>
5:21 pm - Thursday July 21, 8411

ይድረስ ለትግራይ ወገኖቼ...!!! (ክርስቲያን ታደለ)

ይድረስ ለትግራይ ወገኖቼ…!!!

ክርስቲያን ታደለ

የትግራይ ሕዝብ ከባለጌ ልጆቹ በላይ አገሩን የሚመርጥበት ጊዜ ደርሷል።  በተለይም የትግራይ እናቶችና አባቶች በራሳቸው ልጆች እኩይ ስምሪት ቀደምቶቻቸው ለአንድነቷ ሰማእትነትን የተቀበሉላት ኢትዮጵያችን ክብሯ እንዲጎድፍ በዝምታ መተባበራቸውን   ይበቃል ለማለት ትክክለኛው ወቅት አሁን መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል።
የዘመን ተጋሪዬ ለሆናችሁ የትግራይ ወጣቶችም «ጅብም ብሆን የወንዝህ ጅብ ስለሆንሁ፤ ልበላህ መብት አለኝ» የሚሉ አገር አጥፊዎችን በመተው ከአገራችን ኢትዮጵያ እና ወንድሞቻችሁ ጎን እንድትቆሙ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ።
የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጨዋው የትግራይ ሕዝብ በአገር አፍራሽ፣ ዘር አጥፊና ዘራፊ ብኩኖች በኩል ዘላቂ መብቶቹ፣ ጥቅሞቹና ፍላጎቶቹ እንደማይከበሩለት አውቃችሁ ሁለንተናው ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር የተሸመነውን የትግራይ ሕዝብ ታሪክ፣ ክብርና የወደፊት በጎ ተስፋ በሚመጥን ስምሪት እንድትገኙ ዝቅ ብዬ እለምናችኋለሁ።
ታላቁ የትግራይ ሕዝብ በሌባ አይወከልም! ከዘፍጥረት ጀምሮ እስካሁን ድረስም እናት ኢትዮጵያም ሆነች ወንድሙ የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ የክብሩ ምንጭ የደኅንነቱ ደጀኖች እንጂ የስጋቱ ምንጮቹኘች ሆነው አያውቁም፤ አይሆኑምም። እንዴት አገር ገንቢው ትግራይ በአገር  አፍራሽ ይወከላል?
ትግራይ የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ብቻ ነው፤ ትግራይ አንገት ደፍታ ኢትዮጵያ አትቃናም። በትግራይ ለቅሶ ፈገግታው የሚደምቅ አንድም ኢትዮጵያዊ አይኖርምም። ሌባና ዘራፊ፤ ባንዳና አገር አጥፊ ግን ከየትም ይሁን የትም የጋራ ጠላታችን ነውና በጋራ ልንደመስሰው ይገባናል። በባንዳ ሞት ደረት የሚደቃና ፊት የሚነጭ ሊኖር አይገባም።
እናም ለተከበራችሁ የትግራይ አባቶቼና እናቶቼ፤ ወንድሞቼና እህቶቼ፥ ስለደማቁ የትናንት ትናንታችን ብቻ ሳይሆን ስለብሩህ ነጋችንም ብላችሁ ለኢትዮጵያችን ኅልውና እንዲሁም ለሕዝባችን ፍትኅ፣ እኩልነትና ነፃነት መረጋገጥ በአንድነት እንድንቆም ስል ጥሪዬን ደግሜ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
ሁሉም ችግሮች ከጋራ አቅማችን በታች ናቸው። ስንደማመጥ፣ ስንከባበርና ስንተማመን ከባዱ ቀላል ይሆናል። ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ሁላችንም እናሸንፋለን!
Filed in: Amharic