>
5:13 pm - Friday April 19, 8599

ሀውልታቸው በደብረብርሀን ከተማ የታነጸላቸው ዐጼ ዘርዓ ያዕቆብ ማን ናቸው...??? (ውብሸት ሙላት) 

ሀውልታቸው በደብረብርሀን ከተማ የታነጸላቸው ዐጼ ዘርዓ ያዕቆብ ማን ናቸው…???

ውብሸት ሙላት 

*… ከንጉሠ ነገሥቱ ታሪክ አንጻር በአጭር ቃል የቀረበ)
፩.  ዐጼ ዘርዓ ያዕቆብ  ማን ነው?
 
የተወለደበት ዘመን በ1391 ዓ.ም. ነው፡፡
የትውልድ ቦታው  በፈጣጋር ግዛት ውስጥ “ጥልቅ”፣ በምንጃር ሸንኮራ ውስጥ ነው።
አባቱ ዐፄ ዳዊት፣እናቱ ደግሞ እግዚእ ክብራ ናቸው፡፡
ከአባቱ እረፍት በኋላ እርሱ እስከሚነግሥ ድረስ  ወንድሞቹ ዐፄ ቴዎድሮስ 1ኛ(ለሁለት ዓመታት)፣ዐፄ ይስሐቅ (ለአስራ ሰባት ዓመታት)፣እንድርያስ (የይስሐቅ ልጅ፣ለወራት ብቻ የነገሠ)፣ሕዝብ ኛኝ (ለአራት ዓመታት)፣ ምሕርካ ናኝ እና በድል ነኝ (የሕዝብ ናኝ ልጆች ሲሆን ለአንድ ዓመት ያህል የነገሡ)  ነግሠዋል፡፡ በመሆኑም ሦስት ወንድሞቹ እና ሦስት የወንድሞቹ ልጆች ነግሠዋል፡፡
ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ የንግሥና ዘመን ከሐምሌ 1426  እስከ ጳጉሜ 3/1460  ነው፡፡ እረፍቱም ድንገተኛ (ሳይታመም) ነበር፡፡ በማግሥቱ፣ በኑዛዜያቸው መሠረት በእደ ማርያም ነገሠ፡፡  አድሱ ነጋሢ “የሞትንም እኛ፣ ያለንም እኛ “ ብለው ቀጥሎ ሥርዓተ ቀብሩ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ መቃብራቸውም ዳጋ እስጢፋኖስ ነው፡፡
ሲነግሥ ዕድሜው 35 ሲሆን ያረፈው ደግሞ በ69 ዓመቱ ነው፡፡
ሁለት የግልጽ የሚታወቁ ሚስቶች (እቴጌዎች) እና አንድ ተጨማሪ ሚስት እንደነበሩት ይታወቃል፡፡ የግራ ባልቴሐት(እቴጌ/ንግሥት) ፍሬማርያም (ዣን ኃይላ) ፣ የቀኝ ባልቲሐት ደግሞ ዕሌኒ መሐመድ (የሐድያው ገዥ የገራድ መሐመድ ልጅ) ስትሆን ዣን ዜላ በመባል ይጠራሉ፡፡ ሦስተኛዋ ሚስቱ የበእድ ማርያም እናት የነበረችው እቴጌ ጽዮን ሞገሳ ትባላለች፡፡
፪. ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብና የሴት አገረ ገዥዎች ሹመት
በንግሥና ዘመኑ፣ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን አዳዲስ ሥርዓቶችን ለአገራችን አስተዋውቋል፡፡ ተግብሯቸዋልም፡፡ ከእነዚህ ውሥጥ በቢትወደድነት የሾማቸው ወንዶች ጸያፍ ድርጊት ቢፈጽሙ፣መንግሥቱ ላይ በክፉ ቢያሴሩ (Coup d’état) እንዲጋዙ አደረጋቸው፡፡
በእዲህ ዓይነት ድርጊት የምትታመሰውን አገር ለመታደግ ንጉሡ በመላዋ ኢትዮጵያ (ከአንድ በስተቀር) ሴቶችን ብቻ ሹሟል፡፡ ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን የራሳቸው ምክትል በማድረግ  እራሳቸው በወቅቱ ለአገሪቱ አደጋ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሕግ ማውጣት፣መጽሐፍት በመድረስ ወዘተ ተግባር ላይ ተሰማርቷል፡፡
እንግዲህ ይሄ የሴቶች ብቻ አስተዳደር የተሞከረው በ15ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡  ምናልባት በዚያን ጊዜ የተጀመረው ቢቀጥል ኖሮ የወንዶች የእኩልነት ጉዳይ አሳሳቢ ይሆን ነበር፡፡  እንኳንስ በአገራችን እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የጾታ እኩልነት አጀንዳ እንደሆነ ነው፡፡
ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብን አንድም የሴቶች መብት ተሟጋችም ይሁን እንስታውያን (Feminists) ስሙን አይጠቅሱትም፡፡ እኛም፣ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብን አናስታውሰውም፡፡
እስኪ ስማቸውን እና የተሾሙት ግዛት እንጥቀስ፡፡
መድኅን ዘመዳ-የቀኝ ቢትወደድ
ብርሃን ዘመዳ-ግራ ቢትወደድ (ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንደማለት ነው፡፡ መድኅን ዘመዳም ብርሃን ዘመዳም ምክትሎቹ ነበሩ።)
ድል ሠምራ-ትግራይ
ባሕር መንገሣ-አንጎት
ሶፍያ-ግድም
አመተ ጊዮርጊስ-ይፋት
ሮም ገነዬላ-ሸዋ
መድኅን ዘመዳ-ዳሞት (በተጨማሪነት)
ፀበለ ማርያም-ቤገምድር
አጽናፍ ሰገዱ-ገኝ (ምድረ ገኝ)
አጽናፍ ሠምራ-ጎጃም
እና ሌሎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉም ሴቶች ናቸው፡፡
፫. ሥርዓት የማቆም ጥረቱና ውጤቱ (በጣም በጥቂቱ ብቻ)
ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብን ያህል ሥርዓት የዘረጋ ተቋማት የፈጠረ መሪ በኢትዮጵያ ያለ አይመስለኝም፡፡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕግጋትም አውጥቷል፡፡ ለወዲያው ሥርዓት መዘርጋት፣ተቋም መፍጠር እና ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን እንዳንዶቹ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዘለቁ የተወሰኑት ደግሞ አሁንም በተግባር ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ስለሆነም፣ማንም ሳይዘምርለት ውርሱ ቀጥሏል፤  ሳይጮኽለት ሥራው ግን አለ፡፡
እነዚህ  ሥርዓታት፣ተቋማት እና ሕግጋት መንፈሳዊና ሥጋዊ ይዘት አላቸው፡፡ በዚያን ዘመን የነበረው የአገር አስተዳደር ዘይቤ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ተጣምረው የሚተዳደሩበት (Theocratic) እንደነበር ያስታውሷል፡፡
ሕግጋት  –  ፍትሐ ነገሥት
በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ከውጭ በማስመጣት ኢትዮጵያዊ እንዲሆን የተደረገው ትልቁ የሕግ  መጽሐፍ “ፍትሐ ነገሥት” ነው፡፡ መንፈሳዊም ሥጋዊም ክፍሎች አሉት፡፡ ሥጋዊው ደግሞ የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ክፍሎች ይዟል፡፡ ሥጋዊ ክፍሉ፣እስከ 1950ዎቹ መጀመሪያ ድረስ በተወሰኑ የአገሪቱ ክፍል ተፈጻሚነት ነበረው፡፡ መንፈሳዊው፣ አሁንም ቢሆን አገልግሎት ላይ ነው፡፡
ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ለሕጋዊ ሥርዓት ትኩረት ይሠጥ እንደነበር መጀመሪያ አካባቢ ላይ ከደቂቀ እስጢፋኖስ ጋር የነበረው ግንኙት አስረጂ ነው፡፡ አባ እስጢፋኖስ ገድል ላይ መረዳት እንደሚቻለው፣ እስጢፋኖስ ብዙ ጊዜ የገዳማቱን ሕግጋት አይከተሉም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከትግራይ አካባቢ ተሰደው ጎጃም እና ጎንደር በነበሩ ገዳማት ይኖሩ ነበር፡፡ ኋላም፣ ቀድሞ የነበሩበት በትግራይ ውስጥ የሚገኝ ገዳም አበምኔት ጠርተዋቸው ከተመለሱ በኋላ አበምኔቱ ቃላቸውን አጥፈው አሰቃይዋቸው፤ይባስ ብሎም ከንጉሡ ዘንድ ከሰሷቸው፡፡
ከንጉሡ ዘንድ ሲቀርቡ ይፈርዱባቸው ዘንድ ወደ ሊቃውንቱ (ግብጻውያንና እስራኤላውያንም ጭምር) ላካቸው፡፡ ዳኞቹም (የውጮቹም ጭምር) የሞት ፍርድ ፈረዱባቸው፡፡ ንጉሡ ግን ወደ ዕድሜ ልክ ግዞት(እስራት) ቀየረላቸው፡፡ (ቀሪውን በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)
ሥርዓተ መንግሥት
ሥርዓተ መንግሥት ከአክሱም ዘመን ጀምሮ ንግሥና የሚፈጸምበትን ሥርዓት የሚደነግግ እና ኋላም የንጉሡን ተግባር የሚነግር ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ከእሱ በፊት የነበሩት ነገሥታት ትተው ስለነበር፣አክሱም ጽዮን በመሄድ ሥርዓተ ንግሥ ማድረግ ስለቀረ ከአንደገና አጠናክሮ ደንግጎታል፡፡ ራሱን አክሱም በመሄድ ከእንደገና አስቀጥሎታል፡፡
እዚህ ላይ አንድ የሚገርም ነገርን መግለጽ ግድ ነው፡፡ በጥንታዊት ኢትዮጵያ ንጉሥ የሚሆነው ሰው ቀድሞ የንጉሥነት ትምህርት የሚማር መሆኑን ነው፡፡ ልጅ ኢያሱ እንኳን ለተወሰኑ ጊዜያት ቢሆንም አንኮበር ላይ መማሩን ያስታውሷል፡፡ ወህኒ አምባዎች የንጉሥነት ማስተማሪያዎችም ነበሩ፡፡ የዘርዓ ያዕቆብንና የበእደ ማርያምን ዜና መዋዕሎች የጻፈው ሰውም እነ ልብነ ድግልን ለማስተማር እንደሄደ መግለጹ ይሔንኑ ሲያጠይቅ ነው፡፡
መንፈሳዊ ሕግጋትና – ሥርዓታት
 
የመስቀል አከባበር
አባቱ ዐፄ ዳዊት ከግብጽ ንጉሥ  መሥከረም 10 ቀን ተረክቦ በእዚያው በአስዋን በዓል ካደረግ በኋላ ይዞ እየመጣ ሳለ ስናር ላይ ጥቅምት 9 ቀን ስላረፈ መስቀሉም በዚያው ቦታ ቀረ፡፡ ከዚያም ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከ46 ዓመታት በኋላ በ1443 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት፣በ1446 ደግሞ ግሼን በመወሰድ አስቀመጠው፡፡ መሥቀሉ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ፣ ከዚያ በፊት የት እንደነበር ፣ ግሼን ላይ ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሥር በምን ሁኔታ እንደተቀመጠ፣የመስቀል በዓል እንዴት መከበር እንዳለበት፣የግሼንን (የቤተ ክርስቲያኗንም የነገሥታቱንም ልጆች አኗኗር) መተዳደሪያ ደንብ ሁሉ ሠራ፡፡ ይሄንንም “መጽሐፈ ጤፉት” የተባለው ላይ ይገኛል፡፡ እሱ የሠራው ሥርዓት የመስቀል አከባበር  በ’ዮኔስኮ’ ተመዝግቧል፡፡ የመስቀል በዓልም በግሼን አሁንም ይከበራል፡፡ ስለመስቀሉ አመጣጥም አቀማመጥም ንጉሡ “መጽሐፈ ጤፉት” የሚባልን መጽሐፍን ደርሶልናል፡፡
ሥርዓተ ጥምቀት
ጥምቀት ከዘርዓ ያእቆብ ዘመን በፊትም ይከናወን የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ”ተዐቅቦ ምሥጢር” ከተባለውና ከሌሎች ድርሰቶቹ ላይ መረዳት እንደሚቻለው በተለይ የከተራ ሥርዓቱ በእሱ ጊዜ ሥርዓት ተበጅቶለታል፡፡ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
