አሳፍ ሀይሉ
“አልገባኝም” ብሎ ባደባባይ መናገር ከሀጥያት ካልተቆጠረብኝ፣ አንዳንድ ያልገቡኝ ነገሮች አሉ። ጥያቄዎቼ የተለያዩ አይደሉም። እንደ ችግሮቻችን ጥያቄዎቹም ቅጥልጥል ናቸው። እስቲ መቼም ሀሳብን ሲካፈሉት መቅለሉ አይቀርምና፣ ያልገቡኝን ጥያቄዎች እንደመጡልኝና እንደወረዱ ልደርድራቸው፦
● ለመሆኑ በትግራይና በሌሎች በህወኀት ቁጥጥር ሥር በዋሉ አካባቢዎች፣ የመንግሥት በጀት አሁንም አለ? ወይስ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል? የመንግሥት ሠራተኞች የሚደርሳቸው ደመወዝ አለ? ወይስ የደመወዝ ተቀባዮች ገቢ ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል?
■ ከማዕከላዊው መንግሥት የሚለቀቅ ባጀት ከሌለና የገንዘብ ተቋማት ሥራቸውን ካቆሙ፣ የጦርነቱ ሥጋትና ወላፈን ገና ካልበረደ፣ በእነዚህ ሥፍራዎች የገንዘብ ዝውውር በምን መልኩ ነው የሚከናወነው? አሁንም በኢትዮጵያ ገንዘብ ነው የሚገበያዩት? ወይስ ሌላ አማራጭ እየተጠቀሙ ነው?
● በትግራይ ሀይሎች ቁጥጥር ሥር በዋሉ አካባቢዎች ሁሉ ሙሉ በሙሉ የመብራት፣ የውሃ፣ የቴሌ፣ የባንክና የመሳሰሉት ሕዝባዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል? ከተቋረጡ የያካባቢው ነዋሪዎች እነዚህን አገልግሎቶች ከየትና በምን እያገኙ ነው? ዜጎች ያላቸው ሌላ አገልግሎቶቹን የማግኛ አማራጭስ አለ? ወይስ እዝጌሩ እንደፈጠራቸው እንደፍጥርጥራቸው ያውጣቸው ተብሎ እርግፍ ተደርገው ተትተዋል?
■ ለመሆኑ መንግሥት ከአገልግሎቶች የሚያገኛቸውን ክፍያዎች የሚሰበስብበት መንገድ አለ? ወይስ አገልግሎትም፣ ክፍያም፣ ሁሉም ነገር ነው ጥርቅምቅም ብሎ የተዘጋው? ለመሆኑ በጦርነት ቀጣናዎች በህወኀቶች ቁጥጥር ሥር ያሉ ህዝቦችን ደህንነትና ህይወት በተመለከተ ኃላፊነቱን የሚወስድ፣ በመንግሥትና በወያኔዎች ለተወሰኑ ጉዳዮች ዕውቅና የተሰጠው ሕዝብ አስተዳዳሪ አካል አለ ግን በአሁኑ ሰዓት? ወይስ ለእነዚህ ዜጎች ሀገር already በላያቸው ላይ ፈርሷል? እና መንግሥት አልባ ሆነዋል?
● ቆይ ግን ጦርነት ላይ ነን ሲባል፣ ጦርነቱ በሁሉም ወገን ያሉ ሠላማዊ የኢትዮጵያ ዜጎችን በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ በማያስገባ መልኩ እንዲካሄድ ምን መንግሥታዊ ተግባሮች ተከናውነዋል? ለሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ህይወት አስፈላጊ የሆኑ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን የማቋረጥ እርምጃዎች ሲቪሎችንና ተዋጊዎችን የለዩ ናቸው? ወይስ በጅምላ (wantonly) ሁሉንም የየአካባቢዎቹን ዜጎች ሰለባ የሚያደርጉ ናቸው?
■ ለጦርነት መቅሰፍት ተጋላጭ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ (ሠላማዊ ዜጎችንና ቤተሰቦቻቸውን፣ በተለይም ህፃናትን፣ ህሙማንን፣ አረጋውያንን፣ ወላጅ ያጡ ረዳት የሌላቸው አቅመደካማ ቤተሰቦችንና የመሳሰሉትን) የዕለት ኑሯቸውንና ህይወታቸውን ለመደገፍና ከረሀብ፣ ከጥማትና ከቸነፈር ለማዳን መንግሥት እያደረገ ያለው ተግባር ምንድነው?
● በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መንግሥት ለዜጎቹ ደህንነት ሲል፣ ከተዋጊ ወገኖች ጋር ቁጭ ብሎ ከመደራደር የሚከለክለው ነገር አለ? ምንድነው? ወይስ ጦርነት ሲባል በመርህ ደረጃ ሁሉም በጅምላ ገፈቱን የሚያጭድበት (የሚያወራርድበት) ማንንም የማያስተርፍ፣ የጋራ፣ የሁሉም፣ ሀገራዊ የእልቂት ድግስ ነው የሚል የጋራ አቋም ተወስዷል?
■ ለመሆኑ አለኝ በሚለው የራሱ መንግሥት የተተወ ሕዝብ ምን ዓይነት መከራ ሊደርስበት እንደሚችል አጢነነዋል? ለመሆኑ በገዛ መንግሥቱ የተተወና መከራ የወደቀበት ዜጋና ቤተሰብ እንዴት ያለስ የሀገር ፍቅር አቋም በውስጡ ሊቀርለት ይችላል?
● ጠላትነትን የሚያገዝፉ የከረሩ የጥላቻ ቃላትን ዕለት በዕለት እያመረቱ ለሕዝብ ማከፋፈል፣ ጦሱ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገውም ትውልድ እንደሚተርፍ፣ በነገው የትውልድ አብሮነት ላይ ክፉ አሻራውን ትቶ የሚያልፍ መሆኑን የሚገነዘብ ኃላፊነት የሚሰማው አካል በመካከላችን ጠፍቶ ነው? የከረሩ የጥላቻና የጠላትነት ቃሎች በተዋጊ ወገኖች መካከል እርቀሠላም የመስፈኑን ዕድል እያጨለሙት፣ ወገናዊ አሰተሳሰብና ሀገራዊ አብሮነታችንን ይበልጥ እየናዱት እንደሚሄዱ ማወቅ አዳግቶናል? ወይስ ውጤቱን፣ መለያየቱን፣ ትውልድን መሰንጠቁን ሁሉ “እሰየሁ! ይሁንልን!” ብለን ተቀብለነዋል?
■ ለመሆኑ መች ነው እርስበርስ መጠፋፋቱ የሚደክመን? ወይም መች ነው እርስበርስ መገዳደሉ ወደጋራ ውድቀታችንና ሀገራዊ መቃብራችን አንደርድሮ እየወሰደን እንዳለ አምነን ለሠላም እጅ የምንሰጠው? ጦርነቱ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? ሰብዓዊ ነገሮችን አንስተን መነጋገርና በዜጎቻችን ላይ ስለወደቀው የጦርነት መቅሰፍት መደንገጥ የምንጀምረውስ ምን ሁኔታ ላይ ስንደርስ ይሆን?
● ጦርነታችን በጠቅላይ አሸናፊ ካልተደመደመ ሰብዓዊ ነገርን አንስቶ መነጋገር ውጉዝ ከመአርዮስ የተባለ አይነኬ፣ አይጠጌ፣ አይነሴ ጉዳያችን ሆኗል? እስከመቼ? ስንት ህዝብ በአጥንቱ እስኪወጣ? ስንት ሚሊዮኖች እስኪቀበሩ? ለስንት ዓመት እስክንጫረስ ነው ስለ ሰብዓዊ ነገሮች አንስተን የማንነጋገረውና መፍትሄ የማናበጀው? ማሸነፍና መሸነፍ ስንት ዓመት ይፈጅ ይሆን? የስንት ዜጎችን ህይወት ለመገበር ዝግጁ ነን? እውነት ጦርነት የመጨረሻው ብቸኛው በዓለም ላይ የቀረን አማራጭ ነው?
ብዙ ያልገቡኝ ጥያቄዎች አሉ። ብዙው ነገራችን እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። በዚህ የማይፈታ እንቆቅልሽ እስከወዲያኛው ለመከራ ለተጣፉ ምውት ነፍሶች እጅግ አዝናለሁ። ፈጣሪ ለመተራረፍ ልብ ይስጠን። “ጨርሶ” ዓይን ያወጣን ከመሆንና ከመባል ይሰውረን ለሁለት ሺህ ዓመታት ያሸበሸብንለት እግዜራችን። ፈጣሪ በቃችሁ ይበለን። በቃን የምንልበትን ሀሞት ይስጠን። ትውልድ ዮዳን። በእኛ ይብቃ። ዕድሜ ይስጠን። ሠላም። ሠላም። ሠላም።
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ ትዘረጋለች! ኢትዮጵያ ሆይ፣ የሀዘን ማቅ የሚያስለብሱሽ ልጆች ሞልተውሻል፣ ማድያቶችሽን የሚያብስ ትውልድ ደግሞ ይፍጠርልሽ!
“የገደለው ባልሽ፣
የሞተው ወንድምሽ፣
ሀዘንሽ ቅጥ አጣ፣
አልወጣም ከቤትሽ!”
ቸር አውሎ ያግባን!