የግብጽ ወታደራዊ ክንድ እና የቀጠለው ጸብ አጫሪነቷ
ደረጀ መላኩ ( ሰብዓዊ መብት ተሟጋች)
እንደ መግቢያ
ከገነባችው የምጣኔ ሀብት አቅም አኳያ ( እጅግ ከበለጸጉት ሀገራት የምጣኔ ሀብት እድገት አኳያ ስወዳደር ለማለት ነው) በአሁኑ ዘመን ግብጽ ገቢራዊ እያደረገች ያለችው ወታደራዊ ግንባታ እንግዳ ነገር ነው፡፡ እንደ ብዙ የምእራብ ሀገራት የምጣኔ ሀብት ጠበብት ጥናት ውጤት ከሆነ የምጣኔ ሀብት እድገቷ መጠነ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና ብልጽግና ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ማድረግ ይጠበቅባት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በአስደናቂ ሁኔታና በፍጥነት ለወታደራዊ መሳሪያ ግዢና ለወተዳራዊ ስልጠና ከፍተኛ ባጀት በመመደብ እንቅስቃሴዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ በፕሬዜዳንት አልሲሲ የምትገዛው ግብጽ በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ አዳዲስ ዘ፣ናዊ መሳሪያዎች በመግዛትና በማስገባት ሶስተኛ ሀገር ለመባል በቅታለች፡፡ ለምንድን ነው ግብጽ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በመመደብ ወታደራዊ ጡንቻዋን የምታፈረጥመው ? ከየትኞቹ ሀገራት ጋር ነው ጦርነት ለመግጠም ያሰበችው ? የትኞቹ ሀገራት ናቸው ስጋት የሆኑባት ?
ግብጽ በወታደራዊ ጥንካሬ ከአለም ሀገራት ሁሉ በ12ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ማለት ከእርሷ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ምርት ወይም ከዜጎቿ የግለሰብ ገቢ 12 እጥፍ ከሚበልጡት ከጀርመን፣ ጣሊያንና ደቡብ ኮሪያን በመከተል መሆኑ ነው፡፡
ከአንድ ወር በፊት ታትሞ በወጣ የግብጽ እለታዊ ጋዜጣ ላይ ቀርበው ቃለ ምልልስ ያደረጉት የግብጽ ከፍተኛ የጦር አታሺዎች እንደተናገሩት ከሆነ ግብጽ ከጎረቤት ሀገራትም ሆነ ከሩቅ ሀገራት የሚመጡ አደጋዎችን ለመከላከል ብቃት ያላት ሲሆን ወደ ውስጥ ዘልቃ ጥቃት የማድረስ ወታደራዊ አቅም እንዳላት ተናግረዋል፡፡ በቀድሞው ፕሬዜዴንቷ አንዋር ሳዳት የነበረው ወታደራዊ ትምክህት በሁሴን ሙባረክ ግዜ ነበር፣ዛሬም በፕሬዴንት አልሲሲ ዘመነ መንግስት እየተደገመ ይገኛል፡፡
በታሪክ እንደምናስታውሰው የፓን አረብ አቀንቃኝ በነበሩት ናስር ግብጽ የመካከለኛው ምስራቅ የበላይ ለመሆን በብዙ ሞክራለች፡፡ በነገራችን ላይ በፓን አረብ ንቅናቄ( አብዮት) ምክንያት የስድሰቱ ቀን የአረብና እስራኤል ጦርነት መካሄዱን ከታሪክ እንማራለን፡፡ የስዊዝ ካናልም መከፈት ይሄንኑ ክስተት ተከትሎ ነበር የተከፈተው፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ የአረቡ አለም መሪ ለመሆን ጥረት ማድረግ የጀመረችው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1952 ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ ከወጣች በኋላና የነጻ ወታደራዊ መኮንኖች እንቅስቃሴ አባላት ስከልጣን ከጨበጡ በኋላ ነበር፡፡
አንዳንድ ግዜ ግብጽ የአረቡን አለም በበላይነት ለመቆጣጠር ከኢራቅ፣ሊቢያ፣ሶሪያ እና ሳኡዲ አረቢያ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ታደርግ ነበር፡፡ዛሬ የግብጽ ተጽእኖ እየቀነሰ ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ዛሬ ግዜው ተቀይሯል፡፡ ግዜው የእነ ሳኡዲአረቢያ፣ኤሚሬትስ፣ እና ኳታር ሆኗል፡፡ ከቅርብ አስርተ አመታት ወዲህ የግብጽ ኢኮኖሚ እየተዳከመ ስለመምጣቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኢኮኖሚ ድክመቱ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ የጂኦፖለቲካ መለዋወጥ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት ( ማለትም ሳኡዲአረቢያ፣ኤሜሬትስ እና ኳታር) የገንዘብ አቅም በመሃከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካው ቀንድና በሌላው አለም እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ነው፡፡
ምንም እንኳን ከእስራኤል ጋር ስምምነት ላይ ብትደርስም ( የካምፕዴቪድ ስምምነትን ልብ ይሏል)፣ ከተባበረችው አሜሪካ መጠነ ሰፊ የሚሊታሪና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ ቢጎርፍላትም፣ በወቅቱ ለግብጽ ከአረቡ አለም የተሰጣት ምላሽ በአካባቢው ግብጽ የነበራትን አቋም የጎዳ ነበር፡፡ በተለይም የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሀይሉ ከግብጽ ወደ እነ ሳኡዲአረቢያ፣ኤሜሬትስ እና ኳታር እንዲያጋድል ሁነኛውን ሚና ተጫውቷል፡፡ ( በተለይም ግብጽ ከእስራኤል አኳያ ባላት አቋም ማለቴ ነው)
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁነቶች ቢኖሩም ግብጽ ራሷን እንደ ጠቃሚ ሀገር፣ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር ከመቁጠር ተቆጥባ አታውቅም፡፡ ስለሆነም በዚህ ዘመን ግብጽ ታላቅ የሚሊተሪ ተቋም እየመሰረተች ያለችበት ሁነኛ ምክንያት ለራሷ (self-conception) የምትሰጠው ግምት ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ወይም ራሷን የአካባቢው ሃያል አድርጋ ስለምትቆጥር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እውነታው ለየቅል ነው፡፡ ግብጽ ጎረቤት ባለጋራ ወይም የተፈጥሮ ( ታሪካዊ) ጠላት የላትም፡፡ በሌላ አነጋገር ለአመታት የግብጽ የጸጥታ ስጋት የሆነ ጎረቤት ሀገር አጠገቧ የለም፡፡ ዛዲያ ለምንድን ነው ግብጽ ከሚገባት በላይ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን የምትታጠቀው በሚለተሪ ሳይንሰ እውቀት አኳያስ ከሌሎች ሀገራት ሁሉ ለምን ይሆን ቀድማ ለመራመድ የፈለገችው (በሚሊተሪ ሳይንስ እድገት ግስጋሴ ከእርሷ በኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጂ አኳያ ቀድመዋት ከሄዱት ከብዙ አውሮፓውያን ሀገሮች እየቀደመች መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) በነገራችን ላይ እንደ ብዙ የሚሊተሪ አዋቂዎች ጥናት ውጤት ከሆነ እንዲህ አይነት የሚለተሪ ጡንቻ ግንባታ የምትከውን ሀገር ወደ ፈሩን የሳተ ግምት ውስጥ ነው የምትዶለው፡፡ በተለይም ትልቁ የሀገሪቱ ስልጣን በወታደራዊ መኮንኖች ቁጥጥር ስር በወደቀች ሀገር ውስጥ በሚያስከፍል ሚለተሪ አድቬንቸር ውስጥ ልትዶል ግድ ይላታል፡፡
ከታሪክ እንደምንማረው ግብጽ በምትገኝበት የአለም ክፍል ውስጥ አንድም ጦርነት ተጀምሮ በድል የተጠናቀቀበት ግዜ የለም፡፡( በጦርነቶቹ አሸናፊም፣ተሸናፊም አልነበረም) ለዚህ በቂ ማስረጃዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ በመሬት ላይ ያለው እውነተና አንዲት ሀገር በዘመናዊ መሳሪያዎች መታጠቅ አኳያ ሰማየ ሰማያት ላይ መድረስ መሃከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ የኢራንና ኢራቅ ጦርነትን መጨረሻ ትተን የቅርቡን በየመን በሚታየው ትራጄዲ አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት ነው፡፡ ምስኪን የየመን ህዝብ ግን ምድራዊ ገሃነም ውስጥ ተዶለ፡፡ ያቺ በተፈጥሮ ዘይት ሀብት የታደለችው ሊቢያ ልጆች ጎራ ለይተው ጦርነት ገጠሙ በመጨረሻ ግን አልሆን ሲላቸው፣ወደ ልቦናቸው ሲመለሱ ቁጭ ብለው መነጋገር ጀምረዋል፡፡ በዚህ አለም ክፍል ማንም ከጦርነት ተጠቃሚ የሚሆን ሀገር የለም፡፡ በርካታ ውድመቶችን ያስከተሉ ጦርነቶችን በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ኢራቅ፣ሶሪያ፣ የመን ከፍተኛ የምዋለ ንዋይ ውድመትና የሰው ልጆች ስቃይ ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ ይሄ ሁሉ መአት የወረደው አግባብ ያልሆነ የሚሊተሪ ጡንቻን ለማሳየት በሚነሱ እብሪተኛ አገዛዞች ምክንያት እንደሆነ ልብ ማለት ይገባናል፡፡
