‹‹እጠብቅሻለሁ ፍቅሬ…!!!››
ሠሎሞን ለማ ገመቹ
*…. ‹‹ይታየኛል! በደንብ ነው የሚተየኝ!… ቁልጭና ወለል ብሎ!… ግን… ግን… ‹መርከበኛንና ወደ ጦር ሜዳ የሄደን ወታደር ፍቅረኛን እስኪመለስ መጠበቁ የራስ ጸጉርን የመቁጠር ያህል ነው፡፡ …› ሲሉ የሰማሁ መሰለኝ፡፡
ክረምት ቢሆንም ከማለዳው ጀምሮ ቀኑ በከፊል ፀሐያማ ነው፡፡ በዋዜማው አንድ መልዕክት ደርሶታል፡፡ እጅግ በጣም ተደስቷል፡፡ ምንግዜም ‹‹ያሰብኩት እየተሳካልኝ ነው…›› የሚለውና ከብርሃናማ ተስፋው የሚመነጭ ሐሣቡ ሲኮረኩረው… እንደሚያደርገው፤ ከናፍሩን በባለቤቱ ግንባር ላይ አሳረፈ፡፡ አንዴ፣ ሁለቴ፣ ሦስቴ፡፡ ቀጥሎም ከአጠገቧ ተቀመጠ፡፡ እጅግ የሚወድላትና የሚሳሳላት ዓይኖቿን ‹‹ምን አገኘህ? ዛሬ ደሞ የትኛው ጉዳይ ተሳካልህ?…›› በሚል ጥያቄ በዐይኖቹ ላይ አሳረፈቻቸው፡፡
ይኸው ነው!… መሠረቱ ልባዊ ፍቅር የሆነውን አብሮነት የሚያጎለብተው በዓይነ የመጠያየቅን፣ የመነጋገርን፣ ተጠያይቆና ተነጋግሮ መልስ የመሰጣጣትን ክህሎት ነው፡፡ ‹‹ምን መሰለሽ ውዴ!… ባለፈው የጀመርኩት ሥራዬን የሚመለከት ጉዳይ ተሳካ፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ ወደ ዱባይ እበራለሁ፡፡ እህቴንና የልብ ጓደኛሽን ኮከቤን አገኛትና በዚያው የግል መርከቦችን ወደሚየሰማራውና ሠራተኞቹን ወደሚያስተዳድረው ቢሮ እሄዳለሁ፡፡ ከዚያ አንዷን መርከብ ይዤ በሕንድ፣ በሰለማዊ… ወቅያኖስ ላይ እቀዝፋለሁ፡፡
እ… ይታይሻል አይደል እኔ ካፒቴን የሆንኳት መርከብ በባሕሩና በውቅያኖሱ ላይ ስትንሳፈፍ? ከአንደኛው ወደብ ተነስታ ሌላኛው ወደብ ዳርቻ ስትደርስ… ጭነቷን ስትጭን፣ ጓዟን ስታራግፍ… ረዳት የነበረው የወዱ ካፒቴን ባለቤትሽ ደሞዝ ዳጎስና ሞቅ ያለ ሲሆን፣ ሌሎች ያሰብናቸው ነገሮች ሁሉ በሂደት መልክ፣ መልክ ሲይዙ፡፡ አንቺ ፍቅሬና ክብርት እናቴ፣ ውዷ እህቴ ኮከብ ፊታችሁ አንደ ዕንቁ ሲፍለቀለቅ፣ ዕልልታችሁን ስታቀልጡት!… ኦ አምላኬ!… አይታይሽም?››
♦ በስስት ማተረችው፡፡ ‹‹ይታየኛል! በደንብ ነው የሚተየኝ!… ቁልጭና ወለል ብሎ!… ግን… ግን… ‹መርከበኛንና ወደ ጦር ሜዳ የሄደን ወታደር ፍቅረኛን እስኪመለስ መጠበቁ የራስ ጸጉርን የመቁጠር ያህል ነው፡፡ …› ሲሉ የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ደሞ በዚህ ላይ አንዳንዴ ያ ብቸኛው ድምፅ ዕንኳ ጥፍት ይላል፡፡ አካልህንማ ተወው!… እንጂማ! ያልካቸው ነገሮች በደንብ ነው የሚታየኝ የእኔ ኩራት! የእኔ ደግ! የእኔ አሳቢ!… እ… ናፍቆትህና ሐሣቡ አንደሚያከሳኝና አንደሚያደክመኝ ባውቅም የሥራ ዕድሉን በማግኘትህ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ ግን ከሁሉም በላይ ፈጣሪ ጤናህን ይጠብቅልኝ፡፡ መቼም ቢሆን!… በሄድክበት ሁሉ! ክፉ አይንካብኝ… እ? የደስታችን ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ግን… እስቲ ሳትደብቅ ንገረኝና ምንም አያምህም? ጤናህ አሪፍ ነው? ይሄ ‹እሷን ይከፋታል፣ ትጨነቃለች…› እያልክ ዝም የምትለውን ነገር የማላውቅ እንዳይመስልህ እሺ?…››
♦ በመሀል የስልክ ጥሪ መጣ፡፡ ‹‹የማን ነው?›› ጠየቃት፡፡ በተለመደው ሁኔታ ጥያቄው የቁጣ ዓይነት ንዝረት አለው፡፡ ከእሷ ጋር በሚጨዋወቱበት ጊዜ ጣልቃ ሊገባ የሚችለውን ነገር አይታገስም፡፡ ‹‹ውይ ውዴ… እህት ዕኮ ነች፤ ደስ አይልም?›› አለችው፡፡ ወዲያው ለስለስ አለ፡፡ ‹‹የሆነች ወፍ ዕኮ ነች! በይ እሷማ ከሆነች አናግሪያትና ስልኩን አቀብይኝ…›› አለና የፍቅር ጨረሩን በዓይኖቿ ላይ ረጨባት፡፡ ከእህቱና ከልብ ጓደኛዋ ጋር ሁለት ደቂቃ ያህል አወራችና ስልኩን አቀበለችው፡፡
♦ ከእህቱ ጋር ጭውውቱን ጀመረ፡፡ ደቂቃዎች ብዙ ደቂቃዎችን ተኩ፡፡ በገጹ ላይ የደስታ ፀዳል ይመላለሳል፡፡ ሳቁ ከሳሎንና ከቤት ወደ ውጭ ከሚያስወጣው የኮሪደሩ ጠርዝ አልፎ… ባለቤቱ ካለችበት የመኝታ ክፍላቸው ድረስ ይሰማል፡፡ እሷ በዋዜማው በነገረችው መሠረት ሳይረፋፍድ ወደ እናቷ ለመሄድ እየተዘገጃጀች ነው፡፡ በሳቁና ለአፍታ በሚሰፍነው ዝምታ መሀል ‹‹እሺ! እሺ!… አንዳልሽኝ አደርጋለሁ ትንሿ!… ኧረ ደህና ነኝ በጣም!…. አንቺ ደግሞ አንዳንዴ እመኚኝ… እሺ ያልሽኝን ሁሉ እያደረኩ ነው፡፡ ለወደፊቱም አደርጋለሁ፡፡… እንደውም!… በፍፁም አልደብቃትም…›› የሚሉትን ቃሎች እያደመጠች ነበር፡፡ በመጨረሻ የመልካም ምኞትና የስንብት ድምፆች ተሰሙና ስልኩ ተዘጋ፡፡
♦ ከባለቤቱ ጋር ኮሪደሩ ላይ ተገናኙ፡፡ ‹‹ምነው ክርክር አበዛችሁ? በደህና ነው?›› ጠየቀችው፡፡ ‹‹ያው የምታውቂው ነው የእኔ ፍቅር!… ጓደኛሽና ትንሽቱ እህቴ ምንግዜም የሕይወቴና የኑሮዬ ዋና ተቆጣጣሪ ልሁን ባይ ነች፡፡ አንድ ቀን ዕንኳ ታላቋ አልመስላትም፡፡ ኧረ የእሷስ የእህትነት ፍቅር አይጣል ነው፡፡ ብትመክረኝ! ብትዘክረኝ!… አይሰለቻትም፡፡ እኔም ይህንኑ ለምጄው ጭራሽ የማይሰለቸኝ ሆኗል… ይቅርታ አድርጊልኝና አሁንም እንደ ልጅነቷ፣ እንደ ልጅነቴ… አዝያት የምዞር ዕኮ ነው የሚመስለኝ፡፡ አካሏን ባይሆን ልዩ ሆኖ የሚሰማኝን እናትነቷን፡፡ ያው እንደምታውቂው ከምንሰፈሰፍላት እናቴ አንድም የሚለይ ባሕሪይ የላትም…›› በማለት መለሰላት፡፡
♦ በስስት፣ በጥርጣሬ… ግን በፍቅርና ግልጽ ባልሆነ የደስታ ስሜት አየችው፡፡ ፈገግ አለ፡፡ ፈገግ አለች፡፡ ሊያሳስቃት ሞከረ፡፡ የግዴታ ሳቅ ለመሳቅ ተጣጣረች፡፡ አውቆባታል፡፡ ‹‹በይ እናትሽ ጋር በጊዜ ሂጂ! ሰላምታዬን አድርሽልኝ፡፡ ከረፈደ መኪና አታገኚም… መልካም መንገድ ይሁንልሽ! እንዳይመሽብሽ ደግሞ ከእናትሽ ቤት ቶሎ ተነሺ… እጠብቅሻለሁ ፍቅሬ›› አለና ሸኛት፡፡ በጥድፊያ ቤቱን ለቃ ወጣች፡፡
♦ ሎሬት ጸጋዬም አለ በ‹‹ደህና ዋይ እማማ›› ስንኙ አንድ አንጓ፡፡ ሕይወት ከስም ባሻገር ዝንተ-ዓለም ሕያው፣ ምንጊዜም ደስታ፣ ዘወትር መፍለቅለቅ፣ ቀን ከሌት ስኬት አይደለምና፡፡ ደግሞም ባልተጠበቀ ቀን፣ ባልታሰበ ሰዓት ደቂቃ… የመንፈስ መጎስቆል፣ የነፍስ መዋከብ፣ የህሊና ትካዜ፣ የሕይወት ተቃርኖ ይሆናል፡፡ ነፋሱ በኃይለኛው ሲነፍስ፣ ነጎድጓዱ ለአጀብ ሲነጉድ፣ ውሽንፍሩ ሲበረታ፣ መብረቁ ሲበርቅ፣ ጉም ዐመዳዩ አይሎ የቀኒቱን ብርሃን ሲጋርድ፣ ጨለማም በጀምበር ምትክ በማለዳውና በረፋዱ… ሲነግስ፤ ያኔ ወር ተራውን ለማያውቀው ቋሚ… ብርቱ ኃዘን ሰቀቀን ይሆናል፡፡ ዕምዬ እናት ዓለምን ሂያጅ በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ‹‹ደህና ዋይ እማማ›› የስንኙ አንጓ ሕብረ-ቃል ዜማ፤ በመንፈሱ፡-
♦ ‹‹አንጀቴ ያንጀትሽ ቁራጭ፣
አጥንቴ ያጥንትሽ ፍላጭ
ሕይወትሽ የሕይወቴ ምንጭ፣
ወዜ የፍቅርሽ ወዝ ምጣጭ
ማኅፀንሽ የፍጥረቴ አማጭ…
ከእንግዲህ በቃሁሽ፣ በቃኝ!
ዕማማ የነፍሴ ቁራጭ›› እያለ ይሰናበታል፡፡
♦ ባትኖርም ዕንኳ ካጠገቡ ግን ደግሞ ድምፁን ባትሰማው፤ ከእሱ ርቃ ያለች ሆና ሊለያት ሲል አንደኛውን ዐይን ዓይኑን እያስተዋለች ‹‹በል ደህና ሁን…›› የማለቱን ቅንጣት ዕድል ባታገኝም፤ የተሰናባች እስትንፋስ ቃል እሱ ለራሱ የሚነግረው፣ እናቴ ትስማኝ የሚለው፣ የሚሰስትላትን ፍቅሩን በነፍስያው እያሰበ ‹‹እንዲህ ነበር የምላት፣ አንደዚህ ነበር የምነግራት…›› እያለ፤ ከሕያውነት ወደ ሕይወት አልባነት ዓለም ሊጓዝ ሲል ለራሱ መልሶ ሹክ የሚለው፤ ያንኑ የጸጋዬን ቃል ትርጉም፣ ያንኑ የነፍስ ሐቁን ነው፡፡
♦ ደግሞም ለትዳር አጋሩም ቢሆን ከሚወዳት በላይ ለምትወደው፣ ከምታፈቅረው በሚከብድ ሸክም የፍቅሯን ሸክም ተሸክሞ ቀን ከሌት በአካል በመንፈስ ሲባዝንላት… ለኖረው፤ የሚተነፍሰው የፍቅሩ ትንፋሽ፣ የ‹‹ደህና ሁኚልኝ…›› ቃሉ! ምናልባትም ከፍሌ አቦቸር ‹‹ስትሞች እንዳትጎጂኝ›› በሚለው ስንኙ እንዳንሰላሰለው፡-
♦ ‹‹አንድ ቀን ክፊብኝ…
ይጥቆርብኝ ፊትሽ…
‹ቂም› ይዤ ልታመም
የወደድኩት ልብሽ፣ በልቤ ላይ ይድከም፡፡
ጉዳቴን ለመርሳት…
በርትቼ ለመጽናት፣ ቆሜ ለማገገም
ብርታት የሚሰጠኝ…
ሕይወት የሚዘራ፣ የለኝምና ደም
ስትሞች እንዳትጎጂኝ፣ ቀድሜሽ ልጋደም!!›› የሚለው ይሆናል፡፡ አንዳንዴ አንዳንድ ጊዜ፣ አንዳንዴ ደግሞ በአብዛኛው… ‹‹ከአንቺ በፊት ያድርገኝ!›› የሚለው ቃል-ኪዳን ተግባራዊ ክንውን መሠረት ነውና የአፍቃሪው ስንብት የፍፃሜ ውሉ፡፡
በጥድፊያ ከቤት እንደወጣች፣ እናቷን… ተሰናብታ ወደ ፍቅሯ የመለስ ጉዞ ጀመረች፡፡ በቀጣዩ ቀን ወይም በማግስቱ እሱ መንገደኛ ነው፡፡ ወደ ዱባይ በራሪ ነው፡፡ ወደዚያ ከመብረሩ፣ የመርከብ ካፒቴንነቱን ሥራ ከመጀመሩና ተመልሶ መጥቶ በአካል እስኪያገኛት ድረስ ከእሱ ጋር የሚኖራት ብቸኛና አስተማማኝ የደስታ ጊዜ የዛሬው ዕለት ምሽት ብቻ ነው፡፡
♦ ከመኪና መኪና ተጋብታ፣ በእግር የሚኳተነውን ኳትና ከቤታቸው ደረሰች፡፡ መዝጊያውን ከፈተች፡፡ በመተላለፊያው ተረማምዳ ወደ ሳሎኑ ተሻገረች፡፡ ከሶፋው ሥር ፍቅረኛዋ ተጋድሟል፡፡ ‹‹ተነስ እንጂ ማንን ለማስደንገጥ ነው? እንዲህ ዓይነት ቀልድ አይመቸኝም!…›› አለች፡፡ መልስ አልነበረም፡፡
♦ ጨለማ በነበረው ክፍል ውስጥ የአምፑሉን ማብሪያ ማጥፊያ ፈልጋ ተጫነችው፡፡ ብርሃን ሆነ፡፡ በብርሃኑ ውስጥ ግን መንፈስን የሚያደነዝዝ፣ ልብን የሚሰነጥቅ… አቅልን የሚያስት… ድቅድቅ የመላዕከ-ሞት መንፈስ ቆሟል፡፡ በርከክ ብላ የተጋደመውንና ‹‹እጠብቅሻለሁ ፍቅሬ›› ያላትን ብቸኛ ወዳጇን፣ የኑሮዋን አልኝታ…. እስትንፋስ ለማወቅ ሞከረች፡፡ በሕይወት አልነበረም፡፡ እየጠበቃት አልነበረም፡፡ ዕሪታዋን አቀለጠችው፡፡ ጎረቤት ተሰባሰበ፡፡ መለያየት የማይሞቱት ሞት ነው… ዛሬን! አሁንን! በፍቅር ለመኖር እንጂ ነገን፣ በኋላን በተስፋ ለመገናኘት ምንም ዓይነት ዋስትና የለም፡፡ ሞት የሕይወት ጥላ ነውና ዛሬን በፍቅር ከማሳለፍ በቀር የመኖር ዋስትና፣ የነገ ሕያውነት ተስፋ ምንድን ነው? ምንም!
ይህ ፅሑፍ መታሰቢያነቱ
ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም
በድንገት ለተለየኝ….
ለወንድሜ ቢሆነኝ ግርማ ነው