>
5:13 pm - Monday April 19, 1204

ይድረስ ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን (አቢይ አባይነህ-ከአዲስ አበባ)

ይድረስ ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን

  አቢይ አባይነህ (ከአዲስ አበባ)

ፈገግታ ጥሩ ነው፡፡ አንዲት ቀልድ አዘል ቁም ነገር ትዝ አለችኝ፤ ከተነሳሁበት ጭብጥ ጋር ስለምትመሳሰል እርሷን ላስቀድም፡፡ አንድ ዓይነ ሥውር ከጥቂት ባልደረቦቹ ጋር ለሥራ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ለተወሰኑ ቀናት ወጥቶ ነበር፡፡ ክፍለ ሀገር ቆይተው ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ ሳለ የመስክ መኪናቸው በኮተቤ በኩል ያለውን የአዲስ አበባ ጫፍ ከመርገጡ ዐይነ ሥውሩ “አዲስ አበባ ገባን አይደል?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ጓደኞቹም በመገረም “እንዴት ልታውቅ ቻልክ?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሱለታል፡፡ እሱም “አሃ! የተቦረቦረው መንገድ እያነሳ ሲያፈርጥህ አንተስ እንደኔ ብትሆን ላይሰማህ ኖሯል?” ይላቸውና በአዲስ አበባ መንገዶች ጎርበጥባጣነተ ተሳስቀው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ፡፡ 

አዎ፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ከጥንት እስከአሁን ዕድለ ቢሶች ናቸው፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተን በዘመኑ አገላለጽ አንዳቸው ከአንዳቸው ተናብበው መሥራት ይጠበቅባቸው የነበሩ የቴሌ፣ መብራት ኃይል፣ ውኃ ልማትና የመንገድ ሥራ ተቋራጮች በየፊናቸው በሚያከናውኑት የመሬትና የመንገድ ቁፋሮ ብዙ ችግሮች እንደሚደርሱ እናውቃለን፡፡ ትንሽ ዕውቀትን በሚፈልግ ነገር ብዙ ሀብትና ንብረት ይወድማል፤ የተጓዦች መንገላታትም ያጋጥማል፡፡ ስለሆነም አዲስ አበባ ብዙ ባለቤቶች እንደሚቆራቆሱባት ብንረዳም ቀዳሚው ኅልውናዋ ነውና በሌለች ከተማ ከሚፋጁ ይልቅ ከተማዋ እንድትኖር ለማድረግ ቢጥሩ ይሻላል እላለሁ፡፡

ከዚህ በላይ ያለው ሃሳብ እንደመግቢያ ይወሰድልኝ፡፡ 

ትናንት ዐርብ ሚዚያ 29 ቀን 2013ዓ.ም ከጧቱ 1፡30 ሰዓት ተነስቼ ከመኖሪያ ቤቴ 14 ኪሎ ሜትሮችን ወደሚርቀው መሥሪያ ቤቴ ለመሄድ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ከቤቴ ብዙ እልፍ ሳልል የትራፊክ ጭንቅንቁ ከወትሮው በተለዬ የማያፈናፍን ሆኖ አገኘሁት፡፡ ምክንያቱን ብጠይቅም የሚነግረኝ አጣሁ፡፡ በካዛንቺስ፣ በአቧሬ፣ በአራት ኪሎ፣ በፒያሳና በጥቁር አንበሣ ት/ቤት እንደኤሊ በሚንቀራፈፍ የጉዞ ፍትሃት መሰል አካሄድ አራት ሰዓት ሊደፍን ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ መሥሪያ ቤቴ ደረስኩ፡፡ እንዲህ ተሁኖ ምን ሥራ ሊሠራ እንደሚችል ማንም ሊያስበው ይችላል፡፡ የአዲስ አበባን የመንገድ ጭንቅንቅና የትራንስፖርት ሁኔታ ለሚመለከት ሥራዎች በመንገድ ላይ እንጂ በቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ አይመስልም፡፡ ቀንም ሌትም መንገዶቹ በመኪናና በሰው እንደተጨናነቁ ናቸው፡፡ መቼ ነው ሥራ የሚሠራው? ማንስ ነው የሚሠራው? በዚህ ሁኔታ ዕድገትና ብልጽግና እንዴት ሊመጣ ይችላል?

