>
5:13 pm - Tuesday April 19, 6912

ግብጽ እና ኢትዮጵያ በታሪክ ጐዳና...!!!   (ቢንያም መስፍን)

ግብጽ እና ኢትዮጵያ በታሪክ ጐዳና…!!!

  ቢንያም መስፍን
 ክፍል አንድ

የጥንታዊያን የሰው ልጆች ስልጣኔ እና ሰፈራን ለህይወት ወሳኝ ከሆነው ውሃ ጋር የታሪክ አጥኝዎች ያያይዙታል:: ይህም መንደሮች እና ከተሞች ይመሰረቱ የነበሩት የወንዝ ዳርን ተከትለው በመሆኑ ነው:: ለዚህም የዓለማችን ታላላቅ ስልጣኔዎችን ማንሳት እንችላለን:: ግብጽ እና ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናቸው::
ጥንታዊ ስልጣኔ አላት ተብሎ የሚነገርላት ግብጽ የቅድመ ታሪኳ እምብዛም ግልጽ ያልሆነ እና በአፈታሪኮች የተሞላ ነው ሲሉ ዮሐንስ ወ/ ማርያም ከፒተር ፓርሌ በተረጎሙት የዓለም ታሪክ መጽሐፍ ላይ ጠቅሰዋል:: በዓለም ላይ የምትታወቅባቸው ፒራሚዶች ሳይቀር ማን እንዳነጻቸው በግልጽ እንደማይታወቅ ጸሐፊ ዮሐንስ ገልጸዋል::
ግብፆች በጥንቱ ዘመን የመጀመሪያ ስማቸው ምስር እንደነበር ይነገራል። ግብጽ የሚባለው ስፍራ ከላይኛው ደጋማው ኢትዮጵያ ተነስተው የአባይን ሸለቆ ተከትለው የወረዱ ኢትዮጵያዊያን ኩሾች ያለሙት ምድር ሲሆን በደለላማዉ የአባይ ሸለቆ ላይ በዓለም ተወዳጅ የሆነችውን ምስር የተባለችውን አዝርእት ዘርተው ያጨዱበት ለም ቦታ በመሆኑ የምድሩን ስም ምስር በማለት እንደጠሩትም አለቃ ታየን ጠቅሰው ጸሐፊ ዮሐንስ ያብራራሉ:: ይህንንም ስም ያወጡላት በምድሩ ለምነትና በጥንቱ ዘመን የወንዝን ዳርቻ ተከትሎ በሚመሰረተው የስልጣኔና የከተማ ግንባታ [ቁርቆራ] የሚታወቁት ኩሽ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ::
በታላቁ አባይ ወንዝ የተሳሰሩት የሰው ዘር መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ እና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የሆነችው የግብጽ ታሪካዊ ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ለመሆኑ የተለያዩ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ::
ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ትስስር
የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ግንኙነት እንደተለያዩ የታሪክ ፀሀፍት እና ማስረጃዎች አንፃር ከክርስቶስ ልደት በፊት መጀመሩን እንገነዘባለን:: ከክርስቶስ ልደት 3000 ዓመታት በፊት በአባይ ሸለቆ /ተፋሰስ/ ውስጥ በተለያዩ የገጠር መንግስታት ይተዳደሩ የነበሩ የተለያየ እምነት፣ ባህል፣ አስተሳሰብ የነበራቸው ህዝቦች በአንድ መንግስት ጥላ ስር እንዲዋሀዱ የአባይ /የናይል/ ወንዝ አስተዋጽኦ ማድረጉን በርካታ ፀሀፍት ይስማሙበታል::
በአባይ ሸለቆ ይኖሩ የነበሩ ህዝቦች በአንድ ጠንካራ መንግስት መተዳደር ወደታችኛው የተፋሰሱ አካባቢ /የአሁኗ ግብጽ/ ጥንታዊ ስልጣኔ ወደጀመረበት ጊዜ ይወስደናል:: በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ታሪካዊ ግንኙነት የጀመረው ከ5 ሺ አመት በፊት መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ:: ኢትዮጵያውያን ከግብፃውያን ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ልዩ ጥናት ካደረጉት የታሪክ ተመራማሪዎች መካከል ሄሮዱተስ የተባለው ግሪካዊ አንዱ ነው::
ፍስሀ ያዜ “የ5 ሺ አመት የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መጽሀፍ በጥንት ጊዜ የስልጣኔ መሠረት በሆነው የናይል ተፋሰስ አንድ ጠንካራ መንግስት እንዲቋቋም በተለያዩ ጐሳዎች መካከል ጦርነት ይካሂድ ነበር:: እነዚህም ጐሳዎች “ነገደ ኩሽ” የሚባሉት ኢትዮጵያውያን ነበሩ” ሲል ሄሮዱተስን ጠቅሶ ጽፏል:: ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ለጥንታዊው የግብጽ ስልጣኔ መሰረት የጣሉ መሆናቸውን ሄሮዱተስ “ኢትዮጵያውያን የስልጣኔ እርሾን ስለሰጧቸው ግብፃውያን የኢትዮጵያውያን ውለታ አለባቸው” ብሎ መፃፉንም ጠቁሟል::
ኢትዮጵያዊው ተክለፃድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ/ናፓታ መርዌ/ አንደኛ በሚለው መጽሀፋቸው “…የታሪክ አባት የሚባለው ስመጥሩው ሄሮዱቶስ ወደ ግብጽ በመሄድ አባይን ከጐበኘ በኋላ በፃፈው የታሪክ መጽሀፍ፤ እንዲሁም ዲዮዶር የሚባለው የሮማ ፀሀፊ ከግብጽ በፊት ስልጡንና ገናና የነበረችው ኢትዮጵያ መሆኗን፣ ህዝቦቿም ደግ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ሰላማዊ፣ በጦርነት ጊዜ ደግሞ ጀግና ጐበዝ መሆናቸውን ጽፏል:: ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታ ላይ የምትገኝ በመሆኗ፣ ዓባይም ከላይ ከኢትዮጵያ ወደ ግብጽ እየፈሰሰ እንደሚያጠጣት፣ አፈርም እንደሚያቀብላት ሁሉ ስልጣኔውንም ለግብጽ መጀመሪያ የሰጠቻት ኢትዮጵያ ነበረች::
17 የኢትዮጵያ ነገስታት ግብጽን በተከታታይ ሲያሰተዳድሯት ከቆዩ በኋላ ግን ግብጽ ከኢትዮጵያ ያገኘችውን ስልጣኔ ይበልጥ አስፋፍታ እንደገና የ18ኛውና የ19ኛው ነግሰው ኢትዮጵያንም መልሰው እንደገዙ፤ ከዚያ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያኖች አይለው እንደገና ግብጽን ይዘው የ25ኛውን ስርዎ መንግስት መስርተው እንደገዙ ተጽፏል…” በማለት ይገልፃል::
አንዳንድ እንደ ፍሬድሪክ ቲቦልት ያሉ የታሪክ ፀሀፍት ደግሞ “ኩሽ ኢትዮጵያውያን” የሚለውን ጥቁር ኑብያንስ ናቸው ይላሉ:: የሆነው ሆኖ ግን እነዚህ ህዝቦች በግብጽ ጠንካራ መንግስት መስርተው ይገዙ እንደነበር ይጠቅሳሉ:: ይህንንም ያደረጉት በመተባበር የአባይ ውሀ ሙላት የሚያስከትለውን ጥፋት ለመከላከል እና ወንዙ በሚያመጣው ድቡሽት /አፈር/ እህል ለማብቀል ነበር:: በወቅቱ በወንዙ ውሀ ጥልቀት መጠንም ግብር ይከፈል ነበር::
የወንዙ ውሀ ከፍታ በጨመረ መጠን የበለጠ አፈር ስለሚያመጣ የምርት ጭማሪ ይኖራል:: የሚከፈለው የግብር መጠንም በዚያው ልክ ያድግ እንደነበር ተገልጿል:: እዚህ ላይ እኛ በዋናነት ማሳየት የፈለግነው የቀደምቱ ስልጣኔ ባለቤት ማን ነው /ይህ ሌላ ጊዜ የምናቀርበው ሆኖ/ የሚለውን አይደለም:: ይልቁንም በአባይ ወንዝ ምክንያት በአባይ ሸለቆ ይኖሩ በነበሩ ህዝቦች በተለይም በዛሬዋ ኢትዮጵያ እና ግብጽ መካከል በአባይ ወንዝ ምክንያት ከክርስቶስ ልደት በፊት ስለነበረው ግንኙነት ለማመልከት እንጂ::
ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበረው ግንኙነት
ግብፆች ከጥንት ጀምሮ አባይን ከነደለሉ በላይኛ የተፋሰሱ ክፍል ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ፈጣሪ ስለለገሳቸው የአበሾችን እንቅስቃሴ እና እርምጃ ከዘመን ወደ ዘመን በጥንቃቄ ሲከታተሉት ቆይተዋል:: በአክሱማውያን ዘመነ መንግስት /100-800 ዓ.ም/ የነበሩ ዶክመንቶች ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል ግንኙነት መቼ እንደተጀመረ ያመላክታሉ:: በእነዚህ መረጃዎች መሰረትም በሁለቱ አገራት መካከል ተቋማዊ ግንኙነት የጀመረው የአክሱም ንጉስ ኢዛና በ330 ዓ.ም የክርስትና ሀይማኖትን መቀበሉን ተከትሎ ነበር::
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሀይማኖት ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ጳጳሳት በኢትዮጵያ ይሾሙ የነበሩት በግብፁ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ሀይማኖት /ግብጽ በወቅቱ የክርስትና እምነት ተከታይ ነበረች/ ፓትርያርክ አማካይነት ግብፃውያን ነበሩ:: ለ1600 አመታት ያህልም በኢትዮጵያ ግብፃውያን ጳጳሳት ነበሩ ቤተክርስትያኗን ይመሩ የነበሩት::
ጳጳሳቱ በኢትዮጵያ ይሾሙባቸው በነበሩ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ከስተጀርባ የግብጽ ነገስታት ተጽእኖ ነበር:: ይህም ማለት በወቅቱ ይሾሙ የነበሩት ጳጳሳት ታዲያ ከሀይማኖታዊ ባሻገር ፖለቲካዊ እና የአገራቸውን ተልእኮ ይዘው በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ እንደነበሩ ብሎግ አፍሪካ ዶት ኦል አፍሪካን ዶት ኮም በተባለው ድረ ገጽ አንድሪው ካርልሰን የተባለው ፀሀፊ አስፍሮታል::
ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበረው ትስስር
ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዚህ መልኩ የተጀመረው የግብጽ እና የኢትዮጵያ የግንኙነት ታሪክ ሰላማዊም በሽኩቻ የታጀበም ነበር:: በሁለቱ አገራት መካከል ለነበረው የሽኩቻ እና ግጭት ዋና ምክንያቶች ደግሞ በሀይማኖታዊ እና በአባይ ወንዝ ጉዳዮች የሚያጠነጥኑ ናቸው:: እ.ኤ.አ በ640 ግብጽ በወቅቱ የእስልምና ሀይማኖትን በሚያስፋፉ ሀይሎች ስር ወደቀች:: አብዛኛው የአገሪቱ ህዝብ እና መንግስትም እስልምናን ተቀበሉ:: በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ አሌክሳንደርያ ውስጥ ከምትገኘው የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ጋር ያላትን ግንኙነት ቀጠለች::
በማንኛውም በቤተክርስትያኗ እና አማኞቿ ላይ የሚደርሰውን ተጽእኖ በመቃወምም ለቤተክርስትያኗ ያላትን ወገንተኝነት ታንፀባርቅ ነበር:: ከዚህ ባሻገር ደግሞ ከግብጽ ተሹመው የሚመጡ ጳጳሳትን በጥርጣሬ መመልከት ጀመረች:: በእርግጥ ግብጽ እስልምናን የተቀበለች አገር ሆና እያለ ወደ ኢትዮጵያ የክርስትያን ጳጳሳትን እንዲላኩ መፍቀዷ ከሀይማኖት በላይ የሆነ ተልእኮ እንዳላት የሚያመላክት እንደነበር አንድሪው ካርልስን ገልፆታል::
እስላማዊቷ ግብጽ እየሩሳሌምን በተቆጣጠረችበት ወቅት በኢየሩሳሌም ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን የማምለኪያ እና መኖሪያ ቦታ በመቆጣጠር ኢትዮጵያውያንን አስለቀቁ:: በእነዚህ እና
መሰል የግብጽ ድርጊት የተበሳጩት የኢትዮጵያ ነገስታት የአባይን ወንዝ እንደማስፈራሪያ በመጠቀም የፖለቲካ የበላይነትን ለመያዝ በተለያዩ ጊዜያት ይሞክሩ ነበር::
“ከአስራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ክርስትያን የኢትዮጵያ ነገስታት ከግብፆች ጋር ሀይማኖታዊ ግጭት በገቡ ቁጥር የአባይን አቅጣጫ እናስቀይረዋለን እያሉ ያንገራግሩ ነበር::” ሲል ሁኔታውን በተመለከተ አንድሪው ካርልሰን ጽፏል:: “በፊትም የወንዙ መጠን በተፈጥሮ የዝናብ አጥረት ምክንያት ሲቀንስ እንኳን የኢትዮጵያውያን ተንኮል አለበት ብለው ያምኑ የነበሩት ግብፆችም ታዲያ የውሀው የተለመደ ጉዞ እንዳይሰናከል የኢትዮጵያን ነገስታት ይማፀኑ ነበር::” ሲሉ ለአባይ ውሀ ሙግት በሚለው መጽሀፋቸው ሀይሉ ወልደ ጊዮርጊስ ጽፈዋል::
አንዳንድ የታሪክ ፀሀፍትም የግብጽ ነገስታት ኢትዮጵያ የአባይ ውሀ ፍሰትን እንዳታሰናክል እና አቅጣጫውን እንዳታስቀይር የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ሀይማኖት ፓትርያርክን ገፀ በረከት በማስያዝ ለምልጃ ወደ ኢትዮጵያ ነገስታት ይልኩ እንደነበር ይገልፃሉ:: የአባይ ወንዝን በማስፈራሪያነት በመጠቀም በግብጽ እና በእስልምና ሀይማኖት ላይ ጫና ለማሳደር የሚያስፈራሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበሩም:: ይህን በተመለከተ አቶ ሀይሉ በመጽሀፋቸው “ከአስራ አራተኛው ምዕተ አመት አጋማሽ ጀምሮ አውሮፓውያን ክርስቲያኖች ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር የጀመሩትን ትግል ለማሳካት የዝነኛው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ፕሪስተር ጆን /በውል ማንነቱ ያልታወቀውን/ እርዳታ እና ድጋፍ መጠየቃቸውን በመካከለኛው ዘመን ላይ የተፃፈ ዜና መዋእል ያወሳል” ብለው ጽፈዋል:
ይቀጥላል
Filed in: Amharic