>

ሊቁ የኔታ ጌታቸው ኃይሌ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ጸሎትና ዝክር ተደርጎላቸዋል!!! (መርሻ አለህኝ ዶ/ር)

ሊቁ የኔታ ጌታቸው ኃይሌ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ጸሎትና ዝክር ተደርጎላቸዋል!!!
መርሻ አለህኝ ዶ/ር

*…በመርሐ ግብሩ ስለሊቁ አንዳንድ ነገሮች የመናገር ዕድል ከገጠማቸው ሰዎች አንዱ ነበርኩ። የሚከተለውን ንባብ አቅርቤአለሁ
         ፕሮፌሰ ር ጌታቸው ኃይሌ፤ ሐራሲ መጻሕፍት    – (1924-2013 ዓ/ም)
በመጀመሪያ ይህ ዕድል ስለተሰጠኝ በእጅጉ አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ባለፈው ማክሰኞ ለት ማታ ደውለው በዚህ ቅዱስ ቦታ ለታላቁ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ መታሰቢያ ጸሎት እንደሚደረግ፤ በዚህም በተለይ ሊቁ ስም ባሰሩበት የግእዝ ጥንታውያት መዛግብት ጥናት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በአጭሩ እንዳቀርብ ሲያዝዙኝ፤ ስለኹለት ነገር ላቅ ያለ ደስታ ተሰምቶኛል። የመጀመሪያው ሊቁ አስቀምጠውት ባለፉት አካዳሚያዊ ሚዛን እዚህ ግባ የማልባል ትንሽ ሰው ሳለሁ፤ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ኩራት ስለሆኑት መምህር አስተዋጽኦ በትንሹም ቢሆን የማውሳት ዕድል በማግኘቴ ነው። ኹለተኛው ምክንያት፤ እኛ የዕውቀት ልጆቻቸው ሳንጠግባቸው የተለዩንን የእኒህን ሊቅ መታሰቢያ እያደረግንበት ያለው ይህ ቅዱስ ቦታ፤ በራሳቸው በሊቁ አገላለጽ ከ«ሕይወት ዘመን ወዳጃቸው የብራና መጽሐፍ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ  ዐይን ለዐይን ተጠቃቅሰው፣ እጅ ለእጅ ተጨባብጠው የተዋወቁበት፣ እስከመቃብር የዘለቀ ፍቅርም የመሠረቱበት ቦታ» ላይ መሆኑ ነው።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ንባብን የተማሩት ከዚሁ ቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ በነበረ አንድ መቃብር ቤት ይኖሩ ከነበሩና የጤና መታወክ ከጠላት ወረራ ጋር ተባብሮ ከነበሩበት የኑሮ ከፍታ ዝቅ ካደረጋቸው አባታቸው ግራዝማች ኃይሌ ወልድየስ ጋር ነበር። ታዲያ በጊዜው መልክዐ ፊደልን ለይተው ንባብ የተማሩበት በዚሁ ግቢ በነበረ አንድ የብራና መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ተአምረ ኢየሱስ ነበር። ይህን መጽሐፍ ፕሮፌሰር ጌታቸው «ማራኪዬ» ይሉት ነበር።
የፕሮፌሰር ጌታቸው የምርምር ጉዞ ረጅም ነው። ርዝማኔውም ከእሳቸው ዕረፍት ጋር የሚገታ አይመስልም። ዐረፉ ብለን ይህንን መታሰቢያ እያደረግንላቸው ባለበት በአሁኑ ሰዓት እንኳ በርከት ያሉ የምርምር ሥራዎቻቸው ሊታተሙ በማተሚያ ቤቶችና በአሳታሚዎች እጅ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም ለቁጥር የሚያታክተውን የእኒህን ሊቅ አካዳሚያዊ ሥራ እንደዚህ ባለ አጭር ንግግር ቀንብቦ ማስቀመጥ አይቻልም።
