>

ወርቃማ ኢትዮጵያዊ ምሥጢሮችና ወቅታዊ የወገን ጥሪ! (አሰፋ ሀይሉ)

 

ወርቃማ ኢትዮጵያዊ ምሥጢሮችና ወቅታዊ የወገን ጥሪ!

አሰፋ ሀይሉ
/ለቁምነገረኛ ልቦች ብቻ! በትዕግሥት የሚነበብ የፍቅር መልዕክት!/
ለምን በመለስ አልጀምርም? አዎ፡፡ ከእሱ ብጀምር፣ የመለስ አፍቃሪ አይደለሁም ማለት አይጠበቅብኝም፡፡ ሁሉም በሚያየው – እና ብዙ ነቀፌታዎችን ተቋቁሜም በመለስ ላይ በማቀርባቸው የሰሉ ሂሶች የማያውቀኝ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ በግል ቂምና ጥላቻ አይደለም፡፡ በፍጹም፡፡ ለሀገር ይበጃል በማለት፣ ለመማማር፣ ውይይትና መነጋገርን ለመክፈት፣ እና በአስተሳቡና በአስተሳሰቡ ላይ ብቻ ተመስርቼ ነው፡፡
እውነቱን ተናገር ከተባልኩ፣ በቅርብ ዓመታት በግለሰብ ደረጃ የእኔን ያህል የመለስንና የድርጅቱን ህወሃትን የርዕዮተዓለምና የታሪክ ስህተቶች በተከታታይና በግልጽ በአደባባይ የሰላ ሂስ ያቀረበበት ሰው አላየሁም፡፡ (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!)ከዚህ በላይ ለራስ ማጨብጨብ አልወድምም፣ አይገባኝምምና፣ ስለራሴ ‹‹የመለስ አፍቃሪ›› እንዳልሆንኩ ብቻ ገልጬ ልለፈው፡፡
ይህ ነገር ‹‹አያ ነብሮ፣ ቀድሞ መማማልን ምን አመጣው?›› እንዳለችው ፍየል እንዳይቆጠርብኝ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ስለ መለስ ያለኝን የጠነከረ በሂስ ላይ የተመሰረተ አቋም አስቀድሜ የገለጽኩት፣ ስለ መለስ ዜናዊ ከዚህ በፊት ተናግሬው የማላውቀውን አንድ ምሥጢራዊ ጉዳይ አሁን ለመናገር ስለፈለግኩ ነው፡፡
ይህም ብዙዎች በአሁኑ ሰዓት ከሚያቀነቅኑት በተለየ፣ መለስ ዜናዊ የብሔር ፖለቲካው አሁን እየሄደ ባለበት መንገድ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ በተግባር እንዳልጠቀመ በህይወት እያለ ተረድቶት የመገኘቱ እውነታ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ለዓመታት የተከተለው ኢትዮጵያን በቋንቋና በዘር የመሸንሸን ፖሊሲ ለትግራይ ህዝብም ሆነ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ አዋጪ እንዳልሆነ በተለይ በመጨረሻዎቹ ዓመታት በሚገባ እንደተገነዘበ የሚያሳዩ የተለያዩ ማስረጃዎችንና የራሱን ንግግሮች በብዛት መጥቀስ እችላለሁ፡፡ /ለጊዜው ይፋ የሆኑት ሁሉ ዝርዝሮች ይቆዩንና በግሌ ስለማውቀው አንድ ምሥጢር የማውቃትን ታህል ላካፍል፡፡/
መለስ ዜናዊ ከመሞቱ ጥቂት ወራት በፊት፣ የቅርቦቹ ከነበሩ (አሁን ስማቸውን በፍጹም የማልጠቅሳቸው) ጥቂት ሰዎች አካባቢ የማውቀውን አንድ በወቅቱ ህቡዕ እንደነበረ የማውቀውን መረጃ ብቻ አሁን ብናገር ደስ ይለኛል፡፡ ይኸውም መለስ ዜናዊ ሞት ባይቀድመው ኖሮ፣ ኢትዮጵያን በአራት ወይም በአምስት ቦታ ከፍሎ፣ በአዲስ (በተሻሻለ) ህገመንግሥት አማካይነት አዲስ ሀገራዊ አስተዳደር የማዋቀር ሀሳብ ቀርቦለት እንደነበረ፣ ያንኑ ተቀብሎ እያስጠና እንደነበረና ሊተገብረውም ጥቂት እርምጃዎች ብቻ ቀርተውት የመገኘቱ እውነታ ነው፡፡
በዚያ በአጋጣሚ ላውቀው በቻልኩት የመለስ ዜናዊ ምሥጢራዊ ሀገራዊ የለውጥ ዕቅድ መሰረት ኢትዮጵያ በጎሳና በዘር መሸንሸኗ ቀርቶ በአምስት ሀገራዊ ዞኖች የምትከፈል ሲሆን፡-
1ኛው/ ሰሜን ኢትዮጵያ፣
2ኛው/ ምስራቅ ኢትዮጵያ፣
3ኛው/ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣
4ኛው/ ደቡብ ኢትዮጵያ፣
እና 5ኛው/ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ
ይሰኛሉ፡፡ መለስ ዜናዊ በወቅቱ በእነዚህ ለጊዜው አቅጣጫዊ ስያሜን በያዙ አምስት ዋና ዋና የሀገር አስተዳደር ክፍሎች የምትዋቀር ህብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባትና፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደ ቀደመው (ማለትም አሁን በሥራ ላይ እንዳለው) ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ተነጣጥለውና ለየብቻ ቆመው የሚሸነሸኑበት ሳይሆን፣ በአንድነት ተዋህደው በአምስቱ ጂኦግራፊክ ዞኖች ውስጥ ተባብረው በኢትዮጵያዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ሀገርን፣ ህዝብን፣ ተፈጥሮን ለማልማት የሚሠሩበት ሀገራዊ መዋቅር እውን ለማድረግ ብዙ ርቀት የሄደ (ነገር ግን ሳይተገብረው በሞት የተለየው) ብዙ ምሥጢራዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ በከፍተኛ ፍጥነት እየሰራበት እንደነበረ አውቃለሁ፡፡
በነገራችን ላይ በዚህ የለውጥ ሀሳብ መሠረት ኢህአዴግን ከብሔሮች ግንባርነት አውጥቶ፣ በሀገራዊ ሀሳቦች ዙሪያ ወደሚደራጅ አንድ ወጥ ህብረብሔራዊ ሀገራዊ ፓርቲነት ለመቀየር ዕቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ ከብዙ ይቅርታ ጋር በአሁኑ ወቅት መረጃ ስለሌለኝ ልሳሳት ከቻልኩ የምታረም ሆኖ – ብልጽግና የሚባለው ፓርቲ ህወሃትን ከማስወጣቱና በተግባር ፓርቲዎቹ አንድ ውሁድ ሊሆኑ ካለመቻላቸው በስተቀር – ሀሳቡና ዕቅዱ ግን በዚያ የመለስ ምሥጢራዊ ዕቅድ ውስጥ ተካትቶ እንደነበር መናገር እችላለሁ፡፡
በሚገርመኝ ሁኔታ በመለስ ዕቅድ መሠረት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተባለው በአዲስ አበባ ዙሪያ 100 Sq. Kms. Radius (በመቶ ኪሎሜትር ዙሪያ-ክብ) የሚከለል ህዝብና አካባቢ ሲሆን፣ ይህም በቃሌ እስከማስታውሰው ናዝሬትን፣ አምቦን፣ ደብረብርሃንን፣ ቡታጅራን፣ አዲስ አለምንና ሰላሌን ሁሉ በሁሉም አቅጣጫዎች የሚያጠቃልል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ዞን ነበር፡፡
በወቅቱ ይህ የመለስ ምስጢራዊ ጥናት ተፋፍሞ በቀጠለበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ግን እጅግ የገረመኝ አንድ ክስተት ተፈጠረ፡፡ እሱም ነገር – ከመለስ እጅግ ምሥጢራዊ ዕቅድ ያፈተለከ በሚመስልና የመለስን ምሥጢራዊ ዕቅድ ለማክሸፍ በሚመስል የተጠናና የተደራጀ ሁኔታ – በተለይ በእነ ጃዋር መሀመድ አማካይነት ከሀገር ውጪ መነሻውን አድርጎ በስፋት የተቀነቀነው ‹‹በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለ የመሬት ወረራ›› እየተካሄደ ነው በሚል አጀንዳ ዙሪያ – በአዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫዎች የሰፈሩ ኦሮሞዎችን አሰባስቦ -በህልውናቸው ላይ የመጣባቸው አደጋ እንዳለ አድርጎ የማሳመጽና አዲስ አበባ እንዳትስፋፋ በተቻለወ ሁሉ የማስተጓጎል መጠነ-ሰፊ ዘመቻ የመከፈቱ ጉዳይ ነበር፡፡
በሚገርም ሁኔታ ያንን የመለስ ዕቅድ ‹‹Land Grabbing›› በሚል ሰፊ ዘመቻ ለማሰናከል የተረባረቡት የኦሮሞ ፅንፈኞችና የኦህዴድም የራሱ ፖለቲከኞች (እነ ጄ/ል አባዱላንና እነ ኩማን ጨምሮ)ብቻ አልነበሩም፣ የኢህአዴግ ሁሉም ተቃዋሚዎች ነበሩ አብረው ሲጮሁ የነበሩት፡፡ እነሱም ብቻ ግን አልነበሩም፡፡ የብሉምበርግና ሌሎች ዓለማቀፍ የዜና አውታሮች ሁሉ እየተቀባበሉ፣ ሌላ ቀርቶ በልማት ስም በመጡና በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲሰማሩ በተደረጉ የውጪ ሀገር (የህንድ፣ የቻይናና የሣዑዲ (የሼህ አላሙዲን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጭምር) እና ኩዌትን ጨምሮ የተለያዩ የአረብ ሀገራት) ባለሀብቶች ፕሮጀከቶች ላይ ነበር ‹‹Land Grabbing›› (‹‹የመሬት ወረራ››) እየተባለ ሰፊ ፀረ-መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የተካሄደው፡፡
ይህ ጉዳይ በወቅቱ በአንድ በኩል የመለስ ዜናዊ ቢሮ – ከረቀቀ የግል ሥለላና ከውስጠ-አዋቂ ሠርጎገብ እንቅስቃሴዎች (ኢንተረናል ሳቦታጆች) ነጻ እንዳልሆነ ዕቅዱን ለሰማ ሁሉ አስተማማኝ ግምት ያሳደረበት አጋጣሚ ሲሆን፣ አሁን በአብይ አህመድ የሚመራው ራሱን ‹‹የለውጥ ሀይል›› ብሎ የሰየመው የኢህአዴግ ቡድን ወያኔዎቹ ላይ አድሞ፣ ማስፈራሪያዎቻቸውን በመቋቋም፣ እና በመጨረሻም ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ግን – የዚያ የአዲስ አበባ የመሬት ወረራ ታሪክና ፕሮፓጋንዳ አመንጪ ነኝ በማለት ወደ አደባባይ የወጣን የአንድ ግለሰብ ጽሑፍ እንደ ዘበት በአጋጣሚ አገኘሁና አነበብኩ፡፡
ያም ሰው የኢሣቱ (የግንቦት ሰባቱ) ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ነው፡፡ ጋዜጠኛ ፋሲል በዚያ ፅሑፉ የአዲስ አበባ የመሬት ወረራ የሚባለውን ኦሮሞውን በፀረ-ወያኔ የአመጽ ትግሉ ለማቀላቀል ይጠቅማል በሚል አምነውበት (ከእነማን ጋር ሆኖ እንዳመነበት ባይገልጽም የማንን ፍቃድ ማግኘት እንዳለበት ግልጽ የመስለኛል)፣ በእሱ አማካይነት ለእነ ጃዋርና ለኦህዴድ ሰዎች ‹‹እነርሱም ሳያውቁት በወያኔ በምሥጢር የተዘጋጀው የአዲስ አበባ ካርታ›› እንዲደርሳቸው ማድረጉንና የኦሮሞ ገበሬ የመሬት ወረራ ጉዳይ ዋነኛ የኦሮሞን ሀይሎች የማሰባሰቢያ ፕሮፓጋንዳ ሆኖ እንዲነዛ ዋናውን ሚና እንደተጫወተ ያመነበትን (በእርሱ እይታ የጀብዱው ፈጻሚ ወይም ባለታሪክ እኔ ነኝ ብሎ አደባባይ የወጣበትን) ታሪክ አነበብኩ፡፡ ጉድ አልኩ፡፡
በእርግጥ ፋሲል የኔዓለም አገኘሁ የሚለው ዋናውን ባለ 100 ኪሜ ስኩዌሩን ሰነድ ሊሆን እንደማይችል በብዙ ምክንያቶች እረዳለሁ፡፡ እና በአንድ በኩል የመለስ ምስጢራዊ ዕቅዶች ከኦሮሞ ሀይሎች ቀድሞ በወቅቱ የኢሣት ጋዜጠኞች (በፋሲል የኔዓለም – ስለሆነም በእነ ዶ/ር ብርሃኑ) እጅ የመግባቱ ክስተት አለ! ያ እንዴት ሊሆን ቻለ? ማን ነው ከመለስ የቅርብ ሰዎች መሀል ያንን መረጃ ለኢሳቶች ሊያሾልክላቸው የሚችለው? ወይስ የእነ ሲአይኤና የሌሎች የውጭ ተዋናዮችም እጅ ነበረበት? የባዕዳን እጅ ባይኖርበት ኖሮ ያንን የመሬት ወረራ (‹‹Land Grabbing››) አጀንዳ ባንዴ ዓለማቀፍ የዜና አውታሮች ከኦሮሞዎቹም ከሌሎች የወያኔ ተቃዋሚ ሆነው ከተነሱትም ሀይሎች በላይ እየተቀባበሉ በዓለም ለማሠራጨትና ለማፋፋም ምን አነሳሳቸው? ወይስ ሁሉም ነገር አጋጣሚ ያጋለጠው ጉዳይ ነበር?
ምናልባትስ የመሬት ወረራ በሚል ኦሮሞው የራሱን አጀንዳ ይዞ እንዲነሳ የመፈለጉና፣ የፀረ ወያኔ ትግሉ ሁሉም በየብሔሩ የሚደራጅበትን ቅያስ እንዲከተል የመደረጉ ነገር – ራሱ ህወሃት (በመለስ ዜናዊ ምስጢራዊ ዕቅድ መሰረት) ራሱን ከነባርና ‹‹በመቃብሬ ላይ ካልሆነ በቀር አልደራደርበትም›› ከሚለው የብሔር ክልላዊ አደረጃጀት የፀና አጀንዳና ስህተቱ በራሱ ታርሞ፣ ከብሔር ክልላዊ አደረጃጀት ወደ ህብረ-ብሔራዊ ሀገራዊ ዞናዊ አደረጃጀት ቢሸጋገር ኖሮ – ተቃዋሚው ጎራ ወያኔ-ኢህአዴግን ሲከስበት የኖረውን የዘረኝነት፣ ወይም የጎሰኝነት፣ ወይም ኢትዮጵያን በዘር የመሸንሸን አጀንዳውንና የተቃውሞ ነጥቡን ሁሉ ይነጠቅና ይጥል ስለነበር – የመለስ ሥርዓት ያንን ታላቅ ለውጥ በራሱ አምጥቶ ከማሳካቱና የተቃዋሚዎችን ነጥብ ሁሉ አስጥሎ የሥልጣን ዕድሜውን ለተጨማሪ አስርት ዓመታት በኢዮጵያ ምድር ከመትከሉ በፊት – አንድ ነገር ተረባርበን እናድርግ ተብሎ የተደረገ – የተቃዋሚው ጎራ በምንም ሀገራዊ ዋጋ ወያኔን ብቻ ከሥልጣን እናውርድ በሚል ሸፍጥ ያጨናገፈው የለውጥ ዕቅድ ይሆን?
ከደምቢዶሎ እስከ ዋሺንግተን ኮንግረስና ሴኔት፣ ከጎንደር እስከ ፀጥታው ምክርቤት፣ ከኤርትራ እስከ አሜሪካ የተዘረጋ አንዳች ምስጢራዊ የፀረ-መለስ ዓለማቀፋዊ ስውር የትብብር ድር (ወይም ድንበር ዘለል ሴራና ቃልኪዳን መገባባት) ያለ አይመስልም? በብዙ ምክንያቶች – ለእኔ እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ /የመለስ ዜናዊ በዚያ ወሳኝ ቅጽበት መሞትም በእኔ እይታ አንዱ የዓለማቀፍ ሴራው አካል ነው ባይ ነኝ፡፡/
የሆነ ሆኖ – አሁን ላይ አንድ ነገር ለሁሉምና ለሁላችንም ግልጽ የወጣ ይመስለኛል፡፡ አንደኛ በአሁኑ ጊዜ በየጎራው ያነገብናቸው የህዝብ መቀስቀሻዎችና የአመፅ አጀንዳዎች (መፈክሮች) ሁሉም ከህዝቡ ብቻ በቀጥታ የመነጩ እንዳልሆኑ – እና ከጀርባ ሆነው አጀንዳዎቹን ያቀበሉ የተለያዩ ባለቤቶች እንዳሏቸው ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ወቅት እውነተኛ የህዝብና የልማት አጀንዳዎችን፣ ከሌሎች ለፖለቲካ ትርፍ ከታለሙ ለሀገርና ህዝብ እድገት እንቅፋት ከሚሆኑ አጀንዳዎች ነጥሎ አንገዋሎ መለየት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህ የቤት ሥራ አለብን፡፡
ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ – በወቅቱ መለስ ዜናዊ ሊተገብረው ተቃርቦ ይሁንም አይሁንም፣ የመለስ ዜናዊ ሀገራዊ ህገመንግሥታዊ ‹‹የለውጥ›› ወይም ‹‹ማሻሻያ›› ዕቅድ በሌሎች ሀይሎች ጣልቃገብነት ይጨናገፍበትም፣ አሊያም ምናልባት  በራሱ የህወሃት ሰዎች የውሰጥ አመጽና እምቢተኝነት የተነሳ ዕቅዱን መተግበር ተስኖትም ይሁን፣ አሊያም መለስ ዜናዊ በተፈጥሮ ህመም ተቀስፎም በመሞቱ ምስጢራዊ ዕቅዱ ይቋረጥ፣ ወይስ (በብዙ አሁን በማልገልጻቸው ዝርዝር ጥርጣሬዎች እንደሚታመነው) በሌሎች ተለክፎም በመሞቱ የተነሳ የሀገራዊ ለውጥ ዕቅዱ ይቋረጥም፣ አንድ ዋናና ወሳኝ ነገር አሁን ላይ ህወሃትን ጨምሮ ለብዙዎቹ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ቀጥላ ማየትን በሚፈልጉ የፖለቲካ ሀይሎች ሁሉ ዓይን ግልጽ ሆኖ የወጣ ግዙፍ እውነታ ግን ያለ ይመስለኛል፡፡
ይህ አሁን በሥራ ላይ ባለው ህገመንግሥት አማካይነት የተተከለው በዘርና በቋንቋ፣ በብሔር ማንነትና በባህል በደም ማንነት እየተገመደ በኢተዮጵያችን የተገነባው የብሔር ብሄረሰብና ህዝብ ክልላዊ መዋቅር ወይም አጠቃላይ ይህን መሠረት አድርጎ የተገነባው ህገመንግሥታዊ ሥርዓት – የቱንም ያህል የራሱ በጎ ጎኖችና ዓላማዎች ቢኖሩት – በአጠቃላይ በተግባር ሲመዘን ግን ያተረፈልን ነገር – እርስበርስ መጠላላትን፣ ይበልጥ መለያያትን፣ መቃቃርን፣ እና እንደዜጎች ልናሳካቸው የምንፈልጋቸውን ሀገራዊ አጀንዳዎች አጨንግፎ፣ ሀብታችንን ሁሉ አስተባብረን ብዙ ነገሮችን እንዳናሳካ ታላቅ መሰናክል እንደሆነብንና፣ ታላቅ የአብሮነትና የሀገር ደህንነት አደጋም እንደጋረጠብን ነው፡፡
ይህን አሁን በተግባር በገሃድ ሁላችንም ስላየነው ከዚህ እውነት የምናመልጥበት መንገድ የሚኖረን አይመስለኝም፡፡ በተለይ አሁን ከአብይ አህመድ ግድያ የተረፉት (በእስር ላይ ያሉትም ሆኑ በትግራይ በመሪነት ወንበር የተመለሱት) እስከዛሬ በህወሃት አቀንቃኝነትና ፊት መሪነት በኢትዮጵያችን የተዘረጋው ህወሃት-መር የብሔር ብሔረሰብ ማንነት ላይ የተመሰረተ ሀገራዊ ክልላዊ ሽንሸናና አስተዳደር – ለኢትዮጵያም ሆነ – በተለይ ደግሞ – ለትግራይ ህዝብ ዘላቂም ሆነ ጊዜያዊ ጥቅሙንና መብቶቹን ለማስጠበቅ እንደማይበጀው ከዚህ አሁን እየሆነ ካለውና ከሆነው በተግባር መሬት ላይ የታየ እውነት ተመልክተው መረዳት ካቃታቸው – በእውነት ጨለማና ብርሃንን መለየት የማይችሉ ሰዎች ናቸው ማለት ይሆናል፡፡
በበኩሌ ዋናው ችግር የህወሃት ሰዎች ይህን እውነታ ለማየት ያለመቻላቸው ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ ዋናው ችግር በተቃዋሚም ጎራ ይሁን በወያኔ ተቀናቃኝነትና በወያኔ-ጠልነት የቆሙት የሀገራችን ነባር ተቃዋሚዎችም ሆኑ በአብይ አህመድ የመሪነት ጥላ ሥር የተሰባሰቡት የጊዜያችን ኢህአዴጋዊ የብሔር ፖለቲካ አራማጆች – ህወሃትን ለማየት ያለመፈለጋቸው ችግር ነው ባይ ነኝ – በአሁኑ ወቅት የችግሮች ሁሉ ዋነኛ መነሻ የሆነው፡፡
ሁሉም በሚባል ደረጃ በወያኔ መቃብር ላይ ካልሆነ በስተቀር – ከወያኔዎች ጋር አብረው ቁጭ ብለው በቅንነት ተመካክረው – ወያኔዎቹ ራሱ ከዓመታት በፊት በመለስ ዜናዊ ጊዜ እውነታውን ተረድተውት በምሥጢር ሊያካሂዱት አስበውት የነበረውን ሀገራዊ የለውጥ ሀሳብ ለመተግበር አንዳችም ፍላጎት ያለመኖሩ ነው ዋነኛው የመቆራቆዞችና አሁን የምናያቸው ግጭቶች ሁሉ መንስዔ፡፡
ይህ የራሱ ምክንያቶች የሉትም ማለት ግን አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድም ወያኔን ከመፍራት ነው፡፡ ሁለትም ወያኔን ካለማመን ነው፡፡ ሶስትም በወያኔዎች ላይ በምንም የማይሽር ቂምና ጥላቻ በማሳደር ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ – ምናልባትም – ራሳቸው የወያኔ ሽማግሌ መሪዎችም – እስከዛሬ ብቻቸውንም ሳይሆን ከሁሉም ጋር አብረው እያቀነቀኑት የመጡበት ሀገራዊ መንገድ የተሳሳተ መሆኑን በግልጽ አምነው ይፋ በማድረግ ፈቃደኛ ካለመሆናቸው የመነጨም ነው፡፡
ለምሳሌ ህወሃቶች ከኦህዴዶች ብርቱ ውስጣዊ የለውጥ ፍለጋ ተቃውሞዎች እየጠነከሩባቸው ሲመጡ – በመጨረሻ – ለኦህዴዶች ሳያሳውቁ – ቀድመው ጦርነት ገጥመው ከጨዋታ ውጭ አድርገው በአሸባሪነት የሚያሳድዱትን ኦነግን ለእርቅና ድርድር ጋብዘው – አዲሳባ ላይ በዝግ ምሥጢራዊ ድርድር እስከማድረግ ደርሰው ነበር፡፡
ይህ ማለት ኦህዴዶችን የኦነግ ጠላት ካደረገና በኦሮሞ ህዝብ እንዲጠሉ ካደረገ በኋላ ዞር ብሎ በምስጢር ከኦነግ ጋር ተስማምቶ፣ እነሱን በኦነግ ሊተካና ከጨዋታ ውጪ ሊያደርግ የሄደበት የሸፍጥ መንገድ፣ ውስጣዊ ድርጅታዊ መተማመንን ከማሳጣቱም በላይ፣ ኦህዴዶችም ሆኑ ሌሎቹ ውስጥ ለውስር ሳይቀድማቸው ለመቅደም በህወሃት ላይ የጋራ ስውር ግንባር እንዲፈጠሩበት ትልቅ ድርሻ ተጫውቷል፡፡
/በነገራችን ላይ ኦነግን ከኦህዴድም፣ ከእነ አብይም በቅድሚያ ወደ ሀገር ውስጥ የጋበዘው ህወሃት ነበር የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን ኦነጎች ህወሃትን በፍጹም ልባቸው ለማመን የተቸገሩና፣ ከዚህ ቀደም በተግባር እንዳደረገው እኛንም ነገ ደግሞ ሶስት አራት ቦታ ከፍሎ ያባላናል ብለው፣ ከግብዣው ያፈገፈጉና በጀርባው ከኢህአዴግ የኦሮሞ ሀይሎች ጋር የገጠሙበት ይመስለኛል!/
ለማንኛውም ምሳሌውን ያነሳሁት፣ ህወሃት ከሌሎቹ አባል ድርጅቶቹና አጋሮቹ ጋር ባለው ግንኙነት ሁሉ – በንጹህ ልብ ለተሻለ ሀገራዊ የሥርዓት ለውጥ በጋራ ተወያይቶ የሚበጀንን በወንድማማችነት ለማድረግ ፈቃደኝነቱንና ቅንነቱንም እምነቱንም በማጉደሉም ጭምር ይመስለኛል በሌሎቹ የተተፋው ወይም የተፈራው፡፡
በበኩሌ አንድ ለእኛ ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም የሰው ልጅ ፍጥረት በሚሊዮን ልሳን አስረግጬ መናገር የምፈልገው መልዕክት ቢኖር – ስህተትን ማመን በምንም መለኪያ፣ በፍጹም ውርደት አለመሆኑን ነው፡፡ አይደለም የሰው ልጅ – ፈጣሪ አምላክ ራሱ ይሳሳት የለም ወይ? ብዬም እሞግታለሁ፡፡ ፈጣሪስ ራሱ የሰውን ልጅ በመፍጠሩ ይፀፀት የለም ወይ?
ስለዚህ በተለይ ለህወሃትም ሆነ ሌሎቻችሁ የሀገራችን ፖለቲከኞች ለማለት የምፈልገው፣ በሠራችሁት ሥህተት፣ ብዙ ዋጋ በተከፈለበት መንገድ ሄዳችሁ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሠራችሁትን ስህተት ለማመንና ለአዲስ ሀገራዊ ሥርዓት ለመነሳት፣ እንዲያውም ግንባር ቀደም ሆኖ ያን ለውጥ ለማምጣት መሰለፍ የታላቅነት ምልክት ነው – ነው! ስህተትን ማመንና አዲስ ዓይነት የተሻለ መንገድን እንቀይስ ብሎ መነሳት፣ የታላቅ ሰብዓዊ ጉዞ ጅማሮ ነው፣ እንጂ በፍጹም ኩነኔና ሞት አይደለም፡፡
As long as a human being is alive, there is always a better way of doing things! ሰው በህይወት እስካለ ድረስ፣ ሁልጊዜም ነገሮችን በተሻለ መንገድ መሥራት የሚቻልበት መንገድ አለ፡፡ የተሻለ መንገድ እስካለ ድረስ የቀድሞውን ስህተት አሻሽሎ፣ ወይም የቀድሞውን በተሻለ መንገድ ሊሠራ የሚችልበትን መንገድ ከፊታችን እንደተዘጋብንና እንደሞተ ጉዳይ አድርጎ መቁጠር ከሰው ልጅ ተፈጥሮና የአዕምሮ አቅም ራስን አሳንሶ ለመገኘት ፍቃደኛ ሆኖ መገኘት እንደማለት ነው!
ሁልጊዜም በማንኛዋም ሰከንድ ከነባር ስህተት ራስን ለማላቀቅ ጊዜው አይረፍድም፡፡ አሁንም ሁሉም የኢትዮጵያ ሀይሎች ከስህተት ጎዳናዎችና የሴራ፣ የሸፍጥና የመበላላት አካሄዶች ወጥተው በጋራ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚመችና የሚበጅ ሥርዓትን ለማዋለድ – በጦርነት ሳይሆን በትብብር መሥራትን አሁኑኑ ለመጀመር ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ አለባቸው፡፡
በወገን መካከል የሚፈስስ ደም – የፈሰሰው ሁሉ ደም – በምንም ቃል ሊመካኝ በማይችል ሁኔታ – ታላቁ የማይተካና የማይመለስ ስህተታችንም ሽንፈታችንም መሆኑን መቼም መርሳት አይገባም፡፡ ግን አሁኑኑ ደም መፋሰስን ማቆምና ከስህተቶቻችን ሁሉ ዛሬውኑ መታቀብ እንችላለን፡፡ ዛሬውኑ ተግባር የመሰከረውንና ግልጽ አውጥቶ ያሳየንን ሀገራዊ ስህተት – መተማመንን በሚያሰፍን መንገድ ተቀራርበን በመወያየት አርመን – ለተሻለ ሀገራዊ መፍትሄና የጋራ መጻዒ አብሮነትና እድገት ለመስራት የምንችልበት ማምጣት ይኖርብናል፡፡
አሁንም ይህ ዕድላችን ሙሉ በሙሉ አልመከነም፡፡ አሁንም ለመነጋጋር፣ ለመቀራረብ፣ እና አብሮ ለመስራት፣ በእኛ መቃቃር ያቃቃርናቸውን ንጹሃን ሕዝቦቻችንን መልሰን ወደ ወንድማማችነታቸው የመመለስ ዕድሉ በእጃችን ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የሚሰማ ጆሮ ካለ፣ ከአሁኑ ስሜትና ብሶት ወጣ ብሎ ስለ ወደፊቱ አሸጋግሮ ለማየት የሚፈቅድ ህሊና ካለ፣ አሁንም ለምክክርና ለትብብር ጊዜው አልረፈደም፡፡ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የታናናሾችን ምክር የማይሰማ ልብ፣ በመጨረሻም ይሰበራል ይላል የፈጣሪ ቃል፡፡ እውነት ይመስለኛል፡፡ እንደ እዮብ የሰፋ፣ መከራን የሚቋቋም፣ ትዕግስተኛና የታናሹን ምክር የሚሰማ ልብ ይስጠን ፈጣሪ፡፡
በዚህ በኩል በመካከላችን ለምናደርገው የሰላም እርምጃ አንዲት የታናሽ ሀሳብ ዝቅ ብዬ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ላለፉት ሁለት ሚሊኒየሞች በዓለም ሁሉ የታወቀ አንድ የማይጣስ የዲፕሎማሲ መርህ አለ፡- ‹‹You never ever kill the messenger!›› (መልዕክት ላኪውን እንጂ፣ መልዕክት አድራሹን – ማለትም መልዕክቱን ለአንተ ሊያደርስ ተልኮ የመጣን ሰው – በምንም ዓይነት፣ በፍጹም፣ መግደል የለብህም!) የሚል ዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ መርህ ነው፡፡
ይህ ማለት ምን ማለት ነው? አሁንም በደም መፋሰስ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን (የሀገራችን የፖለቲካ ቡድኖች) – አሁን በደም አፋሳሽ አውደ ውጊያዎችና ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ወገናችንን በቀጠፉ ዘግናኝ እልቂቶች ውስጥ አሊያም በአስጊ መፋጠጦችና ስጋቶች ውስጥም ሆናችሁ – በዚህም ሁሉ መካከል – የድርድር ሀሳቦቻችሁን፣ የፖለቲካ የልዩነትና የአንድነት ነጥቦቻችሁን፣ ለወደፊቱ በጋራ በምክክር መለወጥ የምትፈልጓቸውን ነገሮች፣ አይ ይሄ ነገር ሳይለወጥ ነው መቀጥል ያለበት የምትሏቸውን ነጥቦች ሁሉ፣ ከመካከላችሁ በመረጣችኋቸው መልዕክት አድራሽ ሽማግሌዎች አማካይነት በመላላክ መነጋገር ትችላላችሁ፡፡
መልዕክት አድራሾቹ በፍጹም በማንኛውም ወገን አይነኩም፡፡ በፍጹም አይገደሉም፡፡ በፍጹም ለአደጋ አይጋለጡም፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ ጫፋቸው አይነካም፡፡ አንዳችም ጉዳት አይደርስባቸውም፡፡ ሁሉም ወገን በየፊናው የመረጠውን የየራሱን አንድ ወይም ሁለት መልዕክት አድራሽ ሽማግሌ ለኢትዮጵያ እና ለዓለም ህዝብ ይፋ ያድርግ፡፡ እና እነዚያ መልዕክት አድራሽ ሽማግሌዎች የገባንበት የደም መፋሰስ ሳይበግራቸው፣ በዜጎቻችን ዋይታና መከራ መሐል እየተመላለሱ፣ የሰላምና የድርድር፣ የመነጋገርና ሀሳብ የመለዋወጥ ሥራዎችን በመካከላችን ያካሂዱ፡፡
ምን ይታወቃል? በመሀል ማንም ሌላ የውጪ አካል ሳያስፈልገን – በአንዳች ኢትዮጵያዊ ተዓምር – በመልዕክተኞቻችን በኩል ብቻ ተነጋግረን፣ ተማምነን፣ ተደራድረን፣ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንመጣና ዓለምን እናስደንቅ ይሆናል?! የሀገሬ ፖለቲከኞች እባካችሁ፣ ስለ መጪው ትውልድ ስትሉ፣ ከሚሊየን አንድ ብትሆንም እንኳ፣ ያቺን የሰላም ዕድል ለትውልድና ለፈጣሪ ስትሉ አታባክኗት!
ከታሪክ ፍርድ ማምለጥ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ዛሬ ላባከናችኋት እያንዳንዷ የሠላም ዕድል፣ ዛሬ ለአንዲት ጎጆ ማትረፍ ስትችሉ እሳት ውስጥ ለማገዳችኋት የደሃ ነፍስ፣ ነገ ታሪክ አጽም ሆኖ ይወጋችኋል! የልጅ ልጆቻችሁ ትውልድ ነፍሳችሁን በተኛችበትም ሰላም አይሰጣትም! ይፋረዳታል! የሠላምን ገበታ ስለረገጣችሁ ስለሁላችሁ፣ ዛሬም እያላችሁ፣ ነገም አልፋችሁ፣ በፈጣሪና ትውልድ ፊት እንፋረዳችኋለን!
በመካከላችን መነጋገር እንዳይኖር የሚፈልግ ሠላምን የማይወድ ብቻ ነው! በመካከላችን እርቅና እረፍት እንዳይኖር የሚወድድ የትውልዳችን የህጻናት ልጆቻችን እና የምስኪን እናቶቻችን ስቃይ የሚያስደስተው ብቻ ነው፡፡ ለሠላም አንዲት ቅንጣት ዕድል ላይ ፊቱን የሚያዞር፣ ለአንዲት ቅጽበት የመነጋገር ዕድልን የሚያመክን፣ የልብን መመለስ የሚጠላ፣ እርሱ ወገኑ ከሠይጣን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ልቦናችንን ወደ ቅን መንገድ ይመልስ! ፈጣሪ አምላክ በደም መፋሰስም ውስጥ ሆነን፣ በደምና በሥጋ የተቀበልነውን ስርየት ይስጠን! ሥርየትን ያሳስበን! ቅን ነገርን ያሳስበን በልቦናችን ፈጣሪ አምላክ!
ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን በውጪው ዓለም ሁሉ በታሪክ የተመሠከረልን አንድ የታወቀ ሰብዓዊ ምግባራችንም አለ፡- ከጦርነት በኋላ፣ አሸነፍንም ተሸነፍንም፣ ፈጥነን ይቅርባይ እና ፈጥነን መሐሪ መሆናችንን ዓለም ሁሉ ያውቃል፡፡ ብዙ የታሪክ ድርሳናትም ላይ በክብር ተጽፎ ተቀምጦልናል፡፡
አይናችንን በእልህ ጭለማ ነገሮች ላይ ብቻ ለማፍጠጥ ስለወሰንን እንጂ፣ ሌላ ሌላ አሉታዊ ነገሮችን እንተው ብንል፣ ብዙ ልናያቸው የማንፈቅዳቸው መልካም ነገሮቻችን አሁንም ከሁላችንም ጋር አብረውን አሉ፡፡ ከቅርብ ወራቶች በፊት እንኳ ለምሳሌ ህወሃቶች (ሌላ ሌላውን ትተን) የማረኳቸውን በሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን ሠራዊት አባላት፣ ያለቻቸውን እህል ውሃ አካፍለው፣ በመካከላቸው አቆይተው፣ አማራጫቸውን አስመርጠው፣ ወደቤተሰቦቻቸው በሠላም እንዲመለሱ ለቅቀዋቸዋል፡፡ ይህን ባለፈው በህዳር ወር ላይ ከመከላከያ ወታደሮች ከራሳቸው የሰማነው ነው፡፡
ይህን አልኩ እንጂ፣ በተመሳሳይም አንዱ ህዝብ ለሌላው ህዝብ ያለውን መተሳሰብና ይቅርባይነት – ከምሬቶች ሁሉ ባሻገር ከፍ ባለ የፈጣሪ ልብ – ብዙ እጅግ ብዙ ድንቅ የወገንነት ተግባራትን እያከናወነ ነው ያለው፡፡ ሌሎችን ስላልጠቀስኩ ያሳነስኩ የሚመስለው ካለ ይቅር ይበለኝ፡፡ በፍጹም በዚያ መልኩ አይደለም፡፡ የባሰውን ለማለዘብ ብዙ ነገሮችን በመተው ቅን ፍላጎት የመነጨ ብቻ ነው፡፡
ቅን ነገሮቻችን እየተነሱ ተደጋግመው ስለማይራገቡ፣ ሁሉ ነገራችን እኩይ መስሎ ይታየናል እንጂ – ህዝባችን አሁንም ቅን ነው፡፡ በየጎራው ተሰልፎ የሚዋጋውም ምስኪኑ ወገናችን ነው፡፡ የግል ቂም ያለው፣ በዕድሜው ሙሉ የሚተዋወቅ ራሱ እኮ ጥቂት ሰው ነው፡፡ የማይተዋወቅ ወገን ነው በእዚህና በእዚያኛው ጎራ ቆሞ የሚታኮሰው፡፡ አንድ ምስኪን የሌላኛውን ምስኪን ወገኑን ገድሎ፣ አድምቶ፣ አቁስሎ፣ የሌላኛውን ምስኪን ወገኑን እናት ያስለቅስ ይሆናል፣ የሌላውን የደሃ ጎጆ ያጎድል ይሆናል እንጂ – ምን የተለየ ጀብዱ ነው ወገንን መግደል፣ ወገንን ማድማት፣ እርስበርስ መደማማት? ጀብዱ አይመስለኝም፡፡
እና መልዕክተኞቻችንን እንምረጥ፡፡ ለህዝብ ይፋ እናድርግ፡፡ መልዕክተኞችን የሚጎዳ ድርጊት የሚፈጽም ቢኖር ሠላም በህሊናው የማይዘልቅ ሠይጣን ብቻ ነው፡፡ እርግማንን በራሱ ላይ የሚጠራ ብቻ ነው፡፡ ያ በመካከላችን እንደማይኖር ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ በመልዕክተኞቻችን በኩል የሠላምንና የእረፍትን፣ የመነጋገርን፣ የመቀራረብን አማራጭ እናፈላልግ፡፡
ይህ ሁሉ መቆራቆዝና ደም መቃባት አንድ ቀን ያልፋል፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ፣ አንድ ቀን፣ የአንዱ በእኛ አረር የገደልነው፣ አሊያም በሌላው አረር የሞተብን ወገናችን፣ በአንዲት የወደፊት ቀን ላይ ልጆቹ፣ እህት ወንድሙ፣ አባት እናቱ፣ ወገን ሁሉ የህሊና ጥያቄ ያቀርብልናል፡፡ የማንተካውን ነገር አናውድም፡፡ የሰው ነፍስ አይተካም፡፡ አይካስም፡፡ የሰውን ቤት አናጉድል፡፡
የዛሬ የጀብዱ ውሎአችን አልፎ፣ አንድ ቀን፣ ከየራሳችን ቤትም፣ ከየራሳችን ወገንም፣ ከየራሳችን ልጅም የማንመልሰው የህሊና ጥያቄ ይነሳብናል፡- ‹‹አባዬ! ስለ ሠላም ስትል፣ በእርቅ መንገድ ስለ መጓዝ ስትል፣ ምን ጥረት አድርገሃል? እስቲ አንዲቷን የርህራሄ መንገድህን አሳየኝ?›› ተብለን የምንጠየቅበት ዕለት ይመጣል፡፡
አንድ ቀን ቤታቸውን ያጎደልንባቸው ሲጠይቁን የምንመልሳትን፣ አንዲቷን ለህሊናችንም፣ ለትውልድም፣ ለፈጣሪም የምትሆነንን የሠላምና የእርቅ መንገድ ሁልጊዜ ከራሳችን ጋር እንያዛት፡፡ ያቺን አንዲት ሠላም የሚቻልባትን፣ ለእርቅ የማርያም መንገድ የምትሰጠንን አፍታ በፍጹም አርቀን አንቅበራት፡፡
ወገን ነን፡፡ መዋጋትና መጣላት ብርቃችን አይደለም፡፡ ክፉው ይነሳ ከተባለ፣ በፍቅር ተሸፋፍነንና ተደራርሰን ከኖርነው ባልተናነሰ፣ በታሪካችን ሁሉ ስንዋጋና ደም ስንፋሰስ ነው የኖርነው፡፡ ያም አልፎ ታርቀን፣ ተጎራብተን፣ ተዋልደን፣ አንድ ወገን ሆነን፣ ባንድ ሀገር ሰማይ ተጠልለን፣ ሌላ ቀርቶ በሁለትም ሰማይ ተጠልለን – በውግንና እየኖርን እዚህ ደርሰናል፡፡ ዛሬ ከዚያ ከምናውቀው የደም አዙሪት ለመውጣት አንዲት የሠላም ድርጊት መፈጸም ነው የታሪክ ጀግና የሚያደርገን፣ እንጂ ያንኑ ሲደረግ የኖረውን የፀብ መንገድ መድገም አይመስለኝም ጀግንነት፡፡ እና በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንገኝ፣ ግን ለዚህ ጀግንነት ልባችንን አንዝጋው!
ይህ የሠላም ተማጽኖ የመቶ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ተማጽኖ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ፈጣሪ ልቦናችንን በቅን መንገድ እንደሚያነሳሳልን አምናለሁ፡፡ በመካከላችን የሞቱት፣ የተሰዉት፣ የቆሰሉት፣ ያቃሰቱት ሁሉ በየፊናቸው እውነት ነው ብለው ላመኑት ሀቅ ቆመው የወደቁ ይመስለኛል፡፡ እልህ ይዞን እንጂ፣ አንድ ክፋት ወደ ሌላ ክፋት እየመራን እንጂ፣ በተፈጥሮ ፍጹም ክፉ ሆኖ የተፈጠረ በመካከላችን አንድም እንኳን የለም፡፡
በእኔ በዚህች አጭር ህይወት እንኳ የምመሰክረው እውነት አለ፡፡ የሀዲያ እናቶች መኪና በእርሻ መሐል ጥሎን፣ ወተታቸውን በንጹህ የእንግዳ ብርጭቆ አጠጥተው ደርሰውልኛል፡፡ የጉራጌ እናቶች ያላበሉኝ ያላጠጡኝ ነገር የለም፡፡ የስልጤ የረዥም ዘመን ወዳጆቼ ልጃችንን እንዳርልህ እስከማለት የዘለቀ የፍቅር ልባቸውን ከፍተው ሰጥተውኛል፡፡ የኦሮሞ እናቶች፣ የኦሮሞ ወዳጆች፣ አብሮአደጎቼ፣ ዘመዶቼ ሁሉ ያስተማሩኝ ቅን መንገዶችና ደግነቶች ሁልጊዜ በልቤ ውስጥ አሉ፡፡
የትግሬ ወንድሞቼ፣ የትግራይ እናቶች አባቶች፣ ደግነት፣ ሩህሩህነት፣ እግዚአብሔርን ፈሪነት፣ ሰው አክባሪነት፣ ፍቅርና አሳቢነት ሁሉ ሁልጊዜም በሕይወቴ ተሸክሜው የምኖረው ነው፡፡ የአማራ እናት፣ የአማራ ህጻናት፣ የአማራ አዛውንት፣ ቄሱ ተማሪው፣ አዋቂው ባላገሩ፣ ሁሉም ያለው ቅንነት፣ ፈሪሃ እግዜር፣ ሀቀኝነት፣ ንጹህ የዝምድና ፍቅር፣ ሰው አክባሪነት፣ ለሰው ደራሽነት ይህ ሁሉ ዘለዓለም በልቤ ታትሞ ይቀራል፡፡
የሱማሌዎች ልክ የሌለው ፍቅርና ነጻነት፣ የአደሬዎች ማህበራዊ መግባባትና የፍቅር አንደበት፣ የአፋሮች፣ የአርጎቦች፣ ትህትናና ቤተሰባዊ አቅርቦት፡፡ የወላይታ የሲዳማ የልብ ወዳጆቼ፣ እና ደግ እናቶችና አባቶች፡፡ ስንቱን ዘርዝሬ እጨርሰዋለሁ? ሕዝባችን ደግ ብቻ አይደለም፡፡ የደግም ደግ፡፡ የጨዋም ጨዋ፡፡ የወገንም ወገን ነው፡፡ ይህ ሁሉ አባባል ኤርትራውያን ወንድሞቼን፣ እህቶቼን፣ እናትና አባቶቼን ሁሉ በተመሳሳይ ልብና ቃል ይመለከታል፡፡
በእኔ በዚህች ብጣቂና ከንቱ ዕድሜ እንኳ ተናግሬ የማልጨርሰው፣ ነገር ግን ፖለቲካና እልህ እያከፋኝ የማልናገራቸው፣ በውስጤ አምቄ የማስቀራቸው፣ ስንት ስንት ልቤን በፍቅር የሚያቀልጥና፣ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጎጆ ጉዳት አንጀቴን ስፍስፍ የሚያደርገኝ ንጹህ የወገን ፍቅር ተሸክሜ ነው የምዞረው፡፡
የሁሉም ኢትዮጵያዊ እናቶች አንዲትም እንባ ልቤን ታስጨንቀዋለች፡፡ ለህጻኖቻችን ሁሉ ሠላምና ቡረቃን ከልቤ ከሁለመናዬ ሁሉ ተንሰቅስቄ እለምንላቸዋለሁ፡፡ እመኝላቸዋለሁ፡፡ ስክን ብለን ብናስበው – ሁሉም ኢትዮጵያዊ – ሀገር ምድሩን በሚያለብስ የወገን ፍቅር የተሰፋ ነው፡፡
እስካሁንም ያቆዩን፣ አናወራቸውም እንጂ፣ ሀይለኝነቶቻችን ሳይሆኑ፣ ፍቅሮቻችን ናቸው! ደግ እናቶቻችን ያጠቡን ፍቅር ነው! የቆዳችንን ቀዳዳዎች ልብ ብለን እንደማንመለከታቸው ሆኖብን እንጂ፣ እልፍ ሚሊየን ደግነቶች በመካከላችን አሉ! በእልፍ ወገናዊ ክሮች ተሰፍተናል፡፡ ይሄን ነው ዛሬ ላይ ማሰብ ያለብን፡፡ ይሄን ነው በፈተናችን ሰዓት ማሰብ፡፡
የኢትዮጵያ አምላክ ክፋትን ከላያችን ይሰውር፡፡ ለልጆቻችን የሚተርፍ ፍቅርን ያሳስበን፡፡ እርቅን፣ እፎይታን፣ ለፍቅር መንበርከክን ያስተምረን፡፡ የእናቶቻችንን እንባ ከአይኖቻቸው፣ ሥጋቶቻቸውን ከልባቸው ላይ ያብስ ፈጣሪ አምላክ፡፡
እናት ኢትዮጵያ፣ ለዘለዓለም፣ በፍቅር ትኑር፡፡

 

Filed in: Amharic