>

የፍልሰታ ጾም እና የደራሲና ሐያሲ ጋሼ አስፋው ዳምጤ ትዝታን በጨረፍታ... (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ፤)

የፍልሰታ ጾም እና የደራሲና ሐያሲ ጋሼ አስፋው ዳምጤ ትዝታን በጨረፍታ…

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ፤

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምጣኔ ሀብት/የኢኮኖሚክስ ምሁር፣ ደራሲና ሐያሲ የሆኑት ጋሽ አስፋው ዳምጤ፤ “ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ” የተባለ ተቋም፤ ከድኅነት-ወደ-ልማት:- ዕውቀትን-ለትውልድ-ማስተላለፍ በሚል አርእስት በሒልተን ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ ትዝታቸውን ለታዳምያን አካፍለው ነበር።

ጋሼ አስፋው የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ በነበሩበት ጊዜ በክረምት ወራት ከእንግሊዛውያን ተመራማሪዎች ጋር በደብረ ማርቆስና ከጮቄ ተራራ እስከ ዓባይ ወንዝ፣ ከእንግሊዛውያኑ የጥናት ባለሙያዎች ጋር በረዳትነትና አስተርጓሚነት ለ2 ወር ቆይታ አድርገው ነበር። ጋሼ አስፋው በፎረም ፎር ሶሻል ስቴዲስ የጥናት መድብል ላይ ለሕትመት ከበቃው ከዚህ ትዝታቸው- የፍልሰታን ጾም አስመልክቶ የሆነውን ነገር እንዲህ ይተርኩልናል።

 
… ይሁንና፣ የፍልሰታ ጾም መጣች። በምግብ ከእነርሱ (ከእንግሊዛውያኑ ማለታቸው ነው) ተለይኹ። እስከዚያ ወቅት ድረስ፤ እነርሱ ከእንግሊዝ አገር ጭነው ያመጧቸውን የታሸጉ፣ እጅግ በርካታ ዓይነት ምግቦች እና በአካባቢው የምናገኘውን ዶሮና እንቁላል አብሬአቸው ስመገብ ነበር- ከአሳማ ሥጋ ነክ ከሆኑ ነገሮች በስተቀር። አሁን ሁሉንም እርግፍ አድርጌ ተውኩ።
 
አገሬው ለካ ሲታዘበኝና ሲያማኝ ኖሯል። የአዲስ አበባ ሰው ሃይማኖት የለውም እያለ! … ሃይማኖተኛ መሆኔ ሲታወቅ እንጀራና ሽሮ ወጥ ከአካባቢው ካሉ ባላገሮች ይጎርፍ ጀመር። በቶሎ ማስቆም ነበረብኝ። በአካባቢያችን ያሉ ፖሊሶች እንኳን እያገዙኝም የሚያልቅ አልነበረም። “እንጀራና ወጡ ቀርቶ፣ ቆሎ ቢሆንልኝ ብሏል” ሲባል ጊዜ ደግሞ ቆሎው በስልቻ ይመጣ ጀመር! ከዚያም ድንችም እንደዚሁ። የመጣው እስኪያልቅ ሁለቱም ዓይነት እንዲቆም ለማድረግ ትግል ነበር። ምክንያቱም እያንዳንዱ ለጋሽ [ባላገር] የራሱን እንጂ ሌላው ምን አደረገ አይልም ነበርና ነው።
 
ጉድ ተባለ! “እኛ ማተብ [ሃይማኖት] የለውም እያልን ስናማ፤ እሱ ፍልሰታን በቆሎ ጿሚ ነው ለካ!” ተባለልኝና ቁጭ። በጣም ነበር የደነቀኝ፣ ልቤም የተነካው [በባላገሮቹ ደግነት]። ፈርንጆቹ ወዳጆቼ በተለይ ከድንቹ  ባያሌው ደረሳቸው። ቅቅሉ፣ ጥብሱ በአትክልት ዘይት።

አዲስ አበባ ስንደርስ የእንግሊዝ ኤምባሲ ግብዣ አደረግልን፡፡ ሁላችንም ጢማችንን አሳድገን ነበር፡፡ የኔ ወሬ ተነሳ፤ በቆሎ 15 ቀን ጾመ ተብሎ። ተጽፎላቸው ኖሯል! ተሰግቶ የነበረው፣ እስከ ስድስት ጦሙን እየዋለ ከዚያ ቆሎ ብቻ በልቶ እያደረ እንዴት ይሆናል? ይታመማል፤ በጉዞ ይደክማል፣ እየተባለ ኖሯል። ይኽን ጎጃም ሳለን አልሰማሁም ነበርና፣ እዚህ በሌሎች መታወቁን አላውቅም ነበር! ለወሬ የሚበቃ ነገር አልመሰለኝም ነበር።
ለመውጫ ያህልም፤ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ፎረም ፎር ሶሻል ስቴዲስ) በ1990ዎቹ በተለያዩ ሙያ ዘርፎች (በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊው፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በአቬዬሽን፣ በሚዲያ፣ በፍትሕና ሕግ… ወዘተ) ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ትልቅ አስተዎጽዖ ያደረጉ አንጋፋ ምሁራንን በመጋበዝ፤ “ከድኅነት-ወደ-ልማት:- ዕውቀትን-ለትውልድ-ማስተላለፍ” በሚል መርሕ የትናንትናዎቹ ባለውለታዎቻችን ለዛሬው ትውልድ እውቀታቸውንና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉን ያደረገው ጥረት እጅጉን የሚደነቅ ነው። ስኬታማም ነበር!!
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ እጅጉን በጉጉት የምንጠብቀው የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ወርሃዊ ውይይት ዋንኛው ነበር። ይህን መድረክ በማዘጋጀት ረገድም በአንድ ወቅት ተቋሙን በዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩት የታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ፣ ፕ/ር ሽፈራው በቀለ፣ አቶ ደሳለኝ ራህመቶ፣ ዶ/ር ምሕረት ዐይነው፣ ዶ/ር አስናቀ ከፍያለው እና እነ ወ/ሮ ቆንጅት በለጠ ይጠቀሳሉ።
እናመሰግናለን!! የማኅበራዊ ጥናት መድረክ/Forum for Social Studies
ሰላም!!
Filed in: Amharic