>
5:13 pm - Tuesday April 19, 3459

ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብን ስናስታውሳቸው...!!! ( ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ)

ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብን ስናስታውሳቸው…!!!

ጸሐፊ፡ አፈንዲ ሙተቂ

አንድን መጽሐፍ ከአንድ ጊዜ በላይ የማንበብ ልማድ የለኝም፡፡ አንዳንድ መጻሕፍትን ግን ሃያ፣ ሰላሣ እና አርባ ጊዜ ያህል እየደጋገምኩ አንብቤአቸዋለሁ፡፡ ከነዚያ መጻሕፍትም አንዱ “እስልምና እና የታላቁ ነቢይ የሙሐመድ ታሪክ” የሚል ርዕስ አለው፡፡ ደራሲው ደግሞ በፎቶግራፉ ላይ የምታዩዋቸው ሃጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ ናቸው፡፡
የሓጂ ሙሐመድ ሣኒን መጽሐፍ ያነበብኩት በታተመበት ዓመት ውስጥ (1980) ነው፡፡ መጽሐፉ ከአዕምሮ ሊጠፋ ያልቻለበት አንዱ ምክንያት በልጅነቴ ያነበብኩት መሆኑ ይመስለኛል፡፡ ከዚያ ወዲህም ለበርካታ ጊዜያት አንብቤዋለሁ፡፡
በሀገራችን ውስጥ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ድረስ እስልምናን በተመለከተ እንደ መጣቀሻ ሆነው ይወሰዱ የነበሩት ከአማርኛው የቅዱስ ቁርኣን በተጨማሪ ይህ የሓጂ ሣኒ መጽሐፍ እና በአቶ አብዱልዋሲዕ መንዲዳ የተጻፈው “መልዕክተ እስላም” ነበሩ (በዘመነ ኃይለ ሥላሤ “ማዕሙን ማሕዲ” የሚባሉ ሰው “ተውሂድና ፊቅህ” የተባለ መጽሐፍ አሳትመው ነበር፤ ሐጂ ሣኒም “የሰላት መማሪያ” የሚባል መጽሐፍ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ አሳትመዋል፤ ይሁንና እነዚህ ሁለት መጻሕፍት መኖራቸውን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው)፡፡
እንግዲህ ዛሬ በየሱቁና በየሼልፉ ለሞሉት እስላማዊ የአማርኛ መጻሕፍት ፋና ወጊ የሆኑት እነዚያ ሁለት መጻሕፍት ነበሩ፡፡ እኛንም በልጅነት ዕድሜአችን ኮትኩተው በማሳደግ የላቀ ሚና ነበራቸው፡፡
—–
ሐጂ ሙሐመድ ሣኒ ከዚያች መጽሐፍ በፊት (በ1963) ከሼኽ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ ጋር በመሆን ቅዱስ ቁርኣንን ወደ አማርኛ ተርጉመዋል፡፡ ያ የቁርኣን ትርጉም በዚህ ዘመን እየወጡ ካሉት ትርጉሞች በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ አንድ ሰው ከቁርኣን ፍቺ ከሚያገኘው መልዕክት በተጨማሪ የዐረብኛ ሰዋስውን ባህሪ ለማወቅ ካሻው ከዚያ የትርጉም ስራ ብዙ ቁም ነገሮችን ይማራል፡፡
—–
ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ሐቢብ የሚጠቀሱበት ሌላው ታሪክ የኢትዮጵያው መጅሊስ እንዲመሰረት ያደረጉት ተጋድሎ ነበር፡፡ በንጉሡ ዘመን መጅሊስ የሚባል ነገር አይታወቅም(“መጅሊስ” ይቅርና ዐረፋና ዒድ አልፈጥርም አይከበሩም ነበር)፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን መብትና ጥቅም በጋራ የሚያስከብር ተቋም አልነበረም፡፡
ሙስሊሞችን ወክሎ የሚናገር፣ የሃጂና ዑምራ ጉዞአቸውን የሚያቀላጥፍ፣ መስጂዶችንና አውቃፍን የሚገነባና የሚያስተዳድር ተቋም ያስፈልግ ነበር፡፡ ሓጂ ሙሐመድ ሣኒ ከሌሎች ዑለማ ጋር በመሆን ሙስሊሞች የራሳቸው ተቋም እንዲኖራቸው ለረጅም ጊዜ ይሟገቱ ነበር፡፡ የ1966ቱ አብዮት ሲፈነዳ ህዝበ ሙስሊሙ መብቱ እንዲከበርለት የሚጠይቀውን የሚያዚያ 20/1966 ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ አደረገ፡፡ ሃጂ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብም የመጅሊሱን ጉዳይ ይዘው ከመንግሥት ጋር መሟገታቸውን ቀጠሉ፡፡ በአላህ ፈቃድ ትግሉ ሰምሮ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በብሄራዊ ደረጃ ተቋቋመ፡፡ ሓጂ ሣኒም ይህንን ተቋም እስከ እለተ ሞታቸው ከመሩት በኋላ በ1981 አረፉ፡፡
አላህ መልካም ስራቸውን ሁሉ ይውደድላቸው፡፡
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ረመዳን 2013 (1442 Hijra)
Filed in: Amharic