ከላይ ከቀረቡት ማስረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የግብጽ አገዛዝ የሚያደርገው ፈሩን የለቀቀ ወታደራዊ ግንባታ ከመጨረሻው ውጤት መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ፍጹም የማይገናኝ መሆኑን ነው፡፡ ምናልባት ግብጽ አንድ ጦርነት ብትጀምር ሌሎች በርካታ ጦርነቶች በበርካታ የአከባቢው ሀገራት ውስጥ ይቀሰቀሳሉ፡፡ እነኚህ ጦርነቶች ደግሞ ወደ ጦርነት ውስጥ የተዶሉትን ሀገራት ሁሉ መጠነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ውስጥ ሚዘፈቃቸው ይሆናል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ማለቂያ ወደ ሌለው ጦርነት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ ልክ የፍልስጤም ህዝብ ከእስራኤል ጋር እንደሚያደርገው ግጭት ሊሆን ይቻለዋል፡፡
በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 2013 ፕሬዜዴንት ኤል-ሲሲ (particularly since President el-Sisi came into power in July 2013) የግብጽ መሪ ከሆኑ ወዲህ ጀምሮ ግብጽ የምታደርገው ወታደራዊ ግንባታ በእጅጉ ጨምሮ እንደሚገኝ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ስለሆነም አካባቢው ሀገራት ግብጽ ስላላት ወታደራዊ አቅም፣ልትወስደው ስለምትችለው ወታደራዊ እርምጃ በተመለከተ ወዘተ መመርመር፣ በንቃት መከታተል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡
ሀ.የግብጽ ወታደራዊ ጡንቻ በግብጽ የምጣኔ ሀብት ውስጥ
የግብጽ ወታደራዊ ተቋም የፖለቲካ ዘዋሪ ብቻ ሳይሆን፣በግብጽ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ ሁነኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የወታደሩን ክፍል ከፍተኛ ተጽእኖ ከምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ መለየት እጅጉን አስቸጋሪ ነው፡፡ ከግብጽ የፖለቲካ ታሪክ ላይ ለመረዳት እንደሚቻለው የግብጽ ከፍተኛ የጦር አታሺዎችና መሪዎች የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት በመዳፋቸው ውስጥ ስር ማድረግ የጀመሩት ከፕሬዜዴንት ጀማል አብዱል ናስር( President Gemmal Abdul- Nasser. ) ዘመነ መንግስት ጀምሮ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የግብጽ ወታደራዊ ተቋማት በማናቸውም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ እጃቸውን ከመዶላቸው ባሻግር፣በርካታ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ሸቀጣሸቀጦችንና የምርት አገልግሎት የሚሰጡ መሳሪያዎችን መርታሉ፡፡ ለአብነት ያህል የሆቴል ኢንዱስትሪዎችን፣የባህር ዳርቻ መዝናና ስፍራዎችን፣የአፓርትሜንት ግንባታዎችን፣ቅንጡ ቪላዎችን ይቆጣጠራሉ፡፡ ከዚህ ባሻግር ከባድ ኢንዱስትሪዎችን፣ የሲሚንቶ እና ብረታ ብረት ማምረቻዎችን፣የጂፕ፣ማዳበሪያና ፓስታ ፋብሪከዎችንና ሌሎች ፋብሪካዎች ጭምር ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር የነዳጅ ማደያዎች ሳይቀሩ በእነርሱ ቁጥጥር ስር የወደቀ ነው፡፡ ታላላቅ አውራ ጎዳናዎች የሚገነቡት በወተደራዊው የኮንስትራክሽን ክፍል ሲሆን፣የማእድናት ማውጣት ስራዎችንም ያከናውናሉ፡፡( የነዳጅ፣ጋዝና ታዳሽ የሃይል ምንጮች ይጠቀሳሉ፡፡)
የተሰማሩበት የምጣኔ ሀብት
- የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች
- ከታንክ ጥይት ጀምሮ፣ማደበሪያ፣እስፖርት ትጥቅና መሳሪያዎች፣ሲሚንቶ፣መኪናዎች.ወዘተ ወዘተ ያመርታሉ
- የግብጽ ወታደራዊ ተቋማት ከኢኮኖሚ ጥቅም አኳያ ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በነዳጅ ላይ ድጎማ ሲደረግ በቅድሚያ እነርሱ ናቸው ተጠቃሚዎቹ፡፡
- እጅግ ውብ እና ውድ ሆኑ የሪል ስቴት ግንባታዎችን በፊት መስመር ሆነው ይቆጣጠራሉ
- መንግስት ለሚሰጠው የኮንትራት ስራዎች አኳያ ከሌሎች መሰል የግል ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ቅድሚያው የእነርሱ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
- በፔትሮ ኪሚካል ኢንዱስትሪና በቱሪዝም ኢንዱስተሪ ውስጥ ሳይቀር ተሰማርተዋል
እንደ አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ጥናት እና ከላይ ከሰፈሩት እውነታዎች በመነሳት በግብጽ የምጣኔ ሀብት ውስጥ የአንበሳው ድርሻ የወታደራዊው ተቋም ነው፡፡ ሌሎች በርካታ የግልና አለም አቀፍ ድንበር ዘለል ካምፓኒዎች ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት በበለጠ ቢሰማሩም፣ ከግብጽ የሚሊተሪው ክፍል እኩል ለመወዳደር ይቸግራዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ከወታደራዊው ተቋም የጥቅም ግንኙነትና ቤተሰብ ካልሆነው በቀር አብዛኛው የግብጽ ተራው ዜጋ እኩል የምጣኔ ሀብት ተቋዳሽ እንዳልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህ ማለት አብዛኛው የግብጽ ህዝብ በድህነት ይማቅቃል ማለት አይደለም፡፡ የግብጽ መሪዎች ለግብጽ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ከማሟላት አልፈው ህዝባቸውን የተሻለ የኑሮ ደረጃ እንዳደረሱት መዘንጋት የለብንም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በርካታ ግብጽ የጦር መኮንኖች የራሳቸው የግል ድርጅት ባለቤቶች ለመሆን በቅተዋል፡፡ በብዙ ስራዎች ላይ አማካሪዎችም ናቸው፡፡ ግብጽ የቀድሞ ጄኔራሎች ሳይቀሩ ቁልፍ የስራ ቦታዎች ላይ ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል ከህዝብ ትራስፖርት እስከ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን፣የኢነትርኔት መስመር፣የቤቶች ግንባታ ተቆጣጣሪነት፣ ወዘተ ወዘተ በአብዛኛው ሃላፊዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሚሊተሪው ክፍል በርካታ ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ለሲቪሉ ህዝብ ሊያገለግሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችን ለማምረት በሚያስችሉ መንገዶች ሁኔታዎች ተመቻችቶለታል፡፡ ለአብነት ያህል በጣም ሰፊ የመንግስት መሬት ባለቤት ናቸው፡፡ በተለየ ሁኔታ ግብር ይቀነስላቸዋል፡፡ ወይም በሚሊተሪው ቁጥጥር ስር የወደቁ የማምረቻ ድርጅቶች ከግብር ክፍያ ነጻ ናቸው፡፡ በአጭሩ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2008 የአሜሪካ ኤምባሲ ባቀረበው ጥናት መሰረት የወታደሩን ክፍል ‹‹ ከፊል የንግድ ድርጅት›› የሚል ስያሜ የሚያሰጠው ይመስለኛል፡፡
in 2008 the American Embassy defined the army as a “quasi-commercial’ enterprise”.
