>
5:31 pm - Sunday November 13, 4061

የሶማሊያ የርስበርስ ጦርነት በአለም አቀፍ ጸጥታና በሰው ልጅ ላይ ያስከተለው ታሪካዊ ዳፋ  ( ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የሶማሊያ የርስበርስ ጦርነት በአለም አቀፍ ጸጥታና በሰው ልጅ ላይ ያስከተለው ታሪካዊ ዳፋ 

ክፍል ሁለት

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)


እንደ መግቢያ

በባለፈው ክፍል አንድ ጽሁፌ ላይ ሶማሊያ እንዴት ወደ ለየለት የርስበርስ ጦርነት ውስጥ ልትዶል እንደቻለች፣ በርስበርስ ጦርነቱ ምክንያት ስለደረሰው አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ በተመለከተ፣ አንዴ የርስበርስ ጦርነት ከተለኮሰ በኋላ እና የተለያየ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ሀገር ሀይሎች በአንድ ሀገር የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እጃቸውን ካስገቡ ሶማሊያን እንደ ተጨባጭ ምሳሌ በማንሳት ሰላም ለማስፈን እጅጉን አስቸጋሪ መሆኑን በማውሳት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ትምህርት እንዲወስዱ የበኩሌን ታሪካዊ እና የዜግነት ሀላፊነቴን ለመወጣት ሞክሬአለሁ፡፡ አልሰማንም አላያንም ካለልን በቀር በሶማሊያ ተከስቶ የነበረው የጎሳ አይነት ግጭት በኢትዮጵያ ምድር ባይከሰትም፣ በሌላ መልኩ ፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ ተመስርቶ የርስበርስ ጦርነት ለብዙ ግዜያት ተከስቷል፡፡ ወደለየለት የርስበርስ ጦርነት እስክንገባ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም  በሶማሊያ በነቢብም፣በገቢርም እንደታየው የውጭ ሀይሎች ሰላም በማስከበር ስም በኢትዮጵያ ምድር እንዲገቡ መፍቀድ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አደጋ መደቀን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ደግሞ በምኞት የሚገኝ አይደለም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በፍጥነት ወደ አንድነት፣ ወደ ሰለጠነ ውይይት፣ንግግር መስመር መግባት አለብን የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ልብ ያለው ልብ ይበል የሚለው ደግሞ ሌላው መልእክቴ ነው፡፡

እስልምና ጽንፈኝነት በርስበርስ ጦርነቱ ውስጥ (የእስልምና ፍርድ ቤት እና አልሸባብ)

በአፍሪካው ቀንድ የፖለቲከ ተንታኞች የጥናት ወረቀት መሰረት የእስልምና ጽንፈኝነት አስተምህሮ የበለጠ ጠቃሚና ተቀባይነት እያገኘ የመጣው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ1980ዎቹ ጀምሮ ነበር፡፡ የጽንፈኛ እስልምና ሃያማኖት ሰባኪዎች በስንቅና ትጥቅ እንዲሁም በዶላር የሚደገፉት፣በጽንፈኛና አክራሪ የሃይማኖት አስተምህሮ ይሰበኩ  የነበረው በሰኡዲአረቢያ፣ ኢራንና ሱዳን መንግስታት እንዲሁም በመድራሳዎቻቸው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍሪካው ቀንድ በተለይም በሶማሊያ ምድር እንደፈለገው በመፈንጨት የሚታወቀው፣ የመጀመሪያው ጽንፈኛ የእስልምና ሃይማኖት ድርጅት ሰባኪ የነበረው አል-ኢትሃድ አል-ኢስላሚ (“al-Ittihad al-Islami”, ) በመባል ይጠራል ( ይህ ድርጅት በአለም አቀፍ አሸባሪ ድርጅትነት በተሰየመው አል-ቃኢዳ  በገንዘብ ድጋፍ ይደረግለት  ነበር፡፡) (financed by terrorism organisation Al-Qaeda ) ሆኖም ግን ይሁንና እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1988 ጀምሮ ይህ ጽንፈኛ ድርጅት ጦርነት መግጠም ወይም ማሸነፍ አልሆነለትም ነበር፡፡ ምክንያቱም  በሶማሊያ ምድር በጎሳ ድርጅት የታቀፉት ሀይለኞች እና ተዋጊዎች ስለነበሩ ነው፡፡ ብዙ ግዜ በጎሳ አምበል ጭፍራዎች በጦር ሜዳ ላይ ተሸንፎ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ ( በመጨረሻም) እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1996 አል-ኢትሃድ አል-ኢስላሚ (al-Ittihad al- Islam ) በኢትዮጵያ ወታደሮች ለመሸነፍ በቅቷል፡፡ 

