>

ብሔራዊ ማንነት እና አንድነት...!!! (ቴዎድሮስ ኀይሌ)

ብሔራዊ ማንነት እና አንድነት…!!!

ቴዎድሮስ ኀይሌ

ብሔራዊ ማንነት አንድ ብሔር ውስጣዊ አንድነቱንና ከሌሎች አቻዎቹ ልዩነቱን የሚረዳበት ታሪካዊና ማኅበረ ሥነ ልቡናዊ ግንዛቤ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ማንነት አመሠራረትም ሆነ ግንባታ ረገድ “ራስ-ገለጽነት” (self-definition) ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ “ራስ-ገለጽነት” ማለት አንድ ሕዝብ የጋራ መጠሪያውን ከመሰየም ጀምሮ እያደር በውስጡ የሚጎለብትና የቡድኑን ማኅበራዊና ኅሊናዊ ድንበሮች የሚያሰምር፤ አባላቱ ስለ ራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ የሚያዳብር አዳጊ የማንነት ስሜት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት በታሪክ ሂደት በውስብስብ ድሮች የተገመደና ለብሔሩ አባላትና ለተቀረውም ዓለም ጭምር “ማነው ኢትዮጵያዊ?” የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያ የምትባል አገር፣ ሕዝብና መንግሥት ብሔራዊ ማንነት ነው፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ብሔርነት የስሜትም የፖለቲካም ማኅበረሰብነት ድምር ነው፡፡ በአንድ ወገን መተሳሰሪያው የጋራ ርዕዮት፣ ታሪክና ባህል የሆነና ያለፈውን እድልና ፈተና ተመርኩዞ የወደፊቱን እጣ ፈንታ ተስፋ የሚያደርግ የጋራ ስብዕና መንፈስ ነው፡፡ በሌላ ወገን ኢትዮጵያዊነት በግዛተ መንግሥቱ የሚገኙ ዜጎች ሁሉ በፖለቲካዊ ማኅበሩ አባልነት በቀጥታ በትውልድ የሚቀዳጁት ሕጋዊ ሰውነት ወይም ዜግነታዊ ማንነት ነው፡፡
ከዘመነ አክሱም እስከ 1966ቱ አብዮት በበላይነት የዘለቀው የብሔረ ኢትዮጵያ ማንነት በሥጋዊና መንፈሳዊ ወይም ትውልዳዊና ርዕዮታዊ (ሃይማኖታዊ) ዝምድና ላይ የተዋቀረ ግንዛቤ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነገዳዊ፣ አውራጃዊ፣ ባህላዊና መደባዊ  ዝንጉርጉርነት በደም፣ በታሪክና በእምነት የሚቃየጡበት አሐዳዊ ማንነት ነው፡፡  የብሔረ ኢትዮጵያ ማቋቋሚያ ሰነድ የሚባለው ክብረ ነገሥት ይፋ እስከወጣበት እስከ መካከለኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጥብቅ መሠረት የያዘው  የዚህ ማንነት ጥምር ባህላዊ መልኮች የሃይማኖት ጥራትና የሥልጣኔ የበላይነት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን የእምነት ጥንታዊነት፣ ንጹሕነትና ትክክለኛነት፤ የሥልጣኔዋን ገናናነት፤ የመንግሥቷን ቀጣይነትና የነገሥታቷን ግርማዊነት፤ የሕዝቧን ሃይማኖተኝነት፣ ደግነት፣ ጀግንነትና ነጻነት ወዳድነት ያካትታል፡፡
ኢትዮጵያውያን በረዥም ታሪካዊ መስተጋብር ያዳበሩት የማንነት ሥነ ልቡና ወደኋላ ከታሪካዊ-ትውፊታዊ መነሻቸው፣ ወደፊት ከአገራቸውና መንግሥታቸው እጣ ፈንታ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ከመንግሥታት ሁሉ መርጦ በፀጋውና ረድኤቱ የማይለያትና ልዩ መሲሃዊ እጣ ፈንታ የተላበሰች ቅድስት አገር፤  ብሔራዊ  ርዕይዋም የፈጣሪዋን ተልዕኮ መፈፀም መሆኑን አጥብቆ ያምናል፡፡ በሦስት ሺሕ ዘመናት በሚሰላ ርዕዮታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሱ ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጠንካራና ዘላቂ የማንነት ስሜት አዳብሯል፡፡