እንደ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ጥናት ውጤት ከሆነ የወታደራዊው ተቋም እጅግ የዘመኑ መሳሪያዎችን በየጊዜው የሚታጠቅ እና የሀገሪቱን የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት የሚቆጣጠር ከሆነ፣የፖለቲካ ስህተት መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህም ባሻግር ስልጣንን ለብቻ መቆጣጠር፣እንዲሁም ወታደራዊ አምባገነንነት ይሰፍናል፡፡ አንዳንድ ግዜ የወታደር ስነልቦና ከሲቪል አስተዳደር ስነልቦና አኳያ የሚጣጣም አይደለም፡፡ እነርሱ የሚመሩት በወታደራዊ ሳይንስ ስነአመክንዮ ነው፡፡ለዚህ ሁነኛ ማሳያው በግብጽ ታሪክ ውስጥ የግብጽ ወታደራዊ ባለስልጣናት የግብጽን ሲቪል ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በሃይል ጨፍልቀው መቅጨታቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከፍተኛ የጦር አታሺዎች የጦር መሳሪያ ሃይል ክምችታቸው ከፍተኛ በሚሆንበት ጊዜ ወታደራዊ ጀብደኝነት ይሰማቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የመጨረሻው ውጤት ብዙ ጉዳትና እልቂት ቢያስከትልም ፣ወታደሮች ሁሉንም የህዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት ሀይልን በመጠቀም ነው፡፡
ለ. ወታደራዊ በጀት
እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2019 ጀምሮ የግብጽ አመታዊ ወታደራዊ በጀት ወደ 9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚደርስ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ( በነገራችን ላይ ይህ ከፍተኛ በጀት ለጦር መሳሪያ ግዢና ለወታደራዊ ሀይል ማፍሰስ ለአንዲት በማደግ ላይ ላለች ሀገር፣ ብልጽናን ለምትሻ ሀገር፣ ድህነትንና የስራ እጥነትን ሙለበሙሉ ችግሮች ሙሉበሙሉ መክላት ላልሆነላት ሀገር አላስፈላጊ ወጪ ነው፡፡)
ሐ.የግብጽ ወታደራዊ ተቋም ዛሬ
አንደ ወታደራዊ ጠበብት ጥናት ውጤት ከሆነ የግብጽ የምድር ጦር የተደራጀው በሜካናይዝድ ደረጃ ነው፡፡ ይህ የጦር ሀይል የተደራጀው ቀላል ጦርነት ለማድረግ አይደለም፡፡ የግብጽ የጦር ሀይል ተንቀሳቃሽ እና ከተቀናቃኙ ጦር በእጅጉ የላቀ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የግብጽ ምድር ጦር የተደራጀው በክፍለ ሀገሩ ደረጃ ሲሆን ከባድ መሳሪያ የታጠቀ በሜካናይዝድ የተከፋፈለም ነው፡፡ እንደ ወታደራዊ ጠበብት የጥናት ውጤት ከሆነ በምእራብ፣ሰሜን፣ደቡብ፣ማእከላዊ የጦር ክፍል፣ እንዲሁም ሁለተኛውና ሶስተኛው ወታደራዊ ክፍል ተብለው በሚታወቁ ክፍሎች ነው፡፡
የግብጽ የጦር ክፍሎች ደግሞ የግብጽ ምድር ጦር፣የግብጽ አየር ሀይል፣የግብጽ አየር መከላከያ እና የግብጽ ባህር ሃይል ተብለው የታወቃሉ
እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ 2010 እስከ 2016 ባሉት አመታት ውስጥ አራት ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች ባላቸው ክፍለጦሮች የተከፈለ ነበር፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2016 ደግሞ ሜካናይዝድ ክፍለጦሯ ከ ሰባት ወደ ስምንት አድጎ ነበር፡፡ሶስት የኤርወለድ ብርጌድ ጦርም አላት፡፡ በነገራችን ላይ የግብጽ ወታደራዊ ጡንቻ በፍጥነት መፈርጠም የጀመረው በቀድሞው የግብጽ መከላከያ ሚንስትር ዛሬ የሀገሪቷ ፕሬዜዴንት አበደል ፈታህ አል-ሲሲ (Abdel Fattah al-Sisi) ዘመነ መንግስት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ የግብጽ ወታደራዊ ሀይል ብዛት ከ438,000 እስከ 468,000 እንደሚደርስ ጥናቶች ያሳሉ፡፡( አንዳንድ ግዜ ይጨምራል፣ሌላ ግዜ ቁጥሩ ሊቀንስ ይችላል፡፡) በሌላ በኩል ግብጽ ሞዴላቸው modern M1 Abrams tanks የሆኑ ብዛታቸው ወደ 973 የሚጠጉ ታንኮች ታጥቃለች፡፡ ከዚህ ባሻግር ግብጽ ሩሲያ ሰራሽ የሆኑ ቲ-90 ታንኮችን ( Russian T-90 tanks) የሚገጣጥም ፋብሪካ ገንብታ ከ500 በላይ ታንኮችን ገጣጥማ ስራ ላይ አውላለች፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ቁጥራቸው ከ762 በላይ የሚሆኑ እና የተቀበሩ ጸረ ተሸከርካሪ ፈንጂዎችን የሚቋቋሙ MRAP (Mine Resistant Ambush Protected armored trucks የጦር ተሸከርካሪዎችን ከተባበሩት አሜሪካ ገዝታለች፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች በኢራቅና አፍጋኒስታን ጥቅም ላይ ውለው ውጤታማ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ግብጽም በሲናይ በረሃ አሸምቀው ሰላሟን የነሷትን የአይሲሲ( ISIS forces ) ሽብርተኞችን ለመዋጋት ጥቅም ላይ እያዋለቻቸው እንደምትገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2017 በርካታ ከባድ እና ዘመናዊ መሳሪያዎችን ከሩሲያ፣ደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ፣ደቡብ ኮሪያና ፈረንሳይ እንደ ገዛች የሚያሳዩ መረጃዎችን ከወታደራዊ የዜና ምንጮች ለማወቅ ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህል S-300VM (Antey-2500) antiaircraft systems የተሰኘ ሩሲያ ሰራሽ መሳሪያ ገዝታለች፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ ከ70,000 እስከ 80,000 ግድም የሚጠጋ ተጠባባቂ ጦር አሰልጥና አስቀምጣለች፡፡ ከእስራኤል አንጻር ግብጽ ያላት ኢኮኖሚ ደካማና የስራ እጥ ቁጥር ወጣቶቿ ከፍተኛ ቢሆንም፣ግብጽ ከመሃከለኛው ምስራቅ ሀገሮች መሃከል ከእስራኤል በመለጠቅ ዘመናዊና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአየር ሀይልና የአየር መከላከያ ተቋም ለመገንባት የቻለች ሀገር ለመሆን እንደበቃች የአለም ሀገራትን ወታደራዊ ተቋማት ከሚያጠናው አለም አቀፍ ድርጅት መረጃ ለማወቅ ይቻላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽ ኤል-ዳባ ተብሎ በሚጠራው ግዛቷየኒኩሌር ማብላያ ተቋም ለመገንባት ወገቧን ታጥቃ ከተነሳች ሰንብታለች፡፡ (el-Dab’a in the Marsa-Matruh area )
