“ከገዢዬ-ጎን-እቆማለሁ እና ፖለቲካ-አይመስጠኝም ” — ፍርሃት-ወለድ የውርደት ባህርያት …!!!
አሰፋ ሀይሉ
Political Apathy and Opportunism: the Highest Forms of Public Cowardice!
ታዋቂው የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ሪሰርቸር ፍራንሲስ ፉኩያማ በሚታወቅበት አንድ ታዋቂ ፖለቲካዊ ምርምሩ (በመጽሐፍም መልክ End of History and the Last Man በሚል ሥራው ውስጥ አካትቶ ያሳተመው) የምሥራቅ-ምዕራብ ጀርመንን የከፈለውን ግንብ መፈራራስና የሶቭየት ኅብረት ኮሚኒስቶች አገዛዝ መፍረክረክን ተከትሎ በአብዛኛው ኮሙኒዝምን ያራምዱ በነበሩት የምሥራቅ ሀገራት ከተሞች ውስጥ የተስተዋለውን ህዝባዊ ባህርይ በሚገርሙ ሁለት ቃላት አስቀምጦታል፡- «ከገዢዬ-ጎን-እቆማለሁ» (Political opportunism) እና «ፖለቲካ-አይመስጠኝም» (Political apathy)!
በሶቭየት የሚመራው የዓለም የሶሻሊስት ካምፕ ሲፈርስ – ምሥራቅ አውሮፓዎችም ሶሻሊስታዊ ሥርዓታቸው አብሮ እንደሚፈራርስ ቁርጡን አውቀውታል፡፡ ሕዝቡም ከ40 ዓመት በላይ አንድ ዓይነት የፖለቲካ ዶክትሪንና አንድ ዓይነት ሶሻሊስታዊ መፈክሮችን እያሰማ እንዲኖር የተገደደበት እንጨት እንጨት የሚልና በጠመንጃ አፈሙዝ የሚመራ የኮሚኒስት አምባገነን አገዛዝ መርሮታል፡፡ የሥርዓት ለውጥ ተስፋ እዚህም እዚያም ማቆጥቆጥ ጀምሯል፡፡ እንደ ሮማኒያና ቼኮዝሎቫኪያ የመሳሰሉት አገሮች ለውጭ ጋዜጠኞች በራቸውን መክፈትም ጀምረዋል፡፡
ሕዝቡስ ግን? ሕዝቡ ምን ዓይነት ባህርዮችን ተላብሶ ተገኘ? – ሕዝቡ ደግሞ ከመጠን በላይ ‹‹ቡካቲያም›› (በጭባጫ ፈሪ) ሆኖ የተገኘበት ወቅት ሆነ፡፡ ፉኩያማን የገረመው ስለ ሥርዓቱ የሚጠየቁት የምሥራቅ አውሮፓ ነዋሪዎች ሁሉ ስለ ሀገራቸው የፖለቲካ ሥርዓት ሲጠየቁ የሚመልሱት አንድ ዓይነት መልስ ሆኖ መገኘቱ ነበር፡፡ የሃንጋሪን መንግሥት እንዴት ታየዋለህ? ዲሞክራሲያዊ ነው? የመሣተፍ መብት አላችሁ? ያልተስማማችሁን ነገር በአደባባይ መቃወም ትችላላችሁ?
