>

በአዲስ አበባ  በ218 የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ተግዳሮቶች  የዳሰሳ  ጥናት ውጤት ! (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ)

በአዲስ አበባ  በ218 የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ተግዳሮቶች  የዳሰሳ  ጥናት ውጤት !
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

1. የጥናቱ መሰረታዊ ሀተታ (Statement of the Problem)
እንደ “UDHR“(1948) ክፍል 3 አንቀፅ 21 ድንጋጌ መሠረት የመንግሥት ሥልጣን መሰረቱ የሕዝቡ ፈቃድ ይሆናል፤ይህ ፈቃድም በየተወሰነ ጊዜ በሚደረግ እውነተኛ ምርጫ አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን ምርጫም በምስጢራዊ የድምጽ አሰጣጥ ወይም መሰል ነፃ ሂደት ሁሉን አቀፍና እኩል አሳታፊ በሆነ መንገድ የሚካሄድ ይሆናል።
በተመሳሳይ ሁኔታ “ICCPR“ (1966)አንቀጽ 25 ድንጋጌ መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ በዘር፣ቀለም፣ፆታ፣ቋንቋ፣ሐይማኖት፣የፖለቲካ ወይም የሌላ አመለካከት፣ብሔር፣ወይም ማሕበራዊ ዳራ፣ሐብት፣ትውልድ ወይም ሌላ አቋም” ላይ ተመስርቶ ምንም አይነት አድልዎ ሳይደረግበት እንዲሁም ምክንያታዊነት በሌላቸው አላስፈላጊ ክልከላዎች ሳቢያ “በእውነተኛ ምርጫዎች [መምረጥና መመረጥ]”ከመሳተፍ ሳይከለከል እንዲሳተፍ የሚያስችለው ዕድል ሊፈጠርለትና የመሳተፍ መብት ሊሰጠው ይገባል ይላል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 38 ድንጋጌ በ“UDHR“ ላይ የተቀመጠውን የፍትሀዊና የነፃ ምርጫ መርሆዎች ከማካተቱም ሌላ፣ይህ መብት በሥራ ላይ ሲውልም ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ለምሳሌ ያህል ከ“UDHR“ መንፈስ ጋራ በሚጣጣም መልኩ እንዲተገበርና ትርጓሜም እንዲሰጠው ጭምር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንገስት አንቀጽ 13 ያሳስባል።
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ይህንን ቢደነግግም በሌላ በኩል ግን የምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እነኝህን ዓለም አቀፍ የፍትሀዊና ነፃ ምርጫ መርሆዎች የሚጥስ ሆኖ እናገኘዋለን፤ለምሳሌ ያህል በአንድ ቦታ ከአንድ በላይ የምርጫ ጣቢያ እንዳይከፈት የሚከለክለውንና በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከ 1,500 በላይ መራጮች እንዳይመዘገቡ የሚያግደውን ድንጋጌዎች መጥቀስ ይቻላል።
ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ያላቸውን የስራ እንቅስቃሴ፣ የምርጫ ጣቢያዎች የስራ ሁኔታ፣ ከአለማቀፍ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ መመዘኛዎች እና ከአለማቀፍ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ ድንጋጌዎች፣ ከህገ መንግስቱ እና ከምርጫ ህጉ አንፃር ያሉበትን ሁኔታ ለመገምገምና እና በምርጫ ቦርድ አዲስ የተከፈቱ 32 ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ያሉበትን ደረጃ ለመቃኘት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለመመዘን በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ጥናት ማድረግ አስፈላጊ ሁኖ ተገኝቷል፡፡
2. የጥናቱ ዋና ዓላማ
የጥናቱ አላማ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ (pre-election process) አካል የሆነውን የመራጮች ምዛገባ ሂደት (voter registration) ከነፃና ፍትሀዊ ምርጫ መርሆዎች አኳያ ምን ያህል ይጣጣማል የሚለውን ጉዳይ በጥናት ማረጋገጥ ሲሆን በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ሁኔታ እና አጠቃላይ የቅድመ ምርጫውን ሂደት የሚዳስስ ጥናት ነው፡፡
2.1. የጥናቱ ዝርዝር ዓላማዎች
የዚህ ጥናት ዝርዝር ዓላማዎች፡-
 ነባር እና አዲስ (ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም ጀምሮ የተከፈቱ) የምርጫ ጣቢያዎችን ያሉበትን ሁኔታ ማዳሰስ፣
 በመራጮች ምዝገባ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መቃኘት፣
 የምርጫ ሂደቱ (pre-election process) ከነፃና ፍትሀዊ ምርጫ መርሆዎች አኳያ ያለበትን ሁኔታ መገምገም፡፡
3. የጥናቱ አስፈላጊነት (Significance of the Study)
