>
5:13 pm - Tuesday April 19, 0349

ነፃነት ግሮሠሪ እና የጠረጴዛዋ ዕድምተኞች...!!! (እውነተኛ ታሪክ) ክፍል ፪ አሰፋ ሀይሉ

ነፃነት ግሮሠሪ እና የጠረጴዛዋ ዕድምተኞች…!!!

(እውነተኛ ታሪክ) ክፍል ፪
አሰፋ ሀይሉ

« A tavern is a place where madness is sold by the bottle. »
    — Jonathan Swift
ይህ ነፃነት በጠርሙስ የሚሸጥበት የወዳጆች ደሴት ነው፡፡ ይህ ደስ የሚል እብደት በብርጭቆ የምትገሽርበት የደስታ ምኩራብህ ነው፡፡ ይህ ከበህ ፓርላማውን የምታስቀናበት ዝጉብኝ የሀሳብ ፍልሚያ ግሮሰሪህ ነው፡፡ ይህ የሰፊው ሕዝብ የነጻነት መስክ ነው፡፡ ብዬ ነበረ የተሰናበትኩት በቀጠሮ፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት፣ ከ‹‹ለውጡ›› በፊት ላይ ነበርኩ በግሮሰሪው፡፡ መጨረሻዬ የነጻነት ግሮሰሪ ነው፡፡ ዛሬ ግን ከሌላ ቦታ ልጀምር፡፡ ሰሜን አትላንቲክን በ11,500 ኪሎሜትር በአየር አቋርጬ፣ በርሊንግተን ላይ ባገኘሁት ሌላ ግሮሰሪ ላይ!
በርሊንግተን ማን ናት? በውሃ የተከበበች ውብ ከተማ ናት፡፡ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ቀይ ህንዶች ይኖሩባት ነበር፡፡ አሁን ደሞ የአውሮፓውያን ትውልዶች የሆኑት ካናዳውያን ይኖሩባታል፡፡ ሌሎችም፡፡ ‹‹በርሊን-ግተን›› ላይ፡፡ መጀመሪያ ስሟን ሳውቅ አዲስ አልሆነችብኝም ነበር፡፡ ምናልባት ነጻነት ግሮሰሪ አብሬያት የቀመቀምኳት ደንበኛ ስም ይሆን? ብዬ ስም ሳስስ… ጉድ ሆንኩ፡፡ የስም መመሳሰል ነው፡፡ እንደ ‹‹ዋሺን-ግተን››፡፡ እንደ ‹‹ኦርሊን-ግተን››፡፡ እንደ ‹‹ሌክሲን-ግተን››፡፡ ማለቂያ እንደሌላቸው ‹‹ግተን›› የሚል የሥፍራ አመልካች ቅጽልን በስማቸው ከደረቡ ከተሞች አንዷ ሆና አገኘኋት፡፡
እነዚህን ሁሉ ከተሞች ምን ግተው ቢያገኟቸው‹‹-ግተን›› በ ‹‹-ግተን›› አድርገው እንደጨረሷቸው፣ ወይ ምን ጉድ ነገር አትንነው ‹-ተን›› የሚል ሆሄ እንደቀጠሉላቸው ሀባ ነገር አላውቅም፡፡ ለምን ስለ ራሴ ሀገር ከተሞች አትጠይቀኝም? ስለ እነ ደብረ-ዘይት፡፡ ደብረ-ሊባኖስ፡፡ ደብረ-ሃይቅ፡፡ ደብረ-ማርቆስ፡፡ ደብረ-ዳሞ፡፡ ደብረ-ወርቅ፡፡ ደብረ-…፡፡ ብዙ ደብረ-ዎች፡፡
ወይ ባይሆን ስለ ‹‹ወረ-››ዎች ብትጠይቀኝ.. ጥሩ ነበር፡፡ ስለ ወረ-ኢሉ፡፡ ወረ-ባቦ፡፡ ወረ-ሂመኑ፡፡ ወረ-ወረ፡፡ ወረ-ቀት፡፡ ወረ-ዳ፡፡ ወረ-ብ፡፡ ወረ-ኛ፡፡ ወረ- … እያልኩ ትንፋሼ እስኪቋረጥ የወረ-ዎች መዓት አንበለብልልህ ነበር፡፡ አሳቀኝ፡፡ ‹‹ገንደ-›› የሚለው የቦታዎች ቅጽል ትዝ ሲለኝ! እኔን ብሎ አንበልባይ! እባክህ የረባ ግሮሰሪም ያላገኘሁ፣ የሰው ሀገር ሰው ነኝና.. እንዲች ብለህ አትጥራብኝ፡፡ በርሊንግ-ተንን፡፡ ለካ በስሙ ላይ ቅጽል ያለውም ሞኝ ነው!
