>
5:21 pm - Sunday July 21, 3630

ይድረስ ከነፃነት በኋላ በሚኖረን መንግሥት ሕዝብንና ሀገርን በቅንነት ለማገልገል ለምትመረጡ ወገኖቼ!  (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ) 

ይድረስ ከነፃነት በኋላ በሚኖረን መንግሥት ሕዝብንና ሀገርን በቅንነት ለማገልገል ለምትመረጡ ወገኖቼ! 

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ 


የነፃነታችን መምጣት የጊዜ ጉዳይ ነው – ማመን ኃይል ነውና አትጠራጠር፤ የምልህ ፍጹም እውነት ነው፡፡ ደግሞም ብዙ ተሰቃይተናልና ገና ከጅምሩ እንደምናየው ወጪው ከባድ ቢሆንም ነፃነት ይገባናል – “ይደልዎነ!”፡፡ ነፃነትን አያያዝ ብዙውን ጊዜ አናውቅበትም እንጂ የመምጣቱ ነገር ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ “ኢትዮጵያውያን ከነፃነት ይልቅ ባርነትን፣ ከጥጋብ ይልቅ ርሀብን፣ ከድሎት ይልቅ መከራን፣ ከዴሞክራሲ ይልቅ አፈናና ጭቆናን … ይችላሉ፡፡” የሚለውን ነባር አነጋገርና የአንዳንዶች እምነት ለመፋቅ ከአሁኑ መጣር ይገባናል እንጂ ነፃነታችን ከደጅ የቆመ ያህል ነውና አንጠራጠር፡፡ ከነጎድጓዳማ ሰማያዊ ወጀብ በኋላ ዝናብ መዝነቡና ጎርፍ መከሰቱ፣ በጎርፉም ምክንያት ብዙ ግሳንግስ ተጠራርጎ ወደጥልቅ ባሕሮች መጣሉ እንዳለ ሁሉ ከዚህ ከገባንበት አዘቅት መውጣታችንና ያለንበትና ያሳለፍነው እጅግ ረጂም የመከራና የስቃይ ዘመን ወደ ታሪክ ማኅደር በቅርብ ጊዜ መግባቱ አይቀርም፡፡ 

“ከገባንበት የመጥፎ አስተሳሰብ አዙሪት እንዴት እንውጣ?” የሚለው ጥያቄ ግን አስቀድሞ መልስ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ አሁን እንደሚስተዋለው ያልጠፋንበት አንድም ማኅበራዊም በሉት ፖለቲካዊ፣ ባህላዊም በሉት ሃይማኖታዊ ዐውድ የለም፡፡ በሁሉም ረገድ በተስተካከለ ሁኔታ ጠፍተናል፡፡ ለዚህ ኪሣራ የዳረገንም በዋናነት በአብርሃም ማስሎው የሰዎች ፍላጎት ትንታኔ መሠረት ገና ከሆድ ጣጣ አለመውጣታችን ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሆድ ካልወጣ ማለትም አስተሳሰቡ “ምን እበላ ይሆን? ምሣውን እንደምንም ምናምን የቀማመሰው ቤተሰቤ ለራቱ ምን ያገኝ ይሆን” በሚል የሚጨነቅ ከሆነ ከሌላው የእንስሳት ዓለም እምብዝም አልተለየም፡፡ ሌላው እንስሳ ከርሱን ለመሙላት እርስ በርስ እንደሚባላ ሁሉ ሰውም ከዚያው ባልተናነሰ እርስ በርሱ ይባላል – በሀገራችን እየሆነ ያለውም ይሄው ነው፡፡ በንግድ ብትል፣ በምርት አቅርቦት ብትል፣ በቢሮክራሲው ብትል፣ … በሁሉም ዘርፍ የሚታየው ሙስናና ንቅዘት እንዲሁም የኢኮኖሚ ውድቀትና የገንዘብ የመግዛት አቅም መንኮታኮት የሚያሳየን አስተሳሰባችን ከሰውነት እየወጣ ወደሆድ ብቻ ማዘንበሉን ነው፡፡ ትልቅ ችግር ነው፡፡

