>

የቀንዱ ፖለቲካ እና ኢትዮጵያ...!!!  (የሺሃሳብ አበራ)

የቀንዱ ፖለቲካ እና ኢትዮጵያ…!!!

 የሺሃሳብ አበራ

በሱዳን በሰሜኑ እና በደቡብ አካባቢ የነበረው ሽኩቻ በ2003 ዓ.ም ሀገሪቱን ከሁለት ከፍሏታል:: ደቡብ ሱዳን ከካርቱም ተለይታ ነፃነት እና ልማትን አረጋግጣለሁ ብላ አልማ ነበር:: ነገር ግን በደቡብ ሱዳን ያለው ጎሰኝነት ዋና እና ምክትል ፕሬዝዳንቶችን አላስማማ ብሎ ጦር እንደተማዘዙ ቀጥለዋል::
ደቡብ ሱዳን ከሰሜኑ ስትነጠል 75 ከመቶውን የነዳጅ ዘይት ይዛ ሄደች:: የካርቱም ኢኮኖሚ የፀናዉ በነዳጅ ሀብት ነበር:: ታዲያ ደቡብ ሱዳን ነዳጇን ይዛ ስትገነጠል ካርቱም በምጣኔ ሀብት እድገቷ ቁልቁል ሄደች::
ለ30 ዓመታት በፕሬዝዳትነት ለቆዩት ለኦማር አልበሽር በዳቦ አብዮት መነሳት መንስኤውም ይሄው ጉዳይ ነው:: እናም አልበሽር በዚህ ሁኔታ ከስልጣናቸው ሲፈነገሉ የካርቱም ፖለቲካ በወታደሩ እጅ ገባ:: ያም ሆኖ በዳርፉር ዓረብ እና ዓረብ ባልሆኑ ብሔሮች መካከል ያለው ግጭት ሱዳንን ክፉኛ ፈትኗታል:: የዳርፉር ጉዳይ ዛሬም መላ አልተበጀለትም::
የሱዳን የሽግግር መንግሥት የአልበሽርን መንገድ ላለመከተል ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ከፍሎ ታረቀ:: ሱዳን ከአሜሪካ ጋር ለመታረቅ እና ከሽብርተኝነት ክስ ነጻ ለመሆን 335 ሚሊየን ዶላር ከፍላለች:: ክፍያው የተፈረመው በ1990  ዓ.ም  በኬኒያ እና በታንዛኒያ የአሜሪካ ኤምባሲ በኩል  በአልቃይዳ በተፈጸመው ግድያ ምክንያት ነው:: በወቅቱ አሜሪካ ከአልቃይዳ ጀርባ ሱዳን አለች ብላ ሱዳንን በሽብርተኛነት ፈርጃ እንደነበር አልጀዚራ በዘገባዉ አስታውሷል:: ሱዳን በ2013 ዓ.ም ክፍያ የፈጸመዉ በሽብር ጥቃቱ ህይወታቸዉ ላለፈ አሜሪካውያን የኤምባሲ ሰራተኞች ነው:: ክፍያዉ ሲፈጸም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “አሜሪካ የሽግግር መንግሥቱን ትደግፋለች:: ግንኙነቱም አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነው” ብለውት ነበር::  ከሽብርተኝነት ደጋፊ ሀገር ሱዳን ስሟ ሲሰረዝ፤ ዲፕሎማሲዋ አንጻራዊ መሻሻል አግኝቷል::  ሱዳን ከእስራኤል ጋርም  በጐ ግንኙነት ስትመሠርት፣ የመካከለኛዉ ምስራቅ ሸምጋይ የሆነችው ግብጽም ከሱዳን ጋር ግንኙነቷን አጠናከረች::
ግብጽ እና ሱዳንም የጋራ የጦር ልምምዳቸውን በሱዳን እያደረጉ ነው:: ግብጽ የፍልስጤም እስራኤልን ጦርነት በመሸምገል የመካከለኛዉ ምስራቅ ተጽእኖ ፈጣሪ ስትሆን፣ በሰሜን አፍሪካ ላይ ደግሞ የሊቢያን ፖለቲካ ለማርጋት በጐ እይታ ከአሜሪካ አግኝታለች:: ከአፍሪካ ሀገራት ጅቡቲን ጨምሮ ግብጽ በዓረብ ሊግ በኩል ጥቅሟን ለማስጠበቅ ትሠራለች:: ከጥር እስከ ዛሬ በአምስት ወራት ጊዜ ብቻ ከአራት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር የጦር ስምምነት አድርጋለች:: ቡሩንዲ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳን እና ኬኒያ ከግብጽ ጋር የጦር ስምምነት ያደረጉ ሀገራት ናቸው:: ስምምነቱ፣ የጋራ የደህንነት እና የመረጃ ልውውጥ፣ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ብሎም መደጋገፍን ያካተተ ነው::
በሌላ በኩል በሶማሊያ የሞቃዲሾ የወጣቱ ክንፍ ጦር (አልሸባብ) ፈተና ሆኗል:: በሶማሊያ ከሞቃዲሾ ፖለቲካ ተገንጣይ የሆነችው ሶማሌላንድ ሀገር ለመሆን እያኮበኮበች ነው:: ሞቃዲሾ ከኬኒያ ጋር መልካም ግንኙት የላትም:: ኬኒያ ወደ ሶማሊያ የአየር በረራዋን አቁማለች:: ሶማሊያ እና ኬኒያ በህንድ ውቅያኖስ በሚጋሩት የባሕር ወደብ ላይ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል:: አሜሪካ በመጪዉ ሃምሌ ጀምራ ከኬኒያ ጋር በቀንዱ ሽብርተኝነትን ለማጥፋት በሚል የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ ስምምነት ፈጥራለች:: ስምምነቱ አሜሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ኬኒያን የቀንዱ ተመራጭ ሀገር ለማድረጓ አንድ ተግባራዊ አብነትም ሆኗል:: ኔሽን አፍሪካ እንደተነተነው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የሽብርተኝነት በተለይም የአልሸባብን እንቅስቃሴ ለመመከት አሜሪካ የምድር ጦሯን ከኬኒያ ወታደር ጋር ቀላቅላለች:: በአንጻሩ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የጸጥታ ዘርፍ ድጋፍ ማቋረጧን  ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች::
ከሁሉም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በጐ ግንኙነት ያልነበራት ኤርትራ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት መስርታለች:: ነገር ግን በህወሓት እና በማዕከላዊዉ መንግሥት መካከል በተደረገው ጦርነት የኤርትራ ሰራዊት የሰባዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል በሚል አሜሪካ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ ጥላለች:: በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ላይም የጉዞ እና የኢኮኖሚ እገዳ ተጥሏል::
ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ባለመርጋት  ባለው የቀንዱ ፖለቲካ ተጨማሪ ቀውስ ወይስ መፍትሄ ነው የሚለው አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል:: ከዚህ ቀደም አሜሪካ እና  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀንዱን ፖለቲካ ለማርጋት በሶማሊያ እና በሱዳን ሰላም አስከባሪ ሃይል አሰማርተው ነበር:: ከተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ሃይል ጋር የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ተሰማርቶ ከባይደዋ- ሶማሊያ እስከ  ዳርፉር ሱዳን ሰላም የማስከበር ሚናውን ተወጥቷል:: ይህም አሜሪካ ለምሥራቅ አፍሪካ መረጋጋት በስትራቴጂክ አጋርነት ኢትዮጵያን እንድትይዝ አድርጎ ነበር::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በውስጧ በተፈጠረ አለመረጋጋት ጅምላ ግድያ እና መፈናቀል በዝቶ ተስተውሏል:: በተለይም አማራ ከኦሮሚያ  እና ከቢኒሻንጉል ክልሎች በገፍ ሲፈናቀል እና ሲገደል  ባጅቷል::
የሀገሪቱን  መንግሥት እየመራ ያለው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከግንቦት 19 እስከ 20 ቀን 2013 ባደረገው ጉባኤ የቀይ ባህር የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ገልጾ፣ የትኛውም ተጽእኖ ግን የኢትጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር አይሆንም ብሏል::
ማዕቀቡ እና ኢትዮጵያ
“ድምጻችን ለነጻነታችን እና ሉዓላዊነታችን” በሚል  አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ኢትዮጵያውያን ተቃውመዋል:: የቅዋሜ ሰልፉ ከሀገሪቱ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባ እስከ አሜሪካ እና አውሮፓ ያካለለ ነበር:: በአዲስ አበባ  ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ሰልፍ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ በጋራ ቁመን  ከውጭ ጣልቃገብነት እንጠብቃለን የሚሉ ድምጾች ተስተጋብተዋል:: በሌላ በኩል በሰልፉ የሩሲያው ፕሬዝዳንት የቭላዲሚር ፑቲን እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ዥ ፒንግ ምስል ጎልቶ ታይቷል:: የእነ ፕሬዝዳንት ፑቲን ምስል በሰልፉ ጎልቶ መታየቱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አጀንዳ ሲያደርጉት ተስተውሏል:: የአጀንዳነቱ ጭብጠ ሀሳብም የዓለም አቀፍ የሃይል አሰላለፍ ሁኔታውን ማዕከል ያደረገ ነበር::
