>
5:13 pm - Thursday April 18, 7535

ኢንሳ እና ከቴሌ ጋር የተዋሃዱ የአፈና ተግባሮቹ (አሰፋ ሀይሉ)

ኢንሳ እና ከቴሌ ጋር የተዋሃዱ የአፈና ተግባሮቹ

አሰፋ ሀይሉ

 

(የኢህአዴግ-ብልጽግና መንግሥታዊ የስለላ መረብ ሲጋለጥ!)
 
በምርምር እና ስርፀት የተደገፈ የኢንፎርሜሽን ሴኩዩሪቲ አቅም በመፍጠር በመንግስት እና ህዝብ ቁልፍ የኢንፎርሜሽን እና ኢንፎርሜሽን መረብ ሊፈጠር የሚችልን ተጋላጭነት መከላከል” በሚል ተልዕኮ እንደተቋቋመ የሚነገርለት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) (Information Network Security Agency (INSA) በማቋቋሚያ ሰነዱ ላይ ተለጥፎለት የምናገኘው ዋንኛ ዓላማው፡-
“አገሪቱ በኢንፎርሜሽን፣ በኢንፎርሜሽን መረብና ቴሌ ኮሙኒኬሽን አገልግሎቶችን በብቃት እንድትጠቀም  በማድረግ ሰላምንና ዴሞክራሲን እንዲሁም የልማት ስትራቴጂዎች የብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ላይ በማይ
ጥሉበት መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ማስቻል”
የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ካየነው ይህ ከውጪው የመረጃ ልውውጥ ሲካሄድ ሊከሰት የሚችል ተጋላጭነትንና የሳይበር ሽብርተኛነትን ለመከላከል እንደተፈጠረ የሚጠቀስለት ድርጅት፣ መስተጋብሩን (ኔትወርኩን) ከፖሊስ፣ ከመከላከያ፣ ከደኅንነት፣ ከመገናኛ የመሳሰሉ መ/ቤቶች ጋር የማቆራኘቱን ሥራ የመጀመሪያ ተግባሩ አድርጎ መገኘቱ አይደንቅም፡፡
ሆኖም ኢንሳ ይህንን በግለጥ የተነገረለትን ሽፋን ተጠቅሞ በተግባር ሲያከናውን የቆየው ሚና ራሱን ወደ ኢህአዴግ ሥልጣን ጠባቂ የሣይበር ሠራዊትነት የመቀየር ሚና ነበር፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውንም ሆነ ከአገር የሚወጣውን የመረጃ ፍሰት መቆጣጠርና ማፈን፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ የሚካሄደውን ማንኛውንም እንቅስቃሴ በመከታተልና በመተንተን የቅድሚያ ጥቃት እንዲካሄድ ለውሳኔ ማቅረብ፣ በጥቂቱ የሚጠቀስለትና በአዋጅ ያልተደነገገለት የኢንሳ “ሥልጣንና ተግባር” ነው፡፡
በብርጋዴር ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይና በሌ/ኮሎኔል አብዮት አህመድ አሊ የሚመራው፣ በኋላም ራሱን ችሎ እንዲደራጅ የተደረገው፣ እና በቀጥታ ተጠሪነቱ ለአቶ መለስ የነበረው የ“መንፈስ” ያህል የሚፈራው ኢንሳ፤ የቻይናው መንግሥታዊ የቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ 1.5 ቢሊየን ዶላር የብድር ገንዘብ ይዞ ኢትዮጵያ በመምጣት ከዘረጋው የቴሌኮም አገልግሎቶች ጋር በቀጥታ የተዛመደ ቴክኖሎጂን በቻይና ኮሙኒስት መንግስት አማካይነት በመታጠቁ፣ በዚሁ ቴክኖሎጂ አማካይት የአገሪቱን የመረጃ ፍሰት መቆጣጠር እንዲችል ተሞክሯል።
በሌላ አነጋገር ነጻ ሞባይል፣ ነጻ መደበኛ ስልክ፣ ነጻ ኢሜል (ጾዳቤ)፣ ነጻ የፌስ ቡክና ተመሳሳይ አገልግሎቶች በኢህአዴግ የስለላ መዋቅር ውስጥ እንዲወድቁ ተለፍቷል፤ እየተለፋም ነው። ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ለማካሄድ የሚያስቸግር ቢሆንም፣ በነጻነት የሚተላለፉ መልዕክቶች ሁሉ የኢህአዴግ የተማከለ የመረጃ ካዝና ውስጥ እንዲዘልቁ የአገር አንጡራ ኃብት ተከስክሷል፤ ያለማቋረጥ እየተከሰከሰም ነው።
