ሞገደኛው ጋዜጠኛና ደራሲ መንግሥቱ ገዳሙ
ታሪክን ወደኋላ
የአንዳንድ ሰዎች ባሕርይና ድርጊት ከተለመደው ማኅበረሰባዊ ልማድ ወጣ ያለና ያፈነገጠ ሲሆን ይስተዋላል። የእነዚህ ሰዎች አስቂኝ፣ አስገራሚና አሳዛኝ ገጠመኞቻቸው እነርሱ በሕይወት በነበሩባቸውም ይሁን ካለፉ በኋላ ሲታወሱ ይኖራሉ። አለቆቹን በሽጉጥ እያስፈራራ ደመወዝ ያስጨመረው፣ ቢሮ ውስጥ አልጋ አስገብቶ የተኛው፣ የእስር ቤቶችን ሁኔታ ለማወቅ ሲል ሆን ብሎ ወንጀል ሰርቶ የታሰረው፣ ሳይሞት በውሸት ‹‹ሞቻለሁ›› ብሎ አስነግሮ ከለቀስተኛው መካከል የተገኘው፣ ከአንድም አራት፣ አምስት… ጊዜ ከሞት ደጃፍ የተመለሰው፣ በደፋር ብዕሩ የመንግሥትን ስርዓት የተቸው፣ የበርካታ መጽሐፍት ደራሲ የሆነውና ‹‹ሞገደኛው ጋዜጠኛና ደራሲ›› የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው መንግሥቱ ገዳሙ ከእነዚህ ዓይነቶቹ አንዱ ስለመሆኑ አያከራክርም።
መንግሥቱ የተወለደው በ 1920 ዓ.ም በቀድሞው የሲዳሞ ክፍለ ሐገር፣ በቡሬ ገጠራማ መንደር ውስጥ ነው። የቤተሰቦቹ ሕይወት በግብርና ስራ ላይ የተመሰረተ ስለነበር መንግሥቱም ገና በልጅነቱ የወላጆቹን ስራ በአቅሙ ያግዝ ነበር። የመንግሥቱ ሕይወት በፈተና የተሞላች መሆን የጀመረችው ገና በማለዳው ነበር። በዚያው የልጅነት እድሜው እባብ ነድፎት ለስድስት ሳምንታት ያህል ሕሊናውን ስቶ ከሰነበተ በኋላ ከሞት ተረፈ። ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የመንግሥቱን የትውልድ መንደር ሲያቃጥል መንግሥቱ ከእሳቱ የተረፈው በተዓምር ነበር። ቤታቸው ሲቃጠል መንግስቱ የሚሄድበት አጥቶ በቤት ውስጥ ይቅበዘበዝ ነበር። በሚቃጠለው በነመንግስቱ ቤት ወስጥ ሰው መኖሩን የተረዳ አንድ የአካባቢው ሰው ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት መንግሥቱን ከሞት አተረፈው።
በፋሺስቶች መምጣት የተደናገጠው የአካባቢው ሰው ቤቱን ትቶ ሲሸሽ ፈረስ መጋለብ የማይችለው መንግሥቱ በፈረስ ሊያመልጥ ወሰነና ከፈረስ ላይ ወጣ። የፈረሱ ፍጥነት አስደንግጦት ከፈረሱ ላይ ለመውረድ ወሰነ፤ ለስላሳ መሬት አገኘሁ ብሎ ከፈረሱ ላይ ተፈናጥሮ ሲወርድ ድንጋይ ላይ ቢወድቅም ከሞት መትረፍ ችሏል። የሞትን ደጅ እየረገጡ መመለስ የተለማመደው መንግሥቱ በአንድ ወቅት በከብት ጥበቃ ላይ ሳለ ጅብ ተሸክሞት ሊሄድ ሲታገለው የለበሰውን ደበሎ ለጅቡ ሰጥቶ ማምለጥ ችሏል። ለዚህም ነው መንግሥቱን ከልጅነቱ ጀምረው የሚያውቁት ሰዎች ‹‹ሕይወቱ በሙሉ የፈተና ዘመን ነበር›› ብለው የሚመሰክሩት።
