>
5:13 pm - Monday April 19, 8652

መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገው የፌዴራሊዝም አነሳስና ውድቀት፣በኢትዮጵያ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ( ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገው የፌዴራሊዝም አነሳስና ውድቀት፣በኢትዮጵያ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

መግቢያ


የማህበራዊ ሳይንስ አስተሳሰብና፣ በማህበራዊ ሳይንስ ላይ የቤተ ሙከራ ምርምር ማድረግ ተገቢ ቢሆንም በአግባቡ ካልተያዘ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ሊጠገን የማይችል ሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በሌላ አነጋገገር በአንድ ማህበረሰብ ወይም ሀገር ላይ ገቢራዊ የሚሆን የፖለቲካ አስተሳሰብ በአግባቡ ካልተያዘ ዘመን ተሻጋሪ ችግሮችን ይቀፈቅፋል፡፡ ኢትዮጵያ ለእንዲህ አይነት ችግሮች ለተደጋጋሚ ግዜ ተጋልጣ ቆይታለች፡፡ የሶሻሊስት አርበኞች ከህዝቡ ስነ ልቦናና ባህል ጋር ሳያዛምዱ እንደው ዝም ብለው በግድ፣ በጉልበት የሶሻሊስት ርእዮትን ለመዝራት ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ የጎሳ ፖለቲከኞች ጥቂት የራሳቸውን ደጋፊዎች በማሰባሰብ፣ የምእላተ ህዝቡን ፍላጎትና ውሳኔ በነጻነት እንዲወስን ሳይፈቅዱ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት በኢትዮጵያ ዘርግተዋል፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ችግሮችን ቀፍቅፏል፡፡ የሀገሪቱን ብሔራዊ አንድነት አላልቷል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንደ አሽን እንዲቀፈቀፉ አድርጓል፡፡ ( በነገራችን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች የመንግስት አካላት፣ የኢመደበኛ ቡድን ታጣቂ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡)በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች እከፊ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈጸሙ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ ልማትን ወደኋላ ጎትቷል፡፡

በዛሬው ጽሁፌ የተለያዩ ቋንቋ የሚናገሩ፣የራሳቸው ባህል እምነት ያላቸው ከ83 በላይ የጎሳ ቡድኖች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ፣ የጎሳ ፖለቲካ አነሳስና ውድቀት በተመለከተ ፣ እንዲሁም ወይም ከዚህ ባሻግር በጎሳ ላይ ተመስርተው እንዲሰሩ በህገመንግስት የተፈቀደላቸው ክልላዊ መንግስታት ስላጋጠማቸው እድልና ተግዳሮት በተመለከተ የግል አስተያየቴን አሰፍራለሁ፡፡ 

በቅድሚያ ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ የነበረውን የኢትዮጵያን ፖለቲካዊና ማህበራዊ አውድ በወፍ በረር ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡ ይህን ተከትሎ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ጉዞ እመረምራለሁኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር ሀገሪቱ የጎሳን ፖለቲካ ገቢራዊ ካደረገች ወዲህ ያጋጠማትን የብሔራዊ አንድነት መላላት ጉዳይ፣ ድህነት በተመለከተ፣የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የጸጥታ ጉዳይ በተመለከተ ለመዳሰስ እሞክራለሁኝ፡፡

በመጨረሻም  የመፍትሔ ሃሳቦች የምላቸውን ለማቅረብ እሞክራለሁኝ፡፡ 

የጽሁፉ አውድ፣ኢትዮጵያ

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 2020 የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 108 ሚሊዮን ግድም እንደሚገመት፣ከአፍሪካ ከናይጄሪያ በመለጠቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በኢትዮጵያ እንደሚኖር የስነ ህዝብ ጥናት ተጠባቢዎች ካደረጉት ጥናት መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በሻግር የራሳቸው ባህል፣ቋንቋ ወይም ዳይሊክቲክስ (dialects ) ያላቸው ከ83 በላይ ጎሳዎች ወይም ብሔሮች እንደሚገኙ በተለያዩ የጥናት መጽፍት ላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንዳንድ የጥናት ወረቀቶች ላይ እንደተጠቀሰው ከህዝብ ብዛት አኳያ በፐርሰንቴጅ ሲቀመጥ የሚከተለውን ስእል ይሰጠናል፡፡ ለአብነት ያህል የኦሮሞ ብሔር 34.4 ፐርሰንት፣ አማራ ብሔር (27 ፐርሰንት)፣ እንዲሁም ሶማሊ (6.2 ፐርሰንት)፣ ትግራይ (6.1 ፐርሰንት)፣ ሲዳማ (4 ፐርሰንት)፣ጉራጌ (2.5 ፐርሰንት)፣ ወላይታ ( 2.3 ፐርሰንት)፣ ሃዲያ (1.7 ፐርሰንት)፣ ጋሞ (1.5 ፐርሰንት)፣ ጌዲኦ (1.3 ፐርሰንት)፣ከፊቾ (1.2 ፐርሰንት)፣ሌሎች ደግሞ ወደ 8.8 ፐርሰንት እንደሚገመቱ አንዳንድ የስነ ህዝብ ጥናት ወረቀት ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተለየች ናት፡፡ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ግንባታ የአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ውጤት አይደለም፡፡በተቃራኒው የዘመናዊቷ ሀገራ ግንባታ ሂደት ብዙ ክፍለ ዘመናትን የተጓዘ ወይም የተሻገረ ነው፡፡ ይህ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ግንባታ እስከ 1974 (እ.ኤ.አ) መቆየቱን ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ይህን ተከትሎ ማለትም እንደ ጎርጎሮሲያን አቆጣጠር 1974 አብዮት ፈንድቶ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም ይመራ በነበረው ደርግ ወታደራዊ ሀይል ሃይጃክ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ደርግ በተራው ኢትዮጵያን ለመግዛት በለስ ቀንቶት እስከ 1991 ( እ.ኤ.አ.) በስልጣን ላይ ለመቆየት ችሏል፡፡ በቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረትና በተባበረችው አሜሪካ መሃከል የነበረው ቀዝቃዘቀው ጦርነት እያከተመለት በመምጣቱ ምክንያት እና በቀድሞው አማጺያን ትግል የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 አክትሞለታል፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1991 አካባቢ በኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሰቱን በዋነኝነት የህዝባ ወያኔ ሀርነትና የኢህአዲግ አባል ድርጅቶች በዋነኝነት፣ኦነግና ሌሎች የጎሳ ድርጅቶች ስልጣኑን ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ ( በኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ዘመን የነበረውን ያስተሳውሷል)፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የጎሳ ፌዴራሊዝም ዋነኛ መሃንዲስ የህውሃት ኢህአዲግ አገዛዝ ከመሆኑ ባሻግር ኢትዮጵያን ለ27 አመታት መግዛቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (እ.ኤ.አ. መጋቢት 2018 የወያኔ አገዛዝ ከማእከላዊ መንግስት ስልጣኑ ለቆ እስኪሄድ ማለቴ ነው፡፡)፡፡ ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የወያኔ ቡድን ከመሃሉ ወጥቶ ሌሎች የቀድሞ አባል ድርጅቶችን በማቀፍ ‹‹ ብልጽግና ›› በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ‹‹ የኢህአዲግ 1- ለ ›› ወይም በእንግሊዝኛው አጠራር  (The current government, dubbed as being a modified extension of EPRDF-I b )  የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው የወያኔ ከማእከላዊ መንግስት ገሸሽ ማለት ዋነኛው ምክንያት ህዝባዊ አመጽና በኢህአዲግ አባል ድርጅቶች ውስጠ ትግል መሆኑ የሚያከራክር አልነበረም፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ የጎሳ ግጭቶች ተባብሰው ቀጥለዋል፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች በሃይማኖት እና በብሔራቸው ማንነት የተነሳ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ የኦሮሞ የፖለቲካ ሰዎች የኦሮሞ ወጣቶች ያካሄዱት አብዮት ተቀልብሷል በማለት የማእከላዊ መንግስቱን በየጊዜው ሲከሱ ይስተዋላል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ፣በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ አንዳንድ ሰዎች በበኩላቸው ዶክተር አቢይን ለማመን እንቸገራለን ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከብልጽግና ፓርቲ ውጪ ያሉና፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግዛት ውስጥ በኦሮሞ ብሔር ስም የተደራጁና የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች በበኩላቸው የዶክተር አቢይን የብልጽግና ፓርቲና መንግስትን ለመገዳደር ህብረት ፈጥረው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ በሌላ አነጋገር ዶክተር አቢይ ለሚመሩት የብልጽግና ፓርቲ ይሁንታ ወይም ድጋፋቸውን ላለመስጠት ከወሰኑ ቆይተዋል፡፡