ይሁን እንጂ በተለይ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ በመንግሥቱ የኀይል መዋዥቅ፣ በእስላማዊ ኀይሎች፣ በኦሮሞና ሌሎችም “የዳር አገር ሕዝቦች” ፍልሰትና ወረራ ምክንያት በመንግሥትና ብሔር ግንባታው ሂደቶች ላይ ተደጋጋሚ መደናቀፍና አለመጣጣም ተከስቷል፡፡ እስልምና ቀስ በቀስ ከጠረፋማው ወደ ማዕከላዊው ግዛት በመስፋፋት አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀለም ሊሆን ችሏል፡፡ የዚህ ሂደት ከፍተኛ ነጥብ የሆነው የግራኝ አሕመድ ጦርነት (1517-1536 ዓ.ም.) እስልምናን በክርስቲያናዊው ደጋማ እምብርት የተከለና የላቀ ተጽዕኖ ላሳደረው የኦሮሞ ሕዝብ መስፋፋት በር የከፈተ ነበር፡፡
ከ16ኛው ምዕት ለጥቆ የነበሩት ሦስት ምዕታት የኢትዮጵያን ባህላዊና ፖለቲካዊ መልክዐ ምድር ለዘለቄታው የቀየሩ፣ ነባሩን ብሔራዊ ርዕዮትና መንግሥት ያዳከሙና ከሞላ ጎደል የዘመናዊውን ኢትዮጵያ ገፅታ የቀረፁ ታላላቅ ክስተቶች አስተናግደዋል፡፡ ማዕከሉን ጎንደር ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ከ1625 እስከ 1761 ዓ.ም.  እነዚህን የእስላም – ኦሮሞ ጥምር ኀይሎች ግስጋሴ መክቶ ሥልጣኑን ለማጥበቅ፣ ቤተክህነትንና ጦር ሠራዊቱን ለማጎልበት አልቻለም፡፡ እንዲያውም ሰፊውን የአገሪቱን ደቡባዊ ግዛት ተቀምቶ ለህልውናው የሞት ሽረት የሚታገል ነበር፡፡
ዘመነ መሣፍንት (1761-1847 ዓ.ም.) ይህ ሂደት በብሔራዊ ማዕከሉ ፍፁም መንኮታኮት የተደመደመበትና እስልምናና ኦሮሞነትን ያጣመሩ የየጁ የጦር አበጋዞች ሥልጣነ መንግሥቱን የተቆጣጠሩበት ዘመን ነበር፡፡ ብሔራዊ መንግሥቱ በአውራጃዊ ኀይሎች የተከፋፈለበት፣ ሰሎሞናዊው ዘውድ ማዕረጉን ተገፍፎ ለታሪካዊ አንድነት ትዕምርትነቱ ሲባል ብቻ የተጠበቀበት ዘመን ነበር፡፡ የየጁ መሳፍንት ባለፉት ሶስት ምዕታት በማዕከላዊውና ዳራዊው ማንነቶች መካከል  የተደረገው ሰፊ መስተጋብርና ውሕደት ውጤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም በብሔራዊው ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉበት አቅም አዳብረዋል፡፡ የብሔረ ኢትዮጵያን ማንነት አስገዳጅ መስፈርት ለማሟላት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትናን ተቀብለዋል፡፡ አማርኛንም ልሣነ መንግሥት አድርገው ቀጥለዋል፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያ የአገር ግንባታ የወረሳቸው ሁለት የብሔራዊ ማንነት እርከኖች ናቸው፡፡ በአንድ ወገን በፖለቲካዊም ባህላዊም (በዋነኝነት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት) ዝምድና የተሳሰሩ፣ የአገሪቱ ጠንካራና ግልፅ የማንነት ስሜት መሠረቶችና የአገር ግንባታው አስኳል ማኅበረሰቦች፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ብሔራዊ ማንነታቸው በመንግሥቱ ፖለቲካዊ ዝምድና የተወሰነ፣ ከማዕከሉ በተለያየ የስሜትና ታማኝነት ርቀት ላይ የሚገኙ ዳራዊ ማኅበረሰቦች ናቸው፡፡ የብሔረ ኢትዮጵያ አሃዳዊ ማንነት በርካታ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦችን ያገለለ ነበር፡፡
ዘመናዊው የአገር ግንባታ የኢትዮጵያዊነትን አገራዊ፣ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ማንነት ግንዛቤ የማሻሻልና የመቀየር ሂደት ነው፡፡ ዓላማውም የአገሪቱን ብዝሃነት በእኩል ማስተናገድና በስሜታዊውና ፖለቲካዊው፣ በአስኳሉና ዳሩ ማንነቶች ድንበር መካከል ያለውን ርቀት ማጥበብ ነበር፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊነትን የማዘመን አዎንታዊ እርምጃ ተቀዳሚ ትኩረቱ የኢትዮጵያን መለኮታዊ ስብዕና ወደ ዓለማዊ ስብዕና መለወጥና አሮጌውን  ባለሁለት እርከን ማንነት  በአንድ ህጋዊ ማንነት ወይም ዜግነት መተካት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ዘመናዊው የማንነት ግንባታ ጉልህ ውሱንነቶችም ነበሩበት፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያ እንደ ብሔረ ኢትዮጵያ ለአዲሱ የአገር ግንባታ የሚሆን ግልፅ፣ ጠንካራና ዘላቂ ርዕዮተ ዓለም አልገነባችም፡፡ በተለይ ከተማሪው ንቅናቄ አንስቶ በደርግና በኢሕአዴግ አገዛዞች ጭምር በጅምላ ተቀድተው ለአገር ግንባታ የዋሉት ፖለቲካዊ ርዕዮቶች ባዕድ፣ ግልብና ዋዣቂ በመሆናቸው የብሔሩን ማንነትና እጣ ፈንታ በግልፅ አያስቀምጡም፡፡
የዘመነ ደርግ የአገር ግንባታ ከብሔር ግንባታ ይልቅ የመንግሥት ግንባታ ያመዘነበት ነበር፡፡ በሙሉ ልብ ያልተያዘው የሶሻሊስት ኢትዮጵያዊነት ግንባታ ሕዝባዊ መሠረት ስላልነበረው ህልውናው ከአገዛዙ ዕድሜ አልዘለለም፡፡ ዘመነ ኢሕአዴግ ደግሞ አገራዊ ብሔር ግንባታው ፍፁም ችላ ተብሎ በንዑስ ብሔራዊ ማንነቶች ግንባታ ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር፡፡ ዘውጋዊ የፌዴራል ሥርዓቱ “ሕገ መንግሥታዊ አርበኝነት” የሚባለውን ሳይቀር የአገራዊ ማንነት ግንባታን ያዳከመ ነበር፡፡ ስለዚህም የጋራ ሕዝባዊ ባህልና እሴቶች እየከሰሙ፣ ከብሔራዊ ማንነት ይልቅ አካባቢያዊና ዘውጋዊ ማንነቶች እየጎሉ መጥተዋል፡፡
በአጠቃላይ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ በአገሪቱ ያሉትን ብዝሃዊ ማንነቶች የሚሻገር የጋራ ልዕለ ዘውጋዊ ስብዕና ሊፈጥር አልቻለም፡፡ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ የብሔረ ኢትዮጵያን ቅርስ በአግባቡ ለመጠቀም አልቻለም ወይም አልፈለገም፡፡ ወይም ደግሞ ለታሪካዊው ማንነት የረባ አዲስ አማራጭ  አላቀረበም፡፡ ዘመናዊው ትውልድ ለባዕዳን ተጽዕኖ የተጋለጠና የማንነት ቀውስ የሚያራዠው መጢቃ በመሆኑ፣ ለመናፍቃዊና ጨለምተኛ አስተሳሰቦች ሰለባ ሆኗል፡፡ የመንግሥቱ ህልውና የተመሠረተው በሥልጣኔ አራማጅነት ስለሆነ፣ ብሔራዊ ርዕዩ የምጣኔ ሀብታዊ  ብልፅግና ነው፡፡ ስለዚህም ለአዲስ ብሔራዊ ማንነት አስተማማኝ መሠረት አልተጣለም፡፡
አንድነት
ብሔራዊ አንድነት ማለት የተለያዩ ማንነትና ፍላጎት ያላቸውን ማኅበረሰቦችና ቡድኖችን በጋራ ታሪክ፣ ባህልና ርዕይ ማስተሳሰር ነው፡፡ በሕዝብና መንግሥት መካከል፣ በመንግሥት ልዩ ልዩ አካላትም መካከል የሚፈጠር የግብርና የዓላማ አንድነት ነው፡፡ ብሔራዊ አንድነት መሠረታዊ ልዩነቶችን ሳይጨፈልቅ ብዝሃነትን በቁልፍ ላዕላይ ትስስሮች የሚያዛምድና የተቀናጀ መስተጋብራዊ ሥርዓት የሚፈጥር አንድነት ማለት ነው፡፡
ታሪካዊው ኢትዮጵያዊነት በርዕዮታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ሥነ ልቡናዊ አንድነት ላይ የቆመ ብሔርተኝነት ነው፡፡ አገርን፣ ሕዝብና መንግሥትን በአንድ አስተምህሮ፣ በአንድ መንፈስ፣ በአንድ ልሣን፣ ለአንድ ዓላማ የሚያቆራኝ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ከንጉሥ እስከ ባላገር ያሉ ማኅበራዊና መደባዊ እርከኖች ሽቅብ በጋራ ርዕዮትና ባህል እየታረቁ የአንድነት መንፈስ የሚጋሩበት ማኅበር ነው፡፡ ብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊነት የማይነጣጠል ተፈጥሯዊ  አንድነት አላቸው፡፡
የብሔረ ኢትዮጵያ አንድነት ከላይ ለፖለቲካዊው መንግሥትና ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በሚኖር ታማኝነት፣ ከታች ደግሞ በማኅበረሰቦች ታሪካዊና ባህላዊ አብሮነት ሐረጎች የታሰረ ነበር፡፡ ዘውዳዊው መንግሥት የኢትዮጵያ አስኳልና ዳር ማኅበረሰቦች አንድነት ዐቢይ ተቋማዊ ሰንሰለት ነበር፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱ በማዕከላዊና (centripetal) ተስፈንጣሪ (centrifugal) ኀይሎች መካከል በሚደረስ ሚዛን ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በረዥም ታሪኩ በግዛቱ ያሉትን ዘውጋዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ብዝሃነቶች በአንድነት የማሰለፍ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አቅም አደርጅቷል፡፡ በመላ አገሪቱ የሰላም፣ የፍትሕና የግብር ሥርዓት ዘርግቶ በጋራ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ማዕቀፎች ያስተሳስራል፡፡ በዜግነት መብቶችና ግዴታዎች ያስተሳስራል፡፡ በጋራ መስዋዕትነትና አርበኝነትም ብሔራዊ አንድነት ያጠናክራል፡፡
ከመንግሥቱ በተጓዳኝ የአገሪቱ ብዝሃዊ ማኅበረሰቦች በበርካታ ድንበር ተሻጋሪ ሀረጎች የተሰናሰሉ ነበሩ፡፡ ከጋራ መልከዓ ምድር ጀምሮ  የጋራ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ እሴቶች፣ ተመክሮዎች፣ አብሮ መኖርና ሰጥቶ መቀበል ያደረጃቸው ዕድሜ ጠገብ ማኅበራዊ ግዴታዎች፣ ደንቦችና ወግ ልማዶች የአንድነቱ ታኅታይ መሠረቶች ናቸው፡፡ እንደ ክርስትናና እስልምና ያሉ ነባር ሃይማኖቶች ዘውጋዊና አካባቢያዊ ድንበሮችን የሚሻገሩና በጋራ ባህላዊና ፖለቲካዊ አውድ ላይ የበቀሉ ናቸው፡፡ ግዕዝ የብሔራዊ አንድነት አማርኛ ደግሞ የመንግሥታዊና ሕዝባዊ አንድነት መሣሪያዎች ሆነው አገልግለዋል፡፡
የአገር ግንባታው የስሜትና የፖለቲካ ገጽታዎች መሳ ለመሳ የሆኑበትና ፍፁም ብሔራዊ አንድነት ያለው አገር የሚገኘው በተምኔታዊው ዓለም ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ስለ አገራቸው፣ መንግሥታቸውና ብሔራዊ ማንነታቸው የሚኖራቸው ስሜትና ቅንዐት  ወይም አገር ወዳድነት፣ አርበኝነትና ሕዝባዊነት መንፈስ በማንኛውም ወቅትና በመላ አገሪቱ ወርድና ቁመት ወጥና ያልተዛነፈ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ በርካታ  ምክንያቶች ቢኖሩም በዋነኝነት የመንግሥቱ ፖለቲካዊ ቁመና በተለዋወጠበት ፍጥነትና ስፋት ልክ፣ በማዕከሉና ዳርቻው ወይም በነባሩና አዲሱ ማንነቶች መካከል በቂ ባህላዊና ትዕምርታዊ ትስስር አለመደርጀቱ ነው፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የዜግነት ሕግ ያቆመው፣ በፖለቲካዊውና ስሜታዊው ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ክፍተት በመድፈን ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ነው፡፡ ዘላቂነት ባይኖራቸውም በሕዝብና መንግሥት መካከል አዲስ ባህላዊና ርዕዮታዊ አንድነት ለመፍጠርም ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ከጥረቶቹ ሁሉ በመንግሥቱ ላይ የተደረጉት ሥር ነቀል መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ለውጦች በከፍተኛ ደረጃ የተማከለና ጠንካራ ተቋም መፍጠር ተሳክቶላቸዋል፡፡
በአጠቃላይ ዘመናዊ ኢትዮጵያዊነት ያበበበትና አገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ተዋሐደ ብሔራዊ መንግሥትነት የቀረበችበት ወቅት መቼ ነው ቢባል የ1950ዎቹ ዐሥርት ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል አስገራሚነቱ በመጭው ዘመናት ለአገር ግንባታው ጥረት ፅኑ ተግዳሮት የሚደቅኑ ተቀናቃኝ ርዕዮቶችና ኀይሎችም ያቆጠቆጡት በዚሁ ዐሥርት ነበር፡፡ ዞሮ ዞሮ የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ በበርካታ ምክንያቶች የተነሳ የታሰበውን ብሔራዊ አንድነት ለማምጣት አልቻለም፡፡
የዘውዳዊው መንግሥት የማዘመን እርምጃዎች በታሪካዊት ኢትዮጵያ አስኳል ማኅበረሰብ መካከል የፈጠረው ስንጥቅ ቀዳሚው ተግዳሮት ነበር፡፡ ኀይለ ሥላሴ አልጋውን ከታሪካዊው ብሔር ቁርኝት ለመነጠል ያወጁት የገደብ ሕግ መራር ተቃውሞ የገጠመው የሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት ተጋሪ ከነበሩ ወግ አጥባቂ አውራጃዊ መሣፍንቶች ነበር፡፡ በሌላ ወገን የዘውዱ ዘገምተኛ ተራማጅነት ያላረካቸውና ለበለጠ መሠረታዊና ትርጉም ያላቸው ለውጦች ግፊት የሚያደርጉ ኀይሎችም ከራሱ ከመንግሥቱ ውስጥ በመነሳት በ1953 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡
ከ1960ዎቹ መባቻ አንስቶ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ዑደት እየተቆጣጠረ የመጣው የአዲሱ ትውልድ ሥር ነቀል አብዮተኝነት በአባቶቹ ላይ ሙሉ ትውልዳዊ ጦርነት በመክፈት፣ ከናካቴው የታሪክና የባህል እትብቱን የበጠሰና የአገር ግንባታውን ሽግግር ያከሸፈ ነበር፡፡ አማጺው ትውልድ በውስጡ የተፈለፈሉትን ርዕዮታዊ ልዩነቶች በማቻቻል የራሱን  አንድነት ለማስፈን፣ በአገራዊ ጉዳዮችም የጋራ መግባባት መፍጠር አልቻለም፡፡ ከናካቴው በጠላትነት እየተቧደነ ከሐሳብ ወደ ትጥቅ ሽኩቻ በመካረር ለውድቀት ተመቻቸ፡፡ ከዚሁ አብዮታዊ  ትውልድ የተገነጠለው ዘውጋዊ  ጎራም  የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንድነት በግልጽ ለመፈተን ታጥቆ ተሰለፈ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ከኀይል በመለስ የጋራ የፖለቲካ አውድ ጠፋ፡፡
በ1966 ዓ.ም. አብዮቱን ከዳር ያደረሰው ወታደራዊ ደርግ በአገራዊ አንድነት ረገድ የማያወላውል አቋም ነበረው፡፡ እንዲያውም የአገዛዙ ርዕዮት እምብርትና የቅቡልነቱ መሠረት ብሔራዊ ሉዓላዊነትና አንድነት ነበር፡፡ እነዚህን ከባዕዳን ወራሪዎችም ሆነ ከዘውጋዊ አማጺያን ተከላክሎ ለማስጠበቅም ለ17 ዓመታት ኀልዮታዊና ወታደራዊ ዘመቻ አድርጓል፡፡ ንዑስ ብሔራዊ የማንነትና የመብት ጥያቄዎችን ከሰላም ይልቅ በጉልበት ለማፈን ሞክሯል፡፡ ይሁን እንጂ የደርግ ሶሻሊስታዊ ኢትዮጵያዊነት እጅግ መሠረተ ጠባብ በመሆኑ ዓለም ዐቀፍ የሶሻሊስቱ ጎራ ከደረሰበት ውድቀት ጋር አብሮ ሊንኮታኮት ችሏል፡፡
የደርግ መውደቅ እንደ አንድነቱ ጎራ ሽንፈት ተቆጥሯል፡፡ ስለዚህም በወታደራዊ ድል ሥልጣን የያዘው የኢሕአዴግ የአገር ግንባታ በአሸናፊው ዘውጋዊ መርህ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ አገራዊ አንድነትን አክስሞ በዘውጋዊ አንድነት ላይ ፌዴራላዊ ሥርዓትም አዋቅሯል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራዊና ሕዝባዊ ሉዓላዊነት የተተካው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት ከአንድነት ይልቅ መነጣጠልን ያበረታታ ይመስላል፡፡  እያደር ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክፍፍሎች የገነኑበት፤ በብሔራዊና ንዑስ ብሔራዊ ማንነቶች መካከል ባላንጣነት የተካረረበት ሥርዓትን ወልዷል፡፡
በደምሳሳው የዘመናዊት ኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሂደት ፖለቲካዊው መንግሥት ባህላዊውን ብሔር አለቅጥ የተጫነበት ወይም ወደዳር የገፋበት ነበር፡፡ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የተነሳ፣ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ከጥንካሬው ይልቅ ልፍስፍስነቱና ተከፋፋይነቱ ሊያመዝን ችሏል፡፡  ከናካቴው ከኢትዮጵያዊነት መንፈሱ እየራቀ ወደ ዘውጋዊና አውራጃዊ ጥጋጥግ በመንሸራተቱ ርዕዮታዊ ውዥንብር፣ ሰፊና መዋቅራዊ የማኅበረሰቦችና ቡድኖች ፍትጊያና ግጭት፣ አልፎም ብሔራዊ የመበታተን ስጋት አስከትሏል፡፡
ዘላቂነት 
ዘላቂነት የአገር ግንባታውን ታሪካዊና ኅሊናዊ ቀጣይነት የሚያሳይ ግንዛቤ ነው፡፡ በተከታታይ ትውልዶች መካከል ስለአንድ ማኅበረሰብ የጋራ ባህል፣ ታሪክና ትውስታ እንዲሁም ስለ መጻኢ እጣ ፈንታው የሚኖረውን ቀጣይነት ይመለከታል፡፡ ከጊዜ አንጻር ዘላቂነት በታሪክ ያልተቋረጠና የተመዘገበ ቀጣይነት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በለውጥ ውስጥ ያለ ቀጣይነት ነው፡፡  አንድ ብሔር የቀጣይነት ስሜቱን ሳያጣ ከፊሉን ወይም ጠቅላላውን ውጫዊ ባሕሪያቱን ሊለውጥና ሊተው ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ አገር ግንባታ መድረሻ ግብ ብሔራዊ ቀጣይነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የታሪካዊት ኢትዮጵያ ዘላቂነት አንዱ መሠረት ግልፅ ብሔራዊ ርዕዮትና ርዕይ ነው፡፡ ሰሎሞናዊው ትውፊት ከይሁዲነት አልፎ ወደ ክርስትና የተሻገረ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሥነ ልቡናዊ ዘላቂነት መሥርቷል፡፡ ብሔረ ኢትዮጵያን በሃይማኖታዊ ኀልዮትና በሥርወ መንግሥታዊ መርህ በማረቅ የመንግሥቱን መረጋጋት፣ ጽናትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ አስችሏል፡፡ እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊነት የማዕዘን ድንጋይና የአገር ግንባታው ዘላቂ መሠረት ሆኖ አገልግሏል፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ አገር ግንባታ ዘላቂነት መሠረት ሕዝባዊ ባህል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከቀደምት አባቶቻቸው ባህሎችና እሴቶች ቅርስ ጋር ያላቸውን የቀጣይነት ስሜት ይመለከታል፡፡ እነዚህ ባህላዊ መሠረቶች እንደ ሃይማኖት ያሉ ሁሉን ዐቀፋዊ (universal) ባሕሪ ያላቸው ፅኑ እሴቶች ይሁኑ እንጂ፣ እያንዳንዱ ትውልድ ለኢትዮጵያዊነት ባህላዊ ንጣፍ የየተመክሮውን ድርሻ ማዋጣቱ አይቀርም፡፡ በዚህ ዓይነት የለውጥና ቀጣይነት መወራረስ ሕዝባዊው ባህል ከታሪክ እየተስማማ የኢትዮጵያን ማንነት በጊዜና በቦታ የሚያሸጋግር ዋነኛው ድልድይ ነው፡፡
የኢትዮጵያዊነት እሳቤ  ለረዥም ዘመናት ተጠብቆ ሊኖር የቻለው  በሰፊው ብሔራዊ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ነው፡፡ ለዚህም አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያዊነት  አዳዲስ ርዕዮታዊና ወታደራዊ ኀይሎችን ለማስተናገድና በየጊዜው የሚፈጠሩ ለውጦችን ለማጣጣም ያለው አንጻራዊ አቻቻይነትና ክፍትነት ነው፡፡ አጠቃላይ የሥርዓቱ ማኅበራዊ ክፍትነትና የዕድገት መሰላሎችን ዘርግቶ  ከአስኳል ማኅበረሰቡ ውጭ ያሉ ዘውጎችንና ባህሎችን ማካተቱ የአገር ግንባታው በራስ የመተማመን ምልክት ነው፡፡ በየዘመኑ ኢትዮጵያ ስትዳከም መልሳ የምታንሰራራው በባህላዊና መንፈሳዊ ጥንካሬዋና አቻቻይነቷ ነው፡፡
በዚህ ረገድ ታሪካዊው የአድዋ ድልም ሆነ የአምስቱ ዓመታት የአርበኝነት ተጋድሎ መንግሥትና ብሔር በአገሪቱ ህልውና ላይ ያላቸውን ታሪካዊ ሚና በግልፅ ያሳዩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ሩሲያና ጃፓን በተሳካ ሁኔታ የአውሮፓን ቅኝ ወረራ የመከላከል ብቃቱንና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጥልቅ ታሪካዊና ማኅበራዊ መሰረት እንዳለው ያረጋገጡ  ናቸው፡፡ በተለይ የአምስቱ ዓመታት የጀግንነት  ተጋድሎ  የኢትዮጵያውያን ጠንካራ የብሔራዊ ማንሰራራት አቅም ምስክር ነው፡፡
የአዲሲቱ ኢትዮጵያ እሳቤ ብሔራዊ መሠረቱን ከእምነት ወደ ፖለቲካዊ ርዕዮት በመቀየሩ፤ ለኢትዮጵያዊነት ሰፊ ትርጉም የሰጠና ብዝሃዊነትን የሚያስተናግድ እርምጃ  መሆኑ አይካድም፡፡ ነገር ግን እያደር አቅጣጫውን የሚያስቱ ድክመቶችንም የፀነሰ ነበር፡፡ በተለይ የግንባታው ርዕዮተ ዓለም ጉራማይሌና ከአገዛዞች ዕድሜ የማይሻገር በመሆኑ የተነሳ የሚያስከትላቸው ለውጦች ቀጣይነት አልነበራቸውም፡፡
