>

የመጅሊስ ችግር እንዳይቀረፍ የሚፈልገው አካል ማን እንደሆነ ለህዝቡ ግልጽ ሆኗል...!!! (አህመዲን ጀበል)

የመጅሊስ ችግር እንዳይቀረፍ የሚፈልገው አካል ማን እንደሆነ ለህዝቡ ግልጽ ሆኗል…!!!
አህመዲን ጀበል

 

*… ሕዝቡ ጥያቄውን በመጅሊስ  በመገኘት ለመጅሊስ አመራሮች ለማቅረብ ሲነሳም ፖሊስ መንገድ ከመዝጋት ባሻገር በየመንደሩ የዉስጥ ለዉስጥ መንገዶች ጭምር ፖሊሶች ተሰማርተው አስለቃሽ ጭምር ተኩሰው ሰዉን በተኑ! ደበደቡ!!!
 
*… «የሕዝበ ሙስሊሞች ትግል የነጻና ሕዝባዊ ተቋም እንጂ የትኛውንም ግለሰብ ለማንገስ አይደለም!!!»
 
በርካቶች «ስለምን የመጅሊስ ችግር ለምን ቶሎ አይፈታም? አትሸወዱ አካሄዱን ስናይ የመጅሊስ ችግር እንዲፈታ አይፈለግም። ዳግም ወደ ትግል እንግባ።» እያሉ ሲጠይቅም ታገሱ ስንል ቆየን። ባለፉት ዓመታት ለሀገራዊ አጀንዳ ቅድሚያ በመስጠት በርካታ ችግሮች እየታዩም ጭምር ችግሮች በሂደት ይፈታሉ በሚል በትዕግስት ቢጠበቅም የመጅሊስ ችግር እንዲወሳሰብ እንጂ እንዲፈታ አልተፈለገም። ችግሮችን በተቋማዊ አሰራር ለመፍታት ሲባል የጠቅላላ ጉባኤ ሲጠራ የሰላም ሚኒስቴር «የመጅሊስን ጠቅላላ ጉባኤን ማድረግ አትችሉም። ከመንግስት ምርጫ በኋላ አድርጉ። አሁን ብታደርጉም እውቅና አንሰጥም» አለ። ያለሰላም ሚኒስተር  ፍላጎት የጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ሲደረግም ፖሊስ ልከው የጠቅላላ ጉባኤውን ለማደናቀፍ ሞከሩ። ዑለሞችን አሳደዱ። የጠቅላላ ጉባኤው ሲጠናቀቅም ወደ ተግባር እንዳይገባ አደናቀፉ።
ዛሬ ሕዝቡ ጥያቄውን በመጅሊስ  በመገኘት ለመጅሊስ አመራሮች ለማቅረብ ሲነሳም ፖሊስ መንገድ ከመዝጋት ባሻገር በየመንደሩ የዉስጥ ለዉስጥ መንገዶች ጭምር ፖሊሶች ተሰማርተው አስለቃሽ ጭምር ተኩሰው ሰዉን በተኑ። ደበደቡ።  የተላኩት ካልተሳካላቸው ላኪው ራሱ ይመጣል እንደሚባለው በዛሬው ሂደት ጭምር የመጅሊስ ችግር እንዳይቀረፍ የሚፈልገው አካል ማን እንደሆነ ለህዝቡ ግልጽ ሆኗል።ይህም በራሱ ግልጽ ስኬት ነው።
የህዝብን ጥያቄ ማፈን የሚያዋጣ ቢሆን ኖሮ ለኢህአዴግ መንግስት ይሳካለት ነበር። ህዝበ ሙስሊሙ ለዓመታት ዋጋ የከፈለበትን ተቋም ጉዳይ በሚያማምሩ ቃላት  ሳይሆን በተግባር ሊመለስለት ይገባል። በመላ ሀገሪቱ ህዝበ ሙስሊሙ ጉዳዩን በአንክሮ እየተከታተለው ነው።የመፍትሄ አቅጣጫ ላይም እየመከረ ይገኛል።
«የሕዝበ ሙስሊሞች ትግል የነጻና ሕዝባዊ ተቋም እንጂ የትኛውንም ግለሰብ ለማንገስ አይደለም»
የሕዝበ ሙስሊሙን አጠቃላይ ሁኔታና አሁን ያሉትን የመጅሊስ ችግሮችን በጥልቀት ያልተረዱ አንዳንድ አካላት የመጅሊስን ችግሮችን ስናነሳ የጉዳዩን ትክክለኛ ገጽታ ካለመረዳት ጉዳዩን የመጀሊስ አመራሮችን፣ ወይም ሽማግሌ ወይም ዑለማ ካለማክበር ጋር አያይዘው ሊያነሱ ሲሞክሩ አስተዉለናል። ፥አንዳንድ የመንግስት አመራሮችና የተወሰኑ የክርስትና እምነት ተከታዮች ደግሞ የመጅሊስ ችግር ሲነሳ «ሙፍቲ ሀጂን  የመሰለ ታላቅ አባት ፈጣሪ ሰጥቷችሁ እንዴት ትቃወማላችሁ?» ሲሉ ይደመጣሉ።
የህዝበ ሙስሊሙ የዓመታት ትግል የህዝቡን ችግሮች የሚፈታ፥መከታ የሚሆንለት፥ አንድ አድርጎ በሕግ አግባብ የሚመራ፥ ለመብቱና ለልማቱ የሚቆምለት ተቋምን መጎናጸፍ ነው። የተቋሙ መሪዎችንም በመንግስት እንዲሾምለት ሳይሆን መሪዎቹን ራሱ ለመምረጥ እንጂ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እድሪስን ወይም ሌላ ግለሰብን ለስልጣን ለማብቃት አይደለም።
 የሩቁን ብንተው እንኳ ከ2004 ጀምሮ በድምጻችን ይሰማ ትግል ጊዜ ከ30 በላይ ሙስሊሞች የተገደሉትት፥ ከ5ሺህ ባለይ በተለያዩ ደረጃ በፖሊስ የተደበደቡትና የቆሰሉት፥ ከ20 ሺህ በላይ ቀናት እስከ ዓመታት የታሰሩት እና በርካቶች ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱት ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ ወይም ሌላ ግለሰብን ለማንገስ አልነበረም።ሕዝበ ሙስሊሙ ከህወሃት ጋር ለዓመታት ሲታገል ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እዚያው መጅሊስ ዉስጥ ከመንግስት ተስማምተው ሲሰሩ ነበር።
መጅሊስ መጋቢት 4 ቀን 1968 ከተመሰረተ ጀምሮ ላለፉት 45 ዓመታት በመጅሊስ ዉስጥ ነበሩ። ጉዳዩን ከግለሰብ ጋር ለማያያዝ የሚፈልጉት አካላት እኔ ከነርሱ በላይ ዑለማን ወይም ሽማግሌን የማከብር ሰው ነኝ። ሆኖም ማንም አካል ከሕዝቡ ሙስሊሙ በላይ ባለመሆኑ ሲያጠፋ ይጠየቃል። ይተቻል። በዑለማ ስም ወይም በሽማግሌ ስም ሕዝባዊ ሀላፊነት ላይ ተቀምጦ ከተጠያቂነት ነጻ መሆን አይቻልም። የትኛውም ግለሰብ ከሕዝብና ከህግ በታች እንጂ ከህግ በላይ አይደለም።እንኳንስ በኛ ዘመን ያለ የነቢዩ ከሊፋዎችና ሰሀባዎች መሪ ሲደረጉ በተሰጣቸው ሀላፊነት ምክንያት ተተችተዋል። ተከሰዋል።ተወቅሰዋል። መሪ የህዝብ አገልጋይ እንጂ አለቃ አይደለም።
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እስከ ዛሬ ሽማግሌንና ዑለማን በማክበር ለህዝብ ይፋ ያላደረግኳቸውን የድምጽ ቅጂን፥ሰነዶችን ጨምሮ ያሉትን እውነታዎች ምንም ሳልደብቅ በዝርዝር ይፋ አደርጋለሁ። ለማንኛው ላለፉት 45 ዓመታት ሀጅ ዑመር እድሪስ በመጅሊስ ዉስጥ እንደነበሩ ያለተረዱና የተቋም ጥያቄውን ከግለሰብ ጋር ለማያይ ለሚፈልጉ ሰዎች ግልጽ ለማድረግ ስል ከመጅሊስ ጋር ተያይዞ ጥቂት እውነታዎችን ላንሳ።
1. በ1968 መጋቢት 4 ቀን መጅሊስ ሲመሰረት በመስራች ጉባኤ አባልነት በመጅሊስ ሰነድ ላይ እንዲመዘገቡና እንዲፈርሙ ከተመረጡት  75 የመስራች ጉባኤ አባላት መካከል ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እድሪስ አንዱ ነበሩ።በዝርዝሩ ስማቸው በ46ኛ ተራ ቁጥር ላይ ተጠቅሷል።
2.  ከ1968 እስከ 1985  ለ18 ዓመታትም የመጅሊስ ጠቅላላ ጉባኤ አባል ነበሩ።
3. ግንቦት 6 ቀን 1981 ከሀጅ ሙሐመድ ሳኒ ሀቢብ ሞት በኋላ በተደረገው የፕሬዝዳንት ምርጫ ፊርሚያቸውን ካስቀመጡ 52 የጠቅላላ ጉባኤ በአላት መካከል ሀጅ ዑመር እድሪስ 15ኛ ተራ ቁጥር ላይ ነበሩ።