በዓለም ላይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዓለም በሁለት የሀሳብ ጠርዞች ቁማ ታይታለች:: ጉዳዩ ከሀሳባዊ ልዩነት አልፎ ቀዝቃዛው ጦርነት እየተባለ ይጠራል:: የካፒታሊዝም ቡድኑ ምዕራባውያንን (አውሮፓውያንን) አካሎ በአሜሪካ ሲመራ፣ የሶሻሊዝም ቡድኑ ደግሞ ምስራቃዊ ክንፉ  በታላቋ ሶቬት ህብረት ወይም በሩሲያ ሲመራ ቆይቷል:: በ1970ዎቹ መጨረሻ እና በ1980ዎቹ መግቢያ የሶሻሊዝሙ ቡድን በካፒታሊዝሙ እየተሸነፈ አሜሪካ ፍጹማዊ የዓለም ልዕለ ሃያል ሆነች:: አሜሪካ ምንም እንኳን የዓለም ቁንጮ ሆና ብትቀጥልም ሩሲያ፣ ቻይና፣ ኢራን፣ ሰሜን ኮርያ፣ ኩባ ወዘተ መሰል ሀገራት ዛሬም ድረስ ከአሜሪካ በተቃራኒ ቁመው የራሳቸውን ዓለም ለመፍጠር ይተጋሉ:: ከዚህ ፍሬ ነገር ተነስተን ስንተነትን፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ወይም ከምዕራባውያን ይልቅ ምስራቃውያኑን እነ ሩሲያን በአጋርነት ለማቀፍ ፈልገዋል የሚል አድምታ ሰልፉ ይኖረዋል::  ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ብሄራዊ ጥቅሜ እስከተከበረ ድረስ የወዳጅነት ምርጫ አልገባም:: ወደነሩሲያ  አሰላለፍ ለመሄድ የተለየ ዝንባሌም የለኝም ብሏል::
በታሪክ ውስጥ፣ በ1970ዎቹ መጀመሪያ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት የኩባ ጦር ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፏል:: ከጦርነቱ ማግስት ደርግ ግንኙነቱን ከወደ ምሥራቁ ሲያደርግ ሩሲያ የኢትዮጵያ አጋር ስትሆን፣ አሜሪካ በተቃራኒ ጎራ ተሰልፋለች:: ለዚህም ይመስላል አሜሪካ ደርግን ጥሎ ዙፋኑን ለተረከበው ኢህአዴግ ቀና ምልከታ የነበራት::
44ኛው የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ባራክ ኦባማ በ2007 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር:: በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ነው ማለታቸው በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር:: ኢህአዴግ ከ99 እስከ 100 ከመቶ የምክር ቤት ወንበር ይዞ በብቸኝነት በተቆጣጠረበት ወቅት ኢህአዴግን ዴሞክራሲያዊ ነው መባሉ በወቅቱ ግርምትን ፈጥሮ አልፏል:: በወቅቱ አሜሪካ በዓባይ ግድብ ዙሪያ በግብጽ እና በኢትዮጵያ ባለው ድርድር አንጻራዊ  ገለልተኛ አቋም ይዛ ነበር::  የሪፐብሊካኑ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን በቀጥታ ውግንናቸውን ከግብጽ ጋር አድርገዋል:: ያለግብጽ ፍላጎት ግድቡ ከተገደበ “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” ሲሉም ተናግረው ነበር:: ትራምፕን የተኩት ባይደን በግድቡ ዙሪያ ግልጽ አቋም አላሳዩም:: ይልቁንም በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ የትኩረት ማዕከላቸው ሆኗል:: የፖለቲካ ድርድር እንዲደረግ፣ የኤርትራ ወታደር ከትግራይ እንዲወጣ፣ የሰባዊ ድጋፎች ያለምንም መሰናከል ተደራሽ እንዲሆኑ አሜሪካ ምክረ ሀሳብ አቅርባለች:: ምክረ ሀሳቤ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ገቢራዊ አልሆነም በሚል በአማራ ክልል የጸጥታ አመራሮች እና አባላት፣ በፌዴራል ባለስልጣናት፣ በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ ወደ አሜሪካ የመግባት ፈቃድ ክልከላ ጥላለች:: ኤርትራም ሆነች ኢትዮጵያ የአሜሪካን ውሳኔ ቀጣናውን የሚጎዳ በትክከል ያልተገመገመ ውሳኔ ብለውታል::