ከባህላዊ ግንባታ አኳያ ነባሩን ባህላዊ ቅርስ መልኩን አሻሽሎ ለመጠቀም የተደረገው ጥረት አመርቂ አልነበረም፡፡ ከባህል፣ ትምህርትና ማስታወቂያ ሚኒስትሮች አንስቶ የብሔር ግንባታውን የሚመሩ መንግሥታዊና ሕዝባዊ አካላት ዘመናዊና አካታች ባህል ለመገንባት ያደረጉት ጥረት በርዕዮታዊና መዋቅራዊ ውዥቀት የተጎዳ ነበር፡፡ የባህል ቀጣይነቱ ዐቢይ መዘውር የነበረው ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት አገራዊ መሠረቱን ትቶ ሙሉ በሙሉ በባዕድ አስተምህሮ መተካቱ ትውልዳዊ የባዕድ አምልኮና የባህል ውልቃት ያስከተለ ይመስላል፡፡
የግራ ዘመሙ አብዮተኛ ትውልድ የአገር ግንባታ እሳቤ በነባሩና አዲሱ፣ በጥንታዊውና በዘመናዊው፣ በሩቁና በቅርቡ መካከል ተቃርኗዊነትን አስፍኗል፡፡ ቀጣይነትን ሳይሆን አዲስ ጀማሪነትን ታሪክ ሠሪነትን የሚያራምድ በመሆኑ ረዥም የታሪክ እይታና ኀላፊነት መንፈስ ተዳክሟል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ግፋ ቢል ከዐፄ ቴዎድሮስ  የሚሻገር አልነበረም፡፡ ከነባሩ ኢትዮጵያዊነት ጋር የሚጣጣምበት ብልሃት ባለማግኘቱ፣ እትብቱን ቆርጦ የመጣል ሂደት ውስጥ ገብቷል፡፡
በተለይም የደርግና ኢሕአዴግ አገዛዞች የተከተሏቸው ስልቶች የባህል ፖለቲካ ተጽዕኖ ያረፈባቸው፣ በብሔራዊና በዘውጋዊ ማንነት ላይ አፅንኦት የሚያደርጉ፣ አንዱ ለሌላው ተቃርኗዊና አፍራሽ ነበሩ፡፡ ወታደራዊው አገዛዝ የብሔረ ኢትዮጵያ ቅርስ በጅምላ ሰፊውን ሕዝብ የማይወክል የፊውዳል ቅርስ ነው በማለት አውግዞ ከአዲስ ለመነሳት ሞከረ፡፡ በተራው ኢሕአዴግ ደግሞ ከእኔ በፊት የነበሩት ሥርዓቶች በሞላ አንድ ዓይነትና በጅምላ ብሔረሰቦችን የማይወክሉ ናቸው በማለት ሌላ አዲስ ግንባታ ጀመረ፡፡  በአጭሩ ዘመናዊው የአገር ግንባታ መሠረተ ሰፊ፣ አስተማማኝና ዘላቂ ብሔራዊ ባህልና ማንነት ለመገንባት አልታደለም፡፡
ምን ይደረግ?
የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ከሥርወ መንግሥታዊ ወደ አብዮታዊ ከዚያም ወደ ዘውጋዊነት ባደረገው ታሪካዊ ጉዞ ምክንያት የጥንታዊነትና ዘመናዊነት፣ ዜግነታዊነትና ዘውጋዊነት፣ ባህላዊነትና ፖለቲካዊነት፣ ወዘተ… መንትያነቶች በአገሪቱ ብሔራዊ ማንነት ግንዛቤ፣ የብሔርተኝነት ፖለቲካና ጥናት ውስጥ በሰፊው ይንጸባረቃሉ፡፡
ስለዚህም ተቀዳሚው እርምጃ እነዚህን ጉራማይሌዎች የሚያስተናግድ ለአገር ግንባታው መሠረት የሚሆን ግልፅና አካታች ርዕዮተ ዓለም መንደፍ ይሆናል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሕዝብን ከመንግሥት፣ እንዲሁም የመንግሥትን አካላት በአዎንታዊነት የሚያቀራርብ መሆን አለበት፡፡ የአገሪቱን የታሪክና ባህል ቀጣይነት የሚያረጋግጥና መጻኢ እጣፈንታዋንም በግልጽ የሚያስቀምጥ መሆን አለበት፡፡
ከዚህም አልፎ አገራዊነት/ብሔራዊነትና ዘውጌነት የሚደጋገፉበትን መንገዶች መተለም ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ለብሔራዊው መንግሥት የሚኖር ውዴታና ታማኝነት መገለጫ እንደየማኅበረሰባዊና ወቅታዊ ጭብጦች ቢወሰንም፣ አገራዊነት ከዘውጌነት ንቃተ ኅሊና ጋር አብሮ ተባብሮ ሊኖር ይችላል፡፡ ኢትዮጵያና  ብሔረሰቦቿ በተቃርኖ የቆሙ ሳይሆኑ፣ ተደጋጋፊዎችና አንዱ ያለሌላው የተሟላ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው፡፡
