በህይወት ላይ ጣጣ-ፈንጣጣ ያለማብዛት ጥበብ…!!!
አሰፋ ሀይሉ
The Subtle Art of Not Giving a Fuck: A Counterintuitive Approach to Living a Good Life (Authored by Mark Manson, 2016)
ይህችን ባለ 200 ገጽ መጽሐፍ እያነበብኩ ደግሞ ደጋግሞ የሚመጣብኝ ሐረር ነው፡፡ በተለይ በመጽሐፉ መጀመሪያ የሐረር ልጆች «አቦ እናትንና…» እንደሚሉት ይሄ ደራሲም «Fuck» የሚለውን ቃል ደግሞ ደጋግሞ ስለሚጠቀመው ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያውም አጠቃቀሙ እጅግ ደስ ይላል፡፡ ደራሲው «Fuck» የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት «ጣጣ» ወይ «አንጃ-ግራንጃ» ወይ «ግግም-ብሎ-ሙጭጭ-ብሎ-መቅረት» እንደማለት አድርጎ ነው፡፡
በቃ ባጭሩ የሚሰብከው ሁሉም ሰው የሐረር-ልጅ፣ የድሬ-ልጅ፣ ወይ በቃ የጂጂጋ-ልጅ ዓይነት ይሁን! ወይ ደሞ የአዲሳባም ከሆነ፣ የጎንደርም፣ የናዝሬትም፣ የአዋሳም፣ የጅማም፣ የመቀሌም፣ የደሴም፣ የመቂም ልጅ ከሆንክ የአራዳ-ልጅ ሆነህ ኑር፡፡ ማጣት ማግኘት ያለ ነው፡፡ ፍቅርን አይተካልህም፡፡ ሁሌ ዓመት በዓል የለም፡፡ ዝነኛ መሆንም፣ ስም አልባ መሆንም ያው ነው፡፡ አንዲት ጸጉር አያረዝምም፡፡ ፍቅረኛህ አፍንጫህን-ላስ ብላህ ሄደች? እንኳን ሄደች! አታካብደው! መሄድ መምጣት ያለ ነው! ሁሉም ነገር ከፈለገ ገደል ይግባ! እንደ አዲስ መጀመር ትችላለህ! Don’t Give a Fuck!
ደራሲው የሚለው በቃ ሕይወትህን አታወሳስባት፡፡ የተለየ ትርጉም አትስጣት፡፡ ራስህን አትቆልለው፡፡ ከሰው የተለየህ አይደለህም፡፡ ከሰው የተለየ ትንቢት አልተነገረልህም፡፡ በቃ ራስህን አቅልለውና ተራ ሰው መሆንን ቻልበት፡፡ ራስህን ለምን ታጨናንቀዋለህ? ነው፡፡ ደራሲው ይህን ሲል በዓለም ላይ ሞልቶ በተረፋቸው ሀገራት ላይ የሚኖሩትን ግን በአብዛኛው የጭንቀት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን አስተውሎ ነው፡፡ ደራሲው ይህን ሲል – አብዛኛው ሰው የሆነ የሀብት ግብ አሳካለሁ ብሎ ዕድሜውን ሲዳክር፣ ወይም ስላላሳካ በገንዘብ እጦት ከተሰቃየው በላይ በመንፈስ ሲሰቃይ ስለተመለከተ ነው፡፡
በዋና ልብስ ‹ቢች› ዳር ብቅ ስትል በዳሌዋ የሰውን ሁሉ ቀልብ የምትገዛ መለሎ ሚስት ፈልገሃል? እና እዚያው ቢች ዳር ቤት ሰርተህ እየተዝናናህ መኖር ተመኝተሃል? ወንድሜ! ህይወት እኮ ዳሌና ጡብ ብቻ አይደለችም! አሸዋና ሲሚንቶ ብቻ አይደለችም! ዓሣ አይደለህም፡፡ ሰው ነህ፡፡ ዕድሜህን ሙሉ ውሃ ላይ የሚያንጦለጡልህ ምክንያት ምንድነው?