ኢንሳ ምን ያህል እንደተሳካለት ወደፊት ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ ቃል የገቡት ወገኖችና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ከቴሌ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑ ወገኖች ከጥንቃቄ ጉድለትም ይሁን ባለማወቅ የኢህአዴግን የስለላ ኮሮጆ በየዋህነት እየሞሉ እንደሆነ አይሸሽጉም።
ወደዚህ የስለላ ኮሮጆ ውስጥ የሚገቡ መረጃዎች እንደ አስፈላጊነታቸው በኢንሳ አማካይነት በየዕለቱ ይተነተናሉ። አንዳዶቹም እንደ ሁኔታው እየተቀጠሉና እየተበጠሱ ለፍርድ ቤት የፈጠራ ወንጀል ማስደገፊያነትና ማስረጃነት ይውላሉ። በኢንሳ ከሚገኙት መምሪያዎች መካከል “የስጋት ትንተና (Threat Analysis)” የሚባለው በዚሁ በመቀጠልና በመበጠስ ሥራ የተካነው ክፍል ነው፡፡
ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከትዳር አጋር፣ ከከንፈር ወዳጅ፣ ከፍቅረኛ፣ ከሥራ ባልደረባ፣ ወዘተ. በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ምልልሶችን ይህ የኢንሳ የሥጋት ትንተና ክፍል ወደኋላ በመመለስ ያገጣጥምና ለይስሙላ ለተቋቋሙት ፍርድ ቤቶች በማስረጃነት ያቀርባል፤ በንጹሃንም ላይ ያስፈርድባቸዋል። [ማስታወሻ፡- እዚህ ላይ በጥናት አቅራቢዎቹ የተዘረዘሩትን የበርካታ በኢንሳ ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እውነተኛ ታሪክ ለቦታ እጥረትና የሰዎቹን ማንነት ለመጠበ ቅ ዘለናቸዋል፡፡]
ሞባይል ስልክን አስመልክቶ የሚመጋገበው የቴሌና የኢንሳ መረብ መረጃ የሚለቀመው በሶስት መንገዶች ነው፦
 አንደኛው፤ ባለሞባይሉ ጥሪውን ሲመልስ ወይም ጥሪ ልኮ ሲመለስለትና ሲያነጋግር፣
 ሁለተኛው፤ በቀጥታ በራሱ ቁጥር ተጠልፎ ክትትል የሚደረግበት ሲሆን፣ እና
 ሶስተኛው፤ (እና አስገራሚው) ባለሞባይል ስልኩን ዘግቶ የሚያደርጋቸው ማናቸውም ውይይቶች፣ ወጎች፣ የቤተሰብ ጨዋታዎች፣ የግል ምስጢሮች፣ ወዘተ. ኢንሳ ጆሮ እንዲገቡ መደረጉ ነው።
በሌላ አነጋገር አንድ የተጠለፈ ሰው የሞባይል ስልኩ ተዘግቶ ስለተቀመጠ (በሞባይል ስልክ ስለማያወራ) መረጃ ማስተላለፍ አያቆምም ማለት ነው። (በተለይ አዲሱ ቴሌ ላለፉት ዓመታት አገልግሎቱን ያሻሽላል ተብሎ ሲጠበቅ ሞባይል ስልክ ሲሸጥ መክረሙ ያለ ምክንያት እንዳልሆነ እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡)
መረጃውን ያስተላለፉት ክፍሎች “ማንም ሰው ስልኩን ሲያጠፋ ባትሪውን ከስልኩ ይለየው/ይንቀለው” ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ። አክለውም የተጠለፈ ወይም እንደሚጠለፉ የሚገምቱ ሰዎች ከዚህ መልዕክት በኋላ የሞባይል ስልካቸውን ለመረጃ መቀያየሪያ ለመጠቀም መሞከር የዋህነት እንደሆነ ይገልጻሉ። የኢንሳን አሳፋሪ ድርጊት ለማስረዳትም ስማቸውን ለጊዜው መጥቀስ ባልፈለግነው በአንድ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ላይ የተፈጸመውን እውነተኛ ገጠመኝ በመጥቀስ ያስረዳሉ።