ብዙዎቹ ሰዎች እነዚህን ጥያቄዎች ሲጠየቁ – በመጀመሪያ አካባቢያቸውን ተገለማምጠው ይመለከታሉ – ማንም እንደሌለ ለመረዳት፡፡ ከዚያ ‹‹እኛ እንዲህ ዓይነት ነገር አልቸገረንም፣ አሁን እኛ የምንፈልገው የደከመ ኑሯችንን የሚያነሳልንን ነው››፡፡ ታዲያ እኮ ይህ ሥርዓት ነው ለዚህ ዓይነቱ ኑሮ የዳረጋችሁ… እና ትደግፉታላችሁ ሥርዓቱን? – ምንም ቃል የለም፡፡
‹‹ሥራዬን ልሥራበት››፡፡ ‹‹ልኑርበት››፡፡ ‹‹ልጄን ላሳድግበት››፡፡ ‹‹አየህ፣ እኔ ለአንተ እውነተኛ ሀሳቤን ብገልጽልህ፣ ነገ ቢዝነሴ ሲዘጋ መጥተህ አታድነኝም፣ ተግባባን? ሌላ ሰው ብትጠይቅ ይሻላል››፡፡ ‹‹በደንብ ነዋ የምደግፈው መንግሥቴን››፡፡ ‹‹አዎ! መንግሥት ይሄኛው መንገድ ይሻለናል ካለም፣ የለም ያኛው መንገድ ይሻለናል ካለም፣ ሁሌም በሀገር ጉዳይ የራሳችን ሀሳብ የለንም፣ ከመንግሥት ጎን ነው የምንቆመው››፡፡
ፉኩያማን በጣም የገረመው አንድ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ፓፓያ የመሳሰሉትን ወደሚሸጥ የአትክልት ግሮሰሪ ሄዶ የገጠመው ነገር ነው፡፡ ሰውየው አንድ ትልቅ የሀገሩን መንግሥት ሶሻሊታዊ አርማ የያዘ ባንዲራ በአትክልት ግሮሰሪው አናት ላይ ሰቅሏል፡፡ ያንን ባንዲራ ብዙዎችም ቤታቸው ከአስፋልት ዳር የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች በየመስኮታቸው ላይ ወደ ውጭ አውጥተው ሰቅለውታል፡፡ እና ይጠይቀዋል ባለግሮሰሪውን፡- ‹‹ቆይ ይሄ ባንዲራ ለአንተ ምንድነው? ባንዲራው ላይ ያሉት ምልክቶች ምንድነው የሚወክሉት? አትክልቶችህን ለመሸጥ (ለገበያህ) የሚያግዝህ ነገር አለ? ወደኸው ነው የሰቀልከው? ወይስ ምን አስበህ ነው?››
ይሄን ሰውዬ ብቻ አገኘ፡፡ ሀቁን ያመነ አንድ አትክልት ቸርቻሪ፡፡ አንገቱን በሀፍረት እያቀረቀረ የተናገረው ለመጽሐፉ ዋና ሀሳብ ዓይነተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ ይመስለኛል፡፡ የሰውየውን ሀሳብ አፍታትቼ ሳቀርበው እንዲህ ነበር ያለው፡-
‹‹ይሄ ባንዲራ ለብርቱካንና ሙዝ ንግዴ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፣ ምንም የሚያገናኘውም ነገር የለም፣ ግን የኑሮ ዋስትናዬ ነው፣ ‹‹መብረቅ መከላከያዬ›› ነው፣ ይሄንን ባንዲራ በመስቀሌ፣ ለኢምፔሪያሊስቶች ጆሮ-ጠቢ ነህ ተብዬ ከመጠርጠር እድናለሁ፣ የሥርዓቱ ጠላት ነህ ተብዬ ከመጠርጠር እድናለሁ፣ እና ታክስ ሰብሳቢዎችም፣ የመንግሥት ተቆጣጣሪዎችም እኔጋ ሲመጡ ጣጣቸውን ቀለል ያደርጉልኛል፣ ከምንም በላይ እኔም ልጆቼም ያለምንም ጥርጣሬና ሥጋት በሠላም ወጥተን በሠላም መግባት እንችላለን፣ ስለዚህ ይሄን ባንዲራ እንደ ሥራዬ አካል ቆጥሬው ጧት ስገባ እሰቅለዋለሁ፣ ማታ ስዘጋ አወርደዋለሁ፣ ራሴን እንደ ወታደር አድርጌዋለሁ ማለት ነው..!
