(ሙሼ ሰሙ)
ዛሬ ላይ የአንድ ዶላር ተነጻጻሪ ሕገ ወጥ ምንዛሪ (Parallel Market) 67 ብር እንደደረሰ በሰፊው እየተወራ ነው። ባለፈው ሶስት ዓመት የሕገ ወጥ ምንዛሪው ከ100% በላይ ንሯል። ሕጋዊ ምንዛሪው ደግሞ በአማካይ በ36.5 % ደርሷል።
የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ ወሳኝ በሆኑ የከተማችን አውራ ጎዳናዎች ላይ ዓይን ባወጣ መልኩ እየተጓተቱ ይቸረቸራል። ወደ አብዛኛዎቹ ባንኮች ጎራ ካሉም ዶላር እንደ ሸቀጥ በደላላና በድርድር ለመሸጥ በራቸው ክፍት ነው።
የዶላር ዋጋ መናር የሚያስከትለውን መዘዝ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው። ምሬቱ የሁላችንንም በር በየቀኑ እያንኳኳ ነው። መስከረም ሲጠባና ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሲገቡ ልብስ፣ ቁሳቁስና ፍጆታ ለማሟላት የሚጠብቀንን ፈተና ማሰብ ያስፈራል።
በአጭር ጊዜ የዶላር ምንዛሪ የ22 ብር ጭማሪ እንዴት ሊያሳይ ቻለ? ከሕጋዊ ምንዛሪው ጋር ያለው ልዮነቱስ በዚህ ደረጃ (22.5) ለምን ሊሰፋ ቻለ? ምክንያቱ ምንድን ነው መፍትሔውስ? እዚህ ላይ ከሕጋዊ ገበያው ይልቅ ስለ ተነጻጻሪ ገበያው ለማንሳት የተገደድኩት፣ ተነጻጻሪ ገበያው ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢኮኖሚያችን ወሳኝ መለኪያ እየሆነ ስለመጣ ብቻ ነው። ከሌላ ማሳያዎች (Indicators) አኳያም ማየትም ይቻላል።
•1) ስጋትና ፍርሃት በመንሰራፋቱ በርካታ ሰዎች ንብረታቸውን እየሸጡ ብሩን በደላር ስለሚለውጡ አቅርቦቱን እያሳሳውና ፍላጎትን እያሳደገ መምጣቱ (Speculation, holding, hording, short-selling and capital flight )
2) አንዳንድ ባንኮች ውስጥ ላኪና አስመጭዎች በደላላና በባንኮቹ አመራሮች ኮሚሽን ኤጀንትነት ዶላር መግዛትና መሸጥ ሕጋዊ መሆኑ፣ የተነጻጻሪ ገበያውን ዋጋ መተመን መቻሉ፣ የኮሚሽኑ ተካፋዩ እያደገ ጭማሪው መናሩ (Capital flight, Under-invoicing, high premiums, expanding brokers premiums)
3) ለዝወውርና መሳርያ ግዢ፣ ከብር ይልቅ አስፈላጊው ዶላር ስለሆነ፣ በሕገ ወጥና በሕጋዊ መንገድ፣ በስፋትና በውድ ዋጋ እየተገዛ ለጦርነት አቅርቦት መዋሉ፣ (War Economy)
4) ሕጋዊ በሆነ መንገድ ባንክ ላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘትና ቢገኝም በቂ አለመሆን፣ ወደ ተጓዳኝ ገበያው ዶላር ፍለጋ ማማተር ( Under invoicing, illegal money transfer, under cutting supply)
5) ባለፈው ሶስት ዓመት እሴት ያልፈጠረና አቅርቦትን ያላሻሻለ መጠነ ሰፊ ገንዘብ በሰበብ አስባቡ ወደ ኢኮኖሚውና ግለሰቦች ኪስ መግባቱ፣ የአቅርቦትና ፍላጎት ሚዛኑን ማናጋቱ (Unbalanced budget deficit, white elephant projects, expanding monetary policy) ( ለአጠቃላይ ግሽበቱ እስከ 40% ድርሻውን ይወስዳል)
ምን ይሻላል? ስራው ፈታኝ ነው። ተከታታይና ዘላቂም መሆን አለበት።የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ አቅድ ያሻል። ምልከታዎቼን በወፍ በረር ልጠቁም፣ ቀሪውን አክሉበት።
1)በአጭር ጊዜ:- ክትትልና ቁጥጥርን ማጠናከር፣ አሰራርን ማዘመን፣ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ የቅንጦት ፍላጎቶችን መገደብ፣ ገበያውን ያፈኑትን ደላሎች ከባንክም ሆነ ከጥቁር ገበያ ማስወጣትና በፖሊሲ እንዲመሩ ማድረግ(ጥቁር ገበያን ሕጋዊ እስከማድረግ መሄድ)
2) በመካከለኛ ጊዜ:- የበጀት ጉድለትን (ማጥፋት ሳይሆን) በተለዋዋጭ ዓመት ሚዛን ባላንስ ማድረግ፣ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ፕሮጀክቶች በስተቀር የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ፕሮጀክቶችን ዘመን ማራዘም፣ ጥብቅ ፊሲካልና ሞኒተሪ ፖሊሲ መመራት፣
3) በረጅም ጊዜ:- በአጭርና መካከለኛ ጊዜ ላይ ተመስርቶ የውጭ ምንዛሪን የሚያሳድጉ ፖሊሲዎችን መቅረጽና ኢንሴኔቲቫይዝ ማድረግ፣ መከታተልና ማጓልበት፣ ኢኮኖሚው እንዲሰፋ “de facto” crawling peg ሲስተምን በመተው ሙሉ በሙሉ ወደ ተንሳሳፊ Floating ሲስተም መሸጋገር ያስፈልጋል።