ይህ የዳሰሳ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ተግዳሮቶችን የሚዳስስ ሲሆን የጥናት ውጤቱ ለተለያዩ የባለ ድርሻ አካላት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከጥናቱ ግኝት ሊጠቀሙ የሚችሉ ሲሆን ማህበረሰቡም፣የምርጫ ታዛቢዎችም፣የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እና ታዛቢዎችም ከጥናቱ ውጤት ስለ መራጮች ምዛገባ ሂደት(voter registration) ያለበትን ሁኔታ  ሊገነዘብ ይችላል፡፡
4. የጥናቱ ወሰን (Scope of the Study)
ይህ ጥናት በዋነኛነት የሚያተኩረው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ የሚያካትት ሲሆን በምርጫ ጣቢያዎች እና በምዝገባ ሂደቱ የታዩ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት ነው፡፡
5. የጥናቱ የምርምር ዘዴዎች
ይህ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የሚታዩ የምርጫ ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት፤ ቅሬታዎች እና አጠቃላይ ተግዳሮቶች ለመለየት ታስቦ የተደረገ ሳይንሳዊ ጥናት ነው፡፡ ይህ ምርምር የምርጫ ወቅታዊ ሁኔታውን ለማብራራት የሚያግዘውን የገላጭ ምርምር (Descriptive research) አይነት ተጠቅሟል፡፡ የገላጭ ምርምር የዳሰሳ ጥናት መንገድን በመጠቀም ጥናቱ ተጠናቅሯል፡፡
ጥናቱ ዓይነታዊ (Qualitative) የምርምር ዘዴ የተጠቀመ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ የምርጫ ምዝገባ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት፤ ቅሬታዎች እና አጠቃላይ ተግዳሮቶች ለመለየት ተሞክሯል፡፡ ጥናቱ ሁለት አይነት የመረጃ ምንጮችን ማለትም ቀዳማይ የመረጃ ምንጭ (primary source) እና ካልዓይ የመረጃ ምንጭ (secondary sources) አገልግሎት ላይ አውሏል፡፡
5.1. የናሙና አወሳሰድ እና አመራረጥ ስልት
ይህ ምርምር ከተጠያቂዎች ግልፅ፣ ዝርዝር፣ ተጨባጭ፣ ተገቢ እና ወቅታዊ መረጃን ይፈልጋል፡፡ ጥናቱ የምርጫ ምዝገባ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን፤ የምርጫ ምዝገባ  ሰራተኞችን እና በምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ የፀጥታ አካላትን ለመምረጥ ወካይነትን (representativeness) እና የመረጃ ሁሉን አካታችነት  (generalizability of the data) መርሆዎች በመከተል ሁሉን አቀፍ እና ተጨባጭ መረጃ ለመሰብሰብ ከተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች ናሙናዎችን ወስዷል፡፡ ጥናቱ የሁሉንም ክፍለከተሞች አደረጃጀት ያማከለ በመሆኑ የስብጥር ናሙና (stratified sampling) በመጠቀም ክፍለ ከተሞች በሁለት ክፍል ማለትም ውስጣዊ (inner) እና ውጫዊ (Peripherian) ደረጃ በሚል እንዲከፈሉ ተደረጓል፡፡
የጥናት ቡድኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና ለመተንትን ከሚያዚያ 20/2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 04/2013 ዓ.ም የተጠቀመ ሲሆን መረጃ የተሰበሰበባቸው ክፍለ-ከተሞች ብዛት ዘጠኝ ሲሆኑ እነርሱም ቦሌ፣ የካ፣ኮልፌ፣ ጉለሌ፣ ንፋስ ስልክ፣ አራዳ፣ አዲስ ከተማ፣ ልደታና አቃቂ ክፍለ ከተሞች ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ አንደ ሺ ስድስት መቶ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የጥናት ቡድኑ መቶ ነባር ምርጫ ጣቢያዎችን እና ከሚያዚያ 15/2013ዓ.ም. በኃላ በምርጫ ቦርድ የተከፈቱ ሰላሳ ሁለት ንኡስ ጣቢያወችን ያካተተ ሲሆን በአጠቃላይ መቶ ሰላሳ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች አካቷል፡፡ ምንም እንኳን በዓይነታዊ (Qualitative) የምርምር ዘዴ ወካይነት የጥናት ዘዴው ባህሪ ባይሆንም ጥናቱ ከአስር ፐርሰንት በላይ ናሙና ተወስዷል፤
በዚህ ጥናት የተሳረፉ የማህበረሰብ ክፍሎች የምርጫ አገልግሎት ተጠቃሚዎች፣ በምርጫ ጣቢያው አካባቢ ያሉትን ነዋሪዎች  እና አገልግሎት በሚሰጥበት ምርጫ ጣቢያ የሚገኙ የፀጥታ አካላት(ፖሊሶች እና ጥበቃዎች) ናቸው፡፡
5.2. የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች
ጥናቱ የቅድመ ምርጫ አገልግሎት አሰጣጥን፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ሁኔታን እና የመራጮችን ቅሬታዎች በተመለከተ ትክክለኛ፣ ወቅታዊ እና ታማኝ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚከተሉትን የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች አገልግሎት ላይ ውለዋል፤
