>

ከዘመነ ዘውግ... እስከ ዘመነ ድሮን...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

ከዘመነ ዘውግ… እስከ ዘመነ ድሮን…!!!

አሳፍ ሀይሉ
Unleashing the Double Standard Within!

“ዘውግ” የሰዎች ጎሣዊ ስብስብ ነው። ከሁለት ክፍለ ዘመናት በፊት ጎሣ (ወይም አሁን “ብሔር” እየተባለ የሚጠራው) ዝም ተብሎ የሚኖርበት የሰዎች ማኅበራዊ ተዛምዶ ነበር እንጂ እንደ ሁነኛ ክስተት የምርምር አትኩሮት ተሰጥቶት የሚጠና ርዕሰ ጉዳይ አልነበረም። ነገር ግን ሆነ። ችግሩ መሆኑ ወይም ሆኖ መገኘቱ ላይ አይደለም። እንዴት ሆነ? የሚለው ጥያቄ ላይ ነው።
የዘውጌን ርዕሰ ጉዳይ በዓለም ላይ የብዙ ሰዎችን አትኩሮት መቀስቀስ የጀመረው በተለያዩ ሀገራት ተጉዘው የጉብኝት ማስታወሻቸውን (ያላዩትንና ያልሆነውንም እያጋነኑ) ያሳትሙ ከነበሩ ተጓዥ-ፀሐፊዎች የተገኙ “የጉዞ ገድሎች” የሰውን ቀልብ መሳብ ሲጀምሩ ነበር። እነዚያ የጉዞ ማስታወሻዎች ስለ ቀይ-ሕንዶች፣ ስለ ፐርሺያዎች፣ ስለ አረቦች፣ ስለ ኢንዶ ቻይና ነዋሪዎች፣ ወዘተ የሚያወሩ ነበሩ።
እነዚያ ፈጠራ የታከለባቸው የጉዞ ማስታወሻዎች በአውሮፓ ጉጉ አንባቢዎች በኩል ሰፊ ተቀባይነት ሲያገኙ ሌላውን ዓለም (ከነኗሪው) ምን እንደሚመስል የማወቅ ጉጉት በአውሮፓውያን ዘንድ ሰረፀ። እንዲያ ዓይነቱ ጉጉት ካደረባቸው መሐል ተማሪዎች፣ መንፈሳውያን ሰዎች፣ ተጓዦች፣ አጥኚዎችና ተመራማሪዎች፣ ነጋዴዎችና ሀብት ፈላጊዎች፣ እና ወታደሮች የመሳሰሉት ሁሉ ይገኙበት ነበረ።
ያን በፀሐፊዎች ማስታወሻ የተቀሰቀሰውን “የአድቬንቸር ስቶሪስ” ፍላጎት መነሳሳት ተከትሎም ቁጥራቸው በርከት ያለ አውሮፓውያን አሳሾችና መንፈሳውያን ተጓዦች (ሚሽነሪ ትራቭለርስ) በተለይ በ18ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ አሰርት ዓመታት ላይ ለጉብኝትና ለወንጌል ሥራ (እንዲሁም ሀገር-ምድሩን-ነዋሪውን ሁሉ ለማሰስ ወይም ለመሰለል) ወደ ደቡብና ምሥራቅ አፍሪካ መጡ።
ሲመጡ ያዩትን ሁሉ እንደወረደ በማስታወሻቸው ማስፈር ጀመሩ። ሞኖግራፍ ይሉታል አጥኚዎች በዚያ ሁኔታ በፅሑፍ የሰፈረውን ቀጥተኛ የእማኝነት ማስታወሻ። እንግዲህ እነዚያ ከ1800 እስከ 1850 ዓመተ ምህረቶች ድረስ (እና እስከ ክፍለ ዘመኑ ማብቂያ – ማለትም እስከ 1900 ድረስ) ባሉት ዓመታት የአፍሪካውያንን የተለያዩ ዘውጌ ነዋሪዎች ማንነት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ባህልና ቋንቋዎቻቸውን አስመልክቶ የተፃፉ የተጓዦች ሞኖግራፎች ናቸው – ኋላ የሳይንስ ጥናት መስክ ሆነው ለበቀሉት ለኤትኖግራፊ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ኤትኖሎጂ፣ ወዘተ መሠረቱን የጣሉላቸው።
ጊዜና ቦታ ለመቆጠብ ስንል አሁን በስም የማንዘረዝራቸው በርካታ የ”ምዕራቡ ዓለም” ቀደምት ተጓዦች፣ አሳሾችና ተመራማሪዎች በተለይ ከ1850ዎቹ ጀምሮ ስለ አፍሪካ የተለያዩ ዘውጌ ማኅበረሰቦች የፃፏቸውን ጥናቶችና ማስታወሻዎቻቸውን፦ “ኧ ስተዲ ኦፍ ፕራይሜትስ”፣ “ኧ ኒው ስተዲ ኢንቱ ዘ ፕሪሚቲቭ ሶሳየቲ”፣ “ፕሪሚቲቭ ካልቸርስ”፣ “ትራይብስሜን ኦፍ አፍሪካ”፣ “ዘ ሆቴንቶት”፣ “ዘ ዮሩባ”፣ “ዘ ጋላ”፣ “ዘ አምሃራ”፣ ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ. የሚሉ ርዕሶችን እየሰጡ በአውሮፓ ማሳተም ጀመሩ። የብዙውን አንባቢ የትኩረት አቅጣጫም ወደ ርዕሰ ጉዳያቸው አዞሩ።
/በበኩሌ የአፍሪካን አውሮፓዊ ቅኝ ገዥዎችንም ራሱ ያላሰቡትን አሳስበው፣ ከተኙበት ቀስቅሰው፣ ባህር አሻግረው ወደ አፍሪካ ጎትተው ያመጧቸው እነዚሁ የተጓዥ ፅሑፎችና ፀሐፍት ናቸው ብሎ መደምደም ስህተት አይመስለኝም! የሚገርመው በቅኝ ግዛት ማግሥትም ደግሞ ቅኝ ገዢዎች ደፍጥጠው ያጠፉብንን ማንነቶቻችንን እንመልሳለን ብለው አፍሪካውያን ይዘው የወጧቸው ማንነቶችም እነዚሁ በተጓዥ ፀሐፍት የተከተቡትን ጥንታዊ ማንነቶች ነበር ብንልም ስህተት የለበትም።/
እነዚያ የጉዞና የጥናት ማስታወሻዎች በወቅቱ ከምዕራብ አውሮፓ በመለየቱ የአድቬንቸር ፍላጎትን ላጫረባቸው የአፍሪካውያን የዘመኑ ዘውጌያዊ (“ጎሳዊ”) አኗኗር የመረጡት ርዕስ የዘመኑን ተጠኚዎቻቸውን (አፍሪካውያኑን) የተመለከቱበትንና የሰፈሩበትን ሚዛን ያሳያል።
ለምሳሌ ከርዕሶቹ አንዱን “ፕራይሜትስ” የሚለውን እንመልከት፦ የሰው ልጅም ከሚመደብበት የአጥቢ እንስሳ ኪንግደም መሐል በዘመኑ ሳይንስ “ፕራይሜትስ” ተብለው የሚጠሩት –  ጭንቅላታቸው ይበልጥ የሚደገፍበት የስሜት ሕዋስ እንደ ብዙዎቹ እንስሳት ማሽተት (የማነፍነፍ ችሎታ) ሳይሆን ማየት የሆነባቸው፣ የፈንጠዚያና የቁጣ ስሜታቸውን በጥቂቱም ቢሆን መቆጠብ የሚችሉት፣ ረዣዥም የመንቀሳቀሻ አጥንቶች በሰውነታቸው ያላቸው፣ ማኅበራዊ አኗኗር የተላበሱት (እና ስለዚህም ለሰው የቀረቡት) የእንስሳት ዝርዮች ናቸው። ጦጣ፣ ዝንጀሮ፣ ቺምፓንዚዎ፣ ወዘተ።
አሁንም ደግመን “ፕሪሚቲቭ” የሚለውን ኤትኖግራፈሮቹና ባለ ማስታወሻዎቹ በወቅቱ በየሥፍራው ያጋጠማቸውን የአፍሪካ ዘውጌያዊ ማኅበረሰብ ለመግለፅ የተገለገሉበትን ቃልም ለምሳሌነት እንውሰድ። “ፕሪሚቲቭ” የሚባለው ምን ዓይነት ማኅበረ-ሰብ ነው? ወይም ነበር? ፕሪሚቲቭ የሚባለው ዘመናዊ ሥልጣኔ ያልዘለቀው ማኅበረ-ሰብ ነው። የቅድመ-ኢንዱስትሪ ዘመን ሰው ነው። የቅድመ-ሳይንስ ዘመን ሰው ነው። “ሳቬጀሪ ኤንድ ኢግኖራንስ” በእጅጉ ያጠቃው ማኅበረ-ሰብ ነው። ያልሠለጠነ ማኅበረ-ሰብ ነው “ፕሪሚቲቭ”።
እንግዲህ – በመቶዎች የሚቆጠሩትን የዘመኑን ቀደምት የአፍሪካ ዘውጌያዊ ጥናቶች (“አፍሪካን ኤትኖግራፊክ ስተዲስ”) ያገላበጠ ማንም ሰው መገንዘብ እንደሚችለው በወቅቱ በአውሮፓውያኑ እይታ የአፍሪካውያኑ የጎሳ (የ”ብሔር”) ማኅበረሰባዊ አኗኗር – ከዘመኑ በአውሮፓ ሊጎመራ ከነበረው የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ማኅበረ-ሰብ አኗኗር ጋር ሲነፃፀር እጅግ ኋላ-ቀር ሆኖ እንዳገኙት ወይም እጅግ ጥንታዊ አድርገው እንደተመለከቱት ግልፅ ነው።
(በነገራችን ላይ አፍሪካዊን እንደ ሰብ-ሂዩመን የቆጠሩና የደመደሙ፣ ብሎም አፍሪካውያንን ህፃናትና ቂጣም ሴቶች ወደ አውሮፓ ወስደው በሙዝየምና ዙ ውስጥ አስገብተው ለጉጉ ተመልካች ያስጎበኙ፣ ለሠርከስ ሾው ያቀረቡ፣… በርካቶች እንደነበሩም አንድ የማይካድ የዘመኑ ሃቅ ነው!)
እዚህ ላይ እጅግ አስምሬ መግለፅ የምፈልገው ነገር – አፍሪካውያንን በተመለከተ – በተለይ ከ1850ዎቹ ጀምሮ ባለው ዘመን የተፃፉ የተጓዦች ትርክቶች፣ ማስታወሻዎች፣ ሞኖግራፎች፣ የተሰበሰቡ ኤትኖግራፊክ ዴታዎች፣ አንትሮፖሎጂክ ሪሰርቾች፣ ካልቸራል ስተዲሶች፣ እና ስቴሪዮታይፕሶች (ማለትም “እነርሱ እንዲህ ዓይነት ሕዝቦች ናቸው ብለው በመፈረጅ የሳሏቸው ማህበረሰባዊ እይታዎች”) ሁሉ – አሁን ዘመን ድረስ እኛን አፍሪካውያንን ለመግለፅና ለማሰብ የሚገለገሉባቸው የእይታ መነፅሮች መሆናቸውን ነው።
ይህን አባባሌን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ብቻ አነሳለሁ።
በምሳሌነት የማነሳው ከብዙ (ከ17) ዓመታት በፊት ስለ ዘመናዊ የፖለቲካ ማኅበሮች በማጥናት ላይ ባለሁበት ወቅት ያስተዋልኩትን እና ፀሐፊውም “የዘመናዊ ፖለቲከል አሶሲየሽንስ ጥናት አባት” እስከመባል የደረሱትን የፕሮፌሰር ጄን ብሎንዴልን በታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎች ለማስተማሪያነት እንደ አብይ ማመሳከሪያ የሚጠቀስ ቀደምት ሥራ ነው።
ያንን ወፍራም ጥራዝ ካነበብኩ በኋላ ነበረ እነዚያን የድሮ አሳሾቹ “ኋላቀር” ያሏቸውን በዘመናት መወላለድና ጥንታዊ የዝምድናና ትስስር ባህል የተፈጠሩትን “የዘውጌ” ማኅበረ-ሰብ ስብስቦች (ማለትም “አንድ ‘ብሔር’ ነን ብለው በማኅበር የተደራጁ ሰዎችን”) የፖለቲካ ሳይንሱ አባት ጆን ብሎንዴልም ሆኑ፣ ዘመናዊው ዓለም (አውሮፓም፣ አሜሪካም፣ ላቲንም) – ለፖለቲካ ስብስብ አስኳል መስፈርት ከሆነው የሀሳብ-ትስስር ይልቅ አባሎቻቸው በደም-ትስስር አሊያም በቋንቋ-ትስስር የተሰባሰቡ “ኋላ-ቀር” (እንዲያውም “የጋርዮሽ”) “ፕራይሞርዲየል ሂዩመን ግሩፒንግስ”  ወይም “ፕራይሞርዲየል አሶሲየሽንስ” ስለሆኑ – በዘመናዊው ዓለም ቅቡልነት ባገኙ አስተሳሰቦች ሲለኩ – የዘውጌ ስብስቦች – “የፖለቲካ ማኅበር” (“ፖለቲከል አሶሲየሽንስ”) ለመባልም ራሱ እንደማይበቁ – በአግራሞት እና በተምታታ ስሜት ለመጀመሪያ ጊዜ አበጥሬ ያስተዋልኩት።
እንግዲህ የማወራላችሁ ዘመናዊው ዓለም ስለተቀበለው የፖለቲከል አሶሲየሽንስ ምንነት ነው። እና ዘመናዊው ዓለም በተቀበለው የፖለቲካ ማኅበር ምንነት አንፃር ካየነው ማንኛውም በዘውጌነት የተደራጀ የ”ብሔር” ስብስብ “የፖለቲካ ፓርቲ” ተብሎ ለመጠራት ብቁ እንዳልሆነ ነው። እውነታው ይሄ ነው። ቲዎሪው ይሄ ነው። ተግባሩስ?
ተግባሩማ የሚከተለው ተግባራዊውን ነው። ዘ ፕራክቲስ ፎሎውስ ዘ ፕራክቲካል። እንግዲህ ቀድሞ ስለ አፍሪካ ማኅበረሰቦች የተሳለውን ኤትኖግራፊክ ስዕል አስታውሱልኝ። እና ሳስበው – ይመስለኛል – አውሮፓውያኑና አሜሪካውያኑ – አፍሪካውያኑን እስካሁንም “ፕሪሚቲቭ ሶሳየቲስ” ናቸው ብለው ከመፈረጅ አልቦዘኑም።
ይመስለኛል – እስካሁንም አሜሪካውያኑና አውሮፓውያኑ ስለ እኛ ስለ አፍሪካውያን ሲያስቡ በሃሳባቸው የሚመጣባቸው ያ ድሮ እነ ጆሃን ክሮፍትና እነ አባ ባህሬ እነ ዲ ሞርጋን ወዘተ. ያጠኑት የአፍሪካ ጎሣዊ ኋላ-ቀር ሕዝብ፣ ዘውጌያዊ ጥንታዊ ማኅበረሰብ (ዘ አርካይክ ኤንድ ዘ ፕሪሚቲቭ አንደርዴቨሎፕድ ትራይብስሜን ኦፍ አፍሪካ”) ነው። የተዛባው ደብል ስታንዳርዱም ያለው እዚህ ቁልፍ ነጥብ ላይ ነው ያለው።
በዛሬው ዘመን ላይ ራሱን በጎሳና በዘውጌ የሚገልፅ አውሮፓዊና አሜሪካዊ ፖለቲከኛ፣ የፖለቲካ ምሁርና የፖለቲካ ፓርቲ ተፈልጎ አይገኝም። እኛንስ አፍሪካውያንን ሲገልፁ እንዴት ነው የሚገልፁን? በምን ቀመር ነው እኛን የሚሰፍሩን? – ራሳችንን ካልዋሸነው መልሱ ቀላል ነው።
የሠለጠነው ዓለም ዛሬም ወደ አፍሪካ ለጉብኝት ሲመጣ ቋምጦ የሚመጣው እነዚያን ከዘመናዊው ዓለም የራቁ ጥንታዊ ጎሳዎች በዓይኑ በብረቱ ለማየት ነው። እነርሱ እኛን ለመገንዘብ የሚሹት ልክ እንደ ድሮው እንደ ጥንቱ፦ As African Tribesmen of the Past! ነው።
አንድ የአሜሪካ ፖለቲከኛ ዛሬ ስለ ሀገሩ የሚያወራው ርዕሰ ጉዳይ፦ ዲሞክራት እንዲህ ሠራ፣ ሪፐብሊካን እንዲህ ፈጠረ፣ ግለሰብ እንዲያ ሆነ፣ ካምፓኒ በዚያ ገባ፣ ንግድ በዚህ ወጣ፣ ወዘተ ወዘተ ነው። ስለ እኛስ? ያው ሰው ስለ እኛ ብትጠይቀው እርሱ ራሱንና የራሱ የሆነውን ነገር በማይገልፅበት ስዕል ሊገልፅ ሲጀምር ታየዋለህ። ትግሬ እንዲህ ገባ፣ አማራ እንዲህ ወረደ፣ ኦሮሞ በዚህ ወጣ፣ ሲዳማ እንዲህ ሆነ፣ ወዘተ ወዘተ ብሎ ያስተነትንልሃል።
እንዴ?! ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ – ስለ ፖለቲክስ እየተወራ – ሰው ለራሱ የማይጠቀምበትን መሥፈርት ለምን ለሌላ ሰው ይጠቀማል???? ብለህ አትገረም። ደብል ስታንዳርዱ ይሄ እኮ ነው። እርሱ ሠልጥኜያለሁ ባይ ነው። ስለዚህ ራሱን ወይም ሀገሩን ወይም የሀገሩን ፖለቲካ በጎሳና በዘውጌ ደረጃ አውርዶ ማሰብና ለሌላ መንገር ለእርሱ ክብረ-ነክ ነው። ለእርሱ ክብረ-ነክ የሆነውን ነገር – ታዲያ እንዴት እና ምን ሲደረግ ነው አንተን መግለጫና መተንተኛ ነገር ሆኖ ያገኘው?
– ራስህን ካልዋሸኸው መልሱ ቀላል ነው። በእርሱ አስተሳሰብ – በእርሱ ስዕል – እርሱ የዘመነ ድሮን – የፖስት-ሞደርናይዜሽን ዘመን – ዘበናይ ዘመነኛህ ነው። አንተ ደግሞ – የዘመነ ፕሪ-ሞደርን – የጥንት ጋርዮሽ ዘመን ትራፊ – ያልታደልክ አፍሪካዊ የሆነ ጎሳ፣ ወይ የሆነ ነገድ፣ ወይ የሆነ ዘውጌ አባል ነህ። አንተ ኋላቀር ስለሆንክ አንተ ልትገለፅ የሚገባህ በዚህ ዓይነቱ መንገድ ነው። እርሱስ?
ስለ እነርሱ ለማወቅ ጉጉቱ ካደረቤሆ ግን ስለዘመናዊ የድሮን ቴክኖሎጂ ነው የምትጠይቀው። ድንገት ተሳስተህ አንዱን ፈረንሳዊ ወይ አሜሪካዊ፦ “ጎሳህ ምንድነው? የየትኛው ጎሳ ፓርቲ አባል ነህ? ዘውጌህስ ምንድነው?” ብለህ ብትጠይቀው – ጤንነትህን ይጠራጠራል። ወይ በሳቅ ይፈነዳል። Come on, we are in the 21st century, aren’t we?! Are you crazy?
እኔ የምለው ደግሞ በአንድ ወቅት ኦባማ ያለውን ነው፦
“Can’t we be our better selves? Sure we can. Then, let’s all be our better selves!”
አዎን። የተሻልን እኛ መሆን እንችላለን። እኛ ሁላችን የምናከብረውና የምንመካበት የየራሳችን ባህልና ማንነት አለን። ነገር ግን በሆነ ዘመን በተሳልንበት የጎሳና የ”ብሔር” ዘውጌያዊ ቅርቃር ውስጥ ተከርችመን እስከ ወዲያኛው የፍርድ ቀን ባለንበት የምንሰነብት ፀረ-ለውጥ እና ፀረ-እድገት ፍጡራን አይደለንም።
We are not static people who have remained dormant ever since some archaic point in history. We are in an era of continuous change. We’ve changed, and can change the ways we do the things we do. And let’s keep the vibes.
እኛ ከሚገልፁን እና ከሚሰፍሩን የተሻለ ታላቅ ዘመነኛ ማንነት አለን። እና ከዚህ አሁን በዓለሙ ዓይን ከተሰፈርንበት እና ራሳችንን እየሰፈርንበት ካለው የ”ትራይብስሜን” ዘውጌያዊ መስፈሪያ ወጥተን የተሻለውን እኛነታችንን እናምጣው። ፈጣሪ ለዚያ ጥረታችን ይርዳን።
ልብ ብሎ ያየው ሰው ካለም በዘንድሮው በአሜሪካ በተከበረው የኢትዮጵያኖች በዓል ላይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ በድሮን ቴክኖለጂ ወደ ሰማይ እጅግ ከፍ ከፍ ከፍ ተደርጋ ተሰቅላ አሻቅባ ተውለብልባለች!!
እንግዲህ ከዘመነ ዘውጌ እስከ ዘመነ ድሮን ተጉዘናል።
ለወደፊቱ ጉዟችን ለሁላችን መልካሙን ሁሉ ተመኘሁ።
የብዙሃን እናት – የጥበብ መፍለቂያ – እምዬ ኢትዮጵያ – በልጆቿ አምራና በልፅጋ – ለዘለዓለም ትኑር።
ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን አብዝቶ ይባርክ።
Filed in: Amharic