>

ካማውያን ተረጋጉ...!!!  (በቀሲስ ስንታየሁ አባተ)

ካማውያን ተረጋጉ…!!!

 (በቀሲስ ስንታየሁ አባተ)

*…. እስቲ ዘመናችንን፣ ኑሯችንን፣ ሃሳባችንን፣ ሀገራችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን እናስተውል። ምድራችን ግፍን አልተሞላችምን? ከዘር፣ ከነገድና ከቋንቋ ሁሉ በመስቀሉ ስቦ ካቀረበን እኛም ጥሩ ምእመናን፣ ሰባክያን፣ ዘማርያን፣ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ ጳጳሳት ወዘተ ሆነን ልናመልከውና ልናገለግለው ቃል ከገባን በኋላ ተመልሰን በቃኤል ልጆች ግብር ተይዘን፣ በፍትወት ሥጋዊት ተቃጥለን፣ በዘረኝነት ልክፍት ተይዘን አንዱን ክርስቶስ በቋንቋ ከፋፍለን የጽድቅ መንገዳችንን ኹሉ በርኵሰት አበላሽተን እንደኖኅ ዘመን ሰዎች አልሆንምን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው በስፋት ከተጻፈላቸውና ቅድስናቸው ከተመሰከረላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ኖኅ ነው።
ኖኅ እግዚአብሔርን መፍራት ጠፍቶ ኃጢአቱ ጽድቅ፣ ጽድቁም ኃጢአት በመሰለበት ዘመን የተገኘ ሰው ነው። በዘመኑ የነበሩ ሰዎች እግዚአብሔር “ሰውን በመፍጠሩ ተጸጸተ” ተብሎ እስኪነገር ያደረሰ ክፉ ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ያደረጉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ንጽህ ጠብቀን ከቃኤል ልጆች ግብር ርቀን ሄኖክን መስለን እግዚአብሔርን እያገለገልን እንኖራለን ብለው በፈቃዳቸው ራሳቸውን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው አቅርበው ነበር። በዚህ መልካም ውሳኔያቸውም “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብለው እስከመጠራት ደርሰው ነበር።
በኑሮ ሂደት ግን የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉት የሴት ልጆች የሰው ልጆች ከተባሉት ከቃኤል ልጆች ጋር መቀራረብ ጀመሩ። ውበት፣ ደም ግባት ሥጋዊ ፍትወት ቀሰቀሰባቸው። ከወንድ ከሴት ርቀን ንጽህ ጠብቀን እንኖራለን ብለው በእግዚአብሔር ፊት የገቡትን ቃል ኪዳን ዘንግተው ከቃኤል ልጆች ጋር ሰሰኑ። የእግዚአብሔርን ቁጣ አነሣሱ።
ከክብር አንሰው፣ ከጸጋ ተራቁተው እንደእንስሳ ሆኑ። ኖኅ በዚኽ ሕዝብ መካከል ይኖር ነበር። ቅዱስ መጽሐፍ “ጽድቅን የሚሰብከውን” በማለት እግዚአብሔርን በዘነጉ ሕዝቦች መካከል ኖኅ የጽድቅ መምህር መኾኑን ገልጧል። 2ጴጥ. 2፥5። በዙርያው ያሉ ሕዝቦች ጫጫታ፣ በፈቃደ ሥጋ ልቅ መኾናቸው፥ ለሥጋ ምኞት ለዐይን አምሮት መሸነፋቸው ኖኅን አልማረከውም። መጽሐፍ እንደመሰከረለት “ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ።” ዘፍ. 6፥9። እርሱ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ሲያደርግ የሴት ልጆች ግን ቃል ኪዳናቸውን ሰብረው በክፉ ሥራቸው “ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተሞላች፤ … ሥጋን የለበሰ  ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና” እንዲባል አደረጉ። ዘፍ. 6፥11-12።
እስቲ ዘመናችንን፣ ኑሯችንን፣ ሃሳባችንን፣ ሀገራችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን እናስተውል። ምድራችን ግፍን አልተሞላችምን? ከዘር፣ ከነገድና ከቋንቋ ሁሉ በመስቀሉ ስቦ ካቀረበን እኛም ጥሩ ምእመናን፣ ሰባክያን፣ ዘማርያን፣ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ ጳጳሳት ወዘተ ሆነን ልናመልከውና ልናገለግለው ቃል ከገባን በኋላ ተመልሰን በቃኤል ልጆች ግብር ተይዘን፣ በፍትወት ሥጋዊት ተቃጥለን፣ በዘረኝነት ልክፍት ተይዘን አንዱን ክርስቶስ በቋንቋ ከፋፍለን የጽድቅ መንገዳችንን ኹሉ በርኵሰት አበላሽተን እንደኖኅ ዘመን ሰዎች አልሆንምን?