የትናንቱን መጨናነቅ በተመለከተ ቆይቼ እንደሰማሁት የብልጽግና ፓርቲ ቅስቀሳ ያደረግ ስለነበር ነው አሉ፡፡ በበኩሌ የቅስቀሳው አስፈላጊነት አልታየኝም፡፡ ለምን ቢባል የተበላን ዕቁብ ለሁለተኛ ጊዜ ስጡኝ ማለት እንደማይቻል ሁሉ በልዩ ሥልት የምርጫውን ውጤት ለራስ ካደረጉ በኋላ እንዲህ ዓይነት ዐይን አውጣነትና በድሆች ጉልበት መቀለድ ነውር ነው፤ የበሉትን ቁማር አበላላቸውን ለመሸፈን በሚመስል መልኩ እንዲህ ሲጃጃሉና ሰውን ሲያጃጅሉ ሳይ እናደዳለሁ፡፡ ነገረ ሥራው ሁሉ የደንቆሮ ለቅሶ ይሉትን ዓይነት ነው፡፡ የሞኝ አራዳ ማለትም አራዳ ነኝ ባይ ጅል አይግጠምህ ወዳጄ፤ ብልጥ አራዳ እኮ ነቄ ካልክበት በቀላሉ ይፋታሃል፤ ጅሉ ግን ልክ እንደብልጽና “ተወኝ እባክህ” እያልከውም ሊያታልልህ በከንቱ ይዳክራል – በአራዳ ቋንቋ ስገልጸው፡፡ በቃ፣ “አሸንፈዋል” – ያሸነፉትን ጦርነት መግጠም ደግሞ በርግጥም ጅልነት ነው፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች በፍጥነት መቀነሻ ጉርብጥብጦች ከአገልግሎት ውጪ እየሆኑ ነው፡፡ በዚህ ነገር አንዳንድ ነጥቦችን መናገር እፈልጋለሁ፡፡ ችግሩ ተባብሶ ከቁጥጥር ውጪ ሣይሆን የሚመለከተው አካል ያስብበት ለማለት ያህል ነው፡፡

በመሠረቱ የፍጥነት መቀነሻ አስፈላጊ ነው፡፡ ግን አሠራሩ ላይ በቂ ጥናት ሊደረግበት ይገባል፡፡ ከውጪ ሀገራት መማርም ጥሩ ነው፡፡ በውጪ ያሉ የፍጥነት መቀነሻዎች ቢበዛ ከሦስት ሣንቲ ሜትር እንደማይበልጡ ይነገራል፤ የሚሠሩትም ከላስቲክ ሆኖ መኪናዎችንና ተሳፋሪዎችን እንዳይጎዱ ሆነው ነው፡፡ ሰውም እንደኛው ሀገር ሣይሆን የነቃና የሰለጠነ በመሆኑ እንዲያ የሚደረገው ፍጥነቱን እንዲቀንስ ለማስታወስ እንጂ መኪናን ለመገነጣጠልና የተሣፋሪን አናት ከመኪናው ጣርያ ለማላተም አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር የኛ የፍጥነት መቀነሻዎች መኪኖችን ከጥቅም ውጪ የሚያደርጉና በተወደደ የውጭ ምንዛሬ ሀገሪቱንም ዜጎቿንም ለኪሣራ የሚዳርጉ ናቸው፡፡ እንደሚስተዋለው በአሁኑ ወቅት የመኪና ዕቃ መለዋወጫ መደብር መክፈት እጅግ አዋጭ ቢዝነስ ሆኗል፡፡ ይህ የሚጠቁመው እነዚህ የፍጥነት መቀነሻዎች ሕዝቡን ላልተፈለገ ወጪ በመዳረግ ትልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሣራ እያስከተሉ መሆናቸውን ነው፡፡ ከኑሮ ውድነቱ በተጓዳኝ ይህ የመለዋወጫ ዕቃ ወጪና መኪኖች በአንደኛና በሁለተኛ ማርሽ እየተንቀራፈፉ ሲጓዙ በሚጨርሱት ብዙ ነዳጅ ሁላችንም ኪሣራ ላይ መውደቃችን መራር እውነት ነው፡፡  

