>

ዓለምን ካፅናፍ አፅናፍ ያደመቁት — የማርሽ ቀያሪው የድል ውሎዎች... !!! (አሳፍ ሀይሉ)

ዓለምን ካፅናፍ አፅናፍ ያደመቁት — የማርሽ ቀያሪው የድል ውሎዎች… !!!

አሳፍ ሀይሉ

ባንዲራችንን በክብር አደባባይ ከፍ ያደረገ፣ የድል ብሥራትን ካፅናፍ አፅናፍ ያስተጋባ፣ የኢትዮጵያውያን የሁልጊዜም ጀግና፣ የመጪው ትውልድ ፅኑ አብነት — “Yifter, the Shifter!” — ምሩፅ ይፍጠር – ማርሽ ቀያሪው!!!
ኢትዮጵያ ዕንቁ-ዕንቁ ልጆች አሏት፡፡ ምሩፅ ዋነኛው ነው፡፡ ማርሽ ቀያሪው፡፡ አንፀባራቂ ኢትዮጵያዊ፡፡ ምሩፅ ይፍጠር፡፡ “Yifter the Shifter”፡፡
ስለምሩፅ ሲወራ ሁልጊዜም ሊጠቀስለት የሚገባ ታላቅ ማንነቱ — ምሩፅ — ለዘር ክፍፍል እና ለዘር መድልዎ ያለው ከብረት የጠነከረ የአውጋዥነት አቋሙ ነው፡፡
ምሩፅ አንፀባራቂ ኮከብ ነው ብለናል፡፡ ሽቅብ በሠማያት ላይ የምድሪቱን ሕዝቦች በእኩል ዓይን የሚያይ፡፡ የሰማይ ኮከብ ነው ምሩፅ፡፡ የዘር ሽንሸናን፣ የዘር ክፍፍልን፣ አንዱ ዘር የበላይ፣ አንዱ ዘር የበታች የሚሆንበትን — የዘር ፖሊሲ የሚቃወም — መንፈሱን በሰው ልጆች ልክ ላቅ አድርጎ የሰቀለ — ታላቅ ሰብዓዊ ሥጦታ ነው — ምሩፅ፡፡
ወቅቱ 1968 ዓመተ ምህረት ነበር፡፡ ምሩፅ በካናዳ ሞንትሪያል ለሚደረገው የኦሎምፒክ ውድድር ሙሉ ዝግጅቱን አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም ወደ ሥፍራው ተጉዞ ልምምዱን እያደረገ ነው፡፡ ዓይኖች ሁሉ በዚያ የሞንትሪያል አትሌቲክስ ውድድር ላይ ተተክለዋል፡፡ ምሩፅ ደግሞ የ10,000 እና የ5,000 ሜትር ርቀቶቹን የወርቅ ዋንጫዎች ያነሣል ተብሎ በብዙዎች ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ምሩፅ ከ 4 ዓመታት በፊት — በሚዩኒኩ የ1972 ኦሎምፒክ — በ10,000 ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ያጠለቀ አትሌት ነው፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት ደግሞ — በሌጎሱ የመላ አፍሪካ ሻምፒዮና ውድድር በ10,000 ሜትር የወርቅ፣ በ5,000 ሜትር ደሞ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀ አትሌት ነበር፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡
ምሩፅ ከ2 ዓመታት በፊት ደሞ — በዩናይትድ ስቴትስ የ1974 ዓለማቀፍ ሻምፒዮና — በሉዊስቪል በ5,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ፣ በኒውዮርክ ደሞ በ2 ማይል (በ3.2 ኪሎ ሜትር) ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ዓለምን ጉድ ያሰኘ አትሌትም ነበር፡፡ እና — ብዙዎች — የሞንትሪያሉ ኦሎምፒክ የ10ሺኅና የ5ሺኅ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎች — የግሉ ናቸው ብለው አስቀድመው ደምድመዋል፡፡
ነገር ግን — ውድድሩ ሊካሄድ 24 ሠዓታት ብቻ ሲቀሩት — ያን ሁሉ የዓለም ግምት የሚያስቀር አንድ ታላቅ ክስተት — በካናዳ ሞንትሪያል የአትሌቲክስ መንደር ተሰማ፡፡
“ኢትዮጵያውያን አትሌቶች — በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደውን — የአፓርታይድ የዘር መድልዎ ፖሊሲ በመቃወም — የሩጫ ውድድራቸውን ሰርዘው — ወደ ሃገራቸው ዕቃቸውን እየሸከፉ ነው” የሚል — ምሩፅን በጉጉት ለሚጠብቀው የአትሌቲክስ ማህበረሰብ — አስደንጋጭ የነበረ ዜና፡፡
“ያ” — ይላል ምሩፅ ኋላ ሲያስታውስ — “ያ — ለምድሪቱ ሰብዓውያን ሁሉ እኩልነት ሲባል የተከፈለ ታላቅ ዋጋ ነበር!”!!