ከዚያ ዘመን የተለየ ነገር በመካከላችን ቢኖር እንደኖኅ ጽድቅን የሚሰብክ ሰው መታጣቱ ብቻ ነው። ምድራችን፣ ሀገራችን፣ ቤተ ክርስቲያናችን፣ አንድነታችን አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎ ጽድቅን የሚሰብክ እንደሙሴ እግዚአብሔርን በሕይወቱ ውስጥ የሚያሳይ ሰው አጥተናል።
ወደ ኖኅ ዘመን እንመለስ። የምድሪቱን ጉስቁልና ያየ እግዚአብሔር ሊያጠራት ወደደ። ዕደ መዓቱን ሊያነሣ ሲልም አካሄዱን እንደፈቃዱ ያደረገውን ኖኅን አሰበው። መርከብ እንዲያዘጋጅ  አዘዘው። ኖኅም መጽሐፍ እንደመሰከረለት “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተሰቦቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ፤ በዚኽም ዓለምን ኰነነ። በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ኾነ።” ዕብ. 11፥7።
ኖኅ መርከብን እንደታዘዘው አዘጋጀ። ነቢዩ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር፥ ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል” እንዳለ በመርከብ አንፃር ልዑል እግዚአብሔርን መጠጊያ አደረገ። የሰማይ መስኮቶች የምድር ቀላያት ተነደሉ። የንፍር ውሃ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ወረደ፣ ወደላይም ፈለቀ። ውኃም በምድር ላይ አንድ መቶ አምሳ ቀናት ያኽል ቆየ። አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገው ኖኅ፣ ሚስቱ፣ ልጆቹ፣ የልጆቹ ሚስቶች፣ ከእርሱ ጋር ወደ መርከብ የገቡ እንስሳትና አራዊት ብቻ ሲተርፉ የተቀረው ዓለም ውበትና ላሕይ ያታለላቸው ወገኖች እነርሱም ያታለላቸው መልክም ምኞታቸውም ኹሉም ከምድር ላይ ታጥበው አለፉ።
ዓለም ከእግዚአብሔር ተለይታ ተድላ ደስታዋን ስታደርግ እርሱ ከዓለም ኹሉ ተለይቶ ፈጣሪውን አስቧልና እግዚአብሔር ኖኅንና አብረውት በመርከብ ውስጥ ያሉትን በምሕረት አሰባቸው። በታጠበች፣ ከርኵሰቷም በጸዳች ምድር በአዲስ ተስፋና ቃል ኪዳን ይኖሩ ዘንድ ከመርከብ አስወጣቸው። ባረካቸው። የማይጠፋ የዘላለም ቃል ኪዳን ሰጣቸው። የቃል ኪዳኑን ምልክት ቀስቱን በሰማይ ደመና ጋረደላቸው።
ኖኅ እንደቀድሞው ኹሉ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎ ግብርናውን ጀመረ። ወይንም ተከለ። ከእርሱም ፍሬን ለቀመ። ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። ከወይኑም ጠጣ። ሰከረ፤ ወደቀ፣ ከልብስም ተራቆተ። እርቃኑም ታየ።
ኀያሉ ኖኅ የቃኤል ልጆች ክፋት ያልበገረው እንዴት በወይን ተሸነፈ? አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ኖኅ እንዴት ለመጠጥ እጁን ሰጠ? ጽድቅን የተጎናጸፈው ኖኅ እንዴት ሰክሮ እርቃኑን ቀረ? በእምነት ታዝዞ ዓለምን የታደገ ፍጥረት እንዳይጠፋ ምክንያት የኾነ ኖኅ እኮ እንዴት እርቃኑ ታየ?
ካም የአባቱን እርቃን አየ። የአባትን እርቃን የሚያዩ ምን ዓይነት ዐይኖች ናቸው? በማየት አላበቃም። በልቡናው ሰክሮ ከመሬት ተዘርሮ የወደቀውን አባቱን አቃለለው። እንደርሱ የአባታቸውን እርቃን ያዩ ዘንድ አይተውም ይዘባበቱበት ዘንድ ሁለቱን ወንድሞቹን ሴምንና ያፌትን ጠራቸው።
በዘመናችን ስንቶቻችን ነን የሥጋም የነፍስም አባቶቻችንና እናቶቻችንን እርቃን ተመልክተን መሳቃችን በልቡናችንም ማቃለላችን ሳያንስ ያላዩ አይተው እንዲስቁባቸው፣ በልባቸውም እንዲታዘቧቸውና እንዲያቃልሏቸው “እነሆ የአባቶቻችን እርቃን” ብለን ላላዩት ላልሰሙት ለማሳየትና ለማሰማት የምንሮጥ???
ካም እንደመልካም ዜና ነጋሪ የአባቱን ኀፍረት ለወንድሞቹ ለማሳየት ሮጠ። ሴምና ያፌት በአባታቸው የኾነውን ሲሰሙ አዘኑ። አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎ የነበረው፣ የጽድቅ ሰባኪው፥ በእምነት ታዛዡ አባታቸው መራቆቱ ለአባታቸው ያላቸውን ክብርና ፍቅር አልቀነሰም። ያ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ መልካም መዓዛ ያለውን መሥዋዕት አቅርቦ የነበረው ኖኅ ዛሬ ቢወድቅም አሁንም አባታቸው ነው። ነገም እግዚአብሔር ዳግም በክብር ከውድቀቱ እንደሚያነሣው ያውቃሉ።
በስካር የወደቀውን፣ እርቃኑን የቀረውን፣ ወንድማቸው የሳቀበትን የአባታቸውን ሰውነት ቀና ብለው ዐይናቸውን ገልጠው ያዩት ዘንድ አልደፈሩም። “ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፤ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውን ራቁትነት አላዩም።” ዘፍ. 9፥23-24።
አንባቢ ሆይ እስቲ ቆም በል። አንተስ ብትሆን ምን ታደርግ ነበር? ዛሬስ በመጠጥ፣ በመሰናከል፣ በዘረኝነት፣ በሙስና ተይዘው ወደቁ ብለህ የምትስቅባቸው አባቶችና እናቶች የሉምን? የአንተ በወደቀው መሳቅ የወደቀውን ከውድቀቱ ያነሣው ይኾንን? አንተስ በሌላው የምትስቀው በሳቅኽበት ጉዳይ አለመውደቅህን መርምረህ ታውቃለኽን?
ሴምና ያፌት የአባታቸውን ራቁትነት አላዩም። ሸፈኑት እንጂ። አንተ ኦርቶዶክሳዊ ወገን ተው የአባቶችህን ራቁትነት ለማየትና ለመሳቅ፣ ለሌላውም ለማሳየት አትሩጥ። ለሃይማኖት መቅናትና መቆርቆር የወደቀውን ሰው ገመና ላላየው ማሳየት ሳይሆን ገመናን ሸፍኖ በርን ዘግቶ መነጋገር ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከኹሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” ብሏል። 1ጴጥ. 4፥8። ካም ለአባቱ ፍቅር ቢኖረው ኖሮ ወንድሞቹን ሳይጠራ የኖኅን እርቃን በሸፈነ ነበር። እምነታችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ አባቶቻችንን፣ ሕዝባችንን ስንወድ ሲበረቱ እኛ የምንናገረውን ሲናገሩ፣ የምንወደውን ሲወዱ፣ የምንጠላውን ሲጠሉ ብቻ አይደለም። ሲቆሙም እንወዳቸዋለን፤ ሲወድቁም እንወዳቸዋለን።  ምክንያቱም የእምነታችን መሠረቱ ፍቅር ነውና። ሐዋርያው “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ያለውን በልባችን ጽፈናልና።
ኖኅ እንደሰከረ አልቀረም። ስካሩ አልፎለት ተነሣ። ካም ያደረገበትን፣ ሴምና ያፌት ያደረጉለትን አወቀ። መልካም ያደረጉለትን መረቀ። ከአባት በምትገኝ በረከት ባረካቸው። ከመርከብ ሲወጡ እግዚአብሔር መላውን ቤተሰብ ባርኳቸው ነበርና እግዚአብሔር የባረከውን ካምን ሊረግመው አልደፈረም። እግዚአብሔር የባረከውን ማን ሊረግም ይችላልና? አበው በትርጓሜያቸው የኖኅን መራቆት መጀመርያ ያየውና ለአባቱ የነገረው የካም ልጅ ከነዓን ነበር። ስለዚህ ኖኅ ከነዓንን ረገመው ብለዋል።
በወደቀው መሳቅ፣ የሌላውን እርቃን ማየትና ለሌላውም ማሳየት በልብም መታዘብ ያስከተለውን መዘዝ አስተዋላችሁን? ከራስ አልፎ ትውልድን ዘርን ያስረግማል። ኖኅስ ወይን ጠጥቶ ሰክሮ ወድቆ እስከ መስቀል ወድዶን የሰው ልጆች ፍቅር አሸንፎት በቀራንዮ ልብሱ ተገፍፎ  በመስቀል ላይ ለተሰቀለልን ለክርስቶስ ምሳሌ ኾነ። ሴምና ያፌት የአባታቸውን እርቃን አናይም ብለው እንደሸፈኑት ክርስቶስ እርቃኑን በተሰቀለባት ዕለት ፀሐይ ጨለመች፤ ጨረቃም ደም ሆነች፤ ከዋክብት ረገፉ፦ የአምላካቸውን መራቆት አናይም፣ በብርሃናችንም ለሌላው አናሳይም ብለው። የካም ወገኖች ግን ልብሱን ገፍፈው ዘበቱበት። በዘመናችም እነዚህ ዘባቾች የራሳቸውን መራቆት ማየት ተስኗቸው በአባቶቻቸው መዛል መድከም ይዘባበታሉ። ማን ነው የማይደክመው? ማንስ ነው የተጎዳው? ሰክሮ ተራቁቶ የወደቀው ወይስ በተራቆተው በአባቱ እርቃን የሳቀው?
ካማውያን የካም ልጆች ተረጋጉ። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የአባቶቿን ድካም መሳቂያ መሳለቂያ አታደርግም። የስካር ጊዜ የድካም ጊዜ ያልፋል። መዘዙ ግን በወደቀው በደከመው ሳይኾን የደከመውን ማበርታት ሲገባው አንዳች ምድራዊ ትርፍ አገኛለሁ በሚል ተስፋ በአባቶቹ ድካም በሚዘባበተው ላይ ነው።
እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን።
Filed in: Amharic