በጣም የሚያሳዝነውና የሚገርመው ደግሞ እነዚህ የፍጥነት መቀነሻዎች ያሉንን አነስተኛ መንገዶች ባልተጠና መልኩ በሁሉም ሥፍራዎች በመጠፍጠፍ ጭንቅንቁን ማባባሳቸው ነው፡፡ እነሱ ባይኖሩም እንኳን ጭንቅንቁ ከፍተኛ ነው፡፡ መንገዶቹና የመኪናና የሰው ብዛት ሊጣጣም ባለመቻሉ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በዚያ ላይ በየ50 እና 60 ሜትሮች ይህ የፍጥነት መቀነሻ የተባለ ክምር አስፋልት ሲጨመርበት ችግሩ ጎልቶ ይወጣል፡፡ በዚህ ችግር ሳቢያም በሰዓቱ ሥራ መግባትን እንደቅንጦት እንቁጠረውና ነፍሰ ጡርንና ሌሎች ታማሚዎችን ይዘው የሚከንፉ አምቡላንሶችne፣ በደቂቃዎች ውስጥ ኆልቁ መሣፍርት የሌለው ሀብትና ንብረት የሚያወድሙ የእሳት ቃጠሎዎችን ለማጥፋት የሚበሩ የእሳት አደጋ መኪኖችን፣ ሀገርን ለማፍረስ ወይም አካባቢን ለማተራመስ የሚሞክር ወንበዴን ለማስቆምና ለመያዝ ከካምፖች የሚወረወሩ የፀጥታ ኃይሎችንና መሰል ፈጥኖ ደራሽ ተግባራትን ያደናቅፋሉ፡፡ አሁን ላይ አዲስ አበባ ልትፈነዳ ደርሳለች፡፡ አንዳንዴ ከመኪና ይልቅ በእግር መጓዝ ወደምትፈልግበት ሥፍራ በፍጥነት ያደርስሃል፡፡ በዚያ ላይ ትንሽ ግጭት ሲያጋጥም ት/ፖሊስ መጥቶ እስኪገላግል ተገትሮ መዋል ነው፡፡

ከዚሁ ከመንገድ ጋር በተያያዘ የውጭ እንግዶችም ሆኑ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚጓጓዙባቸው የተለዩ መንገዶች የሉም፡፡ በመሆኑም አቢይ በወጣ በገባ ቁጥር፣ የውጭ ሀገር ባለሥልጣን በመጣ በሄደ ቁጥር የሚታየው ጭንቅንቅ ቦሃ ላይ ቆረቆር ወይንም እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ከመንገዶች ጥበት፣ ከእግረኞችና ከመኪናዎች ብዛት ጎን ለጎን ከየት ሀገር እንደተኮረጀ ግራ የሚያጋባው ይሄ በየ10 ሜትር ልዩነት የሚቀመጠው አንዱ የባለአምስት መስመሮች ሌላው የችግኝ መደብ የመሰለ የአስፋልት ግግርና ክምር ደግሞ ትልቅ ራስ ምታት ነውና ይታሰብበት፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ወይም የአዲስ አበባ መንገዶችን ያገባኛል የሚል አካል ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ አሁን አሁን እንደምናየው ቁልቁለት ላይ ብቻ ሳይሆን አቀበት ላይም የፍጥነት መቀነሻ እየተሠራ ነው፡፡ የፍጥነት መቀነሻ ሥራ በስፋት የሚቀጥል እንጂ በቀላሉ የሚቆም አይመስልም፡፡ ይህም የሚነግረን በዚህ ፕሮጀክት ስም የሚሠራ ብዙ የሙስና ስንክሳር መኖሩን ነው፡፡ ለምሣሌ – ማን ያውቃል – አንድ የፍጥነት መቀነሻ በአምስትና በስድስት ሽህ ብር ቢሠራ የሚወራረደው ግን በመቶና በሁለት መቶ ሽዎች ሊሆን ይችላል – ይህ የሙስና ሰንሰለት ልክ እንደማንኛውም ሙስና ሁሉ ከታች እስከላይ የተሳሰረ መሆኑ አይካድም፡፡ ሀገር እንደሎሚ ተመጣ ያለቀችው በዚህ መንገድ ነውና ይህም ይታሰበብበት፡፡ ግን ማን ያስብበትና! ሁሉም በዚህ ቆሻሻ ቱቦ ውስጥ ላለማለፉ ምንም ማስረጃና ዋስትና የለም፡፡ የምንገኝበት ወቅት – የኖኅ የውኃ ጥፋት ዘመን፣ የሎጥ የድኝ እሳት ዝናብ ቃጠሎ ዘመን ነው፡፡ 

ለማንኛውም ይህ የመኪና መንገድ መጨናነቅ ችግር ከዚህም በከፋ ቀጥ አድርጎ ሳያቆመን የሚመለከተው ክፍል ያስብበትና ዘላቂ መፍትሔ ያብጅለት፡፡ የሚመለከታችሁ ወገኖች ወደኅሊናችሁ ተመለሱና ታሪክ ሥሩ፤ እኛም ይግረመን፡፡ “በዘመነ ሀሰትና ድንቁርና ለሀገር የሚያስቡ ቅኖች ተፈጠሩ” ብለን እንደሰት፡፡ ቅንቅኖች በበዙባት ምድራችን ቅኖች ናፍቀውናልና ሰው ሆናችሁ ብቅ በማለት ጥደቁብን፡፡

Filed in: Amharic