ደሞ ልብ በል! ሴት ልጅ ቂጥ ብቻ አይደለችም! ሰው ነች! ከሚስትህ ሚሊዮን ወርቃማ ነገሮችን ልታገኝ ትችላለህ! ለምን ቀላዋጭና ርካሽ ታደርገዋለህ ራስህን? የተመኘኸውን ካገኘህ እሰየሁ! ግን ሕይወት አንድ ነገር ብቻ አይደለችም! የባህታዊም ህይወት እኮ ህይወት ነው! ደስ ካለህ እንደ ወታደር በጀግንነት ተዋግተህ ባጭር ዕድሜህ መሞትም እኮ ረዥም የተንዘላዘለ ዕድሜ ኖረህ ከመቆዘም የተሻለ ሊሆን ይችላል! አስበኸዋል?
«ክላስን መጠበቅ» ከሚሉት ነገር ራቅ! ሲጀመር ሰው ነህ! ሁሉም ሰው ዝርያህ ነው! ቢያድልህ እንስሶችንም ቀርበህ ብታያቸው እንደ ሰው ያለ ብዙ ባህርይ አላቸው፡፡ እና ከሰው መሐል መርጠህ የምን ክላስ መጠበቅ ነው? ለምን ራስህን ታሰቃየዋለህ? የተማሩ ሰዎች ብቻ የሚሰበሰቡበት የምሁር ክላስህን እየጠበቅክ ነው? ከሆነ ወዳጄ፣ አንድ ነገር ስማ! በዚህች ዓለም ላይ አንተ አንጠርጥረህ ልታውቅ የምትችለው አንድን ወይም ሁለትን ሙያ ብቻ ነው፡፡ ያንንም ስንት ዓመት ፈጅተህበት!
ስለ አንድ ወይም ሁለት ነገሮች ታውቃለህ፡፡ ስለብዙ ሺኅ ነገሮች ደግሞ ድብን ያልክ ጨዋ ነህ! እንካ ይህን ቫዮሊን ተጫወት ቢሉህ ይዘፈን ይለቀስ አታውቀውም፡፡ ይህቺን ሄሊኮፕተር ጠግንልን ቢሉህ፣ ወይም የህጻናት መጫወቻ መኪና ገጣጥምልን ቢሉህ የማታውቅ ነፈዝ ልትሆን ትችላለህ፡፡ በየሙያ ዘርፉ ያሉ የኬሚስትሪ፣ ወይም የማቴማቲክስ፣ ወይም የፊዚክስና ኢንጂነሪንግ ቀመሮችን ፍታ ብትባል ትንፋሽ ያጥርሃል፡፡ እነዚህን ብትፈታ የዱቅዱቄ ጎማ መፍታት አትችልም!
ፒያኖ መጫወት ብትችል፣ ማሲንቆና በገና ስታይ ያዞርሃል፡፡ መረብ ኳስ ብትሞክር፣ እግርኳስ ባፍጢምህ ይተክልሃል፡፡ ሃኪም ብትሆንና የሰውን አካል አንጠርጥረህ ብታውቅ – ከርሰ ምድርን በሚያውቁ ጂኦሎጂስቶች፣ አርኪኦሎጂስቶችና ፓለንቶሎጂስቶች ፊት ስትቀርብ ደደብ ህጻን ሆነህ ትገኛለህ፡፡ የዓይን ሃኪም ሆነህ፣ የኩላሊት ሃኪም በነፍስህ ይጫወትብሃል፡፡ የአውሮፕላን ሹፌር (ፓይለት) ብትሆን፣ የሎቤድና የላዳ ሹፌር ፊት ስትቀርብ ሸምቃቃ መሆንህን አትርሳ፡፡
የቤቶቨንን ዜማዎች በቃልህ ስትወጣ ብትከርም፣ የቤተክርስትያን ቅዳሴ ጉሮሮህን ያንቅሃል፡፡ አስር ቋንቋ በመቻልህ ራስህን እንደተለየ ሊቅ ቆጥረኸዋል? ነፍሴ፣ በዚህ ዓለም ላይ 6,500 ቋንቋዎች አሉ – አብዛኛው ዓለም ላይ ብቻህን ብትለቀቅ – የማትሰማ፣ የማትለማ ጦጣ ነው የምትሆነው! እና ነፍሴ! በጣም ራስህን አትስቀለው! የምትጠብቀው ክላስ አይኑርህ! ከላስ!