የሊቁን አካዳሚያዊ ሥራዎች በሚመለከት ሁለት ምንጮች አሉ። አንደኛው ራሳቸው ሊቁ አንድ አፍታ ላውጋችሁ ብለው ያሳተሙት የዜና ሕይወት መጽሐፋቸው ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው በዚህ መጽሐፋቸው ከገጽ 243 እስከ 246፤ «ካልታተሙት የግዕዝ መጻሕፍት ውስጥ ከሠላሳ በላይ የሚሆኑትን አጥንቼ ከእንግሊዝኛ ትርጉሜ ጋር አሳትሜአለሁ። ከዚህ በታች ለምሳሌ ያህል እነዚህን ልዘርዝር» በማለት 33 የሚሆኑትን ጥናቶቻቸውን ዘርዝረዋል። ሁለተኛው ምንጭ ደግሞ እሳቸው በተመሰከረለት ትኅትናቸው  ቁጥሩን ዝቅ አድርገው ያቀረቡትን ዝርዝር ላቅ ባለ ሁኔታ ያቀረበው መዘርዝራዊ ጥናት ነው። ይህ ፕሮፌሰር ባውዚና ቶማስ ራቨ  በተባሉ ሊቃውንት Studies in Ethiopian languages, literature, and history: festschrift for Getatchew Haile, presented by his friends and colleagues (2017) በተሰኘና ለሊቁ አስተዋጽኦ ዕውቅና ለመስጠት በተዘጋጀ መድብል ላይ «A selected bibliography of the publications of Getatchew Haile» በሚል ርዕስ ከገጽ 609-619 ያሳተሙት መዘርዝር ነው። ይሁንና ይኸኛው መዘርዝራዊ ጥናትም ቢሆን ያተኮረው በርዕሱ እንደተገለጠው «የተመረጡ» ባላቸው ጥናቶች ላይ ብቻ ነው።
በእነዚህ መዘርዝራዊ የጥናት ምንጮቸ መሠረት ሊቁ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ 163 የሚሆኑ ጥናቶችን በታወቁ የምርምር መትልው (series)፣ መጽሔቶች (journals)፣ መድብሎች (proceedings) ወዘተ. አሳትመዋል። ከላይ የጠቀስኳቸው ምንጮች ሊቁ ስማቸው ባልገነነና አካዳሚያዊ ባልሆኑ ጥናቶች ያሳተሟቸው በርካታ ጥናቶችን አያካትትም። የሦስተኛ ዲግሪ ጥናታቸውን ጨርሰው ወደአገራቸው በመመለስ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ባገለገሉባቸው ጥቂት ዓመታት ብቻ አዲስ ዘመንና The Ethiopian Herald ን ጨምሮ በልዩ ልዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ያሳተሟቸው ውርጅናል ጥናቶች ከላይ በተጠቀሱት መዘርዝራዊ ጥናቶቹ አልተመዘገቡም።
ተመዝግበው ከተገኙት 163 ጥናቶች ውስጥ 23 የሚሆኑት መጻሕፍት ናቸው። ከእነሱም ውስጥ ሰባቱ በማይክሮፊልም ተነሥተው ሊቁ «የእኔ ዓለም» ብለው ይጠሩት በነበረው በሀገረ አሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት በኮሌጅ ቪል መንደር ቅዱስ ዮሐንስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው ሂል የብራና መዛግብት ቤተ መዘክርና ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ከተቀመጡት የግእዝ መጻሕፍት የተወሰኑትን ይዘት ያስተዋወቁባቸው ካታሎጎች ናቸው። የቀሩት ኅትመቶች ሊቁ የልዩ ልዩ ብራና መጻሕፍትን ምሥጢራት ከማድነቅ ውጪ ማንም ተምሮ ሊተገብረው በማይችል ዘዴና ሥልት አዋልደው ያቀረቡባቸው መጻሕፍት ናቸው። 36 የሚሆኑት ደግሞ በታወቁትና በነገረ አትዮጵያ ላይ አትኩረው በተዘጋጁ መዛግብተ ጥበብ (Encyclopedia)  ተካተው የታተሙ ጥናቶች ናቸው።
