>

"ጽና....!!!"  (  ኃይሉ አርአያ (ዶ/ር))

“ጽና….!!!”

        ኃይሉ አርአያ (ዶ/ር) 

*….. እዚህ ላይ የጊዮርጊስ ገድልን ያመጣሁት ለምንድን ነው? ኢትዮጵያ ያለችበት የጭንቅ ሁኔታ ጊዮርጊስ ካለፈበት የአካልና የአዕምሮ ስቃይ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነና ይህ ቅዱስ ፍጡር ስቃዩን ችሎ ፈተናውን እንዳለፈ ሁሉ፤ ኢትዮጵያም መከራዋን ተቋቁማ ፈተናዋን ለማለፍ የሚያስችላት የብሔራዊ አንድነት ጽናት እንዲኖራት ጸሎቴን ለመግለጽ ነው።
ከሃምሳ ዐመት በፊት፣ በግዕዝ በተጻፈ አንድ የብራና መጽሐፍ ውስጥ ይመስለኛል፣ ያየሁት ሥዕል እስካሁን በአዕምሮዬ በጉልህ ይታየኛል። መጽሐፉን ግን የት እንዳየሁት ማስታወስ አልቻልኩም። ሥዕሉ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስት ትልልቅ፣ ስለታምና ሹል ጫፎች ባሉት ጦር ከመቀመጫው ጀምሮ ወደላይ ተወግቶ ሲሰቃይ ያሳያል። አጠገቡ  አንድ መልአክ “ጽና ጊዮርጊስ!” ሲለው ይታያል።
የጊዮርጊስ ስቃይ ታሪክ በክርስትናው ብቻ ሳይሆን፤ በስልምናው ዓለምም በስፋት የታወቀ ነው። የስቃዩ ዐይነትና ክብደት ከአገር፣ አገር፤ በአንድ አገርም ውስጥም ከቦታ፣ ቦታ ይለያያል። በአገራችንም የጊዮርጊስ የክርስትና ዕምነት ገድል፣ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክስቲያን ከፍተኛ ቦታ ይዟል።
ለዚህ ጽሑፌ በመነሻነት ይረዳኛል ብዬ የወሰድኩት በሊቀ-ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ፣ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ባልደረባ፣ “በገድል የተፈተነ ሰማዕት” የሚል ጽሑፍ ነው። ጽሑፉ ጊዮርጊስ በጊዜው “ልዳ” በሚባል አገር እንደተወለደ ይገልጻል። ለዚህ ነው፣ በግዕዝ መጻሕፍት “ጊዮርጊስ ዘልዳ” እየተባለ የሚጠቀሰው። በዚያን ጊዜ “ልዳ” ይባል የነበረው አገር፣ በአሁኑ ቤይሩት የሚባለው አካባቢ ነው። የቀድሞው አገር  የጣኦት አምልኮ የነገሠበት ቢሆንም፤ በሌላ በኩል የክርስትና ዕምነት እየተጠናከረ የመጣበት ጊዜም ነበር። ጊዮርጊስ የተወለደው ክርስትናን ከተቀበለ መስፍን ቤተሰብ ነው። የአገሪቱ ንጉሥና አብዛኛው ሕዝብ ግን ጣኦት አምላኪዎች ነበሩ። ጊዮርጊስ ያደገው በጠለቀ የክርስትና ዕምነትና በመልካም ሥነ-ምግባር ተኮትኩቶ ነው።
ሃያ ዐመት በሞላው ጊዜም አባቱ ስለሞተ፣ በነበረው ደንብ መሠረት፣ የአባቱን መሥፍንነት ለመረከብ ንጉሡ ወዳለበት ቦታ ሄደ። እዚያ ሲደርስ ግን ንጉሡ፣ መሣፍንቱ፣ መኳንንቱና ሕዝቡ ጣኦት ሲያመልኩ፣ ዳንኪራ ሲረግጡና ሲሰክሩ አገኛቸው። ባየው ሁኔታ ከልብ አዝኖ ወደመጣበት የእናቱ አገር ለመመለስ ሲነሳ፣ ንጉሡ ጠርቶ ጣኦቱን እንዲያመልክና የሚታየው ፈንጠዝያ ኣካል እንዲሆን ጠየቀው። ጊዮርጊስ ግን የንጉሡን መንገድ ነቅፎ፣ የክርስትና ዕምነቱን አጠናክሮ ወደመጣበት ለመመለስ ተነሳ። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተናድዶ ጊዮርጊስን መቀጣጫ ለማድረግ የመከራ ድግሱን ኣዘጋጀ። በንጉሡ ትዕዛዝ፣ በጊዮርጊስ ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ ተግባራት ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፦