ይህ ችግር ሊታረም የሚችለው በመማር ብቻ ነው፡፡ መማር ሲባል በመደበኛም በኢመደበኛም ይከናወናል – ማለፍ መውደቅ ባለበትም በሌለበትም፡፡ ፊደል መቁጠር ብቻውን እርግጥ ነው መማር አይደለም፡፡ እንጂ በዲግሪና በዲፕሎማማ ቢሆን ሀገራችን በምሁራን ቁጥር ከማንም ሀገር የምታንስ አትመስልም፡፡ ዲግሪ ለማግኘት መማርና ዕውቀት ለማግኘት መማር ለየቅል ናቸው፡፡ ባገራችን የዶክተር ማይም ብናይ ሊገርመን አይገባም፡፡ በኬንያ ገበሬው በእንግሊዝኛ ወጉን እየጠረቀ ስለዓለም ሰላም ሲያወራ በሀገራችን ሦስተኛ ዲግሪ ይዞ በተማረበትና ምርምር ባደረገበት ቋንቋ ሳይቀር ራሱን መግለጽ የማይችል አለ፡፡ አንድ የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት ለሦስተኛ ዲግሪው ሲዘጋጅ “የትኛው የትምህርት ዘርፍ ነው የሚያበላው?” ብሎ ትምህርቱን ከሆድ ጋር ሲያያይዘው ስታይ ትኩረታችን እምን ላይ እንደሆነ ትረዳለህ፡፡

ስለዚህ በመደበኛም ሆነ በኢመደበኛ ፈርጆች ትምህርታችንን ስንማር ዋና ትኩረታችን ከማይምነት ጨለማ ለመውጣት ይሁን፡፡ ወደ አብርኆት ለመዝለቅ እናቅድ፡፡ አእምሯዊ ልዕልና ካለን እየተራብንም ቢሆን ከፍ እንላለን፤ እየታረዝንም ቢሆን ላቅ ያለ የአስተሳሰብ ኑባሬን እንላበሳለን፡፡ በዚያ ላይ ንባብ ባህላችን ይሁን፡፡ የማያነብ ሰው ወደ መቃብሩ የሚጣደፍ እንስሳ ነው፡፡ ካልተማርንና ካላነበብን ጥሩ መሪ አናገኝም፡፡ ንባብ ስልህ ደግሞ የማኪያቬሊንና የአንቷን ሌቪን ዓይነት ሰይጣናዊ መጻሕፍት ሣይሆን ገምቢዎቹን ነው፡፡

ሁለት ነገሮችን በአጭሩ ለማንሳት ነበር አጀማመሬ፡፡

  1. የኢትዮጵያ ነፃነት ሲመጣ አዲስ ትውልድ ቦታውን አይዝም፡፡ አሁን ካለነው እየተመረጠ ነው፡፡ ለምሣሌ ከአንድም ይሁን ከሁለት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ አሁን ሰቅዞ ከያዛት የአጋንንቱ መንግሥት (የጎሣ ፖለቲካ ማለቴም ነው) ነፃ ብትወጣ ያኔ የሚወለድ ሰው አይደለም አራት ኪሎ የሚገባው፡፡ በዚያን ዘመን ሥልጣን የሚይዙ ሰዎች አሁንም ከጎናችን አሉ – እንደኛው በአጠገባችን ሆነው እየተጫወቱ፡፡ ለዚህ ሃቅ ምሣሌ በመስጠት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም – ባጭሩ ግን መንግሥቱ የቀ.ኃ.ሥ አገልጋይ ነበር፤ መለስ የቀ.ኃ.ሥ ዘመን ተማሪና የደርግ ዘመን የትህነግ አባል ነበር፣ ግራኝ አቢይም የወያኔ/ኢህአዴግ ሎሌ ነበር፡፡

