>

“እስኪ ምርጫው ይለፍ...!!!” (በፍቃዱ ኃይሉ)

“እስኪ ምርጫው ይለፍ…!!!”

በፍቃዱ ኃይሉ

ብዙ ሰዎች ዘንድ ያለውን የፖለቲካ ድባብ የሚልግልጽ ንግግር ምረጥ ብባል “እስኪ ምርጫው ይለፍ” የሚለውን እመርጣለሁ። ብዙዎች በግል ሕይወታቸው ላይ መወሰን ያለባቸውን ጉዳይ ለመወሰን ይህንን ገለጻ ደጋግመው ሲጠቀሙ ሰምቻለሁ። ይህንን ምርጫ ብዙኃን የሚመለከቱበትን መንገድ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ንግግር ይመስለኛል።
ምርጫ 2013 የተለየ ነው። ጥቂቶች ከ1997ቱ ምርጫ ጋር ያመሳስሉታል፤ ይሁን እንጂ ይህ ምርጫ ከምርጫ 97 በእጅጉ ይለያል። ምርጫው ባልተለመደ ሁኔታ ዜጎችን በሦስት ምድብ አስቀምጧቸዋል። በከፊሎች ዘንድ እንደ ሞት ቀጠሮ ተፈርቷል፣ በከፊሎች እንደ ዕፀ ሕይወት ተናፍቋል፣ በከፊሎች ደግሞ እንደ ዘመድ ገዳይ ተጠልቷል። ነገር ግን በእሾሕ እና ጋሬጣ መንገድ ላይ ተጉዞ፣ ቆሳስሎ እና ተሰባብሮ የፍፃሜው መጀመሪያ ደጃፍ ላይ ደርሷል።
በመጪው ሰኞ ብዙዎቹ (444 ገደማ) የምርጫ ክልሎች ምርጫ ይካሔድባቸዋል። ምንም እንኳን ጳጉሜ 1 ሌሎች (65 ገደማ ያህሉ) የምርጫ ክልሎች ውስጥ ምርጫ የሚካሔድ ቢሆንም፣ የሰኔ 14ቱ ምርጫ የፌዴራል መንግሥት የሚመሠርተው ፓርቲ የሚታወቅበት ምርጫ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። በመጪዎቹ ሳምንታት ውስጥ ምርጫውን የፈሩትም፣ የናፈቁትም፣ የጠሉትም ሰዎች መልሳቸውን ያገኛሉ።
ምርጫ 2013 በምን ይለያል?
የምርጫ 2013 የመጀመሪያው መለያ ምልክቱ በቀውስ ማዕበል ውስጥ መከሰቱ ነው። ከዚህ በፊት የተካሔዱ ምርጫዎች በሙሉ በተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የተካሔዱ ነበሩ። የምርጫ 97ቱ ቀውስ እንኳን የተከሰተው ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ነበር። ምርጫ 2013 ግን በጦርነት ምክንያት ምርጫ የማይካሔድበት አንድ ክልላዊ መስተዳደርን (ትግራይን) ጨምሮ ብልጭ ድርግም በሚሉ ግጭቶች ሳቢያ ሒደቱ የቆመባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች አሉ። በቅድመ ምርጫ ሒደቱ ላይ በተነሱ ቅሬታዎች እና በምርጫ ሰነዶች ዝግጅት ጉድለት ሳቢያ ሒደቱ የተራዘመባቸው ክልሎችን (ሶማሊ፣ ሐረሪን) ጨምሮ ሌሎች የምርጫ ክልሎችም አሉ። የጳጉሜ አንዱ ምርጫ ያስፈለገበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ በዚህም ይለያል።
ምርጫው፣ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ ኢሕአዴግ እንደ ኢሕአዴግ የማይሳተፍበት ምርጫ መሆኑም ሌላው መለያው ነው። ኢሕአዴግ የርዕዮተ ዓለም አባቱ የሆነውን ሕወሓትን አስወጥቶ እና በጦርነት ገጥሞ ሲያበቃ፣ በሌላ በኩል ርዕዮተ ዓለሙን ሽሮ እና ብልፅግና የተባለ ወጥ ሥም ለብሶ የሚወዳደርበት ምርጫ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል። በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ብቻውን (ጥምረት ሳይመሠርት) ካሸነፈ የፌዴራል መንግሥት መመሥረት የሚያስችለውን የዕጩዎች ቁጥር ይዞ የሚወዳደር የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ (ኢዜማ) ያለበት ምርጫ መሆኑም የተለየ ያደርገዋል። ኢዜማ 350 ያህል ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፣ ለምክር ቤቱ ከሱ ቀጥሎ ትልቅ ቁጥር ያቀረበው እናት ፓርቲ 177 ዕጩዎች ብቻ አሉት።
ኦነግ አገር ውስጥ ተቀምጦ ምርጫውን ያልተወዳደረበት፣ ኦፌኮ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምርጫ የተገለለበት፣ በእስር ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ዕጩ የሆኑበት፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያ ሿሚ እና ሻሪ በሆነበት ጊዜ የሚካሔድ ምርጫ በመሆኑ የተለየ ምርጫ ነው። የተለየነቱ ግን በረከት ነው ማለት አይደለም፤ መርገምትም ጭምር ነው። ብዙዎች ቀድሞም እየዳኸ የመጣው ግጭት ምርጫውን ተንተርሶና ተባብሶ ይቀጥላል በሚል ስጋት ተወጥረዋል። የተፈራውን ያህል ግጭት ይኖር ይሆን?
 
“እስኪ ምርጫው ይለፍ”
ብዙ ሰዎች ዘንድ ያለውን የፖለቲካ ድባብ የሚልግልጽ ንግግር ምረጥ ብባል “እስኪ ምርጫው ይለፍ” የሚለውን እመርጣለሁ። ብዙዎች በግል ሕይወታቸው ላይ መወሰን ያለባቸውን ጉዳይ ለመወሰን ይህንን ገለጻ ደጋግመው ሲጠቀሙ ሰምቻለሁ። ይህንን ምርጫ ብዙኃን የሚመለከቱበትን መንገድ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ንግግር ይመስለኛል። ጥቂት ያልሆኑ ሰዎች ከአሁን አሁን ግጭት ይፈነዳል በሚል ጭንቀት ሊፈነዱ ነው።
ምርጫ ነክ ግጭቶች የታወቁ ናቸው። በተለይም ደግሞ የረጋ ዴሞክራሲ በሌላቸው አገራት ውስጥ ምርጫዎች ከሚያመጡት ለውጥ ይልቅ የሚያስከትሉት ነውጥ ይከፋል። ምርጫዎች በቅድመ ሒደታቸው፣ በምርጫ ቀኑ ድምፅ አሰጣጥ ወቅት፣ እንዲሁም በድኅረ ምርጫ ውጤት ገለጻ ወቅት ነውጦች ሊከሰቱባቸው ይችላሉ።
በቅድመ ሒደቱ የሚከሰቱት ግጭቶች ብዙ ጊዜ በምረጡኝ ቅስቀሳዎች ወቅት በሚጋጋሉ ግርግሮች እና መንግሥት ወይም ምርጫ ቦርድ በሚወስዳቸው ውሳኔዎች የመነሳት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው። በኢትዮጵያ የቅድመ ምርጫ ሒደቱ ቅልጥ ያለ ነውጥ ያስከትላል ተብሎ ተሰግቶ የነበረ ቢሆንም፣ የተከሰተው ነገር ከተሰጋው በታች ነበር። ምርጫ ነክ ነውጦች ባሕርያት ውስጥ አንዱ የፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ እና ሲቪል ሠራተኞች መዋከብ እና መገደል ነው። እስካሁን አብንና ኢዜማ እያንዳንዳቸው ሁለት፣ ሁለት የፖርቲ አባላት እንደተገደሉባቸው ሪፖርት አድርገዋል። የምርጫ አስፈፃሚዎች የተገደሉባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ተሰምቷል። የምርጫ ጣቢያዎች ተዘርፈዋል እንዲሁም ተቃጥለዋል የሚሉ ሪፖርቶችም ነበሩ። ሒደቱ ከነውጥ የፀዳ ባይሆንም የተሰጋውን ያክል አልከፋም። ለዚህም የበርካታ ባለድርሻ አካላት ርብርብ የተወሰነ አስተዋፅዖ ሳያደርግ አልቀረም።
የምርጫ ዕለት የሚከሰቱ ነውጦች ብዙ ጊዜ መራጮችን፣ ወይም የምርጫ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረጉ ነው የሚሆኑት። እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች በተለይ በአፍጋኒስታን በሰፊው ታይተዋል። አሁንም በኢትዮጵያ የምርጫውን ቅቡልነት የማይፈልጉ እና ይህንንም በይፋ እየተናገሩ ያሉ የአመፅ ቡድኖች እንዲህ ዓይነት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ መገመት ነቢይነት አይጠይቅም። ስለድምፅ አሰጣጡም የተለያዩ የተዛቡ መረጃዎች ሁከት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። ስለዚህ የፀጥታ ኃይሎች፣ ሲቪል ማኅበራት እና ብዙኃን መገናኛዎች በንቃት ቆመው መጠበቅ አለባቸው።
ሌላው ከቆጠራ እና ውጤት ገለጻ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የድኅረ ምርጫ ነውጥ ነው። ምርጫ ነክ ነውጦች የከፉ የሚሆኑት ውጤቶቹ ላይ ተፎካካሪ ወገኖች ሳይስማሙ ሲቀሩ እና ተሸናፊ ወገን ያሉት አሸናፊ ነን ብለው ከምርጫ ቦርዱ ውጤት በተቃራኒ ያወጁ ጊዜ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ግጭት በኢትዮጵያም በምርጫ 97 ወቅት ታይቷል። ብዙ ጊዜ ተፎካካሪዎች በጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ጉድለቶችን እንደማሳያ በመጥቀስ በመላው የምርጫ ክልሎች ውስጥ አሸናፊ መሆናቸውን ሊያውጁ ይችላሉ። በዚህ ምርጫም፣ ከኦሮሚያ በስተቀር፣ በተለይ በክልሎች ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ቅሬታ የመነሳት ዕድል አለ። ማኅበራዊ ሚዲያው እና ወገንተኞቹ መደበኛ ብዙኃን መገናኛዎችም እነዚህን እና ሌሎችም የተዛቡ መረጃዎችን በማራገብ ችግሩን ሊያጋግሉት ይችላሉ።
ብዙዎች በኢትዮጵያ አሁን ያለው የፖለቲካ ምኅዳር እንደሚያሳየው አመፅ ሊከሰትባቸው የሚችሉባቸው ቦታዎች እና ሁኔታዎች ቀድመው ስለታፈኑ፥ ቢያንስ ምርጫውን ተንተርሶ የሚነሳ ግጭት አይኖርም ይላሉ። ሆኖም፣ የትኛውንም ሰበብ ተጠቅመው ሊቀሰቀሱ የሚችሉ የተዳፈኑ በርካታ ግጭቶች መኖራቸውን ሁሉም አይክዱም። ለዚህም ነው “እስኪ ምርጫው ይለፍ” በማለት ብዙዎች ጉዳያቸውን ለነገ እያሳደሩ ያሉት።
ምርጫው በሰላም እንዲያልፍ…
ምርጫው በሰላም የሚያልፈው በአንድ ወገን ምኞት ወይም ትጋት ብቻ አይደለም። የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራ ትብብር ይጠይቃል። ምርጫ ቦርድ የድምፅ አሰጣጡን፣ ቆጠራውን እና ውጤት እወጃውን በተቻለ መጠን ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና በሕግ አግባብ ውስጥ እንዲሄድ መረባረብ አለበት። የፖለቲካ ድርጅቶች ቅሬታዎች ሲኖሯቸው በመረጃ አስደግፈው እና የቅሬታው መጠን በጠቅላላው ውጤት ላይ ያለውን አንድምታ ሳያጋንኑና ሳያንኳስሱ በማቅረብ ባሉት ሕጋዊ እና አስተደራደራዊ አማራጮች እንዲስተካከልላቸው መጣር አለባቸው። ታዛቢዎች እና የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች፣ እንዲሁም ብዙኃን መገናኛዎች ዜጎችን ወክለው እውነቱን በማጣራት እና በመናገር፣ ቅሬታዎች ሲኖሩ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማመላከት የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ልምምድ እንዲኖር የበኩላቸውን መጫወት አለባቸው።
ከሁሉም በላይ ግን “እስኪ ምርጫው ይለፍ” እያሉ ጉዳያቸውን ሲያሳድሩ የከረሙ ዜጎች በእርምጃቸው በሙሉ የየትኛውም ፖለቲካ ወገን እኩይ አላማ ላለመሆን በተጣራ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ሰላማዊ እርምጃቸውን አጥብቀው መያዝ ይኖርባቸዋል። የፖለቲከኞች ጦስ ብዙውን ጊዜ የሚጎዳው ብዙኃን ዜጎችን ነውና ዜጎች ነውጥን እምቢ ማለት ይኖርባቸዋል።
Filed in: Amharic