የኢስላሚክ ህብረት ፍርድ ቤት ማን ነው (“Union of Islamic Courts”  ) ?

በመጀመሪያ ደረጃ የኢስላሚክ ፍርድ ቤት የሚባለው የተለያዩ የሸሪያ ፍርድ ቤቶች ጥምር ሲሆን ፣ከሀዊዬ ጎሳ“ (in Hawiye- clan- bosses) የተወጣጡ ሰዎች ያሉበት ፣ለዘብተኛ የእስልምና አስተምህሮ የሚከተሉ ሰዎች ስብስብ  እና አንዳንድ የቀድሞው አል-ኢትሃድ አል-ኢስላሚ አባላት ስብስብ ነበር፡፡ አንዳንድ ጽንፈኛ የሆኑ ለአብነት ያህል ከአለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን አልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው የወጣቶች ድርጅት አልሻባብ ቡድን አባላት በውስጡ ተሰግስገው ነበር፡፡ የኢስላሚክ ህብረት ፍርድ ቤት በአፍሪካ የአልቃይዳ ተወካይ የሚል ስያሚ ተሰጥቶት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2006 የሞቃዲሾን ስልጣን የተቆጣጠረው የእስልምና ህብረት ፍርድ ቤት ተዋጊ ሀይል ከጦር አበጋዞች እና ከሶማሊያ የሸግግር መንግስት ጋር ውጊያ ከፍቶ የነበረ ሲሆን፣  በተባበረችው አሜሪካ ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ የሸግግር መንግስት ላይ ሰሳይቀር ጂሃድ ( partially declaring the Djihad ) አውጆ እንደነበር ይታወሳል፡፡

እንደ አንዳንድ የሶማሊያ የፖለቲካ ተንታኞች ጥናትና ድምዳሜ ከሆነ በኢስላሚክ ህብረት ፍርድ ቤቶች ስር የነበረችው ሞቃዲሾ ፣ በሶማሊያ የሽግግር መንግስት ስር ካለችው ሶማሊያ የበለጠ ጸጥታዋ የተጠበቀ ነበር፡፡( በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች እና ከእነርሱ ፍልስፍና ውጭ የሚያራምዱ ግለሰቦች ላይ የሚወስኑትን አሰቃቂ  ፍርዳቸውን  ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡) ይህም ብቻ አይደለም ከሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጋር በከተማ ውስጥ በሚያደርጉት ጦርነት አጥፍቶ መጥፋት በሚለው ዘዴያቸው በርካታ የመንግስት ተቋማትን አጥቅተዋል፡፡ በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች አለም አቀፉ ህብረተሰብ ያረጋገጠው ነገር ቢኖር የኢስላሚክ ህብረት ፍርድ ቤቶች ሀገር መምራት ወይም መገንባት እንዳማይሆንለት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ  የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ይህ ጽንፈኛ ድርጅት በሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጦር እና በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የጦር ወንጀል ፈጽሞ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር የኢስላሚክ ህብረት ፍርድ ቤቶች በሞቃዲሾ ከተማ ውስጥ የሚከተሉትን ስር ነቀል ትእዛዞች እንዲፈጸሙ አዞ ነበር፡፡ እነኚህም፡-

  • ሲኒማ ቤቶች ፣ክለቦች፣ዘመናዊ የሙዚቃ ቤቶች ሁሉ እንዲዘጉ ትእዛዙን አስተላፎ ነበር፡፡
  • በፊፋ አመሃኝነት የሚተላለፉ አለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታዎች እንዳይተላለፉ አግዷል
  • በቀን 5 ግዜያት ያህል የማይሰግዱ ወይም የማይጸልዩ ሰዎች የሞት ፍርድ ምሳቸው ነበር
  • የተባበሩት ኢስላሚክ አቅድ የነበረው በሸሪያ ህግ የምትተዳደር ኢስላማዊ ግዛት ለመመሰረት ያለመ ነው፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2006 ላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ባደረሱበት ከባድ ምት ለግዜውም ቢሆን ከሶማሊያ የፖለቲካ መድረክ ገሸሽ ለማለት ተገዷል፡፡

አል-ሸባብ ( the Al-Shabaab.)

ጠንካራውና በጣም አደገኛው የሽብር ቡድን ወይም ድርጅት አል-ሸባብ ( the Al-Shabaab ) በመባል ይታወቃል፡፡ እንደ አካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች ጥናት ውጤት ከሆነ ይህ ድርጅት የተጸነሰው ከኢስላሚክ ህብረት ፍርድ ቤቶች የወጣቶች ወታደራዊ ክንፍ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ‹‹ ቀስበቀስ እንቁላል በግሯ ትሄዳለች ›› እንዲሉ ራሱን አጠናክሮ የራሱ አላማ ያለው አደገኛ ጽንፈኛ ቡድን ለመሆን በቅቷል፡፡ የአልሸባብ ዋነኛ አላማ  በሶማሊያ ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት እንደሆነ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡

በዛሬው ዘመን አል-ሸባብ  በአፍሪካ ከሚገኙት አሸባሪ ድርጅቶች ዋነኛውና አደገኛው የአሸባሪ ቡድን ነው፡፡ ድርጅቱ አላማውን ገቢራ ለማድረግ ይረዳው ዘንድ የመሳሪያ ሀይል መጠቀምና ወንጀል መፈጸም እለታዊ ግብሩ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል፡፡

እንደ የሚሊተሪ ሳይንስ ባለሙያዎች ጥናት ውጤት ከሆነ አልሻበብ ከወታደራዊው ክንድ ጥንካሬው ባሻግር ይህ ለሚመለምላቸው ተዋጊዎቹ በሚሰጠው ከፍተኛ እና ጥራቱን የጠበቀ የወታደራዊ ስልጠና፣ በሚታጠቃቸው የዘመኑ መሳሪያዎችም ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ ከርእዮት አለም ትጥቅ ጋር የተጣመረ ነው፡፡ እንደ አካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች የጥናት ወረቀት ከሆነ የዚህ ጽነፈኛ ቡድን አባላት ከጎሳ ማንነታቸው ይልቅ ለሃያማኖት ማንነታቸው ያደላሉ፡፡ እነርሱ ለጂሃድ ጦርነት የተዘጋጁና ህይወታቸውን ለመስጠት የወሰኑ ተዋጊዎች ናቸው፡፡

በነገራችን ላይ የአልሻባብ ተዋጊዎች በደቡብ ሶማሊያ የሚገኙ በርካታ አካበቢዎችን እንደተቆጣጠረ ይገኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ቡድኑ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሸሪያን ህግ ገቢራዊ ማድረጋቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የምእራባውያን ፍልስፍናም ተቀባይነት የለውም፡፡ የሶማሊያ ሴቶች መድልኦ ይደረግባቸዋል፡፡ ቀን በቀን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የሞት ፍርድ ይሰጣል፡፡ ሴቶች ሱሪ መታጠቅ አይፈቀድላቸውም፡፡ ወንዶች ደግሞ ጺማቸውን ማሳደግ ግዴታቸው ነው፡፡

አልሸባብ የሰብኣዊ መብቶችን ብቻ አይደለም የሚገፈው፡፡ አልሸባብ የሶማሊያን ቅርስና ታሪክንም እያጠፋ ነው የሚገኘው፡፡ የጥንታዊት ሶማሊያን ታሪክ የሚያወሱ ሙዚዬሞች፣ጥንታዊ የዋሻ ውስጥ ስእሎች፣የስነጥበብ ውጤቶች ወዘተ በዚህ ጽንፈኛ ቡድን አባላት ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ባሻግር አልሻባብ በሚቆጣጠራቸው ግዛቶች የሰብዓዊ እርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ዝር እንዳይሉ ይከላከላል፡፡ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭቶችንም ይገታል ወይም ያስተጓጉላል፡፡

አል-ሸባብ ማህበራዊ ችግርም ነው፡፡ በሞቃዲሾ እና በሌሎች ትልልቅ ከተሞች ለሚኖሩ ወጣቶች ከፍተኛ ደሞዝ በመክፈል አባል ካደረጋቸው በኋላ ለራሱ አላማ መጠቀሚያ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደ አለም አቀፍ ድርጅቶች ትናት ከሆነ 90 ፐርሰንቱ የሶማሊ ህዝብ በአስከፍ ድህነት ውስጥ የሚማቅቅ ነው፡፡ ስለሆነም አልሸባብ የሚያቀርበው አጓጊ ክፍያ ብዙ ወጣቶችን የሚስብ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የአልሸባብ ተዋጊዎች ድህነት ቤቱን ከሰራባቸው ሀገራት የሚመጡ ወጣቶችን የሚያካትት እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

እንደ መደምደሚያ እና የግል ምልከታ

እንደ መደምደሚያ በርካታ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ የሶማሊያ አጠቃላይ ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ማቆጥቆጥ የጀመረው በፕሬዜዴንት መሃመድ ሲያድባሬ ( Mohammed Siad Barre ) አገዛዝ ዘመን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሲያድባሬ መንግስት ጠንካራ ነበር፡፡ ይህም ብቻ አይደለም መንግስታቸውም በርካታ ለውጦችን አስገኝቶ ነበር፡፡ ከቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ባገኘው መጠነ ሰፊ እርዳታ ትምህርትን በሶማሊያ ምድር በማስፋፋት ወይም በእውቀት አመሃኝነት የማህበረሰብ ለውጥ አምጥቶ ነበር፡፡ ከተባበረችው አሜሪካ በተገባላቸው ቃል መሰረት ደግሞ የጎሳ ስርአትን ለማጥፋት በብዙ ባጅቶ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ መሀመድ የሶሻሊስት ርእዮት አለም አቀንቃኝ እንዲሁም፣ ይመሯት በነበረችው ሶማሊያ ሰማየ ሰማያት ላይ የሶሻሊስት ፍልስና እንዲናኝ በብርቱ የሚተጉ እንጂ  የጎሳ ስርአትን የሚያራምዱ እና የሚመሩ  መሪ አልነበሩም፡፡ 

ሆኖም ግን ይሁንና የሶማሊያ ህዝብ እጅጉን ባህላዊ ከመሆኑ ባሻግር ለጎሳ መሪዎች እና ለጦር አበጋዞች የሚደማ ልብ ነበረው ወይም የነበረው ሲሆን ለመሃድ ሲያድባሬ አገዛዝ ግን ድጋፍ ነፍጎት ነበር፡፡ ( በነገራችን ላይ የዚያድባሬ አገዛዝ በርካታ ህይወት ቀጥፏል፣አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያን ግዛት የሆነውን ኦጋዴንን በእብሪት ከወረረ በኋላ በኢትዮጵያ የጦር ሃይል የሀፍረት ሸማ ተከናንቦ እንዲመለስ በመደረጉ የዚያድ አገዛዝ በሶማሊያ ህዝብ ዘንድ ድጋፉን አጥቶ ነበር፡፡) 

በመጨረሻም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 የዚያድ ባሬ አገዛዝ እንደወደቀ፣ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1995 በምእራቡ የአፍሪካ ክፍል በምትገኘው ናይጄሪያ በስደት ላይ እንዳሉ የሶማሊያ መሪ የነበሩት ፕሬዜዴንት መሀመድ ዚያድባሬ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከመሃመድ ውድቀት በኋላ ሶማሊያ ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት ማንበር የተሳናት ሲሆን፣ በሀገሪቱ ደግሞ የርስበርስ ጦርነት ተጀምሮ  አሁን ድረስ ማጠፊያ አልተገኘለትም፡፡ ውድ ወገኖቼ አንዲት ሀገር ዲሞክራቲክ ስርአት ማንበር ከተሳናት፣በአምባገነን ስርአት ለብዙ አመታት ከቆየች፣ ከጎሳ ፖለቲካ መገላገል ከተሳናት መጨረሻዋ እንደማያምር ሶማሊያ ማሳያ ናት፡፡ ምድሪቱ ላይ የሸፍጥና ሴራ አቀንቃኞች በናኙበት ሁኔታ፣ ሀይለስላሴ ደስታ እንዳሉት ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ እንዳሉት በሰላም ስም ሀገር አፍራሾችን መታገስ ኋላ ላይ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ኢትዮጵያን የሚያሳጣ ገደል አፋፍ ላይ መሆናችንን በፍጥነት ተረድተን ከጎሳ ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ መገላገል አለብን፡፡ ከድንክዬ ፖለቲከኞች እርቀን ፣ በዘር ሳይሆን በአስተሳሰብ መሰባብ አለብን፡፡ ታሪክን  የረሳ  ስህተቱን ይደግማል እንዲሉ የውድቀት ታሪካችንን በመዘንጋት ደግመን ደጋመን ስህተት እየሰራን ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ እንደማይሰራ በነቢብም በገቢርም ስላየነው ዛሬ ለማህበራዊ ፍትህ ብንታገል መጪው ግዜ ብሩህ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

በነገራችን ላይ ሶማሊያ በሁሉም ህዝቧ እውቅና እና ድጋፍ ያለው ማእከላዊ መንግስት ማግኘት ያልቻለች እና ያልታደለች ሀገር ናት፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም የአንዲት ሶማሊያ ግዛት የነበሩት ሶማሌላንድ፣ፑንትላንድ፣አዛኒያ እና ሌሎች የሶማሊያ ክፍሎች . Somaliland, Puntlang, Azania and other parts of Somalia declared their independence of the central administration ( ከደቡብ ሶማሊያ በቀር ማለቴ ነው) ከሶማሊያ ማእከላዊ መንግስት ራሳቸውን በማግለል ነጻ ግዛት ከመሰረቱ አመታት ነጎዱ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሁሉም ነጻ ግዛቶች በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና ተነፍጓቸዋል፡፡ ለምን ይሆን ሶማሊያ የተዳከመች ወይም የጨነገፈች ሀገር ለመሆን የበቃችው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ ቢታወቅም ( የውስጥና የውጭ ምክንያቶች ማለቴ ነው) ሶማሊያ ለዚህ የበቃችው በዋነኝነት የጎሳ ፖለቲከኞች መፈንጫ በመሆኗ ነው፡፡ የሶማሊያን ህዝብ በአንድነት ሊያሰባስብ የሚችል ጠንካራ ማእከላዊ መንግስት ማግኘት ስለተሳናት ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለግዜውም ቢሆን ልዩነታችንን ገሸሽ በማድረግ፣ አንቺ ትብሽ፣አንተ ትብስ በመባባል ወደ አንድነት ፣ወደ መነጋገር እንድንመጣ እማጸናለሁ፡፡ በቅርቡ ጃፓን ቶኪዮ ከተማ የኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ ኢትዮጵያን የወከለው የእስፖርት ልኡክ ቡድን ጉራማይሌ አለባበስ በማሳየቱ በውጤቱ ላይ ያሳረፈውን ተጽእኖ ህሊና የፈጠረበት ኢትዮጵያዊ የሚገነዘበው ይመስለኛል፡፡አንድነትና ህብረት ውጤት ያመጣል፡፡

በነገራችን ላይ የዚያድባሬን ውድቀት ፣የመንግስታቸውን ውደቀትን እና የሶማሊያን መከፋፈል ተከትሎ አዲሰ የአለም አቀፍ ግንኙነት ጥናት መስክ እንዲከፈት ግድ ብሏል የሚል አስተያየት የሚሰጡ የአፍሪካው ቀንድ ፖለቲካ ተንታኞች ሶማሊያ የጨነገፈች ሀገር ለመሆን እንደበቃች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ጽሁፎቻቸው አስፍረውት ይገኛል፡፡

በአለም አቀፍ ህግ መሰረት የአንድ ሀገር ትርጉም የነበረው የሉአላዊነት መከበር ለመጀመሪያ ግዜ በሶማሊያ ውድቀት የተነሳ ከሽፏል፡፡ አንዲት ዘመናዊት ሀገር ሉአላዊነቷ እንደማይደፈር  The Westphalian በተሰኘው አለም አቀፍ ህግ ላይ ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ እንደተቀመጠ ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሶማሊያ አንዲት ዘመናዊ ሀገር የምታሟለውን ትርጉም መስጠት አትችልም፡፡ ስለሆነም ሶማሊያ ዛሬ የጨነገፈች ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡  በነገራችን ላይ ሌሎች ሀገራት እንደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ሃይቲ፣ሱዳንን የመሳሰሉት ሀገራት የተዳከሙ ሀገራት እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያም በፍጥነት ከጎሳ ፖለቲካ በፍጥነት ካልተገላገለች መጪው ግዜ እጅጉን አስፈሪ መሆኑ ምነም የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡በእውነቱ ያሳዝናል፡፡

በአሁኑ ዘመን የበቀሉ አምባገነን መንግስታት የህዝባቸውን ድምጽ ሊያዳምጡ ይገባል፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ከከዳቸው ‹‹ የሶማሊያ ታሪክ›› በድጋሚ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ አይነት ሂደት በገቢር በተለያዩ የአለም ክፍሎች እየታየ ይገኛል፡፡ በተለይም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2010 ከተከሰተው ‹‹ የአረቡ ጸደይ አብዮት›› ወዲህ አምባገነን መንግስታትን መቃወም እየተለመደ መጥቷል፡፡ ስለሆነም አለም አቀፉ ህብረተሰብ ሰልፉ ከዲሞክራሲ፣ሰብዓዊ መብት እና ከህግ የበላይነት አኳያ መሆን ይገባዋል እንጂ ከአምባገነን መንግስታት ጋር መሆን አይገባውም፡፡

እንዲህ አይነት ጽሁፍ ማዘጋጀት ጭንቀት ውስጥ ይዶላል፡፡ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ብዙዎች ቤተሰቦቻቸውን በሞት ተነጥቀዋል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ አለም አቀፉ ህብረተሰብ ዝም ብሎ ተመልካች ስለሆነ ፣እንዲሁም የለሌሎች አካላት ፍላጎትን ለሟሟላት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለምን ይሆን አኑሶም 1 እና አኑሶም 2 (UNOSOM and UNOSOM II ) የተባሉት የብይነ መንግስታቱ የሰላም አስከባሪ ሀይሎች በሶማሊያ ተልእኳቸው ለምን የተሳካ ስራ ለማካናወን አልቻሉም ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1993 በሞቃዲሾ ከተማ የውጭ ሀገር ወታደሮች እና ረዳቶቻቸው በመገደላቸው ምክንያት የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር በአንድ ሀገር የርስበርስ ጦርነት ከተጀመረ እና የውጭ ሀይል ጣልቃ ገብነት እጅጉን አስቸጋሪ መሆኑን ነው፡፡ የውጭ ሀይሎች የተለያዩ ፍላጎት ስላላቸው በአንድ የርስበርስ ጦርነት በምትታመስ ሀገር ሰላም ለማምጣት በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡ በሶሪያ፣የመን፣ አፍጋኒስታን፣ሊቢያ የታየው መራር ሀቅ ይሄው ነው፡፡ ለአብነት ያህል በአፍጋኒስታን ሙጃሂዲኖች በቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ታግዘው የታሊባንን ሀይል አሸንፈው የነበረ ሲሆን፣ በሌላ ግዜ በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ታሊባኖች በአሜሪካ እገዛ አሸንፈው መንግስት ለመሆን በቅተው የነበረ ሲሆን፣ አሜሪካኖቹ ተመልሰው ታሊባኖችን አይናችሁ ላፈር በማለት ራሳቸውን ወዳጅ መንግስት በአፍጋስታን መዲና ካቡል ለማቆም የቻሉ ሲሆን፣ አልሆን ሲላቸው ደግሞ ሀገሪቱን የደም አባላ ካለበሱ 20 አመት ቆይታ በኋላ ጓዛቸውን ሸክፈው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ዛሬ በታሊባን ሀይሎች እና አህመድ ካርዛይ የአፍጋን መንግስት ወታደሮች መሃከል ውጊያው ተፋፍሟል፡፡ ምስኪን የአፍጋኒስታን ንጹሃን ግን ፍዳቸውን እየቆጠሩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከዚህ የመከራ ታሪክ መማር ያለብን ቁምነገር ቢኖር በመጀመሪያ ደረጃ ለግዜውም ቢሆን የጎሳ፣ሃይማኖት እና ፖለቲካ አመለካከታችንን ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ አንድነታችንን ማጥበቅ ይገባናል፡፡ የህብረት ፍልስፍና መከተል ካቃተን የማንም መፈንጫ መሆናችን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጉዳይ መሆኑን አበክሬ አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሪያ ቤታችን ድረስ እስኪመጣ መጠበቅ የለብንም፡፡በራሳችን ላይ ወይም በቤተሰባችን ላይ ካልተፈጸመ እኔ ምን አገባኝ ማለቱ አይጠቅመንም ነገ ተነገ ወዲያ በራችን ድረስ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ሀገር ስትኖረን ነው መጨቃጨቅም፣ መነጋገርም የምንችለው በምድሪቱ ላይ የሸፍጥ አንጋቾች እንዳሻቸው ሲፈነጩ ፣የዲሞክራሲ ማጅራት መቺዎች የመብት አስከባሪዎች እንዲህ ሲፏልሉ  ማየቱ ያማል ፡፡ ወያኔ በሚባል ማህበራዊ ነቀርሳ ለ27 አመታት ግፍ የተፈጸመበት ህዝብ ፣ እምብርት ላልፈጠረባቸው ሆዳሞች ፍዳውን ያየ ሕዝብ ከአሁን በኋላ ግፍን ለመሸከም ትከሻ የለውም፡፡ ታሪኩን የረሳ ያለፈውን ስህተት ይደግማል እንዲሉ፣ ህብረት ስለሌለን፣ ከጎሳ ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ መገላገል ባለመቻላችን፣ በእኔ እና በቤተሰቤ ላይ ግፍ ካልደረሰ እኔ ምን አገባኝ በሚል የድንቁርና ትምክህት መገላገል ባለመቻላችን፣መርዶ ነጋረዎችን ፊት ለመንሳት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ባለመቻላችን፣ለዋሾ ነጋሪዎች ጆሮ በምሰጠታችን ወዘተ ወዘተ ዛሬም ከግፍ አዙሪት መውጣት አልቻልንም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በሌሎች ሀገሮች ላይ የደረሰው ውርደትና ውድቀት በበቂ ሊያስተምረን አልተቻለውም፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ማሳዘን ብቻ አይደለም ህሊና ያደማል፣ ሆድንም ይበጠብጣል ለማናቸውም የዛሬውን ጽሁፌን የምቋጨው በፓስተር ማርቲን ናይሞለር (Martin Niemoller ) ዘላለማዊ ቃል ይሆናል፡፡

የፓስተር Martin Niemoller ቃሎች !

በርካታ ሰዎች፤ በሌሎች ሰዎች ላይ ሆነ ቡድን በደል፤ወይም ሀገር ( ለአብነት ያህል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች አርሰው ከሚኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ፣ውድ ህይወታቸውን ከእብድ ውሻ በከፉ ሰው መሳይ አውሬዎች ውድ ህይወታቸው ሲቀጠፍ ድምጻቸውን የሚያሰሙት ጥቂቶች ናቸው፡፡)  ጭካኔ ፤ ችግር ፤ ሃዘን ፤ የመንፈስ ስብራትና ሌሎች እክሎችና ችግሮች ሲያጋጥማቸው ፤ ችግሩ በእነርሱ ላይ ብቻ የሚቀርና የሚኖር ፤ ነግ በኔ መሆኑን ረስተው ፤ እነርሱ ያ የማይደርስባቸውና እርግጠኞች ሆነው ለመታየትና ከችግሩ ራሳቸውን ንፁህና የበደሉን ገፈት ነገ እነርሱ የማይቀምሱት መስሏቸው ይታያሉ።

ነገር ግን ይህንን ጉዳይ በጥሞና ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በማሰብ የራሳቸው ምቾትና ደህንነትም ተመሳሳይ ዕጣ ሊደርሰው እንደሚችል የእኒህ አስተዋይ ፓስተር ቃል ጥሩ ምክር ነውና እንደወረደ ላቅርበው ።

In Germany, first they came for the Communists and I did not speak up because I was not a Communist. 

Next they came for the Jews and I did not speak up because I was not a Jew. 

Then they came for the trade unionists and I did not speak up because I was not a trade unionist. 

Then they came for the Catholics and I did not speak up because I was a protestant. Then they came for me – and by that time there was no one left to speak up .

 በጀርመን ምድር በመጀመሪያ የናዚ ፋሺስቶች  ኮሚንስቶችን ገደሏቸው ፡፡ እኔም ዝምታን መረጥኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ ኮሚንስት አይደለሁም በሚል ራስ ወዳድነት ስሜት የተነሳ ነው፡፡

በሚቀጥለው ቀን ይሁዴዎችን ሲገድሏቸው በዝምታ ተዋጥኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ ይሁዳ ስላልነበርኩ ነው፡፡
በማስከተልም የሙያ ማሀበር መሪዎቹን ሲገድሉ የሙያ ማህበር አባል ባለመሆኔ ድምጼ አልተሰማም፡፡

የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮችን ሲገድሏቸው እኔ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆኔ አሁንም ዝምታን መረጥኩ፡፡

በመጨረሻም ወደ እኔ መጡ፡፡ በፍጥነት ናዚዎች ወደ እኔ መጡ ፡፡ አጠገቤ ግን ማንም አልነበረም፡፡ ብቻዬን ቀረሁ፡፡

 

ሰውዬው ይህንን አሉ። 

ነፍስዎን ከገነት ያኑርልን ! 

ለምን አሉ? 

ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም ። 

አያገባኝም ፤ አይመለከተኝም ፤ አይኮነስረኝም፤ ስሜት አይሰጠኝም ………… ወዘተረፈ ማለት ለማንም አይበጅ። 

በተቃራኒው ግን ብንቆም የምንፈልገውንና የምንመኝውን ኑሮ ለመኖር የሚያዳግተን አይመስለኝም ።

ስለ አገርህ ጉዳይ ካላገባህ ስለማን እንዲያገባህ ትፈልጋለህ ?

የማንንስ ጎፈሬ ታበጥር ይሆን ?

Filed in: Amharic