ከጠቅላይ ፍርድቤቶችና ከምርጫቦርዶች በስተጀርባ – ድሮና ዘንድሮ!
አሰፋ ሀይሉ
*…እየታደምን ያለነው የሁለት ጠንካራ ሴቶችን ፍልሚያ?
ወይስ የተለመደው ኢህአዴጋዊ ተቋማዊ ቁማር?
ሰው በሚያየው ነው የሚፈርደው፡፡ ብዙዎች ከድሮው የተለወጠ ነገር አጋጥሟቸው ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ያጋጠመኝ ያ አይደለም፡፡ የሰዎችን ከቦታ ቦታ መለዋወጥ እንጂ ከወያኔ-ኢህአዴጓ የተለየ ሊባል የሚችል (እና ፋይዳ ያለው) ለውጥ በአብይ አህመዷ ኢትዮጵያ አላየሁም፡፡
በአብይ አህመዱ ኢህአዴግ አማካይነት የተካሄደ ተቋማዊ ለውጥ አለ ወይ? ለእኔ የለም፡፡ የለም ስል ግን በግለሰቦች ደረጃ የታዩ ደፋር የለውጥ እርምጃዎችን እንዳላየን እንለፋቸው እያልኩ አይደለም፡፡
በእነዚያው በመቶ ፐርሰንቱ ኢህአዴግ ቁጥጥር ሥር በዋሉ በምናውቃቸው ተቋሞች ውስጥ፣ የተለዩ አዳዲስ ጠንካራ ሰዎችን በመሾም ረገድ የአብይ አህመዷ ኢትዮጵያ ምናልባት ከኃይለማርያም ደሳለኟ ወይም ከመለስ ዜናዊዋ ኢትዮጵያ ሳትሻል አትቀርም፡፡ ይህንንም ያለጥናት ለመናገር መድፈር ስህተት ላይ እንዳይጥለኝ እሰጋለሁ፡፡
ለማንኛውም ከእነዚህ በአብይ አህመድ የሥልጣን ዘመን ካየናቸው ‹‹ለውጥ›› ተብለው ሊጠሩ ከሚችሉ ከተለመዱት አንፋሽ-አጎንባሽ ሰብዕናዎች የተለየ ሰብዕና ያላቸውን ሰዎች በመሾም ረገድ የታዩ ለውጦች እንዳሉ መካድ አይቻልም፡፡
በአብይ አህመድ አቅራቢነት፣ በኢህአዴግ 100 ፐርሰንት ቁጥጥር ሥር የዋለው ፓርላማ (ማለትም ራሱ ኢህአዴግ) አማካይነት የተሾሙ እነዚህ በሰብዕናም፣ በልምዳቸውም፣ በሙያዊ ብቃታቸውም የተመሰከረላቸው ሁለት ጠንካራ ሰብዕናን የተላበሱ ሴቶች – ለዲሞክራሲ መረጋገጥ ወሳኝ ወደሆኑ ሁለት ተቋማት በሹመት ተመድበዋል!
በሁለት ወሳኝ የዲሞክራሲ ተቋማት፡- በምርጫ ቦርድና በጠቅላይ ፍርድቤት፡፡ ሁለት ወሳኝ ሰብዕና ያላቸው ሴቶች፡- መዓዛ አሸናፊና ብርቱካን ሚዴቅሳ፡፡ የአብይ አህመድ ሹመት ከጎበኛቸው እልፍ የካድሬ ግሪሳዎች መሐል ለየት ብለው የወጡ እንቁዎች ናቸው ሁለቱ ብንል ግነት የለበትም፡፡ ተቋማዊ ለውጥን ባይተካም፣ የምስጋና ጭፍጫፊ ሊፈነጠቅለት ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ሁለቱም ሴቶች የህግ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ መዓዛ አሸናፊ በወያኔዎች ምሪት የተጻፈውን የኢህአዴግ ህገመንግሥት ሲረቀቅ በታዛቢነት የተሳተፈችና፣ ድፍረት የተሞሉ ጠንካራ ሂሶችን በህገመንግሥቱ ላይ በመጻፍ ጠንካራ ሰብዕናዋንና ለእውነት ያላትን ወገንተኝነት ያስመሰከረች ብቁ ባለሙያ ነበረች፡፡