የጥናት ቡድኑ በቀጥታ በአካል በመገኘት ሁኔታዎቹን የመረመረ ሲሆን የተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ተጠቅሟል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ምልከታ እና በምስል መረጃዎችን(ቪዲዮዎች) የተደገፈ ቃለ መጠይቅ ሲሆን በምርጫ ጣቢያወች ላይ የተቀመጡ ምልክቶችና ፅሁፎች በጥናቱ ትንተና ያልተካተቱ ማስረጃዎችም በአባሪነት ቀርበዋል፡፡
5.3. የመረጃ ትንተና ዘዴና አቀራረብ
የመረጃው ወጥነት እና ምሉዕነት በመረጃ ሰብሳቢዎች ከተረጋገጠ በኋላ ከቃለመጠይቅ እና ከምልከታ የተገኘው መረጃ ወደ ፅሁፍ ተቀይሯል፡፡ ከዚያም ፅሁፉን በተደጋጋሚ በማንበብ፤ ኮድ በማድረግ እና ዋና ዋና ጭብጦችን በመለየት ለመተንተን ተሞክሯል፡፡ በመቀጠልም ንዑሳን ጭብጦችን ከዋና ጭብጥ ስር በማደራጀት ትንታኔ የመስጠት ተግባር ተከናውኗል፡፡ የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጠናከር በእያንዳንዱ የጥናት ጥያቄዎች ወይንም ግቦች ስር ከባለ ጉዳዬች፣ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከፀጥታ ኃይሎች፣ ከምልከታ፣ የተገኙ መረጃዎች በአይነታዊ ሃተታዎች አብረው ቀርበዋል፡፡ የጥናቱን መረጃ በመጠቀም የጥናቱ ውጤቶች በተለያዩ ክፍሎች ተከፋፈለው ቀርበዋል፡፡
5.4. የጥናቱ ተዓማኒነት ማረጋገጫ መንገዶች
የአጥኝ ቡድኑ የሚከተሉትን የጥናቱ ተዓማኒነት እና ትክክለኛነት ማረጋገጫ መንገዶችን ተጠቅሟል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን እና የጥናቱን አጠቃላይ እቅድ በባለሙያ ተተችቷል፤ ዋናው ጥናት ከመጀመሩ በፊት ቅድመ ጥናት ተካሂዷል፤ በመቀጠልም ሳይንሳዊ ተቀባይነት ያላቸውን የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ ተሰብስቧል፡፡
ተዓማኒነት፡ የጥናቱን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ በተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች የተሰበሰቡት መረጃዎች እና ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን በአንድ ላይ በማቀናጀት የመረጃውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የመረጃ ሰብሳቢዎች የትምህርት ደረጃ ጥናቱ ከሚጠብቀው የትምህርት ደረጃ በላይ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጥናቱ የመጀመሪያ ትንታኔ በአጥኝ ቡድኑ  በጋራ ተመርምሯል፤ እንዲሁም የመጀመሪያ የጥናት ትንታኔ በአንድ የከፍተኛ ተመራማሪ እንዲገመገም ተደርጓል፡፡
5.5.የጥናቱ ምስጢራዊነት እና ሌሎች የስነ-ምግባር ጉዳዮች
የመሳተፍ ነፃነት፡ መረጃ በመስጠት በጥናቱ የተሳተፉ አካላት በጥናቱ ላይ የመሳተፍ መብታቸው እንዲከበር ተደርጓል፡፡ የጥናቱ ምንነት እና አጠቃላይ አላማ ማብራሪያ ከተደረገላቸው በኋላ ፈቀደኝነታቸውን ተጠይቀው ፈቃደኛ የሆኑት ብቻ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡
ምስጢራዊነት፡ የጥናቱን ምስጥራዊነት በተመለከተም፡ መረጃ በመስጠት በጥናቱ የተሳተፉ አካላት የሚሰጡትን መረጃ ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ እንደሚሆን መረጃው በተሰበሰበበት ጊዜ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከጥናቱ አገልግሎት ውጭ ምንም አይነት መረጃ ለማንም ተላልፎ እንደማይሰጥ ተነግሯቸዋል፡፡ ይህንንም ለመጠበቅ መረጃው በሚተነተንበት ወቅት የተጠያቂዎች ስም አልተጠቀሰም፡፡
6. በዳሰሳ ጥናቱ የተደረሰባቸው ግኝቶች
የጥናት ቡድኑ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የሚከተሉትን የምርምር ግኝቶች ለማግኘት ችሏል፡፡ የምርምሩ ግኝቶች በፅንሰ ሀሳብ ተዛማጅነት በአራት ክፍሎች የተከፈሉ ሲሆን በእያንዳንዱ ክፍል ስር የምርምር ግኝቶች በአስረጅነት ቀርበዋል፡፡
6.1. የምርጫ  አስተዳደር ድክመቶች
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች የስራ ትጋት እና የስራ ግብረ-ገብነት እንደሚጎላቸው የጥናት ውጤቱ ያመለክታል፡፡ የሚከተሉት የጥናት ግኝቶች ከብዙ በጥቂት እንደ አስረጅነት የቀረቡ ናቸው
 በአንድ ምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈፃሚዎች ባንክ ቤት ሄደዋል በማለት የምርጫ አስፈጻሚ ያልሆነች ህፃን ልጅ ‘’ካርድ አንዴት አንደሚሰጥ አሳይተውኝ ነበር አሁን ጠፋኝ’’ እያለች ስታስተናግድ ነበር፡፡