በወቅቱ — አይበገሬነቱን በዓለም ፊት ሊያስመሰክርና የድል ሜዳሊያዎችን ሊያጠልቅ በከፍተኛ የመንፈስና የአካል ብርታት ላይ ሆኖ ይጠባበቅ የነበረው ምሩፅ ይፍጠር — የኢትዮጵያ ውሣኔ ሲነገረው — ዱብ-ዕዳ ቢሆንበትም — በሙሉ ፈቃደኝነት ነበር — ለሰው ልጅ እኩልነት የተከፈለውን ዋጋ — ተቀብሎ ዕቃውን ሸክፎ ወደ እናት ሀገሩ የተመለሰው፡፡
በወቅቱ ብዙዎች በዚያው እንዲቀር ሊያግባቡት የሞከሩ ነበሩ፡፡ የምሩፅ መልስ ግን ሁሌም ያው ነበር፡-
“ሀገሬን እወዳታለሁ — ሀገሬን ከእኔ ልታርቃት አትችልም — ኢትዮጵያዊ ነኝ — ሀገሬ በአፓርታይድ የዘር መድልዎ ላይ የወሰደችው አቋም የእኔም የግሌ አቋም ነው — ያን አቋም በመያዜም እጅግ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል — እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ — በሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት አምናለሁ” — የሚል ቆራጥ ቃል ነበር መልሱ፡፡
“We did it for South Africa, who was fighting against Apartheid. That at least lessened the pain.” (- Athlete Mirutse Yifter)
በነገራችን ላይ — ምሩፅ ስለ ሀገሩ ሽንጡን ገትሮ ሲከራከር — ምሩፅን ሀገሩ ምሉዕ-በኩልዔ ደስታ ሰጥታው ነበረ ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ምሩፅ የ1972ቱን የሚዩኒክ ኦሎምፒክ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፡-
“በሚየኒክ የተወዳደርኩት በ10,000 ሜትር ብቻ ነበር፡፡ በዚያም የነሃስ ሜዳሊያን ነው ያገኘሁት፡፡ ዋናው የተዘጋጀሁበት ውድድር ግን የ5,000 ሜትሩ ውድድር ነበር፡፡ በውድድሩ ዕለት — በጠዋት ተነስቼ ሰውነቴን ካሟሟቅኩ በኋላ — ትጥቄን ሁሉ ሸክፌ — ከቡድኔ ጋር በውድድሩ ሥፍራ ለመሄድ መጠባበቅ ጀመርኩኝ፡፡ ሆኖም ማንም ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ስለዚህም ዞር ዞር ብዬ ሥፍራውን ለመጠየቅ ሞከርኩኝ — ላገኘው አልቻልኩም፡፡ በመጨረሻ — ወደ ተነሣሁበት መንደር ተመልሼ ስመጣ ማንም የለም፡፡ ጥቂት ቆይተው ግን የቡድናችን አሠልጣኞች — ሮባ እና ወልደመስቀል ኮስትሬ እየተቻኮሉ ወደ እኔ መጡ፡፡ የውድድሩ ሠዓት ደርሶብን ነበረና እየተጣደፍን ወደ አትሌቲክሱ ስቴዲየም ሄድን፡፡” ከዚያስ?
“ከዚያ ግን የሚያሳዝነው ልክ እኛ ሥፍራው ስንደርስ — ውድድሩ ተጀምሮ ነበር፡፡ በጣም አዘንኩኝ፡፡ አሠልጣኞቼም ራሳቸው ደንግጠው — እኔን ለማፅናናት ከመሞከር በቀር — ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር አልነበራቸውም፡፡” ይህን ሲያስታውስ የተለመደው ፈገግታው ሳይለየው ነው።
በዚያ ዓይነት — ምሩፅ ይፍጠር — የተዘጋጀበትንና በጉጉት የተጠበቀውን የሚዩኒኩን የ5,000 ሜትር ሜዳሊያ ሳያጠልቅ ቀረ፡፡ እና ወደ እናት ሀገሩ — የነሃስ ሜዳሊያውን ይዞ ተመለሰ፡፡ የጠበቀው ግን ጭብጨባና አቀባበል አልነበረም፡፡ እስር ቤት ነው፡፡ የጠበቀው፡፡ ከሚዩኒክ የአትሌቲክስ መንደር በቀጥታ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት፡፡ እና ወደ ከርቸሌ።
ከሚዩኒክ መልስ ምሩፅ ለ3 ወራት ታሠረ፡፡ በከርቸሌ ግቢ ውስጥ ሆኖም ግን — ከማረሚያ ቤት ፖሊሶች ጋር ጠዋት ጠዋት እየተነሳ ልምምዱን አላቋረጠም፡፡ “እፈታለሁ” በሚል ተስፋ ትሬኒንጉን ቀጠለ፡፡ “አንድ ዕድል ብቻ ሥጡኝ እክሳለሁ!” በማለትም የወደፊት የድል ቃሉን እንደ መታያ አቀረበ።፡፡
በእርግጥ — ምሩፅ — አውቆ ሆን ብሎ ነው የኒዩኒኩን 5ሺህ ሜትር ‹‹ቦይኮት›› ያደረገው በሚል ያረፈበት ጥርጣሬ በዚህ ጉዳይ አንዳችም ‹‹ቀልድ-በማያውቁት›› የሀገሪቱ አስተዳዳሪዎች ዘንድ  እንዳለ ቢሆንም — ነገር ግን — የቁርጥ ቀን ልጅ ነውና — አንድ የመፈተኛ ዕድል ይሰጠው ተባለ፡፡
እናም — ያ ዕድል — ምሩፅ የ3 ወሩን እስራት እንዳገባደደ — ከአትሌቲክስ ጓዶቹ ጋር — ወደ ናይጄሪያ ሌጎስ የመሄድ — ወርቃማ ዕድል ነበር፡፡
ምሩፅም ግን ያን ወርቃማ ዕድል ተጠቀመበት፡፡ ሁለት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ፡- በ10ሺኅ የወርቅ፣ በ5ሺኅ ደሞ የብር ሜዳሊያዎች። እና እነዚያ የሌጎስ የድል ሜዳሊያዎች — ስሙንም፣ ሀገሩንም፣ ንፅህናውንም አዳኑ!!!
ምሩፅ ይፍጠር — በህይወቱ — ብዙ ውጣ ውረድን ያሳለፈ — በህይወት ፈተና የጎለመሰ — እና ምራቅን ዋጥ ያደረገም ሰው ነበረ፡፡
ዓለማቀፍ — ሩጫን በወጣት አትሌትነት በ1968ቱ የሜክሲኮ ኦሎምፒክ ሲጀምር — ምሩፅ — በ24 ዓመቱ — ገና ፀጉሩ በራሱ ችምችም ያለ — ቀልጠፍ ያለ የዘመኑ አፍሮ ነበረ፡፡ በ1980ው የሞስኮ ኦሎምፒክ ላይ — ማለትም ከ12 ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን — ብዙው ዓለም የሚያውቀውን — ፀጉሩ መሐል ለመሐል መክዳት የደረሰውን — የትልቅ ጎልማሳ ሰው ፊት — ከወጣት ተክለቁመና ጋር የተላበሰ — የአንድ ብርቱ ጎልማሳ አትሌትት ገጽታ ተላብሶ ነበር ብቅ ያለው። ጥቂት ዓመታት እጅጉን አስረጅተውታል። እርሱ ግን — ታሪክን ሠራ፡፡
እስካሁን ድረስ ዓለም ሁሉ ምሩፅን በጠራው ቁጥር አብሮ የሚጠራበትን — ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› – “Yifter the Shifter” — የሚል ቅፅል ስሙንም ያገኘው — በዚሁ የሞስኮ ውድድር — ከአትሌቶች ሁሉ መሐል — በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ — ከድሉ መስመር — ገና 300 እና 400 ሜትሮች እየቀሩት — ተምዘግዝጎ ሲወጣ በታየበት — አስገራሚ ብቃቱ ነበር፡፡
በዚያ ውድድር — ምሩፅ በ5,000 እና በ10,000 ሜትሮች — ሁለት የወርቅ ኒሻኖችን በማፈስ — ድንቅ ተዓምርን ሠራ፡፡ ለራሱና ለሀገሩ ደግሞ — ድንቅ ስምን — ድንቅ ታሪክን፡፡ “የምንጊዜም የሞስኮ ኦሎምፒክ የአትሌቲክስ ጀግና” ተብሎም ቀረ፡፡
በነገራችን ላይ — በዚያን የሞስኮ ኦሎምፒክ ባሣየው ብቃቱ — ምሩፅ ይፍጠርን ‹‹ከሌላ ፕላኔት የመጣ አይበገሬ አትሌት›› ብሎ እስከመጠራት ባደረሰው — አስገራሚ ክስተት ብቻም አልነበረም — የምሩፅ ድል አነጋጋሪ የነበረው፡፡
ለብዙዎች አስገራሚ የሆነባቸው — የዕድሜው ነገር ጭምር ነበር፡፡ ሲያዩት አንጋፋ ጎልማሳ ሰው ይመስላል፡፡ ብቃቱ ግን የ19 ዓመት ኮበሌ ብቃት ሆነባቸው፡፡ እና ግራ ተጋቡ፡፡
እርሱም ታዲያ በድሉ ለተደመሙት የስፖርት ዘጋቢ ጋዜጠኞች ሲመልስላቸው — ብሔራዊ ቡድኑ ምሩፅ ተወልዶበታል ብሎ ካስመዘገበው የትውልድ ቀኑ — ማለትም ከግንቦት 7 ቀን 1936 ዓመተ ምህረት (እ.ኤ.አ.15 May 1944)— 6 ዓመታትን አክሎ — የትውልድ ቀኑን ወደ 1930 ዓመተ ምህረት (ማለትም በጎርጎሮሳውያኑ በ1938 ዓ.ም. – 1 January 1938) ነው የተወለድኩት ብሏቸው ነበር — እየተባለ ይነገራል፡፡ ምሩፅ እንዲህ የወጣለት ቀልደኛም ኖሯል!
እናም አንዳንዶች በዜናዎቻቸው “የ33 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ” ድርብ የኦሎምፒክ ድልን ስለመቀዳጀቱ ሲዘግቡ፤ ሌሎች ደግሞ “የ42 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ” እያሉ ነበር የሚዘግቡት፡፡ በዚህም የተነሣ እስካሁንም ድረስ ብዙዎች ስለ ምሩፅ የትውልድ ቀን ሲጠቅሱ — “አወዛጋቢ ነው”፣ “በእርግጠኝነት ባይታወቅም”፣ “ምናልባት”፣ እና የመሣሠሉትን ቃላት ማስቀደም ይቀናቸዋል፡፡
እርሱ ግን ስለዕድሜው ልዩነት ሲጠይቁት — እርሱ እቴ! የምን መቀባባት? — ዕቅጯን ነበር ንዴቱን በሚያንፀባርቁ ቃላት ያስቀመጠላቸው፡-
‹‹ሰዎች ዶሮዎቼን ሊሠርቁኝ ይችላሉ፣ ሰዎች በጎቼን ሊሠርቁኝ ይችላሉ፣ ያ ችግር የለውም፣ ዕድሜዬን ግን ማንም ሰው ሊሠርቀኝ አይችልም!›› በማለት!! (“Men may steal my chickens; men may steal my sheep. But no man can steal my age!”)፡፡
እና ደግሞ እንዲህ ነበር ያላቸው:—
“ከዕድሜዬ ይልቅ — ስለ አስደናቂው ሥራዬ — እና ለዚያ አሥደናቂ ድል ስላበቃኝ ኢትዮጵያዊ ፅኑ መሠረቴ ጠይቁኝ!” (“I told journalists who saw me to count my enthusiasm, not my age,” he laughs. “I told them you need an Ethiopian motivation to win races.”)፡፡
እናም — ልክ እንደ ቀዳሚው ኢትዮጵያዊ የማራቶን ጀግና — እንደ አይበገሬው ሻምበል አበበ ቢቂላ ሁሉ — ይሄ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጀግና — ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርም — “ኢትዮጵያዊነት – አይበገሬነት ነው!” — ሲል — ታላቁን የኢትዮጵያውያንን ጀግና ማንነት — በዓለም ሁሉ ፊት አንገቱን ቀና አድርጎ አብሥሯል!!!
ይህች አጭር ህይወት — ብዙዎቻችንን — ትዘግይም ትፍጠን —  ብዙ ዕድሎችን ከፊታችን ደቅና ትፈትነናለች፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ — ብዙዎቻችን — ብዙ ዕድሎች ተሰጥተውን — በብዙዎቹ ሳንጠቀምባቸው እናልፋለን፡፡ አንዳንዶች ደግሞ — ህይወት አንዲትን ወሣኝ ዕድል ብቻ ሰጥታቸው — በዚያች ዕድል ተጠቅመው — ታላቅን ነገር ሠርተው — የህይወታቸውን አቅጣጫ ይቀይራሉ፡፡ እና ‹‹ዕድል ፊቷን ያዞረችላቸው›› እየተባሉ ሲጠሩ ይኖራሉ፡፡
የማርሽ ቀያሪው — የምሩፅ ይፍጠርም ታሪክ — እንደዚያ ካሉት — አንዲት ዕድል ተሰጥታቸው — ያቺኑ ዕድል ወደ ወርቅነት ከቀየሩ ሰዎች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ አንዲት ዕድል ተሰጠችው — እና ያችን ዕድል ተጠቀመባት፡፡ እና — የራሱን ብቻ ሣይሆን — የሀገሩንም ታሪክ — ቀየረባት፡፡
በሀገሩ ፈጽሞ የማይደራደረው — የጀግናው ኢትዮጵያዊ ባለድል — የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ኢትዮጵያዊ ገድሎች ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ ድሎቹም ያነሣሣናቸው ብቻ አይደሉም፡፡
ምሩፅ ለሀገሩ ክብር ተሰልፎ በሮጠባቸው ዓለማቀፋዊ የውድድር መድረኮች ሁሉ — የአሸናፊነት ሜዳሊያዎችን በመቀዳጀት የሀገሩን የኢትዮጵያን ባንዲራ በየዓለሙ ማዕዘናት ሁሉ ከፍ አድርጎ ያውለበለበ — እውነተኛ የኢትዮጵያውያንን የጀግና ልብ የተላበሰ ጀግና ነው፡፡
በ1968 ዓ.ም. ላይ በካናዳ ሞንትሪያል ላይ ከአፓርታይድ የዘር መድልዎ ለመላቀቅ ለሚታገሉ አፍሪካውያን የነፃነት ታጋዮች ሲል ብዙዎች የተነበዩለትን ድል መስዋዕት ያደረገው ምሩፅ — ያን ባደረገ በ3 ዓመቱ — ወደዚያችው ካናዳ ተመልሶ — በ1979ኙ የኦታዋ ሻምፒየንሺፕ — የ3,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያን ተቀዳጅቶ — የሀገሩን ባንዲራ በድል አውለብልቦ የተመለሰ ጀግና ነው። ያውም — ባንድ ወቅት ለታላቅ ዓላማ የጣለውን ወርቅ — ከጣለበት ሥፍራ ተመልሶ የሚያነሣ — ልባም ኢትዮጵያዊ ጀግና። ነው። ምሩፅ። ይፍጠር።
በሞንትሪያል የተወውን ወርቅ በኦታዋ ማንሳቱን እንዳየን — እንዲሁ ደግሞ — ያኔ ለእስር ያበቃውን ውድድር በሚዩኒኩ የ1972 ኦሎምፒክ – የውድድሩ ሥፍራ ተደናግሮበት የተወውን ያን የሚቆጨውን የጀርመን ምድር ሜዳሊያ ደግሞ — እ.ኤ.አ. በ1977 ላይ — በጀርመኗ ሰሜን ራይንላንድ፣ በዱሰልዶርፍ በተካሄደው — የዓለማቀፉ አትሌቲክስ ሻምፒዮና (የአይ ኤ ኤ ኤፍ) ውድድር ላይ — ምሩፅ — የ10,000 ሜትሩንም፣ የ5,000 ሜትሩንም የወርቅ ሜዳሊያዎች ጠቅልሎ በመውሰድ — በድል ላይ ድልን እየያዘ — በወርቅ ላይ ወርቅን እየደረበ ወደ እናት ሀገሩ የሚመጣ — የሁልጊዜም አይረሴ የኢትዮጵያውያን ጀግና ነው!!
ይህ የአፓርታይድ የዘር ልዩነት ታጋይ ጀግና ኢትዮጵያዊ — ይህ የኢትዮጵያችንን ባንዲራ ከፍ ከፍ ሲያደርግ የኖረ የትውልድ ጀግና — ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር — ምናልባት በሀገሩ ላይ የሰፈነው የዘር ፖለቲካና የብሔር ሽንሸና አስጠልቶት ይሁን — ወይስ የጤንነቱ ሁኔታ በልጦበት — ምን እንደሆነ ባይታወቅም — ከዚህች ከሚወዳት ሀገሩ በሺህዎች ኪሎሜትሮች ርቆ — በለጋነቱ ድል አድርጎ የወርቅ ሜዳሊያን ባጠለቀባት፣ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት ብሎ ኦሎምፒክን “boycott” ባደረገባት — በሀገረ ካናዳ — ለበርካታ ዓመታት በስደት ቆይቶ —  በዚያችው የስደት ሀገሩ — ዳግመኛ በድል ወዳገሩ ላይመለስ — እስከ ወዲያኛው አሸልቧል፡፡
ጀግናውን አትሌት በእርጅናው ዘመን ስላደረበት ህመም ቤተሰቦቹ ሲናገሩ — የመተንፈሻ አካላት ችግር ነበር ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ይህን ስትመለከት የዕድሜ፣ የእርጅና፣ ባጠቃላይ የህይወት ነገር ግርም ነው የሚልህ፡፡ ያ በጉብዝናው ወራት በትንፋሹ ዓለምን ያስከነዳ ጀግና — በፍጻሜው ከትንፋሽ ጋር ግብግብ ገጥሞ — ትንፋሽ እያጠረው — ወደዚያች ማንም ወደማይቀርባት ዓለም መሰናበቱ የሆነ የሚናገረው እንቆቅልሽ የህይወት አያዎ አለው።
ምሩፅ ይፍጠር — ፀጥታና ሠላሙን፣ ድሉንና ታላቅ ስሙን፣ ጀግንነቱንና ኢትዮጵያዊ አይበገሬ ልቡን ይዞ — የሚወዳትንና የተዋደቀላትን ሀገሩን፣ በወርቅ ያሸበረቀ በዘርና በጎሳ፣ በጎጥና በምጥማጥ ያልተከፋፈለ አኩሪ ታሪክን ያወረሰውን ኢትዮጵያዊ ትውልድ ሁሉ — ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተሰናበተ፡፡
የህይወት ታሪኩ ማገባደጃ ላይ በውጭ ቋንቋ እንዲህ የሚል ፅሑፍ ሳገኝ ከርታታውን ኢትዮጵያዊ ጀግና ምሩፅ ይፍጠርን እያሰብኩ ልቤ ተሸበረ፡—
‹‹ማርሽ ቀያሪው እየተባለ የሚጠራው
ኢትዮጵያዊው የአትሌቲክስ ስመ-ገናና
ባለድል ሯጩ ምሩፅ ይፍጠር በግንቦት
7 ቀን 1936 ዓመተ ምህረት በአዲግራት፣
ኢትዮጵያ ተወለደ፤ በህዳር 13 ቀን 2009
ዓመተ ምህረት በቶሮንቶ፣ ኦንታሪዮ፣
ካናዳ ህይወቱ አለፈች፡፡››
ለዚህ ታሪኩና ለማይሞት ኢትዮጵያዊነቱ — የሀገሩን ባንዲራ በዓለም ሁሉ እየዞረ በኦሎምፒክ አደባባይ ሲያውለበልብ ለኖረው — ለዚህ የፀረ-አፓርታይድ ቆራጥ ታጋይ — ለዓለማቀፋዊው ኢትዮጵያዊ አይበገሬ አትሌት — ለ”Yifter the Shifter” — ለማርሽ ቀያሪው ኢትዮጵያዊ ጀግና — ለሻምበል ምሩፅ ይፍጠር — በትውልድ ሁሉ ሲወሳ ለሚኖረው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ድንቅ ሥራው እና አሻራው — እጅግ የከበረ ጥልቅ ክብር እና ፍቅር ነፍሱ ባረፈበት ሠማያዊ አፀድ ይድረሰው።
ለአካለ ሥጋ ወ ነፍሱ — ባረፈበት ሥፍራ — ዘለዓለማዊ ዕረፍት ይሆንለት ዘንድ እየተመኘሁ ተለየሁ፡፡
የጀግኖች እናት — እምዩ ኢትዮጵያ — ለዘለዓለም — በክብር — ትኑር!
Filed in: Amharic