ብርቱካን ሚዴቅሳ በበኩሏ ለወያኔ-ኢህአዴግ ባለጠብመንጃዎች ሸብረክ ሳትል 550 የኢህአዴግ ፓርላማ ካድሬ ተሰብስቦ በአንድ ግለሰብ ላይ ህግ ያወጣበትን የወያኔ አንጃ አቶ ስዬ አብርሃን ከእስር እንዲፈታ የማያወላዳ ትዕዛዝ የሰጠች ዳኛ ነች፡፡ በፖለቲካው መድረክ ገብታም በሴራ የሰነፈጠውን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በሀቅ ያደሰች ሰው ናት፡፡
ብዙዎች ለመለስ ዜናዊ “አጥፍቼያለሁ ይቅርታ ይደረግልኝ” ብለው በፊርማቸው ሲጠይቁና ከእስር ሲፈቱ፣ አላጠፋሁም፣ ይቅርታም አልጠይቅም በማለት መታሰርን የመረጠች ለሀቅ ሽንጧን ገትራ በመቆም የምትታወቅ ጠንካራ ብቁ ባለሙያ ነበረች፡፡
በቲዎሪ ደረጃ እንደ እነዚህ ያሉ ሁለት ጠንካራ ሴቶች በትክክል እንደ አቅማቸውና እንደ ሰብዕናቸው እንደችሎታቸውም ሊሠሩ የሚችሉባቸው ከኢህአዴግ አምባገነናዊ ትብታቦች ነጻ የሆኑ ተቋማት ቢያገኙ ኖሮ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ለውጥን ሊያመጡለት የሚችሉ ጠንካራ ሰብዕና ያላቸው ዜጎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
ሆኖም በተግባር ግን ይህን ያህል ሊሠሩ የሚፈቅድላቸው ሥርዓት ውስጥ አይደሉም ሁለቱም፡፡ ሁለቱንም የሚመርጣቸውም፣ የሚሾማቸውም፣ እና ካንገራገሩበት ደግሞ ከፈለገ ከሥልጣናቸው መንቅሮ የሚያወርዳቸውም – ያው ራሱ ጠቅላዩ አምባገነን ኢህአዴግ ነው፡፡ ስለዚህም ነው የቱንም ያህል ጠንካራ ሴቶች እንደሆኑ ቢያውቅም፣ ዲሞክራትነትና ለውጥ አምጪ ለመምሰል እንደ አደባባይ አሻንጉሊት አምጥቶ በኢህአዴግ የጎሳና የአምባገነንነት ጥምጣም በተሸበቡ ሁለት ተቋማት ላይ አምጥቶ ያስቀመጣቸው፡፡
ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን እነዚህ ሁለት ጠንካራ ሴቶች በኢህአዴግ የተሰጣቸውን ሹመት ከተቀበሉ በኋላ ተቋማቱን በቻሉት አቅም ጠንካራ ለማድረግ እንደጣሩ ግልጽ ነው፡፡ አሁን በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚታየው ፍጭትም በበጎ ጎኑ ካየነው የዚህ የተቋማቱ ጠንካራ ሆኖ የመውጣት ግልጽ ምልክት ነው፡፡ ከተቋማቱስ ጀርባ? እነዚህ ሁለት የህግ ባለሙያ ሴቶች ከተቋማቱ ጀርባ ተከልለው እኔ-እበልጥ እኔ-እበልጥ ፍልሚያ ውስጥ ገብተው ይሆን?