 በ16 ምርጫ ጣቢያዎች ካርድ ያላለቀ ቢሆንም የምርጫ አስተባባሪዎች ጣቢያዎችን ዘግተዋል፤ ከምክንያቶች ውስጥ ደሞዝ አልተከፈለንም የሚለው አንዱ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለጥበቃ ሰራተኞች ‘’ዛሬ እንደማንገባ ተናገር‘’ የሚል መልዕክትና የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደነገሩት እና አብዛኛው የምርጫ አስፈፃሚ ያለ ምንም ምክንያት እንደሚቀሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡
 የምርጫ አስፈፃሚዎች በሰዓቱ እንደማይገቡና/አርፍደው ይገቡና አምስት ሰዓት ሳይሞላ መልሰው ዘግተው ይወጣሉ(ቀጨኔ መዳኅኒዓለም ቤ/ክርስቲያን ፊት ለፊት)፤
 የምርጫ አስፈፃሚዎች እስከ 8:24 ድረስ ቢሮ እንደማይገቡ የቃለ መጠየቅ ተሳታፊዎች አስረድተዋል(ንፋስ ስልክ ክ/ከተማ፣ ጀሞ)
በአጠቃላይ የቀረቡት ሃሳቦች እንደሚያስረዱት ከሆነ የምርጫ አስፈፃሚዎች የሚጠበቅባቸውን የስራ ኃላፊነት እንዳልተወጡ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመላመል፣ ስለ ምርጫው ያላቸው ግንዛቤ፣ በምርጫው ላይ ገለልተኛ አለመሆናቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች ትጋት ማነስ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ዳሩ ግን ይህ ሁሉ ችግር የሚያጠነጥነው ምርጫውን በሚያስተዳድረው በምርጫ ቦርድ ላይ ነው፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ ይውል ዘንድ ምርጫ ቦርድ በየጊዜው ህዝቡ ምርጫ ካርድ እንዲወስድ በመገናኛ ብዙኃን ይለፍፋል መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን የተለየ ነው፡፡ መራጮች ምርጫ ካርድ መውሰድ አልቻሉም፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የመራጮችን የምዝገባ ሂደት ተዘዋውረው ለመገምገም ምርጫ ቦርድ ምቹ ሁኔታን አለመፍጠሩ ችግሩ በዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል፡፡
6.2. የምርጫ ጣቢያ- ነክ ጉዳዬች
A. የምርጫ ጣቢያዎች የምዝገባ ሂደት እና ያሉበት ሁኔታ
 ለምሳሌ የቀረቡ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ጣቢያው ያለበት ሁኔታ
1 ብዛት ያላቸው ናቸው በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ተመዝጋቢ እየመጣ የምርጫ አስፈፃሚዎች 1500 መዝግበው የተዘጉ ናቸው (ብዛታቸው 43)
2 አያት ጸበል አካባቢ በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ረዘም ላለ ግዜ 1,500 ሞልቶብናል በማለት ለምዝገባ የሚመጡ ተመዝጋቢዎችን ይመልሳሉ፡፡
3 ጉለሌ ምርጫ ጣቢያ 16/17 በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ውስጥ ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተዋል
4 ኮልፌ፣ ምርጫ ጣቢያ 11
 በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ለብዙ ቀናት የምርጫ አስፈፃሚዎች 1500 ሳይመዘግቡ ዘግተዋል
5 እየሱስ ቁጥር 2 የጋራመኖሪያቤት፤ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ
ወረዳ 1 ምርጫ ጣቢያ 10 በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ለብዙ ቀናት የምርጫ አስፈፃሚዎች በተጋነነ መልኩ ዘግይተው ወደ ስራ ይገባሉ፤ ከስራም ያለ ስዓቱ ቀድመው ይወጣሉ
ከላይ ባለው ሰንጠረዥ መረዳት እንደሚቻለው በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርጫ ጣቢያዎች 1500 የምርጫ ካርድ ሰጥተው የዘጉ ሲሆን በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች የምርጫ ካርድ እንዳልወሰዱ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ 1500 ሳይመዘግቡ የተዘጉ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች ያለ ስዓቱ እንደሚዘጉም የጥናት ውጤቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱ እንደነበር የጥናት ቡድኑ በምልከታው አመላቷል፤ይህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ካወጣው ህግ ጋር የሚፃረር ነው፡፡
