ታሪክን የሗሊት
<<ለኤርትራ ነፃነቷ ከኢትዮጵያ መቀላቀል ብቻ ነው….!!!
ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ
……ተዚህ ሁሉ በሗላ የኤርትራ የውስጥ አስተዳደር በፌደራል አክት መንፈስ ተተሰራ በኋላ ፣ የኤርትራም ህዝብ አሴምብሊውን መርጦ ታፀደ በኋላ ፣ ጃንሆይ ፌደራል አክቱንና የኤርትራን የውስጥ አስተዳደር ህግ አፀደቁት። ተዚያም አስመራ ገብተው ምፅዋንም ጎበኙ ፣ እኔም አብሬ ነበርኩ። በዚያን ጊዜ የኤርትራን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ደስታ ለመግለፅ ቃልም አይገኝለትም!
……………በአውሮፕላን ያደረኩት ጉዞ (ኤርትራን ለማስመለስ) አንድ ጊዜ ሲታሰብ ላንድ ወር ያህል (ወደ 700 ሰአት) በሰማይና በመሬት መካከል እንደቆየሁ ነበር።ያደረኩት ዲስኩር እና ኢንተርቬንሽን በሺህ የሚቆጠር ገፅ ይሆናል። ይህ ሁሉ በአርካይቭ ይገኛል። ተዚህ በኋላ ራስ አንዳርጌ የጃንሆይ ሪፕረዘንታቲቭ ሆነው፣ አቶ ተድላ ባህሩ (ያንድነት ወኪል) ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ሆነው ኤርትራን ማስተዳደር ጀመርን።…>>
<<…..የሳንፍራንሲስኮ ጉባኤ እንደተቃረበ እንደሌሎቹ ነጻ መንግሰቶች ና አላይ የሆኑት ጥሪ ተደረገልን /በአሜሪካን ድጋፍ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ተአፍሪካ ሦስት መንግስቶች ብቻ ነበሩ/ኢትዮጵያ ፣ላይቤሪያ እና ግብጽ ፡፡/ ተእስያ ማንም የለም፤ ሕንድም ገና ነጻ አልወጣችም ነበር፡፡ የስብሰባው ተካፋዮች ጠቅላላው ወደ 52 መንግስታት ነበሩ፡፡
የኛ ዴሊጌሽን የሚመራው በቢትወደድ መኮንን ነበር፡፡እኔ ምክትል ሄድ ኦፍ ደሊጌሽን ነበርኩ፡፡ ሌሎቹ ብላታ ኤፍሬም ፣ አቶ አማኑኤል ፣ አቶ አምባዬ ፣ አቶ ምናሴ እና አቶ ጴጥሮስ ነበርን፡፡ ቢትወደድ መኮንን የቋንቋም ፤ ሌላም ችግር ስላገኛቸው ወዲያው ተመለሱ፡፡ እኔም ሄድ ኦፍ ዲሊጌሽን ሆኜ ሥራው ተጀመረ /ግንቦት 1944/
በሥራውም ጊዜ የኢትዮጵያ ዲሊጌሽን ብዙ አመንድመንት እያቀረበ ለጉባኤው ኮንትሪቢውሽን አድርጓል፡፡ /ፕሮሲቨርባል ማየት ፤ የዩናይትድ ኔሽን ዶክመንት፡፡/ እኔም ተጣልያን ጋር ባለን ኤክስፒሪያንስ እየጠቀስኩ ብዙ ኢንተርቬሽን አድረግ ነበር፡፡ አንዱ በምሳሌ ያስቀበልነው ፤ “አንድ መንግስት አንድ ሌላ ሀይል ሊጠቃኝ ይሰናዳል ብሎ አቤት ባለ ጊዜያት ሴኩውሪቲ ካውንስል መሰብሰብ አለበት” ብዬ ቀርቤ ነበር፡፡ አሜሪካኖች ይህን ሃሳብ በሆነ ባልሆነው እውነቱ ሳይረጋገጥ መሰብሰብ የለበትም ብለው በብርቱ ተቃወመው ነበር፡፡ እኔም “ሰባት ወር ሙሉ ጣልያን ሊወጋን ነው እያልን ጄኔቭ አቤቱታችንን የሚሰማው ጠፍቶ ጣልያን ጦሩን መድፉንና ታንኩን በሬድሲ ለማጋዝ ጊዜ ተሰጥቶት ፤ በኋላ ሰላሳ ኪሎ ሜትር ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ በኋላ ነው አቤቱታችንን ለማየት የተቀበሉት፡፡በክርክሩም ጊዜ ጣልያን እኛን ለመውረር ቻለ” እያልኩ አስረዳሁ፡፡ ብዙ መንግስቶች ይልቁንም ፈረንሳዮች በዚህ ኢምፕሬስ ሆነው አመንድማውን ተቀበሉት ፡፡በዚህ ምክንያት ነው አሁን ማንም መንግስት አቤት ሲል በየጊዜው ሴኩውሪቲ ካውንስል የሚሰበሰበው፡፡ ታንድ ወር በኋላ ስራው አለቀና በቻርተሩ ላይ የሃምሳ ሁለት ሀገራት ሄድ ኦፍ ዴሊጌሽን ዲክላራሲዮን እያደረጉ በየተራ ፈረሙ፡፡ እኔም በተራዬ በኢትዮጵያ ስም ፊርማዬን ዲክላራሲዮን አደረግሁ፡፡ ስፈርም የተነሳው ፎቶግራፍና ዲክላራሲዩን አርካይቭ ይገኛል፡፡…>>
~~~~~~~
ምንጭ:- ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ መስከረም 10 ቀን ፣ 1967 ዓ.ም. ላይ ለመርማሪ ኮሚሲን ያቀረቡትን ጽሁፍ ሰንዶ ፥ በ 2003 ዓ.ም ላይ “የአክሊሉ ማስታወሻ ” (Aklilu Remembers) በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ካሳተመው መፅሐፍ ላይ የተወሰደ።