ከፍታና ዝቅታ ሁለቱም የሰው ልጅ ተደስቶ መኖር የሚችልባቸው የህይወት ፈርጆች ናቸው፡፡ ሕይወትህን እንደየፈርጇ፣ እንደየአመጣጧ አስተናግዳት፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም ሆነህ መኖር አይጭነቅህ፡፡ ሁለቱም ስላለ ነው ቃሉ የተፈጠረው፡፡ የሽንት ጨርቁን በአስማት ዘልሎ ምራቅ የዋጠ ህጻን በዓለም አልተፈጠረም፡፡ ሁሉም ሰው ጨምላቃነት አለበት፡፡ እና በምንም ነገር ተጨማለቅኩ ብለህ ህይወትህን አታጨናንቃት፡፡ ረጋ ብለህ፣ ፈገግ ብለህ፣ ጨምላቃህን አራግፈህ፣ በደስታ ተመላለስ፡፡
ህይወትን ነጻ ሆነህ ኑርባት፡፡ አንጃና-ግራናጃ አታብዛ፡፡ ይሄን ባገኝ ነው የምደሰተው፣ ይሄን ከማላገኝ ብሞት ይሻለኛል፣ ለምን እንዲህ ሆንኩኝ፣ ለምን መኪናው እኔ በተሳፈርኩበት ቀን ተገለበጠ፣ ወዘተ ወዘተ እያልክ ህይወትህን በክስተቶችና በመስፈርቶች ላይ አጥረህ ዕድሜህን ሁሉ እኝኝኝ ስትል አትኑር፡፡ በቃ ያ የተከሰተው መከሰት ስለሚችል ነው፡፡
ብትነግሥም፣ ብትከስርም፣ ሌላ ቀርቶ ብትሞትም – በዚህ ዓለም ላይ አንተ ከዓለም ሁሉ ህዝብ መሐል እጅግ የተለየህ በመሆንህ ስለ አንተ ተመርጦ የተነገረ ትንቢት ስለነበረ አይደለም፡፡ እንደ ሎተሪ ዕጣው አንተ ላይ ስለወጣ ነው! «ሪጎላው» ስለዞረልህ፣ ወይም ስለዞረብህ ነው፡፡ ምንም ነገር፣ ምንም ስኬት፣ ምንም መከራ፣ ምንም ነገር – በፍጹም ብርቅ አይደለም!
አደጋም ቢደርስብህ፣ ሎተሪም ቢደርስህ፣ ንጉሥም ብትሆን፣ በባርነትም ብትጠረዝ – በቃ ዓለም ሁሉ ተመካክሮ ያደረገልህ፣ ወይም ያደረገብህ ነገር አይደለም! ምንም ማለትም አይደለም! ንጉሥም ብትሆን አንዲት ነፍስ ነች ያለችህ! ያጣህ የነጣህ ተመጽዋችም ብትሆን ያቺው አንዲት ነፍስ ነች የምትኖርህ፡፡ ይህን አውቀህ – ለምንም ነገር ሳትፈነድቅ፣ ለምንም ነገር ሳትንበቀበቅ፣ በቃ ደስ ብሎህ ህይወትህን በእርጋታ ተራመዳት፡፡
ብዙዎች ሰዎች የሆነ ዱብዕዳ ውስጥ ሲገቡ የሚጨነቁት – ሁልጊዜ ቀና ቀናውን እንዲገጥማቸው 24 ሰዓት ሲጠበቡ ስለሚኖሩ ነው፡፡ የብዙ ጭንቀቶችና የህይወት መጨለሞች መንስዔ ይሄ በሌሎች ሰዎች ፊት – «ኑሮ የተሳካለት» ሆኖ ለመገኘት የመቧተር አጉል አባዜ ነው፡፡ ይህን ልክፍት ከላይህ ላይ አስወግድ፡፡
እንደ ሀይሌገብረስላሴ የአትሌቲክስ ሪከርድ መሰባበር ሳትችልም፣ በእርጋታ እርምጃ እየተራመድክ ህይወትህን በደስታ መኖር እንደምትችል አስብ፡፡ የምርኩዝ ዝላይም ሪከርድ ሳትሰብር፣ እግሮችህን አጥተህ በዊልቼር ላይ ደስተኛ ኑሮ መምራት እንደምትችል እወቅ፡፡ የሀገር መሪ ሳትሆንም፣ የባጃጅ መሪ ጨብጠህ እጅግ ደስተኛና ከጭንቀት ነጻ ሕይወት መኖር እንደሚቻል እንዳትረሳ! የትኛው የኑሮ ‹ክላስ› እንዳይቀርብህ ነው ህይወትህን እንዲህ የምታስጨንቃት? ካንዱ ክላስ ወደሌላው ክላስ ስትሸጋገር ህይወት እዚያ ላይ ታበቃለች ያለው ማን ነው?!
በዚህ ዓለም ላይ ‹ጥሩ› የምትላቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ ‹መጥፎ› የሚባሉ ነገሮችም እንዳሉ ፈጽሞ አለመርሳት! ይህ ነው የህይወት ሁሉ ጥበብ! ይህ ነው የግልግል ምንጭ! በውጫዊ ነገሮች ራስህን አትለካ! ውጫዊ ነገር ውጫዊ ነው! ስትቀበር አብረኸው አትቀበርም! ያንንም ስታገኘው ሌላ ትራባለህ! ውስጣዊ ነገሮች ሁሉ ደግሞ የደስታና የሠላም ምንጮች ናቸው፡፡
በውስጥህ ያሉ መልካም ነገሮችን አጎልብታቸው! ሃቀኝነትን፣ መውደድን፣ ማክበርን፣ ደስተኝነትን፣ ራስን ከማንም ጋር አለማወዳደርን፣ ስክነትን፣ ትዕግሥትን፣ ታማኝነትን፣ ወዘተ. ከራስህ ጋር እንዲኖሩ ውስጥህን አትጋው፡፡ እነዚህን ወርቃማ ነገሮች የሚነጥቅህ የኑሮ ከፍታና ዝቅታ አይኖርም፡፡ እነዚህ ሲኖሩህ ራስህን የማቅለልን ጥበብ ትቀዳጃለህ! ራሱን ያቀለለ ሰው ደግሞ የሚያጣው ነገር የለም! ራሱን ይቀበላል!
ለምሳሌ በቁመት አጭር ነህ? እና ሴቶች ሁሉ ረዥም ወንድ በመፈለጋቸው የተነሳ ገርልፍሬንድ አጥተሃል? በቃ ተቀበለው ራስህን! የሆንከውን ነገር አትርገም! ሌሎችንም አትርገም! ሴቶችን አታማርር! በራስ መተማመን አይራቅህ! ኮረሪማነትህን ውደደው! አንድ ቀን እንዳንተ አጭር ወንድ የምታስስ ገርልፍሬንድ ታገኛለህ! ባታገኝስ? ኩሩና ኩሩሩ ሆነህ መኖር – እና በሕይወትህ ብዙ ሌሎች ነገሮችን ማሳካት አትችልም? ሴት ካላገኘህ ከዋክብቱ ሁሉ በላይህ ይረግፉብሃል ብሎ የጠነቆለልህ ማነው?!
“No matter where you go, there you are!” የሚል የቆየ አባባል አለ፡፡ የትም ሄድክ የት – ያው ራስህ ነህ፣ ዶጮ?! እንደማለት፡፡ ያው ራስህ ነህ፡፡ ሜሪላንድም ተገኘህ ሀገረማርያም፣ ዳንግላም ተገኘህ ቨርጂኒያ፣ ባሃማም ተገኘህ ቡታጅራ፣ ሃዋይም ተገኘህ ሃረር፣ አሜሪካም ተገኘህ ጋሞጎፋ – ነፍሴ፣ ያው ራስህ፣ ያው የምታውቀውና አብረኸው የኖርከው ራስህ እኮ ነህ! እና ምን የተለየ ነገር ተገኘ? ምንድነው ቡረቃው? ምንድነው ኩምታው? ለምን ህይወትህን በተገኘህበት ቦታ ሁሉ ሸብረቅና ቀለል አድርህ በደስታ አትኖራትም? ለምን ራስህን ከቦታ ጋር ታቆራኘዋለህ?
ጃማይካም ብትሄድ፣ ቀበናም ብትሄድ፣ ቦርከናም ሄድክ ሰሎሞን አይላንድ… ያው ውሃ ውሃ ነው! አጠገብህ ባለው ውሃ ዘለህ ግባና ተንቦጫረቅ! ውሃው የት በመገኘቱ ሳይሆን፣ በውሃህ ውስጥ በመንቦጫረቁ ደስ ተሰኝበት! በቃ ህይወት ማለት እኮ ባለህና በሆንከው ተደሳች መሆን ነው! ቆይ ዝሆን የሚያህል ኬክ ቢሰጥህ ችለህ ትውጠዋለህ? የምትበላት ኬክ ያቺኑ በሆድህ ልክ የሆነችዋን ብቻ ነው! ለምን ሁሉንም ላግበስብስ የሚል አልጠግብ-ባይ ትሆናለህ?!
መጠርቃት! ይህ ነው የህይወት የተደሳችነት ቁልፉ! ለመጠርቃት የምትፈልገውን ነገር ምረጥ፡፡ የሚያስፈልግህ ነገር ምን እንደሆነ እወቅ፡፡ የምትፈልገውን ነገር ማወቅ፣ ያንኑ በእርጋታ ለማግኘት መሥራት፣ እስከዚያው በጉዞው መደሰት፣ ቢሆንም ባይሆንም «እንጦረጦስ ሊገባ እንደሚችል» ማወቅ፣ ራስህን መጠበቅ፣ ለምትሠራው ነገር ኃላፊነት መውሰድ፣ እና ስላለመቻልህ እና ስላልቻልካቸው ነገሮች እያነሳ ጠዋት ማታ የሚጨቀጭቅህ ነዝናዛ ህሊና ካለህ ያንን ማስታገስ፣.. እነዚህን አድርግና ህይወትህን በወጉ አጣጥማት፡፡
ደራሲው «The Subtle Art of Not Giving a Fuck» ምን እንደሆነ ሲያብራራ፣ ንዴተኛ ሆነህ ንዴተኝነትህን ለማስወገድ ውስጥህን ከማለማመድ ይልቅ፣ ንዴትህን በማገንፈልህ መልሰህ በንዴት መገንፈል መሆኑን፤ ማጣትህን ለማስወገድ ከመሥራት ይልቅ ማጣትህን እያሰብክ መብከንከን መሆኑን ይዘረዝርና፣ ይህን ‹‹አንተ እኮ ቀሽም ነህ! አንተ እኮ አትችልም! አንተኮ ትገነፍላለህ! አንተኮ…›› የሚለውን የውስጥ ጩኸት (Feedback Loop from Hell) ማስወገድና፣ ካለህበት ጋር ተስማምቶና ያለህን ተቀብሎ የሚጓዝ ቀናና ነገርን ሁሉ ያቀለለ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን የስኬተኛ ህይወት ቁልፍ አለ ከተባለ ይህ መሆኑን ደጋግሞ ያወሳል፡-
“It’s this part that gets us into trouble. We feel bad about feeling bad. We feel guilty for feeling guilty. We get angry about getting angry. We get anxious about feeling anxious. What is wrong with me? This is why not giving a fuck is so key. This is why it’s going to save the world. And it’s going to save it by accepting that the world is totally fucked and that’s all right, because it’s always been that way, and always will be.
“By not giving a fuck that you feel bad, you short-circuit the Feedback Loop from Hell; you say to yourself, ‘I feel this shit, but who gives a fuck?’ And then, as if sprinkled by magic fuck-giving fairy dust, you stop hating yourself for feeling so bad. The desire for more positive experience is itself a negative experience. And, paradoxically, the acceptance of one’s negative experience is itself a positive experience.
“This is a total mind-fuck. To not give a fuck is to stare down life’s most terrifying and difficult challenges and still take action, and feel happy about the voyage.”
በመጨረሻም ደራሲው እስካሁን በሰማናቸው ነገሮች ላይ 5 (አምስት) እጅግ መሠረታዊ የሚባሉ የህይወት ቁምነገሮችን (ጥበቦችን) አነግበን (embrace አድርገን ወይም በውስጣችን ተቀብለን) እንድንጓዝ ይመክረናል፡፡ እነዚህም፡-
1ኛ/ በህይወታችን ስለምናደርጋቸው ነገሮች ሀላፊነትን መውሰድ (Accepting Responsiblity)፣
2ኛ/ በህይወታችን ስለሚከሰቱ ብዙ ነገሮች በእርግጠኝነት ማወቅ የማንችል ፍጡራን መሆናችንን መቀበል (Accepting Uncertainty)፣
3ኛ/ በህይወት ስንጓዝ ውድቀትን በጸጋ መቀበልና ብርቅ እንዳልሆነ ማወቅ (Accepting Failure)፣
4ኛ/ በህይወት ውስጥ ‹አትፈለግም!› እና ‹አልፈልግሽም!› የሚሉትን ቃላት ለመስማት ዝግጁ መሆንና በጸጋ መቀበል (Accepting Rejection)፣ እና
5ኛ/ ህይወት የቱንም ያህል ብትረዝም የሆነ ቀን ላይ ግን ሁሉንም ጥለን እንደምንሞት ደጋግመን ማሰብና ሞትን በጸጋ መቀበል (Accepting Mortality)፡፡
መጽሐፉ 206 ገጾች አሉት፡፡ አሁን 4ኛ ገጽ ላይ መግባቴን በዓየኔ-ቂጥ እየገረመምኩት ነው፡፡ ብዙ ማለት እፈልግ ነበር፡፡ ሲበዛም ይሰለቻልና፣ እስካሁን ያልኩትን ለበጎ ያድርግልን ብዬ እዚህ ላይ ላብቃ፡፡
ላበቃ ስል አንድ የቆየ ወዳጄ ከዓመታት በፊት ከት ብሎ እየሳቀ እኔን የተረበባቸው ቃላት ድንገት ትዝ አሉኝ፡፡ በአንድ ዝነኛ ሆቴል በእሱ አጠራር ካለፈላቸው ሰዎች ጋር፣ የሀብታም አጥርን ዘልዬ» ተቀላቅዬ ስዝናና፣ ከሩቅ በግርምት ተመልክቶኝ ያለፈበትን አጋጣሚ እያነሳ በሳቅ ፈረሰብኝ – በድፍረቴ! እና ያላቅሜ ኪሴን ለማሟጠጥ ባለኝ ያልተቆጠበ ተነሳሽነት! (ጉድ እኮ ነው!) በጣም ያሳቀኝ ግን እሱ ያን የእኔን ነገር እንደ አጠቃላይ የሐረር ልጆች ጸባይ አድርጎ ያቀረበበት መንገድ ነበር፡- «እናንተ ሐረሮች እኮ የምትገርሙኝ… ሀብት ሳይኖራችሁ ልክ እንደ ሀብታም ተንደላቃችሁ የምትኖሩት ነገራችሁኮ ነው!»
ወንድሜ! እኔ’ኮ በዚያ ያ ወዳጄ በማይደፍረው ሥፍራ ሌላ ነገር አልሠራሁም፡፡ ስኳር ያልገባባትን ያቺኑ የምወዳትን የተለመደች እንደወረደች ቡናዬን፣ ከድንች ጥብስ (ቺፕስ) ጋር ነበር ደልቀቅ ብዬ ሳወራርድ ያገኘኝ፡፡
አሁን ሳስበው፣ ለካ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ማርክ ማንሰን – የሚመክረን – ልክ እንደዛ እንድንሆን ነበር! በቃ የፈለገው ቦታ ሂድ! ራስህን ከሰው ጋር አታነጻጽር! ቡናህን ከድንችህ ጋር ደስ ብሎህ ጠጣ! እና ውልቅ ብለህ ወደምትሄድበት ጉዳይህ ሂድ! ዓለም ይቺው ናት! በኋላ ኪስህ የአስር ሚሊየን ብር ቼክ ብትይዝ ኖሮ የቡናውና የቺፕሱ ጣዕም ከዚያ የተለየ ይሆን ነበር? በፍጹም! ቡናውም ያው ራሱ ቡናው ነው! ድንቹም ያው ራሱ ነው! አንተም አንተው ራስህ ነህ! ባለህ ተደሰት! እንደ ሐረሮች ሁን! ጣጣ-ፈንጣጣ አታብዛ! ቡናህን ጠጣ! ድራፍትህን ጠጣ! ትኩስ ድንችህን ግመጥ! ግን እንዳያቃጥልህ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ! ያለንን ይባርክልን! የበዛ ሠላሙን ይስጠን!