በአጠቃላይ በአለፉት ሶስት አስርተ አመታት በጎሳ ፌዴራሊዝም በተዋቀረው መንግስት የነበረው የኢትዮጵያ ጉዞ ጠመዝማዛና ጎምዛዛ ነበር ወይም ነው በማለት መደምደም ይቻላል፡፡ ሀገሪቱ በአስር ክልላዊ መንግስታት የተከፋፈለች ሲሆን ፣ በመሃከላቸው ያለው ድንበር በውል የተሰመረ አይደለም፡፡ በብዙ አካባቢዎች  በድንበር ይገባኛል ምክንያት የሚደረጉ ግጭቶች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ ሌላው የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት ያመጣብን ጣጣ ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እስከመገንጠል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን ይችላል የሚለውና በኢፌድሪ ህገመንግስት አንቀጽ 39 (1) ይገኝበታል፡፡ ከዚህ ባሻግር የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሁሉንም የኢትዮጵያ ጎሳዎች (ብሔር) የፖለቲካ ማህበረሰብ ቀይሯቸዋል፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዳቸው የራሰቸውን የፖለቲካ መንግስት እንዲመሰርቱ የሚፈቅድ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን የመረጃ ምንጭ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተጻፈውን እንዳለ ለአንባቢው ዋቢ እንዲሆን ጠቅሼዋለሁ፡፡

<<   The constitution thus accords official recognition of Ethiopia’s ethnic communities, transforming them into political communities. This means that the Ethiopian Constitution allows every ethnic group to form its own political state. These 12 Marara Gudina interview with Addis Getachew Tadesse. 06.12.2019. https://www.aa.com.tr/en/africa/ethiopiamerger-election-and-popular-apprehension/1665642 13 Ministry of Foreign Affairs. (Feb 2021). General Country of Origin Information Report Ethiopia. PP 7-9 14 Addis Fortune News. (Jan 4,2020). English Weekly Newspaper, Vol 19. No.1027. Addis Ababa, Ethiopia. 15 The regional states or Kililoch that formed the federation in 1991 were: 1. Tigray; 2. Afar; 3. Amhara; 4. Oromia; 5. Somali; 6. Benishangul-Gumuz; 7-11 Southern Nations, Nationalities, and Peoples (merger of 5 regions); 12. Gambella; 13. Harari; and 14. The two administratively independent cities are Addis Ababa and Dire Dawa. Sidama becomes the 10th National Regional States in June 2020, while the other ethnic groups from the Southern Region were also filing their demands to become independent regions. 16https://www.constituteproject.org/constitution/Ethiopia_1994?lang=enPage 4 of 15 narratives accord the sovereignty of states in Ethiopia to what it generically refers to as Nations, Nationalities and Peoples,

 የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሉአላዊ ስልጣን የሚሰጠው ለብሔር ብሔረሰቦች ሲሆን የኢትዮጵያ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት መሰረት በአንድ የጎሳ ክልል አባል መሆን የሚችሉት የክልሉ ተወላጆች ብቻ ናቸው የሚል መብት አጎናጽፏል፣ በአንድ ሉአላዊ የጎሳ ክልል   የተወለደ አንድ ከሌላ አካባቢ በስራም ሆነ በሌላ ምክንያት ከሰፈሩ ወላጆች የተወለደ ግለሰብ ነባር የአካባቢው ጎሳ አባላት እኩል የሆነ መብት እንዳይኖረው ያደረገ መሆኑ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በክልሉ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ቅድሚያ የሚሰጠው ለዛው ክልል የጎሳ (ብሔር) አባላት ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይሁንና በህገመንግስቱ ውስጥ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚለው አስደንጋጭ አንቀጽ ቢደነቆልም አሁን ድረስ ኦፊሻል በሆነ ሁኔታ የጠየቀ አካል ወይም ክልል የለም፡፡ ወደፊት ግን ያስፈራል፡፡ ይህ ግን እውን ያልሆነበት ስትራቴጂክ ምክንያት ነበረው፡፡ በተለይም ባለፉት 27 የወያኔ ኢህአዲግ የግፍ አገዛዝ ዘመን፣ ወያኔ አንድ ጠንካራ ብቸኛ ፓርቲ ለመመስረት ምኞትና አቅድ ስለነበረው ነው፡፡ ( ሌሎች የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የአንድ ጎሳ ፖለቲካ ድርጅት ሳተላይቶች ነበሩ፡፡) ሆኖም ግን ይሁንና እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2018 የወያኔ ቡድን ከማእከላዊ መንግስቱ ስልጣን ለመልቀቅ በመገደዱ ምኞቱ ምኞት ሆኖ ቀርቷል፡፡ በተቃራኒው የፌዴራል መንግስቱ ተቃዋሚ በመሆን በመጨረሻም ድርጅታዊ መዋቅሩ ፈርሶ በተበታተነ ሁኔታ ላይ የሚገኝበት ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንን ባለፉት 27 አመታት  እጅግ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ግብረስየል ስለመፈጸማቸው ከበቂ በላይ ማስረጃ ቢገኝባውም አብዛኛዎቹ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በፍትህ አደባባይ አልቀረቡም፡፡ ይህቺ አለም አስገራሚም፣አስተዛዛቢም ናት፡፡ በተለይም የምእራቡ አለም፡፡ አንዳንድ የምእራብ ሀገራት ፣ በተለይም የተባበረችው አሜሪካ እነኚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙትን የህውሃት መሪዎች ከኢትዮጵያ መንግስት መደራደር አለባቸው በማለት ሲሞግቱ ሳይ ምን ያህል ከራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ባሻግር ሌላ ሀገር ደንታ እንደሌላቸው ማሳያ ነው፡፡

በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ዛሬም ስልጣንን ለግል፣ ለብቻ ለመቆጣጠር ሩጫው በዝቷል፡፡ አንዳንድ የኦሮሞ ብሔርተኞች በፌዴራል ስርአቱ ውስጥ በቁልፍ የስልጣን መሰላል ላይ እየወጡ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አንዳንድ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች በየጊዜው እንደሚሄሱት ከሆነ ቁልፍ የሀገሪቱ የስልጣን ርካብ ወደ አንድ ወገን ብቻ ሊያደላ ይችላል የሚለው የብዙ ኢትዮጵያውያን ብርቱ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገው የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የፖለቲካ ስሪት

የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት እውን እንዲሆን የሚያቀነቅኑ ወይም የጎሳ ፌዴራሊዝምን ስርአት የዘረጉ ግለሰቦች ምክንያታቸውን ያገኙት ‹‹ ከጎሳ ብሔርተኝነት ››ጽንሰ ሃሰብ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ (Proponents of ethnic federalism derive their rationale from the idea of ethno-nationalism)