ከላይ በሰንጠረዡ ማየት እንደሚቻለው በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ተመዝጋቢ እየመጣ የምርጫ አስፈፃሚዎች 1500 መዝግበው የተዘጉ ናቸው፡፡ ከላይ እንደቀረበው መረጃ 43 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች እንደተዘጉ ተረጋግጧል፤ ይህ ጥናት 12ፕርሰንት የሚሆነውን የምርጫ ክልል ይወክላል ብንል፤ በጥናቱ ያልተካተቱ የምርጫ ጣቢያዎችን ግምት ውስጥ ካስገባን ወደ 358 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች 1500 መዝግበው ሊዘጉ እንደሚችሉ ከጥናቱ መረዳት ይቻላል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ አዲስ ከተከፈቱ 32 የምርጫ ጣቢያዎች ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአንድ የምርጫ ጣቢያ 1500 ብቻ እንዲመዘገብ በሚያዘው የምርጫ ህግ ስሌት ሲታሰብ እንኳን 32 የምርጫ ጣቢያዎች ሙሉ በሙሉ ቢከፈቱ ሊመዘገብ የሚችለው አጠቃላይ የሰዎች ብዛት 48000 ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ ካልተመዘገበው የማህበረሰብ ቁጥር አንፃር ሲቃኝ በጣም ትንሽ ቁጥር ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ደንብን ያልተከተሉ እንደነበር የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል፡፡ የሚከተለው ሰንጠረዥ ለአስረጅነት የሚሆኑ መረጃዎች ያሳያል፡፡
ተ.ቁ የምርጫ ጣቢያው ስም የምርጫ ጣቢያው ልዩ ባህሪ
1 አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 9 ኮዬ ልማት በፍቅር ከብሎክ 739-762 ኮንዶሚኒየም ምርጫ ጣቢያ 26/27-700 ቤት 3 የሀሰት ምስክር እያቀረቡ የምርጫ ካርድ እንደሚያወጡ ጥቆማ ደርሶናል
2 ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 አባ ሻሜ ምርጫ ጣቢያ ቁማር ቤት አጠገብ ያለ ምርጫ ጣቢያ ነው
3 የካ ክ/ከተማ ወረዳ 3 አስተዳደር የቀበሌ 18 (1) ምርጫ ጣቢያ ሀ ልዩ ቦታ 18 ቀበሌ መዝናኛ ክበብ ምርጫ ጣቢያው መጠጥ ቤት ውስጥ ነው
4 አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ምርጫ ጣቢያ 14 ጄሪ ኬክ ቤት ሄዳችሁ ውሰዱ የሚል ማስታወቂያ ተለጥፏል
5 49 አደባባይ ምርጫ ጣቢያ ተመዝጋቢ የለም ብለው ካርዶቹን ይዘው ሌላ ቦታ ሄደዋል
ከሰንጠረዡ ለመረዳት እንደሚቻለው የምርጫ አስፈፃሚዎች ተመዝጋቢ የለም ብለው ካርዶቹን ይዘው ሌላ ቦታ እንደሚሄዱ የጥናት ቡድኑ አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የምርጫ ካርድ ሊሰጥባቸው በማይችሉ ቦታዎች ላይ ተመዝጋቢዎች ሂደው መወሰድ እንዳለባቸው በማስታወቂያ እንደሚገለፅላቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታ(መጠጥ/ቁማር ቤት) መሆናቸው ከምርጫ ህጉ ጋር የሚፃረር እንደሆነ በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ካርድ መውሰድ የማይገባቸው(ምናልባት) ከሌላ አካባቢ የመጡ ዜጎች የሀሰት ምስክር በማቅረብ የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱ በጥናቱ የተረጋፈጠ ጉዳይ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጥናት ቡድኑ ባደረገው ምልከታ መሰረት አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት አካባቢ ለምርጫ ምዝገባ ለሚመጡ ዜጎች ምቹ እንዳልሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የሚከተሉት የጥናት ግኝቶች ከብዙ በጥቂት እንደ አስረጅነት የቀረቡ ናቸው፡፡
 በግለሰብ መኖሪያ ቤት የተከፈተ የምርጫ ጣቢያ
 በተጨማሪም አንድ የምርጫ ጣቢያ ጫት በሚቃምበት አካባቢ የተከበበ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በእንዲህ አይነት ምቹ ባላሆኑ ቦታዎች የተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ነፃ ሁነው እንዳይንቀሳቀሱ እና የምርጫ ካርድ እንዳይወስዱ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ ለመገመት አያዳግትም፡፡
B. የምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከነዋሪው ህዝብ ጋር የማይጣጣሙ እና ቁጥራቸው አነስተኛ እንደነበር ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የሚከተሉት የጥናት ግኝቶች ከብዙ በጥቂት እንደ አስረጅነት የቀረቡ ናቸው
 በቦሌ እና በየካ በተለይም በኮንደምኒየሞች ውስጥ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች አነስተኛ ከመሆናቸውም በላይ የቦታ ርቀታቸውም በጣም ሠፊ ሲሆን ከነዋሪዎች ጋር አለመመጣጠን እጅጉን መኖሩን የጥናት ቡድኑ ተመልክቷል
 በሌላ ሁኔታ በአራዳ፣ በአዲስ ከተማ እና ልደታ ክፍለ ከተሞች የምርጫ ጣቢያዎች በአንድ ቤት ውስጥ ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች አነደሚገኙ የጥናት ቡድኑ ተመልክቷል፡፡
 የምርጫ ጣቢያዎች በአብዛኛው ምንም አይነት መለያ የሌላቸው ሲሆን  የቦታ አቀማመጣቸውም ለመራጮች ምቹና ተደራሽ አለመሆናቸውን ተረጋግጧል፡፡