የቅዳሜ እና የእሑድ ሰንበትነት እንዲሁም 33ቱ የማርያም በዓላት፤
ከዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ንግሥና በፊት፣ቅዳሜ፣ በቤተ ክርስቲያኗ ዘንድ አትከበርም ነበር፡፡ በእርግጥ ደቂ እስጢፋኖሶቹ እና እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ [የሐይቁ ዐቃቤ ሠዓት ሠረቀ ብርሃን በ1403(4?) ካረፉ በኋላ] ዘንድ ሁለቱም ሰንበቶች ይከበሩ ነበር፡፡
 በኤውስጣጤዎሳዊያንና በደብረ ሊባኖሳውያን (ቤተ ተክለ ሃይማኖታውያን) ዘንድ ግን አይከበሩም ነበር፡፡ ንጉሡ ደብረ ምጥማቅ ላይ (ተጉለት ጻድቃኔ ማርያም ?)ጉባኤ በማከናወን ከመቶ ዓመታት በላይ የቆየውን ክፍፍል አስቀርተው ኤውስጣጤዎሳውያኑንም ደብረ ሊባኖሳዉያኑንም አስማምቶ፣ነገር ግን በተጨማሪነት ሁለቱ ሰንበታት እንዲከበሩ አድርጓል፡፡
በመቀጠልም፣ወቅቱ በሰይጣን፣በድኖ፣በደስክ ወዘተ የሚያመልኩትን የአገሪቱ ሕዝብ በሰፊው ወደ ክርስትና የማዞር ዘመቻ ስለነበር በእነዚህ በሁለቱ ሰንበታት ማንኛውም ክርስቲያን በእነዚህ ቀናት በአቅራቢያው ወደሚገኝ ቤተ ክርሥቲያን እንዲሄድ እና እንዲማር ፣ቤተ ክርሥቲያን በሌለበት አካባቢ ደግሞ የነፍስ አባቶች አርብ ማታ ጀምረው ወደ እነዚህ ቦታዎች በመሄድ ሁለቱንም ቀናት የነፍስ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ ለየአገረ ገዥዎቹ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ ይሄን የተላለፈ(ሳይፈጽም የቀረ) ቄስም መሬቱ እንዲወረስ አውጇል፡፡
ይሕ እንግዲህ አዲስ ክርሥቲያን የሆኑት ወደ ቀድሞ እምነታቸው እንዳይመለሱ የተበጀ ሥርዓት ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩት ግብጻውያን ጳጳሳትም (አባ ገብርኤልና አባ ሚካኤል) በግብጽ ባይኖርም፣ቀድመው የተቃወሙት ቢሆንም፣ ተቀብለው አጽድቀውታል፡፡ ተዓምረ ማርያምንም በማስጻፍ በየቤተክርስቲያኑ  እንዲነበብ አድርጓል፡፡ በየቤተክርስቲያኑም አነስተኛ ቤተ መጽሐፍ እንዲኖር ወስኗል፡፡
 ብዙዎቹ እነዚህ ሥርዓቶች አሁንም በቤተ ክርስቲያን የሚተገበሩ ናቸው፡፡ ቁርባን እንዴት መወሰድ እንዳለበትም ያኔ ነው ከነ ቅጣቱ የተደነገገው፡፡ በአገር ውስጥ የሚያወጣቸውን እንዲህ ዓይነት ደንቦች ኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ምዕመናንም  ጭምር ተልከዋል፡፡
፬. ደራሲው ንጉሠ ነገሥት
ንጉሠ ነገሥቱ በወቅቱ አገሪቱ ላይ ተጋርጠው የነበሩትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ ድርሰቶችን ጽፏል፡፡ መንፈሳዊም ሥጋዊም ይዘት የነበራውን ሕግጋት ደንግጓል፡፡ መጽሐፍትን አስተርጉሟል፡፡ አስጽፏልም፡፡ ራሱ ደግሞ (በትንሹ) ሰባት መጽሐፍት ከነገሠ በኋላ ደርሷል፡፡
ንጉሡ ደርሷቸዋል ማለት እራሱ ብራና ዳምጦ፣መንጎል ቀርጦ፣ቀለም በጥብጦ በእጁ ጻፈ ማለት አይደለም፡፡ ይሔንን የሚሠሩት ሌሎች ናቸው፡፡ ደራሲው ሐሳቡን ይነግራል፤ሌሎች ይጽፋሉ፡፡ ይሄ ሌሎች ጸሐፍትም የሚያደርጉት ነው፡፡ ሌላው በቀድሞ ዘመን አንድ ሰው ጽሑፍ ሲያዘጋጅ ‘’እኔ’’ እያለ መጻፍ ወይም በአንደኛ መደብ መተረክ አልተለመደም፡፡ እንኳንስ ‘’እኔ’’ እያለ ሊጽፍ ቀርቶ ስሙን እንኳን አያስቀምጥም፡፡ በተለይ በሦስተኛ መደብ መተረክ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በአውሮፓውያንም ዘንድ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ቀድሞ አልተለመድም፡፡ ስሆነም፣የንጉሡን ድርሰት ለሚያነብ ሰው በሦስተኛ መደብ ሲተረክ ቢያገኝ ሌላ ሰው ነው የጻፈው አያሰኝም፡፡ የአተራረክ ልማድ ነው፡፡