‹‹በባንዲራው ላይ ያለውን አርማ? አሱን አስተውዬ ተመልክቼው ራሱ አላውቅም፣ ትርጉሙንም አላውቀውም፣ ለማወቅም አልፈልግም…! ሥርዓቱን ትደግፈዋለህ ወይ? ላልከኝ – እንዳልኩህ ካልደገፍኩት በሠላም መኖር ስለማልችል ነው! እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ… ሥርዓቱን እጅግ ከሚጠሉት ሰዎች መሐል እንደ እኔ በምሬት የሚጠላው ሰው እዚህች ከተማ ውስጥ ፈልገህ የምታገኝ አይመስለኝም፣ እኔን ብቻ አይደለም፣ እዚህ የምታያቸውን ነጋዴዎች ሁሉ ሥርዓቱ አቅለሽልሿቸዋል፣ ግን መንግሥት ራሱ ሥርዓቴን ልቀይር ነው ብሎ ካልነገረን በስተቀር፣ ይህንን ሀሳቤን ወጥቼ መናገር አልችልም፣ ያን ሀሳቤን ዛሬ ብናገር፣ ነገ ሱቄ ተዘግቶ ልጆቼ በረንዳ ላይ ይወድቃሉ!
‹‹አየህ? ለዚህ ነው፣ እዚህ ሀገር በሠላም መኖር ከፈለግክ፣ የፓርቲውን ባንዲራ ቢዝነስህ ላይ በትልቁ ትሠቅላለህ፣ ለሥርዓቱ ታማኝነትህን እየገለጽክ ነው፣ እና በቻልከው መጠን ከፖለቲካ-ነክ ነገሮች ትሸሻለህ፣ አስተያየትህን ለሚጠይቅህ ለማንም ሰው ትንፍሽ አትልም፣ እና የራስህን ኑሮ አንገትህን ደፍተህ ትኖራለህ! አሁን ካንተ ጋር ያወራሁትን ወሬ፣ ከጎኔ ከተጎራበተው ሰውዬ ጋር አውርተን አናውቅም፣ ለምን? አላምነውማ! አንድ ቀን የተናገርኩትን ለሥርዓቱ ሰዎች ነግሮ ህይወቴን ሊያሳጥረው ይችላል፣ ማንም ማንንም አያምንም!
‹‹ሁሉም ከፖለቲካ ርቆ፣ አድርግ፣ ተናገር፣ ሁን የተባለውን እየሆነ፣ እያለ፣ እያስመሰለ – አንዳንዱም ሥርዓቱ ምን እንደሚፈልግ አውቆ አድርግ ያልተባለውን ሁሉ የራሱን ፈጠራ ተጠቅሞ ገዢውን ፓርቲ እያስደሰተ – የግሉን ኑሮ መኖር ነው! ይህንን ነው ማድረግ የምትችለው እዚህ በሠላም ሀገር መኖር ከፈለግክ! ኑሮ ላልከው.. አዎ ኑሮው በጣም ከብዶናል፣ ገበያ የለም፣ ገቢ የለም፣ ልጆችህን የምታበላው ሁሉ በስንት ድካም የምታገኘው ነው፣ ምንም ነገር ያለሰልፍ አይገኝም፣ ግን ችለነው ከመኖር በስተቀር ስለዚያ መተንፈስም ማማረርም አንችልም! አደራ ይህን የምነግርህን ነገር በምሥጢር ያዘው.. የልጆች አስተዳዳሪ ነኝ ብዬሀለሁ መቼም አይደል?››
ይሄ በአፈሙዝ ጉልበት፣ እና ጭካኔ በወለደው ፍርሃት የታፈነ የፖለቲካ-ምንቸገረኝነት እና የፖለቲካ-አጎብዳጅነት ለዓመታት ታፍኖ፣ ታፍኖ ኖሮ… ድንገት ሲፈነዳ ነበር – ምሥራቅ አውሮፓን ህዝባዊ የተቃውሞና የአመፅ ማዕበል የናጣት፡፡ የሶቭየቶችን መፍረክረክ ተከትሎ የየሀገሩ የኮሚኒስት አገዛዞች ብትንትናቸው ወጣ፣ ኢኮኖሚያቸው ኔጌቲቭ ገባ፣ ባለሥልጣኖቻቸው የሕዝባዊ ቁጣ ማብረጃዎች ሆኑ!
