>

መሬት በመስጠት ላይ የተመሰረተው የኢትዮ ሱዳን ዲፕሎማሲ (ጌጥዬ ያለው)

መሬት በመስጠት ላይ የተመሰረተው የኢትዮ ሱዳን ዲፕሎማሲ

ጌጥዬ ያለው
የሱዳን ታጣቂ ቡድን ጓንግ (ሱዳኖች አትባራ ይሉታል) ወንዝን ተሻግሮ የኢትጵያ ግዛት ውስጥ ከገባ አንድ አመት አልፏል፡፡ ይህ ሜካናይዝድ የሆነ ጦር በኢትዮጵያ ግዛት ላይ ምሽግ መሽጓል፡፡ ኮረዲም፣ ምድሪያ፣ ግራር ውሃ የተባሉ ቦታዎችን ባለፈው አመት ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በሌላኛወሸ አቅጣጫ እስከ 5ዐ ኪሎ ሜትር ድረስ የኢትዮጵያን ግዛት ይዟል። የተለያዩ የአረቡ አለም መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ኢትዮጵያ ለሱዳን ለም የእርሻ መሬት ለመስጠት መስማማቷን ሲዘግቡ ከርመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አሽራክ አልሳውት የተባለው ጋዜጣ  ጉዳዩን በስፋት አስነብቧል፡፡ እንደ ጋዜጣው ዘገባ ኢትዮጵያ በ1995 ዓ.ም. በአቶ አባይ ፀሐዬ ፊታውራሪነት ከተሰጠው በተጨማሪ 600 ስኩየር ኪሎ ሜትር ለም የእርሻ መሬት ለመስጠት ተስማምታለች፡፡ የመሬት እርክክቡም በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አብራርቷል፡፡ አሁን የተባው ሁለት ሳምንት አልፏል፡፡ የሱዳን ታጣቂዎችም ከኢትዮጵያ ምድር አልወጡም፡፡ እውነትም የተቆጣጠሩት የኢትዮጵያ መሬት የሱዳን ግዛት እንዲሆን ፀንቶላቸው ይሆን? የአብይ አህመድ መንግሥት በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ከተናገረው አንፃር ይህ እውነት የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው፡፡
መንግሥት ምን አለ?
‹‹ከሱዳን ጋር ያለንን ግንኙነት በተለየ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው የምናየው፡፡ ምክንያቱም የአባይ ግድብ ከሱዳን ጋር አወዳጅቶናል፡፡ በሱዳን ላይ ጦርነት መክፈት አንፈልግም፡፡›› ይህ መንግሥት በቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኩል የተናገረው ነው፡፡ ሱዳን በአባይ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ከግብፅ ይልቅ የኢትዮጵያን አቋም በመደገፏ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ደፍራ ብትወርም ሊያስቀይማት እንደማይፈልግ መንግሥት ተናግሯል፡፡ ከላይ የተገለፀውን የጋዜጣው ዘገባ በተመለከተ ሌላኛው የአዲሱ ኢሕአዴግ (ብልፅግና) ሰው አቶ መላኩ አለበል እንዲህ አሉ፡- ‹‹የኢትዮጵያ ድንበር በመስዋዕትነት የተከበረ እንጂ በችሮታ የተገኘ አይደለም፡፡ ሱዳን እና ኢትዮጵያን በማጋጨት የታላቁን ሕዳሴ ግንባታ የማደናቀፍ ህልማቸው የሚሳካ የሚመስላቸው ከስረው ጥግ የያዙ ቁሞ ቀር ፖለቲከኞችና የውጭ ቅጥረኛ ሚዲያዎችን እለፏቸው፡፡›› አቶ መላኩ ቅጥረኛ ያሉት ጋዜጣ በአራት አህጉራት፣ በ14 የዓለም ከተሞች በየቀኑ እየታተመ የሚሰራጭ ጋዜጣ ነው፡፡ በወቅቱ ቁሞ ቀር ያሏቸው ወያኔዎችን እንደነበርም አያሻማም። ሆኖም ዛሬ ወያኔ በሽብር ተፈርጆ ፖለቲካዊ አቅሙንም ተነጥቋል። ሱዳን ግን የኢትዮጵያን መሬት እየሸነሸነች ለዜጎቿ ማደሏን ተያይዛዋለች።