ግብጽ በሚከተለው መልኩ የአየር ሀይሏንና የባህር ሀይል ጦሯን ለማዘመን የሚከተሉትን እርምጃዎች ወስዳለች፡-
የአየር ሀይሏን ለማዘመን የወሰደችው እርምጃ
- ባለፉት 10 አመታት ውስጥ የተባበረችው አሜሪካ ስሪት የሆኑ እጅግ ዘመናዊ የአየር ሀይል ተዋጊ ጀቶች( F-16 aircrafts) ቁጥር ወደ 151 ከፍ ብሎ ይገኛል፡፡
- 50 MiG-29s( በግብጽ አየር ሀይል ውስጥ የመጀመሪያው ነው) እጅግ ዘመናዊ ጄት ገዝታለች
- እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር የፈረንሳይ ስሪት የሆኑ 24 ዘመናዊ ጄቶች ( French Raphael fighters )አፓሼ ሄሊኮፕተር Forty-six Apache attack helicopters
ከላይ ለመዘርዘር የሞከርኳቸውን እጅግ የዘመኑ የጦር ጀቶችና ሌሎች ቻይና ስሪት መሰራያዎች የታጠቀው ከአፍሪካ ሀገራትና ከመሃከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሁሉ የበለጠ ዘመናዊ የአየር ሀይል ለመገንባት ችላለች፡፡ ( ግብጽን በአየር ሀይል የበላይነት የምትበልጣት የበለጠ ዘመናዊ ጄቶችን፣ ማለትም እንደ ስተሊዝ ተዋጊ ጄቶችን (stealth fighters ) ሳይቀር የታጠቀችው እስራኤል ብቻ ናት፡፡ በነገራችን ላይ የተባበረችው አሜሪካ ሌሎች ከሰሃራ በታች ለሚገኙ ሀገራት እንድ ግብጽ አይነት እጅግ ዘመናዊ የአየር ሀይል ጀቶችን በሽጭም ሆነ በወታደራዊ እርዳታ መልኩ ለማቅረብ ፍላጎት የላትም፡፡ ለምን ?ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡
ስለሆነም ግብጽ ለምንድን ነው እጅግ የዘመኑ የጦር መሳሪያዎችን መታጠቅ የምትሻው? ብሎ መጠየቅ ምክንያታዊ ነው፡: ለምንድን ነው የተባበረችው አሜሪካ የኢኮኖሚ አርዳታን በተቃረነ መልኩ ( በነገራችን ላይ ግብጽ የኢኮኖሚ እርዳታ እንደሚያስፈልጋት በርካታ የምጣኔ ሀብት ጠበብት በጥናት ወረቀታቸው ላይ የጠቀሱት መራር እውነት ነው፡፡) ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ወታደራዊ እርዳታ በየአመቱ ለግብጽ የምትለግሰው ምክንያቱ ምንድን ነው ? እውን አብዝሃው የግብጽ ህዝብ የሚጠቀመው ከወታደራዊ እርዳታ ነው ወይንስ ዳጎስ ካለ የምጣኔ ሀብት እርዳታ ? የተባበረችው አሜሪካ የሞራል መሰረት ምንጩ ከየት ነው ?
የባህር ሀይሏ
- እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2014 ግብጽ ከፈረንሳይ ጋር የ1ቢሊዮን ዩሮ የግዢ ስምምነት በማድረግ የባህር ሀይሏን አዘምናለች
- እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2016 ከጀርመን እጅግ ዘመናዊ በርካታ ባህር ሰርጓ መርከቦችን ገዝታለች፡፡ ( ለአብነት ያህል ዶልፊን በመባል የሚጠራ ከእስራኤል ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ባህር ሰርጓጅ መርከብ ታጥቃለች)
- በተጨማሪ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2016 ላይ እጅግ የዘመኑ የባህር ሃይል የመጠቀምባቸው ፈጣን ጀልባዎችና መሳሪያዎችን በግዢ ሸምታለች፡፡
- ከተባበረችው አሜሪካ ሳይቀር ግዙፍ የጦር መርከብ ለመግዛት በመቻሏ ከመሃከለኛው ምስራቅ የአለም ክፍለ አለም ከሚገኙት ሀገራት ከእስራኤል በመለጠቅ እጅግ ዘመናዊ የባህር ሀይል ለመገንባት የቻለች ሀገር ስትሆን፣ ዛሬ እንደ ቱርክ የመሳሰሉትን ሀገራት ለመገዳደር በፍጥነት እየተራመደች ትገኛለች፡፡
- ግብጽ ላይ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት እንዲደርስባት ያደረገው ደግሞ ከፈረንሳይ በግዢ ያገኘችው ሂሊኮፕተር ተሸካሚው ግዙፍ መርከብ ነው፡፡ ግብጽ ከ11 በላይ ሂሊኮፕተር መሸከም የሚችል የጦር መርከብ ለመግዛት የቻለች ሀገር ናት፡፡
በነገራችን ላይ የግብጽ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ በአንድ ወቅት በመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው እንደተናገሩት ግብጽ የባህር ሀይሏን እጅግ በዘመኑ የጦር መርከቦች ባለቤት የምታደርገው፣ዘመኑ የዋጀውን መሳሪያዎች የባህር ሀይሏን የምታስታጥቀው የግብጽን የነዳጅ መሬቶችን ለመጠበቅና አሸባሪዎችን ለመዋጋት ነው የሚል መግለጫ ቢሰጡም በብዙ የፖለቲካ ተመልካቾች አኳያ የሰጡት ቃለ ምልልስ ፌዝ እንደሆነ ግምት አሳድሮ ነበር፡፡ በእውነቱ ለመናገር ይህ አስገራሚ ንግግር ነበር፡፡ ምክንያቱም የተፈጥሮ ጋዝ የሚገኝባቸውን ሜዳዎች ለመቆጣጠር ፈጣን ጀልባዎችና የረዥም እርቀት ተምዘግዛጊ ሚሲያሎች ጥቅማቸው እምብዛም ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር እጅግ ዘመናዊ የጦር ጀቶች፣ሄሊኮፕተሮችም ቢሆኑ ለእንዲህ አይነት ጥበቃዎች ጥቅምቻው እምብዛም እንዳልሆነ የወታደራዊ ጠበብት ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ የግብጽ ባለስልጣናት በየጊዜው እንደሚናገሩት ከሆነ ግብጽ እጅግ ዘመናዊ የአየር ሀይል ጀቶችን እና ፈጣን ጀልባዎችን የምትገዛው በከተሞች የሚቀሰቀሱ አመጾችን ለመቆጣጠር እና የከተሞችን ደህንነት ለመቆጣጠር ነው የሚል አምደምታ ቢኖረውም ይህም ቢሆን አሳማኝ ምክንያት አይመስለኝም፡፡
በነገራችን ላይ ለግብጽ የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡ ሀገራት በርካታ ናቸው፡፡ ስለሆነም ግብጽ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የማግኘት እድሏ ሰፊ ነው፡፡
ስለሆነም ግብጽ የጦር መሳሪያ ግንባታዋን ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረች ትገኛለች፡፡ ሆኖም ግን በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ግብጽ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ ልትወደቅ ትችላለች፡፡ለአብነት ያህል ግብጽ አዲስ የጦር ጀቶች መጠገኛ ተቋም ለመክፈት ብትሞክር ከተባበረችው አሜሪካ፣ሩሲያ እና ከአውሮፓ ህብረት በግዥም ሆነ እርዳታ ላገኘቻቸው የጦር ጄቶች የተለያዩ መለዋወጫዎች እና የተለያዩ የአየር ሀይል አባላት ስልጠና ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ደግሞ በግብጽ የአየር ሀይል ከባድ ጫና ይደርስበታል፡፡
ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች
ግብጽ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችና የኒኩሊየር ፕሮግራም እየጀመረች ስለመሆኑ በርካታ በተለያዩ የዜና አውታች የሚነገር መራር ሁነት ነው፡፡ ጅምላ ጨራሽ የመጠቀም ታሪኳ እንደተጠበቀ ሆኖ ግብጽ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎችን ላለመጠቀም አንፈርምም ካሉ አራት እምቢተኛ የአለማችን ሀገሮች አንዷ ናት፡፡ ከዚህ ባሻግር የባዮሎጂካል መሳሪያ ለመጠቀም የሚከለክለውን አለም አቀፍ ስምምነት ሳይቀር ገና ለመፈረም ዝግጁ አይደለችም፡፡
በገራችን ላይ የግብጽ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ፕሮግራም ዕጅግ ያደገና ዘመናዊ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ከአንደኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎችን በሰሜን የመን የርስበርስ ጦርነት ግዜ ጥቅም ላይ እንዳዋለች ይነገራል፡፡ ግብጽ ፎሲጅን እና ሙስታርድ ( phosgene and mustard gas) በመባል የሚታወቁ የኬሚካል መሳሪያዎችን የተጠቀመችው የመንግስትን ታማኞች ለማጥቃት እንደሆነ በግዜው በአለም መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል፡፡
- የመገናኛ አውታሮች ለመዘርጋት የፈሰሰው መዋእለ ንዋይ (Infrastructure )
በእንዲህ አይነት አጭር ጽሁፍ የግብጽን ወታደራዊ አቋም ለመግለጽ አስቸጋሪ ነው፡፡ በቅንጹል ጥናትም የግብጽን ወታደራዊ ግንባታ ለማወቅ አይቻልም፡፡ በነገራችን ላይ ወታደራዊ ሀይልን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስፍራ በቀላሉ ለማንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ ወታደራዊ ሀይልን ለማንቀሳቀስ መዋእለ ንዋይ ግንባታ ግድ ይላል፡፡ ለአብነት ያህል እንደ መንገድ፣የባቡር መሰመር ዝርጋታ ያስፈልጋል፡፡ በመገናኛ አውታር ዝርጋታ አኳያ ግብጽ መጠነ ሰፊ መዋእለ ንዋይ አፍስሳለች፡፡
ለአብነት ያህል አዲሱ የስዊዝ ካናል ቦይ ዝርጋታ እውን መሆን፣ የስዊዝ ካናል ከዚህ ቀደም ከሚሰጠው አገልግሎት ሁለት እጥፍ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ከዚህ ባሻግር ከመካካለኛው ምስራቅ ሀገራት ሁሉ ትልቁን የወታደራዊ ቤዝ (Mohammed Naguib base ) በግብጽ ትልቋ ሁለተኛ ከተማ አሌክዛንድሪያ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ መክፈቷ፣ ይህን ተከትሎ የመገናኛ አውታሮችን በሰፊው መዘርጋቷን ልብ ይሏል፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ በአፍሪካው ቀንድ ሳይቀር ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለማቋቋም የምታደርገውን ስውርና ግልጽ ሴራ የአካባቢው ሀገራት በትኩረት መከታተል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ግብጽ ይህን አደገኛ እቅዷን እውን ለማድረግ የምትሞክረው በወታደራዊ እርዳታ እና ትብብር ስም መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
- ከዚህ በተጨማሪ ግብጽ በአብዛኛው ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ እጅግ ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻዎችን እንደገነባች የሚያሳዩ ጽፎች እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ ( ግብጽ ለሲቪል ህዝቧ የሚተርፍ ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት ስላላት የሲቪል ህዝቡ ችግር ላይ እንዳልወደቀ ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡)
- በመጨረሻም ግብጽ ታንኮችን ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ለማጓጓዝ የሚችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከባድ መኪናዎችን ገዝታ ጥቅም ላይ የዋለች ሀገር ናት፡፡ ከዚህ እውነት መረዳት የምንችለው ቁምነገር ቢኖር ግብጽ አንድን ትልቅ ወታደራዊ ሀይል በአጭር ግዜ ውስጥ ለማንቀሳቀስ የምትችል ሀገር መሆኗን ነው፡፡ በነገራችን ላይ የግብጽ ወታደራዊ ግንባታ የሚያተኩረው ወታደራዊ ወረራ ለማካሄድ በሚያስችል መልኩ እንጂ ራስን ጥቃት ይከፈትብኛል ከሚል አመክንዮ እንዳልሆነ አንዳንድ ወታደራዊ ጠበብት ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት አስተያየት ለመረዳት ይቻላል፡፡
ስልጠናን በተመለከተ
በወታደራዊ ሳይንስ ያልታነጻና እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ሰራዊት፣በወታደራዊ ሳይንስ ትምህርት ከሰለጠነና ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀ ሰራዊት ጋር ሲወዳደደር የውጊያ አፈጻጸሙ ለየቅል ነው፡፡ (ውጤታማነቱ አስተማማኝ አይደለም፡፡) የወታደራዊ ስልጠናን አስፈላጊነት የተረዱት ግብጾች በከባድና ቀላል መሳሪያዎች የታገዙ ( ለአብነት ያህል በታንክና ጀቶች፣ባህር ሰርጓጅና የጦር መርከብ በታገዙ) ስልጠናዎችን ለወታደሮቻቸው በየጊዜው እንደሚሰጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከቀድሞ ወዳጆቿ፣ እንዲሁም ከአዲስ ወዳጅ ሀገሮቿ ጭምር አንድ ላይ በመሆን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ታደርጋለች፡፡ ለአብነት ያህል ጽሁፍ በማዘጋጅበት ግዜ ከሱዳን ጋር የጋራ ወታደራዊ ስልጠና ማደረጓን የሚያወሱ ዜናዎች ተሰምተዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2017 የተባበረችው አሜሪካ ጦር ሀይል እነ የግብጽ ጦር ሀይል ‹‹ አንጸባራቂ ኮከብ ›› የተሰኘ የሁለትዮሽ የጦር ለምምድ አድርገው ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2011 ላይ የተጠቀሰውን የጦር ልምምድ እንዳይደረግ ከልክሎ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡
The biennial joint American- Egyptian military exercise “Bright Star” was held again in 2017
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብጽ ጦር ሀይል ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚከተሉትን ወተዳራዊ ልምምድ ማካሄዱን የሚገልጹ መረጃዎች አሉ፡፡ የተወሰኑትን ዝቅ ብዬ እጠቅሳለሁኝ፡፡
- ላለፉት 5 አመታት ከዮርዳኖስ ስፔሻል ጦር ጋር የተደረገው ልምምድ ይጠቀሳል
- ከሩሲያ የጦር ሀይል ጋር በመጣመር ከጦር አይሮፕላን በፓራሹት ዘሎ መወረድና የቤት ለቤት አሰሳ ልምምድ፣ወደ ሩሲያ በሚገኙ የጦር አካዳሚዎች የጦር አታሺዎቿን በየጊዜው እየላከች አስተምራለች
- የግብጽ የባህር ሐይል አባላት ፣ከሩሲያ የባህር ሀይል ጠበብት ስልጠና ወስደዋል
- የግብጽ ምድር ጦር ከተባበረችው አረብ ኤሜሬትና ባህሬን ወታደሮች ጋር በመጣመር የጦር ልምምድ አድርገዋል
- በቅርብ ግዜ ውስጥ ደግሞ ከግሪክ አየር ሀይልና ባህር ሀይል፣ እንዲሁም ከእስራኤል የጦር ሀይል ጋር በመጣመር ያካሄዱት ወታደራዊ የጦር ልምምድ የሚጠቀስ ነው፡፡
- በአጠቃላይ የግብጽ የጦር ሀይል ከመቼውም ግዜ በበለጠ የጦር ሀይል ልምምድ ማደርጉን፣ ከግብጽ የጦር ሀይል ጋር ጥምረት በመፍጠር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የሚያደርጉ ሀገራት ቁጥርም መጨመሩን እንረዳለን፡፡ ከዚህም ባሻግር ግብጽ በርካታ ወታደራዊ ማስለጠናዎችን እጅግ ዘመናዊ እና ዘመኑን በዋጀ መሳሪያዎች እንዲታገዙ በማድረግ መክፈቷን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
የቢሆን ማብራሪያዎች
ከላይ በቀረቡት መረጃዎች መሰረት፡
- የግብጽ ወታደራዊ ሀይል ወደ ላቀ ወታደራዊ ደረጃ እየገሰገሰ ነው፡፤
- ግብጽ ወታደራዊ አቅሜ ጠንከራ ነው በማለት እየተኩራራች ትገኛለች
- ግብጽ ከካይሮ አንስታ እስከ ሲናይ በረሃ አዲስ ወታደራዊ ተቋም እየገነባች ትገኛለች
- በርካታ ታንኮችና የተቀበሩ ፈንጂዎችን መቋቋም የሚችሉ ከባድ ተሸርካሪዎችን ለመግዛት በመቻሏ የሲናይ በረሃን ለመቆጣጠር የሚያስችለው አቅሟ እየጠነከረ ይገኛል፡፡
- የግብጽ ጦር ሀይል በብረት ለበስ ተሸርካሪዎች በመታገዝ ጦርነት የማድረግ አቅሙ እየጠነከረ ይገኛል፡፡
በነገራችን ላይ ግብጽ እጅግ መጠነ ሰፊ ሀብት በማፍሰስ ወታደራዊ ጡንቻዋን ባልተለመደ ሁኔታ የማፈርጠሟ ግልጽ ምክንያት ለመረዳት ያስቸግራል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የግብጽ ወታደራዊ ግንባታ ሌሎች ሀገራትን የሚረብሽ ነው፡፡ ለማናቸውም ግብጽ የሚከተሉት ምክንያቶች ሊኖራት ይችላሉ መገመቱ አይከፋም፡፡
- አንዱና ዋነኛው ምክንያት በአረቡ አለም ያላት ተሰሚነትን ለማስጠበቅ ነው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ይህ ደግሞ የኢኮኖሚ ድክመቷን ሊሸፍንካት ይችላል፡፡ እንዲሁም በመሃከለኛው ምስራቅ የአለም ክፍል ያለውን የጦር መሳሪያ እሽቅድድም ለመቋቋምና አራን የምታደርገውን ግስጋሴ ለመገዳደር ይረዳታል፡፡
- ከዚህ ባሻግር ተለዋዋጭ የሆነውን የተባበረችው አሜሪካን የፖለቲካ አቋም ለመቋቋም ይረዳኛል ብላ በማሰብ፡፡ ይህም ማለት አንድ ቀን የግብጽ ህዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄ በመያዝ ግልብጥ ብሎ ወደ አደባባይ ቢወጣ አሜሪካ ከዲሞካረሲ ጋር ድንገት ብታብር ከሩሲያና መሰል ሀገረት ጋር በመተባበር የህዝብን አመጽ በመሳሪያ ሀይል በጉልበት ለመደፍጠጥ ያስችለኛል በሚል የአምባገነኖች ባህሪ የተነሳ ሊሆን ይቻለዋል፡፡
- ወደፊት ባልታወቀ ግዜ ከእስራኤል አኳያ ሊገጥማት የሚችልን ጦርነት ለመቋቋም ( በተለይ በሲናይ በረሃ ላይ ለብዙ ግዜ ሲነታረኩ ይሰማል)
- የሐገሪቱን መንግስት ውስጣዊ አቅም ለማጠንከር
- የግብጽ ወታደራዊ ሀይል የናይል ወንዝን እንዲቆጣጠር ለማስቻል፣የላይኛው የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ህጋዊ መብታቸውን በመጠቀም የአባይ ወንዝ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያደርጉትን ሙከራ ለመከላከል፡፡ ለአብነት ያህል ኢትዮጵያ ታላቁን የአባይ ወንዝ ገንብታ ሀይል ለማመንጨት የምታደርገውን ሴራ ማየት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ ምናልባት የአየር ሐይል ከመጠቀም ውጭ ኢትዮጵያን በምድር ላይ ውጊያ ለማጥቃት እድሏ የጠበበ እንደሆነ አንዳንድ ወታደራዊ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡
ከላይ የቀረቡት የቢሆን ምክነያቶች ሲሆኑ የግብጽን ትክክለኛ አቋም ወይም ምክንያት ሊያስረግጡ አይችሉም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከረዥም ጊዜ በኋላ ከእስራኤል ጦር ጋር ግጭት ብትፈጥር ለመከላከልና በአሁኑ ግዜ በምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በመነሳት የናይል ወንዝን ለመቆጣጠር የሚሉት ምክንያቶች ሚዛን ሊደፉ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ልኡካን ጋር በምታደርጋቸው ውይይቶች ላይ አንድ ሁል ግዜ የምታነሳው ነጥብ አለ፡፡ ይህም ሁሉም አማራጮች በጠረቤዛው ላይ አሉ የሚለው ነው፡፡ ይህም ማለት ወታደራዊ አማራጮችን መጠቀም እንችላለን የሚል መልእክት ነው፡፡
We should keep in mind that the constantly repeated phrase “all options are on the table” in the discussion on the Renaissance Dam with Ethiopia is in reference to military option.