እኚህ በተቃዋሚ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰብ፣ ስልካቸው ሙሉ በሙሉ በኢንሳ የመረጃው መረብ ውስጥ እንዲወድቅ ሲደረግ፣ እርሳቸው ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ እኚህ ግለሰብ እንደ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር በግል ስልካቸው የወደዱትን መልዕክት ሲያስተላልፉ ይቀዳሉ፤ ለማስረጃነትና ለስም ማጥፋትም ይመዘገባል። የፍቅርና የግል ማኅበራዊ ምስጢራቸው ሳይቀር ልቅም ተደርጎ ይቀዳል። በመጨረሻ ላይ የተቀረጹትን ሁሉ አገጣጥመው እንደ ሬዲዮ መግለጫ ካሰሟቸው በኋላ የቀረበላቸው ጥያቄ «አርፈው ይቀመጣሉ? ወይስ አይቀመጡም!» የሚል ዛቻ ነበር።
በተመሳሳይ በ1997 የቅንጅት አመራሮች የሚያደርጉት ስብሰባና የጉባዔ ክርክሮች ወቅት አንዳንዴ በሚዘጉ የሞባይል ስልኮች፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ብዕርና ሰዓት ወይም ወንበር ስር በሚለጠፉ የድምጽ መቅረጫዎች በመያዝ፣ የድምጽ መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩት በከፍተኛ ደረጃ ካሉ የደኅንነት ባለስልጣናትና ከአቶ መለስ ጋር ግንኙነት ያላቸው የፓርቲው አመራሮች የሚፈጽሙት ክህደት እንደነበር የመረጃ ምንጮቻችን በዝርዝር አስረድተዋል።
አንድ ባለስልጣን፣ አንድ አባወራ/እማወራ፣ ፍቅረኞች ወይም የንግድ ሰዎች የሞባይል ስልካቸውን አጥፍተው አንድ ቦታ ሆነው የግል ጨዋታቸውን ቢያደሩ ሰዎቹ በተጠርጣሪነት በኢንሳ ዝርዝር ውስጥ ምልክት የተደረገባቸው ከሆኑ፣ የስልኩ ባትሪ እስካልተነቀለ ድረስ፣ የሚያወሩትን ወሬ ወይም ቁምነገር ኢንሳ እንደ ሸገር ሬድዮ ሊሰማው ይችላል።
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ባለ ሞባይሎቹ አድራሻ ቀይረው እንኳን ቢቀመጡ የት እንዳሉ በሞባይላቸው አማካይነት በጂፒኤስ ይታወቃል። የትኛው ሰው ከማን ጋር ወይም ከእነ ማን ጋር በየትኛው ሥፍራ ወይም በስንት ሰዓት ላይ እንደተገናኘም በዚሁ የጂፒኤስ (ጂኦ-ስፓሺያል) ትራኪንግ ሲስተም ተጠቅመው በቀላሉ ማግኘትና፣ ግብረአበሮች ናችሁ ብለው ሰዎችን በማሰር ለማንገላታት መጠቀም ችለዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ዱካ የሚከታተሉት በዚሁ ቴክኖሎጂ አማካይነት ነው።::
ከሁሉም አይነት የግንኙነት መስመሮች ስልክ፣ ኢሜልና ፌስቡክ የኢንሳ ሰላዮች እንደፈለጉ የሚፈነጩባቸው መገናኛ ዘዴዎች ሲሆኑ፣ በፌስቡክ በኩል የሚተላለፉ መልዕክቶችን ለምሳሌ ወደ አገር ቤት እንዳይደርሱ በፈለጉት ሰው አካውንት ውስጥ ገብተው ያጠፉታል፤ ይሰርዙታል።
አሜሪካ በምስራቅ አፍሪቃ አሸባሪነትን ለመቋቋም በሚል ህወሃትን ያስታጠቀችው ዘመናዊ የስለላ መሳሪያ ንጹሃን እየታደኑበት እንደሆነ የሚገልጸው መረጃ ቃላቶች፣ ሃረጎችና ስሞች ኮድ ተደርገው በመረጃው ቋት (ዳታ ቤዝ) ውስጥ ይታሰራሉ። ከታሰሩት ቃላቶች ውስጥ አንዷ በድንገት ከአንድ ሰው አንደበት ስትወጣ ኔትወርኩ በቀጥታ “ኮዱ ተጠርቷል” በማለት ለኢንሳ (ስለሆነም ለብሔራዊ ደህንነት መ/ቤቱ) ያሳብቃል።