የአደሬዎችን ጉዳይ እናንሳ፡፡ ከዚህ በፊት በወያኔ-ኢሀአዴግ ዘመን ሁሉ ሲደረግ እንደቆየው ከሐረሪ ክልል ውጭ ያሉ አደሬዎች፣ ካሉበት ሆነው ለሐረሪ ተመራጮች ድምጽ የመስጠት ጉዳይን በተመለከተ የምርጫ ቦርድና ጠቅላይ ፍርድቤቱ የያዙትን ተጻራሪ አቋም እናስታውስ፡፡ ምርጫ ቦርዱ ከሐረሪ ክልል ውጭ ያሉ አደሬዎች ድምጻቸውን መስጠት አይችሉም – የሚል ውሳኔ ሰጠ፡፡
ይህን አንዳንዶቻችን ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችና በውጭ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ድምጽ የመስጠት መብታችው እንዲከበር ሊመጣ የሚችልን ጥያቄ ለመቀልበስ ከበስተጀርባ ኦሮሙማው ዲክቴት እያደረገ ያሰጠው ውሳኔ ይሆናል የሚል ስጋት አሳድሮብን የነበረ ውሳኔ ቢሆንም፣ ሌሎች ደግሞ በወያኔ ሲደገፉ የነበሩ አደሬዎች አሁን ከሌላው እኩል በህግ መሠረት እንዲጓዙ መደረጋቸውን በማድነቅ ምርጫ ቦርዱን ሲያበረታቱ ተስተውለዋል፡፡
በመጨረሻ ግን ጠቅላይ ፍርድቤቱ መጣና የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ በመሻር ከክልላቸው ውጪ ያሉ አደሬዎች ድምጻቸውን መስጠት እንደሚችሉ ውሳኔ ሰጠ፡፡ የአደሬዎቹ አቃቤ ህግ አዩብ መሀመድ ለዶቼቬለ ራዲዮ በሰጠው ቃለምልልስም ላይ የተናገራት ንግግር አስገርማኝም ጥርጣሬ አሳድራብኝም ነበር፡፡ ከየት እና ለምን የመነጨች አባባል ነች? ብዬ፡፡
የአደሬዎቹ አቃቤህግ ከጠቅላይ ፍርድቤቱ ውሳኔ በኋላ የተዛባው ፍትህ እንደተስተካከለ ከገለጸ በኋላ የተናገረው እንዲህ በማለት ነበር፡- ‹‹ምርጫ ቦርዱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አክብሮ መብታችንን እንደሚፈቅድልን እምነት አለን!››፡፡ እንዴ? ይሄን ማለትን ምን አመጣው? የጠቅላይ ፍርድቤቱ ፍርድ በእምነት የሚወሰን ሆነ እንዴ? ወይስ ምርጫ ቦርዱን ለማሳጣት ሆነ ተብሎ የተሄደበት እኩይ መንገድ መኖሩን ጠቋሚ ነው?
አሁን ደግሞ በእነ እስክንድር ነጋ ተመራጭነት ጉዳይ ላይ ምርጫ ቦርዱና ጠቅላይ ፍርድቤቱ በድጋሚ በተጻራሪ መደብ ላይ ቆመው ተገኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ፍርድቤቱ እስካሁን ድረስ ተኝቶ ከርሞ፣ የምርጫ ወረቀቶች ታትመው መሰራጨት በሚጀምሩበት ወቅት ላይ በአናት መጥቶ፣ እስክንድር ነጋና ጓዶቹ የዜግነት መብታቸውን የሚከለክል እገዳ በፍርድ እስካልተጣለባቸው ድረስ በምርጫ ለመወዳደር የሚከለክላቸው ነገር እንደሌለ በማረጋገጥ ውሳኔ ሰጠ፡፡
ምርጫ ቦርዱ በበኩሉ የፍርድቤቱ ውሳኔ ከጊዜ አንጻር ለመፈጸም የማይቻል መሆኑን በመግለጽ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ሁለቱ ጠንካራ ሴቶች በምርጫ ነክ ጉዳዮች ከሁለቱ ተቋማት ጀርባ ቆመው ዳግመኛ ፈልሚያ ገጠሙ ማለት ነው! ዲሞክራሲ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ በተረጋገጠባቸው ሀገራት የአንዱን የመንግሥት አካል፣ ሌላኛው የመንግሥት አካል ‹‹ቼክ›› ማድረጉ፣ ወይም አንደኛውን ተቋም ሌላኛው መፈተኑ፣ ተገቢና የሚፈለግም የዲሞክራሲ ዓይነተኛ ገጽታ ነው፡፡