 ቀጨኔ መዳኅኒዓለም ቤ/ክተ ክርስቲያን  ፊት ለፊት ስያሜ የሌለው ምርጫ ጣቢያ ታይቷል፤
 ኮንዶሚኒየሞች(ጀሞ፣የካ፣ አባዶ፣አራብሳ፣ኃይሌ ጋርመንት፣ገላን፣ቡልቡላ፣ ቱሉዲምቱ፣ ኮየ ፈቸ) እንዳልተመዘገቡ ቅሬታ አለ
ከላይ እንደተጠቀሰው አብዛኛዎች ኮንዶሚኒየሞች አባውራ እና እማውራ ሲኖራቸው ለነዚህ አባውራዎች እና እማውራዎች የተመደበው የምርጫ ጣቢያ በቂ አለመሆኑ ታይቷል፡፡ ከምርጫው በፊት የህዝብ ቆጠራ አለመካሄዱ ለእንዲህ አይነት ችግሮች ምክንያት ሲሆን የምርጫ ቦርድ ትክክለኛ ግምታዊ ስሌት አለመጠሙ የችግሩን ስፋት አግዝፎታል፤
የምርጫ ቦርድ የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ለማህበረሰቡ ተገቢውን መረጃ ማቅረብ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ የመረጃ እጥረት ግን የመራጮችን የምዝገባ ሂደት አወሳስቦታል፤አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችም እንዳይታወቁ አድርጓታል፡፡
በውስጣዊ ወይም በነባር ክፍለ ከተሞች ውስጥ ብዙ ነዋሪ በሌለበት ቦታ በርካታ ምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ውጫዊ/ማስፋፊያ በሆኑ ክፍለ ከተሞች ለምሳሌ (በየካ፣ቦሌ፣ አቃቂ) በቂ ምርጫ ጣቢያ እንደሌለ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች በፖለቲካ ግፊት ምክንያት በቡድን ከኦሮሚያ ክልል እየመጡ የምርጫ ካርድ ቀድመው ስለወሰዱ በነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ማግኘት አልቻሉም፡፡
የጥናቱ የምልከታ ውጤት እንደሚያሳየው የኮንደሚኒየም ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ለመውሰድ በጣም ሲቸገሩ አጥኝ ቡድኑ ተመልክቷል፤በተለይም ኮታ ሞልቷል ተብለው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲንከራተቱና በስተመጨረሻም አምስት ስድስት ቦታ ደርሰው ተስፋ ቆርጠው የተመለሱ እንዳሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡
6.3. የምርጫ  ካርድ ከሚወስዱ ግለሰቦች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዬች
የመራጮነት ካርድ ከሚወስዱ ግለሰቦች ማንነት ጋር በተያያዘ በርካት ችግሮች የታዩ ሲሆን ለአስረጅነት የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቃለ መጠየቁ የተሳተፈ ግለሰብ  የሚከተለውን ብለዋል፡
 ከአምቦ/ከሰንዳፋ የመጡ ዜጎች ካርድ ያወጣሉ(ንፋስ ስልክ)የቪዲዬ ማስረጃ
በተጨማሪም ይህን ጉዳዩን አስመልክቶ ሌላው ተሳታፊ እንዲህ ብላለች፡-
 ከብሄር ማንነት በተጨማሪ የእምነት ማንነትም የምርጫ ካርድ በመወሰዱ ሂደት አስተዋፅዖ ነበረው፤ የሙስሊም እና የኦሮሞ ማንነት የሌላቸው ዜጎችን አናሰተናግድም እያሉ እነደነበር ከአካባቢው ፖሊስ የተገኘ የድምጽ ሪኮርድ ያሳያል(አባሻሜ የተባለ ጣቢያ፣ቦሌ ቡልቡላ)፣የቪዲዬ ማስረጃ
በተመሳሳይ ሁኔታ በጥናቱ የተሳተፉ አካላት የሚከተሉትን ብለዋል፡
 የምርጫ ካርድ የሚሰጡ መዝጋቢዎች ‘’አማርኛ አንችልም በኦሮምኛ አናግሩን’’ በማለት አማርኛ መናገር የማይችሉትን ካርድ ሳይሰጡ መልሰዋቸዋል(ጎሮ በተባለ ቦታ)፣
 ሌላው የክልል መታዎቂያ አንቀበልም የሚሉ ምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ የኦሮሚያ መታወቂያ የያዙ አየተጠሩ እንደሚሰጣቸው ለማረጋገጥ ተችሏል፤ መዝጋቢዎች ከብሄር ማንነት ጋር በተያያዘ መታወቂያ እያዩ የአማራ ክልል መታወቂያ ከሆነ ይመልሳሉ፣የኦሮሚያ ክልል መታወቂያ ከሆነ ደግሞ የምርጫ ካርድ ይሰጣሉ(መብራት ኃይል አካባቢ፤አያት ጸበል ኮንዶሚኒየም)፣
 በሶስት ምስክር የምርጫ ካርድ አንሰጥም ብለው ተመዝጋቢ አባረዋል(መብራት ኃይል አካባቢ)፣
 መዝጋቢዎች ካርድ ጨርሠው፣ በር ዘግተው የስም ዝርዝር እያዩ ምርጫ ካርድ እያዘጋጁ እንደነበር የጥናት ቡድኑ ተመልክቷል(ጣፎ ኮንደሚኒየም 3ኛ በር)፣
 ጣቢያዎች ዝግ በሆኑበት በአርበኞች በዓል የምርጫ ጣቢያውን ከፍተው ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑ ግለሰቦችን ብቻ ሲያስተናግዱ እንደነበር በምልከታ ሂደቱ ለመረዳት ተችሏል (ቦሌ አራብሳ ቤቶች ልማት ፕሮጄክት ግቢ)፤
እንደ ጥናቱ ተሳታፊዎች  ገለፃ የምርጫ ካርድ የሚታደለው የዜጎችን ማንነት መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሆነ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡
6.4. መራጮች የምርጫ ካርድ መወሰድ አለመቻላቸው
የጥናት ቡድኑ ባደረጋቸው ቃለ-መጠይቅ አብዛኛው ማህበረሰብ የምርጫ ካርድ እንዳልወሰደ ለመረዳት ተችሏል፡፡ እንደ አስረጅነት የቀረቡ የጥናት ግኝቶችን እንመልከት
 አራት አምስት ቀናት ተመላልሰን ካርድ የለም ተባልን፤ የምርጫ አስፈሚዎች አስር ስዓት ላይ ዘግተው ይወጣሉ(ምርጫ ጣቢያ 14)፣
 ብዙ ሰው የምርጫ ካርድ አልወሰደም፤ ሂደው አጣን ብለው ሲመለሱ አያለሁ(ምርጫ ጣቢያ አያት ቁጥር አንድ)፣
 አንዳንድ ግለሰቦች በግላቸው በርካታ የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱ ታውኳል፤
 ዜጎች የክፍለ-ሀገር መታወቂያ ይዘው፤ ከስድስት ዓመት በላይ አዲስ አበባ እየኖሩ፣አስመስክረው የምርጫ ካርድ ማውጣት አልቻሉም(አያት)
ከላይ ከቀረቡት የቃለ መጠይቅ ምላሾች መረዳት እነደሚቻለው ዜጎች የምርጫ ካርድ ለመወሰድ እንዳልቻሉ ለመረዳት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በርካታ የምርጫ ካርዶች ያላግባብ ማውጣታቸው፣ ከአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች እየመጡ ሰዎች ካርድ መወሰዳቸው፣ የምርጫ ቦርድ ከነዋሪዎች ጋር ተመጣጣኝነት ያለው የምርጫ ጣቢያዎችን አለመክፈቱ፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች የስራ ትጋት ማነስ ለተፈጠሩ ችግሮች መንስኤዎች እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡
7. ማጠቃለያ እና መደምደሚያ
የጥናቱ አላማ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ (pre-election process) አካል የሆነውን የመራጮች ምዛገባ ሂደት (voter registration) ከነፃና ፍትሀዊ ምርጫ መርሆዎች አኳያ ምን ያህል ይጣጣማል የሚለውን ጉዳይ በጥናት ማረጋገጥ ሲሆን በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ሁኔታ እና አጠቃላይ የቅድመ ምርጫውን ሂደት የሚዳስስ ጥናት ነው፡፡
ጥናቱ ዓይነታዊ (Qualitative) የምርምር ዘዴ የተጠቀመ ሲሆን ጥናቱ የሁሉንም ክፍለከተሞች አደረጃጀት ያማከለ በመሆኑ የስብጥር ናሙና (stratified sampling) በመጠቀም ክፍለ ከተሞች በሁለት ክፍል ማለትም ውስጣዊ (inner) እና ውጫዊ (Peripherian) ደረጃ በሚል እንዲከፈሉ አድርጓል፡፡የጥናት ቡድኑ በቀጥታ በአካል በመገኘት ሁኔታዎቹን የመረመረ ሲሆን የተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ተጠቅሟል፡፡ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ምልከታ እና በምስል መረጃዎችን(ቪዲዮዎች) የተደገፈ ቃለ መጠይቅ ሲሆን በምርጫ ጣቢያወች ላይ የተቀመጡ ምልክቶችና ፅሁፎች በጥናቱ ትንተና ያልተካተቱ ማስረጃዎችም በአባሪነት ቀርበዋል፡፡ የሚከተሉት ግኝቶች የጥናቱ ዋና ዋና መደምደሚያዎች ናቸው፡፡
• የምርጫ አስፈፃሚዎች የሚጠበቅባቸውን የስራ ኃላፊነት እንዳልተወጡ ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመላመል፣ ስለ ምርጫው ያላቸው ግንዛቤ፣ በምርጫው ላይ ገለልተኛ አለመሆናቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች ትጋት ማነስ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ሁሉ ችግር የሚያጠነጥነው ምርጫውን በሚያስተዳድረው በምርጫ ቦርድ ላይ ነው፡፡ ለሚዲያ ፍጆታ ይውል ዘንድ ምርጫ ቦርድ በየጊዜው ህዝቡ ምርጫ ካርድ እንዲወስድ በመገናኛ ብዙኃን ይለፍፋል መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን የተለየ ነው፡፡ መራጮች ምርጫ ካርድ መውሰድ አልቻሉም፡፡
• በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርጫ ጣቢያዎች 1500 የምርጫ ካርድ ሰጥተው የዘጉ ሲሆን በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች የምርጫ ካርድ እንዳልወሰዱ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ 1500 ሳይመዘግቡ የተዘጉ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች ያለ ስዓቱ እንደሚዘጉም የጥናት ውጤቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱ እንደነበር የጥናት ቡድኑ በምልከታው አመላክቷል፤ይህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ካወጣው ህግ ጋር የሚፃረር ነው፡፡
• የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታ(መጠጥ/ቁማር ቤት) መሆናቸው ከምርጫ ህጉ ጋር የሚፃረር እንደሆነ በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡
• በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከነዋሪው ህዝብ ጋር የማይጣጣሙ እና ቁጥራቸው አነስተኛ እንደነበር ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በውስጣዊ ወይም በነባር ክፍለ ከተሞች ውስጥ ብዙ ነዋሪ በሌለበት ቦታ በርካታ ምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን ውጫዊ/ማስፋፊያ በሆኑ ክፍለ ከተሞች በተለይ በኮነደሚኒየሞች የሚገኙ ዜጎች ለምሳሌ (በየካ፣ቦሌ፣ አቃቂ) በቂ ምርጫ ጣቢያ እንደሌለ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ላይ በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች በፖለቲካ ግፊት ምክንያት በቡድን ከኦሮሚያ ክልል እየመጡ የምርጫ ካርድ ቀድመው ስለወሰዱ በነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ማግኘት አልቻሉም፡፡
• ከብሄር እና የእምነት ማንነትም ጋር በተያያዘ የምርጫ ካርድ እንደሚታደል ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ መራጩ ህዝብ በማንነቱ እየተለየ የምርጫ ካርድ እንደሚታደል ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምርጫ ካርድ መውሰድ የማይገባቸው(ምናልባት) ከሌላ አካባቢ የመጡ ዜጎች የሀሰት ምስክር በማቅረብ የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱ በጥናቱ የተረጋፈጠ ጉዳይ ነው፡፡ የምርጫ ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እና እኩል አሳታፊ መሆን እንዳለበት የተቀመጠ ቢሆንም ከላይ እንደተመለከትነው የምርጫ ጣቢያዎች የአሰራር ሁኔታ ከዚህ መርህ በተቃራኒ መልኩ እየሰሩ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን፡፡
• አንዳንድ ሰዎች በርካታ የምርጫ ካርዶች ያላግባብ ማውጣታቸው፣ ከአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች እየመጡ ሰዎች ካርድ መወሰዳቸው፣ የምርጫ ቦርድ ከነዋሪዎች ጋር ተመጣጣኝነት ያለው የምርጫ ጣቢያዎችን አለመክፈቱ የችግሮች መንስኤዎች እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል፡፡
• የምርጫ ቦርድ አቋቋምኳቸው ያላቸው ንኡስ ጣቢያዎች ግልጽ አድራሻ አለመኖራቸው ፣በፍለጋ ቦታዎች አለመገኘታቸው፣ በአንድ  ቦታ ላይ በተለይም በአንድ ቤት በርካታ ጣቢያዎች መገኘት፣በተከለከሉ ቦታዎች ማለትም በመጠጥ ቤቶች፣ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣  በጫት ቤቶች ላይ ምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት ከምርጫ ህጉ በተቃራኒ ያሉ አሰራሮች እንደሆኑ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
• ከላይ ከተዘረዘሩት ግኝቶች አንጻር የ6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት አንፃር ሲፈተሸ ነፃና ፍትሀዊነት የሚጎድለው፤ የቅድመ ምርጫ መራጮች ምዝገባ አንፃር መርሆዎች ያልተከተለ እና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡
• ምንም እንኳን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ከህዝባችን ጋር በመሆን የምርጫውን ሂደት በከፍተኛ ትኩረት በመከታተል የምርጫ ሂደቱ ፍትሀዊ እንዲሆን ትግላችንን
እንቀጥላለን፡፡
8. የመፍትሄ ሃሳብ
ከቀረበው ዝርዝር ጥናት አንጻር ጥናቱ የሚከተሉትን የመፍትሄ ሀሳቦች ያቀርባል፡፡
• የምርጫ ጣቢያዎችን ከማብዛት ይልቅ በአንድ የምርጫ ጣቢያ 1500 የምርጫ ካርድ ብቻ እንዲመዘግብ የተቀመጠው ቁጥር ተሰርዞ የቁጥሩ ወሰን ሊጨምር ይገባል፤
• የምርጫ ካርድ ያልወሰዱ ዜጎች ካርድ ያገኙ ዘንድ የምርጮች የምዝገባ ካርድ ማውጫ ጊዜ መራዘም እንዳለበት እንጠይቃለን፤
• በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ያልሆኑ ተመዝጋቢዎች በርካታ የምርጫ  ካርድ ስለወሰዱ ምርጫ ቦርድ ይህንን ጉዳይ አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ እናሳንባለን፤
• በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ውስጥ የተካሄደው የምዝገባ ሂደት በርካታ ችግሮች ስላሉበት የምርጫ ምዝገባ ሂደቱ በምርጫ ቦርድ እንዲጣራ እንጠይቃለን፤
• የመራጮች ምዝገባ ሂደት ግልፅነት ስለሚጎድለው እና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ስለሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ ታዛቢዎች የምዝገባ ሂደቱን እንዲያጣሩ፤
• የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታ በምርጫ ህጉ መሰረት እንዲሆን ምክረ-ሀሳብ ማቅረብ እንወዳለን፤
• የምርጫ አስፈፃሚዎች በግብረ-ገብነት የታነፁ፤ገለልተኛ የሆኑ እና የስራ ትጋት ያላቸው ዜጎች እንዲሆኑ ማሳወቅ እንወዳለን፡፡
Filed in: Amharic