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
ዕድሌ ሰምሮልኝ በሄድኩበት አንገት ማስገቢያ የምትሆን ዛኒጋባ ግሮሠሪ አጥቼ አላውቅም፡፡ አሁን ያለሁበትም ቦታ (ስሙን አትጥራብኝ ያልኩህ!) ሰፊ ‹‹ቢር-ጋርደን›› አለው፡፡ የድራፍት-ወ-ቢራ ሰፊ ማሳ! በማማር ከሆነም የነጻነት ግሮሰሪን የሚያስቀኑ ማለፊያ ግሮሠሪዎች አሉ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን እነዚያ የነጻነት ግሮሰሪ ትያትረኛ ታዳሚዎች እዚህ የሉም፡፡
በእርግጥ እዚህም በሳምንቱ ማለቂያ በየግሮሠሪው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ቢኖሩም እኔን ባይተዋሩን አይመለከቱም፡፡ ቢኖሩም ግን ገና በጉባዔተኝነት አልመዘገቡኝም፡፡ ሰዎች ያሽካካሉ፡፡ የተጠበሱ ድንቾችና የዶሮ ክንፎች ይመጣሉ፡፡ የእንቁላል አምቦቲቶዎች ይሸታሉ፡፡ እዚህ ግሮሰሪ ውስጥ ያለውን ነገር ከምዘረዝር፣ የሌለውንና ግሮሰሪነቱን በዜሮ የሚያስገባውን የራሴን ነገሮች ብዘረዝርልህ እመርጣለሁ፡፡
ለምሳሌ፡- የተቀቀለ እንቁላል በእንቅብ ተሸክሞ፣ እፊትህ ፈንክቶ፣ ሚጥሚጣና ጨው ነስንሶ.. የሚሰጥህ ደንበኛ እዚህ የለም፡፡ የባቄላ በቆልት ሰናፍጭ ከሞላበት የሚያቃጥል አዋዜ ጋር ባረጀ የስኒ ማስቀመጫ ላይ አውጥቶ ድራፍትህ አጠገብ የሚያስቀምጥልህ የሀበሻ እጅ እዚህ የለም፡፡ ማስቲካ ግዛኝ ብሎ በምሽት ከመቀመጫህ አጠገብ ቆሞ እየተቁለጨለጨ በሙዚቃው ስልት የሚወዛወዝ ከልጅነቱ ሠርቶ መብላትን ከ‹‹ሙድ›› ጋር ቀላቅሎ የሚያዘግም የህጻን ደንበኛ እዚህ የለም፡፡
የመጠጡ መዓት ሞልቶ፣ ከየዓለማቱ ካለ የሰው ዘር የተውጣጣ የተ.መ.ድ. ኮንፈረንስ እስኪመስል፣ ሰዉ በያይነቱ ሞልቶ፣ ቺልኑና ሳንድዊቹ ሞልቶ፣ በቆልትና እንቁላል ቅቅል ግን ሲታጣ፣ እንዴት ይደብራል? ጨዋታህን በጥቅሻ ከምትግባባ ወዳጆችህ ጋር የማታደራበት ግሮሠሪ፣ ሰው ሞልቶበትም የሰው በረሃ ነው፡፡ የሰው መዓት አጠገብህ ተሰድሮ፣ እንዴት ሰው ያስመኝሀል!? ምናውቄው?!! ‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው›› የሚሉት የእኛ ማዶ ሰዎች ነገር ይሆናላ!
ትዝ አሉኝ፡፡ «ሀገር ማለት ሰው ነው» የሚሉት ህብረ-ዘማሪዎች፡፡ ነው ግን? እውነት ሀገር ማለት ሰው ነው? በዚህ ርዕስ ዙሪያ ያኔ ከነጻነት ግሮሠሪ ዕድምተኞቼ ጋር ጠረጴዛችንን ከበን ሳንነታረክበት አልቀረን ይሆን? ግን ግንጥል ትርጉም እንደሆነ ይሰማኝ ነበር፡፡ አባባሉ፡፡
‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው›› የሚለው አባባል፡፡ የሆነ የጎደለው ነገር እንዳለ የሚሰማኝ ነገር ነበረው፡፡ እንዲያውም.. ከጠየቅከኝስ.. ለምን ይዋሻል? ‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው›› የሚለው ዜማ… የአውራው ፓርቲ ቱማታ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ምድር ላይ.. ኤርትራን የሚያህል ሀገር ከነባህሩ የማስገንጠሉን ቅሌት ለመሸፋፈን.. በኢህአዴግ አጫፋሪዎች የተነዛ ዜማ የተለበጠበት የፊት ጭምብል ነው፡፡ ያን እንደ ባህር የሰፋ ትልቅ ሸፍጥ ከትውልድ ፊት የማድበስበሻ ሕዝባዊ እንጉርጉሮ ነው፡፡ ሀገር ማለት ሰው ነው…፡፡