ስለሆነም አዲስ ሰው የማይመጣ መሆኑን ተረድተን ጥሩ ጥሩ ዜጎችን በዕጩነት የምንይዝበት የማስታወሰሻ ደብተር ይኑረን፡፡ እርግጥ ነው ንግግርና ተግባር እየተለያዩብንና ጊዜ ባለውሉ የሰዎችን አቋም እንደስስት እየለዋወጠ ክፉኛ መቸገራችን መሪር እውነት ነው፡፡ በዚያ ላይ ይሄ የዘር ሐረግ የሚባል መርዘኛ የወያኔ ሥሪት ብዙ የሁላችን የምንላቸውን ሰዎች እያበላሸብን እንደሆነ በግልጽ እያየን ነው፡፡ ለማንኛውም ሰው ጨው ወይ ስኳር ባለመሆኑ ተቀምሶ አይታወቅም እንጂ በአነጋገራቸውና በአድራጎታቸው የተሻሉ ናቸው የምንላቸውን መዝግበን መያዝ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን እንድል ያነሳሳኝ ከደቂቃዎች በፊት አርአያ ተ/ማርያምና አታኽልቲ የሚባለው የመቀሌ ከንቲባ – አንዲት ሴትም አለች – በዩቲዩብ ሲወያዩ መመልከቴ ነው፡፡ አርአያ ግሩም ጋዜጠኛ ነው፤ ከግራኝ ጋር ያለውን ግንኙነት እግዜር ይጠብቅለት እንጂ በእስካሁኑ ሁኔታ መልካም ስብዕና ያለው ይመስላል፡፡ አታኽልቲም በአነጋገር ብስለቱ ወድጄዋለሁ፡፡ እንደነዚህ ያሉ በሳልና ከመንጋ አስተሳሰብ እንዲሁም ከዘር ጣጣ ወጣ ያሉ ሰዎች ለነገ በእጅጉ ያስፈልጉናልና መዝግበን እንያዛቸው፡፡ 

  1. ጧት ስመጣ በአንድ አደባባይ ዙሪያ ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርግ አየሁ፡፡ ተናጋሪው ሰው እንግሊዝኛንና አማርኛን እየቀላቀለ በጉራማይሌኛ ያወራል፡፡ “ … ‹ሉዝ› ያደረግናቸውን ማኅበራዊ ዕሤቶች ለመመለስ …” እያለ ስብከቱን ያስነካዋል፡፡ በዚህ የቋንቋ አጠቃቀም ዙሪያ ትንሽ ማለት ወደድኩ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ ዜጎች ሊያሸንፉት የሞከሩ አንድ መጥፎ ወረርሽኝ አለ – እሱን ላስቀድም፡፡ ቋንቋዎችን እየቀላቀሉ መናገር በጣም እየተለመደ መጥቷል – ሲያስፈልግም ሳያስፈልግም፡፡ እንደእውነቱ ጉራማይሌ ንግግር አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም፡፡ በአማርኛ ከጀመርክ በሱው መጨረስ፤ አለዚያ በምትቀላቅለው ቋንቋ መቀጠል፡፡ የማይገባው ሰው ሊኖር ስለሚችል ጉራማይሌን መጠቀሙ አይመከርም፡፡ በዚያ ላይ አላግባብ የሚቀላቅሉ ማለትም ሳያውቁት የሚዘባርቁም አሉ – ሰዋስዋዊ ግድፈት፣ ደካማ የቃላት አጠቃቀም ወዘተ. የሚስተዋልባቸው በርካታዎች ናቸው፡፡ እናም ቢቻል አንቀላቅል፡፡ 

ቋንቋ በመሠረቱ የመግባቢያ መሣሪያ ነው፡፡ አክራሪዎች ለዘዴያቸው ሲሉ እንደሚሰብኩት አንድ ቋንቋ የተናጋሪው ሀብትና ንብረት አይደለም፡፡ በዘር አይወረስም፡፡ ስለወደድከው የምትሰጠው፣ ስለጠላኸውም የምትነሳው የግል አንጡራ ሀብትህ አይደለም፡፡ የሚገኘው በተወለዱብሽ ሳይሆን ባደጉብሽ ነው፡፡ ሁለት የቋንቋ ማግኛ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው መልመድ ነው፣ ሁለተኛው መማር፡፡ ከሁለት በአንዱ ወይ በሁለቱም መንገዶች አንድን ቋንቋ ገንዘባችን እናደርጋለን፡፡ ንብረታችን ሆኖ የሚቆየውም እስክንሞት ብቻ ነው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነጥብ ላንሳ፡፡ የጎሣ ፖለቲካ አራማጆች ሕዝብን ከሚለያዩበትና የግዛት አጥር ከሚያቆሙበት ሥልቶች አንደኛው ቋንቋ ነው፡፡ ዜጎችን ማይም አድርጎና በቋንቋ ለያይቶ ቀጥቅጦ መግዛት የዘር ፖለቲካ አራማጆች ዋናው ዘዴ ነው፡፡ እነሱ ግን በዚያ አጥር ውስጥ የሉበትም፡፡ ምን በወጣቸው!