1. በቅጽበት የሚገድል መርዝ እንዲጠጣ ተደረገ። ሆኖም የክርስትና ዕምነቱ መርዙን አክሽፎታል።
2. ሰውነቱ በስለት ተቆራርጦ፣ በእሳት ተጠብሶ ካረረና አመድ ከሆነ በኋላ፣ አመዱ በአቅራቢያው በነበረው ተራራ ጫፍ ላይ እንዲበተን ተደረገ። በወቅቱ ተራራው ላይ በቅለው የነበሩ ዕጸዋት “ጽና ጊዮርጊስ!” እያሉ አበረቱት። በአምላክ ፈቃድና ድጋፍ ጸንቶና ከሞት ተነስቶ ገድሉን ቀጠለ።
3. በመንኮራኩር ላይ ታስሮ በከፍተኛ ፍጥነት እንዲሽከረከርና ሰውነቱ እንዲገነጣጠል ተደረገ። አምላክ ግን ከሞት አድኖታል።
4. ቆዳው ተገፍፎ፣ ሰውነቱ ላይ ጨው ተነስንሶ፣ በእሳት ተጠብሷል። ሆኖም በመለኮት ኃይል ድኖ፣ በርካታ ሰዎችን በአንድ አምላክ እንዲያምኑ አስተምሯል።
5. በመጨረሻም አንገቱ በሰይፍ ተቆርጦ ነፍሱ ወደ ሰማየ-ሰማያት ስትሸጋገርና በአምላክዋ ፊት ቀርባ የቅድስና አክሊላትን ስትቀዳጅ፣ ምድራዊ አካሉ ደግሞ ወደተወለደበት አገር ልዳ ተወስዶ ተቀበረ። ጊዮርጊስ ለብዙ መከራ የተዳረገው ‹ዓለምን በፈጠረ አንድ አምላክ እንጂ፤ በሰው በተፈጠረ ጣኦት አላምንም› በማለቱ ነበር። ለመከራ ሲዳረግ ስቃዩ ከፍተኛ ስለነበር፣ አንዳንድ ጊዜ  ከስቃዩ መሪርነት የተነሳ በጣኦቱ አመንኩ ለማለት “አ…አ…አ…!” ሲል፣ መልአክ አጠገቡ ሆኖ “ጽና ጊዮርጊስ!” እያለ ያበረታው እንደነበር የቤተ-ክርስቲያን አባቶች ሲያስተምሩ ሰምቻለሁ።
እዚህ ላይ የጊዮርጊስ ገድልን ያመጣሁት ለምንድን ነው? ኢትዮጵያ ያለችበት የጭንቅ ሁኔታ ጊዮርጊስ ካለፈበት የአካልና የአዕምሮ ስቃይ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነና ይህ ቅዱስ ፍጡር ስቃዩን ችሎ ፈተናውን እንዳለፈ ሁሉ፤ ኢትዮጵያም መከራዋን ተቋቁማ ፈተናዋን ለማለፍ የሚያስችላት የብሔራዊ አንድነት ጽናት እንዲኖራት ጸሎቴን ለመግለጽ ነው።
በአገራችን በአሁኑ ጊዜ፣ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉና ለአካልና ለአዕምሮ ጉዳት እየተዳረጉ ነው። የግልና የጋራ ንብረት እየወደመ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከረጋ ህይወታቸው ተፈናቅለው፣ ለከፋ የአካልና የመንፈስ ጉዳት እየተዳረጉ ነው። በብዙ ቦታዎች ዜጎች ለህልውናቸው ዋስትና ኖሯቸውና ተረጋግተው ለመሥራት የሚያስችላቸው ሠላም የለም።  እነዚህ ችግሮች ተደምረው፣ በብዙዎች አዕምሮ፣  በአገሪቱ መንግሥት፣ ሕግና ሥርዐት እንደሌለ ነው የመሰለው። ‹መንግሥትም ሕግና ሥርዐትም አለ› ከተባለ ደግሞ፣ ተግባራዊ ለማድረግ ባለሥልጣናቱ ቅንነቱ፣ ብቃቱና ቁርጠኝነቱ የሌላቸው እንደሆነ ነው የመሰለው፡፡ በእውነትም፣ በብዙ ቦታዎች የዘርፈ-ብዙ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ወገኖች በውስጣቸው ቢያመርሩ፣ በመንግሥት ላይ ቅሬታ ቢያሰሙ አግባብ አላቸው። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎቻችንም ሁሉ እንደዜጋ የስቃያቸው ተካፋዮች ነን።
ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ ታሪኳ በበርካታ ችግሮች ተፈትናለች። በአሁኑ ጊዜ የገጠማት ፈተና ግን፣ በባህሪው የተለየና የከፋ ነው።  በአንድ በኩል፣ በታሪክ የታወቁት የማኀበረሰብ ጠንቀኞች፣ ማለትም የሀብት፣ የሥልጣንና የአክራሪ ሃይማኖት ሱሰኞች፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እየታገዙ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል። ሁለተኛ፣ ሕወሓት ባወጣው ሕገ-መንግሥት የተከለው የጎሣ ፖለቲካ መርዝ፣ የኢትዮጵያን የዘመናት የአንድነት መሠረት ክፉኛ እየተፈታተነው ነው። ሦስተኛ፣ “ዳያስፖራ” የሚባል ዐዲስ ማኀበረሰብ ተፈጥሯል። ዕድሜ ለዘመኑ ተክኖሎጂ፤ እያንዳንዱ ግለሰብ የ”መረጃ” ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን፣ የ”መረጃ” አሰራጭና ተርጓሚ የመሆን ዕድል አለው። ታዲያ ከላይ የተጠቀሱት ጠንቀኛ ሱሰኞች፣ የዚህ ዳያስፖራ ህብረተሰብ በርካታ አባላትን በስልት በመቀስቀስ ከአገር ማዶ ሆነው፣ በኢትዮጵያ በሚነደው እሳት ቤንዚን የሚጨምሩ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። አራተኛ፣ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዓባይ ውሃውን ማንንም ሳይጎዳ፣ ለልማቱ ለማዋል ቆርጦ በመነሳቱ፣ በንዴት ዓይናቸው ደም የለበሰ ታሪካዊ ባላንጣዎቹ ከውስጥ ተባባሪዎቻቸው ጋር ተቀናጅተው በዙሪያው የግጭት እሳቶችን በማቀጣጠል፣ አንድነቱን ለማናጋትና ልማቱን ለማደናቀፍ ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ዓላማ በውስጣችን በሚፈጥሩት ውዥንብር ግራ እንድንጋባ፣ ሚዛናችንን እንድናጣ፣ የአንድነት አቋማችንን እንድናላላና የጥላቻ ሰለባ ሆነን እርስ-በርሳችን እንድንባላ ማድረግ ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የተፈጸሙበትን ስቃዮች ችሎ አሸናፊ ሊሆን የበቃው በአንድ አምላክ ዕምነቱ በመጽናቱ፣ አምላክም  ጽናቱን አይቶ፣ መልአኩን በአቅራቢያው አቁሞ፣  “ጽና ጊዮርጊስ!” እንዲለው ስላደረገና በሰዋዊ ጽናቱ ላይ መለኮታዊ ጽናቱን ስላከለበት ነው። ጊዮርጊስ በዘመኑ፣ በአንድ አምላክ ዕምነቱ ምክንያት በመከራ እንደተፈተነ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም በአሁኑ ጊዜ፣ አንድነቱን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት የተላቀቀና በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት የተመሠረተ ህብረተሰብ የመፍጠር ህልሙን ለማሳካት በሚያደርገው ትግል በከባድ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ችግሮች እየተፈተነ ነው።
Filed in: Amharic