ይሄን ሀሳብ በነጻነት ግሮሠሪ ጠረጴዛ ላይ ሳንወያየው አንቀርም፡፡ ግን ተዘንግቶኛል፡፡ አሁን እንደ አዲስ ወስጄ፣ እንደ ‹‹ቢግ-ቦይ›› እንደተሰኘው ትልቁ የአተም ቦምብ፣ በነጻነት ግሮሰሪ የውይይት ጠረጴዛችን ላይ ድንገት ዱብ ባደርገውስ ኖሮ.. ምን ነበረበት? ጉባዔተኛችን አስተያየቱን ለመስጠት የሚራኮትበት ‹‹ጭቅና›› የመሰለ (ከጮማ ከፍ ያለ)፣ ሁሉም ባንዴ ካልተናገርኩ ስለሚል ጊዜያዊ አፈ-ጉባዔ የሚያስሾም መከራከሪያ ነጥብ ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው? አሁን በገንደ-በርሊን ማንም የለም፡፡ ያለኝ ምርጫ ሃሳቡን መተው፣ ወይ ከራሴ ጋር ብቻዊ ክርክር መግጠም ነው፡፡ ገጠምኩት፡፡ ራሴን፡፡
ሀገር ማለት ግን እውን ሰው ነው? ሰው ብቻ ነው? ታዲያ ከሰው በላይ ምን ይምጣ? አሁን በተቀመጥኩበት ግሮሠሪ ሆኜ ሳስበው እውነት እውነት ሆነብኝ ቱማታው፡፡ ግን ደሞ ሰው ብቻ አይደለማ ሀገር፡፡ ሀገር ከሰውም ይሰፋል እኮ፡፡ ሀገር ማለት ብዙ ነገር ማለት እኮ ነው፡፡ በእልፍ ነገር መገለጽ ነበረበት የሀገር ፍቺው፡፡ ሁሉንም ነገር ነዋ ሀገር፡፡.. እያልኩ ገጠምኩ! ራሴን፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
አንዴ ጋሽ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር – ድሮ ወጣት ሆኖ የተጫጫሰባትን ስዊዘርላንድ በስተርጅና የሚያስጎበኘው አንድ አድናቂውን አገኘ፡፡ እና ሄደ፡፡
ከስዊዘርላንድ ከርሞ ሲመለስ ጋዜጠኛ እየጠየቀው ነው፡፡ መጀመሪያ ሀገርህ ናፍቃሀለች ወይ? ብሎ ጠየቀው፡፡ እንዴ! ሰው አይደለሁ እንዴ? እንዴት አይናፍቀኝም? ብሎ መልሶ ጋዜጠኛውን ጠየቀው ጋሽ ስብሃት፡፡ ቀጠለና ጋዜጠኛው ከሀገርህ ምን ናፈቀህ? ብሎ ጠየቀው፡፡ ጋሽ ስብሃት ሲመልስ አፍታ አልፈጀበትም፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ነዋ የናፈቀኝ፣ ሁሉም ነገር፣ ሰዉም፣ አየሩም፣ ዛፉም፣ መሬቱ አፈሩም፣ ዝናቡም፣ ንፋሱም፣ አዙሪቱም፣ ከብቱም፣ ኩበቱም፣ ሌላ ቀርቶ ዝንቡ!
በጧት ሰፈርህን የሚያሞቅልህ የአውራ ዶሮዎች ጩኸት ቀላል ነገር ይመስልሀል፡፡ ግን እሱም ይናፍቅሀል፡፡ አቧራው፣ ጭልፊቱ፣ ቁራው፣ ዛፉ፣ ቅጠሉ፣ ዝንቡ ሁሉ ይናፍቅሃል፡፡ ‹ከሁሉም በላይ የናፈቀህ ማነው?› ብለህ ከጠየቅከኝ፣ አቡቹ ነው እልሃለሁ፡፡ አቡቹ፣ የኩኩሻ ልጅ፣ የልጄ ልጅ፡፡ እኔ ስሄድ ስሜን በትክክል መጥራት እንኳን የማይችል እንቦቃቅላ ህጻን ነበር፡፡ እና ያ አንደበት የሌለው አቡቹ.. ከስንቱ ሰው መሐል ተለይቶ ይናፍቀኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ግን ሆነ፡፡
እንግዲህ ወሬ አናወራ?! ገና በደንብ አፍ አልፈታ?! ወይ አብረን አንጠጣ!? አብረን ብዙ ዓመት አላሳለፍን!? ምሥጢሩን አላዋየኝ!? ‹እንዴት ከሰው ሁሉ በልጦ አቡቹ ሊናፍቅህ ቻለ?› ብትለኝ ‹ምክንያቱን አላውቀውም!› እልሀለሁ፡፡ በቃ የሆነው ግን እንደዚያ ነው፡፡ የምትናፍቀውን ትናፍቃለህ፡፡ የማትናፍቅውን ብሽቅ ነገር ደሞ ስለተገላገልከው ደስ ይልሃል፡፡ (ሳቅ) ብሽቁንም ራሱ እያየህ ለመብሸቅኮ ትናፍቀዋለህ፡፡ ወገን ማለት እሱ አይደል? ምንም ምክንያት ሳይኖርህ ሁሉን ስትናፍቅ፡፡ አብልጠህ የምትናፍቀውም ይኖራል – እንደነገርኩህ እንደ አቡቹ፡፡ ያ ሁሉ ተጠራቅሞ ነውኮ ሀገር የሚባለው!
