>
5:13 pm - Thursday April 20, 9690

የሚሰማችሁ ከሆነ ምከሩት (ከይኄይስ እውነቱ)

የሚሰማችሁ ከሆነ ምከሩት

ከይኄይስ እውነቱ


ሃይማኖትና ፖለቲካ፣ ቤተክህነትና ቤተመንግሥት ስላላቸው ግንኙነትና ልዩነት፣ የሃይማኖት ሰው በፖለቲካ ባጠቃላይ በሥልጣን ፖለቲካ በተለይ ስለሚኖረው ተሳትፎ በተለያዩ የትምሕርት ዘርፎች በርካታ ጥራዞች ተጽፈዋል፡፡ በአገራችን በሃይማኖትና ፖለቲካ ዙሪያ የጠራ አመለካከት ባለመኖሩ አንድ ተራ ምእመን ሳይሆን የቤተክርስቲያን ታዋቂ መምህር ሁላችን ስለ አገራችን ጉዳይ ያገባናል በሚል መልኩ በጥቅሉ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳለን ከሚነገረው ውጭ በሥልጣን ፖለቲካ ወይም የፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ተዋናይ ከሆነ፣ በዚህ ድርጊቱ ብቻ ውጉዝ ከመ አርዮስ የሚለው ወገን ጥቂት አይደለም፡፡ ለማናቸውም ከፍ ብዬ ያቀረብኋቸውን ሃሳቦች መተንተን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ባለመሆኑ ልለፈውና ሁሌም የሚገርመኝና በሌሎች ሕግጋተ መንግሥት ያልገጠመኝ በወያኔ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› አንቀጽ 11 (3) ስለ ሃይማኖትና መንግሥት ግንኙነት እንዲህ የሚል ቃል ተደንግጎ ይገኛል፣

‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡›› (አጽንኦቱ በኔ የተጨመረ)

በዚህ ድንጋጌ የመጀመሪያው ክፍል በአስገዳጅነት የተገለጸው አባባል በተለያዩ አገራት ሕግጋተ መንግሥት ውስጥ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ የእምነት ነፃነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባገኙ የሕግ ሰነዶችም ሆነ በብሔራዊ ሕግጋተ መንግሥት ውስጥ የሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎች መካከል አንዱ ነውና፡፡ በመጠኑ በማውቀውም የክርስትና ሃይማኖት አስተምሕሮ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር ባለ አእምሮ አድርጎ ለባዊት፣ ነባቢት እና ሕያዊት ባሕርያት ያሏት ረቂቅ ነፍስ ገንዘቡ እንድትሆን አድርጎ ስላበጀው የሚፈልገውን ለመምረጥና የመረጠውንም ለመከተል በነፃነት የተፈጠረ ፍጥረት መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ግዕዛን (ነፃነት) ተሰጥቶት የተፈጠረ የሰው ልጅ በአምላካዊም፣ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ሕግ የአምልኮ ነፃነት አለው፡፡ በዚህ የአምልኮ ነፃነት ውስጥ ጣልቃ መግባት ከአምላካዊ፣ ከተፈጥሮ እና ከዓለማዊው ሕግጋት ጋር መቃረን ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ የድንጋጌው ክፍል በአንድ አገር የበላይ ሕግ ውስጥ መካተቱ ተገቢና ተቀባይነትም ያለው ነው፡፡ ባንፃሩም የዚህ ድንጋጌ ሌላኛው ገጽታ ‹ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡› የሚለው ክፍል ነው፡፡ 