የሆነው ሆኖ አቶ መላኩ ግልፅ አድርገው መሬቱን አልሰጠንም ግን አላሉም፡፡ የሱዳን ታጣቂዎች ሉዓላዊነታችንን አልደፈሩም እንዳይሉም የአካባቢውን ገበሬ አሰድደው የኢትዮጵያን መሬት ተቆጣጥረዋል፡፡ የአካባቢው ኗሪ በአይኑ ተመልክቷቸዋል፡፡ አይናቸውን በጨው ታጥበው ይህንን ቢክዱ እንኳን የሱዳን መንግሥት ‹‹ገብቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያን እወራለሁ›› የሚል መግለጫ ሊያወጣ እንደሚችልም ያስቡ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ነገሩን ከአባይ ግድብ ጋር አገናኝተው አድበስብሰውት አለፉ፡፡ ግድቡ እስከተገነባ ድረስ መሬት እንሰጣለን፡፡ ሉዓላዊነታችን አያሳስበንም ለማለትም ፈልገው ይሆናል፡፡ ንግግራቸው ግልፅ አይደለም፡፡
የአካባቢው አርሶ አደሮች በጎንደር በኩል በሱዳን አቅራቢያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱ ድንበር እንደተደፈረና መሬታቸውን እንደተነጠቁ አቤቱታ ቢያቀርቡ ‹‹ችግሩ በዲፕሎማሲ ይፈታል፡፡ ጠብቁ›› ተብለዋል፡፡ ወታደር ድንበር ላይ ተቀምጦ የሀገሩ ሉዓላዊነት ሲደፈር በዲፕሎማሲ ይፈታል ብሎ ዝም የሚልበት ወታደራዊ ሳይንስ ከየት እንደመጣ እንጃ? ውትድርና እና ፖለቲከኝነት ሲቀላቀሉ እንዲህም ይሆናል፡፡ ጉዳዩ በአዲስ አበባና በካርቱም ድርድር የሚታይ ከሆነ እያዚያ አካባቢ የመከላከያ ዕዝ ለምን ተቀመጠ? አዲስ አበባ ላይ ከቢሮ ቢሮ እየተዘዋወረ ጭማቂ በስትሮው እየጠጣ መኖር ሲችል ጠረፍ ድረስ ውሃ በኮዳ ለምን ይሸከማል? ድርድርና ውይይት የሚደረገውስ ሱዳን ከኢትዮጵያ ግዛት ወጥታ ወይስ ኢትዮጵያን እንደወረረች?
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ካላት ድንበር ሁሉ ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበት ከሁሉም የበለጠ ሰፊው ነው፡፡ 1 600 ኪሎ ሜትር ድንበር ከሱዳን ጋር ትጋራለች፡፡ ይህም ማለት ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ከሱዳን ጋር የሚያዋስናት መሬት እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በጎንደር፣ በወለጋ ፣ በጎጃም፣ በኢሉባቡርና በከፋ ሁሉ ኢትዮጵያ ለሱዳን ጋር ትዋሰናለች፡፡ ይህንን ድንበር ግን ፖለቲከኞች ራሳቸው በትክክል አያውቁትም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ጠረፍ ላይ ያሉ ኗሪዎችን የቀበሌ ሹም መድበው አዲስ አበባ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ውስጥ ተቀምጠው ያስተዳድራሉ፡፡ ድንበሩን እንደማያውቁት ምክትል ጠቅላ ይሚንስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ራሳቸው ከሁለት ዓመታት በፊት የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባዔን አስመልክቶ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል፡፡ የእሳቸውን ንግግር ከዚህ ዝቅ ብሎ እመለስበታለሁ፡፡ ወደ ተነሳሁበት የሱዳን አዋሳኞች ልመለስ፡፡
ከሱዳን ጋር የሚያወስነው የኢትዮጵያ መሬት የተለያዩ ክፍላተ ሀገራትን ያካለለ ቢሆንም በሕወሓት ሲመራ የቆየው አሮጌው ኢሕአዴግ ቆርሶ ለሱዳን የሰጠው በጎንደር በኩል የሚያዋስነውን ነው፡፡ በኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚመራው አዲሱ ኢሕአዴግ፤ ብልፅግናም በአሁኑ ጊዜ እየሰጠ ያለው የጎንደርን መሬት ነው፡፡ ሕወሓት መሬት ቆርሶ ሲሰጥ የሚጠቅሰው ምክንያት ‹‹ቀደም ሲል የነበሩ መንግሥታት የተስማሙበትን የድንበር ከለላ ተከትየ እንጂ በራሴ የሰጠሁት መሬት የለም፡፡›› የሚል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት እና የደርግ ሊቀ መንበር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡
መንግሥቱ ኃይለማርያም ምን አሉ?