አንዱ ተቋም በህግና በእውነት ላይ ብቻ ተመሥርቶ ሌላውን የሚኮረኩም፣ አንዱ ተቋም በህግና በእውነት ላይ ብቻ ተመሥርቶ ሌላውን የሚቋቋም ቢሆን ኖሮ እስከዛሬ ሀገሪቱ የተነከረችበት የአምባገነንነት ገደልና የደም ማዕበል ውስጥ አንነከርም ነበር፡፡ እና በበጎ ጎኑ ከታየ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
የሴቶቹ ፍልሚያ ወደየት እንደሚያመራ ለማየት ከመጓጓት ባሻገርም፣ አብይ አህመድና ኢህአዴጋዊ ግብረአበሮቹ ምንም እንኳ ባሰኛቸው ጊዜ አሽቀንጥረው የሚጥሏቸው ቢሆንም፣ እስከዚያውም ቢሆን ወለም ዘለም የማይሉ ሁለት ጠንካራ የህግ ባለሙያዎችን አምጥተው በመሾም በማንቁርተቸው ላይ እንዳስቀመጡ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጧቸውን አብነቶች ያገኙ ይመስለኛል፡፡
ይህ ሁሉ በጎ በጎውን ብቻ ካሰብን ነው፡፡ ነገር ግን ከአይጥ ጉድጓድ ጥሬ፣ ከአንበሳ መንጋጋም ሥጋ ይወድቅልኛል ብሎ መጠበቅ የዋህነት መሆኑን አለመዘንጋትም ተገቢ ነው፡፡ ኢህአዴግ በ30 ዓመት ተሞክሮው – ለሀገርና ለህዝብ ትልልቅ ፋይዳ ሊያበረክቱ የሚችሉ ትላልቅ ተቋማትን – በተራ ታዛዥ ካድሬዎች በመገጥገጥ – ተራ ተላላኪ ጩሎዎች አድርጓቸው እንደኖረ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
ኢህአዴግ በሚመስል የተማማሉ ምስጢረኛ ሽፍቶች ተደራጅተው የመሠረቱትን የሲሲሊ ማፊያዎችን ስውር መንግሥት በሚስተካከል አኳኋን በሀገራችን ተቋማት ሁሉ ላይ እንደ ዘንዶ ተጠምጥሞ ሲፈልግ ሲያደቅቃቸው፣ ሲፈልግ ሲሰለቅጣቸው፣ ሲያሰኘውም ከተሰባበሩበት ለቃቅሞ እንደገና ሲያዋቅራቸው – እንደ ህጻናት የጡብ መጫወቻዎች በነፍሳቸው ሲጫወትባቸው ነው የከረመው!
ከስማቸው በቀር የሚኒስትርነት ስልጣን የሌላቸው፣ ከስማቸው በቀር የኮሚሽነርነት ስልጣን የሌላቸው፣ ከስማቸው በቀር የዳይሬክተርነት ስልጣን ያልተሰጣቸው፣ ከስማቸው በቀር የፕሬዚደንትነት ሥልጣን በአጠገባቸው ያላለፉ ብዙ ታዛዥ ካድሬዎች ምርጫ ቦርድንም፣ ጠቅላይ ፍርድቤቱንም፣ ሌሎቹንም የመንግሥት አካሎች በስም-ሲያስተዳደሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ሥርዓቱን ተገዳድሮ በቦታው መቀመጥ የሚችል አንድም ባለሥልጣን የለም፡፡ በኢህአዴግ የማፊያ ሥርዓት መሀል ሆኖም፣ መቼም ሊኖርም አይታሰብም፡፡
ኢህአዴግ በእነ የከብቶች ሳይንስ ፕሮፌሰር በሆኑት በመርጋ በቃና እጅ ምርጫ ቦርዱን እንዴት ሲጫወትበት እንደነበረ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከአናሳዎቹ የአደሬ ፓርቲ የወጣውን ከማል በድሪን የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዚደንት አድርጎ በትዕዛዝ ይሰራ የነበረውን ግፍና ሸፍጥ ብዙው ጸሀይ የሞቀው ነው፡፡
እነ መንበረጸሀይ ታደሰ ከላይ እነ ከማል በድሪን አስቀምጠው፣ በምክትል ፕሬዚደንት ማዕረግ በሪፎርም ስም ጠቅላይ ፍርድቤቱን በነፍሱ የተጫወቱበት ታሪክ፣ የኢህአዴግ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ አሁንም በሌሎች ሰዎች – ስምና አዛዦቹ ብቻ ተቀይረው ያው ታሪክ እየተደገመ ስለመሆኑ የሚጠራጠር ካለ እጅግ የዋህ ወይ እጅግ ምስለኔ መሆን አለበት፡፡
