>

"የሐሳብ አፍላቂውን" ሐሳብ ለመተቸት መጀመሪያ ስለ ሐሳቡ ግንዛቤ ይኑረን...!!! (ኤርሚያስ ለገሰ)

“የሐሳብ አፍላቂውን” ሐሳብ ለመተቸት መጀመሪያ ስለ ሐሳቡ ግንዛቤ ይኑረን…!!!
ኤርሚያስ ለገሰ

ከአንድ ሳምንት በፊት (July 13)  የአማራን ህዝብ ያጋጠመውን የሕልውና አደጋ በመመልከት የአገር መፍረስን የሚታደግ “የኃይል ሚዛን የመጠበቅ ስትራቴጂ የመከተል አስፈላጊነት” በሚል ባለ አራት ነጥብ የያዘ ምክረ-ሃሳብ አቅርቤ ነበር። እነዚህም አንደኛ <የአማራ ህዝባዊ ጦር ኃይል (APMF)> ማቋቋም። ሁለተኛ የAPMF ኃይል የፓለቲካ እና የወታደራዊ ውሳኔ የሚሰጥ ሁለት ክንፍ እንዲኖረው ማድረግ። ሶስተኛ በግፍ የተቀነሱ የጦር አመራሮችና ሰራዊቱ በክብርና ይቅርታ እንዲመለሱ ማድረግ። አራተኛ በስራ ላይ ያሉ የአማራ ተወላጅ የጦር አዛዦችና ሰራዊት APMF እንዲቀላቀሉ ማድረግ የሚል ነበር።
በሃሳቦቹ ዙሪያ ከሩቅም ከቅርብም የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ተመልክቻለሁ። ይሄ በጣም ጥሩ እና የሚያበረታታ አልፎ ሄዶም ምስጋና ሊቀርብበት የሚገባ ነው። ጭንቅላቴን ዝቅ በማድረግ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ለነገሩ የተለፋውም ይህ እንዲሆን ነበር። በአጭሩ የሃሳብ ሰው (The Thinker) ዋነኛ ተግባሩ ከተለመዱ አስተሳሰቦች ወጣ ያሉ አከራካሪ ጉዳዮችን ይዞ በመምጣት የውይይት ምህዳሩን መክፈት ነው።
ሆኖም ግን የሐሳብ አፍላቂውን የእቅዱ ታሳቢዎች (Assumption)፤የእቅዱ ዓላማና ግብ የሁኔታዎች ትንተና (SWOT analysis)፣ ስትራቴጂያዊና ስልታዊ የሃይል አሰላለፍ ትንታኔ፤  ሁለንተናዊ እይታ ( system thinking)፤ የአፈፃፀም አቅጣጫዎች፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች …ወዘተ በቅጡ ካለመረዳና በቁንጽል በመያዝ አስተያየት ሲሰጥ ተመልክቻለሁ። ይህም አንባቢና ተመልካቾች ከአውዱ ውጪ እንዲመለከቱት በር የሚከፍት ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ከእነዚህ መካከል በተለይም በቁጥር አራት የቀረበው ምክረ-ሃሳብ በተለያዩ መድረኮች ከፍ እና ዝቅ ሲደረግ አይቻለሁ። በቁጥር አራት የቀረበው ምክረ-ሃሳብ “ከመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ካሉ የአማራ ተወላጆች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ወደ አማራ ሕዝባዊ ኃይል ይቀላቀሉና የአማራን የሕልውና አደጋ ይታደጉ” የሚል ነበር።
ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ይህ ፓራዳይም ሽፍት ሊያመጣ የሚችል የለውጥ ሃሳብ ሲቀርብ የሊደርሺፕ አእምሮ ውቅሩ ትራንስፎርሜሽንን ታሳቢ ያደረገ ነበር። እንደዚህ አይነት የአእምሮ ውቅሮች የማይቻልን ተብሎ የሚታሰብን ነገር ወደ የሚቻል መቀየርን እምነት ይይዛሉ።
ለማንኛውም አንባቢያንን ላለማሰልቸት በዚህ መጣጥፍ ላይ የእቅዱን( ምክረ-ሃሳቡን) ታሳቢዎች ላይ ብቻ ላተኩር። ሌሎቹን እንደአስፈላጊነቱ እመለስባቸዋለሁ።
የእቅዱ ታሳቢዎች፣
ታሳቢ1. መከላከያ ሰራዊት ጦርነቱን አቁሞ በሌላ ስራ ላይ ተሰማርቷል።
     1.1. በምክረ-ሃሳቡ ላይ እንደሰፈረውና በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት አፈ-ቀላጤ ለሮይተርስ ” ውጊያ ላይ አይደለንም” ወይም ” ተኩስ አቁም ላይ ነን” ብለዋል።
      1.2. የፌዴራል መንግስት የፓለቲካና ወታደራዊ ባለስልጣናት ደጋግመው እንደገለጡት የመከላከያ ሠራዊቱ ተኩስ አቁም ላይ ነው።
      1.3. እጅግ አስደንጋጭ እና አናዳጅ በሆነ መልኩ በመንግስትና የፓርቲ ልሳኖች የሚተላለፉት ዜናዎችና ዘገባዎች ” ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ችግኝ ተከሉ” የሚሉ ነበር።
      1.4. እስከዛሬ ድረስ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች እንደሚሰማው የመከላከያ ሰራዊት ተሳትፎ በካምፕ የታጠረ ነው። <ከበላይ አመራሮች ትዕዛዝ አልተሰጠንም> የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ።
     1.5. ጦርነቱን በአንድ ወገን ሆነው በሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል (ፌዴራል መንግስት፣ የአማራ ኃይል፣ የሌሎች ክልል ኃይሎች) የማይካድ የመተማመን እጦት አለ።
ታሳቢ 2. የአያምጣውና ቢሆንስ (Worst case scenario) መከተል ያስፈልጋል።
     2.1.  አያምጣውና የህውሃት ተስፋፊ ሃይል የተለያዩ የጦርነት ስትሬቴጂዎች፣ ታክቲኮችና ሳቦታጆች ተጠቅሞ አማራ ክልልን ሙሉ በሙሉ ቢቆጣጠርስ?
     2.2. አያምጣውና የህውሃት ሃይል ወልቃይት፣ ጠገዴ የመሳሰሉ መሬቶችን ቢቆጣጠርስ?
     2.3. አያምጣውና ኦሮሙማ መራሹ ፌዴራል መንግስት ከላይ በተራ ቁጥር 2.1. እና 2.2. አጋጣሚዎች በተፈጠሩበት ሁኔታ የስምምነት ተኩስ አቁሞ ወደ ድርድር ቢገባስ?
     2.4. አያምጣውና የመተማመን እጦቱ አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎ የሚያስኬድ የመከዳዳት የመጨረሻው ጫፍ ቢደርስስ?
ታሳቢ 3. አማራው ከፊቱ ከተደቀነው የህልውና የመፍረስ ናዳ ተመንጭቆ መውጣት አለበት።
   3.1. የሕልውና አደጋውን የመታደግ የጊዜ የለንም ጥድፊያ ( Sence of Urgency) ውሳኔ ያስፈልጋል።
     3.2. ከተለመደው ወጣ ያለ ስር-ነቀል ለውጥ ( Paradigm shift) የሚጠይቅ ውሳኔ ያስፈልጋል።
    3.3. የአማራ ኃይሎችን በሙሉ ያሳተፈ መተማመንን የሚፈጥር ስትራቴጂካል አሊያንስ የሚያመጣ እቅድ ያስፈልጋል።
ታሳቢ4 . ከመከላከያ ወጥተው ወደ “አማራ ሕዝባዊ ኃይል” የሚቀላቀሉት አማሮች ግልፅ ተልዕኮ ይኖራቸዋል።
July 13 በቀረበው ምክረ-ሃሳብ ላይ  ከመከላከያ ወጥተው ወደ “አማራ ሕዝባዊ ኃይል” የሚቀላቀሉት አማሮች አራት ግልፅ ተልዕኮና ጠቀሜት እንዳላቸው ተመላክቷል። የሚከተሉት ነበሩ፣
   4.1. የመጀመሪያው ተልዕኮ የዚህ መጣጥፍ መሰረታዊ ቁም-ነገር የሆነውን የኃይል ሚዛን በማሳየት ከጦርነት በፊት ለውይይት እና ለድርድር ደጋግሞ ማሰብን ይፈጥራል የሚል ነበር።
    4.2. ሁለተኛው ጠቀሜታ ጦርነት በቀጠለበት ሁኔታ የተኩስ አቁም ላይ የተገደበው የጦር አዛዥና ወታደር ወደ ስራ ይገባል የሚል ነበር።
    4.3 ሶስተኛው ጠቀሜታ እነዚህ በስራ ላይ ያሉ የጦር መሪዎችና ወታደሮች ህዝባዊ ሰራዊቱን የማሰልጠንና የማደራጀት ስራ ይሰራሉ የሚል ነበር።
    4.4. አራተኛው ጠቀሜታ የፓለቲካ ክንፉ በማንኛውም ወቅት ለሚያደርገው ድርድር የኃይል ሚዛን አስጠባቂ ሆነው ያገለግላሉ። በድጋሚ የዚህ ኃይል በጀትና ሪሶርስ የፌዴራል መንግስት ሊሆን ይገባል።
ታሳቢ 5. በሁሉም የባለድርሻ አካላት መካከል የውህደትና መተባበር ማዕከል ያደረገ መተማምናዊ ሲነርጂ በየደረጃው ይፈጠራል።
        5.1. የአማራ ኃይሎች በሙሉ ( የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የወጣት ንቅናቄዎች ቢሮክራሲው፣ የፀጥታ ሃይሎች፣ የምሁራን መማክርቶች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ዲያስፓራዎች…ወዘተ) ወደ አንድ ጥላ ማለትም ” የአማራ ሕዝባዊ ኃይል” መሰባሰብ ይኖርባቸዋል። የሚፈጠረው ሲነርጂም በፓለቲካና ወታደራዊ ውህደት የሚመጣ ሊሆን ይገባል።
         5.2. የፌዴራል መከላከያ የተናጠል ተኩስ አቁሙን አቋርጦ የህውሃትን ተስፋፊ ኃይል ለመመከት ከወሰነ በአግድሞሽ የአመራር ስርዓት ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል ጋር በመቀናጀት የመተባበር ሲነርጂ መፍጠር ይችላል። የሕልውና አደጋው ከተወገደና ድርድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ አማራ ሕዝባዊ ኃይል የተቀላቀለው የመከላከያ ሰራዊት ወደ ቀድሞው ቦታ በመመለስ የፌዴራሉ ንብረት ይሆናል።
         5.3. ከሌሎች ክልሎች የመጡ ኃይሎች ከፌዴራል መከላከያ ኃይል ጋር በቀጥታ (ቨርቲካል) የእዝ ሰንሰለት የአመራር ስርዓት ውስጥ ሊካተቱ ይገባል። ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል ጋር ግን ለጊዜው የአግድሞሽ ግንኙነት ብቻ ሊኖራቸው ይገባል። ሲነርጂውም በመተባበር የሚፈጠር ይሆናል።
Filed in: Amharic