 << የጎሳ ብሔርተኝነት ›› የአንድ የተለየ የህዝብ መጠሪያ ሲሆን፣ የአንድ  ዘውግ ወይም ጎሳ ተወላጆች በተወለዱበት አካባቢ ራሳቸውን የመምራት መብት እንዳላቸው የሚያሳይ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1995 ላይ በወጣው የኢትዮጵያ ህገመንግስት መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ‹‹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን እድል ለመወሰን ሙሉ ነጻነት አላቸው ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁም ነገር ቢኖር ( እንደ ቁምነገር ከተቆጠረ ማለቴ ነው) ኢትዮጵያ ከአለም ሀገራት ሁሉ በተለየ ሁኔታ የፌዴራል ስርአቱ አደረጃጀት በዋነኛነት በጎሳ መሰረት ላይ እንዲሆን የፈቀደች ሀገር መሆኗን ነው፡፡ ይህም ማለት እያንዳንዱ ብሔር ብሔር ብሔረሰብ የራሱን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብት አለው፡፡ ( ይህ የተጠቀሰው በህገመንግስቱ ውስጥ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ጥናትና ምርምር ውጤት መሰረት ፈረንሳይ ለአለም ያስተዋወቀችውን ብሔረሰብ የሚለውን ትርጉም በኢትዮጵያ ከሚገኙት የዘውግ ማህበረሰቦች መሃከል ሊያሟሉ የሚችሉት ከሶስት አይበልጡም፡፡ መሰረቱን ጎሣ ላይ ያደረገው ፌዴራሊዝም የፈጠረብን ችግር እንዲህ በአጭር ጽሁፍ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ አንዱና ትልቁ አደጋ በሀገሪቱ ምድር ላይ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች እንድ እንጉዳይ እንዲበቅሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠሩ እውነት ነው፡፡ አንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መረጃ መሰረት በሀገሪቱ ወደ 100 የሚጠጉ የተመዘገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ መሰረታቸው ጎሳ ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር  የፌዴራል መንግስቱ አባል የሁኑት ሁሉም ክልሎች የጎሳ ክልሎች ናቸው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን ከብዙ የፌዴራል ስርአትን ከሚከተሉ ሀገራት የተለየች ሀገር ያደርጋታል፡፡ ለአብነት ያህል በአፍሪካ ከሚገኙት የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክና ናይጄሪያ፣ በቀድሞው ዘመን የኮሚንስት ሀገር ከነበሩት ጎዝላቪና ሲቪዬት ህብረት፣ ሌሎች ነጻነት ባለባቸው ሀገራት ማለትም ህንድ፣ የስዊዝ ኮንፌዴሬሽን፣ ካናዳ ካላው የፌዴራል ስርአት የተለየ ነው፡፡ የተሌ የሚያደርገው ደግሞ ጎሳን መሰረት በማድረጉ ነው፡፡( እውቋ የህግ ሰው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሃላፊ ከሆኑ በኋላ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ለግዜው መረጃው የለኝም፡፡) 

ባለፉት ሶስት አስረተ አመታት በሀገሪቱ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ነጻ አውጪ ድርጅቶች እንዲጎመሩ ሰትራቴጂካሊ ነዚች ሀገር ላይ ተሰርቷል፡፡ በዚች ሀገር ላይ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አሽን እንዲፈሉ ሁነኛውን ሚና የተጫወቱት ትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሆናቸው ክርክር የሚያጭር አይመስለኝም፡፡ የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከመጨበጡ በፊት የነበሩት የጎሳ ነጻ አወጪ ድርጅቶች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣የኦጋዴን ነጻ አውጪ ድርጅትና የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ሌሎች ነገዶች የተጠቀሱትን የዘውግ ፖለቲካ ድርጅቶች ዱካ እነዲከተሉ በህገመንግስቱ ሳይቀር እውቅና መሰጠቱ ሲስተዋል የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ሌላው አስገራሚ ዚቅ ሁሉም የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ቅድሚያ የሚሰጡት ቆመንለታል ለሚሉት ነገድና ክልል እንጂ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚደማ ልብ አለመሆኑ ነው፡፡ እዬዬ ሲዳላ ነው፡፡ እንዲሉ ስንቶቹ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ቆሜለታለው የሚሉትን አጠቃላይ ምልአተ ህዝብ የኑሮ ደረጃ አሻሻሉት ተብሎ ቢጠየቅ መልስ የሚገኝለት አይመስለኝም፡፡ ሁሉም የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የሚያመሳስላቸው ግን አንድ ነጥብ አለ፡፡ ሁሉም ነፍጠኛ ብለው በሰየሙት አማራ ተጨቁንን ነበር፡፡ ተበድለናል በማለት ነው ደጋፊያቸውን የሚያሰባስቡት፡፡ አማራውን እንደ ጨቋኝ በማቅረብ የጥላቻ መርዝ በመላው ሀገሪቱ ሲረጭ የነበረው ደግሞ ወያኔ እና ሸሪኮቹ ነበሩ ወይም ናቸው፡፡ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት ሲባል ተጨቁነናል፣ ተገፍተናል ባዮች ናቸው የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶችን የመሰረቱት፡፡ እነርሱ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በስምምነት እንገነባለን ባዮች ናቸው፡፡ መሰረታቸውን ጎሳ ላይ ያደረጉ ፖለቲካ ድርጅቶችን ደጋፊዎቻቸውን በመስበክ ብቀላ እንዲፈጸምም ያደርጋሉ፡፡ ብዙዎቹ በተለይም በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ነጻ አውጪ ድርጅቶችን በማቋቋም የኢትዮጵያን ወተደራዊ አገዛዝ ገርስሰው የጣሉት የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ታሪክ እንደማይቀበሉት መሪዎቻቸው ሳይቀር በአደባባይ ነግረውናል፡፡ እኛ ግን አልገባም ነበር፡፡ ሟቹ አቶ መለሰ ዜናዊ ‹‹ የአክሱም ታሪክ ለወላይታው ›› ምኑ ነው ከማለት ውጪ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ከ100 አመት አይበልጥም በማለት ተዘባብተውብንም ነበር፡፡ መሀመድ ሀሰን የተባሉ ምሁር በአንድ የጥናት ወረቀታቸው ላይ ፍንትው አድርገው እንደ አስቀመጡት ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት የተሰሩ አንዳንድ ሀውልቶች፣ ግጥሞችና ዜማዎች አንድን ብሔር በሌሎች እንዲጠላ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በተለይም ጥላቻው፣ የጎሳ ፖለቲካን መርዝ በተጋቱ ወጣቶች አኳያ መራር ነው፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ የእኛ እና የእነርሱ በሚል በልዩነት ላይ የሚያተኩር፣ እነርሱ በዳይ እኛ ደግሞ ተበዳይ ነበርን በሚል የተመሰረተ ስለሆነ ጥላቻን ለመዝራት ያመቻል፡፡ ሰውን ስሜት በተለይም ወጣቶችን በአጉል ቅስቀሳ ያነሳሳል፡፡ ለማናቸውም የመሃመድን  በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከጻፉት ጥናታዊ ጽሁፍ ለማስረጃነት እንደወረደ ጠቅሼዋለሁ፡፡

‹‹Mohammed Hassen. a Short History of Oromo Colonial Experience 1870 -1990: Part One 1870s-1935,”. The Journal of Oromo Studies. Vol 6, Number 1&2. July 1999.Page 6 of 15 and amplified newly created banners, songs and monuments, resulting in the inculcation of anti-Amhara sentiments. The sentiment is especially held among the younger generations, ››

እድሜአቸው ከ30 አመት በታች የሆኑ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች፣ በጎሳ ክልል ተወልደው ያደጉ ወጣቶች ርበርሳቸው አይተዋወቁም፡፡ ኢትዮጵያንም በቅጡ አያውቋትም፡፡ ወጣቶቹ በአብዛኛው ራሳቸውን የሚገልጹት እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ተጋሩ፣አማራ፣ሶማሊ ወዘተ ወዘተ በማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ማስቀደም አልቻሉም፡፡ ይህ ሁላችንንም ሊያሳዝነን፣ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ከአንድ አመት በፊት ይመስለኛል እኛ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ሲሉ በማህበራዊ ድረገጽ የታዩ ወጣቶች ነበሩ፡፡

የጎሳ ፌዴራሊዝም እውን ከሆነ በኋላ አንዳንድ በጎ ተግባራት አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ በብዙ ክልሎች አወራ ጎዳናዎች ፣ አንድን ክልል ከሌላው ክልል፣የገጠር ከተሞችን፣ ከዋና ዋና ከተሞች ጋር የሚያገናኙ በብዙ ሺህ ኪሎሜትር የሚርቁ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት ማሟላት ባይቻልም በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ከተሞች የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ የኤሌክትሪክና የውሃ መስመሮች ተዘርግተዋል፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ቋንቋዎች ትምህርት ለህጻናት እየተሰጠ ሲሆን፣  የኦሮምኛ ፣ትግርኛ እና ሶማሊ ቋንቋዎች ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ መወሰኑ፣ ፖለቲካ፣ህግና አስተዳደራዊ፣ ባህላዊ ጉዳዮችን ለማሳለጥ የተጠቀሱት ቋንቋዎች ስራ ላይ መዋላቸው  መልካም እርምጃ ይመስለኛል፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እነኚህ መልካም እድሎች የጎሳ ፌዴራሊዝም በፈጠረው ሳንካ ተሸፍነዋል፡፡ ምክንያቱም የጎሳ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያውያንን በዘውግ መሰመር በመከፋፋል ብሄራዊ አንደነታቸውን እያዳከመው በመምጣቱ ነው፡፡