ወይ ጋሽ ስብሃት፡፡ ህይወትን ፍልስፍናው፣ ፍልስፍናን ደሞ ህይወቱ አድርጎ የኖረ፡፡ የታደለ ነጻ ሰው፡፡ በዚያ ሁሉ ዓመት ወደ ነጻነት ግሮሠሪ ብቅ ብሎ አብሮን ከእብደት ማዕዳችን ተቋድሶ አለማወቁ አሁን ከስንት ጊዜ በኋላ ቆጨኝ፡፡ ጋሽ ስብሃት የጓደኛውን የሰሎሞን ዴሬሳን እህት አግብቶ ይኖር ነበር፡፡ የ66ቱ አብዮት ሲፈነዳ፣ ለውጡ ከምቾት ኑሮ ነቅንቆ ስደተኛ ካረጋቸው መሐል ነበሩ፡፡ ባለቤቱ አንድ ልጁን ይዛ ሄደች፡፡ ጋሽ ስብሃት አሻፈረኝ ብሎ ቀረ፡፡ ወደ እንግሊዝ፡፡
ጋሽ ስብሃት ለትምህርት ፈረንሣይም ሀገር የሄደ ሰው ነበር፡፡ ምናልባት እዚያ እያለ ይሆን ሀገሩ የናፈቀው? እሱ እንደዚያ ነው አይልም! ተመችቶን ስንምነሸነሽ ነበር የቆየነው – ይልሃል ስለፓርስ ሲያወራ፡፡ እንጂ ሀገር ናፈቀን አይልህም፡፡ በወጣትነት እብደቱም መሀል ግን፣ በውስጡ ሀገሩን መናፈቅ የት ይቀርለታል?
ምናልባት እዚያ አውሮፓ እያለ ይሆናል፣ ‹‹ሰባተኛው መልዓክ›› የሚባለውን በሰው ሀገር የተመሳቀለ ወዝጋባ ሰውዬ ገጸ ባህርይው አድርጎ የጻፈው፣ እና ከሀገሩ የወጣ የሚደርስበትን አበሳ ያውጠነጠነው፡፡ እና የዚያኔ ገና ይሆናል የሀገር ናፍቆትን ያወቀው፡፡ ሆነህ ሞክረው፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ፡፡ ዓለም የኔ ናት ብትልም፡፡ ለስደተኛ ግን፡፡ ሀገር ማለት ሰዉ ነች፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
የ‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው›› ወይ ብለህ የምትከራከረው ወገን በሞላበት ሀገር ላይ ሆነህ ነው፡፡ ሰው የጠፋብህ እለት ግን፣ ሀገር ማለት ሰው ይሆንብሃል፡፡ ካላመንከኝ፣ እንዲያ የነጻነት ግሮሰሪ ጠረጴዛ ይጠበኝ የነበርኩት የምሽት አርበኛ፣ አሁን እንዴት ኩምሽሽ ብዬ ሞባይል ስልኩ ላይ ተጠምዶ የሚውል የምሽት ኮሳሳ እንደወጣኝ… ገባ በልና የስደተኛውን ግሮሰሪ አሳላፊ ጠይቅ፡፡ ይህን ስል.. ‹ሀገር ማለት ሰው ነው› – እያሉ ያቀነቀኑት አድርባይ ሙዚቀኞች – ድጋሚ ፊት ለፊቴ መጡ፡፡
ስንት ጊዜ ነበር የወረፍኳቸው እነዚያን ሙዚቀኞች? ብዙ ጊዜ፡፡ ሀገር ማለት ሰው ከሆነ ፍልስጥዔምና እስራኤል 70 ዓመት ሙሉ (እስካሁን ድረስ) ለቁራሽ መሬት ለምን ይጋደላሉ? ሀገር ማለት ሰው ከሆነ…፡፡ ብዙ ምሳሌዎች፡፡ እነዚያን ምሳሌዎች መደጋገሙ፣ ውስጤን ሁለት ሶስት ቦታ ከፈለብኝ፡፡ ከራስ ጋር ሙግት እንደመቀመጥ የመሰለ ምን አስቀያሚ ነገር አለ? አፎ በሉኝ ማለት ቃጣኝ፡፡ የውስጤን ሞጋቾች፡፡ ‹‹ሀገር ማለት ሰው ነው፣…›› ብለው የሚዘፍኑ አድርባይ ሙዚቀኞቹን ጭምር፡፡
