6ኛውን አገር አቀፍ የምርጫ ሂደት አስመልክቶ የተሰጠ አጭር መግለጫ
አ.ብ.ን..
ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተሳትፎ ሲያደርግ ምቹ የምርጫ ምህዳር አለ በሚል እምነት ሳይሆን ያሉ ችግሮች በሂደት ተፈትተው ቢያንስ የምርጫ ዕለት ህዝባችን በአንፃራዊነት ድምጹን በነፃነት ይሰጣል በሚል እምነት ነበር፡፡
ሆኖም ግን የምርጫው ሂደት ከተለመደው የገዥው ፓርቲ ጫናና ህገ ወጥ ተግባር መላቀቅ አቅቶት ህዝባችን ተስፋ የጣለበትን የዴሞክራሲ ሂደት የሚያደበዝዝ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በተለይም በአማራ፤ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የታየውን የምርጫ ሂደት አስመልክቶ ከድርጅታችን አመራሮች፤ አባላት ፤ደጋፊዎችና ታዛቢዎች የተለያዩ የምርጫ ሂደት ግድፈቶችን በሚመለከት ተጨባጭ ማስረጃዎች ደርሰውናል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በጉዳዩ ላይ ከሰዓታት በፊት መግለጫ ሰጥቶበታል፡፡ አብን እንደ ድርጅት ዝርዝር ማጣራት አድርጎና ሪፖርቱን አደራጅቶ የምርጫ ህጉና የስነ ስርዓት መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የንቅናቄው አባላት፤ተመራጮች ደጋፊዎችና የምርጫ ታዛቢዎች የምርጫ ድባቡ በተጀመራበት አግባብ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጀመሩትን በጎ አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል፡፡
የአማራና የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት በየደረጃው ያላቹህ አመራሮች የምርጫ ህጉ በሚፈቅደው አግባብ ህጋዊ ግዴታችሁን እንድትወጡና ሰላማዊዩን የምርጫ ሂደት ከማሰናከል እንድትቆጠቡ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
ሰኔ 14/2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