ጥናት፣ ምርምርና ኅትመትን በተመለከተ የፕሮፌሰር ጌታቸውን ጉዞ ስንመለከት ወደ መነሻው አካባቢ የምናገኘው ሥነ ልሳን የተሰኘውን የቋንቋ ሳይንስ ነው። ሊቁ በሀገረ ጀርመን ቱቢንገን ዩኒቨርሲቲ በዶክትሬት ዲግሪ ማሟያነት በጀርመንኛ ሠርተው ያቀረቡት ጥናት የግዕዝን ግስ መንገድ ከሌሎች የሴም ቤተሰብ ቋንቋዎች ጋር አነጻጽረው በግሩም ሁኔታ ያሳዩበት Das verbalsystem in Äthiopischen: ein morphologischer vergleich mit den orientalischen semitischen sprachen (1962) ያሉት ሥነ ልሳናዊ ጥናት ነበር።  በዚህ ጥናት ገና ከጅምሩ የሊቁን የቋንቋ ችሎታ እናያለን። በአንድ አፍታ ላውጋችሁ ገጽ 94 እንደነገሩን ጀርመን በሚገኘው ዩኒቨርሲቲያቸው እንደደረሱ እራሳቸውንም ባላረካ የጀርመንኛ ቋንቋ ኮርስ እንዲሳተፉ ቢደረግም፤ በግላቸው ኮንት የተባለ «መናጢ» ጀርመናዊ ወጣት ቀጥረው ቋንቋውን በሚገባ ተምረው የዲግሪ ማሟያ ጽሑፋቸውን በቋንቋው ጽፈዋል። ጥናታቸውም ግእዝን፣ አረብኛንና ዕብራይስጥን ጨምሮ ሌሎች የሴም ቋንቋዎችን የግስ አካሔድ ማነጻጸር በመሆኑ የእነዚህ ቋንቋዎች አጥጋቢ ዕውቀት እንደነበራቸው መረዳት ይቻላል። በመሆኑም ፕሮፌሰር ጌታቸው በጥንታውያት መዛግብት ጥናት (Philology) ዘርፍ የተሰማራ አንድ ባለሙያ ሊኖሩት ከሚገባው ችሎታዎች አንዱና ዋናው የሆነውን የቋንቋ ችሎታ በማሟላት ቀድመው ያስመሰከሩ ነበሩ ማለት ይቻላል።
ፕሮፌሰር በዚህ መንገድ የጀመሩት ሥነ ልሳን ተኮር ጥናትና ምርምር ለተወሰኑ ዓመታት ቀጥሎ ነበር። ከተመረቁበት እ.ኤ.አ. 1962 ዓ.ም ጀምሮ ረዘም ላሉ ዓመታት ተመራምረው ጽፈው ያሳተሟቸው ጥናቶች፤ በተለይም የአማርኛ ቋንቋ ልዩ ልዩ ጠባያት ላይ ያተኮሩ ነበሩ።  በዚህ የሊቁ የጥናትና ምርምር የሕይወት ምዕራፍ ካሳተሟቸው ነገር ግን በዬትኛውም የሥራቸው መዘርዝር ጥናት ውስጥ ሲወሳ ያላየሁት ዋጋው እጅግ ከፍ ያለ ጥናት በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲና ቤተ ክህነት ምሁራን መካከል ተነሥቶ በነበረው የፊደል ይቀነስ ጆሮ አደንቁር ክርክር ወቅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተከታታይ እትሞች ያወጡት እጅግ ጠቃሚ ጥናት ነው።
ፕሮፌሰር ጌታቸው እስከ ዕለት ዕረፍታቸው ድረስ የዕድሜአቸውን አመዛኝ ክፍል ከወሰደው የግእዝ መዛግብት ጥናት (Geez Philology) ጋር የተዋወቁት ሁላችንም በምናውቀው እሳቸውም ለምክንያት ብለው ሲገልጹት በነበረው ሰበብ የተነሣ ከሀገራቸው ወጥተው አሜሪካን አገር ከሚገኘው ሂል የብራና ማይክሮፊልም መዛግብት ቤተ መዘክርና ቤተ መጻሕፍት ሲደርሱ ነበር። ሊቁ በዚያ ቦታ ተከማችተው የነበሩ የግእዝ መዛግብትንና የእሳቸውን መገናኘት ሲያወሱ፤  «ለሆዳም በሬ ጭድ ያዝለታል ይሉ ነበር»። ዘመኑ በወለደው ዕብደት የተነሣ በተተኮሰባቸው ጥይት ተጎድተው እስከመጨረሻ ትንፋሻቸው በሰቀቀን ያነሷት የነበረች አገራቸውንና ሕዝቧን ለቀው ቢሄዱም፤ በእሳቸው አገላለጽ አዛኝቱ እመቤቲቱ ድንግሊቱም ማርያም ያገናኘቻቸው ለብዙ ሺ ዓመታት በትጉኃን አበው ከተጻፉና ከተቀዱ የግእዝ መጻሕፍት ጋር ነበር። ፕሮፌሰር ጌታቸው ከባለቤታቸውና