የጎሳ ፌዴራሊዝም ዳፋ በማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ላይ የሚከተሉትን ቀውስ አስከትሏል፡፡

1.መሰረታቸውን ጎሳ ላይ ያደረጉ ግጭቶችና የብሔራዊ አንድነት መላላት

ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት የህዝቡ ፍላጎት ምን እነደሆነ በዲሞክራሲዊ መንገድ፣ በነጻነት እንዲናገር አልተፈቀደለትም፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም አስፈላጊነትና ጠቃሚነት በተመለከተ የየጎሳ ወኪል ነን የሚሉ ኤሊቶችና የፖለቲካ መሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ይናገራሉ፡፡ ጥናታዊ ጽፎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው ኢትዮጵያዊ ምሁራን አይናቸው ደም እስኪመስል ስለ ጎሳ ፌዴራሊዝም አደገኛ ውጤት በብዙ መልኩ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ( ለአብነት ያህል ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ጋሼ ጸጋዬ ገብረመድህን ቀዌሳ፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( አፈሩን ገለባ ያደርግላቸው)፣ ዶክተር ሀይሉ አርአያ፣ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ አቶ ክፍሌ ሙላት፣አቶ ጎሱ ሞገስ፣አቶ ደርበው ተመስገን፣ታዬ በላቸው፣አጥናፉ አለማየሁ፣ አቶ ያሬድ ሃይለማርያም፣ልበሙሉው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ መምህርት መስከረም አበራ ይጠቀሳሉ፡፡ ታሪክ ምንግዜም ቢሆን ውለታቸውን አይረሳም፡፡)

በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት ኤሊቶች ያለፈውን ኢትዮጵያን ታሪክ በመክዳት ወይም በመናድ ኢትዮጵያን እንደገና እንገነባለን ባዮች ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዱን ብሔር ጨቋኝ ነበር፣ በደል ፈጽሞ ነበር በማለት የጎሳ አጋሮቻቸውን ይሰብካሉ፡፡ በውጤቱም ግጭቶች ይስፋፋሉ፡፡በዳይ የተባለው ብሔር አባላት ባልሰሩት ሀጢያት አስከፊ ጥቃት ይከፈትባቸዋል፡፡

በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች የጎሳ ግጭቶች የተቀጣጠሉት፣ ኢትዮጵያውያን በብሔር ማንነታቸው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸው እንደው ዝም ብሎ ሳይሆን፣ የጎሳ ኤሊቶች ወይም አምበሎች በዘሩት የጎሳ መርዝ ምክንያት አቅላቸውን የሳቱ ወጣቶች በከፈቱት ቀውስ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ይኖሩ በነበሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ብቻ ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ አቶ አብዲ ኢሌ የሶማሊ ክልል ፕሬዜዴንት በነበሩበት ጊዜ በሶማሊ ክልል ይኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ በግፍ መፈናቀላቸው፣እንዲሁም በጌዶ እና ጉጂ አካባቢ የነበረው የጎሳ ግጭት በሀዘን የሚታወስ ነው፡፡

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የጎሳ ፖለቲካ በህገመንግስቱ ተቀባይነት በማግኘቱ ምክንያት በብዙዎች ዘንድ እንደ መልካም ነገር እየተቆጠረ መምጣቱ ነው፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች አስከፊ ግድያዎች ቢፈጸሙም፣የጎሳ ማጽዳት ቢፈጸምም፣አስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ቢፈጸሙም፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ስቃይ ቢፈጸምባቸውም በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካን ለማምከን አልተቻለም፡፡ ያሳዝናል፡፡ በነገራችን ላይ እዚህና እዚያ በተለያዩ ግዜያት የሚከሰቱ የጎሳ ግጭቶች፣ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በብሔር ማንነታቸው ብቻ የሚድስባቸው ጥቃት በግዜ ማቆሚያ ካልተበጀለት ውጤቱ የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ለማንም አይበጅም፡፡ ነገሩ አስፈሪና ሁላችንንም የሚያጠፋ ነው የሚሆነው፡፡

ከሰብዓዊ መብት አኳያ በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የጎሳ ፌዴራሊዝም ለጎሳና ለቡድን መብት ቅድሚያ ሚሰት ነው፡፡ ለሰብዓዊነትና ለግለሰብ የሰብዓዊ መብት መከበር በሁለተኛ ደረጃ ትኩረት የሚሰጥ ነው፡፡ ( ሁላችንም እንደምናውቀው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1995 የጸደቀው ህገመንግስት በተባባሩት መንግስታት ቻርትር ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጾችን አካቷል፡፡ ሆኖም ገቢራዊነቱ ሲመዘን አነስተኛ ነው፡፡)  በጎሳ ክልሎች ዋነኛው የስልጣን ባለቤት ወይም ሉአላዊነት የተሰጠው ለጎሳው ክልል ተወላጆች ነው፡፡ ለአብነት ያህል ባለፉት 27 አመታት የሀገሪቱ ስልጣን የያያዘው በጎሳ ድርጅቶች ሲሆን ( ወያኔ ኢህአዲግ ማለቴ ነው፡፡) ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት ቅድሚያ ጥቅም የሚሰጠው ለጎሳው ተወላጆች ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የጎሳ ፖለቲካ መሪዎች በተለያዩ ጎሳዎች መሃከል ልዩነት እንዲፈጠር ስለሚሰብኩ ዜጎች አንዳይግባቡ፣ ስለ ልዩነቶቻቸው ብቻ እንዲያስቡ ያደርጓቸዋል፡፡ በአንድ የጎሳ አጥር ውስጥ የሚኖሩትን የሌላ አካባቢ ተወላጆችን ደግሞ መጤ፣ በደል አድርሰው ነበር በማለት የጎሳ መርዛቸውን ስለሚረጩ ጥቃት እንዲደርሰባቸው ያደርጋሉ፡፡ ለአብነት ያህል ኦሮሞ ተወላጆች በቁጥር ከፍተኛውን ስፍራ በሚይዙበት አካባቢ( በአንዱ የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ሊሆን ይችላል) የሚኖሩ ኢትዮጵዊ ዜጎችን የማግለል፣ ብቸኛ ማድረግ ፣ እንዲሁም እንደ ሁለተኛ ዜጋ አድርገው ይመድቧቸዋል፡፡

 በወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ዘመን፣ ባለፉት 27 አመታት የታዩ ወይም የተመዘገቡ ሪኮርዶች እንደሚያሳዩት ዋና ዋና የመንግስት ስልጣኖች ተይዘው የነበረው በተለይ በጸጥታ አገልግሎት፣ መከላከያ ሰራዊት፣ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ኢኮኖሚክ እድገት ወዘተ በገዢው ፓርቲና በአርሱ ደጋፊ ባለሀብቶች ነበር ( ጥቢ ባለሀብቶች ) አይን ያወጣ አድሏዊነት ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን በተለይም በክልሎች የክልሉ ጎሳ ተወላጆች በማናቸውም እንቅስቃሴዎች አንበሳው ድርሻ የእነርሱ ነው፡፡ በክልላቸው አዛዥ ናዛዥ የክልሉ የጎሳ ፖለቲካ ኤሊቶች ወይም መሪዎች ናቸው፡፡ ምናልባት ከመጪው የምርጫ ውድድር በኋላ የጎሳ ፖለቲካ በሰለተነ መንገድ የሚያከትመለት ከሆነ እንዲህ አይነት ፈሩን የለቀቀ ኢፍትሃዊነት አሰራር ይቀንስ ይሆናል፡፡

በነገራችን ላይ በሀገራችን ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው ( እ.ኤ.አ. 2018-2021 ባሉት ሶስት አመታት የተፈጸሙትን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ልብ ይሏል) ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀጽ 32 ከቦታ ወደ ቦታ ተነቀሳቅሶ የመኖር መብትን ቢፈቅድም፡፡ ይህ ህገመንግስታዊ መብት በብዙ ቦታዎች በየጊዜው ተጥሷል፡፡ ለአብነት ያህል የሌላ ጎሳ ተወላጅ የሆኑና በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች፣ በቤኒሻንጉል፣ በደቡብ ብ/ክ/መ ወዘተ አንዳድ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በነጻነት ሰርተው መኖር እንዳልቻሉ የሚያሳዩ ዜናዎች ሰርክ አዲስ ይሰማል፡፡ የአንዳንድ አካባቢዎች ሹመኞች የንግድ ምልክቶች በአማርኛ ቋንቋ እንዳይጻፍ የከለከሉ አሉ፡፡