በዚያ መረጃ መሰረት ያቺን ቃል፣ ሃረግ ወይም ስም የተጠቀሙ ሰዎች ወዲያውኑ የክትትል ዝርዝር ሊስት ውስጥ ይገባሉ። ከዚያም ይሰለላሉ፤ ይበረበራሉ። የመረጃው ምንጮች ለዚህ ጥናት አቅራቢዎች ስለዚሁ ተሞክሯቸው ሲያስረዱ፣ በተለይ የሀገራችን ፖለቲከኞች በተመሳሳይ ኮድና በሚታወቀው የመለያ ስማቸው እየተጠራሩ ሲነጋገሩ፣ አንዳንዴ የኢንሳ የደኅንነት ሠራተኞቹ ራሳቸው “ሰዎቹ ምን ነካቸው?” እስከማለት የሚገረሙበት ወቅት እንደነበር ተናግረዋል።
ስለ ኢንሳ ለጥናት አቅራቢዎቹ ከደረሱ መልእክቶች መካከል፣ በመያዶች (መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች)፣ በኤምባሲዎች፣ በዲፕሎማቶችና ታዋቂ ተቋማት ላይ የሚካሄደውን የኢንሳ ስለላ ያካትታል። መረጃው በስም ጠቅሶ እንዳብራራው፣ የክርስቲያን ዕርዳታና ልማት ማኅበር (ሲአርዲኤ) – Christian Relief and Development Association (CRDA)፣ አክሽን ኤይድ በኢትዮጵያ (ActionAid Ethiopia)፣ ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል፣ የሉተራን ዓለምአቀፍ ፌዴሬሽን (LWF)፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የተለያዩ ርዳታ ሰጪ ተቋማትና ሃላፊዎቻቸው፣ እንዲሁም ዲፕሎማቶች የሚጠቀሙባቸው የመገናኛ ዘዴዎች በኢንሳ በመደበኛነት ከሚጠለፉት ወይም በኢንሳ የስለላ መረብ ውስጥ ገብተው 24 ሰዓታት ከሚሰለሉት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
የመገናኛ ዘዴዎቻቸውን በመጠቀም ከሚያደርጉት የስለላ ተግባር በተጨማሪ፣ ኢንሳ ያሰለጠናቸው የተለያዩ ኤክስፐርቶችና ባለሙያዎች በሚጠረጠሩ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው እንዲሠሩ አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል። የደኅንነት መዋቅሩ በሚፈልገው ድርጅት ውስጥ ሰራተኛ በማስመሰል ሰላይ አስርጎ ማስገባት፣ ካልቻለ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎችን በመንግሥት አማካይነት በማስቀመጥ ከድርጅቱ ጋር ድርድር እንዲካሄድ ያደርጋል። [NB. አሁንም በጥናት አቅራቢዎቹ በእውነተኛ አስረጅነት የቀረቡ የበርካታ ድርጅቶች ተሞክሮዎችና የብሔራዊ ደህንነት ሰዎች ስም መውጣቱን እገልጻለሁ፡፡]
ከስለላው በተጨማሪ በአስገዳጅ ሁኔታ የሚከናወኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ። በመረጃው ትንታኔ መሰረት በሰብዓዊነት ስራ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ ኃላፊዎች፣ የዕርዳታ ድርጅቶችና ሲቪክ ተቋማት ከስለላ መረብ ነጻ የሆኑበት ጊዜ የለም። መጨረሻ ላይ በህግ መስራት እንዳይችሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የህግ አማካሪና ተጨማሪ የህግ ባለሙያዎች የተዘጋጀው ህግ እንዲጸድቅ የተደረገው ኢንሳ ባቀረበው የስለላ ሪፖርት መሰረት መሆኑን ይህ ጥናት በዝርዝር መረጃዎች አስደግፎ ያስረዳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ከሚደገፉት እጅግ ጥቂት ኤምባሲዎች በስተቀር አብዛኞቹ ኤምባሲዎች፣ ታዋቂ ተቋማትና በሰብዓዊ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ዲፕሎማቶችና የመሳሰሉት በኢንሳ የደኅንነት መረብ ሥር ተይዘው ሲሰለሉና ሲበረበሩ የሚውሉ መሆናቸውን ይህ ጥናት በማያሻማ መልክ ያስረዳል።
በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙ ታላላቅ ሆቴሎች ውስጥ የሚከናወኑ ስብሰባዎችና በግል ደረጃ የሚካሄዱ ውይይቶች ሁሉ ተለቅመው በኢንሳ የመረጃ መረብ ውስጥ እንዲካተቱ እንደሚደረግ ለአገዛዙ ቅርበት ያላቸውን ሆቴሎች በመዘርዘር መረጃው ይተነትናል።
በተለይ በአንድ (ስሙን ለጊዜው መጥቀስ ባልፈለግነው) በአዲስ አበባ በሚገኝ ትልቅ ሆቴል ውስጥ፣ ግለሰቦችንና ታዋቂ ሰዎችን በመከታተል መረጃ የመሰብሰብ፣ በግል (በምስጢር) የሚደረጉ መዝናኛዎች ሳይቀሩ እየተቀረጹ ለፖለቲካ ስራ ማስፈራሪያነት እንደሚውሉ የሚያስረዳው መረጃው፣ በሁለት ተጨማሪ ሆቴሎች ውስጥ ደግሞ በስውር የድምጽ፣ የስዕልና የቪዲዮ መረጃ የሚሰበስቡትን የውጪ አገር ዜጎች ማንነት፣ ክፍያ ከሚያከናውኑላቸው መንግሥታዊ ክፍሎችና የመኖሪያ አድራሻቸው ጋር ይፋ አድርጓል።
እነዚህ ለኢንሳ የሚሠሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ የቅንጅት ፖለቲካ በተፋፋመበት ወቅት ከአረብ አገራት ተቀጥረው እንደመጡና አሁን ድረስ የመረጃ ሰራተኛነታቸውን እያከናወኑ እንደሆነ ያጋልጣል የጥናት አቅራቢዎቹ መረጃ። እነዚህን የስለላ ተግባራት የሚያከናውኑት ክፍሎችና ግለሰቦች የሚታወቁት ከኢህአዴግ ውስጥ እጅግ ውስን በሆኑ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ብቻ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የሚገኙ ታላላቅ ሆቴሎች የተቋቋሙት ለኢህአዴግ ቅርበት ባላቸው ግለሰቦች ወይም የኢህአዴግን ዓላማ በግልጽ በሚያራምዱ ሰዎች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆቴሎቹ እንደ መዝናኛ ቦታ ለንግድ የተከፈቱ ቢሆንም ከበስተጀርባው ግን የሚያካሂዱት ከፍተኛ የሆነ የስለላ ሥራ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሰለጠነው ዓለም እንደዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር የሰውን ነጻነትና ክብርን የሚጋፋ፤ የሚያስወነጅልና የሚያስፈርድ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ይህንን ለማድረግ የማይታሰብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ከአገዛዙ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ በሌላቸው ግለሰቦች የተከፈቱ ሆቴሎችም ቢሆኑ፣ አንዳንድ «ተጠርጣሪ» ናቸው የተባሉ ሰዎች የሚያዘወትሩባቸው ከሆኑ፣ ይህንን መሰሉን የስለላ ተግባር ሆቴሎቹ እንዲፈጽሙ በኢህአዴግ የደህንነት ሰዎች መገደዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ዓላማው የሰዎችን እጅግ ምስጢራዊና የግል የሆኑ ጉዳዮችን በማስረጃ በመያዝ ከትግልና ከፖለቲካ ማራቅ ነው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ሰው በገሃድ ወጥቶ “ጥፋት ሰርቻለሁ፤ ይህ ግን ከቆምኩለት የትግል ዓላማ ሊያስወጣኝ አይገባም” በማለት ሕዝብን በግልጽ ይቅርታ መጠየቅ ባልተለመደበት ኅብረተሰብ ውስጥ፣ ይህ ዓይነቱ በኢንሳ አማካይነት ሌት-ተቀን የሚፈጸም የኢህአዴግ መንግሥት እኩይ ተግባር፣ ዋና ዓላማው በርካታዎችን ከትግል ሜዳ ፎጣ ወርውረው እንዲወጡ፣ ወይም