መንግሥቱ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብቶ ፊደል መቁጠር ቻለ ። ከፍ ሲልም በወታደርነት ለማገልገል ተመዘገበ። በውትድርናው ግን አልገፋበትም። ከውትድርናው ዓለም ወጥቶ በፖስታና ቴሌፎን ሚኒስቴር ውስጥ ተቀጠረ ። በስራው የተመሰገነ ታታሪ ሰራተኛ ስለነበርም በአጭር ጊዜ ውስጥ እድገት አግኝቶ ወደ ድሬዳዋ ተዛወረ።
ደመወዙ ግን አጥጋቢ ስላልሆነለት ስራውን ለቆ በእጥፍ ደመወዝ በምድር ባቡር ኩባንያ ውስጥ ተቀጠረ። የፖስታና ቴሌፎን ሚኒስቴር ይህን የመንግሥቱን ድርጊት ሲሰማ ወደ ቀድሞ ስራው በግዳጅ መለሰው። መንግሥቱ ግን ለአለቆቹ ውሳኔ የሚመች አልሆነም። ‹‹አለቃም ይሁን ምንዝር በእጄ ከመጥፋቱ በፊት በሰላም አሰናብቱኝ›› ብሎ አስፈራራቸው ። ይህ ፉከራው ሳያዋጣው ስለቀረ ሌላ መላ ዘየደ። ‹‹ራሴን አጠፋለሁ›› ብሎ ማስፈራራት የመንግሥቱ ሌላኛው ዘዴ ነበር። እንዳጋጣሚ ሆኖ ይህኛው መላ ሰራለትና መስሪያ ቤቱ ‹‹ ራስህን ከምታጠፋ እንለቅሃለን›› ብሎ አሰናበተው።
ወደ ምድር ባቡር ኩባንያ ሄዶ ለጥቂት ጊዜያት ያህል ከሰራ በኋላ ‹‹የኩባንያው ስራ አስኪያጅ እብሪት አስመረረኝ›› በማለት ስራውን በፈቃዱ ለቀቀ። ጥቂት ሰንብቶ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጥሩ ደመወዝ በመዝገብ ቤት ሹምነት ተቀጠረ። በመዝገብ ቤት ሹምነት ጥቂት ከሰራ በኋላ ወደ ትርጉም ክፍል ተዛወረ ። ከዚያም ወደ ባንኩ አስተዳደር ክፍል ስልጣን ቢጤ አገኘ። በወቅቱ ሁለት ጊዜያት ያህል ጥሩ የደመዝ ጭማሪ ማግኘት ችሏል። ጭማሪዎቹን ያገኘበት መንገድ ግን የተለየ ነበር ። ይኸውም ሕንዳዊውን የባንኩን ሥራ አስኪያጅ በሽጉጥ በማስፈራራት ነበር። ሌላ አጋጣሚ ተፈጥሮ ሳይሳካ ቀረ እንጂ መንግሥቱ ከሽጉጥ ተሻግሮ በናስማስር ጠመንጃ በማስፈራራት ሦስተኛ ጭማሪ ለማስደረግ እየተዘጋጀ ነበር።
‹‹ባሕል አስከብራለሁ›› በሚል ምክንያት በርኖስ እየለበሰ ቢሮ መግባት ጀምሮም ነበር። በዚህም ተከሶ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት በብዙ ልመና በርኖሱን አወ ለቀ። በዚህ የተናደደው መንግሥቱ ባንኩን በጋዜጣ ጽሑፍ ሙልጭ አድርጎ ተሳደበ። ይባስ ብሎም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የባንኩን አገልግሎትና አሰራር ሊጎበኙ ወደ ባንኩ በሄዱበት ወቅት መንግሥቱ ወደ ክፍሉ ደብቆ ያስገባው ተጣጣፊ አልጋ ላይ ተኝቶ ተገኘ። ለምን ቢሮ ውስጥ እንደተኛ ሲጠየቅም ‹‹አለቆቼ ስራ ስለማይሰጡኝ የምሰራው ስራ ሳይኖር በከንቱ ደመወዝ እንደሚከፈለኝ ለማሳወቅ ነው›› ብሎ ተናገረ። በዚህ አድራጎቱ የተበሳጩት አለቆቹ በማግሥቱ የስንብት ደብዳቤ በፖሊስ እጅ ደረሰው።
በባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ውሳኔ ያልተስማማው መንግሥቱ መስሪያ ቤቱ ላይ ክስ መሰረተ ። መንግሥቱ መስሪያ ቤቱን አሸነፈ። ነገር ግን ጉዳዩን ተከታትሎ ሳያስፈፅም በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኛነት ተቀጠረ። በዚህኛው መሥሪያ ቤት የመንግሥቱ መንፈስ የተረጋጋ መሰለ። በወቅቱ በጋዜጣ ላይ በሚያቀርባቸው ጽሑፎቹ በብዙዎች ዘንድ እውቅና ለማግኘት በቃ። መንግሥቱ በወቅቱ በጽሑፎቹ ይዳስሳቸው የነበሩት ርዕሰ ጉዳዮች አብዛኞቹ የሥራ ባልደረቦቹ የማይደፍሯቸው ነበሩ። በጋዜጠኝነት የጀመረው ጽሑፍ ወደ ደራሲነት አሸጋገረው። የድርሰት ስራውን የጀመረው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በጋዜጠኛነት ተቀጥሮ ማገልገል ከጀመረ ወዲህ ነበር። የመጀመሪያ ስራውንም ‹‹ሌላው እንደሚያይህ›› በተሰኘ ርዕስ በ1949 ዓ.ም ለአንባቢያን አደረሰ። መጽሐፉ ልብ ወለድ ሲሆን ከጋዜጠኝነት ወደ ደራሲነት የተሸጋገረበት የበኩር ስራው ነው። ከዚህ በኋላ ብዙ መጽሐፍትን መጻፍ ችሏል።
ከስራዎቹ መካከልም፡-
— አመፀኛ ሞግዚት — እንኮዬ ደማሜ
— ብታምንም ባታምንም — ኮሳሳው ተማሪ
— የእንስሳት ሮኬት — ፃድቁ አራምዴ
— ማጅራት መቺ — አሳማና ድመት
— ከምሱር — አንተ ማን ነህ
— የሃምሳ አለቃ ገብሬ — አመሰግንሻለሁ
— The Psychology of The White Races
— የአልማዝ እዳ
— ከማን አንሼ …..… የሚሉት ይጠቀሳሉ።
‹‹ከማን አንሼ›› የተሰኘችው የልብ ወለድ መጽሐፉ የፊት ሽፋኗ ላይ አህያ ሙሉ ሱፍ ከነሰደርያውና ካፖርት ደርባ፣ ባርኔጣ ደፍታ፣ መነጽር አጥልቃ ትታይበታለች። ድርሰቱ በአህያዪቱ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን የመጽሐፏ አንዱ ክፍል የአህያ ጸሎት ነበር። ‹‹በስመ ጎርማንዴዎስ ወሰርዶ ወፋንድያ›› በማለት ጸሎቷን አድርሳ ወደ ቀለቧ እንደምታመራ ተጠቅሷል። አንድ ሰው እጅ እንዲነሳት ተደርጋ የተሳለችው አህያ ‹‹የወቅቱን የፓርላማ አባላት ለመሳደብ ሆን ብሎ ያዘጋጃት ናት›› ይባላል። ከላይ ከተጠቀሱት ሥራዎቹ በተጨማሪ የትርጉም መጽሐፍትንም ለአንባቢያን አድርሷል።
መንግሥቱ ገዳሙ ጥሩ ጸሐፊ ብቻም ሳይሆን ጥሩ አንባቢም ነበር ። በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ድንቅ ቤተ-መጽሐፍት አደራጅቶ ነበር። መንግሥቱ ራሱን በራሱ የፈጠረ ምሁር ነበር። በመደበኛ ትምህርት ብዙም ባይገፋም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጭምር መጽሐፍ (‹‹The Psychology of The White Races››) መጻፍ ችሎ ነበር ። ለአንድ ዓመት ሥራ ሲፈታ ግን መጽሐፍቱን በሙሉ ቸበቸባቸው። ከዚያ ጊዜ በኋላም የመጽሐፍት ድሃ እንደሆነ ይነገራል።