በውጤቱም በርካታ የንግድ ሰዎችና ባለሀብቶች በብሔር ማንነታቸው ብቻ ተለይተው ለዘመናት ያፈሩት ንብረቶቸቻው በአንድ ለሊት ወደ ዶግአመድነት ተቀይሮባቸዋል፡፡ተዘርፎባቸዋል፡፡ በቅርብ ግዜ በተፈጠረው አሳዛኝ ሁነት በሻሸመኔ፣ዝዋይ ( ባቱ)፣ አርቦዬ፣ ወዘተ የተፈጸሙት አስከፊ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቋሚ ምስክር ናቸው፡፡ በጎሳ አምበሎች ቅስቀሳ አቅላቸውን የሳቱና በኢመደበኛ ቡድን የተደራጁ ወጣቶች የባለቤቶቹን ማንነት ከለዩ በኋላ ሆቴሎችን፣ትምህርት ቤቶችን፣ የመኖሪያ ቤቶችን ወዘተ ማቃጠላቸውን፣ መዝረፋቸውን በሀዘን እናስታውሰዋለን፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በየጊዜው ጥቃት ከሚፈትባቸው የሃይማኖት ተቋማት ዋኛዋና ቀዳሚዋ ናት፡፡

ከላይ እንደምሳሌ ያቀረብኩት በተለያዩ አካባቢዎች በነቢብም ሆነ በገቢር የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በጎሳ ክልሎች የግለሰብ መብት መከበር ትኩረት እንደማይሰጣቸው ማሳያ ናቸው፡፡ ( በተለይም በአንድ የጎሳ ክልል ነዋሪ ሆነው የክልሉ(ዘውግ) ጎሳ ተወላጅ ላልሆኑት በቁጥር አነስተኛ የሆኑት የማህበረሰብ አካላት….) ከዚህ ባሻግር በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ላይ የተቀመጠውንና ከመብት አኳያ ማለትም በጎሳ፣በዘር ማንነታቸው፣ በሰው ልጆች ላይ ሁሉ ልዩነት መደረግ የለበትም የሚለውን አንቀጽ በጉልህ የጣሰ ድርጊት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጎሳ ላይ መሰረቱን ያደረገው የፌዴራሊዝም ስርአት ለዜጎች እኩል የፖለቲካ ተሳትፎ መሰጠት አለበት የሚለውን አለም አቀፉን  የሰብዓዊ መብት ህግ የጣሰም ነው፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ  ከአለም አቀፉ የሲቪልና ፖለቲካ መብት በተጻራሪ መልኩ ( አንቀጽ 25 የሲቪልና ፖለቲካ መብቶቸ አንቀጽ 25 ፍንትው ብሎ ተቀምጦ ይገኛል) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ሐረሪ እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ነዋሪ የሆኑና የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ ኢትዮጵያዊ ዜጎች የመራጭነት መብታቸው የተጠበቀ ቢሆንም ተመራጭ እጩ ሆኖ ለመቅረብ እጅግ መጠነ ሰፊ ችግሮች ተጋርጠውባቸው ይገኛል፡፡ የዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ህገመንግስቱ የሰጠው መብት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሰረት ክልሎችና የመነግስት ስልጣን የተሰጠው ለየክልሉ ተወላጅ የጎሳ አባላት( ነባር ነዋሪዎች)  እንጂ ከሌላ አካባቢ ኑሮ እያዳፋ ያመጣቸውን ኢትዮጵያዊ ገበሬዎች፣ ነጋዴዎች ወይም የመንግስት ወዘተ ዘወዘተ ሰራተኞችን አይደለም፡፡በግለሰብ ደረጃ ያለውን ትተነው በህብረ ብሔር የተደራጁ ፓርቲ አመራሮች ሆኑ አባላት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርስባቸውን ጫና እንግልት ማጤኑ ተገቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የህብረ ብሔር አመራሮች ላይም ሆነ አባላት ላይ ጫና የሚያሳድሩት የመንግስት አመራሮች ብቻ አይደሉም፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ በቅርቡ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፓርቲያቸው ወልዲያ ላይ በጠራው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በተገኙበት ግዜ ፈሩን የሳተ ተቃውሞ ለኢትዮጵያ የሚበጃት አይመስለኝም፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑንና የፓርቲያቸውን አቋም በሰለጠነ መንገድ መሞገት፣ ወደ አዳራሽ ገብቶ በጥያቄ ማጣደፍ፣በሃሳብ መሞገት፣ አጥጋቢ ምላሽ ከመድረኩ ካልተገኘም ስብሰባቸውን ጥሎ ውልቅ ማለት ያባት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ መረጃ የተሰኘው ከውጭ ሀገር  በሀገር ልጆች የሚተላለፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው ከሆነ ማንነታቸው የማይታወቅ ወጣቶች በወልዲያ ከተማ ኢዜማ ስብሰባ ማካሄድ አይችልም በማለት ስብሰባውን አውከዋል፡፡ በእውነቱ ለመናገር ይህ ገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ጋዜጠኛ ኤርምያስ ዋቅጅራ እንደሞገተው ወጣቶቹ በህዝባዊ ስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ገብተው ፕሮፌሰር ብርሃኑና ጓደኞቻቸውን በሀሳብ መሞገት ይችሉ ነበር፡፡ ይህን የሰለጠነ ፖለቲካ ገቢራዊ ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ስለከዳቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑን በሃሳብ መሞገት፣ መጠየቅ ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡ እውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባት የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደተናገሩት ተጨቆንኩ ግፍ ደረሰብኝ የሚለው፣ በተራው ጨቋኝ ለመሆን የተዘጋጀ ይመስላል ፡፡ ይህ የግፍ አዙሪት አንድ ቦታ መሰበር አለበት፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ተረኛ ጨቋኝን ለመቀበል የሚችል ትከሻ የላትም፡፡ ግፍ የተቀበልን፣መከራ የደረሰብን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ለኢትዮጵያ ሲባል ይቅር ለእግዛብሔር በመባባል ( የደረሰብንን መከራ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፣ ልክ የደቡብ አፍሪካዊው ታጋይ ታላቁ ኔልሰን ማንዴላ እንዳደረጉት ) ለእውነተኛ እርቅና መቻቻል ልባችንን ክፍት ማድረግ አለብን፡፡ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮና ተጽፎ የማያልቅ ግፍ የፈጸማችሁ የጎሳ አምበሎችና ተከታዮች ደግሞ ግፋችሁን ተናዛችሁ ወደ የእርቅ መንገድ ብትመጡ እናንተም ተጠቃሚ መሆናችሁን ማወቁ ብልህነት ነው፡፡