ልጆቻቸው ቀጥሎ በዚያ ያገኟቸውን መጻሕፍት የሕይወት ዘመን ጓደኞቻቸው፣ ወዳጃቸው፣ አማካሪያቸው አድርገው እያጠኑና እያስጠኑ ቆይተዋል። ለተለዩአት ሀገራቸው የነበራቸውን ሰቀቀን በማስታገስ ረገድ እነዚህ መጻሕፍት የዋሉላቸውን ውለታ በአንድ አፍታ ላውጋችሁ (ገጽ 234) ሲያወጉን፤ «ኢትዮጵያን ማጣቴ እንደፈራሁት አልሆነም። በአካል ባጣትም በመንፈስ አልተለያየንም። ውሎዬ ቀኑን ሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ። አንገቴን ደፋ አድርጌ የደብረ ሊባኖስን፣ የደብረ ሐይቅን፣ የላሊበላ ገዳማትን መጻሕፍት ሳነብና ከመነኮሳቱ ጋር «ሳወራ» መንፈሴ ምንም ሳይቀር ጭልጥ ብሎ እነሱው ዘንድ ይሔዳል፤ እንደአጋጣሚ ሰዎች በእንግሊዝኛ እያወሩ በአጠገቤ ሲያልፉ ስሰማ፤ «ደሞ ደብረ ሊባኖስ፣ ደብረ ሐይቅ፣ የላሊበላ ገዳማት ከመቼ ወዲህ ነው እንግሊዝኛ የሚወራባቸው?» እስከማለት እደርሳለሁ።» ብለዋል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው አዛኝቱ ወደሀገረ አሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ወስዳ በዚያ ካሉ ዕልፍ መዛግብት ጋር ካገናኘቻቸው ጀምሮ፤ ለእኛ በአካል አግኝተን ማብራሪያ ጠይቀን ለተማርንባቸው ቀርቶ እስከ ኅልፈተ ዓለም የሚመጣው ትውልድ እያነበበ የሚማርባቸው ዘመን ተሻጋሪ (Master Piece) ጥናቶችን አጥንተው አሳትመው አበርክተውልናል። በነገረ መዛግበት ግእዝ በዬትኛውም ደረጃና ግለሰብ የሚሠራ ጥናት የሳቸውን ስምና ሥራ ያላጣቀሰ አይገኝም።
ሊቁ በዚያ ቦታ አጥንተው ያሳተሟቸውን ጥናቶች በሁለት መክፈል ይቻላል። የመጀመሪያውና ዋናው በዚያ ያሉ መዛግብትን ሌላው ዐውቆ ጥናትና ምርምር እንዲያደርግባቸው የሚጋብዘው የመዛግብት ዝርዝር ከሙሉ የይዘትና የቁመና ገለጻ ጋር የሚያቀርበው ካታሎግ ሥራቸው ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው ለንደን ሕክምናቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ ኮሌጅቪል የሄዱት ይህንን ሥራ የመሥራት ሐላፊነት ተቀብለው ነበር። እግራቸው ቦታውን ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት ድረስ ሰባት የሚሆኑ የግእዝ መጻሕፍት ካታሎጎችን አሳትመዋል። እነዚህ ካታሎጎች በዚያ ተከማችተው የሚገኙ የግእዝ መጻሕፍትን ለተመራማሪዎች በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል፤ ወደፊትም ይጫወታሉ።  በሁለተኛው ክፍል የምናገኛቸው የሊቁ ሥራዎች፤ ከላይ የተጠቀሱ ሥራዎቻቸውን ሲያዘጋጁ ከመጻሕፍቱ ጋር በሚያደርጓቸው ትውውቅ በሚያስገርም ችሎታ ፈልቅቀው እያወጡ ከእንግሊዝኛ ትርጉምና ትንታኔ ጋር ያሳተሙልን በርካታ መጻሕፍትና ጽሑፎች ናቸው። በዚህ ረገድ ሊቁ ያሳተሟቸው ሥራዎች በዬትኛውም ተመራማሪ ያልተደረሰባቸው፤ አዲስና ውርጅናል ሥራዎች ናቸው። በዚህ የተነሣ ብዙዎቻችን እነዚህን ሥራዎቻቸውን በማንበብ የጥናትና ምርምር ዳዴአችንን ጀምረናል።  ወደፊትም የሚመጣው ትውልድ በተመሳሳይ እንደሚጠቀምባቸው ጥርጥር የለውም።