ከታሪካችን እንደምንገነዘበው የአገሪቱ ህልውና ምርጫ በአሐዳዊነትና በመበታተን መካከል አይደለም፡፡ ሁለቱም ተሞክረው ያላዋጡ መንገዶች ናቸው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የአገር ግንባታ ሥርዓት ብዝሃነትና አሐዳዊነትን በዴሞክራሲ አማካይነት የሚያቻችል  ነው፡፡ ፌዴራሊዝም ለብዝሃነት ባለው ትኩረትና ዴሞክራሲ ለእኩልነት ባለው ትኩረት መካከል አለመጣጣም የለም፡፡ ብዝሃዊ መንግሥታት በመገንባት ረገድ ቀንደኛው ተግዳሮት ሕዝቡ መንታ ዘውጋዊና ብሔራዊ ማንነት እንዲላበስ ማስቻል ነው፡፡ ለዚህም ማንነት ንብርብራዊ ተፈጥሮ እንዳለውና በደመነፍሳዊ ጥጎች ብቻ እንደማይገደብ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ያለንበት ፌዴራላዊ ሥርዓት በዋነኝነት በቋንቋ መሥፈርት የተሠራ መሆኑ መሠረታዊ ግድፈቱ ነው፡፡ በተጨማሪ አብዛኞቹ የፌዴራል ሥርዓታችን ግዛታዊ አሐዶች ታሪካዊ መሠረት የላቸውም፡፡ ይህም የክልሎችን ተቀባይነት አሳንሶታል፡፡ ስለዚህም ተመራጩ የአገር ግንባታው ርዕዮት የባህል ነጻነትን ወይም ራስ ገዝነትን ኢግዛታዊ (‹ኮንሶሲየሽናል ዴሞክራሲ› ተመራጭ ነው) የሚያደርግ ሊሆን ይገባል፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱን ከዘውጋዊነት ወደ አስተዳደራዊነት አሐዶች መቀየር ብቻ አይበቃም፡፡ አሁን እንደሚታየው ፌዴራላዊ ሥርዓቱ ከአገር ዐቀፋዊ ትብብር ይልቅ የክልሎች ፉክክር ማዕቀፍ እንዳይሆን፣ በክልሎችም ሆኑ ክፍለ አገራት መካከል ጠንካራ ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮችና ትስስሮችን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
የአገር ግንባታ ዕቅዶች የዜጎችን ባህላዊ አድማስ በድምር በሚያሰፉ እርስ በርሳቸው በሚሰናሰሉና በሚመጋገቡ ለውጦች መተለም አለበት፡፡ ከርዕዮታዊና ባህላዊ ጉዳዮች በተጨማሪ መሠረቱ ሰፊ የሆነ ማኅበረ – ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችንም ማካተት አለበት፡፡
አገር ግንባታ ነባሩን የሚያጠናክር፣ የሚያሻሽልና አዲስ የሚፈጥር ዘርፈ ብዙ የለውጥ ስልቶችን ያቀናጀ መሆን አለበት፡፡ ማንኛውም አዎንታዊ የግንባታ ጥረት ታሪካዊና ባህላዊ ቀጣይነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል፡፡ በአዲሱ የብሔርተኝነት እሳቤ ውስጥ ነባሩን ማንነት ችላ ማለት ፅኑ ግድፈት ነው፡፡  በተጨማሪም የአገር ግንባታውን በአገር በቀልና በማኅበረሰቦች የጋራ እሴቶች ላይ መመሥረትም የማይታለፍ ቁም ነገር ነው፡፡
የአገር ግንባታ በሁለት መልኩ በላዕላዊና ታኅታዊ መዋቅሮችና ሂደቶች የተቀናጀ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት በግንባታው ሂደት ማዕከላዊ ቦታ ቢኖረውም፣ በተጓዳኝ ከታች በሰፊው ሕዝብ ፈቃዳዊ ጥረት የሚደገፍ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ እንደታየው መንግሥታዊ ብሔርተኝነት ራሱ በታሪክና በፖለቲካዊ ኀይል አሰላለፍ ተጽዕኖዎችና በፖለቲካዊ ብልጠት የተነሳ አገራዊነቱ ወይም ዘውጋዊነቱ ሊጎላ ይችላል፡፡ ለዚህ ሚዛን የሚያስይዝ ዘላቂ ሕዝባዊ ብሔርተኝነት ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ የአገር ግንባታው በልሂቃዊ መደቦች ተንጠልጥሎ እንዳይቀር በስፋትና በጥልቀት ከሕዝባዊነት ጋር ማጣጣም ተገቢ ነው፡፡
በአጠቃላይ በአገር ግንባታው ሂደት ማን ምን እንዴት ይሥራ የሚለው ፍኖተ ካርታን በጥንቃቄ ማዘጋጀት ታላቅ ትኩረት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት የሕዝባቸውን ብሔራዊ ማንነት በመቅረፅ ጥረት ላይ ሊሠሩ የሚፈቀድላቸው፣ የሚበረታቱት፣ የሚፈለግባቸው ወይም የሚከለከሉት ተለይቶ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የአገር ግንባታው ባህላዊ ዘርፍ ሕዝባዊ ትዕምርቶችን በየትኞቹ የጋራ እሴቶች ላይ ይገንባ፤ ከታሪካችን የጋራ ብሔራዊ ትውስታን በመገንባቱ ጥረት የቱ ይፈቀድ፣ ይበረታታ ወይም ይከልከል? የሚሉትን በቅጡ የሚለይ ሊሆን ይገባል።
Filed in: Amharic