>

ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የ‹‹ጐሣ›› ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ  (ከይኄይስ እውነቱ)

ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የ‹‹ጐሣ›› ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ 

ከይኄይስ እውነቱ


የዘረኛውና አረመኔው ዐቢይ አገዛዝ የሕዝብን ዓመፃና ድል ነጥቆ ሕዝብ ባመፀበት በቀዳማዊው ኢሕአዴግ አማካይነት በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ላይ ተሰይሜአለሁ ካለና በተግባር ራሱን ካልዓይ ኢሕአዴግ ካደረገ በኋላ ‹‹ለሽግግር መንግሥት›› ባልተገባ ሥልጣን (በጉልበቱ ‹አሻጋሪ› ነኝ ብሏልና) በአገዛዞች እንደተለመደው በርካታ ‹ሕገ ወጥ› ሕጎችን ለጥፋት ዓላማው ማስፈጸሚያ እያወጣ ይገኛል፡፡ የሜዲያ ሕጉን እንደ አንድ አብነት ማንሣት ይቻላል፡፡ አገዛዞች በባሕርያቸው ከሕግ የበላይነት መርህ ጋር የተጣሉ በመሆናቸው ሕግን የሚፈልጉት በጉልበት የያዙትን ሥልጣን ተቀባይነት ያለው ለማስመሰል፣ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጽሟቸውን ወንጀሎች ለመሸፈንና ለጭቆና መሣሪያነት መሆኑን ያለፉት ሠላሳ ዓመታት ከበቂ በላይ አረጋግጠውልናል፡፡ 

የተረኛው ዐቢይ አገዛዝ የጥፋት ዓላማ ያልነውም በአሁኑ ጊዜ ለአብዛኛው ኢትዮጵያው የተገለጠለት ኦሮሙማ የሚባለው – ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በጠላትነት ፈርጆ ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሠራበት ያለ – ፕሮጀክት ነው፡፡ 

ይህ ፕሮጀክት ግንባር ቀደም የጥፋት ዒላማው ካደረጋቸው መካከል መናገሻ ከተማችን አዲስ አበባና ነዋሪዎቹ አዲስ አበቤዎች ይገኙበታል፡፡ 

ኦሮሙማ በአዲስ አበባ ላይ ‹ልዩ ጥቅም› አለኝ በሚል የጀመረው ጥያቄ፣ በባለቤትነት ይገባኛል ወደሚል ከተሸጋገረ በኋላ አሁን የደረሰበት ምዕራፍ አዲስ አበባን ከጥቅም ውጭ/የማትረባ ከተማ የማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ የዚህንም አፍራሽ እንቅስቃሴ መገለጫዎች ዕለት ዕለት እያየናቸው ነው፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ይገኙበታል፤

  • የከተማዋና ቻርተር ሆን ተብሎ ለኦሮሙማ ዓላማ ማስፈጸሚያ በሚመች መልኩ በሕገ ወጥ መልኩ በማሻሻል በከተማዋ ላይ አዲስ አበቤ ያልሆኑ ከተሜ-ጠል እና ሕገ ወጥ አስተዳዳሪዎችን ከኦሮሙማ አራማጆች መሰየም፤ በሕገ ወጥ ሹመኞቹም አማካይነት፣
  • ይሉኝታ ያጣ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ÷ በወራራ በተያዙ ቦታዎች የኦሮሙማ ተቋማትን የመገንባት፣ በዚህም ምክንያት ነዋሪዎችን በገፍ የማፈናቀል፤ 
  • ታሪካዊ ቅርሶችን የማውደም፤ 
  • የቦታ ስያሜዎችን የመቀየር፤ 
  • ነዋሪው ከዕለት ጉርሱ ነጥቆ በቆጠበው ገንዘብ የተሠሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በጠራራ ፀሐይ የመቀማት፤ 
  • የከተማውን በጀት በከፍተኛ ንቅዘት የማባከንና ለከተማዋ ሳይሆን ለኦሮሙማ ዓላማ ማስፈጸሚያ የማዋል፤ 
  • የኦሮሙማውን ሕገ ወጥ ‹ልዩ ኃይል› በከተማው የማሠማራት፤ 
  • ተቋማትን በተለይም የክፍለ ከተሞችን ሹመኞችና ሠራተኞች መለወጥ፣ ቢሮክራሲውንና የመንግሥት ት/ቤቶችን ርእሳነ መምህራን፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞችን በኦሮሙማ ኃይሎች የመተካት፤ 
  • ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳይደረግ ከግዛቱ ውጭ ኦሮምኛ ቋንቋን በግድ የመጫን፤ እና ሌሎችም በግልጽና በኅቡዕ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፤ ወደ ርእሰ ጉዳያችን ስንመጣ ደግሞ፣

እነሱ በተቀበሉት የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› መለኪያነት እንኳን ሲታይ ‹ኢ-ሕገመንግሥታዊ› የሆነ አፓርታይዳዊ ሕግ በማውጣት የከተማዋን ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን መንጠቅ የማንአለብኝነቱ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ የሰየመው ግዛት ምክር ቤት ‹‹በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፊንፊኔ ከተማ ፍርድ ቤት›› የሚል ሕገ ወጥ ‹ፍርድ ቤት› አዲስ አበቤዎች ለሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች አቋቁሟል፡፡ 

OBN ግንቦት 17/2013

⇐ የፊንፊኔ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በይፋ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በኢትዮጵያ ላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት በጉልበት የሠለጠነው አገዛዝ መክሸፍ/መጨንገፍ ዓይነተኛ መለያው የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ የአገዛዙ ደንገጡር ሆኖ እንደ ዓይን መጥፋቱ መሆኑን ደጋግሜ ለማሳሰብ ሞክሬአለሁ፡፡ ለምን ቢባል የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ለማናቸውም መንግሥት ዋና ዓምድ ነውና፡፡ ካለፉት 27 ዓመታትም በከፋ መልኩ የዳኞችና የአስተዳደር ሠራተኞች ምደባ ዘርን መሠረት ያደረገ መሆኑ፣ በተለይም የፖለቲካ/የኅሊና እስረኞችን በተመለከተ የአስፈጻሚው አካል ፍላጎት ውሳኔ እንደሚሆን፣ አገርንና ዓለምን ጉድ ባስባለ ሁናቴ በኅሊና እስረኞች ጉዳይ ከመጋረጃ ጀርባ ‹ምስክሮች መቅረባቸው፣ፍ/ቤት የለቀቃቸውን የኅሊና እስረኞች ፖሊስ አሻፈረኝ አልለቅም ብሎ ለሕግ ልዕልና ማሳያ የሆነውን የፍ/ቤቶች ክብር ደጋግሞ መዳፈሩ፣ የወኅኒ ቤት (በአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ማረሚያ ቤቶች የሉም) አስተዳዳሪዎች የፍ/ቤቶች ትእዛዞችን በማቃለል በኅሊና እስረኞች ላይ የሚፈጽሟቸው ሕገ ወጥ ድርጊቶች ሃይ ባይ ማጣታቸው ፣ በወንጀል ጉዳይ ተጠርጥረው በሕግ ቊጥጥር ሥር የሚገኙ ዜጎች በሕግ በተቋቋመ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ካልተላለፈባቸው በስተቀር በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግ መርህ መሠረት ወንጀለኛ ተደርጎ ያለመቈጠር የንጽሕና ግምት (presumption of innocence) እና የመደመጥ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው በይፋ ተጥሶ/ተነፍጎ በፍርድ ቤት መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም የፖለቲካ ውሳኔ የሚሰጥበት ተጠያቂነት የሌለበት አሠራርና ሥርዓተ አልበኝነት መንገሡ፣ በተረኝነት ምደባ የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሆነው ሹመኛ ዜጎችን በእኩልነት የሚመለከት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሳይሆን የገዢው ፓርቲ አባል እና ዓላማ አስፈጻሚ ከመሆንም አልፎ ለምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበበት ሁናቴ (በዚህም ለእውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና አገዛዙ ‹ጦርነት እንከፍታለን› ብሎ የዛተባቸውና የፖለቲካ አደጋ ናቸው ብሎ ወኅኒ ቤት የወረወራቸውን እስረኞች ጉዳይ በምን መልኩ እንደሚያስተናግደው ግልጽ መሆኑ) ወዘተ. የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ በጻዕረ ሞት ላይ የሚገኝ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህም ዜጎች በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ያላቸው እምነት እንዲሟጠጥ እያደረገ ነው፡፡ 

በቡሃ ላይ ቈረቈር እንዲሉ ፋሺስታዊው የዐቢይ አገዛዝ በቅርቡ በጀሌው በሽመልስ በኩል የኦሮሙማ ተልእኮው ማስፈጸሚያ አድርጎ አንድ አፓርታይዳዊ ‹ሕግ› ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ይሄ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን በመታወቂያቸው ላይ በለጠፈው የዘር ማንነት አማካይነት ልዩነት የሚያደርግና በራሳቸው ‹ሕገ መንግሥት› የኢትዮጵያ ርእሰ ከተማ አዲስ አበባ መሆኑ በግልጽ ተመልክቶ እያለ የከተማዋን ስም ኢ-ሕገመንግሥታዊ በሆነ መልኩ ‹ፊንፊኔ› በማለት የሚጠራውን እና ‹‹የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ሥልጣን እና ተግባር እንደገና ለመወሰን የወጣውን ዓዋጅ ቁጥር 216/2011ን›› መሠረት አድርጎ እንደተደራጀ የተነገረው የጐሣ ፍርድ ቤት በይፋ ሥራ መጀመሩ ተነግሯል፡፡ በመሠረቱ ይህ የተጠቀሰው ሕግ በአዲስ አበባ ከተማ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የ‹ጐሣ ፍርድ ቤት› እንዲያቋቁም ሥልጣን አይሰጥም፡፡ ቢሰጥም እንኳ እነሱ ‹ሕገ መንግሥታችን› ከሚሉት ሰነድ ጋር በግልጽ ስለሚቃረን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ይሆናል፡፡

አረመኔው ዐቢይንና አገዛዙን በጥቅምም ይሁን፣ በእምነት ሰበብም ይሁን በኅሊና ቢስነት የሙጥኝ ያሉት ደጋፊዎች በሥልጣን ፍትወት ዐቅሉን ከሳተው ሰው እና ከአገዛዙ ምን ተአምር እንደሚጠብቁ ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ከ‹ሰውየው› ጋር አብረው ለማበድና እስከ መጨረሻው ለመደንቆር የወሰኑ ይመስላል፡፡ በውኑ ኢትዮጵያ ለነዚህ ጉዶች አገራቸው ናት? በዘረኝነትና በተረኝነት ሕይወቱን እያጣ፣ ቤት ንብረቱን እየተዘረፈና በገፍ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ የፈሰሰው ሕዝብ እንደ ወገናቸው ያዩት ይሆን? አይመስለኝም፡፡ ይህን ለማስተዋል ቅን ልቡና እና በጎ ኅሊናን ይጠይቃል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ አነሰም በዛም የራሷ ፍርድ ቤቶች እና ሌሎችም በሕግ የዳኝነት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት እያሏት (የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ዓዋጅ ቊ.311/1995 አናቅጽ 39-50)፣ ነዋሪዎቿም የዘር ማንነታቸው ግምት ውስጥ ሳይገባ የሚዳኙበት ሥርዓት እያለ፣ በወያኔ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› አንቀጽ 49/1 እና የአዲስ አበባ ቻርተር አናቅጽ 3፣ 4 እና 6 የፌዴራሉ መንግሥት ርእሰ ከተማ መሆኗ፣ የከተማውም ስያሜ አዲስ አበባ መሆኑ እና አማርኛ የከተማው የሥራ ቋንቋ መሆኑ በሕግ ተደንግጎ እያለ፣ አማርኛ ቋንቋ መናገርና መረዳት ለማይችል ሰው ፍርድ ቤቶቹ (በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው) አስተርጓሚ አቅርበው እያሰተናገዱ እያለ የትኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይም ዜጋ ጥያቄ አቅርቦ ነው ይህ አፓርታይዳዊ የዳኝነት ሥርዓት ሊፈጠር የቻለው? በመሠረቱ የትኛውም አዲስ አበቤ በዘር/ጐሣ ማንነቱን እንደማይገልጽ እየታወቀ ማኅበረሰቡን ለመከፋፈል በማለም ይህን የጥላቻ ግንብ በከተማዋ ለማቆም ለምን ተፈለገ? ወይስ ኦሮሙማ አዲስ አበባን ከመሰልቀጥ ዓላማዎቹ መካከል አንድ መገለጫው መሆኑ ነው? የኋለኛው አገላለጽ ከግምትም ባለፈ ውኃ ያነሣል፡፡ 

ለማጠቃለል ወያኔ ኦሮሚያ በሚል ባደራጀው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ባሉ ‹ወጠጤ አስተዳዳሪዎች› ማንአለብኝነት፣ ተረኝነትና የኦሮሙማ ፕሮጀክት አስፈጻሚነት ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የተቋቋመው የ‹ጐሣ› ፍርድ ቤት እነሱ በተቀበሉትና እንሞትለታለን በሚሉት የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥትም› ሆነ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሠረት ኢ-ሕገመንግሥታዊ እና ሕገ ወጥ አደረጃጀት በመሆኑ ባስቸኳይ ሊፈርስ ይገባል፡፡ ለዚህም ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ በፍርድ ቤት ሞግቶ ለአገዛዙ ፍርድ ቤቶች ባልተለመደ መልኩ በእስር የሚገኙ የአመራር አባላቱ በእጩ ተመራጭነት ለመወዳደር እንዲመዘገቡ እንዳደረገ ሁሉ፣ በዚህም ጉዳይ ለአዲስ አበባና ነዋሪዎቹ መብት ቆመናል የምንል ሁሉ፤ ባልደራስም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት መዝቀጥ እና የሕግ የበላይነት መርህ የዴሞክራሲ ሥርዓት ምሰሶ መሆኑ የሚያሳስባቸው የፖለቲካ ተቃዋሚ ማኅበራት (ውጤቱ የትኛውም ይሁን) የ‹ጐሣ› ፍርድ ቤቱን ኢ-ሕገመንግሥታዊነት (የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› አንቀጽ 78/1) እንደ ሁናቴው በፍርድ ቤት ወይም የወያኔ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› በሚፈቅደው ሥርዓት ሊሞግቱት ይገባል፡፡

Filed in: Amharic