>

የናይል ሸለቆ ፖለቲካ፣ ታሪካዊ ምልከታና አሁን ያለው ሁነትክፍል ሁለት (ደረጀ መላኩ - ሰብዓዊ  መብት ተሟጋች)

የናይል ሸለቆ ፖለቲካ፣ ታሪካዊ ምልከታና አሁን ያለው ሁነት

ደረጀ መላኩ ( ሰብዓዊ  መብት ተሟጋች)

ክፍል ሁለት


ኢትዮጵያ እና መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገው ፖለቲካ፣ ጊዜውን ጠብቆ በሚፈነዳ ፈንጂ ላይ መደነስ

 ምንም እንኳን ይሁንና በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ላይ ( በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ) በተያዘለት የግዜ ገደብ የውሃ ሙሌት ተከናውኖ ካበቃ በኋላ ግድቡ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ኢትዮጵያ የሃይል ምንጭ ማመንጨት ብትጀምርም ኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግሯን መፍታት የምትችል አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ ያለባት ይመስለኛል ፡፡ ኢትዮጵያ ከተደቀነባት አደጋ ለመውጣት ከጎሳ ፖለቲካ ፍልስፍና መገላገል አለባት፡፡ ኢትዮጵያ ወንድማማችነት፣ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት ሀገር መሆን አለባት፡፡ በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ግዜ በኢትዮጵያ ምድር የጎሳ ፖለቲካን ገቢራዊ ያደረገችው ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1936 እስከ 1941 በወረረችበት ግዜ ነበር፡፡ በቅርብ ግዜ ውስጥ ደግሞ ማለትም ከ30 አመታት በፊት የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ቅኝ ገዢ ጣሊያን እንዳደረግቸው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ስርትን በመዘርጋት በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካን መርዝ ረጭቷል፡፡ ይህ ኢትዮጵያን የጎሳ ፖለቲካ ቤተ ሙከራ የማድረግ እኩይ ተግባር አሁን ድረስ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፡፡ በተቃራኒው ይህ የጎሳ ፖለቲካ በአሳዛኝ ሁኔታ ሰላም፣አንድነትና ፍቅር እንዲሁም ፍትህና እኩልነት ለኢትዮጵያ ህዝብ  ከማስፈን አኳያ ወድቋል፡፡ ይህ እውነት እየታወቀ አሁን ያለው የኢትዮጵያ አገዛዝ ከጎሳ ፖለቲካ መላቀቅ የፈለገ አይመስልም፡፡ አሁን ያለው አገዛዝ ከሩሲያ ጋር ተመሳስሎ ካለውና በቀድሞው ኢህአዲግ አገዛዝ የተቀመረውን የጎሳ ፖለቲካ መቼ ለመቀየር እንዳሰበ ገና አልነገረንም፡፡ በዚሁ የጎሳ ፖለቲካ ካርድ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

እንዲህ አይነት የቆየ የቅኝ ገዢዎች ሰትራቴጂ ወደ ታሪክ ማህደር ውስጥ መዶል አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ከዚህ ባሻግር  የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያውን መሃከል ጥላቻ እንዲዘራ መፍቀድ የለብንም፡፡ ከዚህ ባሻር የጎሳ ፖለቲካ መደብለ ፓርቲ ስርአት ለመዘርጋት እንቅፋት ደንቃራ የሚፈጥር ነው ተብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡

አሁን በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት የወጣው በዋነኛነት በወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ይህ ህገመንግስት የጎሳ ፖለቲካን ገቢራዊ እንዲሆን የሚፈቅድ በመሆኑ በሰለጠነ መንገድ በውይይት መሻሻል ያለበት ይመስለኛል፡፡ በተለይም የህግ ባለሙያዎች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች እና ኢትዮጵያዊ ምሁራን እንዲሁም የተፎካካሪ ፖለቲካ መሪዎችና የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች አንድ ላይ በቀና መንፈስ ቁጭ ብለው ህገመንግስቱ ስለሚሻሻልበት መንገድ በሰከነ መንፈስ መነጋገር ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ በእኔ የግል አስተያየት ህገመንግስቱ መሻሻል አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ህገመንግስቱ የግለሰብ መብትን ለማስከበር፣ የህግ በላይነት እንዲከበር ዋስትና መስጠት መቻል አለበት፡፡ የመንግስት ቅርንጫፎች ( ህግ አስፈጻሚው፣ተርጓሚውና ህግ አውጪው) አንዱ በሌላኛው ጣልቃ እንዳይገባ አስገዳጅ አንቀጾችን ማካተት አለበት፡፡ከዚህ ባሻግር የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በነቢብም በገቢርም እንዲከወኑ የሚያዙ አንቀጾች መካተት አለባቸው፡፡ ከዚህ በግልባጩ በህገመንግስቱ ውስጥ እንደው ዝም ብሎ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ የሚያወሱ አንቀጾችን ብቻ ማካተቱ ጠቃሚነቱ የጎላ አይደለም፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራያዊ መብቶችን ለማስከበር የሚረዱ መንገዶችን ማካተት ተገቢ ነው፡፡