መንግሥቱ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ የቆየው ለ15 ዓመታት ያህል ቢሆንም ያቀርባቸው የነበሩት ጋዜጣዊ ጽሑፎች ግን ጥቂት የሚባሉ ነበሩ። ብዕሩን ሲያነሳ ግን ‹‹ጉድ ለማውጣት›› ነበር። በወቅቱ የሚከናወኑና ከባለስልጣናትም ሆነ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የተደበቁ ነገሮችን ይፋ ለማውጣት የመንግሥቱ ብዕር ደፋር ነበረች። ‹‹ሞገደኛ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውም ከግላዊ ባሕርይውና ድርጊቱ ባሻገር በሙያዊ ተግባሩ ሞጋች ስለነበር ነው። ጽሑፎቹ የሕዝቡን እውነተኛ ሕይወት የሚዳስሱ እንዲሁም ችግሩንና በደሉን ከፍላጐቱ ጋር የሚያመለክቱ ነበሩ። በተለይም የሥርዓቱን ንቅዘት በመዋጋት የሚደርስበት አሳርና መከራ ከሙያው አላገደውም። መንግስቱ ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች የገና ዳቦ ናቸው›› ሲል ብዙ ጊዜ ተናግሯል።
መንግሥቱ የማተሚያ ቤት እዳ መክፈል ተስኖት ሲሰቃይ ቢሸጡ ኖሮ ከማተሚያ ቤቱ እዳ የሚበልጥ ገንዘብ ሊያወጡ የሚችሉ መጽሐፍቱን ለየድርጅቶቹ በነፃ ያድል እንዲሁም ለመጻሕፍት አዟሪዎችም በነፃና በዱቤ ይሰጥ ነበር። ስለአብዛኞቹ መጽሐፍቱ ይዘት ግን አያስታውስም ነበር፤ የመጽሐፍቱ ቅጂም ኖሮት አያውቅም ነበር ይባላል። ስለመንግሥቱ ገዳሙ ሲነሳ አብሮ የሚታወሰው አወዛጋቢና አስቂኝ ባህርያቱ እንዲሁም በፈተና የተሞላው የሕይወት ጉዞው ናቸው። የመንግሥቱ ሕይወት በሙሉ ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር። የሚሰራቸው ነገሮች አብዛኞቹ የሚያስደምሙና የሚያስቁ ነበሩ። ከላይ ከተጠቀሱት አለቆቹን የማስፈራራትና የመናቅ ድርጊቶቹ በተጨማሪ ሌሎች አስገራሚ ባህርያቱንና ድርጊቶቹን በጥቂቱ እንመልከት።
በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ወደ አስመራ ይላካል። ታዲያ በየፖሊስ ጣቢያው ስለሚገኙት ማረሚያ ቤቶች ሁኔታ መጻፍ ፈለገ። ባለስልጣኑን ለማስፈቀድ ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀረ። ሞገደኛው መንግሥቱ ግን ወንጀል ሰርቶ ፖሊስ ጣቢያ መግባትን ለዓላማው ማሳኪያ አድርጎ ሊጠቀምበት አሰበ። ወደ አንድ መጠጥ ቤት ጎራ ይልና ባዶ ጠርሙሶችን እየመረጠ መሰባበር ጀመረ። ኡኡታው ቀለጠና ፖሊስ እያዳፋ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰደው። ከሦስት ቀናት በኋላ በዋስ ተለቆ አዲስ አበባ ሲመለስ ስለአስመራ ፖሊስ ጣቢያዎች በርከት ያሉ መጣጥፎችን መፃፍ ቻለ። የአዲስ አበባን ፖሊስ ጣቢያዎች ለመጎብኘት ስላቀደ ሌላ አምባጓሮ ፈጥሮ ፖሊስ ጣቢያዎቹን በእስረኛነት ጎብኝቷቸዋል።
