>

የብርቱካን ሚደቅሳ የሶማሌ ክልል <<ቁጥር መቀቀያ ቶፋ>> (ኤርሚያስ ለገስ)

የብርቱካን ሚደቅሳ የሶማሌ ክልል <<ቁጥር መቀቀያ ቶፋ>>

ኤርሚያስ ለገስ

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እንኳንም ይሄን አልሰሙ!!
               (ክፍል አንድ)

እነሆ ድራማው ቀጥሏል፣
ሁላችንም እንደምናስታውሰው የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ ከሦስት ሳምንት በላይ ሲሆነው በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ተከፍተው ድምጽ ሰጪዎችን ይመዘግባሉ ተብለው የተዘጋጁት 50 ሺህ ያህል የምርጫ ጣቢያዎች ነበሩ። አስገራሚ በሆነ መንገድ ከእነዚህ ውስጥ በዛን ጊዜ ምዝገባ እያካሄዱ ያሉት 25 ሺህ አካባቢ ነበሩ። ከ24 ሺህ በላይ በሚሆኑት ምርጫ ጣቢያዎች ግን ገና ሥራ አልጀመሩም ነበር።
ከሁሉም አስደንጋጩ ደግሞ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ውስጥ የመራጮች ምዝገባ አልተጀመረም ነበር። የመራጮች ምዝገባው እየተካሄደባቸው ባሉት የምርጫ ጣቢያዎችም ምዝገባው በተፈለገው መልኩ እየሄደ ነው ማለት እንደማይቻል ወይዘሪት ብርቱካን በተደናገጠ እና የተረበሸ ሁኔታ ማሳሰቧ የማይረሳ ነው።
እንግዲህ ይታያችሁ መጋቢት 16 የተጀመረው የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ 10 ቀናት ያህል በቀሩት ቀናት ውስጥ የሚጠበቀውን ያህል ሰዎች ባለመመዝገቡ በቀጣይ ምን አማራጮች እንደሚመጡ ሳይታለም የተፈታ ነበር። የምርጫ ምዝገባውን ማራዘም!
እንደተገመተው የመራጮች ምዝገባ ተራዘም። ኃላፊነቱም በግላጭ ተነጥቆ ዓብይ አህመድ እና የብልግና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተረከቡት። የክልል የብልፅግና ባለስልጣናት ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እየተገኙ የተቀቀለውን ቅጥር ማቅረብ ጀመሩ። እነ ሽመልስ አብዲሳ ከኪሳቸው መዝረጭ አድርገው በማውጣት ማቅረቡን ቀጠሉ። ምርጫ ቦርድም አይኑን በጨው ታጥቦ ከብልፅግና ባለስልጣናት የሚሰጠውን ቁጥር ወደ መቀበልና ማስተጋባት ተሸጋገረ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሶስተኛ ጊዜ ሕሊናዋን እንደሸጠች ያረጋገጥኩት የዛሬውን የመራጮች ምዝገባ ውጤት ካየሁ በኋላ ነው። እርግጡን እንነጋገር ከተባለ በተለይ በሶማሌ ክልል የተፈፀመው እጅግ አስገራሚ የቁጥር መቀቀል ስርዓት ከእድሜ ዘመኗ በኃላም በታሪኳም ጥቁር ጠባሳ ሆኖ የሚታወስ ነው። በተለይም ነብሳቸውን በገነት ያኑርልና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ይህን ቅሌት ቢሰሙ ኖሮ ምን ያህል ያዝኑ ነበር? ወይዘሪት ብርቱካን መጽሐፋቸውን አንብባ ቢሆን ኖሮ ላትሳሳት ትችል ይሆን ብለው ይፀፀቱ ነበር።
ለማንኛውም ወደ ሶማሌ ክልል የተፈፀመው ታሪክን የመድገም ቧልት ስንመለስ የሚከተሉትን ቁምነገሮች እናገኛለን፣
#አንደኛ:- ቀደም ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ 10 ቀናት እስኪቀረው በሶማሌ ክልል አንድም የምርጫ ክልል አልተከፈተም። ምርጫ ጣቢያዎቹ የተከፈቱት ምዝገባው በተራዘመበት ሁለት ሳምንት ውስጥ ነው። በዚህ ሁለት ሳምንት የሶማሌ ክልል ከሁሉም ሪከርድ በመስበር ወደ 4ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበዋል።
#ሁለተኛ፡- በሶማሌ ክልል የሚኖረው ሕዝብ ብዛት ወደ 6 ሚሊዮን ይገመታል። በኢትዮጵያ ስታትስቲካዊ መረጃ መሰረት ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህፃናት እና ታዳጊዎች ከ65 በመቶ በላይ ናቸው። ይህም በቁጥር ሲሰላ ወደ 4ሚሊዮን የሚጠጋው የሶማሌ ክልል ነዋሪ ምርጫ ለመምረጥ መመዝገብ የማይችሉ ህፃናትና ታዳጊዎች ናቸው። በዚህ ዳታ ከሄድንና መቶ ፐርሰንት መመዝገብ ያለበት የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ መመዝገብ ያለበት አሟጦ ተመዘገበ ቢባል እንኳን የሚመዘገው ቅጥር 2ሚሊዮን ጣራው ይሆናል። እውነታው ይሄ ሆኖ ሳለ የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሶማሌ ክልል የቁጥር መቀቀያ ቶፋ 3,844,129 እንደተመዘገበ ይፋ አድርጓል። እናም ክብርት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ከ1.8ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከየት መጣ ብለን እንጠይቃለን?
#ሶስተኛ፡- በምርጫ ክልል አደረጃጀት መሰረት አንድ ምርጫ ክልል እስከ 100ሺህ ሕዝብ የሚይዝ ነው። የሶማሌ ክልል የፓርላማ ወንበር ብዛት 23 እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ክልሉ ብዛት 23 ይሆናል። በመሆኑም በአሁን ሰዓት በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ በአማካይ በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል 170ሺህ ያህል ተመዝግቧል። አሰራሩ የሚያዘው ግን ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው 100ሺህ ብቻ ነው።
#አራተኛ፡- ከነባራዊው ተጨባጭ እውነት በመነሳት ካሉት የኢትዮጵያ ክልሎች ለምርጫም ሆነ ለመራጮች ምዝገባ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ተደርገው ከሚወሰዱት አንዱ የሶማሌ ክልል ነው። አብዛኛው ነዋሪ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የሚኖር አርብቶ አደር መሆን፤ የፀጥታ ችግር፣ ለምርጫ ስርዓት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን በዋናነት የሚነሳ ነው። እንዲህም ሆኖ የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሶማሌ ክልል የቁጥር መቀቀያ ቶፋ ከ6ሚሊዮን ሕዝብ ተጠጋግቶ 4ሚሊዮን ለምርጫ ተመዝግቧል። በተቃራኒው ከ20 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ይኖርበታል ተብሎ የሚገመተው የደቡብ ክልል ለመምረጥ የተመዘገበው 3ሚሊዮን ብቻ ነው። ከ30 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርበት የአማራ ክልል ለመምረጥ የተመዘገበው 5ሚሊዮን ብቻ ነው። ከዚህ በላይ ቧልት ይኖር ይሆን?
Filed in: Amharic