እኔ ሦስተኛ የምለው የመጨረሻ የምርምር ሕይወታቸው ምዕራፍ፤ የጥናት በረከታቸውን ለቀረው ዓለም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማበርከታቸውን ሳይተው፤ ኢትዮጵያውያን የቀደሙ ሊቃውንት አባቶቻችንን ዕውቀትና ጥበብ እንድናውቅ በአማርኛ ቋንቋ መጻሕፍትንና  አጫጭር ጽሑፎችን በማዘጋጀት አሳትመው ያበረከቱበት ምዕራፍ ነው። በዚህ ምዕራፍ በተለይ በእሳቸው የሙያ ዘርፍ ለተሰማራን እንደ መስታወት ከምንወስደው አንድ አፍታ ላውጋችሁ (2000 ዓ.ም) ዜና ሕይወት መጽሐፋቸው ጋር እንደ ባሕረ ሐሳብ ()፣ ደቂቀ እስጢፋኖስ ()፣ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች ()፣ ግዕዝ በቀላሉ ()፣ ስለግዕዝ ሥነ ጽሑፍ የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስታወሻዎች () የመሳሰሉ አስተማሪ መጻሕፍትን በማበርከት፤ ምርምር በፈረንጅ አፍ ብቻ ለሚመስለን ጆሮ ጠገቦች በአማርኛ ቋንቋችን እንዴት ተመራምሮ ማቅረብ እንደሚቻል አሳይተውናል። ዕረፍታቸውን ሊጠራ እጃቸው ዝሎ አልጋ ላይ ከመዋላቸው በፊት ጊዜውን ተሻምተው አዘጋጅተው ለኅትመት የላኳቸው መጻሕፍትና ጽሑፎች እንዳሉም ዐውቃለሁ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በሕይወት ዘመናቸው ያስተማሩን ባሳተሟቸው መጻሕፍትና ጽሑፎች ብቻ አይደለም። በአካዳሚያዊ ሥነ ምግባራቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናቸውና ለሀገራቸው በነበራቸው ፍቅር፣ በቤተሰብ ሕይወታቸው፣ ወዘተ. ሁሉ ነበር። ሌላውን ሁሉ ትተን አካዳሚያው ሥነ ምግባራቸውን ብናይ፤ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሊጠኑ ቀርቶ ሊዘረዘሩ የሚያዳግቱ ሥራዎችን ሠርተው አበርክተው ሳለ፤ ራሳቸውን ያላስታበዩ፣ ይልቁንም የእግራቸውን ጫማ ጠፍር እንኳን መንካት የማንችለውን ልጆቻቸውን አስተምሩኝ ብለው የሚጠይቁ፤ መጻፍ ቀርቶ ገና አንብቤ ያልጨረስኩ ተማሪ ነኝ እያሉ ራሳቸው ሲገልጹ የነበሩ ትሑት አባታችን ነበሩ። አንድ አፍታ ላውጋችሁ መጽሐፋቸውን ሳነብ በእጅጉ ካስገረሙኝ ግለ ገለጻዎቻቸው አንዱ «የባለሞያ እርዳታ አልጠየኩም እንጂ የማንበብ ችግር (dyslexia) እስከአሁን ድረስ አለብኝ፤ በዚያም ብዙ ተጎድቼአለሁ» (ገጽ 19)  ያሉት ነው። ኅትመት ያልገቡ፣ በፎቶ ከመቀዳታቸው የተነሣ ለማንበብ ዓይን የሚያደገድጉ ጀርባ የሚያጎብጡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትን አገላብጦ አንብቦ ያስተዋወቀ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ መጻሕፍትንና የጥናት ጽሑፎችን ያሳተመ ሰው የማንበብ ችግር አለብኝ ሲል ቢገኝ፤ እጅግ የሚያስገርም ትሕትና ነው ብሎ ከማለት ባለፈ ምን ተብሎ ሊገለጽ ይችላል?  በእርግጥ ይህንን ትሕትና ያገኙት መጽሐፋቸውን ከመረመሩላቸው ሊቃውንት ነው። ድሮስ ብራና ፍቆ አለስልሶ ብርዕ ቀርጾ በጅ ሊያነሱት የከበደ መጽሐፍ ጽፎ ያበረከተ ሊቅ «እስመ አንተ ተአምር አነ ኀጥእ ወአባሲ፤ ኅጢአተኛና በደለኛ መሆኔን ታውቃለህና» እያለ ብዙ ጊዜ ሳይጠቅስ ቢጠቅስም ስመ ጥምቀቱን አስቀምጦ የሚዘጋ ሊቅ ሥራን ሲያነቡ የኖሩ አባት እንዴት ይህን ሠራሁ ይበሉ?