ምንም እኳን የኢትዮጵያ ህገመንግስት በአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ውስጥ የሚገኙትን ሁሉንም የሰብኣዊ መብቶች አንቀጾች ያካተተ ቢሆንም እነኚህ መብቶች እየተመረጡ፣ሰትራቴጂካሊ ፣ በተጠና ሁኔታ ገቢራዊ የሆኑ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል የዜጎች በነጻነት ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ የመንቀሳቀስ መብት፣ በፈለጉበት የሀገሪቱ ክፍሎች የመኖር መብት ዋስትና ማግኘት፣ስራ የማግኘት መብት፣ የፖለቲካ ስልጣን የማግኘትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የማድረግ መብት ወዘተ ወዘተ ቅድሚያ ሚሰጡት ወይም አንበሳው ድርሻ በጎሳ ክልል ውስጥ ለሚኖሩ ነባር ነዋሪዎች ወይም ለዛው ክልል ጎሳ ተወላጆች ነው፡፡ ለአብነት ያህል ያስችላል ሽታዬ ከአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ( ከአማራ ብሔር) ቤተሰብ ተወላጅ የተወለደ ሶታ ወጣት፣ ጋሩማ ኤቢሳ ከተባለ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰብ ( የኦሮሞ ብሔር  ) ከተወለደ ወጣት ለስራ ቢወዳደሩ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሁለተኛው ወጣት ነው፡፡ ይህን እንደ ማሳያ ጠቀስኩት እንጂ በሁሉም የጎሳ ክልሎች አድሏዊነቱ የመጠን ልዩነት ይኑረው እንጂ የግለሰብ መብትን መጣስ የተለመደ ነው፡፡ይህ ብዙም የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ብዙዎች ኢትዮጵያዊ ዜጎች ከተወለዱበት ቀዬ ለቀው ወደ ሌላው የሀገሪቱ ክፍል ለመሄድና ለመስራት ያላቸው ፍላጎት እየቀነሰ ሲሆን፣ ኑሮ እያዳፋ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሄዱ ኢትዮጵያዊ ዜጎች እጣ ፈንታቸው አፈር ገፍተው ከኖሩበት የገጠር መንደር መፈናቀል፣መሰደድ፣በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር መሆን ከጀመረ ሰነበተ፡፡ በአቦምሳ፣አርቦዬ፣ ባቱ(ዝዋይ)፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ምእራብ ወለጋ ፣ጉራፈርዳ፣ደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶና ሸካ ዞን ፣ አርባባ ጉጉ ወዘተ ወዘተ ለዚህ ቋሚ ምስክር ናቸው፡፡ ባለፉት 27 አመታት በተጠና መንገድ በተዘራው የጎሳ ፖለቲካ አስተምህሮ ምክንያት ሁሉም የጎሳ ክልሎች ወደራሳቸው ወደ ውስጣቸው ማተኩራቸው ለኢትዮጵያ አንድነት ትኩረት እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ የፌዴራል መንግስቱም የጎሳ ክልሎች ለኢትዮጵያ አንድነት ቀናኢ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ስራ ኣዳጋች እንዳደረገበት ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የታዘብነው ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል በጎሳ ክልል ነዋሪ የሆኑ በርካታ ወጣቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጦር  አዲስ የሰራዊት አባል ለመቅጠር ፈልጎ የስራ ቅጥር ማስታወቂያ በተለያዩ የጎሳ ክልሎች  ቢያወጣም የተመዘገቡ ወጣቶች ቁጥር አነስተኛ ነበር፡፡ ለምን ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ በነገራችን ላይ ወጣቶቹ  እንዲመዘገቡ ጥሪ የተደረገላቸው ከፌዴራል የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር አታሼዎች ሲሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን የሰጡት ምላሽ አጥጋቢ አልነበረም፡፡ ለምን ?ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ በአጭሩ በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባልነት ስር እንዲመዘገቡ ጥሪ ተደርጎላቸው የሰጡት ምላሽ እንደተጠበቀው አልነበረም የሚለው የእኔ የግል አስተያየት ብቻ ሳይሆን የፌዴራል መንግስቱ ሳይቀር በአንድ ወቅት ቅሬታውን የገለጸበት ጉዳይ ነው፡፡ ለማናቸውም ይህ በአንድ ወቅት የተከሰተ ሲሆን አሁን በአለንበት ጊዜ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ወጣቱን ማስተማር ከተቻለ ይህ አሳዛኝ ሁነት  መፍትሔ ሊገኝለት ይቻለዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የጎሳ ፖለቲካ ፌዴራሊዝም ስርአት የድምር ውጤት የሀገሪቱን አንድነት የበለጠ እያዳከመው ከመገኘቱ ባሻግር፣ ጠንካራ የጎሳ ክልሎችን እየፈጠረ ነው፡፡ እንዲሁም በጎሳ ክልሎች የፉክክር ስሜት ( የመጥፎ ፉክክር ማለቴ ነው፡፡)፣ በጠላትነት የመፈላለግ ሁኔታዎችን ለማብቀል ለም መሬት እየሆነ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በፖለቲካው ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ የነበረው ጎሰኝነት ዛሬ ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ የሆኑ የኢኮኖሚ አውታሮች በጎሳ በተደራጁ ቡድኖች ስር ወድቀዋል፡፡ ከገንዘብ ተቋት ጀምሮ በርካታ የኢኮኖሚ ሀብት በጎሳ በተደራጁ ቡድኖች ስር ወድቀዋል፡፡ ጋሼ እሳቱ ተሰማ መናደድ ሲበዛ ያስቀኛል እንዳለው የእኛ ነገር አንዳንዴ ሳስበው ያስቀኛል፡፡  በአለም ላይ ታቶ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በመታወቂያ ካርዳችን ላይ( ምስጋና ለዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ይግባውና በመታወቂያ ላይ ብሔር መገለጹ እየቀረ ነው)  እና በመኪና ታርጋ ላይ ሳይቀር የብሔር ታርጋ የለጠፍን ነንኮሮና መጥቶ ገላገለን እንጂ ሰላማዊ የእስፖርት አደባባዮች ሳይቀሩ  የጎሰኞች መራኮቻና የብጥብጥ አምባዎች ሆነው ነበር፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ማሳዘን ብቻ አይደለም፣ ህሊናን ያደማል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

በነገራችን ላይ ይህ የኢኮኖሚ ሞኖፖሊ በጎሳ አኳያ ብቻ የሚቀጥል ከሆነ  የኢኮኖሚ ውድድርን ይቀንሳል፡፡ መጨረሻው ደግሞ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ያደቀዋል፡፡ ስለሆነም በተለይም ላለፉት 27 አመታት በወያኔ ኢህአዲግ ክፉ አገዛዝ ዘመን የተከሰተው ትምህርት ሆኖን አውቀን እንታረም የሚለው የግል መልእክቴ ነው፡፡ የጎሳ ክልሎች ከጎሳ ፖለቲካ አዙሪት ወጥተው ኢኮኖሚ ፖሊሲቸውን ኢትዮጵያውያን ባለወረቶችና ሌሎችም አለም አቀፍ የቢዝነስ ሰዎች በነጻነት የሚወዳደሩነትን የምጣኔ ሀብት ገበያ እንዲፈጥሩ እንማጸናለን፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት የፌዴራል መንግስቱ የኢኮኖሚ ነጻነትን ለመፍጠር የሄደበት መንገድ የሚያስመሰግነው እና እንደ መልካም እድል የሚቆጠር ሲሆን፣ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ግን ተስፋ አስቆራጭ ሁነቶች መሬት ላይ ተከስተዋል፡፡ ለአብነት ያህል በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ባለሀብቶችን ንብረት በጎሳ ፖለቲካ የሰከሩ ወጣቶች በጎሳ ማንነታቸው በመለየት ብቻ፣ የባለ ወረቶቹን ንብረቶችን ማውደም የጎሳ ፖለቲካ ያመጣብን ጣጣ ነው፡፡ እነኚህ ኢትዮጵያዊ ባለወረቶች ለብዙ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የከፈቱ ሲሆን አንድ ግርግር በተፈጠረ ጊዜ እየተመረጡ ንብረታቸው መውደሙ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ የሀገር ውስጥ ባለወረቶችን ብቻ የሚያሸሽ ሳይሆን ድንበር ዘለል ኩባንያዎችን ሳይቀር የሚጋብዝ አይደለም፡፡

የማጠቃለያ ነጥቦች

ባለፉት ሃምሳ (50) አመታት ውስጥ እጅግ ህመም ላይ በሚጥል ሁኔታ የመንግስት ድርጅት ቤተሙከራ የሆነች ሀገር ናት፡፡ በስመ ሶሻሊዝም በብዙ ተቀለደባት፡፡ ባለፉት 30 አመታት ውሰጥ ደግሞ በጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት ፍዳዋን እየቆጠረች ትገኛለች፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለማመዘኑ ለመገንዘብ ሰላሳ አመታት ከበቂ በላይ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ አፋጀሽኝ ስለመሆኑ በሚከተሉት ዜና አውታሮች የቀረቡት ዜናዎች ወይም ትንተናዎች ማስረጃዎች ወይም ማሳያዎች ናቸው፡፡ ጊዜው ያላችሁን የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባችሁ እንድታነቡት እጋብዛቸወኋለሁ፡፡

ESAT News. (April 2013). Ethiopia: New Amhara People Evicted from the South. 38 Zecharias Zelalem. Aljezera. (20 Mar 2021). https://www.aljazeera.com/news/2021/3/20/worsening-violencewestern-ethiopia-forcing-civilians-to-flee accessed on 5/2/2021Page 11 of 15 ethnic-based federalism, under the TPLF/EPRDF,   could serve the majority of its citizens the right to justice, sustainable peace and inclusive development.

