፁህ ትግሬ ነኝ” ቢለኝ አነጋገሩ ሁሉ ‹‹ለማያውቅሽ ታጠኝ›› ነው፡፡
…………………………..
• “– እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ቀድሜ የትምህርት እድል በማግኘቴ ወጣሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ውስጥ ታግቼ የምኖር መስሎኝ ነበር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከኢትዮጵያ ውጪ መኖር አልችልም የሚል አስተሳሰብ ስለነበረኝ ነው፡፡ በባዕድ አገር ይህን ያህል ዘመን እኖራለሁ የሚልም ግምት አልነበረኝም፡፡ በ1965 ዓ.ም ከሃገሬ በወጣሁ ጊዜ ዳግመኛ ወደ ውጪ አገር ለመሄድ እንደማልሻ ለእናቴ ገልጬላት ነበር፡፡ በዚያም መሰረት ከሁለት ዓመት በኋላ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ስነሳ ደርግ አረመኔያዊ ጭፍጨፋውን ጀመረ፡፡ እኔም ላለመመለስ ወሰንኩ፡፡ ከዚያማ ቀስ በቀስ የአሜሪካንን ኑሮ መለማመድ ጀመርኩ፡፡ ሃገሩን ወደድኩት፤ የአሜሪካን ተቋማትንም ማድነቅ ጀመርኩ፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ያገኘሁት እርዳታ፤ ሳልገፈተር፣ ሳልፈተሽ፣ መለዮ ለባሽ ሳይጮህብኝ ሰርቼ ለማደር እድል ማግኘቴ ነው፡፡ ሳስበው ከኢትዮጵያና ከአሜሪካ ውጪ መኖር የምችል አይመስለኝም፡፡ በአጭሩ አሜሪካ ዳግማዊ አገሬ ሆናለች ማለት እችላለሁ፡፡
…………………………….
•“–እና ለኔ መንፈሳዊነት የእምነት ነገር ሳይሆን ሳልሞት ምናልባት ምናልባት አንድ ሰሎሞን ሊፈጠር ይችላል ወይ? መንፈሳዊነት በመጨረሻው ከብትንትኑ የተጣጣፈ ሰው፣ አንድ ሆኖ ተሰብስቦ ይሞታል ወይ ነው? እናቴ ንጹህ ብራና ወለደች፤ ያልተጻፈበት፡፡ እዚያ ብራና ላይ ሕይወት እንዳጋጠመኝ ተጻፈበት፡፡ በየቦታው በመዞር እኔነቴ ተበታተነ፡፡ በዚህ በእስካሁኑ ሕይወቴ ቁልቁልም ሆነ ወደ ላይ የማየው፤ ከቀረብኩት ደግሞ የማላፈቅረው ሰው እንደሌለ ተረድቻለሁ፡፡ በተጨማሪም ሰውን ሳትዳኘው፣ ስለራሱ ሲያወራ ብታዳምጠው ስላንተ እያወራ ነው የሚመስልህ። ሲሆን የሰራሁትን አለዚያም ባልሰራውም ያሰብኩትን ነው የሚያወራኝ፡፡ እኔ ቢሮክራሲ የሚሉት ነገር ተስማምቶኝም አያውቅም – ምንም ዓይነት፡፡ ምናልባት ከሞትኩም በኋላ መንግሥተ ሠማይ የሚባል ቦታ እንዳለ፣እዚያም ቢሮክራሲ ካለ፣ እነ ጴጥሮስን– እነ ጳውሎስን— ማስፈቀድ ማስፈረም ካለ፣ እንደማይስማማኝ አውቃለሁ፡፡
…………………………
•“–ደስታውም ሆነ መከራው የሚያምረው በራስ አገር ሲሆን ነው፡፡ የጠነነ የአገር ፍቅር እንዳለኝ አይረሳ፡፡ የወለጋ ትዝታ፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ውበት፣ የአማርኛ ቋንቋ ቅላጼ፣ በተለይ የጎጃምና የሸዋ፣ የወላይታ ጭፈራ ወዘተ መንፈሴን ያድሱታል፡፡ ለመጻፍና ለመግጠም ስነሳ ደግሞ በልበ ሙሉነት መጻፍ የምቸለው ስለኢትዮጵያ ነው፡፡ በደንብ ስለማውቃት፡፡ ኢትዮጵያውያንን እወዳለሁ። ስለዚህም አብሬያቸው መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ስሞት አገሬ ልቀበር በሚል ስሜት አይደለም፡፡ የትም ብቀበር ቁብ የለኝም፡፡ ከመሞቴ በፊት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር እፈልጋለሁ፡፡
Filed in: Amharic