 ‹‹የኢትዮጵያና የሱዳን መንግሥታት በድንበር ጉዳይ የተስማሙበት ጉዳይ በታሪክ የለም፡፡ በምኒልክም፣ በኃይለስላሴም፣ በደርግም የለም፡፡ በአብታችን ጊዜ ከሱዳን ጋር ግጭት ላይ ነበርን፡፡ ወያኔ ደርግ ተቀብሎታል ብሎ ለምን እንደሚዋሽ አልገባኝም፡፡ በታሪክ ያደረግነው ስምምነት የለም፡፡ ሱዳኖችም ቢጠየቁ ተዋውለናል አይሉም፡፡ አንድ እንግሊዛዊ ሻለቃ ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችበት ጊዜ የሱዳንን ድንበር ወደ ኢትዮጵያ ለማስፋፋት ሞክረዋል፡፡ ወያኔዎች ኤርትራን ሽጠዋል፡፡ ይበቃል፡፡ ሌላ ሀገር መሸጥ የለባቸውም፡፡›› ብለዋል ኮሎሌል መንግሥቱ ኃይለማርያም፡፡ በእዚህ እሳቤ ሱዳኖች በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን ለመውረር የሚሞክሩት ቅኝ ገዣቸው እንግሊዛዊው ሻለቃ የነበረውን ህልም ተከትለው ነው፡፡
በ1995 ዓ.ም. ለሱዳን የተሰጠው የኢትዮጵያ መሬት
በ1988 ዓ.ም.  የወቅቱ የግብፅ ፕሬዚደንት በአዲስ አበባ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው፡፡ ሙከራውን ያደረጉት ደግሞ ሱዳናውያን ነበሩ፡፡ ወንጀለኞች ሩጠው ሀገራቸው ገቡ፤ ሱዳን፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የግድያ ሙከራውን ያደረጉት ግለሰቦች እንዲሰጡት ቢጠይቅም የሱዳን መንግሥት ዜጎቹ አሳልፎ እንደማይሰጥ ተናገረ፡፡ በዚህ ምክንያ በዚያው አመት የኢትዮጵያና የሱዳን ጦርነት ተደረገ፡፡ በኢትዮጵያ አሸናፊነትም ተጠናቀቀ፡፡ የደርግ መንግሥት ተወግዶ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሱዳናውያን በጎንደር በኩል የኢትዮጵያን መሬት ተቆጣጥረው ነበር፡፡ ይህንን ለማድረግ ሁለት መልካም አጋጣሚዎችን ተጠቅመዋል፡፡ 1ኛው ሕወሓት ወደ ሥልጣን እንዲመጣን ሱዳን ታግዘው ስለነበር ያለፈ ወለታዋ የኢትዮጵያ መሬት እንድትወስድ አስችሏላታል፡፡ 2ኛው ኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ አመረጋጋት ላይ ስለነበረች ለሱዳን አመችቷታል፡፡ ሀገሪቱ በሽግግር መንግሥት የምትመራበትና በርካታ ነገሮች ፈርሰው እንደ አዲስ የሚገነቡበት ጊዜ ስለነበር ለሱዳን አመች ነው፡፡ በየጊዜው የሚጮሁ ምሁራን ሁሉ ተገልለው ፊደል ያልቆጠሩ ሕወሓታውያን ጠመንጃ እያንቀጫቀጩ በዋና ዋና የሀገሪቱ ተቋማት የሚዘዋወሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ወራው የነበረው መሬት ሱዳን በ1988ቱ ጦርነት ለቀቀች፡፡ ሱዳን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተቃዋሚዎች የመደገፍ ልምዷ ከፍተኛ ነው፡፡ ሕወሓት ተቃዋሚ በነበረ ጊዜ ትደግፈው እንደነበረው ሁሉ ተገልብጣ የሕወሓትን ተቃዋሚዎች ደግሞ መደገፍ ጀመረች፡፡ ጥቂት የማይባሉ ተቃዋሚዎች ሱዳን ውስጥ እየመሸጉ ሕወሓትን ለሥልጣኑ አሰጉት፡፡ ቀጥሎም ኢትዮጵያ ሱዳን በምስጢራዊ ድርድር ተስማሙ፡፡ በዚህ ሂደት ተለዋዋጩ የሱዳን ባህሪ በርካቶችን ዋጋ አስከፍሏል፡፡ ሱዳን ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር የውክልና ጦርነት የምታደርግባት ሀገርም ነች፡፡ በመሆኑም የራሷን ጥቅም እስካስከበረላት ድረስ በየጊዜው አቋሟን ትቀያይራለች፡፡ እስስት የሆነችው ሱዳን በሀገሯ የነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን ለሕወሓት አሳልፋ ሰጠች፡፡ የመሬቷን ጉዳይም አልዘነጋችም፡፡ በ1988 ዓ.ም. መልሳ ያጣችውን የኢትዮጵያ መሬት እንዲመለስላት ጠየቀች፡፡ ሕወሓት ፈቀደላት፡፡ የኢትዮጵያ ገበሬዎችን አፈናቅላ መሬቱን ዳግም ተቆጣጠረችው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የመተማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ገሌ ጉዳዩን በመቃወማቸው ለእስር ተዳርገዋል፡፡
