>
5:13 pm - Saturday April 19, 5377

ይድረስ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ! (ከይኄይስ እውነቱ)


ይድረስ ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ!

ከይኄይስ እውነቱ


በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በመንግሥትም ሆነ በግል ት/ቤቶች የትምሕርት አሰጣጡ ከመደበኛው በተለየ መልኩ ከክፍልም ውጭ በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰጠ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንኳንስ ዘንቦብሽ ድሮውንም ጤዛነሽ እንዲሉ ኮቪዱ ሳይመጣም ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ከተንኮታኮቱት ማኅበራዊ ዘርፎች አንዱ የትምሕርት ሥርዓቱ መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ኢሕአዴግ በሚባለው አገር-አጥፊ ድርጅት ስም የተፈራረቁት አገዛዞች ሲከተሉት በቈዩት ትውልድ አጥፊ የትምሕርት ፖሊሲ አማካይነት አገራችን በርካታ ፊደል የቈጠሩ ‹ማይምናንን› እንደ አሸን አፍልታለች፡፡ የኮቪድ ወረርሽኝ ደግሞ ሁናቴውን የበለጠ አባብሶታል፡፡ አገዛዙ በተጠናወተው ዘረኛነት፣ አቅሙም፣ ፍላጎቱም አለመኖር ታክሎበት ከድጡ ወደ ማጡ እየሄድን እንገኛለን፡፡ 

ወላጆችም የተለየ አማራጭ ባለመኖሩ ሁሉም እንደየ አቅሙ ልጆቹን ወደ ግልም ሆነ የመንግሥት ት/ቤቶች ይልካል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የልጆቹን ትምሕርት ሁናቴ በቅርብ የሚከታተልም ወላጅ ጥቂት ነው፡፡ 

በግል ት/ቤቶች ከጥቂቶች በስተቀር ከክፍያው እስከ ትምሕርት አሰጣጡ፣ ከመምህራን ብቃት (ሥነ ምግባርና ግብረብነት ጨምሮ – ሁሉንም በጅምላ እንደማይመለከት ግንዛቤ ይወሰድ) እስከ ትምሕርት መደገፊያ መሣሪያዎች ያለውን ዝግጅት በቅጡ ላስተዋለ ዜጋ ዕብድ የሚያደርግ ነው፡፡ ክፍያው ዝርፊያ ነው የሚለው ቃል ብቻውን የሚገልጸው አይመስለኝም፡፡ በዚህች አገዛዞች ባደቀቋት አገራችን መንግሥታዊ፣ ድርጅታዊና ግለሰባዊ ንቅዘት መደበኛ የሕይወታችን አካል እስኪመስል ተስተካክለን ጠፍተናል፡፡ ከዚህ አሠራር ከማዕከል እስከ ክፍላተ ሀገራት ያሉ የትምሕርት አስተዳደር አካላት ነፃ እንዳልሆነ ተቋማቱ ራሳቸው ይመሰክራሉ፡፡ ያም ሆኖ ኅብረተሰቡ የልጆቹን የትምሕርት ጉዳይ በሚመለከት አቤቱታ/ቅሬታ ሲኖረው (በአቅሙ የሚያደርገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ) ያለው አማራጭ ወደነዚህ ተቋማት ቅሬታውን ማሰማት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም በግል ትምሕርት ቤቶች ‹የወላጆች ኮሚቴ› የሚባል አካል ቢኖርም ባብዛኛው ሥራውን ባግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡ አንድነት/ኅብረት ካለመኖሩ በተጨማሪ አንዳንዶች ከትምሕርት ቤቶቹ አስተዳደር ጋር በመመሳጠር በመደበኛና ልዩ ልዩ ክፍያዎች ለሚደረገው ዝርፊያ ተባባሪዎች ሆነው አስተውለናል፡፡ ወላጆችም በየግላቸው ከማጉረምረም ባለፈ በአካል ተግኝተው ድምጻቸውን ባንድነት ለማሰማትም ሆነ ሕገ ወጥ አሠራርን ለመገዳደር ኅብረት እንደሌላቸው ተደጋግሞ ተስተውሏል፡፡ በአንዳንድ ት/ቤቶች ደግሞ ርእሳነ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች በኮቪድ በማሳበብ ወላጆች በአካል ተገኝተው ቅሬታቸውን እንዳያሰሙ እንደሚከላከሉም በቂ መረጃዎች አሉ፡፡ 

በቅርቡ ደግሞ በአንዳንድ የግል ትምሕርት ቤቶች ከት/ቤቶቹ ይፋ ዕውቅና ውጪ ነገር ግን ከውስጥ ባሉ አንዳንድ መምህራን ጋር በመመሳጠር ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች በድምጽና በምስል ‹‹የትምሕርት ማገዣ ሲዲዎች›› አዘጋጅተናልና ለወላጆቻችሁ ንገሩ በማለት በተማሪዎች መካከል መከፋፈል ከመፈጠሩም በተጨማሪ ወላጆች ሕገ ወጥ ለሆነ ብዝበዛ ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ወላጆች በስልክም ሆነ በአካል ተገኝተው ርእሳነ መምህራኑን በሲዲ ታትመው ስለሚሠራጩት ሲዲዎች ሲጠየቁ ት/ቤታቸውን እንደማይመለከት ይገልጹና እገሌ የሚባለውን መምህር አነጋግሩ ብለው ጉዳዩን ወደመምህራን ሲገፉ ተስተውሏል፡፡ የአንድ ት/ቤት ርእሰ መምህር የሚያስተዳድራቸው መምህራን በእንደዚህ ዓይነት ሕገ ወጥ ድርጊት ተሳታፊ መሆናቸው ከተረጋገጠ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ ዋና ተግባሩ ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም በራሱም ሆነ የወላጅ ኮሚቴ በተባለው አካል አማካይነት ለወላጆች ተገቢውን ማስጠንቀቂያ መስጠት ይኖርበታል፡፡ በት/ቤቱ ታምኖበት የሚዘጋጅ የትምሕርት ማጠናከሪያ ሰነዶችም ሆኑ ሲዲዎች ካሉ ለትምሕርት ቢሮው በማሳወቅና ከወላጆች ጋር በመመካከር በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ይቻላል፡፡

ለማጠቃለል በንቅዘት ሀብት አፍርቶ እኔን ምን አገባኝ ከሚል ጥቂት ወላጅ በስተቀር አብዛኛዎቹ ወላጆች ከትርፋቸው ሳይሆን ተለቅተው ተበድረው ወይም ሆዳቸውን ቋጥረው ነው ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት የሚልኩት፡፡ 

ስለሆነም የት/ት ቢሮው በሥሩ ያለትን ት/ቤቶች የት/ት ጥራት፣ የክፍያ ሁናቴ እንዲሁም የመምህራንና ርእሰ መምህራንን ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም ሥነ ምግባር የሚከታተልና የሚቆጣጠር ከሆነ፣ በተጠቀሱትና ባጠቃላይ በመማር-ማስተማር ሂደት በተለይም በግል ት/ቤቶች የሚታዩትን ተገቢ ያልሆኑ አሠራሮች ተከታትሎ አስቸኳይ እርምት እንዲያደርግ በማክበር እንጠይቃለን፡፡

Filed in: Amharic