በቃ ምናልባትም ሁለቱም፣ ሁሉም ልክ ይሆናሉ፡፡ ሙዚቀኞቹ ባለጊዜን መስለው ለማደር አስበው ሳይሆን፣ ሁሉም ስደትን ዘመናቸው ቀምሰውት መሆን አለበት፡፡ ሰው ሞልቶ ሰው አይኖርህማ በስደት፡፡ ‹‹ሀገር ማለት ልጄ..›› የሚለው የበላይ በቀለ ወያ ይሁን፣ የበድሉ ዋቅጅራ ይሁን፣ ወይስ የኑረዲን ኢሣ.. ብቻ ‹‹ሀገር ማለት ልጄ..›› የሚለው ስንኝ እንደዘበት መጣብኝ፡፡
ቆይ ግን ይሄ ሀገራዊ ብሔርተኝነት እኛ ላይ ሲሆን ትንሽ አልበዛም ግን? ‹‹ዓለም ማለት ልጄ…›› ብሎ መግጠምስ አይቻልም ነበር? – አሰብኩት፡፡ ሆሆ..! ዓለም የወዛደሮች መሆኗን ከልባቸው ተቀብለው ሲያበቁ በእኛ የአማርኛ መማሪያ መጻህፍት ላይ ‹‹ዓለም በተፈጥሮሽ ትርጉምሽ ምንድነው…?›› እያሉ ያሸመደዱን እነ ዶ/ር ዓለሜ እሸቴ አሁን ግን የት ናቸው? እኛን ዓለም ላይ አውጥተው ጥለው… እነርሱ የትኛው ዓለም ላይ ይሆኑ? ብዬ አሰብኩ፡፡
ኧረ በህጋምላክ!? ለሀሳብህ ቡሽ አብጅለት እንጂ ጌታው?! ‹‹ለምን ጠባብ ብሄርተኛ አላደረጉኝም? ቢያንስ ለምን ሀገራዊ ብሔርተኛ አላደረጉኝም?›› ብለህ እየከሰስክ ነው የልጅነት የቀለም አባቶችህን? የሚል ሀሳብ መጥቶ ታገለኝ፡፡ ተውኩለት፡፡
ያኔ የመጀመሪያው ባለሰማያዊ ቀለም የጠመኔ ማጥፊያ ዳስተር የሚያህለው የኖኪያ ሞባይል ስልክ በመጣ ጊዜ፣ ስልክህን ስታጠፋና ስታበራው የሚጨባበጡትን የዩኤስ-ኤይድ ግብረሰናይ ድርጅት ምልክት የሚመስሉ እጆች ማየት ካልፈለግክ፣ በምትኩ የፈለግከውን አጭር የሠላምታ ቃል መክተት ትችል ነበር፡፡
እና በዚያች ጠባብ የኖኪያ ዕድል ተጠቅሜ ‹‹I AM A GLOBAL CITIZEN›› የሚል ሠለምታ ለራሴ ሳሰጥ የከረምኩ ሰው ነበርኩ፡፡ የዓለም ዜጋ ነኝ፡፡ የሚለው የዳስተሩ ኖኪያ ሠላምታ ብልጭ አለብኝ ፊቴ ላይ፡፡ ከዓለም ዜግነት ወደ ሀገር ዜግነት በፈቃደኝነት ካወረድኩት ቆየሁ ራሴን፡፡
ከሀገር ዜግነት ደግሞ ወደ ሰው ዜግነት፡፡ እያለ ይቀጥላል፡፡ እናቴ ሆድ ውሰጥ ተመልሼ እስክገባ ድረስ በ‹‹ሪቨርስ ኦስሞሲስ›› በዚህ ዓለም ላይ ያፈራሁትን ማህበራዊ ካፒታል ሁሉ ከላዬ እየጣልኩ ሄጄ፣ በመጨረሻም ወደ ቤተሰቤ፣ እና ወደ አንድ ነጠላ ራሴ ክርታስ እስክገባ ድረስ… እየተምዘገዘግኩ እወርዳለሁ፡፡ ወደ ምድሬ፡፡ ወደ ሀገሬ፡፡
ግን እውን.. ሀገር ማለት ሰው ነው? እሺ ይሁን! ግን ስንት ሰው? አንድ ራስን? አንድ ሺህ? አንድ ሚልዮን? መቶ ሚልዮን? በስንት ሰው ‹‹ኢኩዌሽን›› ሲቀመር ነው ሀገር ሰው ማለት የሚሆንበት ‹‹ኢኩዊሊብሪየም›› (የስሌቱ እኩሌታ) የሚገኘው? በስንት ሰው ነው ሀገር የተሰላው? የሆነ መሬት፣ የሆነ አየር፣ የሆነ ግዛት፣ የሆነ ባህር፣ የሆነ አጥር፣ ተነጥሎ ሲሄድ – አብሮ ሰውንም ይዞ አይሄድ ይሆን? ሰው አይጎድልበትም ይሆን ሀገር? እውን የምንለውን ያህል ለሰውስ ግን ትኩረት እንሰጣለን እኛ? ሀገር ማለት ሰው በሆነባት ሀገር ከሰው መወረር የበለጠ ‹‹የመሬት ወረራ›› ለምን ትልቅ ርዕሳችን ይሆናል…??