ለማንኛውም ኢህአዴግ ድንገት ባልጠበቅኩት መልክ እንደ ኒውክሊየር ጨረር ቢያፈተልኩብኝና – ከቁጥጥሬ ውጪ ቢወጡብኝስ? የሚል ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የከተቱትን ሁለቱን ተቋማት – ማለትም ጠቅላይ ፍርድቤቱንና ምርጫ ቦርዱን – እያፈራረቀ ለማፊያ ግቡ ዓላማ ለማዋል ይጠቀምባቸው የነበሩ ሰልቶቹ በ1997ቱ የምርጫ ወቅት ግልጽ ብለው ወጥተዋል፡፡
ኢህአዴግ ምርጫ ቦርዱን በሚያምናቸው ሰዎች ብቻ መሙላቱን አምኖ ሊቀመጥ ስላልቻለ ፍርድቤቶችን በእርሱ ቁጥጥር ሥር ማዋል እንዳለበት አመነ፡፡ ስለሆነም በግንቦት 97 ዓ.ም. ሀገርአቀፍ ምርጫው ተከናውኖ በወሩ፣ በሰኔ 7 ቀን 1997 ዓ.ም ላይ የሀገሪቱን ፍርድቤቶች በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር ያዋለበትን ሁለት ቅጠል ያላት አዋጅ አወጣ፡፡
አዋጅ ቁጥር 454/1997 ዓ.ም. የተሰኘው ይህ አዋጅ የሀገሪቱን የክልል ፍርድቤቶችን የመጨረሻ ውሳኔዎች የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድቤት በሰበር ሰሚ ችሎት የመሻር ሥልጣን እንዳለውና፣ የጠቅላይ ፍርድቤቱ ሰበር የሚሰጡ ማናቸውም ውሳኔዎች እንደ ህግ ተቆጥረው በመላ ሀገሪቱ ተፈጻሚ የሚደረጉ መሆኑን ኢህአዴግ ያወጀበት አዋጅ ነው፡፡ ብዙ ግዙፍ ማብራሪያዎች ተሰጥቶት፣ እስካሁንም በፍቅር ይሠራበታል፡፡
በዚህ አዋጅ ላይ ነው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ውሳኔዎች ለሌሎች የሀገሪቱ ፍርድቤቶች እንደ ህግ እንዲያገለግሉ በየጊዜው እየታተሙ በመላ ሀገሪቱ እንዲሰራጩ እንዲደረግ የሚያዝዝ ድንጋጌ የወጣው፡፡
በዚያ አዋጅ ላይ በቀጥታ በጠቅላይሚኒስትሩ አቅራቢነት በኢህአዴግ ፓርላማ እንደሚሾሙ የሚታወቁትን የፌዴራል ፍርድቤቶች ፕሬዚደንቶች በየደረጃቸው ባሉ የፍርድ ችሎቶች ሁሉ በፈለጉት ችሎት ገብተው እንደ ዳኛ በመሰየም ውሳኔ መወሰን ይችላሉ የሚል አንቀጽም አለበት፡፡
ይህ የተደረገው ሌሎች በአቋማቸው ጥንካሬ የሚታወቁ ዳኞች ድንገት እንኳ በምርጫ ህጉ የተሰጣቸውን ስልጣን በመጠቀም በኢህአዴግ ላይ እንዳይወስኑ፣ ካስፈለገ እነዚያን ዳኞች ከችሎታቸው በማንሳት የፈለገውን መዝገብ አንስቶ በእነዚሁ ቅጥረኛ የፍርድቤት ሹመኞቹ (ፕሬዚደንቶቹ) አማካይነት ለመወሰን እንዲያስችለው ነበር፡፡
ይህ የሰኔ 7/1997ቱ አዋጅ ቁጥር 454/1997 ዓ.ም. በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡ በሶስት ዳኞች ሲመሩ የነበሩት የከፍተኛ ፍርድቤቶች የፍታብሄር ችሎቶች በአንድ ዳኛ ብቻ እንዲከናወኑም አዋጁ ይደነግጋል፡፡
ይህም የዳኞች እጥረት አለ የሚል ምክንያት የተሰጠው ቢሆንም በዚያ የምርጫ ወቅት በዚያ የጥድፊያ ደረጃ አዋጁ እንዲወጣ የተደረገበት እውነተኛ ምክንያት ግን – በየፍርድቤቶቹ ለኢህአዴግ አልታዘዝም ብለው የሚጠረጠሩ የከፍተኛ ፍርድቤት ዳኞች ካሉ – እነሱን ለኢህአዴግ ታዛዥ በሆኑና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በገፍ ተመርተው በወጡ የኢህአዴግ ካድሬ ዳኞች በመተካት የፈለገውን ውሳኔ ለመወሰን ነበር፡፡