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የምትሞክረው በአየር ሀይሏ በመታዝ ብቻ ይሆናል፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያን በጦርነት መግጠም የሚቻላት ከኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገሮች በአንደኛዋ መተላለፊያ ካገኘች ብቻ ይሆናል፡፡ ይሄ ደግሞ አደገኛ ሙከራ ሲሆን ውጤቱም የብዙ ጦርነቶች ጅማሮ ይሆናል፡፡ ከዚህ ባሻግር ጦርነቱ አካባቢውን ወደ ለየለት ትርምስ ይወስደዋል የሚለው መላምት የእኔ ብቻ ሳይሆን አካባቢውን የፖለቲካ ትኩሳት የሚከታተሉ የብዙ ሰዎች ስጋት ይመስለኛል፡፡ ጦርነቱም ለአመታት ሊዘልቅ ይቻለዋል፡፡ ጦርነትን ይጀምሩታል እንጂ አይጨርሱትም፡፡
በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ፕሬዜዴንት ኤልሲሲ ግብጽ ወራሪ ሃይል እንደማያሰጋት ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም ግብጽን ለማጥቃት የተዘጋጀ የተደራጀ የጦር ሀይል ለግዜው የለም ነበር ያሉት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የመካከለኛው ምስራቅ የአለም ክፍል ያልተረጋጋና ሰላም የሌለው ስለሆነ ግብጽ ታላቅ የጢር ሀይል መገንባት ያስፈልጋታል ሲሉም ተደምጠው ነበር፡፡ የአልሲስን ንግግር ስንተረጉመው ግብጽ በመሃከለኛው ምስራቅ ግዙፍ ወታደራዊ ሀይል ማሰመራት ፍላጎቷ እንደሆነ ነው፡፡ አልሲሲ ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግና በቀይ ባህር ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀት የተባበሩት አረብ ኤሜሬትን እርዳታ እንደጠየቁ ይታወሳል፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ የውክልና ጦርነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ለመክፈት ያላትን ሴጣነዊ ውጥን እውን ለማድረግ በቅርቡ ከሱዳን ጋር ያደረገችው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ወተዳራዊ ጡንቻዋን ሊያፈረጥምላት ይቻለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከእስራኤል ጋር ግጭት ለመጫር መሞከር ለግብጽ ራስን እንደማጥፋት ይቆጠራል፡፡ ሆኖም ግን ግብጽ ወደፊት ከእስራኤል ጋር መጋጨቷ አይቀርም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እስራኤል የጎላን ከፍታን እና አየሩሳሌምንበመቆጣጠሯ ወደፊት ደግሞ ዌስት ባንክን (West Bank ) ለመቆጣጠር ስለምታስብ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ግብጻውያንን በማስቆጣቱ እንደሆነ ብዙዎች የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ሌላው ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ግብጽ የሰብዓዊ መብት ባለማክበሯ ምክንያት የተባበረችው አሜሪካና አውሮፓ ህብረት የሚደርጉትብ እርዳታ ሊቀንሱ ከቻሉ ግብጽና እስራኤል ወደ ውጥረት፣ወደ ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይቻላቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ በአንድ ሀገር የማእከላዊ መንግስቱ ዋነኛ ስልጣን በአምባገነን ወታደሮች ቁጥጥር ስር ሲወድቅ ስህተት የመፈጠር ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ የወታደራዊ ሀይል ጡንቻን በከፍተኛ ደረጃ ማጠንከር፣እንዲሁም አንድን ሀገር ድንገት በጦር ሐይል መወረር ሊታይ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ታሪክ እንደሚያስተምረን ግብጽ ብዙ ግዜ ከሀገራት ጋር ጦርነት ገጥማ የሽንፈትን ጽዋ እንደተጎናጸፈች ነው፡፡ ለአብነት ያህል ከብዙ መቶ አመታት በፊት ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ አካሂዳ ውረደትን ተከናንባ ተመልሳለች፡፡ ከዚህ ባሻግር በአረቦችና የእስራኤል የስድስቱ ቀን ጦርነት፣ እንዲሁም የመንን ለመወረር ሞክራ አልተሳካትም ነበር፡፡ ስንፈትን ነበር የተከናነበችው፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡
እንደ መደምደሚያ
ምንም እንኳን ይሁንና ግብጽ ከቅርብ አመታት ወዲህ ከወታደራዊ አቅም ግንባታ አኳያ የምታደርገው መጠነ ሰፊ ዝግጅትና ስራ አላማ ፣ አሁን ባለበት ሁኔታ በትክክል ምን እንደሆነ ለማወቅ ባይቻልም፣ የምታደርገው ወታደራዊ ግንባታ ራሱ የሚናገር ይመስለኛል፡፡
ግብጽ የምታደርገው ወታደራዊ ግንባታ ማለትም፡-
- በግዢ የምታገኛቸው የረቀቁ የጦር መሳሪያዎች
- እጅግ የዘመኑ የመገናኛ አውታሮች ግንባታ ( ለሲቪልና ለወታደራዊ ተሸርካሪዎች እንቅስቃሴን የሚያቀላጥፉ)
- ከብዙ ሀገራት ጋር የምታደርገው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ወዘተ ጎረቤት ሀገራትን ወይም ሌሎች ሀገራትን የሚያነቃና ራሳቸውን ከወታደራዊ ሀይል አኳያ ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ የሚጋብዝ ነው፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው ማብራሪያዎች ሙሉበሙሉ የግዜውን የግብጽን ፍላጎትና አላማ ላይገልጹ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንደ እስራኤል የመሳሰሉ ሀገራት፣በመሃከለኛው ምስራቅ ግዛት የሚደረጉ ግጭቶች፣ በአካባቢው የቱርክ ተጽእኖ መጨመር፣በሊቢያ የግብጽ ተጽእኖ ወይም ሁነኛ ሚና፣የአፍሪካው ቀንድ፣ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ወዘተ ወዘተ ግብጽን ታላቅ ወታደራዊ ሀይል እንድትገነባ ሳያስገድዳት አይቀርም፡፡ በነገራችን ላይ የአንድ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት በብዙ መልኩ በተለይም ከወታደራዊ ሃይል አኳያ መጠናከር ሲታይ ሌሎች ሀገራት ፖሊሲያቸውን እንዲመረምሩ የሚያስገድድ ነው፡፡
ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንቲስት ሄነሪ ኬሲንጀር በአንድ ጽሁፉ ላይ እንደጠቀሰው ‹‹ ፍጹማዊ አንድ አምባገነን መንግስት ፍጹማዊ የሆነ የደህንነት ጥበቃ ከገነባ፣ለሌሎች ሀገራት የጸጥታ ችግር ስጋት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ መንግስት ፍጹማዊ የሆነ ወታደራዊ ግንባታ የሚያደርግ ከሆነ ጎረቤት ሀገራት ስጋት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ As Henry Kissinger had said, Absolute security for one party means total insecurity for other parties በውጤቱም የጦር መሳሪያ እሽቅድድም መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለይም ግብጽ እስራኤል ወደ የጦር መሳሪያ እሽድድም ውስጥ መዶላቸው አይቀሬ ሀቅ ነው፡፡
አሁን የኢትዮጵያና ግብጽን ግንኙነት፣ በተለይም በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ዙሪያ የገቡበትን እሰጥ እገባ በመዳሰስ ጽሁፌን ለመቋጨት እሞክራለሁኝ፡፡
በነገራችን ላይ እያንዳንዷ የጥቁር አባይ ወንዝ የውሃ ጠብታ የኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽን ህዝቦች የጋራ እምነት የሚወክል ይመስለኛል፡፡