ለዓመታት እጅግ ሲፈሩ የኖሩ የመንግሠት ኮሚሳሪያት ጽ/ቤቶች በሕዝቡ ተወረሩ፣ የኮሚኒስት ባንዲራዎች ተቃጠሉ፣ የተከለከሉ የምዕራቡ ዓለም ሙዚቃዎች በወጣቶች እብደት ታጅበው በአደባባይ ተሞዘቁ፣ እና ለጥቂት ጊዜያት ያን የቀድሞውን ሁሉን ሰጥ-ለጥ ያለበት የታፈነ የፖለቲካ አየር – በተቃራኒው ፍጹም ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሥርዓት-አልበኝነት ነገሠበት፣ ብዙዎቹ መንግሥታት የህዝቡን የአመጽ ማዕበል ማብረድም፣ የህዝቡን የኢኮኖሚ ዋስትና ማስጠበቅም ተስኗቸው ፈራረሱ፡፡ እና አዲስ የአሸናፊዎቹ የምዕራባውያኑ ሥርዓት ሆኖ በተገኘው – በሊበራል-ዲሞክራሲ ሥርዓት ተተኩ (ወይም የተተኩ መሰሉ)፡፡
ይህ ከሆነ ከአራትና አምስት ዓመታት በኋላ ግን ህዝቡን የተጫነው የኢኮኖሚ አዘቅት እጅግ እየከበደ በመምጣቱ፣ ያንን አስታክከው፣ የቀድሞዎቹ ኮሚኒስቶች፣ እኛ ከአሁኖቹ ይልቅ ለህዝቡ እንቀርባለን በሚል እንደ አዲስ አቆጥቁጠው፣ ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍና ተቃውሞዎችን አስነስተው፣ በአንዳንድ የአውሮፓ ሀገሮች ጭራሽ ድጋሚ በህዝቡ ድጋፍ እስከመመረጥም በቁ፡፡ ድሮ በአፈሙዝ በግድ፣ አሁን ደሞ በምርጫ ካርድ በውድ – ለመመረጥ ቻሉ ኮሚኒስቶቹ፡፡
ይህ ክስተት የምሥራቅ አውሮፓ ጀማሪ ዲሞክራሲዎች የተራቆተ ኢኮኖሚያቸውን የሚያደላድሉበት ከፍ ያለ የኢኮኖሚ እገዛ ከምዕራቡ ዓለም ስላልተደረገላቸው መሆኑ አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ ቆይቶ በአውሮፓ ህብረትና በአሜሪካኖቹ ዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት አማካይነት ከገቡበት ማጥ እያገገሙ ብዙዎቹ ወደ ነጻ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትነት ለመሸጋገር ችለዋል፡፡ ሌሎቹ ግን እንደ ቼኮዝሎቫኪያ እርስ በእርስ ተጨራርሰው፣ ሀገራቸውን በታትነዋል፡፡
በእኛም ሀገር በወቅቱ አለኝታችን የነበረችው ሶቭየት ህብረትና ሶሻሊስታዊ ሥርዓቷ ሲፍረከረክ የገጠመን ዕጣ-ፈንታ እንደ ምስራቅ አውሮፓዎች ያለ ነው፡፡ የእኛ ለውጥ የጀመረው ከመንግሥቱ ከራሱ ነው፡፡ ግዙፉን የሌኒንን ሀውልት አፈራረስን፡፡ ቅይጥ-ኢኮኖሚ የሚባል ሶሻሊስታዊ የዕዝ ኢኮኖሚን ከነጻ-ገበያ ጋር ያዋሃደ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማራመድ መጀመራችንን ለፈፍን፡፡ ከሀገር ገንጣዮችና አስገንጣዮች ጋር በምዕራባውያኑ አደራዳሪነት በለንደንና አሜሪካ በጠረጴዛ ዙሪያ ለድርድር ተቀመጥን፡፡
በእነ ሶቭየት ህብረት መውደቅ ድንጋጤ፣ ሁሉነገራችን መፍረክረክ ጀመረ፡፡ አማጺያን የልብ ልብ አገኙ፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያምም ፈረጠጡ፡፡ እና ልክ እንደ ምሥራቅ አውሮፓ ያልታደሉ ሀገሮች፣ የእኛም ሀገር ሁለት ቦታ ተቆረሰች፡፡ የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት ለሀገራቸው ነጻነትን በተጠሙ ሊበራል ሀይሎች እጅ ሲወድቁ፣ እኛ ደግሞ ሀገራችንን አምርረው በሚጠሉ፣ ያልሰለጠኑ ጦረኞች እጅ ወደቅን፡፡
የምሥራቅ አውሮፓ የግማሽ ክፍለዘመን ኮሚኒስታዊ አፈና ያመጣባቸው ሁለት ዋና ዋና የህዝባዊ ፍርሃት መገለጫ ባህርያት ቀስ በቀስ ከላያቸው ተገፎ፣ ነጻነታቸውን ተቀዳጁ፡፡ በእኛ ሀገር ግን ኮሚኒስቱን ወታደራዊ ሥርዓት ጥለው በምትኩ የነገሱት ኮሚኒስታዊ የጎሳ ሀይሎች፣ ቀድሞ የነበረውን የአፈና አገዛዝ አጠናክረው፣ ሀገሪቱን ውስጥ ለውስጥ ከፋፍለው የመበተን ሥራቸውን አጠናክረው ሲቀጥሉ፣ እነዚያ ከምሥራቅ አውሮፓ ምድር በነጻነት ማግሥት የጠፉ ህዝባዊ ፍርሃቶች እኛ ጋር ከሶስት አሰርት ዓመታት በኋላም እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
«ከገዢዬ-ጎን-እቆማለሁ» (Political opportunism) እና «ፖለቲካ-አይመስጠኝም» (Political apathy) – ሁለቱ ፉኩያማ ከምሥራቅ አውሮፓ ምድር በኮሚኒስቱ ሥርዓት ውድቀት ዋዜማ ላይ የተረዳቸው ዋነኛ የአፈና መገለጫ ባህርያት – እኛ ሀገር እስካሁንም አሉ፡፡ ሀገር በፖለቲካው አፋኝ ሥርዓት እና ሥርዓቱ በወለደው የጥላቻና ፉክክር ጦስ ሀገር እየነደደች ባለችበት በዚህ ሰዓት፣ አንዳንዱ አንዱም ነገር እኔን አይመለከተኝም ብሎ የቼልሲና የሊቨርፑልን የእንግሊዝ የፕሪምየር ሊግ የእግር ኳስ ጨዋታ እያየ የሚመሽለትና የሚነጋለት ነው፡፡
አንዳንዱ ስለ ሀገሩና ስለ ህዝቡ ያለበትን የዜግነት ድርሻና ሃላፊነት ነገር ዓለሙን ትቶት – ገንዘብ ሲቆጥርና ትርፍ ሲመትር የሚውል ነው፡፡ አንዳንዱ ዓለምንና ሞላዋን ትቶ ለራሱ የሐይማኖተኝነት ሚና አላብሶ – ከምድሪቱና ለህዝቧ ከሚፈይደው ፖለቲካ ራሱን በሺኅ ኪሎሜትሮች አርቆ አምላኩን እያወደሰ የጸሎትና የምስጋና ህይወትን እየመራ ነው፡፡ አንዳንዱ ፖለቲካንና እሳትን በሩቁ ብሎ – ራሱን የፖለቲካ አላዋቂ ማድረግን የዘመናዊ ሰውነት መገለጫ አድርጎት ‹‹ፖለቲካ አታውራብኝ! መለስ ዜናዊ ማን ነበር?›› ባይ ሆኗል፡፡
ሌላው ሶስት አራተኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ደሞ ከእነዚህ ሁሉ «ፖለቲካ-አይመስጠኝም» (Political apathy) ጎራዎች ፈንጠር ብሎ፣ «ከገዢዬ-ጎን-እቆማለሁ» (Political opportunism) የሚለውን መርህ አራማጅ ሆኗል፡፡ መንግሥት አሜሪካን ደገፈ – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡ መንግሥት 200 ሰዎችን ገደለ – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡ መንግሥት አሜሪካንን አወገዘ – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡ መንግሥት የሱሉልታ ከተማ ነዋሪዎችን አፈናቀለ – ከመንግሥት ጎን እቆማለሁ፡፡ እሺ መንግሥት 70 ሺኅ ነዋሪዎች ከመተከል ተፈናቅለው ወደ ቻግኒ ሲጓጓዙ እጁን አጣጥፎ በተመስጦ እየተመለከተ ነው – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡
መንግሥት የአባይ ግድብን ሙሌት እያካሄደ እንዳልሆነ አስታወቀ – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡ መንግሥት የአባይ ሙሌትን እንደሚጀምር አስታወቀ – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡ መንግሥት በወለጋ ንጹሃንን እያሰረና እየገደለ ይገኛል – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡ መንግሥት 44ሺህ የአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየሞችን ለኦሮሞ አርሶ አደሮች አደለ – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡ መንግሥት በአዲስ አበባ ሠላማዊ ሠልፍ እንዳይካሄድ ከለከለ – ከመንግሥቴ ጎን እቆማለሁ፡፡
መከላከያ ህወሃትን ሙሉ በሙሉ መደምሰሱን አስታወቀ – ከመንግሥት ጎን እቆማለሁ፡፡ መከላከያ ከህወሃት ጋር የሚደረገው ግብግብ እስከመጨረሻው እንደሚቀጥል አስታወቀ – ከመንግሥት ጎን እቆማለሁ፡፡ አስራ ስምንት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በታጣቂዎች ታግተው የደረሱበት አይታወቅም – ከመንግሥት ጎን እቆማለሁ፡፡ የምርጫ ኮሮጆ ተገልብጦ ገዢው ኢህአዴግ-ብልጽግና ፓርቲ 100 ፐርሰንት ማሸነፉ ተረጋገጠ – ከመንግሥት ጎን እቆማለሁ፡፡
ይህ 3/4ኛው ሁልጊዜና በማንኛውም ሁኔታ ከመንግሥት ጋር የሚቆመው ህዝብ፣ መንግሥት የመለስ ዜናዊን የለቅሶ በዓል ሲያውጅም – ከመንግሥት ጎን ቆሞ ቤተመንግሥት በሰልፍ እየሄደ እዬዬውን ያስነካ ሕዝብ ነው፡፡ አንበሣውን በጣዖስ (በፒኮክ) ያስለወጠውም፣ በዚያው ለመለስ ባለቀሰበት ቤተመንግሥትም እጆቹን ግራና ቀኝ ዘርግቶ «Ţ» የምትለዋን ፊደል ሞልቶ ፎቶ በመነሳት ከተረኛው አገዛዝ ጎን መቆሙን የሚያረጋግጥ ህዝብም ነው፡፡
በመጨረሻም ይኸው 3/4ኛው ሕዝብ «አብይ አህመድ ሥልጣን ልቀቅ» የሚል መፈክር ይዘህ በፌስቡክ ላይ ስትወጣ – «አንተ ግን ምን ሆነህ ነው? ደህና ሰው አልነበርክ? እንዲህ ዓይነት ጥላቻማ ይደብራል! ገና እርር ትላታለህ – እስከ ዘለዓለሙም ከአብይ ጎን እንቆማለን!!» – የገጠመን ሕዝባዊ ፈተና ይህ ነው፡፡ «ከገዢዬ-ጎን-እቆማለሁ» (Political opportunism)፤ እና «ፖለቲካ-አይመስጠኝም» (Political apathy)፡፡ እስከመጨረሻው!
እግዚአብሔር ይፍታን፡፡