ሃይማኖት ሰማያዊ መንግሥትን ሲመለከት ለግዛቱ ዳር ድንበር የለውም፡፡ እንኳን ግዙፉን ዓለማዊ መንግሥት ረቂቁን ዓለማት ሁሉ ይመለከታል፡፡ የሚመለከተውም የሰው ዘርን በሙሉ ነው፡፡ በዋናነት የሰው መንፈሳዊ ሕይወት ታንፆ መዳረሻ ግቡ የሰማያዊ መንግሥት ባለቤት ማድረግ ቢሆንም ምድራዊ አነዋወሩንም ይመለከታል፡፡ ለሰማያዊው መንግሥት ለመብቃት መዘጋጃ ቦታው ነውና፡፡  የእግዚአብሔር መንግሥት ‹ሕገ መንግሥት› ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ባንፃሩ ሕገ መንግሥት ምድራዊ መንግሥትን እና አስተዳደርን ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ በሕግ የግዛት ዳር ድንበሩ በታወቀ አገር ውስጥ የሚኖር ሕዝብን በበላይነት ለማስተዳደር ከሰዎች አእምሮ ፈልቆ የሚጻፍና እንደ ሁናቴውም ሊሻሻል አልፎም ሊቀየር የሚችል ሕግ ነው፡፡ ምድራዊ መንግሥት በቦታም በጊዜም ውሱን ነው፡፡ ስለሆነም ዘላለማዊ የሚባል መንግሥትም ሆነ ሕገ መንግሥት የለም፡፡ ታዲያ ምድራዊው ሰማያዊውን፤ ጊዜያዊው ዘላለማዊውን፤ ግዙፉ ረቂቁን፤ ውሱኑ የማይወሰነውን ወዘተ. እንዴት አድርጎ ነው ገደብ ሊጥልበት የሚችለው? ደኸ ሲበደል ፍርድ ሲጓደል ይሄ የምድራዊ መንግሥት ጉዳይ ነው ብሎ ሃይማኖት ወይም መንግሥተ እግዚአብሔር ዝም ይበል? መብትና ነፃነትን ለማስከበር እንኳን በሰማያዊው ሕግ በምድራዊውም ሕግ ሰላማዊ ፍልሚያ ከማድረግ የሚከለክለን የለም፡፡ ስለሆነም ሰማያዊው መንግሥት (ሃይማኖት) በምድራዊው መንግሥት ጣልቃ የሚገባባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አረመኔው ዐቢይ የኢትዮጵያን ርትዕት ተዋሕዶ ቤክ በትርያርክ በትግራይ ሕዝብም ሆነ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጸመውን ግፍና በደል ለምን ያነሣሉ በማለት ቡራ ከረዩ እንዳለውና ጉልበትና መሣሪያውን ተመክቶ ድምጻቸውን ለማፈን እንደሞከረው ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ሊከለክል አይችልም፡፡ ይሄ ሃይማኖትን የሚያንቋሽሹ÷ ሕዝብን የሚንቁ አምባገነን አገዛዞች ለሥልጣናቸው ማስጠበቂያ ይሆነኛል ብለው ሕዝብ ባልተሳተፈበትና ባላጸደቀው የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ውስጥ የሚሰነቅሩት የግል ፍላጎታቸው ማሟያ ድንጋጌ ነው፡፡ 

ዛሬ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁናቴ በውስጥና በውጭ ፈተናዎች ተሰቅዛ ተይዛለች፡፡ በሕዝባቸው ላይ ተጨማሪ ቀንበር የሚጭኑ፣ በጊንጥና በጨንገር የሚገርፉ ክፉና መጥፎ መንፈስ ያደረባቸው ‹ሳዖሎች›፣ ‹ናቡከደነፆሮች›፣ ‹ሮብአሞች›፣ ‹ፈርዖኖች› ተነስተውባታል፡፡ ከዐላውያኑ ጋር በመሆን የሃይማኖት ሰዎችን (እውነተኛ ጳጳሳትንና መምህራንን) የሚያሳድዱ፣ ለ‹ቄሣሮች› አሳልፈው የሚሰጡ በርካታ ‹ጸሐፍት ፈሪሳውያንም› በቤታችን ውስጥ እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡

አልቦ እግዚአብሔር ብሎ ከተነሣው የደርግ አገዛዝ ጀምሮ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ቤተ መንግሥቱ በቤተ ክህነቱ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ብቻ ሳይሆን ተቈጣጥሮት ያሻውን እየፈተተ ይገኛል፡፡ ዛሬ ታሪካዊት፣ ብሔራዊት እና ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን፣ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ድርና ማግ ሸምና በመሥራት ረገድ ቀዳሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ያላትን ርትዕት ተዋሕዶ ቤክ አገዛዙ በቅጥረኛ ካድሬዎቹ፣ በዘረኝነት በተለከፉና ለሆዳቸው ባደሩ የውስጥ ከሀዲዎች እና አፅራረ ቤክ በሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮች እንዲሁም እምነት የለሾችን በውስጧ ሰግስጎ በማስገባት ጣልቃ ከመግባት እና የወንበዴዎች ዋሻ ከማድረግ አልፎ ቤተክርስቲያኒቷን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም የጥፋት ተልእኮው ሽብር ፈጣሪዎችን በማሰማራት ካህናትን እና ምእመናንን ከመግደል ጀምሮ አብያተ ክርስቲያናትን በማውደምና ቅርሶችን በማጥፋት ተጠምዶ ይገኛል፡፡ አለመታደል ሆኖ ነቢየ እግዚአብሔር ቅ/ዳዊት ‹‹ኵሉ ዐረየ ወኅቡረ ዐለወ›› (ሁላችን ተካክለን በድለናል) እንዳለው እግዚአብሔር ባወቀ በበረሃ ወድቀው ከሚለምኑና በከተማ ከሚገኙ ሥውር ባሕታውያን ጸሎት ጨርሶ እንዳንጠፋ አድርጎናል እንጂ ቤክርስቲያናችን ዛሬ መንፈሳዊነትን ከጥብዐት ጋር ያስተባበረ ሰው የላትም፡፡ ሁሉም ሆዴ ይሙላን ደረቴ ይቅላን የሕይወቱ መመሪያ ያደረገ ይመስላል፡፡ የአገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ የኢኦተቤክንም ህልውና ለአደጋ መጋለጡ እሙን ነው፡፡ የጋራ ርስታችን ሰፊው ‹ቤተ መቅደሳችን› ሀገረ እግዚአብሔር ራሷ ኢትዮጵያ ናትና፡፡

የአገርንና የቤተክርስቲያንን ህልውና አደጋ ላይ ከጣለ አገዛዝ ጋር አብሮ መሥራት በተለይም በሥልጣን ፖለቲካ ተሳታፊ የሆነ የተዋሕዶ ልጅ ካለ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አገርንና ቤክንን በማፍረስ አባሪ ተባባሪ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ በይሉኝታ የምናድበሰብሰው ጉዳይ የለም፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ ከብዙ ማመንታት በኋላ ዛሬ ላነሣው ያሰብሁት ርእሰ ጉዳይ በከፍተኛ የመንግሥት (የአገዛዙ) የፖለቲካ ሥልጣን ላይ የሚገኝ የቤተክርስቲያን ወንድማችንን ይመለከታል፡፡ የአገርና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ባይሆንብኝ እና የዐደባባይ ሰው ባይሆን ኖሮ ስለ ግለሰብ መጻፍ ሃሳብም ፍላጎትም የለኝም፡፡ ጉዳዩ ወንድማችን ዲ/ን ዳንኤል ክብረትን ይመለከታል፡፡ ወንድማችን በየጊዜው የሚያደርጋቸውን ቃለ መጠይቆች፣ በግጥም ምሽት ያደረጋቸውን ንግግሮች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ስለ ፖለቲካ ተሳትፎውና አቋሙ በአመዛኙ በአሉታ የጻፏቸውንም አስተያየቶች በተወሰነ ደረጃ ተከታትዬአለሁ፡፡ አንድ የቤተክርስቲያን ሰው በሥልጣን ፖለቲካ መሳተፉ፣ ለምርጫ ውድድር እጩ ሆኖ መቅረቡ፣ የሚያምንበትንም የፖለቲካ አስተሳሰብና አቋም ማራመዱ የግሉ ምርጫና መብቱ ነው፡፡ ቀድሞም በቤተክርስቲያን መምህርነቱ የዐደባባይ ሰው የነበረው ዲ/ን ዳንኤል (እሱን ጨምሮ በተወሰነ ደረጃ ከማውቃቸውና ዛሬ ቅስና ከተቀበሉ ወንድሞቼ በሚያስተምሯቸው ትምህርቶችና በስብከቶቻቸው መንፈሳዊ ዕውቀትን ከመግብየት በተጨማሪ ሃይማኖቴን ለማጽናት እንዳገዙኝ ይሰማኛል) አሁን ደግሞ በተለየ መድረክ የዐደባባይ ሰውነቱ ከአወዛጋቢ ሰብእናው ጋር ቀጥሏል፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የዐደባባይ ሰው በበጎም ሆነ በመጥፎ ከትችት ነፃ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይም መሠረትና ጉልላቱ ውሸት፣ ሸፍጥ፣ ጥላቻና መጠላለፍ በሆነው የቆሸሸ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ደረጃው ይለያይ እንጂ ንጽሕናውን ጠብቆ አደፍ ጉድፍ ሳይነካው የሚቆይ የፖለቲካ ሰው ከተገኘ የተአምር ያህል የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡ እንደኔ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ዳንኤል በቤተክርስቲያን መምህርነቱ፣ በመንፈሳዊ መጻሕፍት አዘጋጅነቱ እና በጦማሪነቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በመልካም ዜግነት ያንፅ ነበር፡፡ በኔ የግል ምልከታ ፖለቲከኛነቱ የተስማማው አልመሰለኝም፡፡ መነሻ ዓላማው ለአገር በጎ አስተዋጽኦ አደርጋለሁ ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ ከጅምሩ የማስተውለው ግን የክፉዎች፣ የዓመጸኞች፣ የአረመኔዎች፣ የአገርና ቤተክርስቲያን አፍራሾች ማኅበር/ጉባኤ ውስጥ ዐውቆትም ሆነ ሳያውቀው? ተቀላቅሏል፡፡ ዛሬ የአረመኔው ዐቢይ እና የጐሣ አገዛዙ ከዓላማው ተጋሪዎች፣ ለሆዳቸው ካደሩ አድርባዮች እና የጥቅም ተካፋዮች በስተቀር በሐሳዊ ኢትዮጵያዊነት እና የእምነት ሰውነት ካባ ተጀቡኖ ኢትዮጵያንና ርትዕት ተዋሕዶ ቤክንን አፍራሽነቱ ፍንትው ብሎ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተገልጧል፡፡ ታዲያ ወንድማችን እንዴት የዚህ አጋንንታዊ ቡድን አጋፋሪ ሆኖ ይቀጥላል? ዛሬ ዓይናችንን ግምባር ያድርገው ብለው በጭፍኑ ዳንኤልን ለመከላከልና ለመደገፍ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ የ‹ቤተክርስቲያን ልጆች› በርካቶች ናቸው፡፡ ከውጭ በአገዛዙ ተጽእኖ/ጫና ከውስጥ ደግሞ በመንፈሳዊነት መራቆት፣ በአስተዳደር ብልሹነት፣ በንቅዘት፣ በዘረኝነት ወዘተ. እየታመሰች ያለች ቤክ መሆኗን ለዳንኤል መንገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል፡፡ ታዲያ እንዴት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንባታል? ወይም ለጥፋቷ አጥብቀው ከሚሠሩ ጋር በአንድነት ‹ጽዋ ይጠጣል›?

የቤተክርስቲያናችን ያልሆኑትን ትተን በውስጥ ያሉ ምእመናን በዳንኤል ምክንያት ቡድን አበጅተው÷ ጎራ ለይተው ተከፋፍለዋል፡፡ መለያየት/መከፋፈል ደግሞ ከክርስትና ውጭ ያደርጋል፡፡ በሌላ አነጋገር የዳንኤል የፖለቲካ ሰብእና ለቤተክርስቲያን ልጆች መሰናከያ ሆኗል፡፡ 

ያሳለፍናቸው ሦስት የግፍና መከራ ዓመታት ወደፊት ሊመጣ ላለው የከፋ ጊዜ ምልክት ይመስሉኛል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ከዚህ በላይ መናገር አልፈልግም፡፡ የጽሑፌ መልእክት ባጭሩ ስማችሁ ከዚህ በታች የዘርዘርኋችሁ ካህናት አባቶቼና በዕድሜ ወንድሞቼ እንዲሁም ዳንኤልን በቅርብ የምታውቁት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ እውነተኛ የተዋሕዶ አባቶችና እናቶች እንዲሁም ወንድሞችና እኅቶች የሚሰማችሁ ከሆነ ምከሩት (ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ እንዲል ቅ/ዳዊት)፡፡ አጥብቃችሁም ጸልዩለት፡፡

 

የከበረ ጥረዬን የማቀርብላችሁ አባቶቼ ካህናት እና ወንድሞቼ ዲያቆናት (በመደበኛ ትምሕርት ያገኛችሁት ማዕርግ ለዚህ ጽሑፍ አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኘሁት ትቼዋለሁ)፤

  • ቀሲስ በላቸው
  • ቀሲስ እሸቱ ታደሰ
  • ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው
  • ቀሲስ ሙሉጌታ
  • ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ
  • ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና
  • ሊቀ ትጉሃን ሙሉጌታ
  • ሊቀ መዘምራን ይልማ
  • መምህር ግርማ ወ/ሩፋኤል
  • ዲ/ን አባይነህ ካሤ
  • ዲ/ን ብርሃኑ አድማሱ
  • ዲ/ን መርሻ አለልኝ
  • መምህር አለማየሁ ዋሴ
Filed in: Amharic