በነገራችን ላይ የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ከማእከላዊ የመንግስት ስልጣኑ ተሸቀንጥሮ ከወደቀም በኋላ (ዛሬ የወያኔ አገዛዝ እገዘዋለሁ ከሚለው ሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የነበረውን ስልጣን ለቋል፡፡) ፣ ባለፉት ሶስት አመታት ማለቴ ነው የወያኔ አገዛዝ የተከለብን የጎሳ ፖለቲካ ሰንኮፍ አልተነቀለም፡፡ በተቃራኒው የሀገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ጥሎት ይገኛል፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ በሀገሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አርሰው ከሚኖሩበት መሬት፣ ከንግድና መኖሪያ ቤታቸው በግፍ ተፈናቅለዋል፡፡ የጎሳ ማጽዳት በሚመስል መልኩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በአክራሪ ጎሰኞች የሃይል እርምጃ በገዛ ሀገራቸው ምድር ተነከራታች እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በብዙ አካባቢዎች ኢፍትሃዊነት ተስፋፍቷል፡፡ የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍል የፖለቲካና አስተዳደር ውድቀት ምክንያት የተነሳ አካባቢዎቹ በወታደራዊ አገዛዝ (ኮማንድ ፖስት ) ስር ወድቀዋል፡፡ በመጪው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ላይ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል እጩዎችን  ለመመርጥ የተመዘገቡ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ቁጥር እንደተጠበቀው አለመሆን፣ በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች የሚደረገው የምርጫ ውድድር ለግዜው ሊራዘም ይችላል መባሉ፣ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ሊያስከትል ይችላል በሚል ምክንያት፣ እንዲሁም የጦርነት አስከፊ ውጤትን በገንዘብ፣ የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም በማስላት፣ ወዘተ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም በምእራባውያን ተቀባይነት አለማግኘቱ ወዘተ ሀገሪቱ ከገጠማት ተግዳሮትና ፈተናዎች  የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ዋና ዋናዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ( ለአብነት ያህል ኦፌኮ የመሳሰሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ) ከመጪው የምርጫ ውድድር ራሳቸውን ማግለላቸው፤ የህበረ ብሔር ፖለቲካ ድርጅት እጩዎች በአንዳንድ አካባቢዎች አላማቸውን በነጻነት ለህዘብ እንዳያሳውቁ መከልከላቸውን የሚያሳዩ ዜናዎች በየጊዜው ከመገናኛ ብዙሃን ይሰማሉ፡፡

በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ በመጪው 6ኛው ሀገር አቀፍ የምርጫ ውድድር ለመካፈል በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበው በሀገሪቱ መዲና አዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች በርካታ ከተሞች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጋቸው፣ በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው አላማቸውን በነጻነት ማስተዋወቃቸው፣ የፖለቲካ ክርክር ማድረጋቸው ይበል የሚያሰኝና ተስፋ ሰጪም ይመስለኛል፡፡ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያን ከሱዳን በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ ( በተለይ በጎንደር መተማ መስመር) የግጭት ዞን መሆኑ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ብሔራዊ አደጋን የሚጋብዝ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች መሳሪያ ታጣቂ ሀይሎች በሲቪሎች ላይ የሚፈጽሙት ግፍ፣በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ክልል ስር ያሉ ዞን የበለጠ ስልጣን፣ ጎሳ ላይ የተመሰረተ ተጨማሪ ክልል ለመሆን የሚያቀርቡት ጥያቄዎች ወዘተ ወዘተ የጎሳ ፖለቲካ ያመጣብን ተጨማሪ ጣጣ ናቸው፡፡ ከሌሎች ክልሎች አኳያ አንጻራዊና ሰላምና መረጋጋት የሚታይበት የሶማሊ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ይመስለኛል፡፡ በተለይም አቶ ሙስጠፌ የስልጣን አክሊል ከደፉ ወዲህ ለሁሉም የኢትዮጵያ ክልላዊ መስተዳድሮች አርአያነት ያለው ተግባር ያከናወኑ እና በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መቀመጥ የቻሉ የሶማሊ ክልል ፕሬዜዴንት ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በቅርቡ የአፋርና ሶማሊ ክልሎች በድንበር ይገበኛል ምክንያት ያደረጉት ጦርነት ግጭት በተደረገበት አካባቢ  በሚደረገው የምርጫ ውድድር ላይ ጥላ አጥልቶበታል፡፡ 

በተጨማሪም በርካታ ከተሞች የሀገሪቱን ዋና ከተማ አዲስ አበባን (the Ethiopian capital which is named Finfinee by Oromo Nationalists; ) ጨምሮ እንደ ድሬዳዋ፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ እንደ ሻሸመኔ፣ዝዋይ (ባቱ) እና አዳማን የመሰሉ ከተሞች የሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆች በየጊዜው ስጋት ውስጥ እንደሚዶሉ ይነገራል፡፡ የስጋታቸው ምንጭ ደግሞ አክራሪ የኦሮሞ ብሔር ፖለቲከኞች በየጊዜው የህዝብ ስብጥርን በተመለከተ የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ (demographic change’ project

እነኚህ ሁሉ ከላይ ያነሳኋቸው አንዳንድ ችግሮች በመጪው የምርጫ ውድድር ላይ ተጽእኖአቸው ሰፊ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና 6ኛው የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምርጫ ወድድር የመካሄዱ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚወድቅ አይደለም፡፡ የምርጫ ውድድር ህጋዊና የሰለጠነ መንግስት እንዲኖረን የሚረዳ አንዱና ዋናው መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ሆና የምትገኝ ሀገር ሆና ትታየኛለች፡፡ ከመጪው የምርጫ ውድድር በኋላ በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካን ጥቅምና ጉዳት ( ጥቅም አለው ከተባለ ማለቴ ነው፡፡)ኢትዮጵያውያን በሰከነ መንፈስ መነጋገር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን መሬት ላይ በሚታየው ተጨባጭ የፖለቲካ አካሄድ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚጠቅም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለይም የፖለቲካ ኤሊቶች ከጎሳ ከረጢት ውስጥ በመውጣት ለኢትዮጵያ የሚበጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ (በጣም የተራራቁትን ፖለቲካ አስተሳሰቦች ወደ መሃል የሚያመጣ ሀሳብ) ለማምጠት መነጋገር መጀመር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኤሊቶች ማተኮር ያለባቸው በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ቢሆን መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

  • ካለፉት የፖለቲካ ስህተቶች መማር አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ለውጦች ሲከሰቱ ስልጣን ተገቢ ባልሆኑ፣በህዝብ ባልተመረጡ ሰዎች እጅ እንዳይወድቅ የሚረዱ ሃሳቦችን፣እንዲሁም  ህጋዊ የመንግስት ስልጣን በሌሎች ህጋዊ ባልሆኑ አካላት እንዳይጠለፍ የሚረዱ ሃሳቦችን ማመንጨት የምሁራን ድርሻ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
  • ባለፈው ግዜ ላይ ብቻ ከማተኮር ለወደፊት ለሀገሪቱ የሚበጁ ሃሳቦችን ማፍለቅ፤ከጎሳ ማንነታቸው ባሻግር የኢትዮጵያ ህዝቡ በህግ መሰረት ላይ፣ በእኩልነት መንፈስ  የመብቱን ምሉሄበኩልሄ በሆነ ሁኔታ ቢያንስ መሰረታዊ መብቱ ለማግኘት ይረዳ ዘንድ የፖለቲካ ሰነድ ማዘጋጀት የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ኤሊቶች ሃለፊነት ነው፡፡

አስቸኳይ የፖለቲካ መፍትሔ የሚያሻቸው ነጥቦች፡-

1.በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ አስከፊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በፍጥነት መቆም አለባቸው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ መከላከል በዋነኝነት ሃላፊነቱ ደግሞ የመንግስት ነው፡፡ 

2.የኢትዮጵያ ህገመንግስት ስለሚሻሻልበት መንገድ ከወዲሁ ማሰብ ተገቢና አንገብጋቢ ነው፡፡ በተለይም የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚለው አንቀጽ ከህገ መንግስቱ መሰረዝ አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር በህገመንግስቱ የተቀመጡት የግለሰብና የጋራ መብቶች በእኩል ደረጃ ላይ መታየት እንዳለባቸው፡፡ እንዲከበሩ መደረግ አለበት