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ጦርነቱ ቅርጽን እየቀያየረ እየተደረገ ነው የሚሉ መረጃዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ አድርጓል:: ፎክስ ኒውስ የተባለው የአሜሪካ የዜና ማሰራጫ ደግሞ አሜሪካ በአማራዉ ላይ የሚደርሰውን ጅምላ ጭፍጨፋ እና መፈናቀል ችላ ብላለች የሚል ዘገባ አስነብቧል:: የዘገባው ጭብጥ በሀገሪቱ ያለው የሰባዊ መብት ጥሰት በትግራይ ክልል ብቻ የተገደበ ሳይሆን በአማራዎች ላይም ያነጣጠረ ነው የሚል ነው::
ኢትዮጵያ ስለዲፕሎማሲዋ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃልአቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግንቦት 25 ቀን 2013 ዓም በሰጡት ሳምንታዊ ይፋዊ መግለጫ ‹‹ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻክር ፍላጎት የላትም›› ሲሉ ተናግረዋል:: የቀይ ባህር ፖለቲካ ኢኮኖሚ አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ የሀገራት ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል:: ይህም የሽኩቻ ምንጭ መሆኑን አምባሳደር ዲና ያነሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ህጎች እና ስምምነቶችን አክብራ ዲፕሎማሲዋን ከማንኛውም ሀገር ጋር ታደርጋለች ብለዋል:: ‹‹በተለየ መንገድ ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ቻይና እና ሩሲያ አዙራለች የሚለው ግን የተሳሳተ አተረጓጎም›› እንደሆነ አሳውቀዋል:: ኢትዮጵያ ፍላጎቷ ከማንኛውም ሀገር ጋር ግንኙነቷን ማጠናከር እንጂ የተለየ ምርጫ አትገባም የሚል  አንድምታ ያለው ሀሳብም አምባሳደሩ አንስተዋል:: ኢትዮጵያ ለ120 ዓመት የዘለቀውን ከአሜሪካ ጋር ያላትን ወዳጅነት የማሻከር ፍላጎት እንደሌላት ያብራራት አምባሳደር ዲና፣ ከየትኛውም ሀገር ጋር ይሁን ብሄራዊ ጥቅማችን እስካልተነካ ድረስ ግንኙነታችን መስመሩን ይዞ ይቀጥላልም ብለዋል::
 የባለሙያ ዕይታ
በሀገሪቱ ያለው መንግሥታዊ መዋቅር ሰላም እና ደህንነትን አስጠብቆ ለዜጎች ደኅንነት ዋስትና መሆን አለመቻሉ፣ በጥላቻ እና በፍረጃ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ መኖሩ እና ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ በታኝ ፖለቲካ መሰራቱ በሀገሪቱ አለመስማማትን አስፍኗል:: በሀገር ውስጥ ያለው አለመስማማት ኢትዮጵያ በቀጣናው ላይ መጫዎት የሚገባትን ሚና እየቀነሰ እና ዓለምአቀፋዊ በጎ ስሟንም እያደበዘዘው ይገኛል:: ዲፕሎማሲውን በሚችሉ ሰዎች ማስመራት፣ ለዜጎች ሰባዊ መብት መከበር ዋስትና መስጠት፣ አካታች መንግሥታዊ ውቅር መዘርጋትን በመፍትሄነት የሚያስቀምጡት ዓለምአቀፍ የህግ ባለሙያው አቶ ሄኖክ አበበ ናቸው:: አቶ ሄኖክ ለበኩር ጋዜጣ  እንደተናገሩት ውስጣዊ ፖለቲካውን በፍትሃዊ እና በሃቀኛ ተቋማት ማከም ከተቻለ ዜጎች ዋስትና ያገኛሉ:: ዲፕሎማሲውንም ከመርህ የለሽ ድንፋታ አላቆ በተሰላ እና በሰከነ መንገድ ማድረግን በመልካም አማራጭነት ያነሳሉ:: ዲፕሎማቶችን ብሄርን እና የፖለቲካ ዝንባሌን መሰረት አድርጎ  ከመመደብ ይልቅ የሀገር ተቆርቋሪነትን እና ችሎታን  በመስፈርትነት ቢያዝ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣበት የሚናገሩት የህግ ባለሙያዉ ሀገራዊ ፖለቲካዊ መሰረታዊ የሰው ልጆች መርሆችን መከተል አለበት የሚል ሀሳብም አላቸው:: እንደ አቶ ሄኖክ በሀገሪቱ ለሰባዊ መብቶች ጥበቃ ማድረግ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማስፈን እና ተቋማትን በሚችሉ ሰዎች ማስመራት ከተቻለ የውስጡም ሆነ የውጩ ፖለቲካ መታከም ይችላል::
Filed in: Amharic