ይህ መሬት በ1995 ዓ.ም ለሱዳን በድጋሜ ሲሰጥ የወቅቱ የኢትዮጵያ የፌዴራል ጉዳዮች ሚንስቴር ሚንስትር የሕወሓቱ አቶ አባይ ፀሃዬ ከአዲስ አበባ መተማ፤ ደለሎ  ድረስ በሄሊኮፍተር ሄደው መሬቱን አስረከቡ፡፡ በአስር ሺህዎች ሄክታር የሚቆጠር ማለትም አብዛኛው የደለሎ መሬት ተሰጠ፡፡ በዚህም ብዙ ኢትዮጵያውያን ተፈናቀሉ፡፡ በተለይም ዘለቀ እርሻ ልማት ተወገደ፡፡ ይህንን አቶ ደመቀ መኮንን ያውቃሉ፡፡ በ2000 ዓ.ም. ላይም ሌላ ተጨማሪ መሬት ለመስጠት እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ በሕዝብ ተቃውሞ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
 የአቶ ደመቀ መኮንን ክህደት
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን እንዲሰጥ የእርሶም እጅ አለበት ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው መልሰዋል፡፡ እንዲህም አሉ፡- ‹‹እኔ በወቅቱ ‹ፊርማ ፈረምህ› በተባልኩበት ጊዜ እንግሊዝ ሃገር ለትምህርት ሄጀ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እጄ የለበትም፡፡ እኛ በሪፖርታችን መሰረት የድሮ መሬታቸው ነው የተመለሰው ብለናል፡፡ (የሱዳኖች ማለት ነው) እዚያው እንጨት ለቅሞና ከብት ጠብቆ ያደገው ሕዝብ ‹አይደለም› ይለናል፡፡ ይሄ የደረቅ ፖለቲካ ነው፡፡ ከጓንግ ወዲህ ማዶ ሱዳኖች የኢትዮጵያን መሬት እንደያዙ ኗሪዎች ነገሩን፡፡ በእነ አባይ ፀሃዬ መሪነት የቃል ስምምነት ከሱዳኖች ጋር ተደርጓል፡፡ ፊርማውን አላውቅም፡፡ ያን ጊዜ የክልል አመራር ነኝ፡፡ የክልሉ መንግሥት በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የመፈረም ስልጣንም የለውም፡፡››
አቶ ደመቀ ይህንን ይበሉ እንጂ መሬቱ በ1995 ዓ.ም. ለሱዳን ከመሰጠቱ አንድ አመት ቀድሞ የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ ነበር፡፡ በወቅቱ እሳቸው አማራ ‹ክልል› ሲል ሕወሓት ለሰየመው አካባቢ የአስተዳድርና ፀጥታ ቢሮ ሓላፊ ነበሩ፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ መሥራች አባልም ነበሩ፡፡ የኢትዮ ዳንን ድንበር የሚወስነው እና መሬቱ ለሱዳን ስለ መሰጠት አለመሰጠቱ የሚወስነውም ይኸው ኮሚሽን ነው፡፡ ስለዚህ የክልል አመራር በፌዴራል ጉዳዮች ላይ የመፈረም ስልጣን እንደለሌለው የገለፁበት አመክንዮ ፉርሽ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የድንበር ኮሚሽኑ በፌዴራል ደረጃ የተቋቋ ነውና፡፡
አቶ ደመቀ ‹‹እጀ የለበትም፡፡ አልፈረምኩም፡፡›› ቢሉም መሬት በእነ አባይ ፀሃዬ ሲሰጥ ግን ያውቁ እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ ስለዚህ መሬት የወቅቱ የመተማ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉዓለም ገሌ   በ1996 ዓ.ም ከድርጅቱ ተባርረዋል፡፡ ታስረዋል፡፡ ከዚህኛው አስተዳዳሪ በፊት የነበሩት የወረዳው አስተዳዳሪ ኮሎኔል ደሳለኝ አንዳርጌ ሽፍታ ተብለው በሱዳን መንግሥት ቲሃ የተባለች የሱዳን ከተማ ድረስ ታፍነው መወሰዳቸውን በቅርቡ በፍትሕ መፅሔት ባሰፈሩት ሀተታ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በኋላም በትምህርት ምክንያት አስተዳዳሪነታቸውን ለቀዋል፡፡