4. በጥቅምት 5-9 ቀን 1985  በአዲስ አበባ በምኒልክ 2ኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት አዳራሽና በየካቲት 66 የፖለቲካ ት/ቤት(የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፋካልቲ) አዳራሽ በተደረገው ጉባኤና ምርጫ ላይ ሀጅ ዑመር እድሪስ ከመጅሊስ ጠቅላላ ጉባኤ አባልነት ተሰናብተው በመጅሊስ ፕሬዝዳንትነት ለተመረጡት ሸኽ መሀመድ አሕመድ ሰኢድ አማካሪነት ከሌሎች ጋር ተመረጡ።
በእለቱ አማካሪ የተደረጉት የመጅሊስ መስራችና አንጋፋ ከተባሉ ሌሎች ዓሊሞችና ሽማግሌዎች ከሆኑት ከእነ ሐጂ ዙልመካን  ጀማል፥ሐጂ ሃሚድ የሱፍ፥ሐጂ መሐመድ ወሌ፥ሐጂ ዘይኑ ሙቀና፥ ሐጂ መሐመድ ባሲጥ፥ሐጂ ሰኢድ አህመድ ሙስጠፋ፥ሐጂ መሀመድ ሣዲቅ አይሐታ፥ ሐጂ ጃዕፈር ኸሊል፥ሐጂ መሐመድ ያሲን፥ሐጂ ሰዒድ ዩሱፍ፥ሐጂ  መሀመድ አህመድ ቡሬ፥ሐጂ ሙስጠፋ ሐቢብ፥ሐጂ ማህመድ ሁሴን አብደላ፥ሐጂ መሐመድ ሥራጂ መሀመድ እና ሐጂ አወል መሀመድ ጋር አማከሪ ተደረጉ። ከ1985-1986 ድረስም የመጅሊስ ሊቀመንበር(ፕሬዝዳንት) አማካሪ ሆነው አገለገሉ።
5. በየካቲት 14 ቀን የአንዋር መስጂድ ግርግርና የመንግስት ጥቃት ከ10 ሙስሊሞች በመንግስት የጸጥታ አካላት ከተገደሉ በኋላ በሙፍቲ ስር ሆኖ የተዛባ መረጃ በመስጠት እያሳሳታቸው ያለው ቃሲም ታጁዲንን ጨምሮ በርካታ የመጅሊስ አመራሮችና ተቃዋሚዎቻቸው ታሰሩ።በጊዜው ሳይታሰሩ የቀሩት ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እድሪስ ሕዝቡ እንዲያረጋጉና የኢድ ሰላት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ሆነው በመንግስት ተመረጡ።
6.  በ1988 ከቢሾፍቱ ከተማ መንግስት ለርሱ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን ሰብስቦ የመጅሊስ አመራርን ሲመርጥ ሀጅ ዑመር እድሪስም በድጋሚ የመጅሊስ ጠቅላላ ጉባኤና የዑለማ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመረጡ።  እስከ 1992 ድረስም በዚሁ ቆዩ።
7. ሕዝቡ በ1988 በጊዜያዊነት የተቀመጡት ምትክ የመጅሊስ ምርጫ ይደረግና መሪዎቻችንን እንምረጥ ብሎ በመጠየቁ። 1992 ሚያዚያ ምርጫ ተደረገ። ሙፍቲም የአዲስ አበባ መጅሊስ ሊቀመንበር(ፕሬዝዳንት) ሆነው ተመረጡ። የአዲስ አበባ መጅሊስ ፕሬዝዳንትም ሆነው እስክ 2001 ቆዩ።
8. በተጨማሪም በተጨማሪነት ከ1992 አንስቶ እስከ 2000 ድረስ የዑለማ ምክር ቤት ሊቀመንበር ነበሩ።
9. በሚያዚያ ከ2001 በጊዜያዊነት ተብሎ በተደረገው ምርጫ ሀጅ ዑመር ከአዲስ አበባ መጅሊስ ፕሬዝዳንትነታቸው ተነስተው ወደ ፌደራል መጅሊስ አቀኑ። በዚያም እስከ 2005 መስከረም ድረስ የፌደራል መጅሊስ መስጊድና አውቃፍ ዘርፍ ሀላፊ ነበሩ።
10. በፌደራል ጉዳይ ሚኒስተር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም መሪነት በተደረገው የ2005 ምርጫ ላይ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር በአዲስ አበባ ተመራጭ ሆኑ።ከ2005 እስከ 2010  የፌደራል መጅሊስ የጠቅላላ ጉባኤው አባል፥የመስጊድና አውቃፍ ዘርፍ ሀላፊ እንዲሁም  የዑለማ ምክር ቤት አባል ሆነው ቆዩ።
11. ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ህዝበ ሙስሊሙና የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በመጅሊስ ጉዳይ ጥያቄ ሲየቀርብ መጀሊስን በመወከል ከጠቅላይ ሚ/ሩ ጋር ከቀረቡት መካከል ነበሩ።
12. በ2010 ሰኔ 26  እስከ ሚያዚያ 23 ቀን 2011 ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባቋቋሙት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ የኮሚቴው ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢ ተደርገው ተሾሙ።
13.  ከሚያዚያ 23 ቀን 2011 በሸራተን በተካሄደው የመጅሊስ ጉባኤ ላይ የሽግግር ጊዜ መጅሊስን ለ6 ወራት እንዲመሩ ከሌሎች 26 ዑለሞችና የቦርድ አባላት ሲመረጡ የመጅሊስ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ። ለስድስት ወራት የተባለው የሽግግር ጊዜ የሚለዉን ሀላፊነት በአግባቡ ሳይወጡ የተሰጣቸው ሀላፊነት 26ኛ ወሩን  ያዘ። አሁን ደግሞ በግልጽና በይፋ የተሰጠ ኃላፊነትን ሆኖ ሳለ አንዴ «ስድስት ወር ብሎ ነገር የለም። ቋሚ ነን።»  ሌላ ጊዜ ደግሞ «እንደ ፓትሪያርኩ አንዴ ተመርጫለሁ እስከ ሕይወት ፍጻሜ ድረስ አልወርድም» ማለት ጀመሩ።
በጥቅሉ ከዘመነ ደርግ እስከ ዛሬ መንግስታት ሲለዋወጡ እርሳቸው ሳይለወጡ ስልጣን ላይ የቆዩ ናቸው። ታዲያ ከመጅሊስ ምስረታ እስከዛሬ ድረስ  ለ45 ዓመታት ከመጅሊስ አመራርነት ንቅንቅ ያላሉትን ሰው ልክ ሕዝበ ሙስሊሙ  ታላቅ ተጋድሎ አድርጎ በ2011 በሸራተን ጉባኤ በተዓምር በድንገት ያገኛቸው መሪ አስመስሎ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጉዳይ በ90 ዓመት አዛውንት መልካም ፈቃድ ስር መወሸቅ የኢትዮጵያ ሙስሊም ተቋም አልባ ማድረግ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም!
 የማንም ግለሰብ ክብር ከኢስላምና ከሙስሊሞች ሕልዉናና መብት በላይ ፈጽሞ እንዲሆን ሊፈቀድ አይገባም! ይህን ያክል ዓመታት ከጅምሩ እስከ ዛሬ የመንግስት መሳሪያ ሆኖ ሙስሊምን ሲያስመታ የነበረ ተቋም ኃላፊነቱንና አማናውን ባለመወጣቱ  ይህን ያክል ዓመታት ከዉልደቱ እስከ ዛሬ በተቋሙ አመራርነት በመቆየቴና ሕዝቡን እንደሚፈልገው ባለማገልገል «ይቅርታ» ጠይቀው  ህዝቡ ለሚመርጠው የተሻለ አካል ማስረከብ አንጂ «እንደ ሲኖዶሱ መሪ ፓትሪያርኩ አንዴ ተመርጫለሁ አልወርድም። ምርጫ አይኖርም።ዘላቂ ነኝ» በሚል በተደጋጋሚ ቃል በማጠፍና ከሕግና ተቋማዊ አሰራር በማፈልገጥ ሌሎች ዑለሞችንና አዛዉንቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነትን እንዳይወጡ ሲደረግ ብሎም ሕዝበ ሙስሊሙን ተቋም አልባ ወደማድረግ ሲኬድ ጉዳዩ የተጣያቂነትና የህግ የበላይነት መሆኑ ቀርቶ ከዓሊም ማክበር ወይም ሸማግሌን ከማክበር  ጋር በማያያዝ ለማዳፈን ሲሞከር፣ በማባበል፣በስም ማጥፋትና በዛቻ እውነታዉን እያወቅን እኔን ጨምሮ ለዓመታት የታሰርንበትና ዋጋ የከፈልንበት ተቋማችን ጉዳይ ላይ ዝም እንላለን ብለው እንዴት አሰቡ?
Filed in: Amharic