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
ማነህ አሳላፊ!? ያመጣህልኝን ድራፍት፣ የጊዮር… (ጊስን..) ብዬ ልጠራ ከአፌ ላይ መለስኩት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብጻዊ ነበር መሰለኝ አይደል? አንዳንድ ቀን አለ ደሞ፡፡ ሀገሮችን የሚያደበላልቅብህ፡፡ ዛሬ አንዱ ነው፡፡ ጊዮርጊ.. (ሱን) ተወው፡፡ በእርግጥ ከ100 በላይ ቢራዎች አሉት ይሄ ግሮሰሪ፡፡ የእኛ ሀገሩ ጊዮርጊስ ድራፍት ባይኖር፣ የራሳቸው ሳንጆርጅ ድራፍት ግን አያጡም፡፡ በቃ እሱ ይቅርብኝ፡፡
‹‹ማነህ አሳላፊ!? ድገመኝ የቅድሙን አልኩህ እኮ! ስሙ ጠፋኛ! ‹‹ኤርዲንገር›› ነበር? ‹‹ፒልስነር›› ነበር ወይስ ‹‹ኮሮና›› ያመጣህልኝ ቅድም??›› ብዬ ትዕግሥቱ በተሟጠጠ ቅላጼ ጠየቅኩት፡፡ እንደማያስታውስና ቶሎ ካልነገርኩት ሌሎችን ሰዎች አስተናግዶ እንደሚመለስ ነገረኝ፡፡ የጭንቅላቴን ደረጃ – በ‹‹ሾርት ሜሞሪዬ›› ከለካ በኋላ ደረጃዬን ወደ 3ኛ ዲቪዚዮን አውርዶ መድቦኛል ማለት ነው፡፡ ሲያንሰኝ ነው፡፡
አሁን የጠጣሁትን ድራፍት እንዴት እረሳለሁ? እኔስ እሺ ረሳሁት፡፡ ግን እሱስ አሁን ያመጣልኝን ድራፍት እንዴት ይረሳዋል?፡፡ ፈገግ አልኩኝ፡፡ እኔ ብቻ ስላልሆንኩ፡፡ ባለ ሾርት ሜሞሪው፡፡ እሱም ነው፡፡ ‹‹ጊዜዬን አትግደልብኝ!›› ማለቱ ነው፡፡ ጊዜዬን እየገደልኩ ነው፡፡ የሰውን ጊዜ የመግደል ግን መብቱ አልተሰጠኝም፡፡ እውነቱን ነው፡፡ በቃ የፈለግከውን ደስ ያለህን አምጣልኝ! አልኩት ፈገግ ብዬ፡፡
‹‹ባድዋይዘር›› ይምጣልህ?! አለኝ፡፡ ደስ ይበለው ብዬ ደገምኩለት ስሙን አዳንቄ! አዎ ‹‹ባድዋይዘር!››፡፡ እስቲ ካልጠፋ ስም ‹‹ባድዋይዘር›› ብሎ የመጠጥ ስም ማውጣት ምንድነው? ባድ-ዋይዘር – ባድ-ዌዘር ይሆን በጀርመንኛ? መቼም የቢራ ዘር አውሮፓ ነው ምንጩ፡፡ እነሱ ናቸው እንዲህ ባድ-ዌዘር ላይ ጥለው የሚያወዛግቡኝ፡፡ ባድ-ዋይ-ዘር አርጎ ያስቀርህ አቦ ያባቴ አምላክ!! ነጃሳ ሀገር!?!
የሀገር ፍቅሩ ተዋናይ ደበሽ ተመስገን በሆነ ትያትር ላይ ‹‹ደብል ጂን ይምጣልህ?›› የሚላት አስቂኝ አባባል መጣችብኝ፡፡ ብቻዬን በተቀመጥኩበት የባድ-ዋይ-ዘር ግሮሰሪ – ሳልወድ በግድ ፈገግ አልኩ፡፡ የኛን ደረቅ ጂን የሚመስል ‹‹ባካርዲ›› የሚሉት አረቄ አለ እዚህ፡፡ የተናደዱም ያልተናደዱም ሲልፉት አያለሁ፡፡ ሞከርኩት ለራሴ አባባሉን፣ በደበሽ ድምጽ አስመስዬ፡- ‹‹ደብል ባካርዲ ይምጣልህ?››፡፡ ብዙ ሳቅ፡፡ ሀሀሀሀ!!!
‹‹ሳቅ! ካንተ ጋር ትስቃለች ዓለም፣
ስታለቅስ ግን፣ ካጠገብህ ማንም-የለም!››
   — የአረቦች ምሳሌያዊ አነጋገር
እነዚህ አረቦች ደሞ! አበዙት! አሁንስ!
ቅድምስ?
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
አሁን ወደ መጀመሪያው ጨዋታዬ ልመለስ፡፡ ወደ ነጻነት ግሮሠሪው ጨዋታ፡፡ አስታወስከው? የጓደኛችንን ጓደኛ? በፀባዩ ገርነት ጠረጴዛችንን በጊዜያዊ አባልነት እንዲቀላቀል የፈቀድንለትን? ታጋዩን ሹም? አዎ! እሱ ባለበት፡፡ የፖለቲካ ጨዋታችን እየጦፈ ሄደ ብዬህ ነበር ባለፈው፡፡
ብዙ እየተናነቀኝ የገዢውን ፓርቲ የህትመት ልሳን ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲን›› ርዕሰ-አንቀጽ የመሰለ የእንጀራ ወሬን፣ ምንም ሳይጨማምርበት፣ ማንም ሳያስገድደው፣ ሰው በግል የዓየር ሰዓቱ አምጥቶ የሚደግመው ለምንድነው? አይገባኝም፡፡ የኢትዮጵያን መጪ ዕቅድ ይሄ የኢህአዴግ ካድሬ ሲናገር ‹‹ማላታይን›› የሚባለውን የሚሰነፍጥ መርዝ ወይ ያን ‹‹ኮድ-ሊቨር-ኦይል›› የሚባል ከሩቅ የሚያንገፈግፈኝን የዓሣ ዘይት በግድ የጋተኝ ያህል ተንገፈገፍኩ፡፡ ቴሌቪዥን ቢሆን በሪሞት አጠፋዋለሁ፡፡ አሁን ግን ምርጫ አልነበረኝም፡፡ ፊት ለፊቱ ቁጭ ብዬ ሰማሁት፡፡ ፈገግ እያልኩ፡፡ ማስመሰል ነው ጠላቴ!
እየሰማሁት አንዲት ጥያቄ ከልቤ አምልጣ ልውጣ-ልውጣ እያለች ታገለችኝ፡፡ ጠያቂው ብዙ ነበር፡፡ የሰውየው መልካም ጠባይ በነቆራ እንድታንጓጥጠው አይፈቅድልህም፡፡ ስለዚህ የሚቀርህ አማራጭ በዚህ በዚያ እያልክ በጥያቄ ማጣደፍ ብቻ ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል? አንድዬ ፀሎቴን ከሰማ በጥያቄ ብዛት ተመርሮ ሊጠፋም ይችላል፡፡ በመጨረሻ ሁሉም ጠያቂ በሆነበት የምሽቱ ጉባዔተኛ ፊት፣ ተራዬን ጠብቄ ያቺን ስትከነክነኝ የቆየች ጥያቄ በተቻለኝ ትህትና ለውሼ አቀረብኩለት፦
“ቆይ እናንተ ህወኀቶች፣ ማለቴ ኢህአዴጎች ግን፣
ከዚህ በኋላ ስንት ዓመት ነው በሥልጣን መቆየት
የምትፈልጉት? ቆይ በናንተ ግምት እንቆያለን
ብላችሁ የምታስቡት እስከመቼ ነው ግን?”
ብዬ ጠየቅኩት። ትዝብት በሚመስል አሳጪ አነጋገር፡፡ ጠረጴዛችንን የተጋራውን የኢህአዴግ ሹም፡፡ ሁሉም ባንዴ ፀጥ አሉ፡፡ ጥያቄዬ ከጥያቄነት ይልቅ ‹‹አይበቃችሁም ወይ እናንተ ሆዳሞች?!›› የሚል ብስጭት ስላለበት፡፡ ጉባዔተኞቹ ከዚያ በላይ ዙሩን እንዳላከረውም ሰግተዋል፡፡ ስለዚህ ጥያቄዬን ተቀብሎ የሚያጋግል ጠፋ፡፡ ሁሉም ጭጭ፡፡ ከዚያ ግን እንግዳው ጉባዔተኛችን ዝምታውን እንደ ድጋፍ ቆጥሮት መሰለኝ፣ ምንም ሳያቅማማ እንዲህ ብሎ መለሰልኝ፡-
“እኛማ ቢያንስ በትንሹ 50 ዓመት እንቆያለን፣
ብለን ነው የምናስበው! የምናስበው በነሲብ
አይደለም.. የምነግርህ በተጨባጭ ተጠንቶ
የተረጋገጠውን ጉዳይ ነው፣ እንደ ህወሃትም፣
እንደ ኢህአዴግም ቁጭ ብለን ገምግመን
የ50 ዓመት ዕቅድ አውጥተን ጨርሰናል..!”
አለ ፍፁም እርግጠኝነት ባደነደነው ኩሩ ፊት፡፡ ሁላችንንም እንደ ድል አድራጊ ጀግና በየተራ በእርካታ እያየ፡፡ አሁኑም ሁሉም ጭጭ አሉ፡፡ ወይም አሉት፡፡ አልገባኝም ዝምታው፡፡ ይሄ መልስ ዝም የሚያሰኝ መልስ ነው እንዴ? በዚህ ዓይነት እኮ ኢህአዴግ ‹‹ብሔራዊ አብዮታዊ ፓርቲ›› የሚባለውን የሜክሲኮውን የ70 ዓመት አምባገነን ገዢ ሊሆን ምሎ ተነስቷል ማለት እኮ ነው፡፡ አልኩ፡፡ አንባቢው እንዳትስተኝ፡፡ እዚያው በነጻነት ግሮሰሪ ላይ ነኝ፡፡ የዛሬ 3 ዓመቱን ነው የማወራህ፡፡ ከ‹‹ለውጡ›› ጥቂት ወራት በፊት፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
ያ PRI የሚባል የሜክሲኮዎቹ ፓርቲ የህዝቡን ስነልቦና እንደ ስኳር ቅሞ የበላ፣ ‹‹ከኮምኒዝም ከራሱ የበለጠ አምባገነን›› የተባለ ፓርቲ ነበር በሰላቢነቱ ብዛት፡፡ PRI እንደ ዓሣ እየተሙለጨለጨ፣ ከመጣው ጊዜ ጋር አብሮ የርዕዮተዓለም አክሮባት ሠርቶ እየተገለባበጠ፣ ግሎ የመጣውን እያበረደ፣ ያንንም ይሄንንም ሃሳብ እያጋበሰ፣ ምሁራንን እያባበለ፣ ያመረረውን በአፈሙዝ እያስወገደ፣ የምርጫ ኮሮጆ እየገለበጠ፣ በሥልጣን ላይ እየተገላበጠ 100 ዓመት ሊሞላው የተቃረበ ፓርቲ ነው፡፡
እና የእኛ አብዮታዊ ፓርቲ ኢህአዴግም በአፈሙዝ የተደገፈ ህልም እንደ ሜክሲኮው አብዮታዊ ፓርቲ በባሌም በቦሌም ብሎ ለአንድ ክፍለዘመን በሥልጣን ላይ መሰንበት ነው፡፡ ማለት ነው?? አይ ሜክሲኮ?! ያኔ ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ትቀላቀል በሚባልበት የተ.መ.ድ. ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ወቅት ሜክሲኮ የአሁኑ ትውልድ የረሳባትን ታሪካዊ ውለታ ውላልን ነበር፡፡ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ታሪክ ሆኖም የሚያስታውሰው የለም አሁን፡፡ ከታክሲ ረዳቶች በቀር፡፡
‹‹ቄራ ሜክሲኮ፣ ሸበሌ ሜክሲኮ፣ አብነት ሜክሲኮ፣ ልደታ ሜክሲኮ፣ ሣርቤት ሜክሲኮ፣ ጥቁር አንበሣ ሜክሲኮ፣ ለገሃር ሜክሲኮ፣ ብሔራዊ ሜክሲኮ..!›› የሜክሲኮ መዓት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የረሳትን ባለውለታችንን ሜክሲኮን፣ የአዲሳባ የታክሲ ረዳቶች ቀኑን ሙሉ ስሟን ጮክ ብለው ሲጠሩላት ይውላሉ! እነዚህ ታሪከኛ ረዳቶች መሸለም ነበረባቸው፡፡
እና ሜክሲኮ መጣችብኝ ተገልብጣ! አንድ ፓርቲ መቶ ዓመት በአምባገነን መዳፉ ጨፍልቆ በሥልጣን የሰነበተብሽ አንቺ ሜክሲኮ! ውለታ የዋልሽልን ሜክሲኮ! የሜክሲኮ አደባባይን በስምሽ ሰይመን ካመት ዓመት በትውልድ አፍ ስናስጠራልሽ ብንኖር… የአንቺ ውለታ ግን ለኢህአዴግ ሞዴል ሆነሽ እኛን ማስጠቃት ሆነ?! እንዲህ ጉድ ታደርጊን ሜክሲኮዬ?! ምነ?!
አንዳንድ ዜማዎች አሉ፡፡ በኩነኔ የተሞላች ነፍስን ተንፈስ የሚያደርጉ፡፡ እና ፈልጌ አገኘሁ፡፡ ፈጣን ዜማ፡፡ የቴዎድሮስ ካሳሁንን፡- ‹‹ጉድ ሠራሽኝ አሃ፣ ጉድ ሠራሽኝ አሄ፣ ጉድ ሠራሽኝ ዋይ ዋይ..›› የሚለውን፡፡ ለሜክሲኮው አብዮታዊ ፓርቲ (ለPRI) ይጋበዝልኝ!!
አሁን አብዮታዊው ፓርቲም – እንደ ኢህአዴግዬ ስሙን ቀይሮ – ተንከረባብቶ – ‹‹ብሔራዊ ፓርቲ…›› ተብሏል! ወይ አምላኬ! አወይ መመሳሰል?! … ብሔራዊ ሜክሲኮ..!! አብነት ሜክሲኮ…!! (እኔስ ይሰማኛል ጡሩምባ! ፍቅሬ ተመልሶ መጣ! ኧረ ጉድ! ኧረ ጉድ.. ፈላ! – በጂጂ ዜማ ተሰናበትኩ)፡፡
. . . / ክፍል-3 (ይቀጥላል)
ሰናይ ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic