>

የማይዘነጋ -ዛሬም የሚተጋ በሳል የሚድያ ሰው እሸቴ አሰፋ  (እሸቴ-ከጃንሜዳ )... .!!! (ተወዳጅ ሚድያ)

የማይዘነጋ -ዛሬም የሚተጋ በሳል የሚድያ ሰው እሸቴ አሰፋ  (እሸቴ-ከጃንሜዳ )… .!!!

ተወዳጅ ሚድያ
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸውን ሰዎች ጠቁሙን ፤ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪካቸዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.comጥቆማዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ አሁን ታሪኩን የምንሰንድለት ሰው እሸቴ አሰፋ ነው፡፡ እሸቴ ስለራሱ ከሚናገር ይልቅ ስራው የሚናገር በሳል ባለሙያ ነው፡፡  በመጽሄት ፣ በጋዜጣ፣ በሬድዮ በቲቪ የሰራ ለወጣት ባለሙያዎች አርአያ የሚሆን የተከበረ ባለሙያ  ነው፡፡ እሸቴ ያለፈበት መንገድ አስተማሪ በመሆኑ ታሪኩን በሚከተለው መልኩ አሰናድተነዋል፡፡
          ትውልድና እድገት፤ 
እሸቴ አሰፋ የተወለደው ሰሜን ሸዋ መንዝ ግሼ ወረዳ ነው፡፡  ጊዜውም  ሀምሌ 19 ፤1953 አ.ም ነበር፡፡  የሚድያ ባለሙያ እሸቴ፣ በተወለደበት እለት፣ታትሞ የወጣውን  አዲስ ዘመን ጋዜጣን፣ አይተን እንደተረዳነው፣ በምእራብና በመካከለኛው  የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች፣ ቀኑን ሙሉ ደመና ነበር፡፡ በተለይ ጠዋት ሰማዩ በሙሉ ተሸፍኖ አንዳንድ ጊዜ አነስተኛ ዝናብ ከሰአት በኋላ መጠነኛ ዝናብ ይጥል ነበር፡፡
ጋዜጠኛ እሸቴ፣ በተወለደበት እለት ምን ጉዳይ ነበር ብለን፣ ዳሰሳ ስንሰራ፣ አዲስ ዘመን ባወጣው የፊት ለፊት ገጽ ዜና፣ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ያላት ተቀማጭ ገንዘብ፣ከ15 ሚሊዮን  ዶላር ከፍ ያለ ነበር፡፡ የስራ አመራር ኮርስም የተቋቋመው የዛኑ ሰሞን ነበር፡፡ (ከ59  አመታት በፊት፣ሀምሌ 19 1953  ታትሞ የወጣውን  የአዲስ ዘመን ቅጂ ከዚህ ጽሁፍ ጋር ተያይዙዋል፡፡)
            የጋዜጠኝነት  ጅማሮ -በወጣትነት  
እሸቴ አሰፋ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን  በተወለደበትና ባደገበት፣ ግሼ ወረዳ በሚገኘው  ራቤል ትምህርት ቤት  ያጠናቀቀ ሲሆን፣ 2ኛ ደረጃን፣  በ መሃል ሜዳ፣ በሆለታና አቃቂ  ተማሪ ቤቶች ነበር ተምሮ ያጠናቀቀው፡፡፡፡
የእሸቴ የሚድያ እና የጋዜጠኝነት አፍቃሪነት የታየው፣ ገና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ  ነበር፡፡ ያንጊዜ በተማሪ ቤቱ ሚኒ ሚድያ፣  በጥዋቱ የተማሪዎች ሰልፍ ላይ የስነ-ጽሁፍ ስራዎችን በማቅረብ እጅና አንደበቱን አፍታታ፡፡
እሸቴ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋዜጣ ጽሁፍ የታተመለት ፣ በአዲስ ዘመን  ‹‹አድማስ ገጽ›› ላይ ነበር፡፡  ከዚያ በኋላ፣በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እየጻፈ አቅሙን አዳብሮ፣   በፍሪላንስ ጸሀፊነት፣ በህትመት ውጤቶቹ ላይ መጻፉን ተያያዘው፡፡ በእነዚያ ጊዜያቶች፣ በአንድ በኩል የዩንቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ፣በሌላ በኩል  ፅሁፎቹን ማቅረብ ቀጠለ ፡፡ ከጋዜጣ እና መፅሄት ጽሁፍ አቅራቢነት በተጨማሪ፣ በለገዳዲ ሬዲዮ፣ እና በኢትዮ ጵያ ቴሌቭዥን ፕሮግራም  ያቀርብ ነበር፡፡
              እሸቴና የካቲት መጽሄት  
እሸቴ ፣ በ1979 ግድም የካቲት መጽሄት ላይ  በፍሪላንስ ጸሃፊነት መጻፍ ጀመረ፡፡ በጊዜው ግለ-ታሪክ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ በሳል ፅሁፎች አቅርቧል፡፡ በጥቅምት 1980 በየካቲት መጽሄት እትም ላይ፣  የዛሬ 33 አመት ከሰራቸው ግለ-ታሪክ ጽሁፎች አንዱ፤ የአንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ የጳውሎስ ኞኞ ታሪክ ይገኝበታል፡፡  ሰፋ አድርጎ የሠራው ይህ ጽሁፍ፤ ጳውሎስ ኞኞን የሚያውቁ የቅርብ ሰዎችን ቃለ-መጠይቅ የተደረጉበት ነው፡፡
ቃለ-መጠይቅ ከሰጡት መሀልም ከፕሬስ መምሪያ ሙሉጌታ ሉሌ ፣ ከኢትዮጵያ  ሬድዮ ታደሰ ሙሉ ነህ፣  ከሥራ ባልደረቦቹም እነ አጥናፍ ሰገድ ይልማ ባለቤቱ ወይዘሮ አዳነች፣ ጭምር የተካተቱበት ነበር፡፡
ስለ ብርሀኑ ዘሪሁን፣ ስለወጋየሁ ንጋቱ፣ ስለይድነቃቸው ተሰማ…. ጥልቀት ያላቸው ጽሁፎች አሳትሟል፡፡ እሸቴ በዚያን ሰሞን በመጽሄቱ ላይ ያወጣቸው የነበሩት ጽሁፎች በበቂ ጥናት እና ዝግጅት የተሰሩ ስለነበሩ አንባቢን የሚያረኩ በሰፊ ገጽ ተሰናድተው የቀረቡ ነበሩ፡፡
የዚህ ዊኪፒዲያ አሰናጆች የእሸቴን ግለ-ታሪክ ሲያጠኑ የካቲት ላይ ከጻፋቸው በርካታ ጽሁፎች ውስጥ 7 ያህሉን ጊዜ ሰጥተው አንብበዋቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል. ስለ ‹‹ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ›› ፤ ሰለሰሜን ኮሪያ፣,እንዲሁም ስለ አርበኞች እንቅስቃሴ የጻፈቸው ይገኙበታል፡፡
እሸቴ ፣ በቂ ንባብ እና የጋዜጠኝነት ፍላጎት ያዳበረ በመሆኑ ፣ የሚጽፋቸው ጽሁፎች ላይ ከፍተኛ ብስለት ይታይባቸዋል፡፡ በየካቲት መጽሄት ላይ ሲሰራ‹‹ የአጻጻፍ እውቀት ሰጥቶኛል›› ብሎ ምስጋና እና አክብሮት የሚሰጣቸው  ዋና አዘጋጁን፣ አቶ ጸጋዬ ሀይሉ ተፈራን ነው፡፡ እሸቴ ስለ የካቲት መጽሄት ሲያነሳ፣ አቶ ጸጋዬ እንደቅርብ አርታኢ  ትልቅ ድጋፍ ሰጥተውታል፡፡ ‹‹ምንጊዜም የማልረሳቸው መምህሬ ናቸው›› ሲል ታላቅ አክብሮቱን ይገልጻል፡፡
 በአሁኑ ሰአት፣ የ78 አመት አንጋፋ የሆኑት፣ አቶ ጸጋዬ ፣ የካቲት መጽሄትን ከ10 አመት በላይ በዋና አዘጋጅነት የመሩና መጽሄቷንም ተወዳጅ እና ተነባቢ ካደረጉ በሳል የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
 አቶ ጸጋዬ ፣የእሸቴን ክህሎት ዛሬም ያደንቃሉ፡፡
 ‹‹…የተረጋጋ፣ በእውቀት ላይ ተመስርቶ የሚሰራ ፣ ውለታ የዋለለትን ሰው የማይዘነጋ መልካም ሰው ነው፤…››
 ሲሉ  ገልጸውታል፡፡
እሸቴ፣ በየካቲት መጽሄት ላይ ሲሰራ የሚያውቁት፣ አቶ ተሾመ ብርሀኑ ከማል ያላቸውን የአድናቆት  ስሜት ሲገልጹ
‹‹በጥሩ ቋንቋ የሚጽፍ ታታሪ ብእረኛ.›› ብለውታል፡፡ ‹‹ከልቡ የሚጽፍ ፤ በምርምር ላይ ተመስርቶ የሚሰራ ፈጣን መጣጥፍ አቅራቢ፣ በ1970ዎቹ መጨረሻ ሀገራችን ካፈራቻቸው ጸሀፊዎች አንዱ ነው…››
ሲሉ አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፡፡
ያለ አንዳች እረፍት መስራት የእሸቴ መገለጫዎች ነበሩ፡፡ በለገዳዲ ራዲዮ፣በየካቲት መጽሄትና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዝግጅቶች የሚያቀርበው በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑ ይህንኑ ይመሰክራል፡፡
በጊዜው ፣ እሸቴን ጨምሮ ብዙዎቹ ፍሪላንስ ጸሀፊዎች ፣ ለአንድ  ጽሁፍ ብር 150 ይከፈላቸው የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ጸሀፊዎች ለምርምር ስራ ከዚያ በላይ የሚያወጡበት ጊዜ ነበር፡፡
እሸቴ አሰፋ በጊዜው ውሎውን ቤተ-መጽሀፍት በማድረግ የሚመለከታቸውን ቃለመጠይቅ በማድረግ የአንባቢን  የንባብ ጥም ሲያረካ የኖረ ስለመሆኑ ብዙዎች መስክረዋል፡፡
እሸቴ የአዲስ አበባ 100ኛ አመት በተከበረ ጊዜ ለክብረ- በአሉ በተዘጋጀው ልዩ መፅሄት ላይ፣ ስለ መዲናይቱ ታሪክ መጣጥፍ ጽፎም ነበር ፡፡
           እሸቴና ለገዳዲ ራዲዮ  
የእሸቴ የለገዳዲ ቆይታ በደስታ የተሞላ ነበር፡፡ ያኔ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ባሻገር እንደ አማራጭ ቀርቦ የነበረው ለገዳዲ ራዲዮ ስለነበር፣ እሸቴ እና ሌሎች ለጥበብ ቅርበቱ ያላቸው በለገዳዲ የእሁድን ለአንዳፍታ ፐሮግራም ተሳትፈውበታል፡፡ እሸቴ በተለይ በሚያቀርባቸው የስነ-ቃል መሰናዶዎች በአድማጭ ዘንድ ተናፋቂ ነበሩ፡፡
ልክ የካቲት መጽሄት ላይ የግለ-ታሪክ ጽሁፎችን ሲጽፍ በበቂ ሁኔታ እንደሚዘጋጀው ሁሉ ስነ-ቃሎችንም ሲተነትን በቂ  መሰናዶ አድርጎ ነው፡፡
‹‹ እሸቴ ከጃንሜዳ›› በሚል ስያሜ፣ የህዝብን ባህል የሚያሳዩ የሥነ-ቃል ስብስቦችን ለሬዲዮ ስርጭት እንዲያመች እያደረገ አስተላልፏል፡፡ በርካታ አድማጮችን ያፈራበትና በሳል መጣጥፎችን በድምጹ ያስተላልፍበት ፕሮግራም ነበር፡፡   በየአስራ አምስት ቀን ይቀርብ የነበረው፣ የሥነቃል ዝግጅቱ፣ ከ 1978 ጀምሮ ለአምስት አመታት ተሰራጭቷል፡፡
አቶ ጠንክር ገብረሰንበት ፣ እሸቴን ከ1978 ጀምሮ በለገዳዲ   ሬድዮ  ሲሳተፍ ያውቁታል፡፡ እርሳቸው ያኔ የስራ ሃላፊም ስለነበሩ የእሸቴን ስራዎች የመከታተል እድል ነበራቸው፡፡