ኢህአዴግ በሥልጣኑ ከመጣህበት ፈጣሪንም አያምንም (ቤተክርስትያንና መስጊዶች ውስጥ ገብቶ የሚፈተፍተውን ተመልከተው)፡፡ ሰውንም አያምንም (ካድሬዎቹና ባለሥልጣናቱን እንዴት እንደሚቀይዳቸው ተመልከተው)፡፡ ተቋማትንም ደግሞ አያምንም (እንዴት ተቋማቱን ሁሉ በጆሮጠቢና በካድሬ ሸብቦ እንደያዛቸው ተመልከተው)፡፡
ከዚህ የኢህአዴግ የማይለቅ ተፈጥሮ በመነሳት፣ ኢህአዴግ የምርጫ ቦርድ ከእጄ ቢያፈተልክብኝ ብሎ ለመጠባበቂያነት፣ በፈጣን አዋጅ ሁሉ በቁጥጥሩ ሥር አውሎ በተጠንቀቅ ያቆመውን ፍርድቤት ራሱ ግን መቶ በመቶ አምኖ ሊለቀው እንዳልፈለገ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የሚሆን አንድ ክስተት አንስቼ ላብቃ፡፡
በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በሥራ ላይ የነበረው የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ – ‹‹በምርጫ ሂደቶች ላይ የተፈጠሩ ህገወጥ ድርጊቶችን በተመለከተ የምርጫ ቦርድ በሚሰጣቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ ያለው ወገን፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት በህግ ጉዳዮች ላይ ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው›› የሚል ግልጽ ድንጋጌ አስቀምጦ ነበር፡፡
ምርጫውን ለማጭበርበር የቆረጠው ኢህአዴግም – ከላይ እንዳስረዳሁት – ወደ ፍርድቤት መጥቶ የሚስተካከል ነገር እንዳይኖር ፍርድቤቱን ለዓላማው ዝግጁ አድርጎ በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ ነበር፡፡ ሆኖም ፍርድቤቱ ራሱ በሆነ ተዓምር ከእጁ ቢያፈነግጥበትስ?
ኢህአዴግ እምነቱን ሁሉ በጠቅላይ ፍርድቤትና በምልምል ሹመኛ ዳኞቹ እጅ ላይም መጣል አልፈለገም፡፡ ስለሆነም አንድ በዓይነቱ የተለየ አዲስ ዓይነት ድራማ አዘጋጀ፡፡ ለዓላማውም አየለ ጫሚሶን አሰማራው፡፡
የአየለ ጫሚሶ ፓርቲ ድምጼ ተጭበርብሮብኛል በሚል የምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንዲሻርለት የሚጠይቅ የክስ አቤቱታውን ምርጫው ይፋ በተደረገ ማግስት በምርጫ ህጉ መሠረት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤቱ አቀረበ – ተባለ፡፡ ከፍተኛ ፍርድቤቱም ክሱን ተቀበለና – የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ትክክል ነው ሲል ፈጣን ውሳኔ ሰጠና አየለ ጫሚሶን አሰናበተው፡፡
አየለ ጫሚሶ ግን (የተሰጠውን ሚሽን አላበቃምና) የከፍተኛ ፍርድቤቱን ውሳኔ አልቀበልም በማለት ለጠቅላይ ፍርድቤቱ የይግባኝ አቤቱታ አቀረበ፡፡ ጠቅላይ ፍርድቤቱም በተመሳሳይ የከፍተኛውን ፍርድቤት ውሳኔ በማጽናት አየለ ጫሚሶን ድምጽ አልተጭበረበረብህም አለው፡፡
በመጨረሻ አየለ ጫሚሶ ወደ ግዳጁ መጨረሻ ደረሰ፡፡ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታውን የማቅረቡን ግዳጅ፡፡ ለሰበር አቤት አለ፡፡ ሰበሩ የወሰነው አስገራሚ ውሳኔ ነበር፡ለለ እንዲህ ይላል፡-