ከኢትዮጵያ የጎሣ ፖለቲካ አራማጆችና አመራሮች መካከል አማርኛን የአፍ መፍቻው ያህል እንዲያውም ከዚያም በበለጠ የማይናገር አንድ ሰው ፈልጉልኝ፡፡ አታገኙም፡፡ ከመለስ ዜናዊ ጀምሩና እስከውርጋጦቹ ጃዋር መሀመድና ጓደኞቹ ድረስ ታዘቡ፡፡ ይራቀቁበታል፡፡ ወጣቱንና የገጠሩን ሕዝብ ግን አያውቅ(ብን)ም ብለው ጢባጢቤ ይጫወቱበታል፡፡ እነሱ የሚወዱትንና በሀብትም በሥልጣንም የሚያድጉበትን ቋንቋ ሌላው እንዲጠላውና ጆሮውን ቢቆርጡት አንዲትም ቃል እንዳይሰማ እንዳይለማ አድርገው ያደነቁሩታል፡፡ እነዚህ መሠሪዎች አማርኛን ለነሱ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻውም ያስተምራሉ፡፡ ቀደም ባለ አንድ ወቅት የቱባ ቱባ የወያኔ ባለሥልጣናትን ልጆች የማስተማር ዕድል ነበረኝ – ከመለስ ልጆች በስተቀር ነው ታዲያ፡፡ እነዚያ ልጆች አዲስ አበባ ላይ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ አማርኛን ከትግርኛ ባላነሰ አንዳንዶቹ እንዲያውም በበለጠ ይናገራሉ፡፡ ለራሳቸው ልጆች ሲሆን አማርኛ ጠቃሚ ነው፡፡ ለሌላው ሲሆን አማርኛ “የጨቋኞች ቋንቋ” ስለሆነ መጥፎና ሊናገሩበት የማይገባ ነው፡፡ የአሁኑ የኦህዲድ ሸኔ መንግሥትም እንደወያኔዎቹ “ከሥጋው ጦመኛ ነኝ ከመረቁ አውጡልኝ” ባይ ነውና ዋና ዋና ባለሥልጣናቱ ተረቱን ከዘይቤው፣ ቅኔውን ከሰሙ አብጠርጥረው የግል ወሬያቸውንና የአደባባይ ዲስኩራቸውን እየጠረቁበት ሳለ መንጋውን ግን ዱዳ አድርገው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለይተውታል፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም መጽሐፍ እየጻፉበት የእንጀራ ገመዳቸው አድርገውታል፡፡

አማርኛ በኢትዮጵያ ቢነገር ባይነገር አማራ ለሚባለው ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ በተለዬ የሚጎዳውም ሆነ የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡ አንድ የጋራ ቋንቋ እንዲኖር የሚደረገው አንድን ጎሣ ወይም ነገድ ለመጥቀም ታስቦ ሳይሆን ብዙኃንን እንደሚያቀራርብ ሲታመንበት ነው፡፡ ከሌሎች ቋንቋዎች ተለይቶ የሚመረጥበት ሥልትም ሥነ ልሣናዊና ኢኮኖሚያዊ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም፡፡ አማርኛን ለጋራ መግባቢያነት ሲመርጡት ብዙ ነገሮች በታሳቢነት ተይዘው ነው፡፡ በዚያም ምክንያት ነው ነገሥታቱ በትውልዳቸው የፈለገውን ያህል ከአማራ ነገድ የራቁ ቢሆኑም እንኳን አማርኛን ከወል ቋንቋነት ማስቀረት ያልደፈሩት፡፡ ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ ለራሳቸውም ነበርና፡፡ አማርኛ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች መካከል በሥነ ጽሑፍም፣ በፊደል ባለቤትነትም፣ በብዙዎች ዘንድ በቀላሉ መነገር መቻሉም ለጋራ ቋንቋነት ሊያሳጨውና ሊያስመርጠው ችሏል፡፡ ይህን በብዙ መቶ ዓመታት የብዙኃን መስተጋብር የተገኘ የጋራ ዕሤት ገና ለገና ዛሬ የንግሥና ዕድል አገኘሁ የሚል አንድ አካል መጥቶ አማርኛን ከሥራ ውጭ አደርጋለሁ ቢል የሚላተመው ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንጂ ከተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍል ጋር ብቻ አይደለም፡፡ አንድን ሕዝብ ፈጅቼ ቋንቋውንም፣ ማኅበራዊ ዕሤቱንም ከሥራ ውጪ አደርጋለሁ ብሎ ቀን ከሌት መጣር ደግሞ በራስ ላይ እሳት ማዝነብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መኖር አለበትና ከአጥናፍ እስካጥናፍ ያለው ዜጋ ይህ ሁሉ ሸርና ሤራ ሲገባው ሆ! ብሎ ይነሣል፤ ያኔ ታምር ይታያል፡፡

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ነገዶች አሏት፡፡ የሁሉም ማኅበረሰቦች ዕሤትና ቋንቋዎች የሀገሪቱ ጌጥ ናቸው፡፡ የአንዱ ቁሣዊም ይሁን አእምሯዊ ሀብት ለሌላው ግርማ ሞገሱ ነው፡፡ ከዚህ በተጻራሪ በመጓዝ በሀሰት ትርክት ናውዞ ጥላቻን ማስፋፋትና በቂም በቀል ተነሳስቶ ትውልድን በማቆራቆስ ሀገራዊ ውድመትን ማስከተል ለጊዜው የተሣካ ቢመስልም ታሪክና ፈጣሪ ውላቸውን አይስቱምና የኋላ ኋላ ለጸጸት ለሚዳርግ ኪሣራ ያጋልጣሉ፡፡

ከፍ ሲል ከገለጽኩት እውነት አኳያ አማርኛን ከኢትዮጵያ ለመለየት የምትባዝኑ ኦሮሙማዎች አደብ ግዙ፡፡ መጀመሪያ ነገር አንጎላችሁን ከፈት አድርጉና ስለቋንቋና ማኅበረሰብ አንብቡ፡፡ አንድ ቋንቋ ከአንድ ግለሰብ ጋር ተፈጥሯዊም እንበለው ባሕርያዊ ግንኙነት የለውም – በአጋም በቀጋ አይገናኙም፡፡ አንተ ኦሮምኛ መናገርህ መርጠኸው ሳይሆን በአጋጣሚ ነው፡፡ በቋንቋ አርበኝነት ውስጥ ገብቶ የሚዋደቅ ሰው ያሳዝናል፡፡ የመጨረሻ ጅልነት ነው፡፡ “የኔ ቋንቋ” ብሎ ነገር የለም፡፡ ያንተ ቋንቋ የኔም ነው፤ የኔም ያንተ፡፡ ይሁን እንጂ የዓለምን ከሰባት ሽህ አንድ  መቶ የሚበልጡ ወይንም የኢትዮጵያን ከ80 የማያንሱ ቋንቋዎች እንድናገር መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ ሲጀመር የተሰጠኝ ምድራዊ ዕድሜ እጅግ አጭር እንደመሆኑ እንኳንስ ይህን ሁሉ ቋንቋ ለመማርና ለመናገር አንዱንም በአግባቡ ለምጄ ወይ ተምሬ በተጠቀምኩበት፡፡ ሲቀጥል ሁሉን የሚያግባባ አንድ ቋንቋ ካለ ያ በቂ ነው፡፡ ብርድ ልብስ የሚያስፈልገው ብርድን ለመከላከል ነው፡፡ ብርድ ልብስ አምራች ኩባንያ ሁሉ እንዳይከፋው ብለህ ግን ዐርባና ሃምሣ ብርድ ልብስ ደርበህ ብትተኛ በሙቀቱ ታፍነህ ለከፍተኛ አደጋ ከመጋለጥህም በተጨማሪ እንደቂል ያስቆጥርሃል፡፡ እናም የኔ ቋንቋ የሚባል በሌለበት ሁኔታ “የኔን ቋንቋ በግድ መማር አለብህ” ብሎ ድርቅ ማለትና በሌላ የብዙኃን ቋንቋ ለመግባባት አለመቻል ወይም አለመፈለግ “ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” ሊመዘግበው የሚገባ የድንቁርናዎች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡ ለኦሮሙማዎች ንገሯቸው፡፡

… የመጪው መንግሥት ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛ ነው – ዝም ብለህ እመነኝ፤ ምድረ ቅዠታሙንም ተወው፡፡ ይህ የሚሆነው አማራጭ ስለሌለ ነው፡፡ ስድስት ሚሊዮን ሶማሌ፣ ስድስት ሚሊዮን ትግሬ፣ ስድስት ሚሊዮን አፋር፣ ስድስት ሚሊዮን ከምባታና ሃዲያ፣ ሦስት ወይ አራት ሚሊዮን ጉራጌ፣ ስድስት ሚሊዮን ጋሞና ሣሆ ወዘተ. ይዘህ 80 ቋንቋዎችን ለጋራ ቋንቋነት አበቃለሁ ወይንም አማርኛን በዘዴ አስወግጄ ኦሮምኛን የጋራ አደርጋለሁ ብሎ በቄሮና በቄሪት በስሜት ወለድ የቀን ቅዠት መነሣት ኢትዮጵያን ካለማወቅ የሚመነጭ ዕብደት ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ኦሮምኛ ይቅርና አሪኛ ብሔራዊ ቋንቋችን ቢሆን ደስታየ ወሰን የለውም፡፡ እንግሊዝኛም ቢሆን አልጠላም፤ ጣሊያንኛም ቢሆን ቅር አይለኝም፡፡ አካሄዱ ግን እንደዚያ ስላልሆነ እየሆነ ያለው ሁሉ ሊሆን ባለው ሲጥረገረግ እየታየኝ በነዚህ ጅሎች የማሞ ቂሎ ሥራ አዝናለሁ፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ አውጥተህ በቅልውጥ ፊደል ሕዝብን ማደናገር ዝቅ ሲል ነውር ከፍ ሲል ወንጀል ነው፡፡ ባሏን የጎዳች መስሏት የገዛ ሰውነቷን በጋሬጣ እንደወጋችው ገልቱ ሴት በግዕዝ ሆሄያት ቢጻፍ በሦስት መቶ ገጽ የሚያልቅን መጽሐፍ ከዕጥፍ በላይ በሆነ በ750 እና 850 ገፆች እንዲያልቅ ማድረግ በጊዜም በገንዘብም በማቴሪያልም መጫወት ነው – ሲያጌጡ ይመላለጡ ዓይነት፡፡ ለዚህ አባባሌ አንድ ምሣሌ ብሰጥ ደስ ይለኛል፡- 

Sii kenninaan diddee, sii dhoogganaan hatte = 37 ፊደላት 

ሲ ከኒናን ዲዴ ሲ ዱጋነን ሃቴ = 14 ፊደላት

37 – 14 = 23  (በነገራችን ላይ የዚህ አባባል ፍቺ – “በፀሐይ ያልሆነ በጨረቃ” ለማለት ነው)

ብቻ ቀን የሰጠው ቅል ነውና ነገሩ ኃጢኣታችን ባመጣብን ኩታራዎች ፍዳችንን እያየን ለጥቂት ጊዜ መቸገራችን አይቀርም፡፡ “ልጅ ያቦካው …” ይባልስ የለም? አዎ፣ አያድርስ ነው፡፡ በርካታ ታላላቅ የዓለም ሀገሮች ልክ እንደኛው ትናንሽና ወራዳ መሪዎች እየገጠሟቸው ዕድገት ብልጽናቸው በመቶዎች ዓመታት ወደኋላ ተጎትቷል፡፡ ከናካቴው የጠፉም እንዳሉ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡ እኛም የተለየን አይደለንም፡፡

እናጠቃል፡፡ በአጉል ፕሮፓጋንዳ ከመስመር ወጥቶ የጠፋውን ወጣቱን እንርዳው፡፡ ቋንቋ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አለመሆኑን እንንገረው፡፡ የጠላትና የወዳጅ ቋንቋ ብሎ ነገርም እንደሌለ እንግለጽለት፡፡ ትልልቆቹ በቅድሚያ ልብ እንግዛ፡፡ ከአማርኛ የራቁ ወንድም እህቶቻችንን በጊዜ ማዕዱን እንዲቀላቀሉ እናድርግ፡፡ የማያዛልቅ ነገር እየተከተሉ ለብዙ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከጥላቻ እናውጣቸው፡፡ ከቂም በቀል እናላቃቸው፡፡ ከተመረዘ ጭንቅላት እንገላግላቸው፡፡ ደግሞም እንጸልይላቸው፡፡ የመለያየትና የመናቆር መንፈስ ከሰይጣን ነውና ከዚያ አቢይ መንፈስ እንዲላቀቁ በኅብረት እንጸልይ፡፡ ጸሎት ግሩም የችግሮች መፍትሔ ነው፡፡ “ሁሉን የኛ” በሚል የጀመሩት ሁሉንም ነገር የማጋፈር ዘመቻ ለማንም እንደማይበጅና በመጨረሻ እነሱንም ይዞ እንደሚጠፋ እናስገንዝባቸው፤ ለወያኔም እንዳልጠቀመ ጭምር እናስረዳቸውና ጊዜ ካላቸው አሁንም ቢሆን እንዲመለሱ እናበረታታቸው፡፡ ከወያኔ ውድቀት የነሱ የከፋ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነውና በግልጽ ይነገራቸው፡፡

የነገዎቹ መሪዎቻችን ከዛሬዎቹ ተማሩ፡፡ በሁሉም ረገድ ራሳችሁን አዘጋጁ፡፡ ቆሻሻ ታሪክን ማጠብና በንጹሕ መጀመር እንጂ የዛሬውን ነገ ለመድገም እንዳታስቡት፡፡ ለእናንተና ለቀጣይ ትውልዳችሁ አይበጅምና፡፡ ሃይማኖት ይኑራችሁ፡፡ ከማንኛውም ዓይነት ሙስና የጸዳችሁ ሁኑ፡፡ ለሆዳችሁና ለሥጋዊ ፍላጎታችሁ ለከት አብጁለት፡፡ ከምንም ዓይነት ደባል ጠባይና ሱስ ራሳችሁን አጽዱ፡፡ ሱስና ያልተገራ ፍላጎት የኅሊናን መንገድ ያስታልና በዚህ በኩል አደራችሁን እንዳትሸነፉ፡፡ ቅንነትና ለመማር ዝግጁነት ይኑራችሁ፡፡ ትዕቢትንና ዕብሪትን አስወግዱ፡፡ አንብቡ፤ ተማሩ፤ ተመራመሩ፡፡ በንጹሕ ገቢያችሁ ብቻ ለመኖር ከአሁኑ ተለማመዱ፡፡ የሰው ወርቅ እንደማያደምቅ ተረዱ፡፡ በአጭር ታጥቃችሁ ቆላ ደጋ በመኳተን ይህችን የቆረቆዘች ሀገርና ይህን የተበታተነ፣ የደኸዬም ሕዝብ በቅን ለማገልገል ተዘጋጁ፡፡ ከማንም ምንም ወሮታ አትጠብቁ፡፡ የሚክሳችሁ ኃያሉ አምላካችሁ ብቻ መሆኑን ተገንዘቡና ለኅሊናችሁ ተገዢ ሁኑ፡፡ መራብ መጠማት መታረዝ ቢኖርባችሁም ለዚያ ተዘጋጁ፡፡ ከጀርመኖችና ከጃፓናውያን ታሪክ ልምድ ውሰዱ፡፡ ራሳችሁን በዕውቀትና በጥበብ እያነጻችሁ ቀኒቷን ጠብቁ፡፡

Filed in: Amharic