ከጎሳ ፖለቲካ መገላገል ካልቻልን ስቃይ፣ደም መፋሰስ እና የሰው ልጆች ፍዳ መቀጠሉ አይቀሬ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አፍሪካ በቅኝ አገዛዝ ዘመን አጋጥሟት የነበረውን መጥፎ እጣፈንታ፣ ሌሎች አፍሪካውያን በቅኝ አገዛዝ ዘመን ማብቂያ ላይ ወደ ታሪክ ትቢያነት የቀበሩትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ( የጎሳ ፖለቲካ ማለቴ ነው) ኢትዮጵያ በፍጥነት ተራማጅ በሆነ የፖለቲካ አስተምህሮ ለመቀየር ጊዜ መፍጀት ያለባት አይመስለኝም፡፡

በአጠቃላይ የጎሳ ፖለቲካ በበላይነት በሰፈነባት ሀገር ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ አይታይም ፡፡ መልካም እድል መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡በአጭሩ በአንድ ሀገር ላይ የጎሳን ፖለቲካ ማራመድ ግዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ፈንጂ የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡

ከላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች የሀገሪቱን አንድነት ለማናጋት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡ በጎሳና ሃይማኖት መሃከል ያሉ ጠባብ ልዩነቶችን ( ቀዳዳዎችን) በመፈለግ ነዳጅ ለማርከፍከፍ ይቅበዘበዛሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በኢትዮጵያውያን መሃከል ጥላቻን ይዘራሉ፡፡ በነገራችን ላይ ጎሳን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በበዘባት ሀገር የውጭ መዋለንዋይ አፍሳሾች ድርሽ ማለት ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ በሌላው ሳንቲሙ ግልባጭ ግን   የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት  በአንድ ሀገር ግጭት ወይም ጦርነት ከተከሰተ በኋላ በሰው እልቂት ለማትረፍ የቋመጡ እና ምንግዜም ቢሆን የራሳቸውን ትርፍ ብቻ በሚያሰሉ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ሲሳይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በአንድ ለሊት የሚመጡ ወይም ለብዙ ግዜያት መቀመጥ አላማቸው ያልሆነ ድንበር ዘለል ማፊያ መሰል ኩባንያዎች  ሀገሪቱን ለመበዝበዝ ምቹ ሁኔታ ( ለም መሬት) ይፈጠርላቸዋል፡፡ (fly-by-night operators will take advantage of the situation and exploit the country)  ( ለአብነት ያህል በኢራቅ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ነዳጅ ዘይት ሀብት፣በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ደቡብ ሱዳን የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት የየትኞቹ ሀገራት ድንበር ዘለል ኩባንያዎች እየቦጠቦጡት እንደሚገኙ ህሊና ለፈጠረበት ሰው ግልጽ ይመስለኛል፡፡)

ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ለታሪካዊ ጠላቶቻቸው በራቸውን ከፍተው መጠበቅ የለባቸውም፡፡ ኢትዮጵያውያን የከፋፍለህ ግዛ ውርዴ የሆነውን የጎሳ ፖለቲካ በሰከነ መንፈስ በውይይት በሰለጠነ የፖለቲካ ፍልስፍና መተካት አለባቸው፡፡ የቀደሙት የኢትዮጵያና አፍሪካ አባቶች እንዳደረጉት ሁሉ  የኢትዮጵያ ወጣቶች ለም አይምሮአቸውን በመጠቀም  የሀገሪቱን ሀብታም ታሪክ፣ብዝሃነት፣ በእኩልነት መንፈስ፣ በኢትዮጵያዊነት እና አፍሪካዊነት መንፈስ ላይ ቆመው አዲስ የፖለቲካ መስመር መከተል የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ በብርቱ ሊያስቡበት ( ሊተገብሩት) ይገባል፡፡ ነገ እነርሱ በመሆኑ እንቅልፍ አጥተው ወደ ዘመናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚያስገባቸውን መንገድ ዛሬውኑ መፈለግ አለባቸው ባይ ነኝ፡፡

ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከባለፈው አመት ወደ ዘንድሮው አመት የተላለፈው የኢትዮጵያው ብሔራዊ የምርጫ ውድድር በሁሉም ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይሁንታ እንዳገኘ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ዘንድሮው አመት መተላለፍ የለበትም ብሎ የተከራከረው መቀመጫውን ትግራይ ክልል ያደረገው የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ወያኔ ብቻ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ምርጫው የተላለፈው የኮቪዲ ቫይረስ በሽታ በአሳደረው  ስጋት ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ዘንድሮ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩ ተወዳዳሪዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በነጻነት እንደፈለጉት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የምረጡኝ ዘመቻ ለማካሄድ የተለያዩ ሰትራቴጂዎች ነድፈው ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም የጎሳ ፖለቲካ ስርአት በደነቀረባቸው ጋሬጣ ምክንያት ያሰቡት አቅድ እንዳልተሳካ የሚያሳዩ መረጃዎች ከብዙ መገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ደግሞ የጸጥታው ጉዳይ አስተማማኝ ስላልነበር  ተጉዘው የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ለማስተዋወቅ ስጋት  ነበረባቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ወይም ምንም እንኳን ተቀባይነት ያለው የምርጫ አካባቢ በሀገሪቷ ቢሰፍንም ምርጫ ብቻውን ዲሞክራሲ ስለመስፈኑ ዋስትና አይሆንም፡፡

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሄሱት ከሆነ በአፍሪካ እና በማደግ ላይ ባሉ በርካታ ሀገሮች የሚደረጉ የምርጫ ውድድሮች ውጤቶቻቸው የሲቪል ነጻነትን ለመግፈፍ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ መራጩ ህዝብ በምርጫ አሸንፍኩ የሚለው ፓርቲ መሪ እና ባለስልጣናት የስልጣን ገደብ የቱ ድረስ እንደሆነ ማወቅ አይችልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የሲቪል ነጻነቶች ስለሚገፈፉ ነው፡፡

          ፌርድ ዘካሪያ የተባላ ምሁር ( Fareed Zakaria) ‹‹ የወደፊቱ ነጻነት ›› (The Future of Freedom, )  በተሰኘው መጽሀፉ ውስጥ በዝርዝር እንዳስቀመጠው በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የተደረጉ የምርጫ ውድድሮች በብዙ ተስፋ የተሞሉ የነበሩ ቢሆኑም፣መሪዎችም ሆነ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ብዙ አማላይና ማራኪ በሆኑ ዲስኩሮቻቸው ቃል ቢገቡም የምርጫው ውጤት ብቻውን ዴሞክራሲን ምሉሄበኩልሄ በሆነ መልኩ ማምጣት አይቻለውም፡፡ 

በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የተደረጉ የምርጫ ውድድሮች ምስክር እንደሆኑት ውጤታቸው ማለትም ከምርጫው ፍጻሜ በኋላ የሚከተሉት ሁነቶች በገቢርም በነቢብም ታይተዋል

  • አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት
  • የግልጽነት ጉድለት
  • የህግ የበላይነት አለመከበር
  • የዲሞክራሲ አለመከበር
  • ሙስና ይጨምራል
  • የድሃው ህብረተሰብ ክፍል ተስፋ ይጨልማል( ወይም ድህነት በከፋ መልኩ ይጨምራል)

በአንዲት ሀገር ላይ ዛቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት ይረዳ ዘንድ፣ የዲሞክራሲ መርሆዎች እንዲጎመሩ ከተፈለገ ብሔራዊ ውይይትና ልዩነትን በሰከነ መንፈስ መፍታት ከብሔራዊ ምርጫው በፊት መቅደም አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንዲት ሀገር የፖለቲካ ቀውስ፣ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ቀውስን ለመፍታት ( ለአብነት ያህል የርስበርስ ጦርነት ውስጥ ከተዶልን) መሰረታዊ ችግራችንን ተረድተን አምነን ተቀብልን፣ ለመፍታት መነጋገር መወያየት አለብን፡፡ በነገራችን ላይ በአንድ ሀገር ብሔራዊ ሰላምና ብሔራዊ እርቅ መቅደም አለበት የሚለው ሌላው መልእክቴ ነው፡፡ 

ግብጽ በአፍሪካ መልክአምድር የምትገኝ ሀገር

ኢትዮጵያ የታላቁ የአባይ ግድብን መገንባት ከጀመረች ወዲህ ግብጽ ቅሬታዋን ማሰማት ቀጥላላች፡፡ ግብጽ በታላቁ የአባይ ግድብ ዙሪያ የሚደረገውን ውይይት ( ሶስቱ ሀገራት ማለትም ግብጽ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ውይይት ወይም የሽምግልና ሂደት) ለማሳለጥ የአፍሪካው ህብረት ችሎታ የለውም ብለው ያምናሉ፡፡ ግብጽ ከአፍሪካ አንድነት ፍልስፍና ውጭ ነው የምትራመደው፡፡ ግብጽ የፓንአፈሪካኒዝም ፍልስፍናን የምትጻረር ሀገርም ናት፡፡ ከዚህ ባሻግር የአፍሪካው ህብረት ሶስቱን ሀገራት እያደራደረ ባለበት ቅስፈት ግብጽ ጉዳዩን ወደ አውሮፓ ህብረትና የተባበረችው አሜሪካ ለመወስድ መሞከሯ የግብጽን ትምክህት ነው የሚያሳየን፡፡ ከዚህ ባሻግር የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት የሚለውን መርህ የጣሰ ነበር፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1963 የተመሰረተውን የአፍሪካውን አንድነት ፍልስፍናም የሚጻረር አቋም ነው ግብጽ እያራመደች የምትገኘው፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ኪሎ ስጋ አንድሺህ ብር በሆነባት ኢትዮጵያ፣አንድ እፍኝ ዳቦ 4 ብር በሚሸጥባት ሀገር፣አንድ እንቁላል ስምንት ብር በሚሸጥባት ኢትዮጵያ ወዘተ ችጋር ቤቱን በሰራባት ኢትዮጵያ  አንድ ታላቅ ግድብ ተገንብቶ እንዳያልቅ ግብጽ የምትሸርበው ሴራ ሲስተዋል በእውነቱ ልብን ያደማል፡፡

ምንም እንኳን ግብጽ በአፍሪካ አህጉር የምትገኝ ሀገር ብትሆንም  የግብጽ ፕሬዜዴንት የነበሩት ናስር ናስሪዝም በሚለው ፍልስፍናቸው የግብጽን ማንነት ከአፍሪካ፣ አረብና እስልምና ጋር ተዳቀለ ነው የሚል ድምዳሜ አላቸው፡፡ ፕሬዜዴንት ናስር ይህንኑ ፍልስፍናቸውን Egypt’s Liberation: The Philosophy of the Revolution (1955)) በሚለው መጽሐፋቸው ላይ አስቀምጠውታል፡፡ በአሁኑ ዘመን የግብጽ ፕሬዜዴንት የሆኑት አልሲሲም ፖለቲካዊ ፍለስፍናም ቢሆን ግብጽ አፍሪካዊ ሀገር አይደለችም፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ በግብጽ የሚኖሩ አብዛኞቹ ጥቁር አፍሪካውያን የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ ግብጻውያን ለአፍሪካዊነት ማንነት የሚደማ ልብ ያላቸው አይደሉም፡፡

በሌላ በኩል የአፍሪካ ህብረት ዋና አላማ፡-

  • በአፍሪካ ሀገራት መሃከል አንድነትና ትብብር ማስፈን
  • አፍሪካውያን በኑሮ ደረጃ የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ለማስቻል ይረዳ ዘንድ ተብብራቸውንና ህብረታቸውን የበለጠ ማጠናከር
  • የአፍሪካ ሀገሮችን ሉአላዊነትና አንድነትን መጠበቅ

የታላቁ አባይ ግድብ  ትሩፋት

የታላቁ አባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፡-

  • ኢትዮጵያ በእድገት ጎዳና ላይ ተጉዛ ከችጋር እንድትገላገል ይረዳታል
  • ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እንድታሰመዘግብ ከመርዳቱ ባሻግር በአካባቢው ሀገራት አኳያ የአካባቢውን ልማት እድገት የሚያፋጥን ይሆናል፡፡
  • እንዲህ አይነት ታላቅ ጥረት ደግሞ አፍሪካ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ጥር 2015 ያወጣችውን 2063 አጀንዳ ገቢራዊ ለማድረግ ያስችላል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው መራር እውነት እንዳለ ሆኖ ግብጽ ከአፍሪካ መርሆ ውጭ የሆነ አስተሳሰብ  ውጭ የምታራምድ ናት፡፡ ወይም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት አይቻልም ብላ ታምናለች፡፡ ግብጽ  በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ የአረብ ሀገራትና ከማግረብ ሀገራት ( በሰሜን አፍሪካ የሚገኙትን ሞሮኮ፣አልጄሪያ፣ቱኒዝያ፣ሊቢያ ያጠቃልላል) ድጋፍ በማግኘቷ ምክንያት በአፍሪካውያንና አረብ ሀገራት መሃከል ስምጥ ሸለቆ ፈጥሮ ይገኛል፡፡ ( ክፈተት ፈጥሯል፡፡)

ግብጽ ለአፍሪካ ታሪክ ደንታ እንደሌላት ማሳያው ባለታሪክ አፍሪካ ላይ የምትሸርበው ሴራ ነው፡፤ይህም ማለት አሁን ያሉት የግብጽ መሪ አልሲሲና መንግስታቸው ከአፍሪካ ፍላጎት ውጭ፣ ከአፍሪካ ታሪክና ከፓንአፍሪካኒዝም ፍልስፍና ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ኢትዮጵያን ማዳከም እና የጥቁር አባይ ወንዝን ከምንጩ መቆጣጠር ነው፡፡

የታላቁ አባይ ግድብ ግንባታ በባለሙያዎች አይን

ከኢትዮጵያ አኳያ የቆሙ ከፍተኛ የውሃ ኤክስፐርቶች ( ወይም በታላቁ የአባይ ግድብ ግንባታ ላይ የኢትዮጵያ ቴክኒክ አማካሪዎች)  ምስክርነት ከሆነ የታላቁ አባይ ግድብ ከቴክኒክ አኳያ እንከን አይወጣለትም፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ጥቅሞችን ለሱዳንና ግብጽ ሰጣል፡፤

  • የናይል ወንዝ ውሃ ፍሰት መጠኑ የተስተካከለ እንዲሆን ይረዳል
  • የጎርፍ አደጋን ይቀንሳል
  • በሱዳንና ግብጽ የሚገኙት ግድቦች በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በትነት ምክንያት የሚባክነው የውሃ መጠን ከፍተኛ ሲሆን፣ በታላቁ የአባይ ወንዝ  ግድብ  ላይ በሙቀት ምክንያት የሚተነው የውሃ መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡
  • ግብጽም ሆነች ሱዳን በተመጣጣኝ ዋጋ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ ያገኛሉ፡፡
  • በግልጽ እንደሚታየው የታላቁ አባይ ወንዝ ግድብ ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ ለሱዳንና ለግብጽም ጥቅም መስጠቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው መራር እውነት እንዳለ ቢሆንም  የግብጽ መሪ አልሲሲ የታላቁን አባይ ግድብ ግንባታ ለውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው መጠቀሚ ካደረጉት ውለው አድረዋል፡፡ ይህ ታስቦበትና ተጠንቶ የግብጽን ህዝብ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለመቀልበስ የቀረበ ሴራ ነበር፡፡ ሌላው የሚያበሳጨው ጉዳይ ሱዳን በታላቁ የአባይ ግድብ የያዘችው አቋም ነው፡፡ ቀደም ብዬ ለመጠቃቀስ እንደሞክርኩት ግድቡ ለሱዳን ጥቅም መስጠቱ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሚሊተሪና ሲቪል ጥምር መንግስቱ ቁንጮ ባለስልጣን የሆኑት ጄኔራል አብዱልፈታህ ቡርሃን (the head of a military-civilian council, General Abdel-Fattah Burhan ) ሁለቱን ጎረቤት ሀገራት ( ማለትም ሱዳንና ኢትዮጵያን) የሚያቃቅሩ በርካታ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፡፡ በነገራችን ላይ በባህል፣ታሪክ፣ፖለቲካና ኢኮኖሚ ለረጅም ግዜ የቆየ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ ሁለቱም ሀገራት የሚጠቀሙት በመልካም የጉርብትና መቀጠል ከቻሉ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ የሱዳን ሁነኛ ፍላጎት የሚጠበቀው በሰላምና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሲያደርጉ ብቻና ብቻ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግብጽ ትምክህቷንና የዜሮ ድምር የፖለቲካ አስተሳሰቧን መቅበር ያለባት ይመስለኛል፡፡ ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበትን ስምምነት ላይ መድረስ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በሻግር ከእስራኤል የዲፕሎማቲክ ዘዴ ብትማር ትጠቀማለች ብዬ አስባለሁ፡፡ ግብጽና እስራኤል የዲፕሎማቲክ ግንኙነት በመመስረታቸው የተጠቀሙት ሁለቱም ሀገራት ይመስሉኛል፡፡ ከዚህ ባሻግር ግብጽ እስራኤል ገቢራዊ ካደረገችው የጠብታ ውሃ እርሻ ልማት መማሩና ገቢራዊ ማድረጉ ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ የእስራኤል የውሃ ቴክኖሎጂ ማለትም ውሃን በአግባቡ የምታደርገው ጥንቃቄና ጥበቃ ለሁሉም ሀገራት የሚጠቅም ነው፡፡ ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ እስራኤል ያላትን ጥቂት የውሃ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀምና ለመንከባከብ የምታደርገው ጥረት የሚያስደንቅ ነው፡፡ ግብጽ አለአግባብ የምታባክነው የውሃ መጠን ከፍተኛ ነው ይባላል፡፡ ስለሆነም ግብጽ ስለ የውሃ አጠቃቀም ከእስራኤል ብትማር ይበጃታል ባይ ነኝ፡፡ የናይል ወንዝ ውሃን ሁሉም ሀገራት በአግባቡ መጠቀም ከቻሉበት በሰላም ተስማምተው ማደግ ያስችላቸዋል፡፡ ግብጽ የበለጠ በአካባቢ እንክብካቤ ላይ ማተኩሩም ይበጃታል ባይ ነኝ፡፡ ግብጾች ማስተዋል ያለባቸው ሌላው ጉዳይ በግብጽ በረሃ ውስጥ በትነት የሚባክነው ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ ከዚሁ የተፈጥሮ ሁነት ጋር ሲወዳደር በኢትዮጵያ ግድብ ስለተገነባ ግብጽን የሚጎዳት ነገር የለም ተብሎ ድምዳሜ ላይ ባይደረስም ያዙኝ ልቀቁኝ የሚያስብል አይደለም፡፡ 

በነገራችን ላይ የታላቁ አባይ ወንዝ ግድብ ፕላን በተመለከተ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 ለሱዳንና ግብጽ ገለጻ እንደተደረገላቸው የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ስለ ቴክኒካል መረጃዎችም ያገኙም ይመስለኛል፡፡ ከዚህም ባሻግር ለግድቡ ግንባታ ይረዳ ዘንድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጋብዘው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ግብጽ የኢትዮጵያን ጥያቄ አልተቀበለችወም ነበር፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ወይም ብድር እንዳታገኝ እረጅም የዲፕሎማቲክ ጉዞ አድርጋለች፡፡ በግብጽ የዲፕሎማቲክ ዘመቻም ሆነ በሌላ ምክንያት የተነሳ ኢትዮጵያ ለታላቁ የአባይ ግድብ መስሪያ የሚሆን ገንዘብ በብድርም ሆነ እርዳታ ስም ከአለሙ የአራጣ አበዳሪ ድርጅት ድጋፍ አላገኘችም፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን እየገነባች ያላቸው መላ ህዝቧ በሚያዋጣው ወረትና የሞራል ድጋፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለታላቁ የአባይ ግድብ ግንባታ ከ5.6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለኑሮው ከሚያስፈልገው ቀንሶ አዋጥቷል ይባላል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ያለችው ግብጽ በበኩሏ ሊቋረጥ የማይችል ቀይ መስመር በማስመር የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ከዚህ ባሻግር ከምንገምተው ውጪ በሀገራችን አለመረጋጋት እንዳይኖር ጉዞዋ እጅጉን ረጀም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት የምትሸርበው እኩይ ሴራ የሚጎዳው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ጦሱ ለአፍሪካውያንና ለአህጉሩ ድርጅቶች የሚተርፍ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የግብጽ ጸብ ያለሽ በዳቦ ትምክህት የአፍሪካ ህብረት የሚያደርገውን ባህላዊ ወይም የተለመደውን ሰላማዊ የግጭት ማስወገድ ዘዴ ይፈታተነዋል፡፡

በሌላኛው ገጽታ የምትገኘው ኢትዮጵያ ግን ከዚህ አኳያ በትክክለኛው መስመር ላይ የምትገኝ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ከባላገራዎቿ ጋር ለገጠማት ውስብስብ ችግር ስትል መፍትሔ የምትጠይቀው የአፍሪካውን ህብረት ሽምግልና ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ችግር የሚፈታው በአፍሪካውያን ነው የሚል ጽ እምነት አላት፡፡ አፍሪካውያን በውስጣዊ ችግሮቻቸው የሌሎች ጣልቃ ገብነትን እንደማይደግፉ ኢትዮጵያ ትረዳለች፡፡ አፍሪካ የአውሮፓውያን ጣልቃ ገብነት የቅኝ አገዛዝ መራር የግፍ ታሪክ ስለሚያስታውሳቸው የውጭ ጣልቃ ገብነት አይቀበሉትም፡፡ ስለሆነም የተባበረችው አሜሪካ ትክክለኛ ፖሊሲ መሆን ያለበት የአፍሪካን መብት ሳትነካ፣ በሞራል መሰረት ላይ ቆማ በቴክኒክና ምክር መርዳት እንጂ ከጠብ ጫሪዋና አልጠግብ ባይዋ ግብጽ ጀርባ መሆን አይጠበቅባትም፡፡ የአሜሪካ መንፈስ መቆም ያለበት ከአፍሪካና ኢትዮጵያ አኳያ መሆን ይገባዋል፡፡ በተለይም የአለም የፖለቲካ ታሪክ ፍንትው አድርጎ እንደሚያሳየን አፍሪካ አሜሪካውያን ከኢትዮጵያ ጋር የቆሙ መሆናቸውን ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ነጻነትም እንዲጠበቅ ድርሻቸው መተኪያ የለውም፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ተጽእኖ አፍሪካን ሊጎዳት ሰለሚችል አፍሪካ አሜሪካውያን ይህን የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት በእጅጉ መቃወም ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በተለይም የትራምፕ አስተዳደር ሁሉንም የአፍሪካ  ሁሉ ሺት ሆል(“shit hole”,)  በማለት የተሳደቡ ሲሆን፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ከዲፕሎማቲክ ውጭ ግብጽ የታላቁን አባይ ግድብ በቦምብ እንድትመታ አረንጓዴ መብራት አብርታላት ነበር፡፡

The former US president insulted African countries, called them a “shit hole”, and undiplomatically gave Egypt a green light to “bomb” the dam. Breaking with Trump foreign policy

ስለሆነም የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዜዴንት የውጭ ፖሊሲን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ አሁን ያለው የባይደን አስተዳደር በገለልተኝነት እሳቤ ላይ ቆሞ የአፍሪካን ህብረት መርዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህን የአፍሪካን ከባድ ቸግር ( በታላቁ የአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ በግብጽ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ መሃከል የጠነሳውን ውዝግብና እሰጥ እገባ ማለቴ ነው፡፡) በአፍሪካውያን እንዲፈታ የአሜሪካ መንግስት ለመርዳት የሞራል ግዴታ አለበት፡፡ የናይል ሸለቆ ፖለቲካዊ ችግር ለአንድ ወገን ወገንተኛ በመሆን የሚፈታ አይሆንም፡፡  አፍሪካውያን የራሳቸውን መዳረሻ እንዲፈልጉ መፍቀድ አለብን፡፡

Filed in: Amharic