የደረሳቸው ሰባት የመጽሐፍት ዝርዝርና ትኩረታቸው  እንደሚከተለው ነው፡፡
መጽሐፈ ሚላድ
“ሚላድ” በዋድላዊው እና በዋሸራዊው የግሥ ርባታ ሂደት “ክምችት፣ስብስብ”  ማለት እንደሆነ ይህንን መጽሐፍ የተረጎሙት  መልዐከ ሰላም ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ እና ሊቀ ጉባኤ ቀሲስ ታረቀኝ ደምሴ ይናገራሉ፡፡ (“አለደ” ከሚለው የግእዝ ዐቢይ አንቀጽ  የወጣ ነው። አለደ- ሰበሰበ፣ከመረ፣አከማቸ ማለት ነው።)
ቀድሞ በኢትዮጵያ በሰፊው ተንሰራፍቶ ከነበረው የአይሁድ እምነት በተጨማሪ፣በመስቀል ጦርነት ምክንያት በርካታ እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ በስደት መጥተው ነበር፡፡ በተለይ በሰሜን ጎንደር አካባቢ በተደጋጋሚ ጦርነትም ተደርጓል፡፡ ከዘርዓ ያዕቆብ በፊትም በኋላም፡፡ ንጉሡ አገሪቱን ለማዋሃድ የተጠቀመበት የነበረው የክርስትና ሃይማኖትን ስለነበር የአይሁድ እምነት ትልቅ ፈተና የሆነበት ይመስላል፡፡ ሸዋ ውስጥም በርካታ የእምቱ ተከታይ የነበሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቤተ መንግሥቱ  ዙሪያም ጭምር፡፡
መጽሐፈ ሚላድ የአይሁድ እምነት በክርስትና እንደተሻረ፣ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ የሚያስረዳ ነው፡፡ የአይሁድ እምነት ተከታዮች እንደተሳሳቱ ያትታል፡፡ በመሆኑም፣በየወሩ በሃያ ዘጠነኛው ቀን (የበዓለ ወልድ/የበዓለ እግዚአብሔር ዕለት) በየቤተ ክርስቲያኑ እንዲነበብ ታዝዟል፡፡ ለአስራ ሁለትም ተከፋፍሏል፡፡
ጦማረ ትስብእት
‘ጦማር’ ማለት ደብዳቤ ሲሆን ‘ትስብእት’ ደግሞ ሰብኣዊነት፣ሰውነት(humanity) ማለት ነው፡፡ ዋና ጭብጡም የጥንቁልና እና የባእድ አምልኮን ስህተትነት ለሕዝቡ ማድረስ ነው፡፡ ከዜና መዋዕሉ ላይ መረዳት እንደሚቻለው ንጉሡን ጠንቋዮች ተፈታትነውታል፡፡ ለጥምቀት ማስፈጸሚያ የነበረውን ቦታ አውድመውበታል፡፡ ቤተ መንግሥቱን ያለምንም እረፍትና ማቋረጥ በመነኮሳትና ቀሳውስት ጸበል እያስረጨ ነበር የሚኖረው፡፡ በወንድሙ፣በንግሥ ይስሐቅ፣ ቤትም በሁለት ሰው የሚነሳ ግዙፍ የጥንቁልና መጽሐፍ እንዳገኘም ይገልጻል፡፡ በመጽሐፉም ቅዱሳንን ማክበርና እነሱን መዘከር እንጂ ጥንቁልና ኃጢኣት እንደሆነ ይገልጻል፡፡
መጽሐፈ ብርሃን
በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጣኦት ይመለክ ስለነበር ሕዝቡን ከጣኦት አምልኮ ለማላቀቅ ሲባል የተጻፈ ነው፡፡ ጣኦት ማምለክ ተገቢ እንዳልሆነ እና ክርስትናን መቀበል ተገቢ እንደሆነ ይሟገታል፡፡ ቀጥሎም ይከለክላል፡፡ በወቅቱ ደስክ፣ዲኖ ወዘተ የሚባሉ የጣኦት አምልኮ እንደነበሩ ልብ ይሏል፡፡
  ተዐቅቦ ምሥጢር
===========