‹‹የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድቤትም፣ ጠቅላይ ፍርድቤትም፣ የክስና ይግባኝ አቤቱታውን ተቀብለው ማሰተናገዳቸው ራሱ ተገቢ አልነበረም፣ የምርጫ ህጉ ለፍርድቤቶች የሰጠው
ሥልጣን በህግ ጉዳዮች ላይ ክርክር ሲነሳ ያ ንን ብቻ ለመዳኘት ነው እንጂ በፍሬነገሮች ላይ – ስንት ምርጫ ካርድ ማን አገኘ? እያለ ኮሮጆ በድጋሚ የማስቆጠር ሥልጣን አልተ
ሰጠውም፣ ፍርድቤት በአስተዳደራዊ ውሳኔ ዎች ላይ ጣልቃ መግባቱም ህገወጥ ነው፣ በመሆኑም ፍርድቤት የምርጫ ቦርድ በሚሰጣቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ላይ ጣል
ቃ ገብቶ መወሰን አይችልም!››
እንግዲህ ከላይ በገለጽኩት ፈጣን-ሎተሪያዊው የሰቤ 97 አዋጅ (አዋጅ ቁጥር 454/1997 ዓ.ም.) መሠረት ይህንን ፍርድቤቶች በምርጫቦርድ አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ጣልቃ መግባት አይችሉም፣ ይህን መሰል ክስም ሲመጣላቸው ከጅምሩ ውድቅ ማድረግ አለባቸው፣ የሚለውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ የሌለው የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ – በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ፍርድቤቶች ሁሉ በተመሣሣይ አኳኋን እንዲወስኑ የሚያስገድድ ነውና – ሰበር ችሎቱ በአየለ ጫሚሶ ላይ የሰጠው ትያትራዊ ውሳኔ – በሁሉም ፍርድቤቶች እንዲፈጸም በቀላጤ ለሁሉም የሀገሪቱ ፍርድቤቶች ተበተነላቸው፡፡
በዚህ ዓይነት ኢህአዴግ – በአዋጅ የተሰጠን የፍርድቤትን ሥልጣን እየነጠቀም፣ ምርጫ ቦርዱ ከእጁ ከወጣበት በአዋጅ ዝግጁ አድርጎ በተጠንቀቅ ባቆመው ፍርድቤቱ ለማፈን ተዘጋጅቶም፣ የ1997ቱን የምርጫ ጦርነት በማንኛውም እጁ ላይ ባለ ህጋዊም ህገወጥም መንገድ ለመቀልበስ በተንቀሳቀሰበት ወቅት – ፍርድቤቶችንና የምርጫ ቦርድን ለመቆመሪያነት የተጠቀመባቸው በዚህ መልኩ ነበር፡፡ ይህ ከሆነው እጅግ በጣም ኢምንቱ ነው፡፡ የሆነው ሁሉ ኢህአዴጋዊ ተቋማዊ ሸፍጥ ይጻፍ ቢባል እንኳን አንድ አርቲክል፣ አንድ ትለቅ ጥራዝ ራሱ አይበቃውም፡፡
እነዚህን ሁሉ ያለፍንባቸውን ኢህአዴጋዊ አብነቶች እንዳነሳ ያስገደደኝ፣ አሁን ያለው ኢህአዴግም (ብልጽግናም) በጠቅላይ ፍርድቤቱ (እና በሌሎቹም የዳኝነቱ ተቋማት) እና በምርጫ ቦርዱ በኩል ያንኑ የምናውቀውን ሸፍጡን ደግሞ የመቆመር ብዙ ምልክቶች ያየሁበት ስለመሰለኝ ነው፡፡
ስላለፈው ለህዝብ ሊያጋልጡና ሊለውጡ ያሰቡ ባለሙያዎችና አጥኚዎች ይጻፉበት፡፡ ለዛሬ ግን ይህንኑ ብዬ ላብቃ፡፡ አሁን የምናየው የምርጫቦርድ እና ፍርድቤት እሰጥ-አገባ የሚመስል ተሳትፎ ነገር፣ የተለመደው የኢህአዴግ ተቋማዊ ሸፍጥ ይሁን፣ ወይስ ከእነዚህ ተቋማት በስተጀርባ የቆሙት የሁለቱ ጠንካራ ሴቶች ፍልሚያ ይሁን፣ ምንነቱንና ውጤቱን ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
መልካሙን ተመኝቼ ተሰናበትኩ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ!