>
5:26 pm - Thursday September 15, 5025

የነጻነት ግሮሠሪ እና የጠረጴዛዋ ዕድርተኞች! (እውነተኛ ታሪክ) ክፍል ፬ አሰፋ ሀይሉ

የነጻነት ግሮሠሪ እና የጠረጴዛዋ ዕድርተኞች!

(እውነተኛ ታሪክ) ክፍል ፬
አሰፋ ሀይሉ

በማግስቱ (ይሁን በሳልስቱ) እንደልማዴ፣ ከታክሲ ሰልፍ ለመጠለል፣ ወደ ወዳጃችን ነጻነት ግሮሰሪ ብቅ አልኩ፡፡ የዕለት ድራፍቴን ለመቀማመስ፡፡ የዳንኤል ዮሐንስ ቆየት ያለ ዜማ ከማይክሮፎኑ ይንቆረቆራል፡፡ «ሠላም ላንቺ፣ ውድ እናቴ፣ እልሻለሁ፣ በናፍቆቴ…»፡፡ ደስ አለኝ፡፡
እፊቴ ላገኘሁት ሁሉ ከጀርባዬ ጎንበስ እያልኩ የአየር ላይ የእጅ ሠላምታዬን እያደልኩ ገባሁ፡፡ የተማረከ ወታደር እመስላለሁ፡፡ በነጻነት የተማረከ ወታደር፡፡ የግሮሠሪ ዘማች፡፡ «ሠላም ላንቺ፣ ውድ እናቴ፣ እልሻለሁ፣ በናፍቆቴ…»፡፡ የተለመደችው ጠረጴዛችን እስክትለቀቅ ፈቀቅ ያለች ጥግ ፈልጌ ተቀመጥኩ፡፡
እንደተቀመጥኩ የግሮሠሪዋ ጌታ፣ ያራዶች ቁንጮ የሆነው ወዳጄ፣ ሞቅ ባለ ሠላምታ ተቀበለኝ፡፡ እና ፉጀጋ አጠገቤ ሳይደርስ ቀድሞ፣ በእጁ አረፋ ከደፈቀ ትኩስ (ማለትም ቀዝቃዛ) ድራፍት በጃምቦ ይዞልኝ ካጠገቤ አረፍ አለ፡፡ ገና አረፋውን ፉት ከማለቴ፣ ብርጭቆዬ ባየር ላይ እንዳለ፣ የእለቱን ትኩስ ግን እንግዳ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡
“ትናንት ከእገሌ ጋር ስትጫወቱ በጣም ሞቅ ብሏችሁ ነበር እንዴ?” የሚል ጥያቄ፡፡ አረፋውን ከከንፈሬ በአይበሉባዬ እየጠረግኩ ቀና ብዬ አየሁት፡፡ ፊቱ ፈገግታ እንደተሞላ ነው፡፡ ሀገር-አማን ነው ማለት ነው፡፡ ዛሬን ከትናንት መጀመር አልወድም፡፡ ግን ፈገግታ አይጠፋውም ብዬ አሰብኩ፡፡ እና የትናንትናውን ለአፍታ እያሰብኩ በእርጋታ መለስኩለት፡፡
በመጠኑ ሞቅ ብሎን ነበር መሰለኝ፡፡ ሞቅ ያለ የጨዋታ ምሽት አሳልፈን ነበር፡፡ ምሽታችን ሲጠናቀቅ ደሞ በደስታ ተቃቅፈን ተመሰጋግነን ተለያይተናል፡፡ ነገርኩት። እና መልሼ ጠየቅኩት፡፡
“ግን ለምን ጠየከኝ? ሰክረው ነበር ተባልክ እንዴ?”
ትንሽ አመነታና የጠየቀበትን ምክንያት ነገረኝ፡፡
“አይ እንደዚያ ሰምቼ አይደለም፣ ግን እገሌ [ያ የኢህአዴጉ ሰውዬ] ‘አሣፍ ማታ ሙልጭ አድርጎ ሰደበኝ’ ብሎ ሲነግረኝ ገርሞኝ ነው፣ ወዲያው ነው የነገርኩት፣ መስሎህ ተሳስተህ ይሆናል እንጂ፣ አሣፍ በምንም ተዓምር አያደርገውም ብዬ፣ እሱ ግን ሰድቦኛል ብሎ ግግም አለብኝ፣ ለእሱ አላልኩትም፣ ግን በሆዴ ምናልባት በሞቅታ የሆነ ነገር ሣት ብሎህ ተናግረኸው እንዳይሆን ብዬ ተጠራጠርኩ…” እያለ የቀረበብኝን ስሞታ ከነሰጠው ማስተባበያ በፈገግታ ተሞልቶና በሠርሣሪ ዓይኖቹ እየፈረሸኝ አስረዳኝ። ገርሞኝ አላባራ አልኩ፡፡
ከዚያ ሁሉ የሞቀ ክርክር መሐል፣ ከሌሎቹ ሁሉ ጓደኞቻችን መሐል፣ እኔን ብቻ ነጥሎ ሰደበኝ ማለቱ ገረመኝ። የሆነውን ሁሉ ለወዳጄ ከልሼ አስረዳሁ፡፡ ጨዋነቱን የማውቀውንና የማከብረውን እንኳን እሱን ይቅርና ሌላንም መደዴ ካድሬ ልሳደብ የሚል ሞቅታም ፍላጎትም እንደሌለኝ ነገርኩት። እሱም ከእኔ መስማት ፈልጎ እንጂ አሳምሮ እንደሚያውቅ ነግሮኝ ሌላ ጨዋታ ቀጠልን።
ሰው ግን እውነቱ ሲነገረው እንደ ስድብ የሚቆጥረው ለምንድነው? ወይስ የኢህአዴጎች ፀባይ ነው? የግድ እንደነሱ መወሻሸት፣ መወዳደስ፣ ያልሆነውን ሆነ ብለን መወሻሸክ አለብኝ? ምን ዓይነቱ ነው? በእግዚአብሔር!
ግን እነሱም [ኢህአዴጎቹም] እኮ እርስ በእርስ መወሻሸት ነባር ባህላቸው አልነበረም፡፡ እንደነሱ ግምገማ የግል ህይወት ራሱ እየተፈተፈተ የሚብጠለጠልበት ቦታ እንደሌለ ነው ከብዙ ካድሬዎች አፍ የሰማሁት፡፡ ታዲያ የማይፈልጉት ምንድነው? እንደሚመስለኝ፣ እነሱ የማይፈልጉት እውነቱ ከሌላ ሰው ሲመጣባቸው ነው፡፡ በእነሱ አመለካከት የድርጅታቸው አቋም የእግዜርን ቃል ያህል ነው፡፡ ራሱ ድርጅቱ ካልቀየረው በቀር ጥያቄም፣ ተቃውሞም ሆነ ስላቅ የማይቀርብበት፡፡ የእግዜር ቃል!
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
አመሻሹ ላይ ሌሎችም ምድብተኛ ጓዶች ጠረጴዛችንን ተቀላቀሉ፡፡ ጨዋታው ደራ። በመሐል የህወኀቱ ወዳጃችን ከሌሎች ሁለት ጓዶች ጋር መጣ፡፡ የጨዋታ መንፈሴ ቅዝቅዝ አለ፡፡ ደግነቱ ከእኛ ፈንጠር ወዳለ ወደሌላ ክፍት ጠረጴዛ ሄዶ ወንበር ሳበ፡፡ እፎይ አልኩ፡፡ እንግዶቹን ካስቀመጠ በኋላ ግን ወደኛ መጥቶ የቁም ሠላምታ አቀረበልን። ሠላምታ መች ጠላሁ፡፡ እኔም ሞቅ ባለ ሠላምታ ከመቀመጫዬ ተነስቼ ጨበጥኩት። በዚያች የሠላምታ ቅፅበት ፊቱን ግራ-መጋባት ሲሞላው የተመለከትኩ መሠለኝ። ከዚህ በፊት ‹‹ሰደበኝ›› ብሎ ያሰበን ሰው፣ ሞቅ አድርገህ ሠላም ስትለው፡፡ የዚያ ዓይነት ግራ መጋባት መሰለኝ፡፡ ወቸጉድ!
እርሱም ወደ ጓደኞቹ ሄደ፡፡ እኛም በጠረጴዛችን ከበን በነጻነት ስንጫወት ቆየን፡፡ ባለትዳሩ ሁሉ በጊዜ ተሰናብቶ ወጣ፡፡ መጨረሻ በጠረጴዛችን ሁለት ብቻ ስንቀር፣ የግሮሰሪው ባለቤት ወዳጃችን መጣና እገሌ (ህወኀቱ ወዳጅ) “ቢራ አዞላችኋል፣ የሰው ግብዣ በፍጹም እንደማትወዱ ብነግረውም ሊሰማኝ አልቻለም፣ እና ትናንትም ያ ስሞታ ስላለ (ብሎ በፈገግታ ወደኔ ዞሮ እየጠቀሰኝ) ስሞትላችሁ፣ ለኔ ስትሉ እሺ በሉትና ላምጣላችሁ!?” አለ። ላፍታ እርስበርስ ተያየን፡፡ ሰውን ማስቀየም አልፈለግንም፡፡ በተለይ የነጻነት ግሮሠሪን ባለቤት፡፡ ወዳጃችንን፡፡ ተስማማን።
እሺ ብለን ግብዣውን አክብረን ቢራው ሲከፈትልን ከሩቅ ሲመለከት ጋባዣችን አልጠበቀውምና በደስታ ተሞላ፡፡ ከጠረጴዛው ተነስቶ ወደኛ መጣ፡፡ እና በደስታ አመስግኖን ሂሳብ ከፍሎ ከነጓደኞቹ ወጥቶ ሄደ። ሳስበው የሚከተለውን ፖለቲካና ፓርቲ ማውገዝና የሚገጥመውን የውድቀት ዕጣፈንታ እንደታየንና እንደመሠለን መናገር ማለት እርሱን በግሉ መጥላትም፣ መስደብም፣ መቀየምም ማለት እንዳይደለ በዚያችው ግሮሰሪ በሁለት ምሽቶች የአብሮነት ቆይታው ከሁለመናችን የተረዳ መሠለኝ።
ያ ሰው ለሕዝብ የተሻለ ለውጥ እናመጣለን ብለው ከተነሱና ዕድሜያቸውን በህወኀት/ኢህአዴግ ቤት ከጨረሱ ጥቂት በሙስና ያልተነከሩ ሀቀኛና ንፁህ ታጋዮች አንዱ እንደሆነ አውቃለሁ። በትምህርቱም ቢባል ገና ድሮ ከትጥቅ ትግሉ በፊት በሳይንስ መስክ ዲፕሎማውን የያዘ መምህር ነበር። ከትግሉ በኋላም እንደ ብዙዎቹ ለወረቀት ሽሚያ ሳይሆን፣ ቀድሞ የሚወደውን ሙያ መርጦ በዲግሪ ተምሯል፡፡
እንደ እርሱ ያሉ ጨዋና በጥላቻ ያልተመረዙ ሰዎችም ኢህአዴግ ቤት ውስጥ መኖራቸው ይገርመኛል፡፡ እንደ እርሱ ያሉ ብዙ ሀቀኞች አሉ፡፡ የግንባሩ የሀይል ሚዛን ወደ እንደዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ቢያጋድል ኖሮ ምናልባት ኢህአዴግ ተብዬው የዝርፊያ ቡድን ሀገርን አቆርቁዞና ገነጣጥሎ ሁላችንንም እንዲህ ያለ መቀመቅ ውስጥ አያስገባንም እያልኩ አስባለሁ አንዳንዴ።
ሳስበው የወያኔ/ኢህአዴግ ጦስ ጠራርጎ የበላው እኛን ፓርቲው በደረሰበት-የማንደርሰውን እና አሁን ጦሱ-ብቻ የተረፈንን ያገሪቱን በሚሊዮን የምንቆጠር አኗኗሪዎች ብቻ አይደለም፡፡ የወያኔ/ኢህአዴግ ሀገራዊ ኪሣራ ጠራርጎ የበላቸው ያንን ወዳጃችንን የመሰሉ ብዙ ንጹሃን ኢህአዴጎችም አሉ፡፡
ቀድሞም ህይወታቸውን አሳልፈው ለድርጅቱ የሰጡ፡፡ ኋላም በየዋሀ ልብ የድርጅታቸውን መመሪያ እንደ እግዜር ቃል ያመኑ፣ እና ለሀገር ለውጥ እናመጣለን ብለው በሀቅ የቆሙ፡፡ ከኢህአዴግ ጋር መሥራታቸው የዜግነት ድርሻቸውን መወጣት የመሰላቸው፡፡ ብዙ ንፁሃን አባሎቹን ጭምር ነው ያስበላው ነፍሰ-በላው ኢህአዴግ።
የሚገርመው ያ ሰው፣ ከኢትዮጵያ ከወጣሁም በኋላ አልረሳኝም፡፡ እስከ ቅርብ የትግራዩ ጦርነቱ እስኪነሳ ድረስ፣ በተለያዩ መንገዶች መለስ ዜናዊንና ህወኀትን (“ወያኔን”) አሊያም ኢህአዴግንና ዘረኛ መሪዎቹን በማብጠልጠል በማህበራዊ ሚዲያና በመጽሔቶች በማወጣቸው ጽሑፎቼ ያደረበትን ቅሬታ ያሰማኝ ነበር፡፡ ሲለው በትህትና ቃላት፣ አላስችል ሲለውም በስድብ-አከል ሀይለ ቃላት ተሞልቶ፡፡
ልክ የትግራዩ ጦርነት ሲጀመር ግን ያ የቀድሞ የነጻነት ግሮሰሪ ተጋባዥ ጉባዔተኛችን በቃ ጠፋ፣ ጠፋ፡፡ እልም ብሎ፡፡ ከሁሉም ማህበራዊ ሚዲያዎች፡፡ እና ተጠፋፍተን ቀረን። ጦርነት አለያየን ማለት ይቻል ይሆን? እንደዚያ መሰለኝ፡፡ ነገሮች ከባድ ሊሆኑበት እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡ የት ይሆን በአሁን ሰዓት? ምን ይሰማው ይሆን? የ50-ዓመት ሕልሙን ሲያረግፉበት እኛን የነጻነት ግሮሠሪ ወዳጆቹን አስታውሶንስ ይሆን? ወይስ ከኦሮሙማው ጋር ተስማምተው ከቀጠሉት መሐል ይሆን?
ስለዚያ ሰው ሳስብ፣ ያኔ ‹‹ኡፍ መጣ ደሞ…›› እንዳላልኩ፣ አሁን ግን ከልቤ አሳዘነኝ፡፡ እሱና እሱን መሰሎች የድርጅቱን የእግዜር ቃል ፈጻሚዎች እንጂ ወሳኞች አልነበሩም፡፡ ወደ ገደል ግቡ ሲባሉ ይገባሉ፡፡ በልቤ ወደ ገደል ግባ ሲባል – ለልጆቹ ሲል – እምቢ እንዲል – ከልብ ተመኘሁለት፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
ደግሜ ደጋግሜ የምገልፀው አቋሜ ይህ ነው፡፡ በጦርነት አላምንም። ነገር ግን ለወያኔ እኩይ ሽማግሌዎችም ደግሞ ጥብቅና አልቆምም። እንደ ጲላጦስ እጆቼን በጠጣኋቸው ድራፍቶች ታጥቤ፣ በደማቸው የለሁበትም እንዳልል የሚጎትተኝ አንዳችም ምክንያት የለኝም። ግን ይህ ሁሉ ራሳቸው በራሳቸው ላይ ያመጡት ጦስ ነው፡፡ ሥራቸው ያውጣቸው።
እኔ ምን በወጣኝ? እንደ እርጎ ዝንብ በሰው ጉዳይ ጥልቅ እያልኩ፣ ለየመጣና ለየሄደው ልቋሰል? የሚል ምሬት የሞላበት ስሜት ናጠኝ። እንዲህ ነኝ፡፡ አምርሬ የምቃወመውን ያህል፣ ሰው በእግዜሩ እጅ ሲያዝ፣ አምርሬ መጨከን ያቅተኛል፡፡ የሐረር አስተዳደግ ይሆን? – አላውቅም፡፡
እውነቱን ስነግረው “ሙልጭ አድርጎ ሰደበኝ” የሚል ስሞታ ያቀረበውን ያን የህወኀቱን ወዳጄን አሁን ላይ አስበዋለሁ፡፡ እሱን ብቻ አይደለም፡፡ አብረን ስለ ቤተሰቦቻችን ከመጠያየቅ በስተቀር፣ ልጆቻቸውን ሚስቶቻቸውን ከማስተዋወቅ በቀር፣ አብረውኝ ስለ ብዙ የህይወታችን ደስታና መከራዎች ከመጨዋወት በስተቀር፣ ከሳቅና ከአብሮነት በስተቀር፣ ለአንዲትም ቀን ስለ ህወሃት/ኢህአዴግ ፖለቲካቸው አንስተውብኝ የማያውቁ – ብዙ ለህወሃት የቀረቡ ወዳጆች ነበሩኝ፡፡ ለኢህአዴግም የቀረቡ ብዙ፡፡
አሁን ሁሉንም አስባቸዋለሁ፡፡ እነዚያ ሰዎች ለእኔ ከፖለቲካ ማንነታቸው ይልቅ ሰዋዊ ማንነታቸው ይበልጥብኛል፡፡ ያሳለፍናቸው ጊዜዎች እፊቴ ይመጣሉ፡፡ ልጆቻቸውን አስባቸዋለሁ፡፡ እንዴት ሆነው ይሆን? የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ያ ከጥቂት አጋጣሚዎች በቀር ብዙም አቅራቦት የሌለን የህወሃቱ ወዳጃችን፣ ድንገት ሳት ብሎት ካስታወሰኝ፣ የያኔዋን የነጻነት ግሮሰሪ ወዳጆቹ የነገርነውን ትንቢት መሣይ የኢህአዴግ ውድቀት፣ የእኔን ወሽመጥ-በጣሽ ግምት፣ ድራፍታችንን፣ ሳቃችንን፣ አብሮነታችንን ሁሉ የሚያስታውስ ይመስለኛል፡፡
እንዳልኩት፡፡ ቢያስታውስ እመኛለሁ፡፡ ከሰው ልብ ርቀው ነበር፡፡ መፈራትንና መጠላትን እንጂ መወደድን አላገኙም ነበር፡፡ የሰውን ከንፈር እንጂ የሰውን ልብ አላገኙም ነበር፡፡ ጉልበትን እንጂ ቅቡልነትን አላገኙም ነበር፡፡ ከቦ አጫፋሪ እንጂ ከቦ መካሪ አላገኙም ነበር፡፡ ‹‹በል በል›› የሚል እንጂ ‹‹ተው ተው›› የሚል የራስ ሰው አልነበራቸውም፡፡ በምክር ብዛት አንገቱን ያደነደነ ድንገት አንድ ቀን ይሰበራል፤ ፈውስም የለውም፡፡ ይላል ጠቢቡ ሠሎሞን በመጽሐፈ ምሣሌ ላይ፡፡ የህወሃቶች ነገር እንደዚያ ነው የሆነው፡፡
በነገራችን ላይ፣ ቀሪውም ኢህአዴግ ከአነሳስ ታሪክ በቀር፣ ከህወሃት የሚለይበት ነገር ብዙም አይታየኝም፡፡ የኢህአዴግም መጨረሻ – ስሙንም ለወጠ፣ አልለወጠ፣ በቅርቡ እንደ ህወሃት መሆኑ አይቀርም፡፡ ብዬ ነው የማስበው፡፡ በብዙ ተመሣሣይ ምክንያቶች፡፡
ያ የጠረጴዛችን የእግረ-መንገድ ጉባዔተኛ – በዚህች መሪር ወቅቱ ላይ ቆም ብሎ – ‹‹በነጻነቷ ግሮሰሪያችን፣ በጉባዔተኞች ጠረጴዛችን ላይ ተቀምጬ – በትህትና የነገርኩት እውነት፣ የቱንም ያህል ቢመር፣ የቱንም ያህል ቢያስደነግጥ፣ ስድብ ግን እንዳልሆነ›› በሚገባ የሚገለጽለት ይመስለኛል፡፡
በነገራችን ላይ ትግል ጦርነት ማለት ነው፡፡ የጦርነት ዓላማ ደሞ ‹‹ባላጋራህ›› አንተን የመጉዳት አቅሙን ማሳጣት ነው፡፡ እንጂ ባላጋራህን ማጥፋት አይደለም፡፡ ያን አቅሙን ካጣ፣ በሰብዓዊ አመለካከት ልትቀርበው ይገባል፡፡ በሀሳብ ተለያየን እንጂ ጠላቴ እንኳ አድርጌ ወስጄው አላውቅም ነበር፡፡ ብቻ ያን ንጹህ ሰው – ከነቤተሰቡ – መልካም ነገር እንዲገጥመው ከልቤ እመኝለታለሁ።
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