የግል ገጠመኜም ቢሆን ከላይ ካነሣሁት የሊቁ ትሕትና ጋር የሚገናኝ አጋጣሚን በማንሣት ንግግሬን ልቋጭ። በአውሮጳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም በጋ ወራት ወደኮሌጅ ቪል በመሔድ ሊቁን ለዐራተኛ ጊዜ የማግኘት ዕድል አጋጥሞኝ ነበር። ከቦታው በደርስኩ ማግሥት በጠዋት ወደቤተ መጻሕፍቱ ሄድኩ። ቀድመው የደረሱት የቤተ መዘክሩና ቤተ መጻሕፍቱ ሠራተኞች ሰብሰብ ብለው እንኳን ደህና መጣህ እያሉ ስንጫወት ፕሮፌሰር ጌታቸው ደረሱ። ከአሜሪካውያኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው ተለይቼ በመሄድ የፕሮፌሰር ጌታቸውን ጉልበት ሳምኩኝ። ለእኔ ለታላቅ የሚቀርብ የአክብሮት መግለጫ ሰላምታ ነው፤ ፈረንጆቹ ግን ባደረኩት ተደነቁ። ፕሮፌሰር ጌታቸው በአፀፋው ግንባሬን ከሳሙኝ በኋላ ሰላምታ ለሁሉም ሰጥተው የወንበር መኪናቸውን አስነሥተው ወደቢሮአቸው ገባን። ያልጠበኩት ሆነ። ፕሮፌሰር ጌታቸው አለቀሱ። ደነገጥኩ። ዕንባቸውን በማህረባቸው ከጠራረጉ በኋላ፤ እሳቸው ጉልበታቸውን የሚያስም ሥራ እንዳልሠሩ፣ በመሳሜ ምናልባት ደግ ያደረኩት አውራ ባሕላችንን ለፈረንጆች በማሳየቴ እንደሆነ፤ የልቤን መሻት ዐይቶ እግዚአብሔር ላደረኩት ዋጋ ይከፍለኝ እንደሆነ በታናሹ በእሳቸው እግር መሳም ሳይሆን እሳቸው ሲያነቧቸው የኖሩትን መጻሕፍት የጻፉትን ቅዱሳን አበው እንደማክበር ተቆጥሮልኝ ሊሆን እንደሚችል አስረግጠው ነገሩኝ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው፤
እርስዎ ያስከበሩንን ያህል ሳናስከብርዎ፤ ያከበሩንን ያህል ሳናከብርዎ፤ የኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያኗን ስም በዓለም መድረክ ከፍ እንዳደርጉልን እኛም ከፍ ሳናደርግዎ፤ እንደሊቅ በቃልም በመጣፍም ከማስተማር ሳይታክቱ፣ ድንገት በሚያሰቅቅ ሁኔታ የተለዩአትን አገርዎን ሳያዩ እንደናፈቋት፤ ስለምድሪቱና ሕዝቧ ዘወትር እንዳለቀሱ፣ እንደተሟገቱ፣ እንደጮሁ፤ ከአባትዎ ጋር በመቃብር ቤት ሆነው ተአምረ ኢየሱስን በማንበብ ከመልካም ወዳጅዎ የብራና ጽሑፍ ጋር ያስተዋወቅዎን ቅድስት ሥላሴን እንደተመኙት ስመው ካስተዋወከኝ ባልንጀራ ጋር ፍቅሬን አጽንቼ ይኸው እዚህ ደረስኩ በማለት ፍጹም መታመንዎን ሳይገልጹ ዐረፉ። እርስዎ አልቀረብዎትም፤ እኛ ግን ቀረብን፤ አገርና ቤተ ክርስቲያን ቀረባቸው። ዕረፍት ይገባዎታል። ይረፉ፤ ነፍስዎ ከቅዱሳኑ ጋር ሆና ትረፍ።
አመሰግናለሁ።
Filed in: Amharic