ከአገር እንዲሰደዱ ለማድረግ ነው፡፡ አድርጓቸዋልም፡፡ እያደረጋቸውም ይገኛል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያካሂዱት ስብሰባ ምሥጢር ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለም። አብዛኛውን ጊዜ “ምሥጢራችን ይፋ ሆነ” በሚል ፓርቲዎች እርስ በርስ ሲካሰሱና ሲወነጃጀሉ ይሰማል። ከዚህም በላይ የሚከፋፈሉበትና ደጋፊዎቻቸው ሳይቀር ተስፋ የሚቆርጡበት ሁኔታ ይስተዋላል። አንዳንድ ዓላማ-የለሾችና ጥቅመኛ “ምስለኔ” ፖለቲከኞች ወደ ፖለቲካ ድርጅቶች ሰርገው ቢገቡም፣ የፓርቲዎች ምሥጢር የሚባክንበት ሌላው መንገድ በስለላ በሚገኝ መረጃ እንደሆነ ከኢንሳ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ለጥናት ክፍሉ ከደረሱ መረጃዎች አንዱን አስደንጋጭ የኢንሳ ተግባር ብቻ ጠቅሰን እንሰናበት፡፡ በህገ መንግሥቱ መሰረት ፈቃድ ጠይቀው በስብሰባ ቦታ ወይም በራሳቸው ቢሮ ተቃዋሚዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ዲፕሎማቶች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የቤተክርስቲያን አመራሮችና ሌሎች ተፈላጊዎች ስብሰባ ይቀመጣሉ፡፡ ሲቀመጡ ከርቀት (ከ200 እስከ 300 ሜትር በሚሆን ርቀት ላይ) የኢንሳ የስለላ ሰዎች መኪና ውስጥ በመሆን ውይይቱን ይቀርጹታል። ይህንኑ ለማከናወን ከርቀት የሚያዳምጥ መሣሪያ (ሪሞት ሊስኒንግ)፣ ከርቀት የሚቀርጽ መሣሪያ (ሪሞት ሪኮርድ ዲቫይስ)፣ እና ከርቀት የመስሚያና ማስተጋቢያ መሣሪያ (ሪሞት ስፒከር)፣ ወዘተ. ይጠቀማሉ።
በዚህ ዓይነት መልኩ ስለላ በማካሄድ የተቀረጹ ድምጾች እየተቆረጡ ከተቀጠሉ በኋላ ለማስፈራሪያነት፣ ለክስ ማስደገፊያነት፣ ለተጨማሪና ለህጋዊ መረጃ መቀበያነት፣ አፋኝ ህግ ቀድሞ ለማውጣት፣ በእጃቸው በያዙት መገናኛዎች እንዲሁም በተቀላቢ ጋዜጦችና በኤፍኤም ሬዲዮኖች ለቅስቀሳ ለማዋል ይጠቀሙበታል።
ባለስልጣኖች እንዴት እንደሚሰለሉ፣ ባለሃብት የሚባሉ የህወሃት/ኢህአዴግ አገልጋዮች እንዴት የመረጃ መዋቅሩን እንደሚያግዙ፣ ምን ያህል የመስመር ሰላዮች አዲስ አበባን እንደሚሰልሉ፣ በመከላከያ የሎጂስቲክ መምሪያ የሚካሄደውን ሙስና ስለምትመራዋ እንስት፣ “ጎንደሬ ነን” ስለሚሉት ሰላዮች፣ የደህንነት አባላትና ባለስልጣናት ሆን ተብሎ ሙስና ውስጥ እንዲዘፈቁ ስለሚደረግበት ስልትና የታላላቅ ሆቴሎችና የኢንሳ የስለላ ቴክኖሎጂ ትስስርን በተከታታይ ጽሁፍ እናስነብባለን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ሕዝባችንን አብዝቶ ይጠብቅ፡፡
ለዛሬ አበቃን፡፡ 
Photos:⇑
ፎቶ 1. ከክንፈ ገብረመድህንና ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ በመቀጠል የብሔራዊ መረጃና ደህንነቱ መ/ቤት ዋና ሀላፊ ጌታቸው አሰፋ፤
ፎቶ2. ለትራፊክ ደኅንነት በሚል ሽፋን በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች ከተገጠሙትና ኢንሳ በቀጥታ ከሚቆጣጠራቸው ካሜራዎች አንዱ፤
ፎቶ 3. የኢንሳ መሥራችና ምክትል ሀላፊ፣ በኋላም በሚኒስትር ማዕረግ የኢንሳ ዋና ተጠሪ ሌ/ኮ አብዮት አህመድ፤
ፎቶ 4. ኢንሳ ከሚጠቀምባቸው የስለላ ቁሳቁሶች አንዱ፣ ማይክሮ ቪዲዮ ሬከርደር የተገጠመለት ብዕር።
Filed in: Amharic