ሁላችንም ከገባንበት ሀገራዊ አዙሪት የምንወጣበት መንገድ ምን እንደሆነ በየሄድንበት የሚከተል የሁልጊዜ ጭንቀት አለብን። አኔም ሀገሬ ሆኜም ሆነ፣ አሁን ከሀገሬ ከወጣሁ በኋላ በየረገጥኩበት ስለሀገሬ ማውጠንጠኔን አልተውኩም፡፡ ይህን ሁሉ ትረካ አምጦ የሚወልድልኝም፣ ያ ስለ ሀገሬ ደጋግሜ የማስብበት በትውስታዎች የታጨቀ አዕምሮ ነው፡፡
አሁን አሁን ለውጥ የተባለውን ነገራችንን ሳስብ – አንዳንድ ጥያቄዎች ደጋግመው ያቃጭሉብኛል፡፡ በለውጥ ስም የሚሆነውንና የቀጠለውን ያነኑ የምናውቀውን ያንገፈገፈንን ሸፍጥና ጥፋት ሁሉ እያየሁ ግራ መጋባት አልቀረልኝም፡፡ እውነት ግን ኢህአዴግ ወድቋል? እውነት አሁን ህወኀት ዕድሜዋ አብቅቷል? የእኔ የ2 ዓመት ትንበያ ነበር ትክክል? ወይስ የህወኀቱ ወዳጃችን በጥናት የተደገፈ የ‹‹50-ዓመት-በሥልጣን-እንቆያለን›› ትንተና?
የኢህአዴግን ሀገርንና ትውልድን ማኮላሸት ጠልተን ለአመጽና ለለውጥ ተነስተን ስናበቃ፣ በተግባር እርስ-በእርስ እንዳባላን ከተረጋገጠው ኋላቀር የጋርዮሽ ሥርዓቱና ህገመንግሥቱ ጋር – የኢህአዴግን ሥርዓት ለማክሰም ካልሆነ ለውጡ፣ ያ ሁሉ የለውጥ ጩኸትና መስዋዕትነት ለምን አስፈለገ? ሥርዓቱን አሜን ብለን በምርጫ ስም ክበን፣ አዲስ የዳቦ ስም አውጥተን አሸብሽበን ካስቀጠልነው… ህወኀትንስ ለምን ጠላነው? ለውጡ የቂም-በቀል መወጣጫ ብቻ ነበር ማለት ነው?
ሳስበው… የዚህ ሁሉ እንቶ-ፈንቶ፣ እና አንቶ-ፈንቶውን ለማምጣት የተከፈለለት ከባድ ዋጋ.. ትርጉሙ ይጠፋብኛል። ግራ ይገባኛል፡፡ የለውጡ ምንነትና ዓላማም ጨርሶ አይገባኝም። ዛሬም ይሄን ስናገር ቃሌን እንደ ስድብ የሚቆጥሩ የዋሃን ጨዋዎች በብዛት እንደሚኖሩም አውቃለሁ። ትናንትም እውነቱን ስናገር እንደ ስድብ ተቆጥሮብኝ ነበር፡፡ ዛሬም ግን እውነት ስለሆነ ደግሜ እናገረዋለሁ። ከህይወቴ የተማርኩት አንድ እውነት ይህ ነው፡፡ ጊዜ ብቻ ነው እውነተኛ ፈራጅ፡፡ ሁላችንንም፣ የሁላችንንም እውነት፣ ጊዜ ይፍታን – ነው የምለው፡፡
               ΩΩ          ΩΩ         ΩΩ     ΩΩ         ΩΩ
ያንኑ ልጡ-የተራሰውን መቃብሩ-የተማሰውን ያንኑ ያረጀውን-ያፈጀውን በዘር ቆጠራ የተደራጀውን ኢህአዴግን ይዘው፣ ያንኑ ኢህአዴግ ተንተርሰው (ብልጽግና ብለው ሰይመው) ቀጣዮቹ ተረኛ ገዢ ለመሆን እየማሰኑ ያሉት የአሁኖቹ የኦሮሙማም ሆነ የእነርሱ ተባባሪ ሀይሎች፣ መውደቂያቸው ቅርብ እንደሆነ ግልፅ ነው መቼም፡፡
እላቸዋለሁም ፊትለፊት፡፡ ለእኔ እና እኔን ለመሰሉ ከቅርብም ከርቀትም ሆነው – በኢህአዴግ ቡኮ ውስጥ ሳይጨማለቁ ለዓመታት አኳኋኑን አስተውለው ለተከታተሉ ሰዎች ሁሉ፣ አጠራጣሪው ነገር የኢህአዴጎች መውደቅና አለመውቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ በቅርቡ እንደሚወድቁ ግልጽ ነው፡፡ የባሰው ሀገራዊ ፈተናችንም ይህ ቁርጡ የታወቀው የኢህአዴግና ኢህአዴጋውያኑ ውድቀትም አይደለም፡፡ የሚያሳስበኝ እስኪወድቁ ድረስ ያለው ጊዜ (‹‹ጋፕ››) ነው።
በእኔ አስተያየት፣ ከሥር ከመሠረቱ በስብሶ ሣለ፣ በጥቂት ፅንፈኛ አልሞት-ባይ-ተጋዳዮቹ ድርቅና ቆሞ ለመሄድ የሚውተረተረው ኢህአዴግ፣ በዚህ አኳኋኑ ከዚህ በኋላ አንድ ዓመት ራሱ ከሰነበተ ሲበዛ ይገርመኛል። በይስሙላ ምርጫ ቡራኬ ለማግኘት መውተርተሩን፣ ያንን የቀደመውም ኢህአዴግ ያገኛቸውን አጫፋሪዎች ጨምሮ አድርጎታል፡፡ በህገመንግሥቱ ስም አሥጊ የሆኑበትን ማሰሩን፣ መግደሉን – ይህንንም የቀደመው ኢህአዴግ አድርጎታል፡፡
ደህንነቱን፣ ፖሊሱን፣ ጸጥታውን፣ መከላከያውን ለገዢነት መሣሪያ አድርጎ መጠቀሙን – ይህንንም የቀደመው ኢህአዴግ አድርጎታል፡፡ ተቋማትን መጠምዘዙን፣ የውጪ ሀያላንን ማስጨብጨቡን – ይህንን ያለፈውም ኢህአዴግ አድርጎት ያየነው ነው፡፡ እስከ መጨረሻው በደም ጨቅይቶ ለሥልጣኑ መጋደልን – ይህንንም የቀደመው ኢህአዴግ አድርጎታል፡፡ ባጠቃላይ የቀደመው ኢህአዴግ ያላደረገው፣ እና የአሁኑ ኢህአዴግ እንደ አዲስ ሊያደርገው የሚችለው ነገር በምድር ላይ የለም፡፡
ሥልጣኑን በሠላም ለቅቆ፣ ለአዲስ ሀገራዊ ሥርዓትና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መንገድን መጥረግን ብቻ ነው የቀደመው ኢህአዴግ ያላደረገው፣ እና የአሁኑ ኢህአዴግ ሊያደርገው የሚችለው አዲስ ነገር፡፡ ይህን ካደረገ ብቻ ነው በቅርቡ ከሚመጣበት የሞትና የውድቀት አደጋ ሊተርፍ የሚችለው ከውድቀት-ተራፊው የአሁኑ ኢህአዴግ፡፡ አለበለዚያ የበጋና የክረምት መምጣት እንደማይቀረው ሁሉ፣ የኢህአዴግም ውድቀት አይቀርለትም፡፡ ያውም በቅርብ ርቀት፡፡
ግን እንዳልኩት ችግራችን የተረኞቹ ኢህአዴጋዊ ሀይሎች መውደቅና አለመውደቅ አይደለም። ችግሩ እስኪወድቁ ድረስ ባለው ጊዜ በሀገር ህልውናና በህዝብ ደህንነትና ጥቅም ላይ እያደረሱት ያሉትን እጅግ የከፋ ሀገር-አውዳሚ ጉዳትና የጉዳት መጠን፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ጉዳቶቹ ከመድረሳቸው በፊት፣ አሁኑኑ፣ በትክክል የተገነዘበው አለመምሰሉ ነው።
ለዚህ ችግር መፍትሔው ምንድነው? መፍትሔው በምርጫ ካርድም አማካይነትም ሆነ በለመዱት የነፍስ መስዋዕትነት፣ የለውጥ ታርጋ የለጠፈውን፣ እና ህጋዊ ቅቡልነት (ሌጂትመሲ) በባሌም በቦሌም ብሎ ሊላበስ ያሰፈሰፈውን “ኢህአዴግ ቁጥር-2” ትራጀዲ ፊልም ተዋንያን፣ ከነተረኛ ገዢነት ህልማቸው ጋር፣ ከዋና ከተማዋ ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያ ከተሞችና ወረዳዎች በሚደረግ፣ ታላቅ የተቃውሞ ማዕበል፣ በእምቢታና በፀረ-አፓርታይድ ሠላማዊ-ግን-ቆራጥ ትግል ባጭሩ ማጨለም ብቻ ነው።
አለበለዚያ – ኢህአዴግ መውደቁ ለማይቀር በራሱ ሂደት ተንገዳግዶ እስኪወድቅ ከጠበቅነው – ሀገርንም፣ ህዝብንም ይዞ ነውና የሚወድቀው – በህዝብና በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ይከፋል፡፡
ይሄን ማድረግ ቀላል ነው። ይህ የሚሳካው ግን አሁን በሀገሪቱ ላይ መንግሥት ነኝ ብሎ የቆመው – ከወያኔ ተቆርጦ የቀረው ኢህአዴግ – ብልፅግና ተብዬው – ከበፊቱም ወደ ከፋ እጅግ አደገኛና አውዳሚ ወደሆነ የኋልዮሽ መንገድ ላይ ሀገሪቱንም ሕዝቧንም ገፍቶ እየጨመረ መሆኑን ሕዝቡ ከነቃና ካወቀ፣ እና በጊዜ የማያወላውል የለውጥ አቋም ካነገበ ብቻ ነው።
ሕዝባችን የሚበጀው ይጠፋዋል የሚል እምነት ጨርሶ የለኝም፡፡ ይህን እውነት እንደማያጣው ተስፋ አደርጋለሁ። ‹‹ሰዶ ማሳደድ ካማረህ፣ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ›› እንዲሉ ነው፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ከአዲስ አበባ ጀምሮ በየከተሞቹ ግልብጥ ብሎ በሠላማዊና በጨዋ መንገድ፣ የኢህአዴግ ሶስት አሠርት ዓመታትን ያስቆጠረ ሥርዓት በጨዋ ደንብ እንዲያበቃለትና፣ ባለሥልጣናቱም ሥልጣናቸውን ለሕዝብ አስረክበው በሠላምና በጨዋነት እንዲወርዱለት ቢጠይቅ – ሥርዓቱ በሁሉም ሕዝብ ላይ ሊተኩስ አይችልም፡፡ ይህ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡
ተራፊው-ኢህአዴግ ለለውጥ በቆረጠ ሕዝባችን ላይ ለመተኮስ የሚደፍር ከሆነም – ያለጥርጥር አወዳደቁን ከታሪካችን ሁሉ፣ ከቀደመውም ኢህአዴግ ጥቁር ታሪክም ሁሉ፣ እጅግ የከፋው የአወዳደቅ ታሪክ ያደርገዋል፡፡ እንጂ መውደቁን አያስቀረውም፡፡
ሁሉም ይህን ሕዝባዊ አቅሙን እስኪያውቀው ባለው ጊዜ፣ የቀሩን እንቁ ሀገራዊ ነገሮቸ ሁሉ በዚህ ተቆርጦ በቀረው ኢህአዴግና መሪዎቹ እጅ እንዳይወድመብንና፣ ሀገር ከምንለው ነገር ላይ አንዳችም የሚተርፈን ነገር እንዳናጣ በእጅጉ እሰጋለሁ። እስከ ኢህአዴግ ውደቀት ያለን አጭር ጊዜ እጅግ የሚያሳስበኝ በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ለውጥ፣ የህይወት ህግ ነው፡፡ የተጀመረ ሁሉ፣ ፍጻሜ አለው፡፡ የተጀመረው ከዳር እንዲደርስ ከልብ እመኛለሁ!
ፈጣሪ አምላካችን ከክፉ ይጠብቀን። ልቦናችንን ያበርታ። በጥረታችን ሁሉ ያግዘን። ሀገራችንን ይጠብቅ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።
Filed in: Amharic