>

የሌለ ፓርቲ እንዴት ምረጡኝ ብሎ ይቀሰቅሳል? (ይነጋል በላቸው)

የሌለ ፓርቲ እንዴት ምረጡኝ ብሎ ይቀሰቅሳል?

ይነጋል በላቸው

(yinegal3@gmail.com)


“አንበሣ ምን ይበላል?” ቢሉ “ተበድሮ” – “ምን ይከፍላል?” ቢሉ “ማን ጠይቆ!” የምትለዋን አባባል “እውን ደርግ አለ?” ከምትለዋ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ታዋቂ ንግግር ጋር በቀብድነት ላስይዝና ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ ሕይወት ሳይኖረው በድርቅና ብቻ… በጉልበት ብቻ … አንድ ሰውና ጥቂት አጋፋሪዎቹ ሁሉን ነገር ስለተቆጣጠሩ ብቻ ያለ መስሎት ሳይኖር ምረጡኝ ስለሚለው “ፓርቲ” ትንሽ ላውራችሁ፡፡ መንጌ መለዮኣቸውን ያወለቁ ደርጎችን እንደአዲስ ሰዎች ቆጥሮ ነበር “እውን ደርግ አለ?” ያለው፡፡ ለጠቅላላ ዕውቀታችን ያህል ደርግ ራሱ ነበር ሰደድን፣ ኢማሌድኅን፣ ኢሠፓአኮንና ኢሠፓን አልፎ ኢሕዲሪ የሆነው፡፡

ከህጋዊ አሠራር አኳያ እኔ እንዳለ የማልቆጥረው ራሱን “ብልጽግና” ብሎ የሚጠራው ፓርቲም ልክ እንደደርግ ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ ደርግና ተተኪው ሕወሓት በማስመሰል ድራማ ብዙውን ጊዜ የተዋጣላቸው ነበሩ – “የተዋጣላቸው” የሚለው ገላጭ ቢከብድባቸውም ከነዚህ ጅሎች ጋር ሲወዳደሩ ግን በአንጻራዊነት ደህና ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የነዚህን የአክራሪ ኦህዲድ ሸኔዎች የድንቁርና ደረጃ ለመግለጽ’ኮ ቃል የለኝም፡፡ ድርቅናቸው ፍጥጥ ያለና ምንም ወዝ የሌለው ነው፡፡ በጉልበት ማሰብን እያስተማሩ ያሉ ገልቱዎች ናቸው፡፡ መጪው ትውልድ ከነዚህ ተምሮ ሀገሪቱን እንዴት በጉልበት እያዳፋ መቀመቅ እንደሚከታት አንድዬ ይሁነን እንጂ መገመቱ አይከብድም፡፡ ማስመሰልን እንኳ አለመቻል ትልቅ የድድብናና የዕብሪት ምልክት ነው፡፡

ኢሕአዲግ ሲመሠረት በዐዋጅ ነበር፡፡ ትያትሩ የተሟላ ገቢርና ፆታ ነበረው፡፡ በመልክ በመልክም ነበር የሚተወነው፡፡ ተግባር ላይ እንጅ ድራማዊ ክንዋኔው ላይ የሚስተዋል ብዙም ህፀፅ አልነበረም፡፡ ከምሥረታው ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው የጠቅላላ አባላት ጉባኤ ያካሂዳል፤ የማዕከላዊ ኮሚቴና ተለዋጭ የማ. ኮሚቴ አባላት ምርጫዎች ያደርጋል፤ ሊቀ መንበሩንና ምክትሎቹን፣ የኦዲት ኮሚሽን አባላትን፣ የፖሊት ቢሮ አባላት፣ የየክፍሎች ዋናና ምክትል ሊቃነ መናብርት ምርጫ፣ በየተወሰነ ጊዜ የማዕከላዊና የፖሊት ቢሮ ስብሰባዎች ወዘተ. እንደሚካሄዱና ለሕዝብም ይፋ እንደሚደረጉ አስታውሳለሁ፡፡ ትያትሩ ቅጥ ያለው ነበር ለማለት ነው፡፡  

ብልጽግና ግን አንዴ ብቻ አዋሳ ላይ ይሁን አሰቦት ላይ ኮምሬድ(ጓድ) ናፖሊዮን (የእንስሳት ዕድር የተሰኘውን መጽሐፍ ያስታውሷል) ብልጽግናን መሠረትን አለ – ከዚያ በኋላ የአማራ የለ የኦሮሞ የለ  (በዱሮው አገላለጽ እንዳልጠቀም ከሳሽ ካለ ብዬ ነው) ሁሉም ዝም ዝም ሆነና መቼም ስም አይገዛም በደፈናው “ብልጽግና” በአንዳንድ ነገረኞች ደግሞ “ብልግና” እየተባለ ሕዝብና አባላት ተብዬዎቹን ማወናበዱን ቀጠለ፡፡ እንደማውቀው የዚህ “ፓርቲ” ጠቅላላ ስብስባ፣ የማዕከላዊ አባላት ማንነትና የሚያካሂዱት መደበኛም ይሁን ኢመደበኛ ስበስባ፣ የአባልነት ምልመላ፣ ዋናም ይሁን ምክትል የአመራሮች ምርጫ፣ አስቸኳይም ይሁን መደበኛ የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ምንትስ ቅብጥርስ አንድም የለም ወይም ተካሂዶም ከሆነ እኔ አላውቅም፡፡ ብቻ ብልጽግና ፓርቲ እየተባለ ሲጠራና ለምርጫ ሲዘጋጅ አያለሁ፡፡ “ሞኝ እንዴት ያሸንፋል?” ቢሉ “እምቢኝ ብሎ!” ይባላል፡፡ ህግ ቢኖር እነሱም የሉም ነበር፡፡

ሌላው ችግር ይሄው ፓርቲ ተብዬ መጪውን የግንቦት ወር 2013 “ምርጫ” በቁጥጥሩ ሥር ካደረገ በኋላ በካፈርኩ አይመልሰኝ የሚያካሂደው የምረጡኝ ዘመቻ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ወጪ የሚከሰክሰው ለምንድን ነው? ከወዲሁ ያሸነፈውን ምርጫ ምረጡኝ ሲል አለማፈሩ የራሱ ጉዳይ ነው እንበልና ለዚህ ቅስቀሳ የሚረጨው ገንዘብ ስንትና ስንት ሀኪም ቤቶችንና ትምህርት ቤቶችን ማሳነጽና ማደስ ይችል አልነበረምን? ድሃ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ፊጥ ብሎ በድሆች ገንዘብ መቀናጣት ወንጀልም ነውርም አይደለምን?

ከዚህ በተያያዘ በብዙ አሥራዎች የሚቆጠሩት እንደአሸን የፈሉት ሌሎቹ “ፓርቲዎች”ም በሀገራችን የሥራ አጥ ቁጥርን መብዛት ከመጠቆም ባሻገር አንድም ፋይዳ የላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ የፓርቲ ጋጋታ የሚያሳየው ብቸኛ ቁም ነገር ሰዎች ሥራ ሲፈቱና መተዳደሪያ የሚሆን የገቢ ምንጭ ሲያጡ በቀላሉ  እንጀራ የሚያገኙት ፖለቲካ ውስጥ ሲገቡ መሆኑን ነው፡፡ የአሁኑ ፖለቲካ ደግሞ ለዚህ አመቺ ነው፡፡ ምክንያቱም ዕድሜ ለወያኔ ይህን የዘር ፖለቲካ አምጥቶ በተነው በዚያ ማዕቀፍ እየገቡ ሰማንያውን ነገድ በአራት እያባዙ ከ320 በላይ ፓርቲ በማቋቋም ሕዝብን ማራኮት እንደፋሽን ተወስዷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አድጎና በልጽጎ እነዚህን ሥራ አጦች አስቀምጦ በነፃም ቢሆን ደሞዝ ቢከፍልልን ትልቅ ግልግል ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ገንዘብ ጠቃሚ የመሆኑን ያህል ጎጂም ነው፡፡ አፍቅሮተ ንዋይ የተጠናወተው ሰው በመጀመሪያ ኅሊናውን ባወጣ ይቀውረዋል፡፡ ከዚያ ገበያ አውጥቶ የማይቸበችበው ነገር የለም፡፡ ኅሊናቢስነት ደግሞ ሀገርንና ሕዝብን ብቻ ሣይሆን የገዛ ልጅንና ሚስትን፣ እናት አባትንና ወንድም እህትን ሳይቀር ያሸጣል፡፡ እንግዲህ በትምህርትም በዕውቀትም በልምድም ያልገፋ ምድረ የአእምሮ ድሃ ሁሉ ወደዚህ ክልክል የሌለበት ነፃ የፖለቲካ ቀጣና እየገባ ሀገራችንን የሚያምሳት የሆድ ጥያቄን ለመመለስ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ሀገራችን ህጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት ቢኖራት ኖሮ ቢያንስ እንደሌሎች ሀገራት በዘርና በሃይማኖት የመደራጀትንና ፓርቲ የመመሥረትን ጠንቀኛ አካሄድ በህግ ይከለክልልንና በዚህ አቅጣጫ የሚመጣብንን ከባድ አደጋ ያስወግድልን ነበር፡፡ እኛ ግን ለዚያ አልታደልንም፡፡ ከዚሁ መሪር እውነት ጋር በተያያዘም የዲያስፖራው ኑሮ ያንገሸገሸው አሰለጥና  ሞሽላቃ ሌባ እዚያ ያጣውን በጎሣና በሃይማኖት የመደራጀት መብት እዚህ እየመጣ ከጠማማው ህገ መንግሥት ይህን አስጠሊታ መብት ተብዬ ያገኝና ከላይ እስከታች ያምሰናል – አንዳች ነገር ያምሰውና፡፡

Filed in: Amharic