ስለሆነም ግብጽም ሆነች ሱዳን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ያለ አንዳች እንከን ለማስከበር ፍላጎቱ ካላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት፣በቅንነት መንፈስ መተባበር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ አባይ ወንዝ ወደ ተጠቀሱት ሀገራት እንዲፈስ አስተማማኝ ሀገር ናት፡፡ ወደፊትም የአባይ ወንዝ ተፈጥሮአዊ ጉዞውን መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የግብጽ የህይወት ምንጭ የሆነውን አባይ ወንዝ ሙሉበሙሉ በመከተር ለመጉዳት የተዘጋች ሀገር አልነበረችም፡፡ ወደፊትም አታደርገውም፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎት እና ምኞት በአለም አቀፍ የድንበር አቋራጭ ወንዞች ህግ መሰረት ሌሎች ሀገራትን ጉዳት ላይ ሳትጥል ራሷን ማልማት ማሳደግ፣ማበልጸግ ነው፡፡ሌላ አላማ ያላት አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ሶስቱም ሀገራት በትብብር መንፈሰና በቅን ልቦና መነጋገር ያለባቸው ይመሰልኛል፡፡ ሆኖም ግን ከመነጋገር ውጭ በሃይል በጉልበት በጦርነት መፍትሔ አይመጣም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን በማናቸውም መልኩ በወታደራዊ ሀይል ማጥቃት ማጠፊያ አይገኝለትም፡፡ ኢትዮጵያን በጦርነት ለማንበርከክም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለግብጽም የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡
በነገራችን ላይ የግብጽ ወታደራዊ ሀይል የሕዳሴውን ግድብ ለማጥቃት መሞከር እንደ ጥሩ አማራጭ አድርጎ አይወስደውም፡፡ ምክንያቱም አንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉት ሀገራት ከግብጽ ድንበር በብዙ ሺህ ኪሎሜትር እርቀት ላይ ስለምትገኝ ነው፡፡ ምናልባት ግብጽ የአየር ሀይሏን አቅም ተጠቅማ የኢትዮጵያን አየር በመጣስ ጉዳት ለማድረስ ልትሞክር ትችል ይሆናል የሚሉ ዜናዎች ይሰማሉ፡፡ግን አንዳንድ የወታደራዊ ሀይል ጠበብት እንደሚተነትኑት ከሆነ ግብጽ ከራሷ የአየር ማረፊያዎች ላይ በመነሳት የኢትዮጵያን አየር ክልል በመጣስ ጉዳት የማድረስ አቅም የላትም፡፡ ሌሎች የወታደራዊ ጠበብት በበኩላቸው ግብጽ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከተባበረችው አሜሪካ በአየር ላይ ነዳጅ ሊሞሉ የሚችሉ የጦር ጀቶች አግኝታለች፡፡ ስልጠናም ለተመረጡ የአየር ሀይል አባላቶች ሰጥታለች፡፡ ምናልበትም በዚህ ተጠቅማ ጥቃት ልታደርስ ትችላላች ወይም እነኚህ እጅግ የዘመኑ የጦር ጀቶች በኢትዮጵያ የአየር ክልል ላይ የመብረር አቅም ሊኖራቸው ይችላል፡፡የሚሉ መላምቶቻቸውን የሚሰጡ የፖለቲካ ሰዎች አሉ፡፡
ሌላው የግብጽ እድል ለታላቁ የአባይ ግድብ በቅርብ እርቀት ላይ በምትገኘው ሱዳን የአየር ማረፊያ ማግኘት ከቻለች ኢትዮጵያን በጦር ጀቶቿ ለማጥቃት ይቻላታል፡፡ ይህ ግን አደገኛ ሙከራ ነው፡፡ በአንድ በኩል ራስን በራስ እንደ መግደል ይቆጠራል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ በኩል በሱዳን ላይ አለም አቀፍ ውግዘት የሚያደርስ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የሱዳንን ሉአላዊነት የሚደፍር ሲሆነ፣ በአፍሪካው ቀንድ ዙሪያ ያለውን የሰላም ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ የሚዶል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያና ሱዳንም በማይጠቅም ጦርነት ውስጥ ለረጅም አመታት ይዘፈቃሉ፡፡
ሌላው ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የጥቃት ሰበዟን ለመምዘዝ የምትችልበት መንገድ የራሷን ልዩ ጦር በሱዳን በድብቅ በማስረግ በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት ለመክፈት ከቻለች ይሆናል፡፡ ግብጽ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክና ታሪካዊ ጠላት ስለሆነች የኢትዮጵያን የውስጥ አንድነት በማላላት የውክልና ጦርነት አትከፍትም ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ግብጽ ጦር ሰብቃ ጦር አዝምታ ኢትዮጵያን ከመወጋት እንዲህ አይነት አማራጮችን ልትወስድ እንደምትችል የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው ግብጽ በኮሎኔል መንግሰቱ ሀ/ማርያም የአገዛዝ ዘመን ኢትዮጵያ ከሶማሊያና ከኤርትራ ተገንጣይ ሀይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ግዜ ግብጽ እጇን አስገብታ ነበር፡፡ በቅርብ ግዜ ውስጥም በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላማዊ ዜጎችን ከሚያጠቁ ሀይሎች ጀርባ እጇ አለበት የሚሉ የዜና ዘገባዎችን የሚያሰሙ የመገናኛ ብዙሃን በርካታ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች የውጭ ወራሪ ሀይል የኢትዮጵን ድንበር አቋጦ ሲገባ በህብረት እና በሀገር ፍቅር ስሜት እንደሚነሳ ግብጾች ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያውያንን ድክመት በማጥናት በውስጥ በመስረግ ሀገሪቱን ለመበጥበጥ ወደኋላ የሚሉ አይዶለም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያውያን በጎሳ ፖለቲካ ምክንያት በተለያዩበት በዚህ ግዜ ለግብጽ ታሪካዊ ሴራ እውን መሆን ምቹ አጋጣሚ እንደሚሆን ኢትዮጵያውን መገንዘብ አለብን፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ደጋግማ እንዳስገነዘበችው የአባይን ወንዝ ጥቅም ላይ ለማዋል የተነሳችው የግብጽንም ሆነ ሱዳን ህዝብ ጉዳት ላይ ለመዶል አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህን መራር እውነት መቀበል የእነርሱ ይሆናል፡፡ ግብጽ ይህን እውነት ለመቀበል ተስኗት የሃይል እርምጃ የምትወስድ ከሆነ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ17 በላይ የአባይ ወንዝ ገባሪ የሆኑ ወንዞቿን አቅጣጫ ሊያስቀይር ይቻለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ውጤቱ አለም አቀፋዊ ሊሆን ይቻለዋል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ ይህም ማለት ግብጽ እንዲህ አይነት ተግባራትን ለማስቆም የምታደርገው ጥረት እጅጉን አዳጋች የሚሆንባት ይመስለኛል፡፡ የግብጽ ጠብ ያለሽ በዳቦ ማቆሚያ ካልተበጀለት የኢትዮጵያ ህዝብ ወንዞቹን ገድቦ ለመስኖ የማዋል እንቅስቃሴውን በእልህ በቁጭት አጠናክሮ እንዲቀጥል ይረደዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ የዒትዮጵያ ገበሬ ዝናብን ብቻ ወደ ሰማይ አንጋጦ እንዳይጠብቅ፣በመስኖ እርሻ ላይ ልዩ ትኩረት እንዲያደርግም ያስተምረዋል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡
በመጨረሻም ሰላም፣ትብብር እና ልማት ለማምጣት የኢትዮጵያ፣ሱዳንና የግብጽ ህዝቦች በተለይም ወጣቶች በህብረትና ፍቅር፣በቀና መንፈስ እንዲቆሙ እማጸናለሁ፡፡ ጦርነት በይበልጥ የሚጎዳው ሰላማዊ ዜጎችን በመሆኑ የሶስቱም ሀገራት ህዝቦች ጦርነትን መቃወም ይኖርባቸዋል፡፡
ሰብዓዊ እልቂትን እና የንብረት ውድመትን የሚያስከትለውን የጦርነት ታምቡር መምታት የለብንም፡፡ ምክንያቱም ከጦርነት የሚገኝ ምንም አይነት ትርፍ የለም፡፡ ጦርነት መጨረሻው ጥፋትና እልቂት ነው፡፡