በዚህ ጊዜ አቶ ደመቀ መኮንን የ‹ክልሉ› ከፍተኛ አመራር ናቸው፡፡ የፓርቲውም ጭምር፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪዎች ሲፈራረቁ ከሕዝቡ ጋር በመሆኑን ለበላይ አመራሮች ጉዳዩን ያሳውቁ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የበላይ አመራር ከተባሉት መካከል  የአስተዳድርና ፀጥታ ጉዳዮች ሓላፊው አቶ ደመቀ ጉዳዩ ቀድሞ እንደሚደርሳቸው አያጠራጥርም፡፡ ታዲያ ለምን መሪ ከሆኑ በወቅቱ የሕዝብን ጥያቄ ሰምተው የሀገሪቱን ሉዓላዊነት አላስከበሩም? ለምንስ የሚመሩትን አካባቢ ሕዝብ ደህንነት አላስጠበቁም? ተባባሪ አልነበሩም ወይ? በዚህ ጉዳይ እጄ የለበትም ማለትስ ምን አይነት ክህደት ነው? የሕዝብ መሪ እኮ ኖት፡፡ ዋናው ወንጀል ሕዝቡን አሳልፈው መስጠትዎ እና ሉዓላዊነትን በማስደፈሩ ጉዳይ ተባባሪ መሆንዎ አይደለምን? በጉዳዩ ከተስማሙ የወረቀት ፊርማውን ፈረሙና አልፈረሙስ ምን ይፈይዳል?
ይህ የደለሎ መሬት አሁንም ድረስ በሱዳኖች እንደተያዘ ነው፡፡ ከሰሞኑ ተሰጠ የተባለው ለም የእርሻ መሬት ደግሞ ሱዳን በአባይ ግድብ ላይ ያላትን አቋም ለኢትጵ በሚደግፍ መልኩ እንድታደርገው የታሰበ መሆኑን አቶ ገዱ ነግረውናል፡፡ ይህም የአብይ አሕመድ መንግሥት ለውጭ ሃገራት ያለውን ተንበርካኪነት የሚያሳይ ነው፡፡ ከሱዳን ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋርም ያለው ዲፕሎማሲ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የጅቡቲ ታጣቂዎች በአፋር በኩል ገብተው ጥቃት ሲያደርሱ ተለማምጦ አልፎታል፡፡ በጋምቤላ በኩል ደቡብ ሱዳናውያን በተደጋጋሚ የሚያደርሱት ትንኮሳ እንደቀጠለ ነው፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ ከኬንያ ቱርካና ጋር የሚደረግ ተደጋጋሚ ግጭት አለ፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚደረገው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግን ተንበርካኪ ነው፡፡
በአጠቃላይ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በግብፅና በኢትዮጵያ እዳለው ግንኙነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የሚመሩበት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ‹ቋሚ ጠላትም ሆነ ቋሚ ወዳጅ የለም› የሚል ቢሆንም ግብፅ ከአባይ ተጥሮ ጋር አብራ የተፈጠረች ቋሚ የኢትዮጵያ ጠላት ነች፡፡ ይህንን በሱዳን በኩል እያስፈፀመች ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ከወቅሮው በተለየ አስጠንቅቋል፡፡ በእነ የመን እና ሶሪያ እንኳን ጦርነት እንዳይኖር እየሰራ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈፀመች፡፡ ይህንን የኢትዮጵያ መንግሥት ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ማሳወቅ ነበረበት፡፡ የአፍሪካ ሕብረትም ጉዳዩን ማውገዝ አለበት፡፡ ነገር ግን ለሱዳን ተንበርክኳል፡፡ ግብፅ የአረብ ሊግን አስተባብራ እንደምትሰራው ሁሉ ኢትዮጵያም ጥቁር የአፍሪካውያንን ማስረባበር ይጠቅማታል፡፡ ለጥቁር አሜሪካውያንም ጭምር ጉዳዩ ማስረት የውጭ ጉዳይ ሥራው አካል መሆን አለበት፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ድምፃቸውን ሊያሰሙና ማሕበረሰቡን ሊያሳውቁ ይገባል፡፡
Filed in: Amharic