‹‹….ያን ጊዜ ለገዳዲ የቅዳሜን ከእኛ ጋር  እና የእሁድን ላንዳፍታ መሰናዶዎች የሚቀረጹት ሜክሲኮ ዲአፍሪክ ወረድ ብሎ በሚገኘው የትምህርት መገናኛ ዘዴዎች ስቱዲዮ ነበር፡፡ ታዲያ እሸቴ ራሱ የጻፋቸውን መጣጥፎች በራሱ አንደበት ያነባቸው ስለነበር አድማጭን የመማረክ አቅም ነበራቸው፡፡  እሸቴ፣ በተለይ የገበሬውን  ውሎ አጠቃላይ የገጠሪቱን የሀገራችንን ክፍል በስነ-ቃል ለማሳየት የተቻለውን ያደርግ ነበር ፡፡እሸቴ ለገዳዲ ጽሁፍ ይዞ ሲመጣ በቂ ዝግጅት ከማድረጉ በላይ የነበረውም ትህትናዊ አቀራረብ ፍጹም አይዘነጋኝም….. የሚያቀርባቸው መጣጥፎች ብስለትን የተላበሱ በመሆናቸው ለማድመጥም የሚጋብዙ ናቸው…››
 ሲሉ አቶ ጠንክር ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች ተናግረዋል፡፡
 እሸቴ፣ለገዳዲ ራዲዮ ላይ ሲሰራ፣ ‹‹ስለሬዲዮ ዝግጅት አስተማሪዬ ናቸው›› የሚላቸውን የፕሮግራም ሀላፊ የነበሩትን አቶ ገበየሁ ደምሴን  ያስታውሳል፡፡
          እሸቴ እና ቴሌቪዥን
እሸቴ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በቋንቋ እና ስነ-ጽሁፍ በቢ.ኤ በዲግሪ ተመርቋል፡፡ ከ1978-1983 በለገዳዲ እና በየካቲት መጽሄት ላይ ያበረከተውን አስተዋጽኦ እንደያዘ፣ በ1979  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በፍሪላንስ ጋዜጠኝነት ተቀጠረ፡፡ በተለይ ደግሞ፣ በዘጋቢ  ወይም በዶክመንተሪ ስራዎች አቅሙን የማሳየት ፍላጎት ስለነበረው፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ አካባቢዎችን  ቦታው ድረስ ሄዶ በማየት ዘጋቢ ፊልሞችን አዘጋጅቷል፡፡
‹‹ንጋት›› በሚል ርእስ ከቀረቡት እያንዳንዳቸው አንድ ሰዐት የሚዘልቁ ፣አምስት ክፍሎች ያሉት ዘጋቢ ፕሮግራም አብዛኛውን የሸፈነው እሸቴ ነበር፡፡
እሸቴ፣ ጣና ሃይቅ ላይ ስላሉት አድባራት የሰራው ዶክመንተሪ በብዙዎች የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ አድባራት በወቅቱ የነበሩበትን ሁኔታ በማጥናት ለተመልካች ጥሩ የሚባል መሰናዶ አየር ላይ አውሏል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ባሉ ክልሎችን ተዘዋውሮ ሰርቷል፡፡
አዲስ አበባ ፣100ኛ አመቷን ባከበረችበት በ1979፣  የአዲስ አበባን ታሪክ በጊዜው ከነበረችበት እድገት ጋር አቀናጅቶ፣ የአንድ ሰዐት ተኩል ፕሮግራም ሊያቀርብ ችሏል፡፡
 ኢህአዴግ በ1983 ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላም የቀይ ሽብር ተጠቂዎችን በተመለከተ  ፕሮግራሞች አቅርቧል፡፡ ምን ያህል መሰናዶዎች አየር ላይ እንዳዋለ ባያስታውስም ብዙ መሆናቸውን ግን ያውቃል፡፡
እሸቴ ፣ቀደም ብሎ በየካቲት መጽሄት ላይ፣ በታሪካዊ ጽሁፎች ራሱን የቃኘና እና ንባቡም የተጠናከረ ስለነበር፣ ቴሌቭዥን ሲገባ፣ የዶክመንተሪ ስራዎችን ምርጥ አድርጎ ለማቅረብ ብዙም አዳጋች አልሆነበትም፡፡
ለ5 አመት ገደማ ኢቲቪ ሲሰራ አርታኢውን አስፋው ኢዶሳንና ነቢዩ ኢያሱን ያስታውሳል፡፡  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሚሰራበት ጊዜ በርካታ ባልደረቦቹን እና አለቆቹን አይዘነጋም፡፡
                እሸቴ እና ሪፖርተር 
 አቶ አማረ አረጋዊ፣ በ1987  ‹‹ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሴንተር›› ብለው ሪፖርተር ጋዜጣን ሲጀምሩ፣ ከመስራች ጋዜጠኞች አንዱ እሸቴ አሰፋ ነበር፡፡ አቶ አማረ አረጋዊ፣ ቀደም ብሎ የኢቲቪ የስራ ሃላፊ ፣በነበሩበት ጊዜ፣ የእሸቴን ችሎታ ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር፣ አብሯቸው እንዲሰራ፣ ግብዣ አቀረቡለት፡፡ እሸቴም አይኑን ሳያሽ፣ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ስራ ጀመረ፡፡ በወቅቱ ሰሎሞን አባተ፣ ከበደ ደበሌ ሮቢ የመሳሰሉ ጋዜጠኞች ሪፖርተርን ከመሰረቱት መካከል የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡
እሸቴ በአዘጋጅነት ለአንድ አመት ከሰራ በኋላ፣ ሰሎሞን አባተ፣ የምክትል ዋና አዘጋጅነቱን ቦታ ሲተው፣ እሸቴ ከ1989 መስከረም ወር አንስቶ የሪፖርተር ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኖ ስራ ጀመረ፡፡  ጋዜጣዋን ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ ለመምራት የበኩሉን ጥረት አድርጓል፡፡
 ዜናዎችን መዘገብ፣ የተሰሩ ዜናዎችን መከታተል፣ጋዜጠኞችን ማሰማራት፣  የአርትኦት ስራዎችን በብቃት ማከናወን… ከእሸቴ የሚጠበቅ  ነበር፡፡  በጊዜው የሰው ሀይሉ በጣት የሚቆጠር ስለነበር እሸቴ ራሱ ትንታኔዎችንና ዘገባዎችን ይሰራል፡፡  በተለይ የፖለቲካ እና የነጻ  አስተያየት አምዶች በአብዛኛው ተሰናድተው ለንባብ ይበቁ የነበረው በእሸቴ አማካይነት ሲሆን ጽሁፎቹንም፣ ሶስት በሚሆኑ የብዕር ስሞች ነበር የሚያቀርባቸው፡፡፡፡
 ሪፖርተር ጋዜጣ፣ በወቅቱ በብዙዎች ዘንድ ተአማኒነት የነበረው የህትመት ውጤት ነበር፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው፣ እነ እሸቴ የስራ መሪ በነበሩ ጊዜ መስመር የያዘ፣ ሙያዊነትን የተላበሰና  በእውቀትና በእውነተኛ መረጃ  የተቃኘ ጋዜጠኝነት  እንዲኖር በማድረጋቸው የተነሳ ነው፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ለ26 አመት አንድም ሳምንት ሳይቋረጥ እስከዛሬ ለመታተም የቻለው፣ በመጀመሪያ በእነ እሸቴ የተቃኘ እና የተገራ በመሆኑ ነው የሚሉ አሉ፡፡ እርግጥ ነው የመስራቹ  የአቶ አማረ አረጋዊ በሳል አመራር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተቀመጡት ባለሙያዎችም  ብስል የሙያ ሰዎች ነበሩ፡፡
 እሸቴ፣ ከሪፖርተር ጋዜጣ በተጨማሪ፣ ሪፖርተር መጽሄት በ1989 ስትመሰረት በምክትል ዋና አዘጋጅነትና በዋና አዘጋጅነት ተመድቦ፣ አቅሙን ሳይቆጥብ ሰርቷል፡፡ አቶ አማረ አረጋዊ ስለ እሸቴ ችሎታ ሲናገሩ በንባብ የደረጀ ለሚድያ የተፈጠረ ነው ይሉታል፡፡ ስነ-ምግባር የተላበሰ የጋዜጠኝነትን ሙያ ያስከበረ እና ከሪፖርተር ጋዜጣ አመርቂ ስኬት ጀርባ ያለ የማከብረው ሰው ነው ሲሉ እሸቴን በአጭሩ ገልጸውታል፡፡ በሪፖርተር መጽሄት ላይ ከእሸቴ ጋር አብሮ  የሰራው ተፈሪ መኮንን በበኩሉ ከእሸቴ  መስራት በጣም እንደሚያረካው ይናገራል፡፡ ለምን ቢባል እሸቴ አሰፋ እውቀትን የታጠቀ ለትጋት ምንጊዜም ራሱን ያዘጋጀ ባለሙያ ስለሆነ ነው ሲል ተፈሪ ሀሳቡን ይገልጻል፡፡
እሸቴና ሸገር ሬዲዮ 
 እሸቴ ፣ በሸገር 102.1  ኤፍ ኤም ሬዲዮ፣ በቅዳሜ ‹‹መቆያ›› መሰናዶው ባለፉት ዘጠኝ አመታት ባስተላለፋቸው ዝግጅቶች፣ ብዙ አድማጮችን አፍርቷል፡፡ የውጭ ሀገር፣ መሪዎችን፣ታዋቂ ሰዎችንና ተቋሞችን፣ ግለ-ታሪክ፣ በብዙ ንባብና ማስረጃዎች የደረጁና የሚደመጡ ዝግጅቶችን በማቅረብ ላይ ነው፡፡ ስለ ሞሳድ ፤ ስለ ቶማስ ሳንካራ ፤ ስለ ሁጎ ሻፌዝ ፤ ስለ ጄኔራል ደጎልና ስለ ሌሎችንም በርካታ  መሰናዶዎችን አየር ላይ አውሏል፡፡
 የዜና ዘገባዎችንም ይተነትናል፡፡
በሸገር ኤፍ ኤም ራዲዮ አሁንም በዋና አዘጋጅነት እያገለገለ ነው፡፡
 ማጠቃለያ 
ጋዜጠኛ እሸቴ አሰፋ፣ በጋዜጣና በመፅሔት ፤ በሬድዮ እና በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት ሰርቶ የሚያውቅ በመሆኑ ሁለገብና በሙያው ላይ ከፍ ያለ የእውቀት ደረጃ ላይ መድረስ ችሏል፡፡ ከ30 አመታት ቀደም ብሎ ገና 20ዎቹ መጀመሪያ እድሜው ላይ፣ በትጋት የጀመረው የጋዜጠኝነት ሙያ፣ ዛሬ የተከበረ ባለሙያ በጥናት ላይ ተመስርቶ መስራት ልክ እንደ እሸቴ አይነት ጋዜጠኛን ይፈጥራል፡፡
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆነው እሸቴ፣ ሙያውን በጣም ከማክበሩ የተነሳ ራሱን ከማሳወቅ ይልቅ ስራው ላይ ብቻ አተኩሮ ብዙዎችን ሲያሳውቅ አመታት ተቆጥረዋል፡፡አድርጎታል፡፡ ከጋዜጠኝነት ሙያ ውጭ አስቦም ሰርቶም አያውቅም፡፡  እሸቴ ዛሬም ይሰራል እንጂ፣ ስለ ራሱ መናገር አይወድም፡፡
 ይህ ብዙ ያልነገረለት በሳል  ባለሙያ  ስለ ሀገራችን የ30 አመት የሚድያ ታሪክ ሲወሳ፣ የእርሱም አሻራ አብሮ መነሳቱ የግድ ነው፡፡ በመሆኑም መጪው ትውልድ በእርሱ የትጋት መስመር እንዲሄድ የእሸቴን ታሪክ በጨረፍታ  አቀረብነው፡፡ /ይህ ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ተጽፎ የተጠናከረ ሲሆን ጊዜውም ሀሙስ ሰኔ 10 2013 ነው፡፡/
Filed in: Amharic