>
5:13 pm - Sunday April 18, 1660

ለፌስቡከኞችና ዩቱዩበሮች! የሴራዋን ሳምንት በጥንቃቄ እንለፋት! (ጌታቸው ሽፈራው)

ለፌስቡከኞችና ዩቱዩበሮች! የሴራዋን ሳምንት በጥንቃቄ እንለፋት!
ጌታቸው ሽፈራው

1) ምርጫው ከሳምንት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል። ቀጣዮቹ ቀናት የምርጫ ቅስቀሳ የማይደረግባቸው ይሁኑ እንጅ በድርጅቶች ደረጃ ብዙ ስራ የሚሰራባቸው ናቸው። ከሕጋዊና ከሚታየው ይልቅ ሌላውም ይቀጥላል። ቅስቀሳው ቢቆም ለማሸነፍ የሚያስፈልጉት ስልቶች ይተገበሩባቸዋል። በአጭሩ ሰሞኑን ሴራው ይፋፋማል።  ተሰርቶ የሰነበተው ሴራ ይተገበራል።  ትልቁ የሴራ ሜዳ ደግሞ ማሕበራዊ ሚዲያና ዩቱዩብ ሆኗል። በመሆኑም በቀሩት ቀናት የሀሰት ወሬዎች የሚነዙበት ይሆናሉ።  ከራሳቸው ጦር ይልቅ ቀናኢ፣ ለሀገር ያስባል የሚባለውን ሳይቀር በስስ ጎኑ ገንተው፣ አሳስተው የዘመቻቸው አካል ያደርጉታል። ይህ ከምርጫው ቀኑ በፊትም ሆነ በኋላ ሊቀጥል ይችላል። ስለሆነም የትኛውንም መረጃ ማጣራት ያስፈልጋል። ከእስካሁኑ በተለየ  የሰሞኑን መረጃዎች በጥርጣሬ ማየት፣ ርቀት ሄዶ ማጣራት ከፀፀት ያድነናል። የማንም ሴረኛ መንጋ ከመሆን ያተርፈናል። ከትህነግ ጋር በነበረው ጦርነት ሰውን አምስት ስድስት ጊዜ ተገደለ ሲባል ይዞ እንደመሮጥ ቀላል አይደለም። ይህኛው ብዙ መዘዝ አለው። እንጠንቀቅ። ከምርጫ በፊትና በኋላ ያሉትን ወሳኝ ጊዜያት በብልህነት፣ በጥንቃቄ እናሳልፋቸው።
2) የሀሰት መረጃ በማሰራጨት ረገድ ቀዳሚዎቹ የሚሆኑት ከምርጫ ውጭ የሆኑ ኃይሎች ናቸው። ተቃዋሚዎችም ገዥው ፓርቲም ምርጫ ላይ ተፍ ተፍ ሲሉ እነሱ ነፃ ነበሩ።  ሰፊ የሴራ ጊዜ ነበራቸው።  ሌላው ምርጫው ላይ ሊያሸንፍ ሲሰራ እነሱ ምርጫው ላይ የራሳቸውን ክፉ ተግባር ፈፅመው ማለፍ ነው አላማቸው። በቁጥር አንድ ደረጃ “ይሄ ምርጫ አይሆንም ብለን ነበር” ለማለት ችግር እንዲገጥመው የሚፈልጉት ያልተሳተፉት ናቸው። ገዥውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በምርጫው የተሳተፉትን ተቃዋሚዎች የሚያብጠለጥሉት፣ ወንጀለኛ፣ ከሃዲ ለማድረግ የሚጥሩት “ተው ይሄ ምርጫ ይቅር ብለን ነበር። ባለመስማታቸው ሰው አስፈጁ፣ የሕዝብ ትግል አኮላሹ……” በማለት ነው። ምርጫው በሰላም ከሚያልፍ ችግር ገጥሞት ሰዎች ተጎድተው ሀገር ሌላ ተጨማሪ ችግር ገጥሟት  “ብለን ነበር” ቢሉ ለእነሱ ድል ነው። ተቃዋሚዎቹ ማሸነፍ የሚፈልጉትን ያህል በምርጫው ያልተሳተፉት ምርጫው እንከን እንዲገጥመው ማድረግ ይፈልጋሉ። የመጀመርያው አላማቸው ጥቃት ሲፈፀምባቸው በከረሙት አካባቢዎች ጥቃት መቀስቀስና ማሸበር ነው።  ጥቃት ተፈፀመም አልተፈፀመም የሀሰት ወሬ እየነዙ ሕዝብን  ሊያወናብዱ ሊያሸብሩ ይችላሉ። በቅርቡ እንደሚቀጣጥሏቸው መልዕክቶች ሕዝብ የሚወዳቸውን የተቃዋሚ አመራሮች ሳይቀር ስም እያጠፉ ግራ ሊያጋቡ ይችላሉ።  ተቃዋሚዎችም ሆነ ገዥዎች ያላደረጉትን ተደረገ ብለው ሊያወናብዱ ይችላሉ። በምርጫው ሳይሳተፉ ምርጫውን አሸነፍን የሚሉት በዚህ መንገድ ነው። በዚህ ውዥንብር ውስጥ የሚጠሉት ሕዝብ ከፀጥታ ኃይል ጋር ቢጋጭላቸው ደግሞ በምርጫው መንግስትን የሚቆጣጠር ድል አደረኩ ከሚለው ያልተናነሰ ድል ተቀዳጀን ብለው ይደሰታሉ።
3) በምርጫ ካልተሳተፉት ኃይሎች ቀጥሎ ሀሰተኛ መረጃ የማሰራጨት አቅምና ልምድ ያለው ገዥው ፓርቲ ነው። ሀሰት የሚያወሩ ሞልተውታል። በጦርነቱ አንድን ሰው ብዙ ጊዜ የገደሉ አወናባጆች ሞልተውታል። ገዥዎቹ በ1997 ዓ/ም ምርጫ ወጥተው አሸንፈናል ከማለት ባለፈ ብዙ አሉባልታ አውርተዋል። ተቃዋሚዎችን እርስ በእርስ ከማናቆር አልፈው በጎጥና በሰፈር፣ በእምነት  ሳይቀር ችግር የሚፈጥሩ አሉባልታዎችን ሊነሱ ስለሚችሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ፌስቡክ ከገዥው ፓርቲ ጋር  ግንኙነት ያላቸውን የሀሰት አካውንቶች መዝጋቱን ገልፆአል። እነዚህ አካውንቶች ተቃዋሚዎችን ያልሆነ ስም ሲሰጡ የሚውሉ ናቸው። ከእነዚህ የተረፉት የሀሰት አካውንቶች በምርጫው ወቅት ገዥው ፓርቲ ቀድሞ ያስቀመጠውን ሴራ ለማስተግበር የሚያስችሉ የሀሰት ዜናዎችን ይለቃሉ። አሉባልታዎችን ያስወራሉ። በስማቸው የሚፅፉት ሀሰተኞች በሰበር ዜና ሕዝብን ያወናብዳሉ። ያልተፈጠረ ተፈጠረ ብለው ይፅፋሉ። በመሆኑም በዚህ ወቅት በስም ታወቀም አልታወቀም የተለጠፈን ጉዳይ ሳያጣሩ ማጋራት መዘዝ አለው። ሁለት ሶስት ጊዜ ያስጠቃል። ተገደለ እያሉ ሁለት  ሶስት ጊዜ እንዳወሩለት ዜና ውሸት ብቻ ሆኖ የሚቀር አይደለም። ተጨማሪ ችግር ይፈጥራል።
4) ምርጫ ካልተሳተፉትና ከገዥዎቹ ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ የሀሰት መረጃ ሲያስተላልፍ የሚችለው በሙሉ ልባቸው ወደ ምርጫ ያልገቡት ናቸው። እነዚህ በድርጅትም፣ በግለሰብም፣ በፌስቡክም በዩቱዩብም ደረጃ አሉ። ምርጫውን አያስፈልግም እያሉ ከርመው አንዲት ጥሩ ነገር ሲያዩ ምርጫውን ግፉበት ሲሉ ቆይተው ሳይቀናቸው ሲቀር ከአፈርኩ  አይመልሰኝ ወለም ዘለም ማለታቸው አይቀርም። ገዥው ፓርቲ በተቃዋሚዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ገንዘብ ከፍሎ የሚልካቸው የራሱ ሰዎች ደግሞ ምርጫው ላይ ወስነው ላልገቡት አጋዦች ናቸው። ጓዶቻቸው ላይ ሳይቀር አሉባልታ ያወራሉ። በምርጫ ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ከገዥው ፓርቲ ጋር የወገኑ በማስመሰል፣ አሸንፈው የገቡትን የራሳቸውን የድርጅት አባል ስም በመስጠት ሴራዎች ይሰራሉ። ከምርጫ በኋላ  የመንግስትን ስልጣን ተረከበም አንድ ወንበር አገኘም ድሉም ሽንፈቱም እንደ ድርጅት የሚወሰድ፣ እንደ ድርጅት የሚገመገም መሆን ሲገባው ወለም ዘለም የሚሉትም፣ ገዥው ፓርቲ የላካቸውም እየመተሩ ለግለሰቦች ይሰጧቸዋል። አንድ ድርጅት ውስጥ በእምነት፣ በብሔር፣ በትውልድ ቦታ፣ ጎጥ ጉዳዩን እየበየኑ ከምርጫው ባሻገር ሌላ ሽንፈት እንዲኖር ያደርጋሉ። ይህ ሁለት ሶስት ጊዜ ሽንፈት ነው። ድርጅቶች ለአንድ ምርጫ አይመሰረቱም። ቢያሸንፉ ይቀጥላሉ። ቢሸነፉም ይቀጥላሉ። ከምርጫ በኋላ ድርጅቶች ችግር እንዲገጥማቸው የሚያደርገው አንደኛው ምርጫው ላይ የነበረውን ጉዳይ በአሉባልታ ሲጠቃ ነው፣ ምርጫ ባልተሳተፈውም፣ በገዥው ፓርቲም ሴራ ከተመታ ነው።
በተለይ በተለይ ከምርጫው ባሻገር የሚታዩ፣ የማናመነታባቸው ጉዳዮች መኖር አለባቸው። የሕዝብ አንድነት ከምርጫው ባሻገር ግዙፍ ነው። የሕዝብና የፀጥታ ኃይሎች መካከል ያለው ግንኙነት ከአምስት አመት ምርጫ በላይ ነው። በተለይ በልዩ ኃይል፣ ሚሊሻውና ሕዝብ መካከል ያለው ከአምስት አመት ከፍ ያለ ጉዳይ ያለው ነው።  በፀጥታ ኃይሉ ችግሮች ካሉ በአንዴ የሚፈቱ አይደሉም። እነዚህ አካላትም ከሕዝብ ጋር ከምርጫ ባለፈ በደም የተሳሰሩ፣ በጦርነት ወቅት አንድ ሆነው የዘመቱ ናቸው። አንድነታቸውን ማስጠበቅ ያስፈልጋል።
የሚቀጥሉት ቀናት የሚፈጠሩ የሀሰት ዜናዎች፣ ሴራዎች ዩቱዩብ ላይ ከሚገኝ ዶላር፣ ፌስቡክ ላይ ከሚገኝ ዝና በላይ ዋጋ አላቸው። በሚቀጥሉት ቀናት የምናደርጋቸው ጥንቃቄዎች ለፀፀት እንዳንዳረግ ያግዙናል። 1997 ዓ/ም በየድርጅቱ፣ በየግለሰቡ ብዙ ስም ተለጥፏል። ዋናውን ስራ የሰራው ገዥው ፓርቲ ነው። አሁን ደግሞ ከእሱ በተጨማሪ በምርጫው  ያልተሳተፈ ምርጫ   እንዳይደረግ የፈለገ  ብዙ ተገንጣይ ኃይል አለ።  ያንም ይህም የሚቃርም ፌስቡከኛና ዩቱዩበር አለ። ለሀሰትና ለአሉባልታ ጊዜው ምቹ ነው።  ከተጠነቀቅን ግን እንደ 1997 ዓ/ም አሉባልታና ፍትጊያ ድርጅት ሳያፈርስ፣ አነሰም በዛም ድልን በጥንቃቄ ይዞ፣ የሰው ነፍስ ሳያልፍ ምርጫውን ማሳለፍ ይቻላል።
ይህ ሲባል ግን ምርጫው ወቅት ላይ መረጃ መሰራጨት የለበትም ማለት አይደለም። እንዲያውም እስካሁን ስናደርገው ከነበረው በላይ ይህ ወቅት መረጃ ማሰራጨትን ይጠይቃል። ማጋለጥን ይጠይቃል። ግንዛቤ መፍጠርን መሞገትን ይጠይቃል። ልዩነቱ ምንጮቹ ላይ ነው፣ የመረጃው እውነታነት ላይ ብቻ ነው። ከፓርቲዎች፣ ከምርጫ ቦርድና መሰል ተቋማት የተገኙ መረጃዎ፣  የተጣሩ እውነቶችን ይዞ ማጋለጥ፣ መታገል ያስፈልጋል።
Filed in: Amharic