3.በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛቶች ( ክልሎች) የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት በህገመንግስቱ ላይ የተቀመጠ ቢሆንም፣ የዜጎች የመመረጥ መብት በመሬት ላይ በአንዳንድ የጎሳ ክልሎች ተጥሶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም እንዲህ አይነት የመብት ጥሰት ለወደፊቱ መታረም አለበት ብዬ አስባለሁ

4.የጎሳ ፖለቲካን ተቋማዊ ማድረጉ አይጠቅመንም 

5.በአንዳንድ የጎሳ ክልሎች ውስጥ ባሉ ደራሲዎች ተደርሰው የቀረቡ የክልሉ መዝሙሮች የሚከለሱበት መንገድ ቢፈለግ መልካም ነው፡፡ ( መዝሙሮቹ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚሰብኩ፣የህዝብን አንድነት ለማቀራረብ የሚረዱ ቢሆን መልካም ነው፡፡)

  1. የክልል ሚሊሻ አባላት መደበኛ የጦር ስልት ትምህርት ከተሰጣቸው በኋላ ወደ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባልነት ስለሚቀየሩበት ሁኔታ በወታደራ ባለሙያዎች የሚጠናበት መንገድ ቢፈለግ ለሀገሪቱ አንድነት በእጅጉ ይጠቅማል ባይ ነኝ፡፡
  2. ምንም እንኳን አንዳንድ አክራሪ የጎሳ ብሔርተኞች መድሃኒቱ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የራስን ነጻ ሪፐብሊክ መመስረት ነው በማለት በአደባባይ ሲናገሩ ቢደመጡም፣ ጥናታዊ ጽሁፎችን ቢያቀርቡም መሬት ላይ ያለው እውነት ለየቅል ነው፡፡ ዴሞክራሲ ምሉሄበኩልሄ በሆነ መንገድ  ባልሰፈነበት ሁኔታ፣የክልሎች ድንበር በቅጡ ባልተሰመረበት ወዘተ ፍቺው እንዲህ ቀላል አይሆንም፡፡ ብዙ መዘዞችን ይዞ ብቅ ይላል፡፡ የእነርሱ ሃሳብና ምኞት የዜሮ ድምር ውጤት ይመስላል፡፡ ለሌላ ዙር ግጭት መዘጋጀቱ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የሚያዋጣው ሰላሟ እና አንደነቷ የተጠበቀ ሀገርን ለመመስረት ቁጭ ብሎ በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ነው፡፡
  3. ኢትዮጵያውያን ከጎሳ ማንነት በፊት ሰብዓዊነትን ማስቀደም ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ የበላይነት በመቀዳጀት በሰላምና በፍቅር መኖርም ከችግራቸው ይገላግላቸዋል፡፡
  4. በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካው ቀንድ የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣በብዝሃነት ውስጥ አንድነት እንዲሰርጽ የፖለቲካ ውይይት፣ ደግሞ ደጋግሞ መደረግ አለበት፡፡ በተለይም የማእከላዊ መንግስቱ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረውን ልዩነት፣ በውይይት መድረክ መፍታት የስልጡን መንግስት ባህሪ እንደሆነ ማወቁ ታላቅነት ነው፡፡ የጡንቻ ፣ የጡንቻ ለማንም አምባገነን መንግስት ሲጠቅም አላየንም፡፡

ማጠቃለያ

ይህን ጽሁፍ በምቋጭበት ግዜ እስራኤል በጋዛ ምድርና ሰማይ ላይ የምታወርደውን የጥይት መአት መቆሟን ከአለም መገናኛ ብዙሃን ሰማሁ፡፡ እስራኤል የአየር ድብደባዋን ቆመችው ወዳ ፈቅዳ አልነበረም፡፡ ከዘላለማዊ ወዳጇ የተባበረችው አሜሪካ በቀር( በነገራችን ላይ የታላቋ ሀገር መሪ ባይደን በሰጡት የቴሌቪዥን መግለጫ ላይ የይሁዳዊት እስራኤልን ሉአላዊነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ከገለጹ በኋላ ጥንቃቄ በተሞላበት ንግግራቸው ከሁለቱም ወገኖች ያሉትን አክራሪዎች እንቅስቃሴ  አሜሪካ እንደማትደግፍ ተናግረዋል፡፡ ) ግራም ነፈሰ ቀኝ እስራኤልን አብዛኛው አለም አይንሽ ላፈር ስላላት ነበር፡ የትቃት ሰበዟን ወደ ሰገባው የከተተችው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ከአፍሪካ ሴኒጋልን እናደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክን ጨምሮ በታላቋ ብሪታኒያ ሎንዶን ከተማ. በተባበረችው አሜሪካ ቺካጎ ከተማ፣ አፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን ወዘተ ወዘተ በበርካታ ሀገሮች የሚኖሩ ትእይነት ህዝብ አድራጊዎች በሰውነት ደረጃ ላይ ቆመው የፍልስጤማውያንን ትግል ደግፈው፣ የእስራኤልን ትምክህት በማውገዝ አደባባይ ላይ ወጥተዋል፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት የሩሲያና ቱርክ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች እስራኤልና ፍልሰጤም በሚወዛገቡበት የጋዛ ሰርጥ ላይ የተባበሩት መንግስት ጦር ስለሚሰፍርበት ሁኔታ መመካከራቸውን ከአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭት ተከታትያለሁ፡፡ጎበዝ ለምን ይሆን የፍልስጤማውያን ትግል ከአንዱ የአለም ጫፍ ወደ ሌላኛው የአለም ጫፍ ድረስ የተሰማው? እስቲ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡ ለማናቸውም የፍልስጤም ዜጎች በጎሳም ሆነ በሌላ በሃይማኖት ሊሆን ይችላል ሳይከፋፈሉ አንድነታቸውን በማጥበቅ፣ በሰውነት ደረጃ ላይ ሆነው የእስራኤልን ክንድ ለመቋቋም ጥረት በማድረጋቸው ነው፡፡ ፍልስጤሞች እራሳቸውን በማክበራቸው አለም ሁሉ አክብሯቸዋል፡፡ ጸሃፊው የፍልስጤሞች አላማ ትክክል ወይም ስህተት ነው የሚል ሃሳብ የለውም፡፡ አለማቸውን የሚያውቁት ራሳቸው ፍልስጤሞች ይሆናሉ፡፡ የፍልስጤም ህዝብ እጅግ በጣም ትንሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ከ110 ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን የፍልስጤሞች የነጻነት ድምጽ በአለም ላይ ጎልቶ ይሰማል፡፡ ውጤትም እያገኙበት ነው፡፡ ኢትዮጰያውያን ከፍልሰጤማውያን አንድነት እንማር፣ በሰውነት ደረጃ ላይ ቆመን፣ሀገራችንን ዴሞክራቲክ ሀገር እንድትሆን አብረን ተባብረን እንታገል፡፡ እግዛብሔር ይርዳን ሰላም፡፡

ግንቦት 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

የጽሁፍ ምንጭ፡- ጽሁፉን ለማዘጋጀት የሚከተሉትን ሰነዶች እንደ ማጣቀሻ ተጠቅሜአለሁ

Addis Fortune News. (Jan 4,2020). English Weekly Newspaper, Vol 19. No.1027. Addis Ababa, Ethiopia Alemante G. Selassie. (2003). Ethnic Federalism: Its Promise and Pitfalls for Africa. The Yale Journal of International Law, Vol 28. BGNRS (1995). The Constitution of the Benshangul Gumuz Constitution http://www.ethcriminalawnetwork.com FDRE. 1995. The Constitution of the Federal Democratic Republic of Ethiopia, Addis Ababa, Ethiopia. https://borkena.com/2021/04/17/amhara-genocide-ataye-oromo-radical-forceslaunch-attack/ Ethiopian Human Rights Commission (31 December 2020). And also Ethiopian Hman Rights  council Report on the investigation of human rights violations in relation to the assassination of Hachalu Hundessa, Addis Ababa, Ethiopia. Ethiopian Politics – Election 2020 www.globalsecurity.org.retrieved on 2021-05-02

Filed in: Amharic