መንግሥቱ አንዱን ምስኪን ፈረንጅ በ700 ብር ደመወዝ ቀጥሮ ካፖርት እያሸከመ በፒያሳ ይዞር ነበር። ይህም ‹‹ፈረንጅ የሐበሻ አሽከር አይሆንም›› የሚለው አመለካከት ስህተት መሆኑን በተግባር ለማሳየት ነበር።
4 ኪሎ አካባቢ አንድ ተወዳጅ ውስኪ ቤት ነበር። ታዲያ የውስኪ ወዳጆች ቤቱን ከአፍ እስከገደፉ ድረስ እየሞሉት መቀመጫ አይገኝም ነበር። አንድ ቀን መንግሥቱ ከአንድ የውጭ ጋዜጠኛ ጋር ውስኪ ለመጠጣት ወደ ውስኪ ቤቱ ሲሄድ እንኳን መቀመጫ መቆሚያም ይጠፋል። መንግሥቱ በሩ ላይ ቆሞ አጨበጨበ። ጠጪው ሁሉ ፀጥ ሲል በወቅቱ የነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድን ጨምሮ ብዙ የመንግሥት ሹማምንትን ስም እያነሳ መሳደብ ጀመረ። ምድረ ጠጪም ‹‹የመንግሥቱ ስድብ ያሳፍሰናል›› በሚል ስጋት ሂሳቡን እየከፈለ ቤቱን ለቆ ወጣ። ቤቱ ጭር ሲል መንግሥቱ ከወዳጁ ጋር ምቹ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ውስኪን መጠጣት ጀመረ። መንግስቱ ገዳሙ አንጋፋ ጠጪ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ለምን እንደሚጠጣ ሲጠየቅ፤ ‹‹እኔ እኮ ለምን እንደምጠጣ እናንተ ደንቆሮዎች ስለሆናችሁ አይገባችሁም፤ የእኔ አእምሮ ከተራው ሰው አእምሮ በጣም የላቀ ነው። ስለዚህ ከእናንተ ጋር ለመነጋገር ያንን ከፍተኛ አእምሮዬን ወደ እናንተ ደረጃ ላወርደው የምችለው በአልኮል ኃይል ነው›› በማለት መናገሩ ይታወሳል።
መንግሥቱ ከጽሑፉና ከንግግሩ ባሻገር በእለታዊ ድርጊቱ ሁሉ ሥርዓቱን ይቃወም ነበር። አንዲት አህያ ጆሮዋ ላይ ብር ለጥፎ በየመጠጥ ቤቱ እየዞረ፣ አስተናጋጆቹ እንዲታዘዟት ያደርግ ነበር። በዚህም የጊዜው ባለስልጣኖች በገንዘብ እንጂ በአስተሳሰብ ከአህያ እንደማይሻሉ ለማስረዳት ያደረገው ነው ተብሏል። አህያዋን ይዟት በየቦታው ሲዞር ‹‹ምንድን ነች?›› ብለው ሲጠይቁትም ‹‹የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ ነች›› እያለ ይመልስ እንደነበር ይወሳል፤ በዚያ ዘመን ማስታወቂያውን በአህያ እየዞረ የሚያስነግረው ብሔራዊ ሎተሪ፤ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥር ነበር። በመንግሥቱ እሳቤ አህያዋ የባለስልጣኖች ተምሳሌት ነበረች። የ 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ደግፎ ሕዝቡን መቀስቀሱም ስርዓቱን የመቃወሙ ምልክት ነበር።
በሌላ ጊዜ ደግሞ በመስሪያ ቤቱ ግብዣ ላይ የአለቃው አለቃ ባለመገኘታቸው ይወርፋቸዋል። ድርጊቱ ‹‹ክብረ ነክ›› ተብሎ በማግሥቱ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለፍርድ ቀረበ። ጥፋቱን የፈጸመበትን ምክንያት እንዲያብራራ ሲጠየቅ ‹‹ሰዎች ገፋፍተውኝ ነው›› ብሎ መለሰ። እነማን እንደሆኑ ሲጠየቅም ለፍርድ የተሰየሙትን አባላት ስም ጠቀሰ። በዚህ የተነሳ የኮሚቴው አባላት ዳኝነቱን ትተው መንግሥቱን ለመደብደብ ከጀሉ። መንግሥቱ ሮጦ ወጣ፤ የተናደዱት የኮሚቴው አባላት ግን ተከትለው ያባር ሩታል። መንግሥቱ የኮሚቴው አባላት ስሜታቸውን መቆጣጠር የሚችሉ አለመሆናቸውን በአደባባይ አሳየ።
ሌላ ጊዜ ደግሞ መንግሥቱን ሮም ከተማን እንዲጎበኝ ተጋበዘ። መንጌ ትኬቱን፣ ፓስፖርቱንና ቪዛውን በእጁ ካስገባ በኋላ በበረራው ዋዜማ ቀን ወደ አለቃው ዘንድ ሄዶ ከሳምንት በኋላ ወደ አውሮፓ እንደሚሄድና ጉዞውን እንዲፈቅዱለትም አንጀት የሚበላ ደብዳቤ ፅፎ ሰጣቸው። አለቃውም የሚያስቸግራቸው ሰራተኛቸው በእጃቸው ላይ መውደቁ አስደስቷቸው ‹‹ደብዳቤው ከማኅደሩ ጋር ተያይዞ ይቀመጥ›› የሚል ትዕዛዝ ጽፈው ማመልከቻውን ወደ መዝገብ ቤት ላኩት። መንግሥቱ እንደተጫወተባቸው አለቃው ያወቁት ጠዋት ለስራ ሲፈልጉት በዚያው ቀን ጠዋት ቀደም ብሎ ወደ ሮም መብረሩ ሲነገራቸው ነበር።
ሌላኛው የመንግሥቱ ጠባይ አምባጓሮ መውደዱ ነበር። በዚህም ጠባዩ ምክንያት ከመቶ ጊዜ በላይ ተቧቅሷል። አራት ጊዜ በጩቤ ተወግቷል፤ አራት ጊዜ በመኪና ተገጭቷል፤ ህሊናውን እስከሚስት ድረስ ያጋ ጠመውን ጨምሮ 20 ጊዜ ማጅራቱን በወሮበላዎች ተመትቷል። አንድ ሙሉ ሌሊት በቆሻሻ ክምር ላይ አሳልፏል። መንግሥቱ በራሱ ላይ መቀለድም ይወድ ነበር። አንድ ጊዜ ሳይሞት ‹‹ሞቻለሁ›› ብሎ በሌላ ሰው በኩል በማስነገር ወደ መስሪያ ቤቱ ስልክ አስደውሎ የቀብሩ ቦታ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን እንደሆነ አሳወቀ። ለቀስተኛው በቤተ-ክርስቲያኑ ተገኝቶ ተሰብስቦ አስከሬን ሲጠብቅ መንግሥቱ ጥቁር ሱፉን ግጥም አድርጎና ባርኔጣውን ደፍቶ ብቅ አለ። ለቀስተኛውን አመስግኖ ሳይሞት ‹‹ሞቻለሁ›› ብሎ ያስነገረው በእውነት ቢሞት የቀብሩ ስነ ስርዓት ምን እንደሚመስል በቁሙ ለማየት ፈልጎ ያደረገው መሆኑን ገለፆ ለቀስተኛውን በተነ።
መንግሥቱ ገዳሙ በዓለም ዙሪያ ታዋቂ ሰዎችን በሚመዘግበው የ‹‹Who is Who›› ባሕረ መዝገብ ውስጥ ስሙ ሰፍሮለታል። ‹‹ትዳርን ለምርምር የሚጠቀምበት ይመስላል›› እስከሚባል ድረስ አራት ጊዜ አግብቶ አራት ጊዜ ፈትቷል።