በይዘቱ ስለ ቅዱስ ቁርባን (Holy Communion)ነው፡፡  በዘመኑ ከአዋማዊነት (Paganism)  እና ከአይሁድ ዕምነት (Judaism) ወደ ክርስትና እንዲቀየሩ የማድረግ ሥራ ስለተከናወነ የቁርባንን ምሥጢር እና ጥቅም ፣ምዕመናኑም ሆኑ ካህናቱ  እንዴት ቁርባን መቀበልና ማቀበል እንዳለባቸው፣ከተቀበሉ በኋላ ማድረግ ስላለባቸው ነገር ይዘረዝራል፡፡ ከትዕዛዙ ውጭ የሚፈጽሙት ደግሞ ምን መቀጣት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ የጥምቀትንም ነገር ይዟል፡፡
ክህደተ ሰይጣን
ይህ መጽሐፍ ምዕመናን በምን ሁኔታ ሰይጣንን መዋጋት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ ንጉሡ ክርስቲያኖች “ሰይጣንን እክዳሁ፣ በክርስቶስ አምናለሁ” እያሉ እንዲነቀሱ አውጀዋልም፡፡
መጽሐፈ ባሕርይ 
ይህ መጽሐፍ ንጉሡ ከጠንቋዮች ጋር የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ይናገራል፡፡ ስለ ኑዛዜና ስለ ቅብኣት እንደሚናገር ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ይገልጻሉ፡፡
 
እግዚአብሔር ነግሠ 
ይህ ድርሰት ዋና ዓለማው ቅዱሳኑን ማመስገን ነው፡፡ የተጻፈውም በግጥም ነው፡፡ አባቱን ዐፄ ዳዊትንም ያመሰግናል፡፡ ስለአባቱ የጻፈው እንዲህ በማለት ይጀምራሉ፡፡ የሦስቱን ብቻ የመጀመሪያ አንድ አንድ ስንኞች እንጥቀስ።
ሰላም እብል ለዳዊት ሐዲስ (ሰላም/ሰላምታ እላለሁ/አቀርባለሁ ለአዲሱ ዳዊት፡፡)
ሰላም እብል ለዳዊት መሲሕ (የተቀባውን ዳዊትን ሰላም እላለሁ/ሰላምታ አቀርባሉ፡፡)
በእንተ ሥጋከ ወደምከ ለዳዊት መሐሮ (ስለ ሥጋህና ስለደም መሐሪው ዳዊት)
እያለ ይቀጥላል፡፡
እንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት ሌሎች መጽሐፍትንም ደርሷል፡፡ ለምሳሌ ‘ስብሃተ ፍቁር’ እና ‘ድርሳነ መላዕክት’ የተባሉትን ይጠቅሳሉ፡፡
እነዚህን መጽሐፍት ለማዘጋጀት እና ሌሎችን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍት ለማዘጋጀት አስራ ሁለት ዓመታት እንደፈጁበት ዜና መዋዕሉ ይናገራል፡፡ ከደብረ ብርሃን (ከዋና ከተማው) ሳይወጣ ነው የጻፋቸው፡፡ የተጻፉት ከ1448 እስከ 1458 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለት ዓመታት ያኽል ከደብረ ብርሃን ብዙ ሳይርቅ ይመላለስ ነበር፡፡ ከዚያም ዕረፍቱ ሆነ፡፡
ዋና ምንጮች፡-
የዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዜና መዋእል፤ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ (የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐጼ ይኩኖ አምላክ እስከ ልብነ ድንግል)፤ኢንሳይክሎፔዲያ ኢቶፒካ ቅጽ 5፤ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለ ዐፄ ዳዊት በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት ቅጽ 16፤ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት Church and State፣የንጉሡ መጽሐፍት -መጽሐፈ ሚላድ፣ጦማረ ትስብዕት፣መጽሐፈ ብርሃን፣እግዚአብሔር ነግሠ…እና ሌሎችም ናቸው፡፡
Filed in: Amharic